Homeአበይት ዜናጋዜጣዊ መግለጫበወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰጠ መግለጫ

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰጠ መግለጫ

Advertise Here
Advertise here

ጠያቂም ተጠያቂም ባለመኖሩ መግደል ቀላል ኾኗል!

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰጠ መግለጫ

በአገራችን ኢትዮጵያ ተጠያቂነት ከመዝገበ ቃላችን የጠፋ ያኽል ሥርዓት አልበኝነት ነግሶ ዜጎችን መጨፈጨፍ  የተለመደ ተግባር እየሆነ  መጥቷል። በአንዱ አካባቢ የተሰማ እልቂት ሳይውል ሳያድር በሌላኛው አካባቢ ደግሞ በበለጠ  ዘግናኝ እልቂት ዑደቱ ተጠናክሮ ሲቀጥል እየተፈፀመ ላለው ፍጅት በዝምታ ማየት በተባባሪነት የተረጋገጠ መስሎ ይታየናል። ሥርዓቱም በሕልሙ በፈጠረው የቅዥት ዓለም እየዋኜ ለምለሙ መስክ እንጂ እልቂቱን ሊመለከት አልፈለገም፤ አይያም  አይሰማም፤ ወይም ኾነ ብሎ ድርጊቱ በሌላ መሰል ድርጊት እየተዳፈነ እንዲረሳሳ እንደሚያደርግ ግንዛቤ እንድንይዝ አድርጓል። ከመጋረጃ ጀርባው ሊኖር የሚችለውን ሤራ ትተነው በአደባባይ የተነገሩ መልዕክቶችን ብናወሳ “ሰበርናቸው”፣ “አኹን ቀና እንዳይል አድርገነዋል”፣ በቅርቡ ደግሞ “ዱላህን ወደ ክላሽ እንቀይርልሃለን ባለበት ጨፍጭፈው” እና መሰል መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ያሉ የእልቂት ቅስቀሳዎች ያለ ሃይ ባይ በመንግሥት ሚዲያዎች ጭምር እንደናኙ ናቸው። አንደኛው ወገን ዱላው ወደተተኳሽ እንደሚቀየርለት ቃል ሲገባለት ሌላው ደግሞ ራሱንና ቤተሰቡን አፍጥጦ ከመጣ ሞት ሊከላከልበት ጥማድ በሬውን ሸጦ የገዛውን መሣሪያ በመከላከያው ጭምር  እንዲገፈፍ እየተደረገ ለበላተኛ ተመቻችቶ፣ ተሳስሮ ሞቱን እንዲጠብቅ እየተደረገ ነው። ድርጊቱን በውጤቱ መገምገም ለማንም ቀላል እንቆቅልሽ ስለኾነ። 

በኦሮሚያ ክልል፣ ምሥራቅ አርሲ ዞን፣ በጉናና መርቲ ወረዳዎች ልዩ ቦታው  ኖኖ ሄቾ ቀበሌ ጥቅምት 13 ቀን እኩለ ሌሊት 5:00-6:00 ላይ በተቀናጀና በተጠና አኳኋን አሥራ ስድስት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ንጹሓን ዜጎች በግፍ ተጨፍጭፈዋል። የእልቂቱ ሰለባዎች ከ 2 ዓመት ጨቅላ ሕጻን ጨምሮ እስከ 70 ዓመት አዛውንት ይገኙበታል፤  ለአብነት ያኽል አራቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት መኾናቸውን ለመረዳት ችለናል፡፡ “በአካባቢው የሚኖሩ የቀሩ ክርስቲያኖች እነዚኹ ነበሩ በተጠና መልኩ ለዘር እንዳይቀሩ ነው የጨፈጨፏቸው” የሚሉት አንድ እማኝ “የፀጥታ ኃይል ጠዋት እንኳን እንዳልደረሰ፣ ሰውም ለቀብር ስለጠፋ አምስቱን በአንድ ጉድጓድ ለመቅበር ተገደናል” ይላሉ። በተመሳሳይ ኹኔታ በዞኑ ሽርካ ወረዳ፣ ሄላ ዘባባ ቀበሌ ጥቅምት 17 ሌሊት በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ታግተው ሦስቱ ወዲያው ሲገደሉ ቀሪዎቹ እስከአኹን የደረሱበት አልታወቀም። እንዲኹም ጥቅምት ጥቅምት 18 ሌሊት በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ አምስት የእምነቱ ተከታዮች ተጨፍጭፈዋል፡፡

የቅንጅቱ ፓርቲዎች አካባቢው የእልቂት ምድር መኾኑን በመግለጽ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ብንሰጥም ከመካድና ከመፈረጅ የዘለለ መልስ አልተገኘም። ይኽም የዘር ፍጅትና ዘር ማሳሳት መገለጫ አድርገን እንወስደዋለን። አኹን ላይ ካለው ጥላቻና መዋቅራዊ ጥቃት እንዲኹም ጥቃቱን በተለምዶ ኦነግ ሸኔ አደረሰው ከሚባለው ዘፈቀዳዊ ግድያ ዘለል ያለና ነገሩ ቀጠናዊ ሽብር ቡድኖች ጋር የተገናኘ ሊኾን እንደሚችል  ማየት ተገቢ መስሎ ይሰማናል። 

ቅንጅታችን እንዲህ ዓይነቱን ግዙፍ ኢሰብዓዊ ድርጊት በጽኑ ያወግዛል፤ እልቂት የየቀን ገጠመኙ ለኾነው የአካባቢው ማኅበረሰብም ብርታትና መጽናናትን እየተመኘን፤

1. ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው ማንነትና ሃይማኖት ተኮር ጥቃት መንግሥታዊ መዋቅርን የተከተለ፣ሥርዓታዊና ተጨማሪ እጅ ያለበት ስለመኾኑ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ እናቀርባለን። 

2. በተለይ የአርሲ ዞን ነዋሪዎች መንግሥታዊ መዋቅሩ ይጠብቀናል ከሚል አዘናጊ እሳቤ ወጥታችሁ  ተፈጥሮዊ በኾነ ራስን ከሞት መከላከልና ከእልቂት ለመዳን በመዘጋጀት ራሳችሁን ከጨፍጫፊዎች መጠብቅ  እንዳላባችሁ  እናሳስባለን። 

3. በፍርሓት ቆፈን እና መንግሥታዊ ጫና ተቀፍድደው ቃል መተንፈስ ያልቻሉ የሃይማኖት አባቶች እልቂቱ መሐል አዲስ አበባ ከመምጣቱ በፊት መንግሥትና ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ላይ ጫና እንዲፈጥሩ እንጠይቃለን። የኹሉም ቤተዕምነት አባቶች ጋር በመኾን ለሕዝቡ ጥሪ በማድረግ በጣም ሳይረፍድ አባታዊ ግዴታችኹን እንድትወጡ እናሳስባለን። 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

4. በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ኾናችሁ ፊት ለፊትም ከመጋረጃ ጀርባም እልቂት የምትጠምቁ ባለስልጣናት፣ ድርጊቱን በቸልታ ያለፋችኹ የፀጥታ አካላት፣ በደሃው ግብር የተቋቋማችኹና ይኽን የግፍ ግፍ እንዳላየ እንዳልሰማ ያለፋችኹ የመንግሥት ሚዲያ ሓላፊዎችና ሠራተኞች ፍትሕ ሲሰፍን ከተጠያቂነት እንደማታመልጡ ልናሳችኹ እንወዳለን፡፡

ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!

ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት 
ጥቅምት ፳፪ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም 
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

_

የቦርከናን ዮቲዮብ ቻናል ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English

ኤክስ ፡ @zborkena

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News