
ቦርከና ዜና
24/02/2018
ህወሓት እና ኤርትራ የኢትዮጵያን መንግሥት ለመውጋ የታጠቁ ኃይሎችን እያስተባበሩ መሆኑን በኬኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ አዲስ ፓራዳይም ከተሰኘ የዩቲብ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል፡፡
የህወሓት እና ኤርትራ “ፅምዶ” የተሰኘው ጥምረት ዓላማ “የኢትዮጵያን መንግሥት መውጋት” መሆኑን ጀነራሉ ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ኃይሎ የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድን መንግሥት መጣል የሚፈልጉትን በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎችን እያስተባበሩ ነው ብለዋል፡፡
ኤርትራ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት “ካልጠፋ” ያለችውን ህወሓት በአጋርት የተወዳጀችው በኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት ለማስቀጠል መሆኑን ጀነራሉ ጠቁመዋል፡፡ ህወሓት እና ኤርትራ የተጣመሩበት የኢትዮጵያን መንግሥት የመውጋት ዓላማ ለማሳካት የታጠቁ ኃይሎችን አስተባብሮ ለመውጋት ዝግጅት እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ እና በኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈርቂ አስተዳደር መካከል ጉልህ ልዩነት የተፈጠረው በፕሪቶሪያው ስምምነት መፈረም ነው ብለዋል፡፡ በኤርትራ መንግሥት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የከረረ ጸብ የተፈጠረው “ጦርነቱን ለምን ታቆማላችሁ” የሚል መሆኑን ጀነራሉ ተናግረዋል፡፡
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈርቂ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ የእርስ በእርስ ውጊያ እንዲቆም ፍላጎት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ የኤርትራን መንግሥት ከኢትዮጵያ አልፎ ቀጠናዊ ትርምስ በመፍጠር የከሰሱት ጀነራሉ፣ ኢትዮጵያም ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ትሰራለች ብለዋል፡፡
የኤርትራ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ካነሳችው የባህር በር ጋር በተያያዘ ሉዓላዊነት በመጣስ የሚቀርበው ክስ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ ለዚህም ያነሱት መከራክሪያ ኤርትራ በውስጥ ገብታ ፈጥራዋለቸው ባሉት አለመረጋጋት ላይ ኢትዮጵያ ተመጣጣኝ እርምጃ የመውሰድ መብት አላት የሚል ነው፡፡
ጀነራሉ የኤርትራ መንግሥት በስም ጠቅሰው በሰጡት ማብራሪያ “አሰብን ስለጠይቅን ሉዓላዊነታችን ተነካ ማለት አይሰራም” ብለዋል፡፡ “አሰብ የኢትዮጵያ አንጡራ ሀብት ነው” በማለት ከሰሞኑ በትግርኛ ቋንቋ ያሰራጩትን መልዕክት የደገሙት ጀነራሉ፣ ኤርትራ አሰብን የወሰደችው በጉልበት ነው ብለዋል፡፡
ጀነራሉ በጉልበት ተወሰድዷል ያሉትን አሰብን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግሥት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡ የኤርትራ መንግሥት በሰብ ጉዳይ ሉዓላዊነቴ ተደፈረ ለማለት ከኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብነት መቆጠብ አለበት ብለዋል፡፡
ጀነራል ለኤርትራ መንግሥት ባስተላለፉት መልዕክት “ከኢትዮጵያ ዳር ድንበር እጅህን አውጣ፣ ጽምዶን አቁም፣ ለተለያዩ ጽንፈኞች የምታደርገውን ድጋፍ አቁም” ብለዋል፡፡ አከለውም “ይሄን ካላቆምክ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ማንም ራሱን ይከላከላል” በማለት የኢትዮጵያ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ ጠቁመዋል፡፡
………………………………..
የቦርከናን ዮቲዮብ ቻናል ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






