Homeነፃ አስተያየትሕዝብ ምንጊዜም ትክክል ነው?

ሕዝብ ምንጊዜም ትክክል ነው?

Advertise Here
Advertise here

ሙሉጌታ ቢያዝን _  ሕዝብ

ሙሉጌታ ቢያዝን

“ሕዝብ አይሳሳትም ወይም ሕዝብ ምንጊዜም ትክክል ነው” የሚል የቆየ የፖለቲከኞች አባባል አለ፡፡ 

ይህ አባባል ላይ ላዩን ሲያዩት የሚያማልል ልብን የሚያሞቅ፣ ብዙኃኑን የሚያነግሥ ይመስላል፡፡ የታሪክ ድርሳናትንና ሥነ ልቡናን ስናገላብጥ ግን የምናገኘው ተቃራኒውን  ነው፡፡ መንጋ/ሕዝብ ፍርድ የሚያሳልፈው በስሜት፣ተቀባይነት ለማግኘትና ጡንቻ ላለው በማጎንበስ ነው፡፡ ‘የደቦ ፍርድ’ ልንለው እንችላለን፡፡ 

ሕዝብ በስሕተት ውሳኔ ጭቃ ላይ ሲንደባለል በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ በርባንን ፍታ እየሱስን ስቀለው ያለው ማነው? ሂትለርን ሚሊዮኖችን እንዲፈጅ በጭብጨባ የገፋው ማነው?

 የታሪክ ድርሳናት አቧራቸውን አራግፈን ስናነብ የምናገኘው ሐቅ ጆሮን ጭው ያደርጋል፡፡

 ‘አፍንጫ ሲመታ …’ ፡፡ ብለን ብንጠይቅ ‘ዐይን ያለቅሣል’ ለማለት የሚቀድመን ያለ አይመስለኝም፡፡ይሄ  ‘ቲዎሪ’ ይባላል፡፡ ጥያቄው:- ተግባሩስ የሚለው ነው?

 ‘ካንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ’ እንዲል የዲሞክራሲ ፈላስፎች “ካንድ አእምሮ ሐሳብ ይልቅ ከብዙ አእምሮ የሚፈልቅ ሐሳብ የላቀ ነው” ይላሉ፡፡ የብዙኃን ጥበብ (collective wisdom) ይሉታል፡፡ መደምደሚያው በ’ቲዎሪ’ ደረጃ ሲታይ ልክ ነው፡፡ ‘ቲዎሪ’ው  ውኃ የሚያነሣው ግን ሕዝብ “አፍጣጭ፣ ገልማጭ” አለብኝ ብሎ ሳይሳቀቅ ካሰበ ብቻ  ነው፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ ጊዜ አይሳካም፡፡ ምክንያቱም ውሳኔ እንጂ ማሰብ ጥንተ ተፈጥሮው የቡድን አይደለምና ነው፡፡ ወይም ሁሉም ‘ኢጎው’ን (Ego)ይዞ ስለሚቀርብ ላለመስማማት መስማማት እንኳ ዳገት ይኾናል፡፡ አንዳንዱ ጭራሽ ሐሳቡን እንኳን አስቦት ሊያውቅ፣ ከቀረበ በኋላም ለመረዳት ይቸገራል፡፡ እናም “የምትደግፉ፣ የምትቃወሙ፣ ድምፅ የማትሰጡ” በሚል ምርጥ ማምለጫ የጓሮ በር ተከርችሞ ያልፋል፡፡ እዚህ ጋ አንድ ድንቅ አባባል ለመምቴ ሠርቶ ኅሊናዬን በር ላይ ከች ይላል፡፡ “One idiot is one idiot, two idiots are two idiots but thousand idiots are a poltical party”

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

እናም ገለል ብሎ በነፃነት ማሰብ ከሌለ የ”ብዙኃን ጥበብ” ወደ “ብዙኃን ጠባይ” ለመለወጥ የሚቀድመው አይኖርም፡፡

ሳይኮሎጂስት ሶሎሞን አስች በ1951 ያረጋገጠው ይሄን ነው፡፡ በግልጽ የሚታይን ነገር አብዛኛው የቡድኑ አባል/መንጋ /የተስማማበትን መምረጡ የታወቀ ነው፡፡ ስሕተት መኾኑን እያወቀ ከብዙኃኑ ውሳኔ ላለማፈንገጥ የተሳሳተ ውሳኔ ይወስናል፡፡ ይለናል፡፡ ከእውነት ይልቅ /accuracy/ይልቅ ተቀባይነትን/acceptance/ ያስቀድማል እንደማለት፡፡ በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት፡-መ በተለምዶው የሒሳብ ሕግ አንድ ሲደመር አንድ ሁለት ነው፡፡ ይህ ሐቅ ሊለውጥ አይችልም፡፡ ግን በቡድን መሃል ቀድመው የሚናገሩት የቡድን አባላት “ሦስት’ ካሉ፣የመጨረሻው የቡድኑ አባል ‘ሦስት’ ይላል እንደማለት ያለ ነው፡፡ስለዚህ ቀድሞ አንድ ነገር የተናገረ ሰው ምንም ስሕተት ቢኾን ተቀባይነቱ የላቀ ነው ማለት ነው፡፡ ኅሊና ለስሜት ስፍራውን ይለቃል ማለት ነው፡፡

የታሪክ ሊቁ ብሮውኒንግ፣ ተርታ ሰዎች/ Ordinary Men/ በሚለው ሥራው “ሂትለር በነፃነት አይሁዶችን በዋናነት ሲፈጅ በነበረ ጊዜ፣ አንድ ተራ ፖሊስ ንፁኃንን ይገድል የነበረው ‘ግደል’ ስለተባለ ብቻ ሳይኾን ሁሉም ሰው ያንን ያደርግ ስለነበር ነው” ይለናል፡፡ (ካልተሰቀለ ግን ድኅነትም ይኖር ነበር? የሚለውን የቅንጦት ተጠየቅ ትተን) ሕዘብ ትክክል ቢኾን ኖሮ በርባን ተፈትቶ ክርስቶስ አይሰቀልም ነበር፡፡ 

ስታንሊ ሚልግራምም አርቪንግ ጃኒስም የሚሉት ይሄን ነው፡፡ተርታው ሕዝብ “አይዞህ” ከተባለ ምንም እንኳ ሰውን የሚጎዳ ቢኾን ያለምንም ማወላወል ያደርገዋል፡፡ ጥላቻን የሚያነብረው የነጆሴፍ ጎብልስ መመሪያ የሚመጣው እዚህ ጋ ነው፡፡  “If you tell a lie big enough and keep repeating it, people will eventually come to believe it.”

- Advertisement -

ይሄን ውሸት ሚዲያው በሙላትና በስፋት  ሲያስተጋባው፣ ሐቅን ደፍቆ ስሜትን ስለሚያነግሥ አደጋው የከፋ ነው፡፡  ጉስታቭ ሊ ቦን የተሰኘው ፈረንሳዊው የማ/ሰብ ሊቅ “ግለሰቦች ሲሰባሰቡ በሚዛን የማሰብ ክህሎታቸውን በደመ ነፍስ ይለውጣሉ” ይለናል፡፡ ፕሌቶ  ሪፐብሊክ (The Republic) በተሰኘው ሥራው “ ሀገር የሚመሩ ፈላስፎች መኾን አለባቸው” ማለቱ ለዛ ሳይኾን ይቀራል? 

“እኔ ዓዋቂ የምለው ያቺን የልቤን የሚነግረኝን ብቻ ነው” እንዲል ፈላስፋ፡፡ ፈላስፋው ሶረን ኪረገሃርድም (Søren Kierkegaard (1846) በሚያምር ቋንቋ ‘ቁርጥ ያጠግባል’ እንዲሉ እንዲህ ሲል አስቀምጦታል “The crowd is untruth.” Truth often begins in solitude, not in the noise of majority opinion. Those who say “people are always right” are usually selling something — whether votes, faith, or approval.”

“…ሕዘብ ምንጊዜም ትክክል ነው የሚሉት የኾነ ነገር ለመሸቀጥ ያለሙ መሰሪ ነጋዴዎች” ይለናል፡፡ 

“ሕዝብ አይሳሳትም” ስሰማ “ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት”ን  የሚያስታውሰኝ ለዚህ ነው፡፡ ከአንድ ወር በፊት ዩቱብ ላይ ተጭኖ ባገኘሁት መረጃ ላይ ዶ/ር መስከረም ለቺሳ “የጦብያ ችግር 99 በመቶ የመሪዎች ነው” ሲሉ ሰማኋቸው፡፡ Really? ይህ ድምዳሜ ሕዝብን በደንብ የሚያስተኛ የእንቅልፍ ክኒን ይመስለኛል፡፡

መሪ ከየት አፈር  ይበቅላል? የሚለውን ጥያቄ የገደፈ ስለኾነ መከራን ያራዝማል ባይ ነኝ፡፡ እሳት ለምን ተነሣ? ሳይኾን እሳቱን የማጥፋት ያህል፡፡ 

ሊዮ ቶልስቶይ Resurrection (ትንሣኤ) በተሰኘው ሥራው፣ ኖቮድቮሮፍ በተባለ ገጸ ባሕርይው  ደረቁን ሐቅ እንዲህ ይግተናል፡፡ ምን አለ? “ሕዝብ ምንጊዜም ሥልጣንን ያመልካል…ሕዝብ እናቴን ያገባ ሀሉ አባቴ ነው” የሚል ነው፡፡ እግዚኦ! ‘ሕዝብ  ታንኩን በጁ ላደረገ ማጎብደዱ ታውቆ ያደረ ነው’ ሲለን ነው፡፡ 

አለያ “ፀሐዩ ንጉሥ” ባለበት አፉ “ሌባ፣ ሌባ “ ለማለት ምን ገፋው? “ቆራጡ መሪ” ባለበት አፉ “ጨፍጫፊ፣ ፈርጣጭ” ለማለት ማን ቀደመው? ዛድያ  ለገሠ ዜናዊን “ዓባይን የደፈረ ብቸኛው መሪ” ባለበት አፉ አሁንም ያንን መድገሙ ለምን ይገርመናል?

አንድ የሃይማኖት መምህር ምእመናንን ሰብስቦ እያስተማረ “ሰይጣን ‘ፓራላይዝ’ ያደርጋል” ሲል “አሜን” የሚል አዳራሹን የሚያናውጥ ድምፅ ይቀበለዋል፡፡ ጆሮውን ባለማመን ደንግጦ “እንዴ?” ይልና “… እሺ እየሱስ ጌታ ነው” ሲል አሁንም “አሜን” ፡፡ ግራ የተጋባው መምህር ምን ቢል ጥሩ ነው? “እረ ሁሉ አሜን አይባልም፡፡” 

ሁሉን አሜን በማለት ትንሣኤ የለም!

“ሥልጣን ለመያዝ ሲል እንዲህ እንዲህ ብሎ አሞካሽቶን ሥልጣን ከያዘ በኋላ ከዳን” ማለትማ የአባት ነው፡፡

ሂትለር “ሕዝብ እውርና ደደብ ነው” ያለው ሥልጣን ከመያዙ በፊት አይደለምን?”

ሙሶሊኒ  “ሕዝብ ነፃነት ከቶ አይፈለግም፤ ከነፃነት ይልቅ መሽቆጥቆጥ፣ጭራ መቁላት የሚወድ በግ ነውና የሚሸነቁጥ መሪ ያስፈልገዋል” ያለው ሥልጣን ከመያዙ በፊት አይደለምን?

እና ሕዝብ በዝምታ መተባበሩ ይቅር፣ ማጨብጨቡን ቢቀንስ የሚሊዮኖችን ሕይወት ማትረፍ አይቻልም ነበር?  

ለብዙኃኑ የሚጮኸውን “አሁን ምን ጎድሎበት ነው? አቤት ጥጋብ!…” ብሎ የሚያሽሟጥጥ፣ ከቶ መሪ እንዴት ሊፈጥር ይችላል? ‘ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ’ የሚል እንደምን ያለ መሪ ሊፈጥር ኖሯል? መሪውን መጠየቅ የማይወድ ማ/ሰብ፣ መሪው መንበሩን ሲቆናጠጥ የሚጠይቀውን በባትሪ እያደነ ቢጨፈልቅ ለምን ይደንቀናል?

“የሀገራችን ጉዳይ እንዴት ታየዋለህ?” ሲባል “ወዳጄ ልቤ… እንኳን ሀገሬ ልጄ ናት ዓለሜ” የሚል አባወራ ገጥሟችሁ ዓያውቅም? ( እቃ ቤቱ እየተቃጠለ ሳሎን ዘና ብሎ ከልጁ እንደሚላፋው ያለ)፡፡  “ቤቱን የሠራኸው ለ ማን ነው?” ስትለው፣ ደረቱን ነፍቶ “ጥሬ ቆርጥሜ ቤት የሠራሁት ሌላ ለማን ኾነና ለልጄ እንጂ…” የሚል ምስኪን!

ጥቂት ቆይተህ ያንን አባወራ “ቤቱ እንደምን ነው?” ስትለው ጭብጥ ኩርምት ብሎ “አልሰማህም ተቃጠለ እኮ ”ይልሃል፡፡ ወግ አይቀርምና ‘አይዞህ’ የምትሉ መብታችሁ ነው፡፡ ‘ሰው ራቁቱን ነው የተፈጠረው ሠርተህ ታፈራዋለህ’  ብሎ ማጽናናትም ይቻላል፡፡  እኔ ግን ለዚህ ሰው አንድ ምክር ነው ያለኝ፡- “ቻለው!”

እኔን ጨካኝ አላችሁኝ? መብታችሁ ነው፡፡

እንደ መውጫ፡-

ግለሰብ ያስባል፣ ጥቂቶች በምልአት ገብቷቸው ብዙውን ከጎናቸው ለማሰለፍ ይቀሰቅሳሉ፣በርካታ ሰዎች በከፊል ገብቷቸው ግን በደንብ እንደገባቸው ኾነው (“በርካታ ሰው ገብቶት እኔ ደደብ ነኝ ማለት ነው?”) ይሉና ወይም ምሬታቸው ገንፍሎ ድምፃቸው ከሐሳብ አመንጪዎች ልቆ፣ጎልቶ ይሰማል፡፡ 

“እናሸንፋለን!”

“እናቸንፋለን!”
“እናሸንፋለን!….ሸንፋለን….ንፋለን… ለን…..ንንን…..”
“ሕዝብ ምንጊዜም ትክክል ነው!“
“ሕዝብ ምንጊዜም ስሕተት ነው!“
“ነው! ነው! ነ…ው! “
ብዙ ‘ነዎች’ በአንድ ቃል ይተካሉ- ‘አሜን’ በሚባል፡፡ 
“ሁሉንም ‘አሜን’ አትበሉ!!”
“አትበሉ!”
“አትበሉ!!”
“መፈክር አይደለም ምክር ነው፡፡”
“አትበሉ!”…….አትበሉ!…… በሉ!….. በሉ!…. በሉ!….ሉሉሉ….”
ያሰንበተን!

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ  

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English

ኤክስ ፡ @zborkena

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News