Homeአበይት ዜናጋዜጣዊ መግለጫከወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ምሁራን ማኅበር

ከወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ምሁራን ማኅበር

Advertise Here
Advertise here
ወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ምሁራን ማኅበር

የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ምሁራን ማኅበር
መግለጫ

የወልቃይት ጠገዴና ጠለምትን ሕዝብ የማንነት ጥያቄዎች በተመለከተ የሚሰጡ አደናጋሪ መግለጫዎችን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

ህወሓት አገር ለማፍረስ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የጀመረው የክህደት እና እብሪት ጦርነት ከሁለት ዓመት ያላነሰ ጊዜ የወሰደ ቢሆንም በኢትዮጵያዊያን ርብርብ ተቀልብሶ የጠላትን ግብ ሳይመታ ጥቅምት 23 2015 ዓ.ም በአገረ ደቡብ አፍሪካ በምትገኘው የፕሪቶሪያ ከተማ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል በተደረገ የሰላም ስምምነት የተደመደመ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳን የስምምምነቱ ፈራሚ አካላት የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት ቢሆኑም ሰላም ጠል ኃይሎች ሊፈጥሩ በሚፈልጉት አጀንዳ ሕዝባችንን ከመደናገር የመጠበቅ ኃላፊነታችንን ለመወጣት ስንል የሚከተለውን ማብራሪያ ለመስጠት ተገደናል።

ስምምነቱ ሰላምን ከማስጠበቅ ጀምሮ ወደ ሰላም ግንባታ ሊወስዱ የሚችሉ እርምጃዎችን በቅደም ተከተል ያስቀመጠ ቢሆንም ወደ ሰላም ግንባታው የሚወስደው መንገድ በህወሓት ጠጠር እየተሞላበት የሰላም ተስፋው የተሸረሸረው ወዲያውኑ ነበር፡፡ ለማሳያ ያክል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የስምምነቱ አንቀጽ 6 ቁጥር ረ (f) መሠረት የሕወሓት ታጣቂዎች ቀላል መሳሪያን ጨምሮ በ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ትጥቅ እንዲፈቱ ቢበይንም ይህ ሳይሆን ቀርቷል፡፡
በስምምነቱ አንቀጽ 7 ቁጥር መ (d) መሠረት ከማንኛውም ዓይነት ወታደራዊ ሥልጠና እና ዝግጅት ይታቀባል ተብሎ ቢጠበቅም ይባስ ብሎ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለውንና የማይካድራን አማራዎች ጨፍጭፎ ከወልቃይት ጠገዴ የወጣውን ኃይሉን ማጠናከሩን በተደጋጋሚ አሳይቶናል፡፡

ሌላኛውና ህወሓት ከስምምነቱ ማግስት ጀምሮ ያልተጻፈ ያነበበት ነጥብ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት እንዲሁም የራያ ወረዳዎችን የተመለከተውና የስምምነቱ አንቀጽ 10 ቁጥር 4 መሠረት ላይ በግልጽ የተቀመጠው ነው፡፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት የጦርነቱን ዋና ምክንያቶች በመለየትና መፍትሔ በማበጀት ለሰላም ግንባታ ጎህ ካሳየባቸው ነጥቦች አንዱ በህወሓት ከሕግ ውጭ ተወርረው ለውስጥ ቅኝ ግዛት ሲዳረጉ የነበሩት እና የተዘገቡም ሆነ ያልተዘገቡ ግፍች ሲደርሱበት የኖሩትን አካባቢዎች ከትግራይ ውጭ ናቸው ብሎ የበየነበት ነው፡፡ አከራካሪ የሚለው አገላለጽ በሕግም ሆነ በአመክንዮ የሚያሳየው ይህን ነው፡፡

ይሁን እንጂ የፕሪቶሪያ ስምምነት ጭብጥ ይህ ሆኖ እያለ እነዚህ አካባቢዎች ወደ ትግራይ የሚመለሱ አስመስሎ በተደጋገጋሚ ማቅረብም ሆነ የተለዬ ስምምነት ያለ ይመስል ከተፈረመ ጀምሮ ሕዝብን ለማደናገር የሚደረገው ተከታታይ ሙከራ የስምምነቱን የሰላም አስተዋጽዖ ከማጨለም ውጭ ሊፈጥረው የሚችለው ውጤት አይኖርም፡፡ 

ሌላው ህወሓት የፖለቲካ መጫወቻ ካርድ ያደረገው ተፈናቃይ የሚለውን አጀንዳ ነው፡፡ ሆኖም ግን በመሠረታዊነት ሊታወቅ የሚገባው ነገር ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ውስጥ በተለያየ ጊዜ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች መኖራቸውን ነው፡፡ በአንድ በኩል ሕወሓት እነዚህን አካባቢዎች ከሕግ ውጭ ወርሮ በያዘባቸው ከ27 በላይ ዓመታት ማንነታቸው እንዲከበር በመጠየቃቸው ምክንያት ቤትና መሬታቸውን እየተቀሙ፣ ቤተሰባቸው እንዲፈርስ እየተደረገ፣ የአብዛኛዎቹ ቤተሰብም በግፍ እየተረሸነ የተረፉት እንደምንም አምልጠው በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ እግራቸው ወዳደረሳቸው የተሰደዱት የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አማራዎች በርካቶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ስለተፈናቃይ ሲነሳ የእነዚህን የግፉዓን ድምጽ ሲነሳ አይሰማም፡፡ ይሁን እንጂ ከእነዚህ ዜጎች መካከል የተነጠቀ ንብረታቸው ተመልሶላቸው የተበተነውን ቤተሰባቸውን ሰብስበው የሚመለሱበት ሁኔታዎች ቢመቻችላቸው ወደቀያቸው ተመልሰው ለመኖር የሚፈልጉት በርካቶች ናቸው፡፡ ከነፃነት ማግስት ከስደት የተመለሱ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎች የተመለሱ እንዳሉ ይታወቃል፡፡

ስለሆነም ተፈናቃይ ሲባል ዜጎችን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ የተደረገው ተካታታይ ሙከራ እንደተጠበቀ ሆኖ ለትግራይ ተወላጆች ብቻ ይሠራ ይመስል በርካታ ግፍ የደረሰባቸው አማራዎችን ባገለለ መልኩ እየቀረበበት ያለው አግባብ በፍፁም ተቀባይነት የለውም። በሰሜኑ ጦርነት ጊዜ ወደ ትግራይም ሆነ ወደ ሱዳን የሄዱ አካላት አብዛኛዎቹ የህወሓት ታጣቂ ሆነው አገርን እየወጉና ንጹሃንን እየገደሉ መውጣታቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በተለይም በሱዳን በኩል ያለው ጨፍጫፊ ቡድን አቅዶና ተዘጋጅቶ የፈጸመው የማይካድራ አማራዎች ጭፍጨፋ አልበቃ ብሎት በቅርቡ በእርሻ ስራ የተሰማሩ በሰላም የሚያለሙ አርሶ አደሮችን ገድሎና ዘርፎ መሄዱ ይታወቃል፡፡ እንዲሁም ከፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት በኋላ በሱዳን እርስበርስ ጦርነት እየተሳተፈ የሚገኘው አርሚ 70 የተባለው የትግራይ ታጣቂ ኃይል ከአልቡርሃን ሰራዊት ጋር ካርቱምን ሲቆጣጠር ተሰድደው የሚኖሩ ንጹሃን አማራዎችን መግደሉን ስናይ አማራን የማጥፋት ጥማቱ ዛሬም እንዳልበረደለት የሚያረጋግጥ ነው።

በጦርነቱ ወቅት እንደማንኛውም ዜጋ በሰላም እንዲኖሩ እየተጠየቁ በድንጋጤ ወደ ትግራይ የተሻገሩ የትግራይ ተወላጆች ሊኖሩ ቢችሉም ቁጥር ከአቅም በላይ እያጋነኑና ሕዝባችን ላይ ዘግናኝ ጭፍጭፋ ከፈጸሙ ቡድኖች ጋር እያጃመሉ በራያና እና በጠለምት እንደተረጋገጠው የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በሚጥስ መልኩ እስከትጥቃቸው ገብተው ሕዝባችን ዳግመኛ እንዲጨፈጭፉና እንዲሳድዱ ለማድረግ ዝግጅቶች እንዳሉ በተጨባጭ ሁኔታ እየተመለከትን ነው፡፡

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ሕዝባችን በትግሉ ያጣጣመውን ነጻነቱን የሚያጠናክሩ የልማት ስራዎች ሲታዩ የሚደነብሩት ዛሬም እንደ ትናንቱ እኛ ቅኝ ያልገዛንበት ልማት ሊኖር አይገባም የሚል ከትዕቢት የሚመነጭ እኩይ እሳቤ መቀጠሉን የሚያመላክት ነው።

ሕዝባችን ለዘመናት የደረሰበት የታቀደና በእውቀት የተመራ የዘር ጭፍጨፋ ዳግም እንዳይደርስበት አካባቢውን ከመንግሥት ጋር ተናቦ እየጠበቀ ባለበት ሁኔታ ትናንት የደረሰበት ዘግናኝ የዘር ጭፍጨፋ ዛሬም ሊደገምበት እንደሚችል በሚያሳይ መልኩ በስሙ የጠሩ አካላት የሚደርስባቸውን ወቀሳ ስናይ፤ ትጥቁን እንዲፈታ እና ከቀየው እንዲፈናቀል የሚደረገውን ጉትጎታ ስንመለከት እነዚህ አካላት ቦታው ላይ መልሰው ቢቀመጡ ምን ለማድረግ እንዳቀዱ የሚያሳይ ምልክት ሆኖ አግኝተነዋል።

ስለሆነም ለሰላም መሠረት ለመጣል ተስፋ የተደረገበትን የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተጻፈውና ከአውዱ ውጭ እየተተረጎመ የሚቀርብበት መንገድ የሰላምን ተስፋ መልሶ የሚያጨልም እንዳይሆን በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ተጠምደው አላስፈላጊ ቅስቀሳ የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እናሳስባለን፡፡

የማህበረሰባችን ችግሮች ለመፍታት እንተጋለን!!!

- Advertisement -

የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ምሁራን ማኅበር
ኅዳር 15/2018 ዓ/ም
ሁመራ፣ አማራ፣ ኢትዮጵያ

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English

ኤክስ ፡ @zborkena

2 COMMENTS

  1. This is very good press release. Keep it up! It is not only Woyane which is the ememy of the Wolkait people but also you have to keep your eye on Abyie who may want to play politics with your Amhara identiy. He is comaring Wolkait with Dire-dawa.

  2. የወልቃይት ጠገዴ ሁመራ ህዝብ በታሪክ የትግራይ ሆኖ አያውቅም። ይሁን እንጂ ወያኔ የሃገር መሪ ነኝ ብሎ አዲስ አበባ ላይ ከከተመ በህዋላ በእነዚህ አካባቢ ኗሪዎች ላይ የደረሰው ግፍ የጀርመኑ ሂትለር በአይሁዶች ላይ ከፈጸመው ጋር ይመሳሰላል። ወያኔ ማለት በዘሩና በቋንቋው የሰከረ ኢትዮጵያ ጠል ስብስብ ነው። ወያኔን ማመን ጊንጥን ኪስ ውስጥ አስገብቶ አይነድፈኝም እንደማለት ይቆጠራል። የራሳቸውን ወገኖች በተኙበት የረሸኑ፤ ለዓመታት በትግራይ የሃገር ድንበር ሲጠብቅ የነበረውን የሰሜን ጦር በጥይት በተኙበት የደበደቡ፤ በማይካድራ ያን ሁሉ ግፍ ፈጽመው ወደ ሱዳን ተሻግረው ከአልቡርሃን ጦር ጋር ሆነው የሚዋጉ ድርቡሾች ናቸው። የሚያሳዝነው ያለፈው ግፍ ላይበቃ አሁንም ተፈናቃይ ይመለስ፤ ምስራቅ/ምዕራብ ትግራይ ወሰናችን ነው ሲሉ አፍረት የላቸውም። ወያኔ አፈር ካልተመለሰበት ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለመላ ሃገሪቱ የመከራ ዝናብ ጠንቅና መዘዝ መሆኑ ይቀጥላል።
    የወልቃይት፤ ጠገዴና ሁመራ ህዝብ ያለው ምርጫ አንድ እና አንድ ብቻ ነው። በአንድ እጅ መዶሻ በሌላ እጅ ማረሻ ይዞ ለመኖሩ መታገል። የፌዴራል መንግስት ያድነኛል፤ ሰራዊቱ ይደርስልኛል ብሎ ማሰብም ራስን ማሞኘት ነው። ከሊቅ እስከ ደቂቅ ወያኔና ተባባሪዎቹ ውጊያ ቢከፍቱ እንዴት መመከት እንደሚቻል መትለም፤ መሰልጠን፤ መታጠቅ ያለበት ህዝቡ አሁን ነው። ወያኔ አንድ የሚገባው ነገር ቢኖር በጦርነት መሸነፉ ብቻ ነው። የደርግን ያህል ሰራዊት ጥለን በማለት ሻቢያና ወያኔ በየዓመቱ ከበሮና ክራር አንግተው ይዘክሩት እንጂ ደርግን የጣለው ጊዜ ነው። ደርግ ራሱ በራሱ ያፈረሰ መንግስት ነው። በ 11ኛው ሰአት ላይ ለማይሳካ መፈንቅለ መንግስት ያ ሁሉ የሃገሪቱ ወታደራዊ መኮንኖች ማለቅ ውድቀቱን አፋጥኖታል። ከዚያ ዛሬ እኛ የምንማረው ምን አለ ብለን ብንጠይቅ ብዙ ጉዳዪች እናገኛለንና መፈተሽ ይገባል። በጭካኔና ህዝብን በማሰቃየት በስልጣን ላይ እድሜ ልክ መኖር እንደማይቻል ያለፈው ታሪካችን ፍንትው አድርጎ ያሳየናል። ለዚህ ነው የክልልና የፌዴራል መንግስቱን ጭምር ተው መጨከን፤ ማፈን፤ መግደል፤ ማሰር ለእናተም ለሃገሪቱም ሰላምና ደህንነት አይበጅም የምንለው።
    የወልቃይት ጠለምትና ሁመራን ጉዳይ በተመለከተ በየድህረ ገጽ ባልገባቸውና ገባን ባሉት ነገር ላይ የሚቀባጥሩ ሁሉ ከዚህ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል። የምትነግድት በህዝብ ደም ነው። ሲጀመር ወልቃይት ጠገዴና ሁመራ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃገር እንጂ የአማራ ብቻ አይደለም። የአፓርታይድ የክልል ፓለቲካ የፈጠረው ስንክ ሳር እንሆ በዚህም በዚያም ሰውን እያባላ ይገኛል። ይህ የክልል ፓለቲካ ደግሞ ሆን ተብሎ ከጣሊያኑ የወረራ ዘመን ስልት ወያኔ የገለበጠው የከፋፍለህ ግዛው ስሌት ነው። ለዚህ ነው በሰላም፤ ሰርቶ ለፍቶ ለማደር፤ የከባቢንና የሃገሪቱን ህግ አክብሮ ለሚኖር ሰው ወልቃይት/ጸለምትና ሁመራ ክፍት ነው እያልን ያለነው። በእነዚህ ስፍራዎች ሰው በዘሩና በሃይማኖቱ አይገፋም። ይህ በስፍራው ያለ እውነታ እንጂ ለፓለቲካ ፍጆታ ከሚያልፍ ወንዝ የተጨለፈ ፕሮፓጋንዳ አይደለም። እሰማለሁ… ይወራል ፋኖ እና የተከዜ ዘብ አይስማሙም ገለ መሌ ይባላል። ፋኖ ወያኔ በአማራው ህዝብ ላይ የፈጸመውን በደል ጠንቅቆ ያውቃል። ግን ጊዜው የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል ስልት ከሆነ ወያኔ ፋኖንም ለራሱ ተግባርና ስልት ተጠቅሞ ቅርጥፍ አድርጎ እንደሚበላው ጥርጥር የለኝም። ስለዚህ ከወያኔና ከሻቢያ ጋር ፋኖ ከተለጠፈ የሃገር ጠላት እንጂ ወዳጅ ሊሆን አይችልም። እነዚህ ሁለት ሃይሎች ናቸው ዛሬ ላለንበት የፓለቲካ ቅርቃር የዳረጉንና!
    እርግጥ ነው ብልጽግና ብዙ ችግር ያለበት መንግስት ነው። ግን በጦርነት ለውጥ እናመጣለን እያሉ ምድሪቱን ወደ ድንጋይ ዘመን መመለስ እብደት እንጂ ጤንነት አይደለም። ፋኖ ከመንግስት ጋር ተነጋግሮ በሰላም ነገሮችን ቢፈታ የጊዜ ገደብ ከሌለው የመገዳደል ፓለቲካ ህዝባችን እፎይ ለማለት ይችላል። እጅ ቆራጩ ማን ነው/መምህራን ገዳዪ/አዛውንትና እናቶችን አንበርክኮ የሚነዳው/መንገድ ዘግቶ ዝርፊያ የሚያካሂደው… ስንቱ ይወራል.. ይህ ነው 27 ዓመት በወያኔ ክርፋት ታፍኖ ለኖረ ህዝብ የሚገባው? ተው ህዝቡን የበለጠ መከራ ውስጥ አትክተቱት። ብዙ ዋጋ የከፈለ ህዝብ ነው። ወልቃይት/ጸለምት/የጠገዴና የሁመራ ህዝብም የዚህ ህዝብ አንድ አካል ነው። ጦርነት ይብቃ፡፤ ለወራሪዎችና ለአፈናቃዪች ግን ራስን አስታጥቆ፤ መጣሁባቹሁ የሚለውን ተው እዚህም እሳት አለ አርፈህ ተቀመጥ ለማለት መዘጋጀቱ በጎነት አለው። ነጻ እናወጣሃለን እያሉ ሰውን ለመከራ መዳረግ ግን ወያኔን መምስል ስለሆነ ለማንም አይጠቅምም። በመጨረሻም ወጠጠአምማ ያወጣው መግለጫ ማለፊያና ገና ትግሉ ቀጣይ እንደሆነ አመላካች ነው። በጥባጭ እያለ ማን ጥሩ ይጠጣልና። ፓለቲካ አውሎ ንፋስ ነው …. አቅጣጫ ይቀይራል፤ አሰሱን ገሰሱን ይዞ ይተማል… አሁን ማን ይሙት ከጌታቸው ረዳ ጋር ተስማምቶ የሚሰራ የብልጽግና መንግስት እነ መስከረም አበራንና አቶ ታዲዎስ ታንቱን የመሰሉ የሰላም ሰዎችን እንበለ ፍርድ ጠፍሮ ጨለማ ቤት ያሰቃያል? ጌታቸው ረዳ…. ” ሲኦል ድረስ ወርደን እንኳን ቢሆን ኢትዮጵያን እናፈርሳታለን” ያለ … አልፎ ተርፎም የሰሜን እዝ እንዲመታ አመራር ከሰጡት ሰዎች አንድና ቀዳሚው ነው። አይ አብይ ትገርማለህ…. ገና ስርህ ሆኖ ብዙ ነገር ይሰራል። አፉ እረፍት የለውምና የሚያፈርሰው በፈንጂና በሞርታር ሳይሆን በቃሉ ነው። ወያኔዎች የማይታመኑ ተኩላዎች ናቸው… እንሰንብት ሁሉን እናያለን። በቃኝ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News