Homeነፃ አስተያየትጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ  የወላይታን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ  የወላይታን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው፡፡

Advertise Here
Advertise here

ለጦርነቱ ወታደር መገበር እንጂ   የሰራዊቱ  መሪ እንዲሆን  የማይፈቀድለት  የወላይታ ህዝብ በብልጽግናው መንግስት  የሚደርስበት  መገፋት፣መናቅና በቀል  ሞልቶ እየፈሰሰ ነው

  በአበራ ገረመው 

ሀገርን  በወጉ መምራትና መንግስታዊ ስርአት ያላጸና.፣ ሰላምና መረጋጋት ያላረጋገጠ፣ልማት አካሂዶ ስራ አጥነትን መቅረፍ ያልቻለ  ወዳቂና ፉርሽ  ለሆነ  መንግስት የወላይታ ወጣቶች  እስከ መቼ  የህይወት መስዋትነት እንሚከፍሉ መጠየቅ ያለበት ትክክለኛ ጊዜው አሁን ነው፡፡  ተምሮም ሆነ ሳይማር ስራ አጥ የሆነው የብሄሩ ተወላጅ በቀየው ይሁን በፌደራል ደረጃ ስራ አገኝቶ ተረጋግቶ ህይወቱን ማስቀጠል ባለ መቻሉ  አማራጭ አድርጎ ወደ  ውትድርና ተቀላቅሎ  ህይወቱን ለአደጋ ማጋለጥ  ማቆም የሚጀምርበት ከዚህ የተሸለ ጊዜ የለም፡፡ በአሁኑ በጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የሚመራ የብልጽግና ዘመን ወደ ውትድርና የመግባት ዕጣ ፋንታ ግልጽ ነው፡፡ እሱም  ህይወቱ ደመ ከልብ መሆን ነው፡፡  በህዝብ ቅቡልነት ያለው፣በአለም አቀፍ ደረጃ ክብርና ዝና ያጎናጸፈ፣ሁሉንም ህዝቦች በእኩልነት የሚያይ፣ሃላፊነት የሚሰማው፣ጉድለቱን አምኖ ህዝብ እንዲሞላለት የሚሻ ቅን ልቦና ያለው መንግስት ቢሆን የሚከፈለው መስዋአትንት  የተቀደሰ ይሆን ነበር፡፡ ዳሩ ግን የወላይታ ህዝብ ለጦርነቱ ወታደር መገበር እንጂ   የሰራዊቱ  መሪ እንዲሆን፤ለሀገረ መንግስቱ ምስረታና ግንባታ ባበረከተው አስተዋጾ ልክ በፌደራል ደረጃ እውቅና ተነፍጎ   በብልጽግናው መንግስት  የሚደርስበት  መገፋት፣መናቅና በቀል  ሞልቶ እየፈሰሰ ነው፡፡ 

የወላይታ ህዝብ ላለፉት አንድ መቶ አመታት በተከናወነው ሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት በውትድርና ሀገር በማጽናት፣በሲቪል ሰርቢስ ሀገሩን በልጆቹ በማልማት፣በአስደናቂው ባህሉ ኢትዮጵያን ለአለም በማስተዋወቅ፣ አርሶ አደሩና ነጋዴው ህብረተሰብ ላቡን አንጠፍጥፎ ከሚያገኘው ገቢ  ግብር በመክፈል ሀገር እንድትጸናና በአለም ካርታ ተመዝግባ እንድትቆይ ከፍተኛ አስተዋጾኦ አበርክቷል፡፡ ታሪኳ የጦርነት ታሪክ ሆኖ እስካሁን በዘለቀባት በዚች አከልዳማ ምድር የወላይታ ወጣት ልጆች  የውስጥንም ሆነ የውጭ ወረራ ለመመከት የከፈሉት መስዋአትን ከሃዲው የብልጽግና መንግሰት ከቁብ ባይቆጥር ታሪክ መዝግቦት ይገኛል፡፡  በሌሎች ሀገሮች ለሀገራቸው የተሰው ወታደሮች ስማቸው በታሪክ መዝገብ ተሰንዶ፣ በሃውልቶች ላይ ተቀርጾ፣በስማቸ መታሰቢያ  ተሰርቶና መካነ መቃብራቸው ተከልሎ  እንዲቀመጥ ያልታደልን  ማህበረሰብ  ሆነን እንጂ  ፈጣሪ ለአለማ የፈጠራት የወላይታ ልጆች ህይወት ደም ከልብ መሆን ለምንድነው  ብለን ጥያቄ አለማንሳታችን  የሞራል ብቃታችንን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው፡፡   በየዘመኑ የተሰው ወታደሮች  ስምና ቁጥር ወታደራዊ ሚስጢር ሆኖ ከህዝብ የሚደበቅበት፤ መረጃው ለጥናትና ምርምር ቢፈለግ እንኳ ለማግኘት የማይፈቀድበት ከድንጋይ ዘመን አስተዳደር ያልወጣን ማህበረሰብ ስለሆንን እንጂ   የወላይታ ህዝብ  ለከፈልነው መስዋአትነት በፌደራል ደረጃ እስካሁን የተሰዘጠ  እውቅና መመዘን.፣መገምገም፣ ብሎም መጠየቅና መሞገት አለመቻላችን የትውልዱን ውድቀት ከማመልከት ውጪ ሌላ ምንም ልባል አይችልም፡፡ 

በስራ ላይ ባለው ህገ መንግስት የኢትዮጵያ  የመከላከያ ሰራዊት ስብጥር  የሁሉም ብሄሮችና ብሄረሰቦች ሚዛናዊ አስተዋጾኦ  መጠበቅ እንዳለበት በማያሻማ አኳኃን ተቀምጧል፡፡ ህገ,-መነግስቱን ተንተርሶ በወጡ ተከታታይ አዋጆችም ተመሳሳይ ድንጋጌዎች ቁልጭ ብለው ተከትበዋል፡፡ ይህ ድንጋጌ ወደ መሬት ወርዶ በሰራዊቱ አደረጃጀት እንዴት እንደሚገለጽ የሚቆጣጠር፣የሚከታተልና የሚገመግም ህግ አውጪና አስፈጻሚ አካል በህገ መንግስቱ ተደንግጎ ቢገኝም በተግባር ግን  የኢትዮጵያ ሲቪል ውትድርና ግንኙነት ብላሽ  እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ በዚህ የተነሳ ህገ መንግስታዊ ሃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ስራቸውን በአግባቡ የማይወጡ በመሆኑ በሀገራችን የማያባራ ጦርነት ውስጥ ገብታ እየዳከረች ነው፡፡  የብሄረሰቦች ጉዳይ “ጉዳዬ ነው” የሚለው አባባል ከአንደበቱ የማይጠፋው የፌደረሽን ምክር ቤትም በአመት አንዴ ተሰብስቦ በጀት ከማጽደቅ ውጪ አንዲህ አይነት ፖለቲካዊ ቁርጠንነትን በሚጠየቁ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምርመራና ግምገማ አድርጎ የአስፈጻሚውን አካል አመል ሊገራ አልቻለም፡፡ በአለም ለረጅም ጊዜ በአስቸኳይ አዋጅ ስር ሀገር የምታስተዳደር የመጀመሪያና ብቸኛ  ሀገር ቢትኖር ኢትዮጵያ  እንደሆነች ምንም የሚያጠራጠር አይደለም፡፡  በሶስት ወር ያልቃል የተባለለትና “የህግ ማስከበር ዘመቻ” የሚል የዳቦ  ስም የወጣለት የእርስ በርስ ጦርነት ድፍን አመት ሲሞላው የመከላከያና የደህንነት ተቋማት ብቃትና ታማኝነት የሚላካበት ስርአት አጥተን በግራ መጋባት እየዳከርን ነው፡፡   ብላሽ ሲቪል ውትድርና ግንኙነት ባለበት ሀገር ወታደሩ የሙያ ብቃት ስለሚጎድለው የአውደ ውጊያ ሽንፈት፣ክዳት፣ የውትድርና ፍቅር መዳከም፣የአገልጋይነት መንፈስ መዳከም፤ፖለቲካዊ ሹመትና የማዕረግ እድገት እንዲሁም ስንብት  መገለጫ እንደሆነ የሲቪል ውትድር ድርሳናት በግልጽ ያስቀምጣሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል ውትድርና መሰረት የሚያስቀመጠው ህገ መንግስት  የሰራዊቱ ስብጥር  የህዝቦች ተዋጾኦ ምክንያታዊ በሆነ ደረጃ መሟላት እንዳለበት የሚያስቀምጠው ግልጽ ድንጋጌ በአሁኑ መከላከያ ሰራዊት በግልጽ ተሸርሽሮ ይገኛል፡፡ በጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥነት የሚመራው መንግስት ከወላይታ ማህበረሰብ ወታደር እየመለመለ ለስልጣኑ ማስጠበቂያ ያቀጣጠለውን ጦርነት ላይ ያሳትፋል እንጂ ከብሄሩ አመራር እንዲወጣ አይፈቅድም፡፡ ከዚህ ተነስቶ በታሪክ አጋጣሚ  በብቃታቸው፣በትምህርትና ስልጠና ዝግጅታቸውና በአመራር ብቃታቸው የታወቁ ሶስት የወላይታ ጀኔራሎችን ከሚያገለግሉበት መከላከያ ተቋም  ከአገልግሎት  በተለየ መመዘኛ በማሰናበት ታሪካዊ በደል በህዝቡ ላይ ፈጽሟል፡፡ በሀገሪቱ ላይ ዘላቂ ጉዳት የሚያስከትል የድንቁርና እርምጃ ወስዷል፡፡ ይህች ሀገር የምትጸናው በሁሉም ህዝቦች እኩል ተሳትፎና ሀገራዊ ስሜት ካልሆነ ጠቅላይ በሆነ የአንድ ብሄር አባላት የበላይ በሆኑባት  ወይም ፓርቲ ፍላጎት በሚመራ ተቋም ባለበት ሀገር ሰላምና መረጋጋት ይፈጠራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ 

የጀኔራሎችን ስንብት ጠ/ሚኒሰትር ዐቢይና  የጦር ሀይሎች ጠ/ኢታማዞር ሹም ፍልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሳያውቁ  እንደማይፈጸም በአዋጁ ላይ በግልጽ ተቀምጦ እያለ ጀኔራሎቹ የተሰናበቱበት አግባብ  መዋቅራዊ አድሎና ማግለል እንደሆነ የወላይታ ህዝብና ለፍትህ የምታገሉና ለአናሳ ህዝቦች የሚቆረቆሩ ወገኖች ልብ ሊሉ ይገባል፡፡  በጠቅላላ የወላይታ ሰራዊት አባላትና ከፍተኛ መኮንኖች ላይ የሚደርሰው ጥላቻ፣ማግለልና ሞራላቸውን መንካት ምንጩና መነሻውን መግለጹ አስፈላጊ ነው፡፡ መነሻው የ2010 ለውጥ ተከትሎ የመጣው  ፖለቲካቂ ውዝግብ ነው፡፡ ወቅቱ የህወሃት መሪዎችና ደጋፊዎች ከለውጥ ሀይሎች ጋር እንካሰላንቲያ የጀመሩበት ወቅት ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ጥቂት የወላይታ ፖለቲከኞችና ማህበራዊ አንቂዎች ከህወሃት ሰዎች ጋር የጀመሩት ያልዘለቀ ግንኙነት ነበር፡፡ እነዚህ ጥቂት ግለሰቦች በፌደራሊስት ሀይሎች በሚባሉ ቡድኖች የተደራጀውን የመቀሌ ስብሰባ በወቅቱ ሲሳተፉ በሚዲያ ታይተዋል፡፡ ይህ ግን  በመከላከያ ውስጥ የሚያገለግሉ ወታደሮችንና መላውን ህዝብ የሚወክል አልነበረም፡፡ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በህገ መንግስቱ በተደነገገው መሰረት ከማንም ሳይወግኑ ገለልተኝነታቸውን እንደጠበቁ ቆይተዋል፡፡ እዚህ ላይ በግለሰብ ደረጃ የወገኑ ስለመኖራቸው መረጃ አልተገኘም፡፡ የሰሜኑ ጦርነት እንደተጫረ የሰሜን ዕዝ መረጃ ሃላፊ የነበሩት ብርጋዴየር ጀኔራል ኢናሶ እጃጆ  ከህወሃት በመወገን በሃሰት ተወንጅለው ለሁለት አመት ገደማ በእስር ከቆዩ በኋላ መረጃ ባለመገኘቱ ከወሂን ቤት ተለቀቁ፡፡ ከዚያም ወደ ስራ ሳይመለሱ ተሰናበቱ፡፡ 

ሁለተኛው ጠ/ሚር ዐቢይ አህመድ መንግስት በወላይታ ህዝብ ላይ ቂም እንዲቋጥርና አግላይ ፖሊሲ እንዲከተሉ ያደረጋቸው  የ2010ሩ የአዋሳው የወላይታ ብሄር ተወላጆች ጭፍጨፋ ነበር፡፡ የአዋሳው ጭፍጨፋ  ተከትሎ በወላይታ ሶዶ ነውጥ ተከስቶ ስለነበር ህዝቡን ለማረጋጋት ጠ/ሚኒስትሩ ሲመጡ የሲዳማ ብሄር ተወላጅ የሆነውንና  በወቅቱ የደቡብ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር  የነበሩትን ደሴ ዳልኬን ይዘው ጉተራ አደራሽ  ውስጥ  በተሰበሰበው ህዝብ ፊት ሲቀርቡ ህዝቡ ማቅ  ለብሶ ጠበቃቸው፡፡ ከዚያም ደሴ ዳልከን ከመድረክ ካወረዱ ከእሳቸው ጋር መነጋገር እንደሚፈልጉ ህዝቡ ሲጠይቋቸው ጠቅላዩ መድረኩን ዘግተው ተነሱ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጠቅላዩና የወላይታ ህዝብ ሆድና ጀርባ እንደሆኑ ቆይተዋል፡፡ ይህ ግንኙነት ጠቅላዩና የእሳቸው ቀኝ እጆች  በሰራዊት ውስጥም ሆነ በሲቪል ሰርቪስ በሚያገለግሉ የወላይታ ተወላጆች ላይ  አቂመው አድሎአዊና አግላይ ፖሊሲ እንዲያራምዱ መነሻ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡  በርግጥም በወላይታ ምድር በታሪክ ህዝብ በንቀት የተቀበላቸው የሀገር መሪ እሳቸው ናቸው፡፡ የህ ደግሞ ካለ ምክንያት አይደለም፡፡ ህዝቦችን በእኩል አለማየት፣ በግለሰቦች የተነሳ ህዝብን እንደ ህዝብ መፈረጅና ማግለል ውጤት ነውና፡፡ ሀገሪቱን ከቀውስ ወደ ቀውስ እየመሩ  ዜጎችን ተስፋ ያስቆረጡ፣ምድሪቱን አከልዳማ ያደረጉ  ወደር ያልተገኘላቸው መሪ ስለሆኑ  ነው እንጂ የወላይታ ህዝብ “ንጉስ የቆረጠው እጅ ጌጥ ነው” የሚል የቆዬ ልማዳዊ አባባል ያደበረ ህዝብ ነው እንጂ አመጸኛ ህዝብ ስለሆነ አይደለም፡፡ 

አሽቀባጩ የወላይታ ካድሬ ግን  ከብልጽግና መንግስት የሚወረወርለትን የኑሮ መደጎሚያ በማየት የወላይታ ህዝብ በታሪክ ለሀገረ መንግስቱ ያበረከተውን አስተዋጾኦ የሚመጥን ውክልና በፈደራል ደረጃም ሆነ በክልል ደረጃ በሰራዊትም ሆነ በሲቪል ሰርቪስ አለመወከሉ ቆጭቶት አንድ ቀን እንኳ ሲጠይቅ አይታይም፡፡ በፓርላማ ህዝብን ወክለው የተቀመጡ አካላትም ጉዳዩን አንስተው ጠቅላዩን ሲጠየቁ አይስተዋሉም፡፡  በወላይታ ማህበረሰብ ላይ  አድሎ፣ ጥላቻና ከወታደራዊ አመራር የማግለል  ፖሊስ በአንድ በኩል በህዝቡ ላይ ተጭኖ በሌላ  በኩል የወላይታ ወጣት  ልጆች የስርአቱን ስልጣን ለማራዘም በአማራና በኦሮሚያ ክልል የተጫረውን የእርስ በርስ ጦርነት ለመመከት ተሰልፈው መስወአትነት በመክፈል ላይ ናቸው፡፡ በየጊዜው ተመልምሎ ሰራዊቱን የተቀላቀለው ምልምል በጦርነቱ ጭዳ ሲሆንበት በየሁለት ወሩ አዲስ ምልምል በግዳጅና በስራ እጦት እየተገፋ  በሺዎች እየገባ ለመስዋአትነት እየተሰናዳ ነው፡፡

 ሳጠቃልለው ጠ/ሚ ዐቢይ አስካሁን በወላይታ ህዝብ ላይ  ለፈጸመው ቂመኝነት ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ከቂም ተነስተው በመከላከያ ሰራዊት ውስጥም ሆነ በሲቪል ሰርቪስ የፈጸሙት  አድሎአዊ ፖሊሲ በይፋ  አነስተው  ከወላይታ ህዝብ ጋር መደራደር አለባቸው፡፡ ካለበለዚያ የወላይታ ህዝብ ይንቃ! አንድም ወታደር ለእርስ በርስ ጦርነት ከወላይታ ተመልምሎ ሕይወቱን ማጣት የለበትም፡፡  ስራ ቢጠፋ፣ የሚበላ  ቢጠፋ ዕድሜ ለምድራችን በነጻ የሚለቀም ቅጠል ቡናና ከመሬት የሚታፈስ ስኳር ድንች ሞልቷልና እቤታችን ተቀምጠን በልተን ይህንን ክፍ ጊዜ ማሳለፍ ያስፈልጋል፡፡ ለማይረባ ጦርነት ሕይወትን ከመስጠት ቆሎ ቆርጥሞ ቅጠል ቡና ጠትቶ ሕይወትን ማቆየት ብልህነት ነው፡፡ በመረጃ እጥረት ተደናግረው ውትድርና የሚገቡ የገጠር ወጣቶች በቂ መረጃ ሰጥቶ ሕይወታቸውን መታደግ የነቁ የህብረተሰብ ክፍሎች ሃላፊነት ነው፡፡  ከሰራዊቱ ዕድሜያቸውንና ወጣትነታቸውን ተጠቅመው አግልግሎት ሰጥተው  በልዩ ልዩ ሁኔታ የተሰናበቱ ወታደሮች ይስሙ! ጠ/ሚ ዐቢይ መንግስት በይፋ ይቅርታ ጠይቆ በወላይታ ህዝብ ላይ የጫነው አድሎአዊ ፖሊሲ ካላነሳ አንድም ወታደር ዳግም ጥሪ ሲደረግ ግንባር ዘምቶ ህይወቱን ማጣት የለትም፡፡   በአማራና በኦሮሚያ የተቀጣጠለው ጦርነት እንዲሁም በትግራይ እያንዛበበ ያለውና የኤርትራ ጦርነት እየገፋ ሲመጣ የክተት አዋጅ ማወጁ አይቀርም፡፡  ከሰመኑ ጦርነት መማር አለብን፡፡ ወታደሮች አለቁ መጨረሻ ላይ መሪዎች ትኬሻ ለትኬሻ ተሳሳሙ፡፡ መንግስት ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ይፍታው እንጂ ስልጣኑን ለማራዘም ብሎ ለሚያካሂደው ጦርነት አንድም ተሰናባች  ወታደር ምላሽ መስጠት ህይወትን ደመ ከልብ ማድረግ ነው፡፡ 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ  

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

- Advertisement -

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English

ኤክስ ፡ @zborkena

ለቦርከና መልዕክት ለመላክ  በሚከተለው አድራሻ ይላኩልን info@borkena.com 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News