
22/03/2018
ቦርከና ዜና
የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ቅዳሜ ዕለት በምስራቃዊቷ የፖርት ሱዳን ከተማ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ ጋር ተገናኝተው በሁለቱ ሀገራት መካከል የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ለማጠናከር እንዲሁም የፖለቲካና የጸጥታ ትብብርን ለማሳደግ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ተወያይተዋል ተብሏል።
መሪዎቹ በውይይታቸው በቀጠናዊ ጉዳዮች እና አከባቢያዊ መረጋጋትን ለመደገፍ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ሀሳብ ከመለዋወጣቸው በተጨማሪ የጸጥታ፣ የኢኮኖሚና የንግድ ግንኙነትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ትብብርን ማጠናከር ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን የሱዳን ዜና ወኪል ሱና ዘግቧል ።
ሁለቱ መሪዎች በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ባለው ቀጣይ ጦርነት ሳቢያ በሱዳን ያለውን የቅርብ ጊዜ ሁኔታ የገመገሙ ሲሆን ሰላምን እና አከባቢያዊ ደኅንነትን ለማምጣት በሚረዱ መንገዶች ዙርያ መወያየታቸውን ዘገባው አመልክቷል።
በዚሁ ወቅት አል-ቡርሃን ሱዳን ከኤርትራ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ለማሳደግ እና ያላትን ቁርጠኝነት አጽንዖት ሰጥተው፤ አስመራ የሱዳንን አንድነትና መረጋጋት አስመልክቶ ለምታደርገው ድጋፍ አድናቆት ሰጥተዋል ተብሏል።
አክለውም መንግሥታቸው በሁሉም ዘርፎች ከኤርትራ ጋር ትብብሩን ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።
አል-ቡርሃን በተጨማሪም የሁለቱንም ሕዝቦች ጥቅም የሚያስጠብቅና የቀጠናዊ ደኅንነትን የሚያጠናክር የላቀ ትብብር እንደሚኖር ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ሀገራቸው ለሱዳን አንድነትና መረጋጋት ያላትን ድጋፍ እንዲሁም በማንኛውም የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን እንደማትቀበል አረጋግጠዋል።
“የሱዳን መረጋጋት ለቀጠናው መረጋጋት ቅድመ ሁኔታ ነው” ሲሉ አክለዋል።
ኤርትራ በሱዳን የርስበርስ ጦርነት ለሀገሪቱ ጦር ድጋፍ እንደምታደርግ ያላትን አቋም ገልፃለች።
የፈጥኖ ደራሽ ሀይል መሪው ጄነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ በበኩላቸው ኤርትራ ላይ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።
……………………………………….
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






