
ቦርከና ዜና
30/03/2018
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎች የአስቻይ ሁኔታ ማረጋገጥ ቅደመ ሁኔታ የቀረበበትን 7ኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማጽደቁን አስታውቋል፡፡
ቦርዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለውይይት ያቀረበው ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ በፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ የተሳበት ቢሆንም፣ ያለምንም ለውጥ አጽድቆታል፡፡ ፓርቲዎች በምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው ላይ በተወያዩበት ወቅት ቅድሚያ አስቻይ ሁኔታ መኖሩ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አለብን በሚል መቃወማቸው ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ በረቂቅ ደረጃ ያቀረበውን የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ያለምንም ለውጥ አጽድቆቷል፡፡ በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫው ግንቦት 24/2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን፣ ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችም የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶላቸዋል፡፡
ፓርቲዎች ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታ የለም ማለታቸው ይታወሳል፡፡ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ከማጽቅ በፊት አስቻይ ሁኔታዎች መፍጠር ላይ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር ጠይቀዋ ነበር፡፡
ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤታቸው በኩል ከ7ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የሕገመንግሥት ማሻሻያ በማድረግ የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ስርዓትን እንዲቀየር መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለመንግሥት ያቀረባቸው ጥያቄዎች ከሕገ መንግሥት ማሻሻያዎች እሰከ ምርጫው ጊዜ ሰሌዳ ማሻሻያ ድረስ ዘለቀ ነበር፡፡
ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገውን ረቂቅ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ስምምነት እንደሌላቸው መገለጻቸው ይታወሳል፡፡ የቀጣዩን ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቅድመ ምርጫ ስራዎችን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ይችሉ ዘንድ በቂ ጊዜ መስጠት በሚያስችል መልኩ እንዲዘጋጅ ተጠይቆ ነበር፡፡
በጋራ ምክር ቤቱ ደረጃ በጥቅል ከቀረበው ጥያቄ በተጨማሪ አንዳንድ ፓርቲዎች በጉዳዩ ላይ በተናጠል ጠንካራ ተቃውሞ ሲያሰሙ ነበር፡፡ እንደ ኢሕአፓ፣ እናት፣ ኦፌኮ፣ መኢአድ፣ ኢሶዴፓ ያሉ ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች የምርጫ ጊዜ ሰሌዳው ከመጽደቁ በፊት፣ በአስቻይ ሁኔታ ላይ ስምምነት እንዲደረግ ጠይቀው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ የፓርቲዎቹን ቅሬታ ውድቅ በማድረግ፣ በረቂቀር ደረጃ ያቀረበውን የጊዜ ሰሌዳውን አጽድቆታል፡፡ የፓርቲዎችን የምርጫ አስቻይ ሁኔታ ምዘና ችላ ብሏል የተባለው ቦርዱ፣ ምርጫውን ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ላይ አካሂዳለሁ ብላል፡፡
ከዚህ ቀደም በ6ኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ እንደተደረገው የጸጥታ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች፣ እንደሚያልፋቸው ቦርዱ አስታውቋል፡፡ በባለፈው ምርጫ ትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ አብዛኛው፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና አማራ ክልል በከፊል ምርጫ ሳይደርግ መቅረቱ ይታወሳል፡፡
ዘንድሮም ምርጫ በተመሳሳይ የሚያልፋቸው አካባቢዎች ለሁለት ተከታታይ ጊዜ ተወካይ ሳይመርጡ ይቀራሉ እንደማለት ነው፡፡ በትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ ነጻኛ ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ አለመሆኑን ፓርቲዎች እየገለጹ ነው፡፡
…………………………………………………………….
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






