
ቦርከና ዜና
09/04/2018
በጋምቤላ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት ባየለበት ወቅት የፌደራል የፀጥታ አካላት ወደክልሉ መግባቱን የክልሉ ፕሬዝዳንት አረጋግጠዋል።
በዋና ከተማዋ ጋምቤላ በተለያዩ አቅጣጫዎች የተኩስ ድምፅ መሰማቱን እና ወደከተማዋ የሚደረጉ ንቅናቄዎች ስጋት መፍጠራቸው ተገልጿል።
የብሄር መልክ ይዟል የተባለው ግጭት አድማሱን እያሰፋ መምጣቱን ተከትሎ፣ ክልሉ የፀጥታ ችግሩን መቋቋም እንደተሳነው ተገልጿል።
የክልሉ ርዕሰ መስተደዳድር አለሚቱ ኡሞድ የግጭቱ መንስኤ አንድ የፖሊስ አዛዥ በመገደሉ ምክንያት ችግሩ መባባሱን አብራርተዋል።
ፕሬዝዳንቷ ሰሞኑን የፖሊስ አዛዡ ከመገደሉ በፊትም የፀጥታ ችግሮች በአካባቢው ተፈጥረው መቆየታቸውን አብራርተዋል።
ነገርግን ከግድያው በኋላ አካባቢው ሠላም የነበረ ቢሆንም አንዳንድ አከባቢዎች ላይ የተለያዩ የተኩስ ድምጿች ሲሰሙ ነበር ሲሉ ክስተቱን አስረድተዋል።
አለሚቱ በክልሉ የተነሳው ግጭት አሁን ላይ መረጋጋቱን እና የከተማው እንቅስቃሴ ሰላማዊ መሆኑን ተናግረዋል። በከተማው የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ ገልፀዋል።
ግጭቱን ለማረጋጋት እና የከተማውን ሠላም ለመጠበቅ ወደ ክልሉ የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ መግባቱንም አረጋግጠዋል።
አሁንም አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ችግሮች መኖራቸውን ገልፀው በቦታው ሠላም ለማስፈን እየተሠራ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
የጋምቤላ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ትናንት ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል፡፡
ከጸጥታ አካላት ውጪ የጦር መሣሪያ የያዘ ግለሰብ ወይም ቡድን አስፈላጊ ሲል የጠራውን እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡
የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ በታጣቂዎች መገደላቸውን በትናንትናው የዜና ሰዓታችን ወደናንተ ማድረሳችን ይታወሳል።
በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ሰሞኑን ባገረሸው የጸጥታ መደፍረስ ችግር ንጹሐን ሰዎች እና የፓሊስ አባላት መገደላቸው ተገልጿል።
በትናንትና እለት የከተማው ፓሊስ አባላት እንደተገደሉ ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን፣ የክልሉ መንግስትም ድርጊቱ መፈጸሙን አረጋግጧል።
ችግሩ ከዓመት በፊት የነበረ ቢሆንም፣ ከታህሳስ ወር መገቢያ ጀምሮ እንደአዲስ ማገርሸቱን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
የጋምቤላ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ ማበር ኮር የተፈጠረውን አለመረጋጋት በተመለከተ በሰጡት ሀሳብ “ዛሬ የሞተው የፓሊስ አባል ብቻ ነው እንጅ ሌላ የሞተ ሰው የለም” ሲሉ ማስተባበላቸውም ይታወቃል።
ማበር “የተገደለው የጋምቤላ ከተማ ፓሊስ አዛዥ ነው፣ ከቢሮው ውጭ ስራ ሰርቶ ወደቢሮ ሲመለስ ነው ጥቃቱ የተፈጸመው” ካሉ በኋላ ማህበረሰቡ እንዲረጋጋ በየቀበሌው የማረጋጋት ስራ እየሰራን ነው፣ ሁኔታው ወደከፋ ችግር እንዳይሄድ ስጋት ባሉባቸው አካባቢዎች የጸጥታ ኃይሎች በማሰማራት ህዝቡ ወደ ከፍተኛ ግጭት እንዳይገባ ተደርጓል ቢሉም፣ ግጭቱ ዛሬም ድረስ በመቀጠሉ የፌደራል የፀጥታ አካላት እንድሰማሩ አስገድዷል።
የከተማዋ ነዋሪዎች አንዳንድ የፓሊስ አካላት በንጹሐን ግድያ ተሳታፊ የሚሆኑበት እና የፓሊስ አባላት ወደ አንድ ብሔር በማተኮር የግድያ ጥቃት እንደሚፈፅሙ መግለፃቸውን በተመለከተም የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊው “ጥቃቱን አይፈፅሙም ማለት ሊከብድ ይችላል፣ ሁሉም ፓሊሶች ሳይሆን የተወሱት ወንጀል የሚፈጽሙበት ሁኔታዎች አሉ፤ ትክክል ነው” ሲሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
አንዳንድ ፖሊሶች በራሳቸው ችግር ምክንያት በእነዚህ የወንጀል ድርጊቶች የሚሳተፉበት ሁኔታ እንዳለ አስረድተዋል።
ኃላፊው የንፁሃን ሞትን በተመለከተም “በእርግጥ ብዙ ሰው ሞቷል፣ ሁለት መኪናዎች በመንገድ ላይ ጥቃት ደርሶባቸዋል፣ በኢታንግ ልዩ ወረዳ አካባቢም ሁለት ሴቶች ተገድለዋል ሲጠቃለ፣ ግን 10 አይሞላም፣ አንድ ሰው ቢሆንም ሞት ነውና እንደ ትልቅ ነገር መቆጠር አለበት” ብለዋል።
የግጭቱ ምክንያት በሁለት ብሔረሰቦች መካከል ያለ አለመግባባት መሆኑን የተናገሩት ማበር፣ ካሁን ቀደም በተፈጠረው ችግር እርቅ ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው ለዚህም ከዚህ በፊት ስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች ከሀላፊነት ሲነሱና የብሄር መልክ የያዘ ፀብ በመፍጠር ተጠያቂ አድርገዋቸዋል።
የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከህዳር 30/2018 ዓ.ም ጀምሮ የሰዓት እላፊ ገደብ ጥሏል፣ ነገርግን የፀጥታ ሁኔታው ከመሻሻል ይልቅ እየባሰበት መምጣቱን ቦርከና ከአካባቢው ነዋሪዎች ያገኘው መረጃ ይጠቁማል።
…………………………….
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






