
ቦርከና ዜና
16/04/2018
በትናንትናው እለት ብቻ ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና ከ100 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን የአይን እማኞች ለቦርከና ተናግረዋል።
በጋምቤላ ክልል ትናንት ረቡዕ ታህሳስ 15 ቀን 2018 ዓ/ም ከንጋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በተከፈተ ተኩስ ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ባለፉት ሳምንታት በጸጥታ ችግር የንጹሐን ህይወት መቀጠፉን፣ ተጎጅዎች የህክምና አገልግሎት እንዳላገኙ ነዋሪዎች፣ የተጎጂ ቤተሰቦች፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ዛሬ ደግሞ በኢታንግ ልዩ ወረዳ ተርፋም ቀበሌ የበርካታ ሰዎች ህይወት አልፏል ተብሏል።
አዲስ ያገረሸው ግጭት በተለይ ከደቡብ ሱዳን በሚያዋስኑ አካባቢዎች በመከሰቱ ከደቡብ ሱዳን የገቡ ታጣቂዎች በተኩሱ ሲሳተፉ እንደነበር ማየታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልፀዋል።
አስተያየታቸውን ለቦርከና የሰጡ አንድ የዓይን እማኝ በኢታንግ ልዩ ወረዳ በነበረው የተኩስ ልውውጥ ከ40 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ብለዋል።
ከሟቾቹ መካከል እናቶች እና በርካታ ህፃናት እንደሚገኙበት የተናገሩት የአይን እማኙ “በተለይ ከደቡብ ሱዳን በሚያዋስነው ቀበሌ በኩል የተኩስ ሁኔታው ከባድ ነው፣ ሁኔታው አሳሳቢ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም “ከሟቾቹ በተጨማሪ በርካታ ሰዎች በጥይት ተመትነው ቆስለዋል፣ ተሽከርካሪዎች እና የንግድ ሱቆች ወድመዋል፣ የመኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል” በማለት መንግስት የግጭቱን አሳሳቢነት ተረድቶ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
በጋምቤላ ተባብሶ በቀጠለው ግጭት፣ ትናንት ረቡዕ ብቻ ከ100 በላይ የቆሠሉ ሰዎች ሆስፒታል መግባታቸውን ተሰምቷል።
ዓለማቀፉ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን (ኤም ኤስ ኤፍ) ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በግጭቱ ለቆሠሉ ታካሚዎች ኩሌ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ የሕክምና እርዳታ መስጠት በጀመረ በ48 ሰዓት ውስጥ ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሠባቸውን 19 ሰዎች ጨምሮ 50 ቁስለኞችን ማከሙን አስታውቋል። ባለፉት 7 ቀናት ከ150 በላይ ቁስለኞችን መቀበሉን ገልጿል።
ግጭቱ ከጀመረ ወዲህ የበርካቶች ሕይወት መጥፋቱን፣ የአካል ጉዳት መድረሱንና ግጭቱ በዚሁ ከቀጠለ ወደ ሕክምና ጣቢያው የሚገቡ ቁስለኛ ታካሚዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ቡድኑ ጠቁሟል።
ቦርከና ከቡድኑ የደረሰው መግለጫ የጋምቤላ ከተማ ሆስፒታል በቁስለኞች በመብዛታቸው ሳምንቱን ሙሉ የተመላላሽ ሕክምና አገልግሎት ማቆሙንና አንዳንድ የሕክምና አገልግሎቶችም መስተጓጎላቸውን ጠቅሷል።
የሲቪሎች ደኅንነት አሳሳቢ ሁኗል ያለው ቡድኑ ፣ የታካሚዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና የሕክምና ተቋማት ከጥቃት እንዲጠበቁም ጥሪ አቅርቧል።
የክልሉ መንግስት በትላንትናው እለት ስለተቀሰቀሰውና ከፍተኛ ጉዳት ስላደረሰው ግጭት የሰጠው ማብራሪያ የለም። በክልሉ በአኘዋክ እና ኑዌር ብሔረሰቦች መካከል በተለያዩ ጊዚያቶች ግጭት ሲነሳ እንደነበር የሚታወቅ ነው። በሀገር ሽማግሌዎች ጥረት እርቀሰላም ተፈፅሞ ቁሞ የነበረ ቢሆንም፣ ጊዜ እየጠበቀ ማገርሸቱን አልተወም።
የክልሉ ብልጽግና ቢሮ በየጊዜው ለሚከሰቱ ግጭቶች በሀላፊነት የነበሩና ከስልጣን የተነሱ የቀድሞ አመራሮችን ተጠያቂ አድርጓል። ችግሩን በዘላቂነት ለማስቆም እየተሰራ መሆኑን የክልሉ መንግስት በተደጋጋሚ ቢገልፁም ተጨባጭ መፍትሔ ግን አልተገኘም።
ከታህሳስ ወር መግቢያ ጀምሮ ባለው ግጭት ክልሉ ሁለት ጊዜ የሰዓት እላፊ ገደብ ቢጣልበትም ውጤት አላስገኘም።
በጋምቤላ ክልል “የጸጥታ ችግር ይስተዋልባቸዋል” በተባሉ አካባቢዎች ከምሽቱ ሁለት ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉን የክልሉ መንግስት አስታውቋል። በእነዚህ አካባቢዎች ከተፈቀደላቸው የጸጥታ አካላት ውጪ፤ “በየትኛውም ቦታ” የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻልም ክልሉ አስጠንቅቋል።
ከረቡዕ ታህሳስ 15 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን የተነገረው የሰዓት እላፊ ገደብ፤ የክልሉ መንግስት መቀመጫ የሆነችው የጋምቤላ ከተማን እንደሚያካትት የክልሉ መንግስት አመልክቷል። በጋምቤላ ከተማ ከሁለት ሳምንት በፊት የተከሰተውን የጸጥታ አለመረጋጋት ተከትሎ ከህዳር 30 ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሎ እንደነበር ይታወሳል።
ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ በሚደረግ የተሽከርካሪ እና የሰው እንቅስቃሴ ላይ ተጥሎ የነበረው ይኸው ክልከላ፤ የጸጥታ አካላትን እንደማይጨምር በወቅቱ ተገልጾ ነበር። በድጋሚ ይፋ የተደረገው የሰዓት እላፊም በተመሳሳይ መልኩ ለጸጥታ ስራ የተመደቡ ኃይሎችን እንደማይመለከት የክልሉ መንግስት አስታውቋል።
የሰዓት እላፊው ገደቡ የተጣለው በጋምቤላ ክልል “ሰሞኑን በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት” እንደሆነም የክልሉ መንግስት በመግለጫው ጠቅሷል። ገደቡ የጸጥታ ችግር በሚስተዋልባቸዉ የክልሉ አካባቢዎች በሙሉ እንደሚተገበር የክልሉ መንግስት ቢገልጽም፤ ከጋምቤላ ከተማ ውጪ ያሉትን ስፍራዎች የትኞቹ እንደሆኑ መግለጫው በዝርዝር አልጠቀሰም።
…………………………………………..
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






