
ቦርከና ዜና
22/04/2018
በፓርሊማ መደበኛ ስብሰባው ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስም ከሶማሌላንድ ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል ተብሏል።
እስራኤል ለሶማሌላንድ ከሰጠችው የነጻ ሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና በኋላ በትናትናው እለት የመጀመሪያውን ስብሰባ ያደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የደረሰችው የመግባቢያ ስምምነት “የት ደረሰ?” የሚል ጥያቄ ማስነሳቱን ቦርከና ከፓርላማ አባላት የደረሰው መረጃ ያመላክታል።
በመደበኛ ስብሰባው ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ እና ሚኒስትር ዲዔታዎች ናቸው ተብሏል።
ጥያቄውን ካነሱት የፓርላማ አባላት አንዱ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተመራጩ ዶ/ር አበባው ደሳለው፤ የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነት ከተፈረመ ሁለት ዓመት ሊሞላው ቀናት እንደቀሩት በማስታወስ ጥያቂያቸውን አቅርበዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በኤደን ባህረሰላጤ ላይ የ20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ በኪራይ ውል ማግኘት የሚያስችላት እንደነበር አንስተዋል። በምትኩም ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት መካከል የመጀመሪያዋ በመሆን ለሶማሌላንድ የሀገርነት እውቅና ለመስጠት ተስማማታ እንደነበር ገልጸዋል።
ዶ/ር አበባው ኢትዮጵያ “የባሕር በሩን ሳታገኝ እና ለሶማሌላንድ እውቅና ሳትሰጥ” በእስራኤል መቀደሟን በጥያቂያቸው ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ እውቅና በመስጠት “ሁለተኛዋ ሀገር” ትሆን እንደሆነም የፓርላማ አባሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል።
ዶ/ር አበባው አክለውም፤ ሌሎች ሀገራት ከኢትዮጵያ ጎረቤቶች ጋር ስምምነት እያደረጉ መሆኑን የተመለከተ ነበር በማለት “የደህንነታችን ስጋት” ሲሉ የጠሯት ግብፅ ከሶማሊያ፣ ከጅቡቲ እና ከኤርትራ ጋር ያደረገቻቸውን ስምምነቶች በማሳያነት አንስተዋል። ግብፅ “ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት እንዳደረገች እና በቅርቡ ከጅቡቲ ጋር የወደብ ስምምነት መፈራረሟ እየተነገረ ነው” ሲሉ ዶ/ር አበባው አመልክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ባለፈው ጥቅምት ወር ግብፅ እና ኤርትራ “ስለ ባህር ኃይል አጠቃቀም” ስምምነት ላይ እንደደረሱ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መዘገቡን አንስተዋል። ዶክተር አበባው “ታዲያ እኛ ከአንዳቸውም ሀገራት ጋር የተጨበጠ የወደብ መብት ሳናገኝ፣ በሚዲያ ብቻ እያወራን የበይ ተመልካች ሆነን የምንቀጥለው እስከ መቼ ነው?” በማለት ጠይቀዋል።
ሌላኛው ያነሱት ጉዳይ “ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የሄደብንን እና የህልውና ጉዳይ” ያሉትን የአሰብ ወደብ የማስመለስ አጀንዳን ሲሆን፣ የአሰብ ወደብን ለማስመለስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አለማቀፍ ሕጎችን እና ዲፕሎማሲን ተጠቅሞ ስለሰራው ሥራ የፓርላማ አባሉ ማብራሪያ ጠይቀዋል። “በዚህ ጉዳይ በመድከማችን ይመስላል ሀገራችን ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦራቸውን ወደ ድንበር ያስጠጉት እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል የቃላት ጦርነት እየተካሄደ ያለው” ሲሉም ዶ/ር አበባው ተናግረዋል።
ሌላ የፓርላማ አባል በበኩላቸው መንግስት የኢትዮጵያን የባህር በር ፍላጐት ለማሳካት ማን እየሰራ እንደሆነ ጠይቀዋል። አቶ ካሚል ሀሺም የተባሉ የፓርላማ አባል፤ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን ለማሳካት ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟን አስታውሰው፣ ይህን ስምምነት ወደ ተግባር ከመቀየር አንጻር “ምን የተሠራ ሥራ አለ? የወደፊት እጣ ፈንታውስ ምን ሊሆን ይችላል?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ይሁን እንጂ በፓርላማ መደበኛ ስብሰባው ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ከሶማሌላንድ ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ አልሰጡም ተብሏል።
ከፓርላማ አባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ቢቆጠቡም ኢትዮጵያ ከአብዛኛዎቹ ጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት “ጥሩ የሚባል” መሆኑን ተናግረዋል። “አብዛኛዎቹ ጉዳዮች ላይ ተግባብተን በጋራ ነው የምንሰራው” ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል።
በአንዳንድ ሀገራት ውስጥ ያሉ የእርስበርስ ግጭቶች፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጠናው ያሉ ሀገራት እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት ላይ የሚያጠላው ጥላ ስለመኖሩ የጠቀሱት ዶ/ር ጌዲዮን፣ ከግጭቶቹ በተጨማሪም ቀጠናው ኃያላንም ሆኑ በመካከለኛ ረድፍ የሚሰለፉ ብዙ ሀገራት አይናቸውን የጣሉበትና የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የሚሻኮቱበት የመሆኑ ጉዳይ፤ ለአካባቢው ሀገራት ግንኙነት ፈተና መሆኑንም አስረድተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የወደብ እና የባሕር በር ጉዳይን በተመለከተ የውጭ በሰጡት ማብራሪያ፤ “ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ግንኙነት እና ትስስር ስትራቴጂያዊ የሆነ የረጅም ጊዜ ጥቅማችንን እና ትልማችንን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ላሰምርበት እፈልጋለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችው፤ “ለረጅም ጊዜ ታቅዶበት እና ታስቦበት በተሰራ ሴራ” እንደሆነም ጌዲዮን ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል።
ይህንን ሁኔታ ለመቀልበስ እና ለማስተካከል “የረጅም ጊዜ እይታ ያስፈልጋል” ያሉት ዶ/ር ጌዲዮን ነገሩ በአጭር ጊዜ የሚፈታ ጉዳይ አለመሆኑን አመልክተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ፍትሃዊ እና ተገቢ” ያሉት የባሕር በር ጥያቄ፤ “እንዴት እውን መሆን አለበት?” ወደሚለው “ምዕራፍ ተሸጋግረናል” በማለት ከፓርላማ አባላቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
ልክ በዛሬው እለት ከሁለት አመት በፊት ታህሳስ 22/2016 ዓ.ም ነበር ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የወደብ ስምምነት የፈፀሙት። በአዲስ አበባ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት፤ ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ የባህር ወደብን ለማልማት የሚያስችላት እንደሆነ ተገልጾ ነበር።
የመግባቢያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ጠረፍ ላይ የራሷን የጦር ሰፈር እንድትገነባ የሚያስችል መሆኑን በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል። ኢትዮጵያ በምላሹ ራስ ገዝ ለሆነችው ሶማሌላንድ እንደ ሀገር ዕውቅና እንድምትሰጥ በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የቀድሞው የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በወቅቱ ገልጸው ነበር።
በአንድ ዓመት ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የነበረውን ይህን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ፤ ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ እውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ ሀገር ልትሆን እንደምትችል ተገምቶ ነበር። ቀጠናዊና ዓለም አቀፍ ትኩረት ስቦ የነበረው ይህ የመግባቢያ ስምምነት፤ ሶማሌላንድን የግዛቷ አካል አድርጋ የምትቆጥራት ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቃቃር በማድረግ ከፍተኛ የዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።
በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት በቱርክ አሸማጋይነት በአንካራ ከተማ እልባት ካገኘ በኋላ ግን ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ እውቅና የመስጠቷ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል። በአንካራ ከተፈረመው ቃልኪዳን በኋላ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ አስቀድመው የደረሱበት ስምምነት ከምን እንደደረሰ ሳይታወቅ ሁለት አመት አስቆጥሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ታኅሣሥ 17፤ 2018 ዓ.ም እለት እስራኤል ለሶማሌላንድ እውቅና መስጠቷን ያወጀችው። የእስራኤልን እርምጃ ጎረቤት ሀገራት ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ ሲያወግዙት ኢትዮጵያ እና ኬንያ ያሉት ነገር የለም
……………………………………………………..
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






