“በበግ ከሚመራ ሺህ የአንበሳ ሠራዊት ይልቅ ;በአንበሳ የሚመራ አስር የበግ ወታደር ድል ያደርጋል”

ከቴድሮስ ሃይሌ!
የአንበሳ እና የበግ የወታደራዊ አዛዥነት ምሳሌያዊ አባባል ከብዙ ገጽ መጽሃፍና የባለሙያ ትንተና በላይ የአመራር እና የውሳኔ ሰጭነትን ብቃት ማሳያ ይሆናል::
በግ የሚወክለው ባህሪ የዋህነትን አላዋቂነትና በቀላሉ ተታላይ መሆንን ነው:: በበግ የሚመሰል አካል የእራሱን እቅድ የማይከተል የመንጋው ጭብጨባ የሴረኞች ከንቱ ውዳሴ መስመሩን ያስቱታል:: በግ በእፍኝ ለምለም ሳር ተታሎ ወደ መታረጃው እንደሚነዳው ሁሉ ብቃት የሌለው መሪና ቡድን ስሌቱን ሳይሆን ስሜቱን የሚከተል በመሆኑ የጠላቶቹ ሰለባ ይሆናል::
በአንበሳ የሚመሰል አዛዥ እና መሪ ; ውጫዊ ጫጫታ አያስበረግገውም:: ከንቱ ውዳሴ የሚሰማበት ጆሮ : ልቡን ሊያሸንፍ የሚችል ጭብጨባ አይኖርም:: በእራሱ እቅድ ይመራል:: አሸናፊ የሚሆንበትን ስልጠና ብቃት እና ቁመና መፍጠር ላይ ያተኩራል:: ይህን አባባል የሚያጠናክረው የቻይናው የጥንት የጦር ሊቅ እንዲህ ማለቱ ይጠቀሳል:: ጦርነት ጥበብ ነው:: ወታደራዊ አመራር እውቀት ብልህነትና አስተዋይነትን ይጠይቃል:: ለወታደር ስርዐት ማክበር ትዕዛዝን መፈጸም በእቅድን እና መመሪያ መንቀሳቀስ ውስጣዊ አንድነቱን ማጠናከር የእስትንፉሱን ያህል አስፈላጊ ነው ይለናል::
ይህ ምሳሌያዊ አገላለጽ ያለንበትን የሕልውና ትግል እንድንገመግም ማንጸሪ ሃሳብ ይሆናል:: የፉኖ ሁኔታንም በዚህ ውስጥ ማየቱ ምናልባት አስፈላጊ የሚሆንበት ሁኔት ያለ ይመስለኛል:: አሁን ላይ ፉኖ በወታደራዊ ቁመናው አገዛዙን ለመገርሰስ የሚችልበት ሃይል እየሆነ ይገኛል:: የፉኖ የሕልውና ትግል ከተጀመረ ካለፉት ሦስት አመታት ወዲህ የተገኘው ድል : ወታደራዊ ልምድ እና ተቋማዊ ተሞክሮ የሚደነቅ ነው:: ሃገሪቱ ካለችበት ሁኔታ : ሕዝቡ ከገጠመው ከባድ ጫና : ከግዜ አንጻር እና በቀጠናው እየመጣ ያለው የሃይል አሰላለፍ ለውጥ የፉኖ አመራር ቆም ብሎ እንዲያስብ ግድ ይለዋል:: ፋኖ ከባለፉት አመታት በተሻለ ሃይሉን እንዲያቀናጅና የትግሉን አድማስ በጠንካራ መዐከላዊ የፖለቲካ : የዲፕሎማሲ የፕሮፓጋንዳ እና የወታደራዊ ኮማንዱን ጊዜ እና ሁኔታውን በሚመጥን መልኩ እንዲያጠናክር ያስገድዱታል::
በዚህ ወቅት ለአማራ ሕልውና ከፉኖ አደረጃጀት ውጪ ሌላ የጎላ አማራጭ የለም:: ሕዝባችን በርሃብ በኑሮ ውድነት እና በጦርነት የሞት ሸለቆ ውስጥ ወድቋል:: አዝመራው ጦር ሜዳ : ጎጆው የመድፍ ናዳ ; ልጆቹ የድሮን ሰለባ ;ከሆነበት እሰቃቂ ሁኔታ የሚያወጣው የአምላኩ ቸርነት እና የፉኖ ብረት ብቻ መሆኑን አምኖ ባለው አቅም ሁሉ እያገዘ ይገኛል:: ልጆቹን ወደ ግንባር መርቆ እየላከ ሌማቱን ከፍቶ እያጎረሰ : ገንዘቡን እየሰጠ ጠንካራ ደጀን መሆኑን አስምስክሯል:: ይህ ወገንተኝነቱ ከባድ ዋጋም እያስከፈለው ቅዬውን ከጠላቶቹ የሞት ሰይፍ ሊከላከል ግን አልቻለም::
ጨቋኝ አገዛዞችን እንደቀድሞ ዘመን ምዕራባዊያን የሚያወግዙበት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና የዲፕሎማሲ ጫና የሚያሳድሩበት ሁኔታ ዛሬ ላይ የለም:: በየማዕዘናቱ ጦርነት : ሞት : ሽብር እና ሁከት አለም ላይ ነግሷል:: ሰብዐዊ መብት ጥበቃ ተረት : ፍትሃዊነት ቀልድ መሆኑ ታይቷል:: ጉልበት ያለው ይከበራል:: ደካማ ይሰበራል:: የሕግ ልዕልና በጥቅምና ጉልበት ሲለወጥ አይተናል:: ሞራል : መርህ እውነት እና ሉዐላዊነት ለአቅም የለሾች ተረት ሆኗል:: የአዲሱ አለም ስርዐት እያዋለደው ያለው አካሄድ ይሄን መሰል እንዳይሆን ያሰጋል::
በዚህ አለም በተወጠረችበት ሃያላኑ በተፉጠጡበት ወቅት ላይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የሦስተኛው ዓለም ሃገራት ውስጥ ለሚሆን ሰቆቃ የሚሰማ ጆሮ የሚያይ አይን አይኖርም:: አንድ ሚሊዮን ሕዝብ አልቆ በጨፍጫፊዎቹ ላይ የደረሰ አንዳች ነገር የለም:: ዛሬም የአማራው ሰላማዊ ሕዝብ ላይ የሚካሄደው የድሮንና የመድፍ ድብደባ : አስከፊ ሆኗል:: ለአቅመ ዐዳም ያልደረሱ ልጃገረዶች ላይ በወታደሮች የሚፈጸመው አስገዶ መድፈር : የሴቶችን ጡት መቁረጥ የአገዛዙ አራዊትነት ማሳያ ከመሆን አላለፈም:: ለጋ ሕጻናትን በግዴታ እያፈሱ ያለ እድሜያቸው ለማያውቁት ጦርነት በውጊያ ሲማገዱ እያየና እየሰማ ያለው ዓለም ጉዳዬ አላለውም:: በዘር ማጥፉትና በሰው ልጆች ላይ ፍጅት ያነገሰው ሰው በላው የአብይ አህመድ የኦሮሞ/ብልጽግና አገዛዝ አለም ሊያገለው ሲገባ በመካከለኛው ምስራቅ በሰላም አስከባሪነት መጋበዙ ምን ያህል የአለም ፖለቲካ የሞራል ዝቅተት ላይ መውደቁን ይጠቁማል::
ከዚህ አጥፊ ሁኔታ ለመዳን የአማራው ሕዝብ ከእራሱ ልጆች ሌላ ሌላ ምንም አማራጭ የለውም:: ፉኖ ሕዝባዊ ነው:: ሕዝባዊ ነው ስንል ለአስተዳደርና ለቁጥጥር ከፊት መስመር ሆነው የሚታዩት የፉኖ መሪዎች እንደ ሌሎች የትጥቅና የፖለቲካ ድርጅቶች አንቅተውና አስታጥቀው ትግሉን ያቀጣጠሉት ሳይሆን ሕዝቡ ከዳር እስከዳር በእራሱ ተነስቶ የለኮሰው ትግል ነው:: የትግሉ ባለቤት ሕዝቡ ነው:: ስለዚህም የሕዝብ ድምጽ ሊሰማ እና ሊከበር ይገባል:: የአማራው ሕዝብ ጥያቄ የግለሰቦች የስልጣን ድልድልና ሽኩቻ ሳይሆን እንደ አንበሳ ግርማው የሚያስፈራ የፉኖ ድርጅት እንዲመሰረት ነው:: የፉኖ መሪዎች ትግሉን እዚህ በማድረስ ክብርም አድናቆትም ይገባቸዋል:: ሕዝብ ለሕልውናው ሆ ብሎ የጀምረውን ትግል ያላቸውን ልዩነት አቻችለው አንድ የፉኖ ድርጅት እንዲመሰርቱ ዋጋ እየከፈለ በታላቅ ትግዕስት ሲጠባበቅ ቆይቷል:: አሁንም በፉኖ ቡድኖች መካከል ተጀምሯል የተባለውን የአንድነት ንግግር በታላቅ ጉጉት እየጠበቀው ይገኛል::
የትግሉ ባለቤት የሆነው መላው የአማራ ሕዝብ በተበታተነ አደረጃጀት እና በቁጥቁጥ ድል ከገጠመው መከራ ሊድን አልቻለም:: የአማራው ሕዝብ የጎበዝ አለቆችን ሳይሆን የሚፈልገው ዘመን ተሻጋሪ የትግል ተቋም እንዲመሰረትለት ነው:: ተቋም ከግለሰቦችም ከቡድኖችም በላይ ነው:: የዛሬዋ ታላቋ አሜሪካ ጸንታና ገናና ሆና ምዕተአመታት የተሻገረችው ከግል ኢጉ እና ጥቅም በላይ ትውልዱንና ሕዝባቸውን የማስቀደም ሞራል እና ስብዕና ባላቸው መሪዎች ነው:: የፉኖ መሪዎች አለን የሚሉትን ውሃ የማይቋጥር ልዩነት ትተው ከግል ፍላጎትና ስሜት ወጥተው ለአማራው ሕዝብ ሕይወታቸውን በጦር ሜዳ ከሚሰውለት በላይ ውለታ የሚውሉለት ጠንካራ እና የተማከለ የትግል ተቋም ሲመሰርቱለት ነው:: በጠንካራ ተቋም የሚመራ ትግል ሕዝብን በፍጥነት እና በስፉት አንቀስቅሶ ለድል ሲያበቃ መሪዎቹን ከጫካ አውጥቶ በሃገር አመራር ላይ የሚያስቀምጥ እድልም እንደሚሰጥ መገንዘብም ያስፈልጋል::
በቅርቡ እየሰማንው እንዳለው ከሆነ አስማሚዎች ባሉበት በፉኖ ሃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ውይይት በሰፊ መግባባት ላይ እንዳለ ይነገራል::ይህን ቅዱስ አላማ ሕዝባችን በታላቅ ጉጉት እየጠበቀው ይገኛል:: በታላቁ የሕይወት መጽሃፍ “እርስ በእርሷ የምትለያይ መንግስት አትጸናም” (ማቴ 15:25) ተብሎ እንደተነገረው በአንድ ታላቅ የ50 ሚሊዮን ሕዝብ ሕልውና ላይ ተነጣጥሎ የሚደረግ ትግል መቼም ቢሆን ለውጤት አይበቃም:: ፋኖ በሚያደርገው ፍልሚያ ለማሸነፍ ብቻ አይደለም ቢሸነፍ እንኳ እንደ አንድ አማራዊ ሃይል እንደገና አቧራውን አራግፎ መልሶ ማሸነፍ የሚያስችል አቅም የሚኖረው አንድ አማራዊ ድርጅት ከሆነ ብቻ ነው:: ስለዚህም የወንድሞቻችንን የአንድነት ጉባዔ የተሳካ እንዲሆን መላው ሕዝባችን በጸሎትም በሃሳብም በሚችለው እና በማንኛውም መንገድ ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል::
ሌላው በትኩረት ሕዝባችን ሊከታተለው የሚገባ ጉዳይ የፉኖ አንድነት ሊያመጣ የሚችለው አቅምና ተጽዕኖ የአብይ አህመድ ሰው በላ አገዛዝ እንቅልፍ ነስቶታል:: ይህንን በሁለቱ የፉኖ ሃይሎች መካከል ያለን ንግግር እንዳይሳካ ቅጥረኛ ሰርጎ ገቦችን ከትግሉ ሜዳ እስከ ዲያስፖራ አሰማርቷል:: አንዳንድ በውጪ የፉኖ ተወካይ ነን ከሚሉ ምሁራንና በየተቋማቱ የተሰገሰጉ የቁስ ሰቀቀንና የገንዘብ ጥማት ያላቸውን ቅጥረኞች በታሪክ እና በፖለቲካ ትንተና ስም መርገምታዊ የመከፉፈል ስምሪት ወስደዋል:: ሌላው የአማራው ሕዝብ ስቃይና መከራ ለእነሱ የደም እንጀራ ያደረጉ ሚድያዎች ናቸው:: ከፍተኛ ሃሜትን አሉባልታንና ከብልጽግና በቀጥታም በተዘዋዋሪም አስተላላፊነት የተጠለፈ የስልክ ንግግር እና በረቂቅ የእስማርት ቴክኖሎጂ የተቀናበሩ መረጃዎችን በማሰራጨት የፉኖን አንድነት ለማጨናገፍ ከአገዛዙ በላይ ተግተው እየሰሩ ይገኛሉ:: በተለያየ ቀጠና ያሉ የፉኖ መሪዎችን ስም በማጥፉት እና በማወደስ ጎራ የለዩ እና ጠበኛ የመሰሉ ነገርግን አስመሳይ የጠላት እርኩስ ፍላጎት አስፈጻሚዎች ናቸው::እነዚህ ግለሰቦችና የሚዲያ ተቋማት እነማን ናቸው? ለሚል ቅን የሆነ አማራ እነማን? እንደሆኑ ከየእለቱ አጀንዳና የመወያያ እርዕሳቸውን ይመልከት:: የሚያራምዱት አቋም ለፉኖ አንድነት ወይስ ለመለያየት ይጠቅማል የሚለውን ሰምቶ አድማጩ የእራሱን ግንዛቤ እንዲዝ እጠቁማለሁ::
“እንዶድ በየዋህነቷ ውሃ ወሰዳት” አበው እንዲሉ የአማራው ሕዝብ በብዙ ሸፍጠኞች ሲታለልና ሲዘረፍ ኖሯል:: በኢትዮጵያዊነት ስም ሕይወቱንም ገንዘቡንም ተቀምቷል:: በአማራነት ስም የማንም ቦዘኔ ባልቴትና የፖለቲካ ነጋዴ ኢጎ መወጣጫ እና ችጋር ማራገፊያ ሆኗል:: ትላንት አብን የሚባል ድርጅት የአማራ ተስፉ ነኝ ብሎ ተስፉውን እንደበላው አይተናል::ጥቂቶች የሕዝብን ትግል ሸጠው በትውልዱ ሞራል እና ሕልም ላይ የቁስ ሰቀቀናቸውን እና የስልጣን ፍላጎታቸውን አሳክተዋል:: አማራው ይሄ ሁሉ ሰምቶና አይቶ የመከተል የዋህነቱ ሕልውናውን ከመጥበሻው ወደ እሳቱ ከማባባሱ ውጪ ምንም ያስገኘልት ትርፍ የለም:: ዛሬም በሚድያና በተንትኝ ስም የሚራወጠውን የደም ነጋዴ ሴራ በጥንቃቄ ልንከታተለው ይገባል:: አማራ ዛሬም እንደ አይን አንድ የቀረው የሕልውና መዳኛ የሆነው ፉኖ ከተነጣጠለ አካሄዱ ወጥቶ በአንድ ጥላ ስር እንዲሰባሰብ ዘመን ተሻጋሪ እና ድሉን አቅራቢ ተቋም እንዲመሰርት ሕዝባችን ግፊት ሊያደርግ ይገባል::
በመጨረሻም ፉኖ እስካሁን በመጣበት ያልተማከለ አካሄድ ይዘልቃል ወይ? ለሚለው በግሌ አይመስለኝም:: ብዙሃኑ በሃገር ቤት ያለውም በውጪ የሚገኘውም በፉኖዎች መለያየት ተስፉ ቆርጧል:: ጎበዞቹ የለንደን ፉኖዎች በቅርቡ ያስተላለፉት ጠንካራ መልዕክት የዚህ ሃሳብ ማሳያ ነው:: ፋኖ እንደ አንበሳ ጠላቱን የሚያደቅ ሠራዊት ገንብቷል:: የአንበሶቹ ጥንካሬ ወረዳ እና ቀበሌ ነጻ በማውጣት የተገደበው አቅም አጥተው ሳይሆን አመራሩ እንደ አንበሳ መሆን ባለመቻሉ ነው:: አንበሳ እንዳይሆን ያደረገው በኢጎ ያበጠ መሪ መኖሩ ግለሰብ ከተቋም መብለጡ ለአሉባልታ እና ለሴራ ተጋላጭ የመሆን አዝማሚያ መኖር ነው:: በዚህም አንድ የጋራ ኮማንድና ወጥ ድርጅት ማዋለድ ሳይችል ቆይቷል:: በዚህም ፉኖ ብዙ እድሎች አባክኗል:: በእርግጥ የፉኖ አንድነት ምን ትርጉም ይኖረዋል:: የአንድነቱስ ፍሬ እና ውጤቱ ምን ይመስላል:: የፉኖ አንድ አለመሆንስ ምን ያስከትላል:: ይጠቅማል ወይስ ይጎዳል? በእኔ እምነት ብዙዎችም ይጋሩታል ብዬ አምናለሁ ከታች በተቀመጠው የቢሆነኝ (Scenario) መልክ ተመልክቼዋለሁ::
ለአማራው ሕዝብ የሕልውና ዋስትና ለቀጠናው ሕዝብ አለኝታ ሆኖ የሚታየው የፉኖ አንድ መሆን የሚያስገኘው ጥቅም!
- የደጀኑን ሕዝብ ለበለጠ ትግል ያነሳሳል:: ድጋፍን በይበልጥ እንዲጠናከር ያግዘዋል::
- የሰራዊቱን ሞራል ያጠናክራል የውጊያ አቅሙን ይጨምራል::
- ፉኖ በቀጠናው ያለውን ተጽዕኖ ከፍ ይላል::
- የዘመቻ አቅሙን የውጊያ አድማሱን ለማቀናጀት እካሁን ካለው የቁጥቁጥ ድል ወጥቶ ሰፉፊ ቀጠናዎችን ለመቆጣጠር የሚችልበት አቅም ይፈጥራል::
- ነጻ በሚያወጣቸው ቀጠናዎች ስርዐት ያለው የሕዝብ አስተዳደር ለመዘርጋት እድል ያገኛል::
- ወጥ የትርክት የፖለቲካ ፍኖት የእራሱ ቃል አቀባይ እና የሚድያ ልሳን አቋቁሞ ለሕዝቡ ተደራሽ ይሆናል::
- በዲፕሎማሲው አለም ቅቡልነት እንዲኖረው ያግዛል::
- በመላው አለም ያለውን ደጋፊ በአንድ ጥላ ስር አደራጅቶ በድጋፍ ማሰባሰብ በዲፕሎማሲ እና በሎጀስቲክ አቅርቦት ውጤታም የሚሆንበትን መንገድ ይጠርጋል::
የፉኖ በጋራ አለመቆም የሚያስከለው አደጋ!?
- ትግሉ ይራዘማል አለያም ይቀለበሳል::
- ሕዝቡ በፉኖ ላይ ተስፉ ቆርጦ ድጋፉን ይቀንሳል::
- የእርስ በእርስ የመዋጋት በር ይከፍታል:: በዚህም ክፍተት አገዛዙ ተጠቅሞ ፉኖን ከሕዝብ ይነጥላል:: በእርስ በርስ ውጊያ የተዳከመውን ጨርሶ የመደምሰስ እድል ይሰጠዋል::
- የፉኖ ተዋጊ ሞራል ይጎዳል:: በዚህም ከትግሉ የሚሸሽ አለያም ወደ አገዛዙ እጅ የሚሰጥበት ሁኔታ ይፈጠራል::
- የፉኖ ሕዝባዊ ተቀባይነቱን ሊያሳጣው ይችላል:: ይዞ የተነሳው ሕዝባዊ አላማ ለጠለፉ ይጋለጣል::
- የፉኖ አንድ አለመሆን በችርቻሮ ለጥቅማቸው ለሚፈልጉት ሃይሎች ጥገኛ ያደርገዋል::
- ሰራዊቱ ወደ ስርዐት አልበኝነት አመራሩም ወደ ቅጥረኝነት ወርዶ የጎበዝ አለቆች ፍላጎት ማስፈጸሚ የመሆን እድል ሊገጥመው ይችላል::
- አገዛዙ የተሻለ ቅቡልነት በሃገርም በዲፕሎማሲውም የማግኘት እድል ይሰጠዋል::
- ኦህዴድ/ብልጽፅግና እንደ ዩናይትድ አረብ በመሰሉ ጌቶቹ እገዛ ምዕራባውያን ፉኖን በሽብርተኝነት እንዲፈርጁት ሎቢ ያደርጋል::
ድል ለሕዝባችን! ድል ለፉኖ!
ኢትዮጵይን እግዚአብሄር ይባርክልን!!!
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena







አስተያየቱ መልካም ነው! ርዕሰ ጉዳዩ ግን “ፋኖ እንዳትሰባበር ተባበር” ከሚል “እንዳትሰባበርና እንዳንሰባበር ተባበር/እንተባበር ” ቢሆን መነሳቱም ሆነ ውድቀቱ የጋራችን መሆኑን ይበልጥ የማሳየት ሃይል ይኖረው ነበር። እንደ ተደራጀና በፍልሚያ ላይ እንደተሰማራ ሃይል ለፋኖ ሂሳዊና ገንቢ ሃሳብን መስጠት ትክክለኝነቱና አስፈላጊነቱ ባያጠያይቅም ስኬቱም ሆነ ውድቀቱ እንደ ግለሰብም፣ እንደማህበረሰብም ወይም እንደ ህዝብም የእኛው በመሆኑ አስተያየታችንም ይህንኑ መሠረት ያደረገ ቢሆን መልካም ነው።