Homeነፃ አስተያየትየአማራ መከራ፣የኢትዮጵያ ፈተና 

የአማራ መከራ፣የኢትዮጵያ ፈተና 

Advertisement
World Wide Travel Group
የአማራ መከራ _ ኤ ኤፍ ፒ
ኤ ኤፍ ፒ

ጥሩነህ ግርማ

1. የመከፋፈል ንድፍ፡ ከ1896 እስከ 1991

የኢትዮጵያ ፈተናና የአማራ መከራ በአጋጣሚ የመጡ ሳይሆኑ፣ ሆን ተብሎ አገራዊ አንድነትን ለመናድ በተቀረጹ ስልቶች የመጡ ናቸው።

  • ከአድዋ በኋላ የተጠነሰሰ ሴራ፡ በ1896 ዓ.ም የኢትዮጵያ ድል የጥቁር ህዝቦች የአንድነት ተምሳሌት ነበር። በ1928 ዓ.ም ፋሺስት ጣሊያን ዳግም ሲወርር፣ በጦር መሳሪያ ብቻ ማሸነፍ እንደማይችል ስለተረዳ ከፋፍለህ ግዛው የሚለውን ስልት ተጠቀመ። ፋሺስቶች አገሪቱን በዘር በመከፋፈል፣ ማዕከላዊውን መንግስት እንደ “አማራ ወራሪ” በመሳል በህዝቦች መካከል የጥል ዘር ዘሩ። የኦርቶዶክስ ሃይማኖትንም ማጥፋት ካልተቻለም ማዳከም አንዱ ኢትዮጵያን የማዳከምና የመያዝ እቅዱ ነበር። የሃይማኖቱ ተከታዮች ያላቸውን ጽኑ እምነትና ለሃገራቸው ህይውታቸውን ሳይሳሱ  እንደሚሰጡ ፋሽስቶትች ከታሪክ ተምረዋል። በአጼ ሲሶኒወስ የግዛት ዘመን ካቶሊኮች የሮምን እምነት ካልተከተላችሁ ብለው በንጉሱ ፈቃድ ያደርጉትን ሙከራና አማኙ የወሰደውን ቆራጥ እርምጃ ጣሊያኖች ያውቁታል። ለሃይማኖታቸውና ለሃገራቸው ሲሉ በገደል እየተውረውሩ ያለቁትን መነኮሳት ጣሊያኖች አይረሱትም። 
  • የህወሃት ዘመን (1983–2010): ህወሃት ስልጣን ሲይዝ የፋሺስቱን የዘር ካርታ ወደ 1987ቱ ህገመንግስት ቀየረው። የብሄር ፌደራሊዝምን በማወጅ በደም ላይ የተመሰረተ ድንበር አበጀ። ይህ ስርዓት ጎረቤት እንደ ጠላት እንዲተያይ በማድረግ፣ “መሬቱ የኔ ነው” በሚል ለዘር ማጽዳት ህጋዊ ሽፋን ሰጠ። የበደኖ፣ የአርባጉጉና መስል እልቂቶች የዚህ ሴራ ውጤት ናቸው። ህወሃት በአማራና በኦርቶዶክስ  በጥላቻ ተወጥሮ ጣሊያኖች ሊያሳኩት ያልቻሉትን ለማስፈጸም ችሏል። የአማራንና የኦርቶዶክስን አከርካሪ ሰብረናል እስከማለት የደረስ ሃገረ ጠለ ሃገር አፍራሽ ድርጅት መሆኑን አሳይቷል። ገና ስልጣን ከመያዙ በፊት በራያና በወልቃይት አማራን ገድሏል አሳዷል: የመሬት ወረራውን እውን ለማድረግ አማራውን የማፅዳት ግፍ በገፍ ፈፅሟል:: ታሪካዊ ቦታዎችን ስም እያነሳ ሌላ የትግራት ስም ሰጥቷቸዋል: ህወሃት የሰበዓዊም የባህልም ፍጅትና ማፅዳት (cultural genocide) ነው ያደረገው: ህወሃት በስግብግብ ፍላጎቱ የአማራን ጥንታዊ እርስቶች ከትግራይ ጋር ካካለለ በሁዋላ አማራን ማዳከሙ በዚህ እንዳያበቃ ለሌሎች ክሎችም እየሸነሸነ አከፋፍሏል:: በመጨረሻዋ ሰዓት ተሸንፎ በሚሸሽበት ወቅት የአማራ ጥላቻው ያንተከትከው ስለነበረ ማይካድራ ላይ በቀን ስራ በተሰማሩ አማሮች  ላይ ያደረሰው ዘግናኝ እልቂት ምን ጊዜም አይረሳም: ምንም አይነት የፓለቲካ ተሳትፎ ያልነበራቸውን ፍፁም ንፁሃንን ለመጨፍጨፍ ምንም ሃይማኖታዊም ሰብዓዊም ስሜት አላገደውም::

ይህን አሰቃቂ እልቂት የፈፀሙት የህወሃት ወታደሮች ዛሬም በሱዳንና በትግራይ እንቅልፍ ተኝተው ያድራሉ::እንዲያውም ተጨማሪ ደም ለማፍሰስ እየቋመጡ ነው: የህሊና ፀፀት በህወሃት በኩል አይታሰብም::

2. የአሁኑ አገዛዝ እና የሰብአዊ ቀውሱ 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

የብልፅግና አገዛዝ ይህንኑ የመከፋፈል መንገድ በማፋጠኑ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች አገሪቱ ወደ መፈራረስ እየተቃረበች ነው። ክህወሃት የተቀበለውን የሰዎች ግድያ ወደ ሙሉ ዘር ፍጅት(Genocide) አሸጋግሮታል። 

  • በአማራ እና በኦሮሚያ ያለው ጦርነት፡ እስከ አሁን  2018 (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2026) ድረስ የፌደራል መንግስቱ ከአማራ እና ከኦሮሞ ነጻነት ድርጅት (OLF) ጋር በጦርነት ላይ ይገኛል። ይህ ጦርነት በገበያዎች፣ በሆስፒታሎችና በትምህርት ቤቶች ላይ የሚደረጉ የድሮን ጥቃቶችን ጨምሮ፣ የአገሪቱን ለም መሬቶች ወደ መቃብርነት ቀይሯቸዋል። ህዝቡን በረሃብ ለመቅጣት ካለው ፍላጎት በመሬት ላይ ያለውንም ሆነ የተሰበሰበውን እህል አቃጥሏል/ ያቃጥላል፣ ይህ ሁሉ ሲህን የሃገሪቱ የግዛት አንድነት እየተቆረሰ በሰሜንም በደቡብም ሱዳን እንደተወሰደ ነው:  የኢትዮዽያ መከላከያ ሃይል እንደሌላት ይልቁንም የአብይ አህመድ ዘበኛ የስልጣን ማቆያ ጅራፉ እንደሆነ በግልፅ እየታየ ነው:: በራሱ ንፁሃን ወገኑ ላይ እልቂት የሚፈፅም በጥላቻ ስለተሰበከ እንጂ ከቆሎ ተማሪ እስከ ህፃናትና ሽማግሌዎች የሚያስጨፈጭፍ ሌላ ምክንያት የለም:: የኦሮሞ ጀኔራሎች ክጥቂት የአብይ አማሮች ጋር ሆነው እየፈጸሙት ያለው ተነግሮ የማያልቅ ግፍ ሃገራችንን ወደ መፍረስ አቅርበዋታል። አልፈረሰችም ካልን!
  • በወለጋ እና በአርሲ የሚፈጸም የዘር ማጽዳት፡ መንግስት ዜጎችን የመጠበቅ ሳይሆን የልቂቱ ተሳታፊ በመሆን  በምዕራብ ወለጋ እና በአርሲ በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች እና ሌሎች አናሳ ቡድኖች በቀን ብርሃን ታርደዋል። በሕይወት የተረፉት ምስክሮች እንደ “ኮሬ ነጌኛ” ያሉ የደህንነት ኮሚቴዎች ያለ ምንም ተጠያቂነት ግድያውን እንደሚያስተባብሩ ይናገራሉ። ከግድያ ያመለጡት በስደት ላይ በየካምፑ በረሃብ እያለቁ ነው። እልቂቱ በእቅድና ከህዝብ በሚዘረፍ ገንዘብ የሚፈፀም ነው: ኦሮሚያን ለማዋለድ የተጠነሰሰው ወደሙሉ ትግበራ እየተሸጋገረ ነው: አዲስ አበባን አነሰም በዛም ተቆጣጥረውታል: በኦሮሚያ ክልል ያሉትንም አማሮች ማፅዳቱን አጠናክረው ተያይዘውታል:: የመስፋፋት አባዜው ከሱማሊም ከጋምቤላም ጋር እያላተመው ነው። 
  • በኦርቶዶክስ እምነት ላይ የሚደረግ ስደት፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአንድነት ምልክት በመሆኗ የጥቃት ሰለባ ሆናለች። በዝቋላ ገዳም እና በሌሎች ስፍራዎች መነኮሳትና ምእመናን ተገድለዋል። ቤተክርስቲያኗን በማዳከም አገሪቱን የሚያስተሳስረውን ባህላዊና መንፈሳዊ ማገር ለመስበር እየተሰራ ነው። በቅርቡ በአርሲ የተገደሉትና በመገደል ላይ ያሉት ክርስቲያኖች ያው አማራንና ኦርቶዶክስ እምነትን ለማጥፋት ከጣሊያኖች ከዚያም ከህወሃት የወረደውን ወደግቡ የማድረስ ዘመቻ ነው:: 

በሌላ በኩል እስልምና እምነት ተከታዮችንና ክርስቲያኖችን ለመጋጨት የአብይ አሸባሪ ስብስብ  ያልሄደበት ጎዳና የለም። የህዝቡ ጥንካሬ ባይሆን ኖሮ እነአብይ ግባቸውን ያሳኩት ነበር: 

3. የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እና የኢኮኖሚ ውድቀት

የኢትዮጵያ ውስጣዊ ጦርነት በውጭ ኃይሎች ፍላጎት እየታገዘ ይገኛል፦

- Advertisement -
Advertise here _ borkena
  • የድሮን ቴክኖሎጂ፡ ከቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኢራን የሚመጡ ድሮኖች መንግስት በገዛ ህዝቡ ላይ  ከፍተኛ የሲቪል እልቂት እንዲፈጽም ረድተውታል። በመሬት ያለውን ጦርነት ሊቋቋመው ባለመቻሉ ድሮን እንደነፍስ  ወከፍ መሳሪያ እየሆነ ነው። እድሜአቸው ያልደረሰ ወጣቶችን በማፈስና በመማገድ ያመጣው ለውጥ የለም ግን አሁንም ከዚህ አረመኔያዊ ተግባሩ አልተመለሰም። ብልጽግና በጠንቋዮቹና ትንቢት ተናጋሪዎቹ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ አውጥቶ ህዝብ በረሃብም በጦርነትም እየፈጀ ነው።   
  • የኢኮኖሚ መላሸቅ፡ ጦርነቱ የሚመራው የብርን ዋጋ ዝቅ በማድረግ (Devaluation) ነው። የኢትዮጵያ ብር ከ100% በላይ ዋጋውን በማጣቱ ምግብ የማይቀመስ ሆኗል። እስከ 2027 ድረስ የሚጠበቀው 125 ቢሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ኪሳራ አገሪቱን ወደ ረሃብና ጽኑ ድህነት እየመለሳት ነው። ለነአብይ ማጣት ማግኘት፣ መራብ ጠግቦ ማደር፣ ጦርነት ሰላም ነውና ይህ ሁሉ የሚያሳስባቸው አይደልም። የብልፅግና ጎስፕል ይኸው ነው::

በዝርዝር ስናየው።

1. የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት (Inflation)

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ካለባቸው አገራት አንዷ ሆናለች።

  • የምግብ ዋጋ ንረት፦ የምግብ ዋጋ ንረት ባለፉት ዓመታት ከ 30%እስከ 40% ባለው ክልል ውስጥ ቆይቷል። ይህ ማለት አንድ ተራ ዜጋ በቀን የሚበላውን ምግብ ለመግዛት ያለው አቅም በየወሩ እየቀነሰ መጥቷል ማለት ነው።
  • የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ፦ እንደ ዘይት፣ ስኳር እና ዱቄት ያሉ መሠረታዊ ቁሶች ዋጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሦስት እና በአራት እጥፍ ጨምሯል።ብዙውኡች ከዚያ በላይ ነው ይላሉ:: ይህ ሸቀጦችም ከተገኙ ነው::

2. የብር ዋጋ መውደቅ (Currency Devaluation)

- Advertisement -

መንግስት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት (IMF/World Bank) ብድር ለማግኘት ሲል የብርን ዋጋ በገበያ እንዲወሰን ማድረጉ (Floating the Currency) ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ህዝብ ክፉኛ ጎድቷል። ጎድቷል ብቻ አይደለም የመግዛት አቅሙን አዳክሞ ህዝቡን ለክፉ ረሃብ ዳርጎታል። 

  • የብር ዋጋ መውደቅ፦ የአሜሪካ ዶላር በባንክ ያለው ምንዛሬ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ57 ብር ወደ 120 ብር በላይ ከፍ ብሏል። እስከ 180 ብር ደርሷል ይባላል። 

በጠቃላይ ኢትዮጵያ አብዛኛውን የኢንዱስትሪና የፍጆታ ዕቃ ከውጭ የምታስገባ በመሆኑ፣ የብር ዋጋ መውደቅ በቀጥታ የሁሉም ዕቃዎች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል።

3. የጦርነት ወጪና የልማት በጀት መቀነስ

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚካሄደው ጦርነት የአገሪቱን ሀብት ለጥፋት እንዲውል እያደረገ ነው። የመከላከያ በጀት፦ መንግስት ለጦርነትና ለድሮን ግዢ የሚያወጣው በጀት ከትምህርትና ከጤና በጀት እጅግ በልጦ ይገኛል። ለምሳሌ ለጦርነት የሚወጣው ወጪ ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት (GDP) ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። ለመሰረታዊ ልማት የሚሆን ባጀት አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን የነበሩትንም ልማቶች፣ እንደትምህርትቤት፣ ክሊኒክ ያሉትን ሆነ ብሎ ያፈርሳል፣ ያቃጥላል። 

በጥቅሉ በብድርም በዝርፊያም ጦርነቱን እንደሚቀጥል ግልፅ ነው: ይህም የአንድ ሰውን የስልጣን ጥማት ለማርካት ሲባል ነው:

  • የኢኮኖሚ ኪሳራ፦ በጦርነቱ ምክንያት በየዓመቱ በአማካይ ከ2 እስከ 3 ቢሊዮን ዶአር የሚገመት የኢኮኖሚ ኪሳራ ይደርሳል። ይህ ገንዘብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከድህነት ለማውጣት ይውል የነበረ ነው። ነገር ግን የኢቫንጅሊካኑ ቀሳውስት ድህነትን መቀበል ሳይሆን ስሙን መጥራት ውድቀት ነው ብሎ ስልሚያምን በየቀኑ ብልፅግና በልፅገናል ኢትዮዽያ በአየር ላይ ተንሳፋለች እያሉ ህዝቡን ይሰድቡታል በረሃቡ ላይ ይሳለቁበታል::

4. የውጭ ዕዳ ጫና እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት

ኢትዮጵያ የውጭ ዕዳዋን መክፈል ተስኗት “Default” ወደማድረግ ደረጃ ደርሳለች።

  • የዕዳ መጠን፦ አገሪቱ ከ 28 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ዕዳ አለባት።
  • የውጭ ምንዛሬ እጥረት፦ መድኃኒት፣ ማዳበሪያና ነዳጅ ለማስገባት የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሬ በመጥፋቱ፣ አርሶ አደሩ ማዳበሪያ አጥቶ ምርት ቀንሷል፣ ታካሚዎች መድኃኒት አጥተው ለሞት እየተዳረጉ ነው።

5. ድህነት እና ስራ አጥነት

  • የድህነት መጠን፦ በጦርነትና በኢኮኖሚ ውድቀት ምክንያት “በከፋ ድህነት” (Extreme Poverty) ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
  • መፈናቀል፦ ከ 3.4 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ከመኖሪያው ተፈናቅሎ ምርታማ መሆን ባለመቻሉ፣ አገሪቱ በቢሊዮን የሚቆጠር የሰው ኃይል ምርት አጥታለች።

*** የሃገሪቱ የማምረት አቅም እያሽቆለቆለ መሆኑን ልብ ይሏል: የግብርና ውጤት ጦርነት ሜዳ ላይ ማሰብ አይቻልም: በአማራ ግዛት ውስጥ በግል የሚታየው እራስን ለመከላከል የሚደረግ ጦርነት እንጂ ምርት ላይ ትኩረት የለም: ቢመረትም ብልፅግና ያቃጥለዋል፣ ቡቃያውን ያዳሽቀዋል:: ርሃብ ሩቅ አይደለም:: 

በዲፕሎማሲው ዘርፍ የታዩትን ዋና ዋና ኪሳራዎች በሚከተለው መልኩ ማጠቃለል ይቻላል፦

1. የአካባቢያዊ ተሰሚነት መዳከም እና ከጎረቤቶች ጋር መላተም

  • ከሱዳን ጋር ያለው ግንኙነት፦ በአብይ የሱዳን የርስበርስ ግጭት ጣልቃ ገብነትና በህዳሴው ግድብ ምክንያት የነበረው ውጥረት ተባብሶ፣ ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት እስከመያዝ ደርሳለች። ይህ ቀደም ሲል የነበረውን የጎረቤትነት ዲፕሎማሲ ወደ ጠላትነት ቀይሮታል። ደቡብ ሱዳንም የተቻላትን ያህል ከኢትዮጵያ መሬት ምንችፋ በስሯ አድጋለች።
  • የሶማሊያ ውጥረት፦ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ (MoU) ከሶማሊያ መንግስት ጋር ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ከትቷል። ይህም ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ባላጋራዎች (እንደ ግብፅ ያሉ) ጋር ወታደራዊ ስምምነት እንድታደርግ በር ከፍቷል። ዘሎ በፉከራ የገበባት የሱማሊላንድ ስምምነት በይፋ ሳይናገር ሾከክ ብሎ ቢወጣም ኪሳራውን አላስቀረም።
  • የቀጠናው የሰላም ባለአደራነት ማጣት፦ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በደቡብ ሱዳን እና በሶማሊያ የሰላም አስከባሪና አጋሪ በመሆን የነበራትን የዲፕሎማሲ የበላይነት አጥታለች። ከየቦታው ውጭ እየተባለች  አብይ ውርደት አከናንቧታል

2. የዓለም አቀፍ ተቋማት እና የኃያላን አገራት ጫና

  • የአሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ማዕቀቦች፦ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና የዘር ፍጅት (Genocide) ስጋቶች ምክንያት፣ ኢትዮጵያ ከ AGOA የንግድ ዕድል ተሰርዛለች። የልማት እርዳታዎችም ተቋርጠዋል ወይም ተቀንሰዋል።
  • የተባበሩት መንግስታት (UN) ሪፖርቶች፦ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርቶች አገሪቱን ለከፋ ወቀሳና የዲፕሎማሲ ጫና ዳርገዋታል። ይህም አገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ እንደ ወንጀለኛ እንድትታይ አድርጓታል።ናትም:: ቢሆንም የዚህ ክብር ለኢትዮዽያ ሳይሆን ለአብይ ነው

3. ለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በር መክፈት

  • የሉዓላዊነት ስጋት፦ አገሪቱ የውስጥ ችግሯን በውይይት መፍታት ባለመቻሏ፣ እንደ ቱርክ፣ ኢሚሬትስና ኢራን ያሉ አገራት የድሮንና የጦር መሳሪያ ሽያጭን ተገን በማድረግ በኢትዮጵያ የውስጥ ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ ዕድል ሰጥቷቸዋል። በተለይ ኢምሬትስ የኢትዮጵያን ዕጣ ፋንታ ወሳኝ ከሆነች አመታት ተቆጥረዋል::
  • የግብፅ ተፅዕኖ መስፋፋት፦ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር መጋጨቷ ግብፅ በቀጠናው ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት እንድታጠናክርና ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው ረገድ እንድታዳክም  ማገዣ ሆኗታል። ለዚህ ነው ሆኖ የማያውቀውን የግብጽ ወታደሮች ሶማሊያ ውስጥ በመግባት እያስፈራራች ያለችው:: 

4. የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነት ስጋት

  • አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እና የህብረቱ መቀመጫ ብትሆንም፣ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ጦርነትና የደህንነት ስጋት ሌሎች አገራት ስብሰባዎችን ወደ ሌላ ቦታ ለማዛወር እንዲያስቡና የኢትዮጵያን አስተማማኝነት ጥያቄ ውስጥ እንዲከቱ አድርጓል።

ባጭሩ ይህ የዲፕሎማሲ ኪሳራ አገሪቱን በኢኮኖሚ እንድትታነቅ፣ በፖለቲካ እንድትገለል እና ለውጭ ወረራ እንድትጋለጥ አድርጓታል። ከታሪካዊቷ የነፃነትና የአንድነት ተምሳሌትነት ወደ የቀጠናው ስጋት መቀየሯ የዚህ አገዛዝ ትልቁ ውድቀት ነው። ትልቁ አነጋጋሪው ነጥብ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አብይ ካለው ፍላጎት ነው ወይንስ የእውቀትና  የአቅም እጥረት? የሚለው ነው። በዚህ ሁለት አስተሳሰቦች እንዳሉ ይታወቃል። አንደኛው አብይ ባለመቻሉ እንጂ የኢትዮጵያን ውድቀት አይመኝም የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ከጅምሩም የነበረው እቅድ ኢትዮጵያን አፍርሶ ኦሮሚያን ማዋለድ ነው የሚሉት ናቸው። አነሳሱ ምንም ይሁን ምን ዛሬ እየታየ ያለው አብይ ኢትዮጵያን ሲያፈርስ ነው።    

4. የመፍትሄ አቅጣጫ፡ ወደ ጥንታዊ እሴቶች መመለስ

በመሰረቱ አብይ አህመድ በስልጣን ላይ እያለ ሰላም ሊኖር አይችልም። ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አብይን ከስልጣን ለማስወገድ መተባበር ይኖርባቸውል። የሰላማዊ ትግልም ሆነ የትጥቅ ትግሉ መቀነባበርና ለአንድ ግብ (ሰላማዊት ኢትዮጵያን) መሰረት በማድረግ መታገል የግድ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ያሉትን ልዩነቶች በሃገር በቀል ልማዳዊ መፍትሄ አፈላላጊ ሽምግልና መመለስ ይገባል። ስለዚህ፣

  1. የተቀናጀ የኃይሎች ጥምረት (የተባበረ ተቃዉሞ) ተደጋግሞ መባልና ወደተግባር መገፋት ያለበት ነው  በመበታተን የሚደረግ ትግል ለአገዛዙ ዕድሜ እንደሚሰጥ ካለፈው የህወሃት ታሪክ መማር ይቻላል። የዓላማ አንድነት፦ በትጥቆ የሚታገሉ (እንደ ፋኖ ያሉ) እና በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ኃይሎች ለአንድ የጋራ ግብ—ማለትም አገራዊ ሽግግርን ለማምጣት መቀናጀት አለባቸው።
  2. ከብሄር ፖለቲካ መውጣት፦ ትግሉ ከአንድ ብሄር ጥበቃ ወጥቶ፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያሳትፍና የሁላችንም አገር በሚል ራዕይ መመራት አለበት።

3. ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ እና ህጋዊ ጫና

አገዛዙ ለውጭ እርዳታና ብድር እጅግ ጥገኛ በመሆኑ ይህንን እንደ መሳሪያ መጠቀም፦

  • የማዕቀብ ግፊት፦ በወለጋ፣ በአርሲ እና በአማራ ክልል ለደረሰው እልቂት ተጠያቂ የሆኑ ባለስልጣናት በአለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) እንዲጠየቁ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረጃዎችን ማቅረብ።
  • የዲፕሎማሲ መገልል፦ የውጭ አገራት (እንደ ቱርክና ኢሚሬትስ ያሉ) ለጦርነቱ የሚያደርጉትን የድሮንና የገንዘብ ድጋፍ እንዲያቆሙ በዲፕሎማሲው ረገድ ከፍተኛ ጫና ማሳደር።

4. ህዝባዊ እምቢተኝነት (Civil Disobedience)

መንግስት ጦርነቱን የሚመራው ከህዝብ በሚዘረፍ ግብር እና በድሃው ህዝብ ልጆች በመሆኑ፦

  • ለጦርነት “አይ” ማለት፦ ወጣቶች ለማይመለከታቸው ጦርነት እንዳይማገዱ በየአካባቢው የግንዛቤ ስራ መስራት።
  • ኢኮኖሚያዊ እምቢተኝነት፦ የጦርነት ማሽን የሆነውን የመንግስት ካዝና የሚያሟሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በሰላማዊ መንገድ ማዳከም።

5. ሁሉን አቀፍ የሽግግር ውይይት (Inclusive National Dialogue)

ይህ አሁን መንግስት ከሚመራው “ብሔራዊ ምክክር” የተለየ መሆን አለበት፦

  • አካታችነት፦ ሁሉንም የታጠቁና ያልታጠቁ ኃይሎች ያሳተፈ፣ በአለም አቀፍ ታዛቢዎች የሚመራ እና የመንግስት የበላይነት የሌለበት የሽግግር ዝግጅት መጀመር።

እርቅና:  ለአውነተኛና ዘላቂ ሰላም ለመድረስ ጥፋቶችን አንጥሮ አውጥቶ መነጋገርና ፍትህ ማስያዝን ይጠይቃል። ትርክትን ማስተካከል ይጠይቃል። የማያስማሙ ታሪኮችን ለታሪክ ተመራማሪዎች መተውና ከምርምራቸው መማር ሁላችንንም ይጠቅማል። 

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በሁለት ተቃራኒ ጎዳናዎች መካከል ትገኛለች፤ አንደኛው ከፋሺስት ወረራ ጀምሮ በህወሃት የታቀደና በአሁኑ አገዛዝ እየተተገበረ ያለ፣ በብሄር ማንነት ላይ የተመሰረተ የከፋፍለህ ግዛ መንገድ ሲሆን፣ ውጤቱም የዘር ማጽዳት፣ የሃይማኖት ተቋማት መዳከም፣ የድሮን ጥቃት እና የኢኮኖሚ ውድቀት ነው። በተቃራኒው ደግሞ አገሪቱን ከመፈራረስ ሊታደጋት የሚችለው፣ በጋራ ዜግነት፣ የሰላምና የአንድነት መንገድ ነው። የዚህ መንግስት መውደቅ ለሃገራችን ሰላምና አንድነት የመጀመሪያው ቢሆንም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ክህወሃት ጀምሮ የተዘራውን ጥላቻ ከስሩ ነቅሎ ማስወገድ ያስፈልጋል። የሃገር አፍቃሪያን ይህን መንግስት አስወግደው በህዝቡ ውስጥ ያለውን ቁርሾና የሃሰት ትርክት ማስተካከል የሚቻለው በባህላዊ መስተጋብራችን ተነስተን የሚቆጡና የሚገስጡ ሽማግሌዎችን ወደ ቀድሞ ስራቸው ሲመለሱ ነው። ስለዚህ  ባህላችንን  በማጠናከር የሰላም አምባሳደሮች መሆን ያለባቸውን  የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ተገቢውን ቦት ማስያዝ ይጠቅመናል። እነዚህ አካላት ወታደራዊ እንቅስቃሴን የማቆም፣ የህዝብ አቤቱታን የመስማትና የማስታረቅ ሞራልና ስልጣን ሊኖራቸው ይገባል። የገዳ ስርአት በኦሮሚያ ባህል በሃይል ስልጣን ላይ የመቆየት አባዜን ለማቆም፣ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍን ባህላዊ ትውፌቱን ተጠቅሞ በቃችሁ ማለት ይችላል፣ ሰላምን ማስተማርና መረጋጋትን ማምጣት ይችላል። 

የኢኮኖሚ ዳታ ምንጮች

** IMF, World Bank, Ethiopian Statistics Service, trading economics(website)

የሰባዊ መብት፣ የዘር ፍጅት፣ የዲፕሎማሲና የሃይማኖት ግጭት ምንጮች

** የኢትዮጵያ ሰባዊ መብቶች ጉባኤ( ኢሰመጉ) አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር (OHCHR፣ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UN OCHA):

ዓለም አቀፍ የስደት ድርጅት (IOM)፣ USCIRF (U.S. Commission on International Religious Freedom): ACLED (Armed Conflict Location & Event Data Project): The Horn of Africa Hub 

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English

ኤክስ ፡ @zborkena

1 COMMENT

  1. የአማራ ህዝብ መከራና የኢትዪጵያ መከራ ጸሃፊው እንደገለጠው ከጣሊያኑ ወረራ በህዋላ እየጎላ የመጣ ጉዳይ ነው። ይህም ኢትዪጵያን ለማፍረስ ሶስት ነገሮችን ያማከለ ሴራ ነው። አንደኛው የአማራን ህዝብ በቁጥርና በእውቀት ማዳከም ሲሆን ይህ የሚሆነው ደግሞ በቀጥታና በእጅ አዙር አሰራር እንደሆነ አይናችን አፍጠን እያየን ነው። አማራ ኢትዮጵያን ከራሱ በፊት ስለሚያስቀድም የፈጠራ የክስ ስም እየሰጡ ያኔም አሁንም ህዝቡን በመመንጠር ላይ ይገኛሉ። ሁለተኛው – የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤ/ክ ማሳደድና ማዳከም ሲሆን ያው በየክልሉ በተደራጅ ሃይሎች የሚገደሉትና የሚፈናቀሉት ሁሉ እምነቱን ለማዳከምና ሃገራዊ አንድነትን ለመናድ ሆን ተብሎ የሚፈጸም ከአንደኛው ጉዳይ ጋር አብሮ የተሰላ ነው። ሶስተኛው ራሱን በራሱ የሚያቆስለው አማራው ነው። ከጦርነት ብልሃት ይሻላል ሲባሉ አንሰማም ብለው ጫካ በሌለበት ጫካ ገባን የሚሉንና በውጭና በውስጥ እነዚህን ሃይሎች የሚደግፉ ሁሉ የሚቆሰቁሱት የአማራ ክልል በሚባለው ሥፍራ የሚነደው እሳት ነው። አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ ሆኖ እንሆ ወያኔና ሻቢያ በተንገዳገድበት መንገድ ዛሬ ሌላ ብሄርተኞች ብረት አንስተው ነጻ እናወጣሃለን የሚሉትን ህዝብ ለመከራና ለስቃይ በመዳረግ ላይ ይገኛሉ። ይህ የጊዜ ገደብ የሌለው ሁሌ እንዳስፎከረ የሚያኖረው የጦር መዛዥነት መንገድ መንግስት ነኝ ለሚለውም ሆነ ለብሄርተኛ ታጣቂዎች እንደማያዋጣ ያለፍንበት የሰጣ ገባ የፓለቲካ ግብግብ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ግን ጦርነት ንግድ በሆነበት የሃበሻ መሬት የሌላው ረሃብና ስቃይ ለተፋላሚ ሃይሎች ስሜት አይሰጣቸውም።
    የአማራንና የኦሮሞን ህዝብ እንደ ገና ዳቦ በመሃል ላይ አሰልፎ የሚያስጠብሰው ይህ የጊዜአችን የታጣቂ ስብስብ እርስ በእርሱ የማይስማማ፤ የነጠረ እቅድና ዓላማ የሌለው ቀምቶ አዳሪ ሃይል እየሆነ መምጣቱ የፓለቲካ ስልቱ ፉርሽ መሆኑን ያሳያል። የአማራ ህዝብ ነጻ አውጭ አይፈልግም። የኦሮሞ ህዝብ ልገንጠል አይልም። ይህን ሁሉ ዶፍ የሚያወርዱት ተምረናል አውቀናል የሚሉ አኞ ፓለቲከኞች ናቸው። አንድ በቅርብ የገጠመኝን ጉዳይ ላካፍላችሁ። ጠጋ አለና በእንግሊዘኛ ቋንቋ ሃበሻ ነህ ወይ አለኝ? እኔም በትውልድ ኢትዮጵያዊ ነኝ አልኩት። ቡና ይዤ ስለነበር እኔው ካለሁበት ጠረጴዛ ላይ ክፍት ወንበር ስቦ ቁጭ አለ። ትንሽ ካወራን በህዋላ ሃኪም/ዶክተር መሆኑን ነገረኝና ከየትኛው ክልል ነህ አለኝ። እኔም ክፍለ ሃገር እንጂ ክልል አላውቅም ስለው እኮ ከየት አለኝ። ያስጨነቀው ነገር ብሄሬን ማወቁ እንደሆነ ገብቶኛል። የትወለድኩት ከዚህ ነው አልኩት። አይኑን ፍጥጥ አድርጎ ያለፈ የሙት ፓለቲካውን ይረጭብኝ ጀመር። እየተወራጨ በራሱ ብሄር ላይ ሌላው አደረሰ የሚለውን ጉዳይ እጅን እያወራጨ ያወራኛል። እኔም በጽሞና ዝም በዬ አዳመጥኩት። የሚያስገርመው ነገር የጥላቻው ምንጭ ሁሉ መረጃ አልባና በተሳከረ እይታ ሆኖ እያለ በደሉ ትላንት በራሱ ላይ የደረሰበት እንደሆነ አርጎ እያወራ እያለ አቆምኩትና ሰማሁህ። አሁን የእኔ ወረፋ ነው አልኩት። እሺ አለ። የህክምና ዶ/ር ነኝ ብለሃል በዚህ ጥላቻ በሞላው እይታህ በደለኝ ከምትለው ብሄር ወደ አንተ ጋ ለህክምና ሰው ቢመጣ እንዴት ባለ ሂሳብ ነው Hippocratic Oath የምትፈጽመው? ልብህ በጥላቻ ተሞልቷል አልኩት። ደንገጥ አለና እሱ ሌላ ይሄ ሌላ አለኝ። እኔም በቃኝና ከተቀመጠበት ትቼው ሄድኩ።
    ይህ ሾተላም የብሄር ሰካራም ሁሉ በስሙ ዙሪያ ዶ/ር፤ ኢንጅኒየር ገለ መሌ እያለ ከአንድ ያልተማረ የሃገራችን ገበሬ ያነሰ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ እይታ ያላቸው እነዚህ ድውያኖች ሞት ካለሆነ በስተቀር ከጥላቻቸው የሚፈታቸው ምንም አይነት ምድራዊ ሃይል የለም። ይህ ሰው ቀኔን አደፈረሰው። እርግጠኛ ነኝ እሱም ሰላም አይኖረው። ታዲያ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲህ ሆነን እስከ መቼ ነው የምንኖረው? በወረፋ እየተጠቃቁ፤ በብሄርና በነገድ ስም እየነገድ እንዴት ሃገር መገንባት ህዝብን ወደ አንድነት ማምጣት ይቻላል?
    ለዚህ ነው በተደጋጋሚ ህዝባችን ያለውን አሹቅ እንኳን በልቶ በሰላም እንዲያድር የትጥቅ ትግል የሚባል ጉዳይ በምድሪቱ ላይ መኖር የሌለበት። የጦርነት አውድማ ከቀየረው ልብ ይልቅ ብዕር የቀየረው ቋሚነት አለው። ጦርነት አፍራሽ ነው። ጦርነት የኋላቀርነት ምልክት ነው። አውቃለሁ መሸታ ቤት ተቀምጦ በለው በይው የሚሉ ጉዶች በምድሪቱ ላይ እንዳሉ። አንዳቸውም ግን ለመሞት ዝግጅ አይደሉም። ለዚያ ነው የወያኔ መሪዎች ፊት ለፊት ጦር ሜዳ ገብተው ተጋፍጠው ቆስለውና ሞተው ቢሆን አሁን ላይ የትግራይን ወጣት እንደገና ለመከራ ባላሰለፉትም ነበር። ፓለቲካ የተኩላዎች ስብስብ የፈጠሩት ስሌት ነው። የወያኔ ነገር አበቃ ያለን የአስመራው ብቸኛ መሪ ወያኔ መሸነፉን ተገንዝቦ ፕሪቶሪያ ሂዶ ከመንግስት ጋር በመደራደሩ አኩርፎ አሁን ሻቢያ ተገልብጦ ከወያኔ ጋ ሆኖ ተንኮል ይሸርባል። ይህ የፓለቲካ እቃ እቃ ጫዋታ የሚያሳየው ጫዋታ ፍርስርስ ያደረ እንጀራ ቁርስርስ እንደሚሉት የልጆች ጫዋታ ነው። እንጀራውም ቆመ የተባለውም ነገር የለምና! መግደል መሸነፍ ነው ያለን ከገደለ፤ በቃኝ ለሰላም እጄን አንስቻለሁ ብሎ ትጥቅ ሊፈታ ቃል የገባው ወያኔ እንደገና ከተደራጀ፤ ትላንት ከመንግስት ጎን ሆኖ ወያኔን የወጋው ፋኖ ዛሬ የወያኔና የሻቢያ ተጓዳኝ ከሆነ የብሄር ፓለቲካ አክሳሪ እንጂ ለሃገርና ለህዝብ ጥቅም የለውም። የአማራ ህዝብም መከራ የሚቆመው በማወቅና በመደራጀት የሃገርና የሌላውን ክብር በመጠበቅ በሰላም እንጂ በጦር መሳሪያ ሃይል አይሆንም። የህዝባችን መከራ እንዲቆም ከተፈለገ ብሄርተኞች ከመንግስት ጋር ተደራድረው በሰላም ነገሮችን መፍታት አለባቸው። ያ እስካለሆነ ድረስ ሁሉ ነገር ውሃ ወቀጣ ነው የሚሆነው። ስንብተን እንይ። በቃኝ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News