Homeነፃ አስተያየት ሶስቴ ያመለጠንን የዲሞክራሲ ዕድል ፋኖ ያጎናጽፈን ይሆን? 

 ሶስቴ ያመለጠንን የዲሞክራሲ ዕድል ፋኖ ያጎናጽፈን ይሆን? 

Advertisement
World Wide Travel Group
 የዲሞክራሲ ዕድል

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com)

ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ “Putting Ethiopia on the Path of a Fano-Sponsored Democracy” በሚል አርዕስት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የጻፈውን የፈረንጆቹን አመት የመጨረሻ መጣጥፉን ሁለቴ በተከታታይ አንብቤ እስክጨርስ ድረስ ጭንቅላቴ ሌላ ነገር የማሰብ ግዜም አልነበረውም። በዚህ መጣጥፉ ውስጥ ፕሮፌሰር መሳይ ሌሎች ከጻፉት ጽሁፍ ጋር እያወዳደረ፣ኢትዮጵያ ዛሬ ከምትገኝበት የህልውና አደጋ እንዴት ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ማድረግ እንደምትችል ያስቀመጠበት መንገድ፣እኔም ነገሮችን በጥልቀትና በስፋት እንድመለከትና የራሴን ሃሳብ እንዳቀርብ በር ከፍቶልኛል። ፕሮፌሰር መሳይ የኔ የሃሳብ ገበታ መሆን የጀመረውና የአስተሳሰብ  አድማሴን ያሰፋው በዚህ ጽሁፍ ወይም በተከታታይ በሚጽፋቸው መጣጥፎችና፣ባለፉት ሃያ አምስት አመታት በጻፋቸው መጻህፍት ብቻ አይደለም። ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ገና በወጣትነቴ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተከታታይ የፍልስፍና ትምህርት ያስተማረኝና ዛሬም በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በተከታታይ ሃሳብ የሚያፈልቅና ምሁራዊ ግዴታውን የሚወጣ ሰው ነው። 

ባለፉት አምስት አስርተ አመታት እኛ ኢትዮጵያዊያን ሰብዓዊ፣ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ መብቶች የሚከበሩበት ሁሉን አቀፍ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት አለብን በሚል ሦስት ሥርዓቶችን አፍርሰናል፣ነገር ግን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ቀርቶ ዛሬም ድረስ እንደ ምንጣፍ እየረገጡ ከሚገዙን አምባገነን አገዛዞች እራሳችንን ማላቀቅ አልቻልንም። እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል በአብዛኛው ያተኮረው ሥርዓትን በማፍረስ ላይ ነው እንጂ የፈረሰው ሥርዓት በምን ይተካል ለሚለው ቁልፍ ጥያቄ ምንም ዓይነት ድርጅታዊም ሆነ ንድፈ ሃሳባዊ መልስም ዝግጅትም አልነበረውም። ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ማዕበል እየተናጠች ነው። ታሪክ በ1966፣ በ1983 እና በ2010 ዓ.ም. የቸረንን ሥርዓት የመለወጥ ዕድል ዛሬም እንካችሁ እያለን ነው። ለመሆኑ ባለፉት ሃምሳ አመታት ሦስት ግዜ በተከታታይ ያመለጠንን የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጅምር የአማራ ፋኖ እንቅስቃሴ እውን ያደርገው ይሆን? ፕሮፌሰር መሳይ ምን ይላል? እኔና አንቺ፣አንተስ ምን እንላለን?

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ህወሓት፣ኦነግ-ሸኔ እና ፋኖን የመሳሰሉ የታጠቁ ኃይሎች አሉ፣እነዚህ የታጠቁ ኃይሎች በተለይ ፋኖና ኦነግ-ሸኔ ከፌዴራል ኃይሎች ጋር ጦርነት ውስጥ ከገቡ ቆይተዋል። ዕብሪተኛው ህወሓት ትግራይ፣አፋርና አማራ ክልል ውስጥ በሰው ህይወት፣በንብረትና በመሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጥፋት ያደረሰ ጦርነት ጀምሮ ሁለት አመት ከተዋጋ በኋላ ጭንቅላቱን ተመትቶ፣ጦርነቱ በፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲቆም ቢደረግም፣ህልውናው በጦርነት ላይ የተመሰረተው ህወሓት ግን  ዛሬም ሌላ ዙር ጦርነት ለመጀመር አመቺ ግዜ እየጠበቀ ነው።

አማራ ክልል፣ አዲስ አበባና በብዙ ትልልቅ የኢትዮጵያ ከተማዎች ውስጥ የሚኖረው ህዝብ የፋኖ ደጋፊ ነው። ህወሓትና ኦነግ-ሸኔ ግን ከራሳቸው ክልል ውጭ ወይም የነሱን ቋንቋ ከሚናገረው ማህበረሰብ ውጭ ደጋፊ የላቸውም፣የህወሓት ድጋፍ ደሞ ጭራሽ ትግራይ ውስጥም በፍጥነት እየቀነሰ ነው። አዲስ አበባ ውስጥና በብዙ የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ፋኖ ድጋፍ ያገኘው አለምክንያት አይደለም። በአንድ በኩል የማንነት ጥያቄ ሲነሳ በከተማዎች የሚኖረው ህዝብ አጉልቶ የሚመለከተው ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ነው እንጂ የብሔር ማንነቱን አይደለም፣ በሌላ በኩል ደሞ አብዛኛው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ የወደፊት ዕጣ ፈንታውን የሚመለከተው በኢትዮጵያዊነት ጥላ ውስጥ ብቻ ነው። ኢትዮጵያዊነቱን ከምንም ከማንም በላይ ለሚመለከትና የመኖር ዋስትናው ኢትዮጵያዊነት ብቻ የሆነ  ዜጋ ሁሉ ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ ትግል መቀላቀል ከፈለገ ሄዶ የሚያንኳኳው የፋኖን በር ነው እንጂ የህወሓትንና የኦነግ-ሸኔን በር አይደለም። የህወሓትና የኦነግ-ሸኔ ትግል ትናንትም ዛሬም የሚጀምረውም የሚያልቀውም በራሳቸው ብሔር ዙሪያ ነው። የፋኖ ኃይሎች ግን ግባቸው አማራን ከኢትዮጵያ መገንጠል ሳይሆን፣የአማራ ህዝብ የተደቀነበትን የህልውና አደጋ ማስቆምና የኢትዮጵያን እንደ አገር ቀጣይነት ማረጋገጥ ነው። ፕሮፌሰር መሳይ ይህንን እውነታ ተመልክቶ ነው ዛሬ አገራችን ከምትገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለመጀመር ከሁሉም የተሻለው አማራጭ የፋኖ እንቅስቃሴ ነውና ይህንን እንቅስቃሴ መደገፍ አለብን ብሎ አማራውን ጨምሮ ብዙ ኢትዮጵያዊያን እየደባበሱ የሚያልፉትን እውነት ፍርጥርጡን አውጥቶ የነገረን! ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በቅርቡ ይህንን አስመልክቶ በጻፈው ጦማር ላይ የሚከተለውን በግልጽና በማያሻማ ቋንቋ አስቀምጧል።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

“በፋኖ የተደገፈ ዲሞክራሲያዊ መንገድን በጋለ ስሜት እንድደግፍ ያደረጉኝን ምክንያቶች በጥልቀት ለመፈተሽ የተሻለና አመቺ መንገድ ነው ብዬ የማስበው በመጀመሪያ ኢትዮጵያ እንደ አገር ዘላቂነቷ ተረጋግጦና አንድነቷ ተጠብቆ ወደፊት የምትራመድ አገር እንድትሆን የሚያስችላትን ከሁሉም የተሻለ መንገድ በማቅረብ ነው። የተሻለ መንገድ ስል ሁለት ነገሮችን ማለቴ ነው፣1ኛ- ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምስረታ በጣም አዋጪው መንገድ፣2ኛ- ባሉን ተጨባጭ መረጃዎች መሰረት በጣም አሳማኝ የሆነው ውጤት። እነዚህን ሁለት መመዘኛዎች ለማሟላት ካሉን አማራጮች ሁሉ የተሻለው ፋኖ “እርግጠኛ አሸናፊ ሆኖ ሲወጣ ወይም የአማራ ብልጽግና ህልውና እንዲያከትም የሚያደርግና የኦሮሞ ብልፅግናን የሚያዳክም ሁኔታን የሚፈጥር አሸናፊ የሌለበት ወታደራዊ ፍጥጫ ሲፈጠር ነው”

እንደ ፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር ግንቦት(May) 4,2015 “ያበጠው ይፈንዳ” በሚል አርዕስት በጻፍኩትና ቦርከና ላይ በወጣው ጽሁፍ እንዲህ ብዬ ነበር-ያበጠው ይፈንዳ!!! (ኤፍሬም ማዴቦ)

“እርስ በርስ መባላቱንና ዛሬ በመካከላቸው የሚታየውን የሜዲያ ጦርነት አቁመው፣ በአንድ የፖለቲካ ክንፍ ከተመሩና፣ ለተቀረው ኢትዮጵያዊ ኑና አብረን ኢትዮጵያን ከአደጋ አድነን፣ተወያይተንን፣ተደራድረንና ተሸማግለን አገራችን ውስጥ የፍትህ፣የነጻነትና የዲሞክራሲ መሰረት እናኑር የሚል አገራዊ ጥሪ ካቀረቡ፣ በኔ ዕምነት ብቸኛው ወደ ኢትዮጵያዊነት ትግል መግቢያው መንገድ የፋኖ እንቅስቃሴ ነው። ይህ የማይሆን ከሆነና፣ እርስ በርሳቸውም፣የአማራን ህዝብ የህልውና አደጋ ውስጥ ከከተተ ኃይል ጋርም እየተዋጉ የሚዘልቁ ከሆነ ግን፣የፋኖ ኃይሎች አባቶቻቸው ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለው ያቆሟትን አገር እነሱ ማፍረስ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል በፍጹም መዘንጋት የለባቸውም”

የአማራ ፋኖን እንቅስቃሴ በተመለከተ እንደ ፕሮፌሰር መሳይ የተለያዩ አሁናዊና ታሪካዊ ዳራዎችን ዳስሼ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ዛሬ ላይ ካሉን አማራጮች ሁሉ የተሻለው የፋኖ እንቅስቃሴ መሆኑን በምክንያታዊነት ዘርዝሬ ባላስቀምጥም፣እንደ አንድ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ላለፉት 40 አመታት በቅርብ እንደተከታተለ ሰው፣ ግራና ቀኙን አይቼና አመዛዝኜ ከፕሮፌሰር መሳይ ጋር የሚመሳሰል ድምዳሜ ላይ መድረስ ችያለሁ። የፋኖ ኃይሎች “መነሻችን አማራ መድረሻችን ኢትዮጵያ” የሚለውንና ከፋኖ መንደር ብቻ እንጂ ከሌሎች የታጠቁ ኃይሎች መንደር ያልተሰማ በግልፅ የሚታይ አላማ አስቀምጠው ነው ከፌዴራል ኃይሎች ጋር የህልውና ትግል ውስጥ የገቡት። የፋኖ ኃይሎች አማራንም ኢትዮጵያንም ማዳን የሚል ጣምራ ግብ እውን ማድረግ ከፈለጉ፣ያላቸው ብቸኛ አማራጭ በአንድ በኩል እነሱ እራሳቸው በአንድ የፖለቲካ ማዕከል መመራት አለባቸው፣በሌላ በኩል ደሞ አስተሳሰባቸውን፣ድርጅታዊ አሰራራቸውንና አካሄዳቸውን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ አለባቸው። እኛም የተቀረነው ኢትዮጵያዊያን 50 አመት ሙሉ የጮህንለትንና የናፈቀንን የዲሞክራሲ ጅምር አገራችን ውስጥ እውን ሆኖ ማየት የምንችለው ፋኖ ከተባባረና ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ከሆነ ነው። እነዚህ አስፈላጊ የሆኑ ሃሳቦች ፕሮፌሰር መሳይም ያነሳቸው ሃሳቦች ናቸው። ልብ በሉ እኔ ፕሮፈሰር መሳይ ያነሳው ሃሳብ ለኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ጅምር ብቸኛ መንገድ ነውና ሁላችንም ይህንን መንገድ ብቻ እንከተል እያልኩ አይደለም። እኔ እያልኩ ያለሁት ሁላችንም አፋችንንም አይናችንንም ዘግተን የወለም ዘለም ኑሮችንን በምንገፋባት ጨለማ ሁኔታ ውስጥ የፕሮፈሰር መሳይ ከበደ ሃሳብ አይን ከፋች ሃሳብ ነውና አይናችንን እንክፈትና ዙሪያችንን እንመልከት፣ ደሞም አገራችን ኢትዮጵያ ፊታችን ላይ ተበታትና ከማይታችን በፈት አብረን መፍትሄ እንፈልግ ነው።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ፕሮፌሰር መሳይ ካቀረባቸው ሃሳቦች ወይም አማራጮች ውስጥ በጣም የተስማማኝ የሚከተለው ነው፣ ይህ አማራጭ እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ መፈጠር አለበት ብዬ ከማምነው የሽግግር መንግስት ሃሳብ ጋር ተመሳሳይ ባይሆንም ይቀራረባል-

“እኔ እንደማየው፣ ወደ ድርድር የሚያመራ አሸናፊ የሌለበት ፍጥጫ አንድ አማራጭ ነው፣ ግን ብቸኛው አማራጭ አይደለም፡ ምክንያቱም አሸናፊ የሌለው ፍጥጫ ወደ መበታተን እና መገንጠል የሚያመራ የረጂም ግዜ ጦርነት ውስጥ ይዞን ሊገባ ይችላል። ስለዚህ ከሁሉም የተሻለው አማራጭ ፋኖ አሸንፎ የበላይ ኃይል ሆኖ የሚወጣበት ሁኔታ ብቻ ነው፡ይህ አማራጭ ለአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያም የሚበጅ ነው። ፋኖ አካታችና ሁሉንም የሚያቅፍ ኃይል ሆኖ እንዲወጣ አንድ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ አለ፣ እሱም የተበታተኑት የፋኖ ኃይሎች ወደ አንድነት መምጣት መቻላቸውና፣ፋኖ እራሱን  ዴሞክራሲያዊ ማድረግ መቻሉ ነው። ፋኖ እነዚህን ሁለት ቅደም ሁኔታዎች ካሟላ  ብቻ ነው ወታደራዊ ጡንቻዉን ተጠቅሞ በሽግግሩ ወቅት ሰላምና ጸጥታን ማረጋገጥ የሚችለው፣ በተለያዩ ኃይሎች መካከል ዲሞክራሲያዊና አካታች የሆነ ድርድር እንዲካሄድ ማድረግ የሚችለውና፣ የሽግግር መንግስት የሚቋቋምበትን አመቺ ሁኔታ መፍጠር የሚችለው”

እራሱን ወደ አንድ ማዕከላዊ አመራር ያመጣና ዲሞክራሲን መመሪያው ያደረገ የፋኖ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሽግግግር ወቅት ሊጫወት የሚችለውን ወሳኝና አዎንታዊ ሚና ከወዲሁ ተመልክቶ ሃሳቡን በጽሁፍ ያጋራን ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ብቻ አይደለም። በዋሺንግተን ዲስ አካባቢ የሚገኘውና እራሱን እምቢልታ ብሎ የሚጠራው የኢትዮጵያዊያን ህዝባዊ ማህበራት ጉባዔም የኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ጅምርና በዚህ ጅምር ውስጥ ፋኖ መጫወት የሚችለውን ወሳኝ ሚና በተመለከተ ተከታታይ ጥናታዊ ጽሁፎች አቅርቧል። የህወሓት አገዛዝ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ እንደ ፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር በ2021 ዓም እምቢልታ ባወጣው መጣጥፍ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ሦስት የሽግግር ዘዴዎችን በዝርዝር አስቀምጧል፣ሆኖም ከሦስት አመት በኋላ “ዜጋ-ተኮር ፍኖተ-ካርታ ለፖለቲካ ስርዓት ለውጥ” በሚል አርዕስት ባወጣው ሌላ ጥናታዊ፣ሰፋ ያለና ገላጭ መጣጥፍ የመጀመሪያዎቹን ሁለት አማራጮች ተግባራዊ ማድረግ እንደማይቻል አስምሮበታል። እምቢልታ ያስቀመጣቸው ሦስት የሽግግር ዘዴዎች የሚከሉት ናቸው-

1-ብልፅግና- መራሽ ሽግግር
2-የብሔራዊ አንድነት መንግሥት-መራሽ ሽግግር
3. ዜጋ-መራሽ ሽግግር

- Advertisement -

እምቢልታ “ዜጋ-መራሽ ሽግግር” ብሎ ባስቀመጠው አማራጭ ውስጥ የለውጥ አራማጅ ፓርቲዎች ጥምረት፣ነጻና ገለልተኛ የሆኑ የመብት ተከራካሪ ድርጅቶች፣ የሙያ ማህበራት፣ሚዲያዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ዜጋ-ተኮር ሽግግሩ ወደ ዲሞክራሲ እንዲያመራ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ አለባቸው ይልና፣እንዲህ አይነቱ ሁሉን አቀፍ የለውጥ ትብብር ህጋዊ የሽግግር ወኪል ከመሆኑም ባሻገር፣የፖለቲካ ሥልጣን ዛሬ በሥልጣን ላይ ካለውና ከከሸፈው የብልፅግና መንግስት በህዝብ ወደተመረጠ ግዜያዊ መንግስት ሽግግር እንዲያደርግ የተቆጣጣሪነትና የአስፈጻሚነት ሚና ሊጫወት እንደሚችል ይናገራል። በኔ እምነት ይህ ሦስተኛው አማራጭም በዛሬዋ ተመሳሳይ አጀንዳ የሌላቸው አምስትና ስድስት የታጠቁ ኃይሎች ባሉባት፣የትጥቅና የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል በሚካሄድባትና በብሔር ግጭት በነጋ በጠባ በምትታመሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ መሆን የሚችል አይመስለኝም። 

ኢትዮጵያ ውስጥ በ1966፣በ1983ና በ2010 ዓም ከታየው ሽግግር ፍጹም የተለየና አካታች የሆነ ዲሞክራሲያዊ የሽግግር ሂደት እንዲጀመር፣አንድ የፈረጠመ ወታደራዊ ጡንቻ ያለውና ከእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ውጭ ሌላ ምንም የራሱ አጀንዳ የሌለው ቡድን ያስፈልጋል። ይህንን የምለው ያለምክንያት አይደለም። የዛሬዋ ኢትዮጵያ የተለያዩ መሳሪያ ያነሱ ቡድኖች ያሉባትና የርስ በርስ ጦርነት የሚካሄድባት አገር ናት። ትግራይ፣አማራና ኦሮሚያ ክልል ህግና ሥርዓት አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሦስት ክልሎች ከፌዴራሉ መንግስት ቁጥጥር ውጭ ናቸው። እንዲህ አይነት ውስብስብ ችግሮች ባሉበትና ውይይትንና ድርድርን የሚያስቀድም የፖለቲካ ባህል በሌለበት አገር ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲኖር ወይ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ መግባት አለበት፣አለዚያም ወታደራዊ የበላይነት፣ቅንነትና በጎነት ያለው አገር በቀል ኃይል መኖር አለበት። ይህ በሌለበት ሁኔታ እምቢልታ የጠቀሳቸው የተለያዩ ባለድርሻዎች የተቆጣጣሪነትና የአስፈጻሚነት ሚና ሊጫወቱ ቀርቶ እነሱ እራሳቸው ተገናኝተው የሚወያዩበት መድረክም በቀላሉ አይፈጠርም።

ፕሮፌሰር መሳይ የተስማማባቸውና እኔም የምደግፋቸው ሁለት የእምቢልታ ሃሳቦች ወይም አማራጮች አሉ- አንደኛው- ዛሬ ባለንበት ሁኔታ ያለን ብቸኛ አማራጭ በዜጎች ፍላጎት ላይ ላይ የተመሰረተ፣ በፋኖ የተደገፈና ሁሉንም መሰረታዊ የኢትዮጵያ ባለድርሻዎች ያቀፈ የሽግግር ፕሮግራም ነው የሚለው አማራጭ ሲሆን፣ሁለተኛው- ዛሬ ባለንበት የታሪክ አጋጣሚ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ የረጂም ዘመን የዲሞክራሲ ራዕይ እውን ለማድረግ፣በፋኖ የሚመራ የአማራ ህዝብ ንቅናቄ ከሁሉም የተሻለ ነው የሚለውን አማራጭ ነው። በእርግጥም እምቢልታ እንደሚለው ፋኖ  የትጥቅና የፖለቲካ ክንፉን በማቀናጀት፣ማዕከላዊ አመራር መፍጠር ከቻለና  ትክክለኛ የፖለቲካ ፕሮግራም ነድፎ መንቀሳቀስ ከቻለ፣የህልውና ስጋት ውስጥ የገባውን አማራንም ኢትዮጵያንም መታደግ ይችላል። የፋኖ እንቅስቃሴ የፖለቲካ አድማሱን ማስፋት ከቻለና፣በጦር ሜዳው ወታደራዊ ድል መቀዳጀት ከቻለ፣ኢትዮጵያን ማለቂያ ከሌለው የአምባገነንነት አዙሪት ማውጣት የሚችል ጠንካራና አገራዊ ራዕይ ያለው እንቅስቃሴ ነው።

የኢትዮጵያን እንደ አገር ቀጣይነት ለማረጋገጥና ዕድሜ ልኳን ከተጠናወታት አምባገነናዊ አገዛዝ ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ ተላቅቀን ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ማድረግ አለብን የሚለው ሃሳብ አማራጭ የሌለው ወርቅ ሃሳብ ነው፣ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲኖር ደሞ እሱ እራሱ ዲሞክራሲያዊ የሆነ የሽግግር መንግስት ያስፈልጋል። ዛሬ ትልቁ ጥያቄ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አይነቱ የሽግግር መንግስት እንዴት ይመሰረታል የሚለው ጥያቄ ነው። ፕሮፌሰር መሳይና እምቢልታ ለዚህ ጥያቄ የሰጡት መልስ የሚመሳሰልና አማራ ክልል የሚካሄደውን የፋኖ እንቅስቃሴ ማዕከል ያደረገ መልስ ነው፣ደሞም ሁለቱም የሽግግር መንግስት የሚመሰርተው ፋኖ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የተለያዩ ሲቪልና ወታደራዊ ባለድርሻዎች ጋር እንደሆነ በግልጽ ተናግረዋል። 

የፋኖ እንቅስቃሴ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት ውስጥ ሊጫወት የሚችለውን ሚና በተመለከተ ከእምቢልታና ከፕሮፌሰር መሳይ የተለየ እይታ የለኝም፣ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የፋኖ እንቅስቃሴ ከሌሎች ታጣቂ ኃይሎች በተለየ መንገድ ትልቅና ጉልህ ሚና መጫወት ይችላል የሚል ዕምነት አለኝ። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ስመለከት ግን እምቢልታና ፕሮፌሰር መሳይ አጉልተው ያላወጡት እኔ ግን በጣም የሚያስፈራኝ አንድ ቢሆንስ (Senario) አለ። ኢትዮጵያ ውስጥ የታጠቁ ኃይሎች በሚያካሄዱት ትግልና በየቦታው ብልጭ ድርግም እያለ በሚካሄደው የአልገዛም ባይነት ትግል ማዕከላዊው መንግስት ተዝልፍልፎ ሊወድቅ ይችላል፣ይህ ቢሆንስ እውን ከሆነ፣ክፍተቱን የሚሞላው ቀድሞ አዲስ አበባን የሚቆጣጠረው የታጠቀ ኃይል ሊሆን ይችላል። ይህ አጋጣሚ በታጠቁ ኃይሎች መካከል ሌላ የሥልጣን ሺሚያ ጦርነት ውስጥ ሊከተን ይችላል። ይህ ማናችንም የማንፈልገው ነገር ግን ሊመጣና እውን ሊሆን የሚችል አጋጣሚ አንጎላ ውስጥ ደርሶ አይተነዋል። ለአንጎላ ነጻነት አንድ ላይ ሆነው የፖርቱጋል ቅኝ ገዢዎችን ለ13 አመት አብረው የተዋጉት የሆልደን ሮቤርቶና የዮናስ ሳቪምቢ ኃይሎች አንጎላ ነጻ ከወጣች በኋላ እኔ ነኝ አንጎላን መምራት ያለብኝ በሚል ለ27 አመታት ተዋግተዋል። በኔ ዕምነት ለሽግግር መንግስት ምስረታ በምናደርገው ጥረት እንዲህ አይነቱ ሁኔታ እንዳይገጥመን ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ቁልፍ ጥያቄ ካሁኑ መመለስ መጀመር አለብን።  

ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት ሊመሰረት የሚችልባቸው ሁለት መንገዶች አሉ- 1ኛ- አንድ የታጠቀ ኃይል ወሳኝ በሆነ መልኩ( Decissisive Military Victory) ማዕከላዊውን መንግስት ማሸነፍ ከቻለና፣ የታጠቁ ኃይሎችንና የተለያዩ አገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ ባለድርሻዎችን ጋብዞ ተደራድረው የሽግግር መንግስት እንዲፈጥሩ ካደረገ ነው፣ በኔ ዕምነት ከአማራ ፋኖ እንቅስቃሴ ውጭ ዛሬ ላይ ይህንን ማድረግ የሚችል ሌላ የታጠቀ ኃይል ያለ አይመስለኝም። 2ኛ- የትኛውም ተፋላሚ ኃይል በአጭር ግዜ ውስጥ አሸናፊ ሆኖ መውጣት የማይችልበት፣ ነገር ግን ማዕከላዊው መንግስት ከቀን ወደ ቀን እየተዳከመ ሲሽመደመድና የኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል አጠራጣሪ እየሆነ ሲመጣ፣ፋኖና ሌሎችም የታጠቁ ኃይሎች በሥልጣን ላይ ለለው መንግስትና ለሌሎችም የተለያዩ ባለድርሻዎች የሽግግር መንግስት እንፍጠር የሚል ጥሪ ካቀረቡ ነው፣ ይህ አማራጭ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ጥሪውን ተቀበለም አልተቀበለ እውን ሊሆን የሚችል አማራጭ ነው። ምክንያቱም የጦር ሜዳ ፊልሚያው ለታጠቁ ኃይሎች እያደላ ከመጣና ማዕከላዊው መንግስት በወታደራዊ ፊልሚያውም በህዝባዊ እምቢተኝነትም እየተዳከመ ከመጣ፣ ያለው ዕድል ወይ የታጠቁ ኃይሎችን ጥሪ መቀበል አለዚያም አጠቃላይ ሽንፈትን መቀበል ነው። በ1970ዎቹ ደርግ የሶማሊያን ተስፋፊዎች ካሸነፈና ኢህፓን ጠራርጎ ከአገር ውስጥ ካስወጣ በኋላ፣ከሻዕቢያና ህወሓት ጋር ተደራደር ሲባል፣እንደ ውኃ የሚያጥለቀልቅ ኃይል ስላለን ከወንበዴ ጋር ድርድር የለም ነበር ያለው። የኋላ ኋላ ግን እንግሊዝ ውስጥ ወንበዴ ብሎ በጠራቸው ኃይሎች የበላይነት ተደራድሮ ከሥልጣን ሊወገድ ችሏል። ከላይ ከጠቀስኳቸው ሁለት መንገዶች ውስጥ የመጀመሪያው መንገድ እውን የመሆን ዕድሉ ከሁለተኛው መንገድ ያነሰ ነው፣ምክንያቱም ብቻውን አሸናፊ ሆኖ ወጥቶ አብረውት ማዕከላዊውን መንግስት የታገሉትን ታጣቂዎችና የተለያዩ ኢትዮጵያዊ ባለድርሻዎችን ጋብዞ የሽግግር መንግስት እንመስርት ለማለት ድፍረቱም የአላማ ብቃቱም ያለው የታጠቀ ኃይል ፋኖ ብቻ ነው። ህወሓትና ኦነግ-ሸኔ አሁንም የ”ትግራይ ነጻነት” የ”ኦሮሞ ነጻነት” ከሚለው ጠባብ አጀንዳቸው አልተላቀቁም ወይም ዋናው አጀንዳቸው የአንድ ብሔር አጀንዳ ነው።

ፕሮፌሰር መሳይና እምቢልታ የፋኖች ኃይሎች በወደፊቷ ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ላይ የሚጫወቱት አዎንታዊ ሚና አለ በሚለው ሃሳብ ላይ ተመሳሳይ አቋም ነው ያላቸው፣ ሆኖም የብልፅግና  አገዛዝ ተሸንፎ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ በፋኖ ደጋፊነት ወይም አመራር (Fano Sponsored Transition) የሚመሰረተው ግዜያዊ/ሽግግር መንግስት እንዴት ይመሰረታል በሚለው ሃሳብ ላይ የሚያቀርቡት ሃሳብ ይለያያል። እምቢልታ የጠሚ አብይ አህመድ አስተዳደር በፋኖ በሚመራው አመፅና በፓርቲው ውስጥ ባለው አለመግባባት ሊፈርስ ጫፍ ላይ ሲደረስ የሚከተሉትን 3 እርምጃዎች መውሰድ አስፈላጊ ነው ይላል፣1ኛ- ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ፓርላማውንና (የፌዴራልና የክልል) ህገመንግስቱን ማገድ፣2ኛ- ሲቪል ቴክኖክራቶችንና ወታደራዊ ባለሙያዎችን ያቀፈ የአደራ መንግስት ማቋቋም፣3ኛ-ግዜያዊ የምክር ቤት/ፓርላማ ምርጫ ማካሄድ። እምቢልታ እነዚህ እርምጃዎች በጣም አስፈላጊ እርምጃዎች እንደሆኑ አንጽንኦት ሰጥቶ ቢናገርም፣ እርምጃዎቹን ማን እንደሚወስድና እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆኑ ወይም ፋኖ በዚህ ሂደት ውስጥ የሚኖረው ሚና ምን እንደሆነ በግልፅ የሚናገርው ነገር የለም። ለምሳሌ፣የአደራ መንግስት ሲቋቋም ማን እንደሚያቋቁመው፣እነማን አደራው መንግስት ውስጥ እንደሚገቡ፣የአደራውን መንግስት ሥልጣንና ሃላፊነትና የአደራው መንግስት ለምን ያክል ግዜ እንደሚቆይ የተባለ ምንም ነገር የለም። እነዚህን የተጠቀሱትን ሦስት እርምጃዎች የሚወስደው ፋኖ ነው ከተባለና ፋኖ እነዚህን ቁልፍ እርምጃዎች ብቻውን ከወሰደ የፋኖ ዲሞክራሲያዊነት ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ነው፣ወይም ባለፉት ሃምሳ አመታት እንዳየነው ሽግግሩ በአንድ ወገን የበላይነት ሊመራ ነው። 

እምቢልታ ከላይ የተጠቀሱትን ሦስት እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ካለ በኋላ ወደ ታች ወረድ ብሎ  ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት የሽግግር መንግስት ሊፈጠር እንደሚችል ሲናገር የሚከተለውን በጣም አስፈላጊና ለውይይት ክፍት የሆነ አረፍተ ነገር ያስቀምጣል- 

“ኢትዮጵያን በመሳሰሉ የተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ውስጥ ፍትሃዊና ሁሉን አቀፍ የሆነ የፖለቲካ ስምምነት ሊደርስ የሚችልበት ሁለት መሰረታዊ ዘዴዎች አሉ፣አንደኛው የበላይነት ያለው ነገር ግን አገራዊ አጀንዳ ያነገበ፣ቅንነትና በጎነትን የተላበሰ ወታደራዊ ቡድን ሲኖር ሲሆን፣ሁለተኛው ተመሳሳይ የፖለቲካ ራዕይ ያላቸው ኃይሎች ወደ አንድነት መጥተው አጥፊ ኃይሎችን በጋራ የሚቆጣጠር ግንባር ሲፈጥሩ  ነው። ኢትዮጵያ ዛሬ ባለችበት የታሪክ አጋጣሚ፣የተለያዩ የአገሪቱ ባለድርሻዎች የፖለቲካ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ከተፈለገ፣ባለድርሻዎችን የማሰባሰብ፣የማስተባበርና ተደራድረው ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የማድረጉን ስራ ከፋኖ በተሻለ መንገድ የሚሰራ ሌላ ኃይል የለም። ዛሬ በሚደረገው የትጥቅ ትግል የአማራ የፋኖ ኃይል ፍጹም አሸናፊ ሆኖ ይወጣል፣ወይም ማንም አሸናፊ የማይሆንበት ሁኔታ ይፈጠርና የአማራ ብልፅግና ይጠፋል፣የኦሮሞ ብልፅግና እና ህወሓት ይዳከማሉ። ይህ ሁኔታ ዋና ዋና ተፎካካሪ ቡድኖች ወደ ድርድር ጠረጴዛ መጥተው ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር ፕሮግራም መንድፍ እንዲችሉ ያበረታታል ደሞም መንገድ ይከፍታል”

እምቢልታ ካቀረባቸው ሁለት ዘዴዎች ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ የሆነው የመጀመሪያው ዘዴ ነው። በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ወታደራዊ የበላይነት ሊኖረው የሚችልና ከራሱ ብሔር ውጭ ሰፋ ያለ አገራዊ አጀንዳ ያለው የታጠቀ ቡድን ደሞ ፋኖ ነው። ይህ ሃሳብ ፕሮፌሰር መሳይ፣እምቢልታና እኔ የምንስማማበት ሃሳብ ነው።

የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ከሥልጣን ሲወገድ ክፍተቱን ለመሙላት የአደራ መንግስት ያስፈልጋል በሚለው ሃሳብና፣ የፋኖ አሸናፊ ሆኖ መውጣት በህዝብ የተመረጠ መንግስት ወደ ሥልጣን እንዲመጣ የሚደረገውን ጥረት እውን ለማድረግ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነው በሚለው ሃሳብ ላይ ከተስማማን፣ ፋኖ በአደራ መንግስት ውስጥ መጫወት ያለበትን ሚናም በግልፅ ማስቀመጥ አለብን። ኢትዮጵያ ውስጥ ሁላችንም የምንፈለገው ዲሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲኖር የፋኖ አሸናፊ ሆኖ መውጣት አስፈላጊ እንደሆነ እኔም የማምንበት ጉዳይ ነው፣የፕሮፌሰር መሳይም አቋም እዚህ ላይ ግልፅ ነው። እዚህ ላይ እምቢልታን መጠየቅ የምፈልገው፣ፋኖ አሸናፊ ኃይል ሆኖ ሲወጣ ሚናው ምንድነው የሚሆነው ወይም መሆን ያለበት። ይህንን ጥያቄ በተመለከተ ፕሮፌሰር መሳይ ፋኖ አሸናፊ ሆኖ ቢወጣም የፋኖ ሚና መሆን ያለበት ሰላምና ጸጥታ ማስከበርና የአደራው መንግስት የሚወስናቸውን ውሳኔዎች ማስፈጸም ነው እንጂ፣ፋኖ ብቻ ሳይሆን የትኛውም የታጠቀ ኃይል በአደራ/ግዜያዊ መንግስት ውስጥ ቦታ ሊኖራቸው አይገባም ባይ ነው። የፋኖ አሸናፊ ሆኖ መውጣት ወይም አሸናፊ የሌለበት ሁኔታ መፈጠር የተለያዩ ባለድርሻዎች ተሰባስበው ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፕሮግራም መንድፍ እንዲችሉ ያበረታታል የሚለውን የእምቢልታ ሃሳብ እኔም የምደግፈው ሃሳብ ነው። ግን የሽግግር ፕሮግራሙ ተነድፎ የሽግግሩ መንግስት ከተቋቋመ በኋላ የፋኖ ሚና ምንድነው የሚሆነው? ፋኖ የሽግግሩ መንግስት አካል ይሆናል፣ ወይስ የፋኖ ሚና ፕሮፌሰር መሳይ እንዳለው በሽግግሩ ወቅት ሰላምና ጸጥታ ማስከበር ይሆናል? እምቢልታ እዚህ ላይ ነው እንደ ፕሮፌሰር መሳይ ግልፅ መሆን ያለበት።

ፕሮፌሰር መሳይም እምቢልታም የአደራ መንግስት መቋቋም አለበት በሚለው ሃሳብ ላይ ልዩነት የላቸውም። እምቢልታ የብልፅግና አገዛዝ ከሥልጣን ሲወገድ መሰራት ያለባቸውን ስራዎች በሁለት ደረጃ ከፋፍሎ ያስቀምጣል። በመጀመሪያ የብልፅግና መንግስት እንደወደቀ የአደራ መንግስት መቋቋም አለበት፣2ኛ- ግዜያዊ ፓርላማ መቋቋም አለበት። የመጀመሪያውን ሃሳብ ዘርዘር አድርገን ስንመለከት ሰላምና ጸጥታ ለማስከበርና በብልፅግና መወገድ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት  የአገር ሽማግሌዎችንና መሪዎችን (Elders and Leaders) ያቀፈ የአደራ መንግስት መቋቋም አለበት የሚለውን ሃሳብ ያጠቃልላል፣ ሁለተኛው ህሳብ ደሞ የሽግግር ቻርተሩን ተከትሎ የሥርዓት ማሻሻያ ህጋዊ ማዕቀፎችን የሚያዘጋጅ ግዜያዊ ፓርላማ እንዲቋቋም ማድረግ ነው። ይህንን የሁለት ደረጃ አስራር በተመለከተ ፕሮፌሰር መሳይ እምቢልታ ያቀረበውን የሁለት ደረጃ አሰራር እሱ እንደማይገፋበት ነገር ግን ሰፊ ውክልና ያለውና የቀን ከቀን የመንግስት ስራዎችን ከመስራት ባሻገር ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ በአጭር ግዜ ውስጥ እንዲካሄድ የሚያደርግ የአደራ መንግስት መመስረት አለበት የሚለው ሃሳብ እሱም የሚስማማበት ሃሳብ እንደሆነ በግልፅ ይናገራል።

ፕሮፌሰር መሳይ የአደራ መንግስት ከዕለታዊ የመንግስት ስራዎች ባሻገር ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የማዘጋጀት ሃላፊነትም መወሰድ አለበት ብሎ አጽንኦት ሰጥቶ ሲናገር፣ምርጫው በአጭር ግዜ ውስጥ (As soon as possible) መካሄድ እንዳለበትም ይናገራል። እኔም የሽግግሩ መንግስት የስራ ዘመን የሚያልቀው አገራዊ ምርጫ ከተደረገና በሽግግሩ መንግስትና አዲስ በተመረጠው መንግስት መካከል የሥልጣን ርክክብ ሲደረግ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን እኔ በሽግግሩ ወቅት የሚሰሩ ስራዎች በጣም ብዙና ውስብስብ ናቸውና የምርጫው ሰሌዳ ይህንን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት የሚል ዕምነት አለኝ። በአንድ በኩል የሽግግር መንግስት እሱ እራሱ የሚሰራቸው ብዙ ስራዎች አሉ፣በሌላ በኩል ደሞ የሽግግሩ መንግስት የሚያቋቋቁማቸው የተለያዩ ኮሚሺኖች (አገራዊ ምክክር፣እውነትና ዕርቅ፣ የሽግግር ግዜ ፍትህ) የሚሰሩት ስራም አለ። ከእነዚህ ኮሚሺኖች ውስጥ አንዳንዶቹ ለምሳሌ፣ አገራዊ ጉባኤው የሚወስናቸው ውሳኔዎች ለምርጫው አስፈላጊ ቅደመ ሁኔታ ስለሆኑ፣አገራዊ ምርጫ መካሄድ ያለበት ሌላ ቢቀር አገራዊ ጉባኤው ካለቀና ጉባኤው የወሰናቸው ውሳኔዎች ህጋዊ ቅርፅ ከያዙ በኋላ መሆን አለበት።

እኔ የሽግግር መንግስት ምስረታን በተመለከተ ከእምቢልታም ከፕሮፌሰር መሳይም ትንሽ የተለየ እይታ ነው ያለኝ። የፋኖ ኃይሎች አሸናፊ ሲሆኑ ወይም ብልፅግና መራሹ መንግስት ከሥልጣን ሲወገድ አገርን አረጋግቶ ወደ ምርጫ የሚወስድ የአደራ መንግስት መቋቋም አለበት የሚለውን ሃሳብ እኔ ብዙ አልገዛውም። ከብልፅግና በኋላ የአደራ መንግስት ከተቋቋመም፣ይህ የአደራ መንግስት ሥልጣኑን ማስረከብ ያለበት በህዝብ ለተመረጠ መንግስት ሳይሆን፣የታጠቁ ኃይሎችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻዎች ተደራድረው ለሚፈጥሩት የሽግግር መንግስት ነው፣ደሞም እንዲህ አይነቱ የአደራ መንግስት ከሦስት ወር የበለጠ ዕድሜ ሊኖረው አይገባም። ከብልፅግና በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ መቋቋም ያለበት እንደስሙ ኢትዮጵያን ከአምባገነናዊ ሥርዓት ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሸጋግር የሽግግር መንግስት ነው(Transitional Government)። 

ይህ የሽግግር መንግስት በአንድ በኩል ሰላምና ጸጥታን ያስከብራል፣አገሪቱ ወደ ሌላ ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ ይከላከላል፣ መደበኛ የመንግስት ስራዎችን ይሰራል፣በሌላ በኩል ደሞ ባለፉት ሃምሳ አመታት ኢትዮጵያዊያንን ለሁለት ከፍለው ያጨራረሱ የፖለቲካ ልዩነቶች ዕልባት እንዲያገኙ የሚያደርግ ዕርምጃ ይወስዳል፣ኢትዮጵያ ውስጥ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ተጀምሮ ያላለቀውን የአገረ-መንግስት ግንባታ ሂደት ከፍጻሜ እንዲደርስ ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪ ህገ-መንግስታዊ ምህንድስና ስራዎችን የሚሰሩ ተቋሞችን ይፈጥራል፣ ከእነዚህ ተቋሞች ውስጥ አንዱና ዋነኛው አገራዊ የምክክር ጉባኤ ነው። በሽግግሩ ወቅት ነጻ፣ገለልተኛና አካታች በሆነ የአገራዊ ጉባኤ መድረክ ላይ ውሳኔ ማግኘት ከሚገባቸው ጉዳዮች ውስጥ ህገ መንግስቱ፣የፖለቲካ ሥርዓታችን መሰረት ምን መሆን አለበት፣የምርጫ ሥርዓቱ፣የመንግስት ቅርፅ፣ የክልል አወቃቀር፣በህግ አስፈጻሚው፣በህግ አውጪውና በህግ ተርጓሚው አካላት መካክል መኖር የሚገባው ግኙኝነት፣ በፌደራልና በክልል መንግስታት መካከል ሊኖር የሚገባው ግኑኝነትና የሥልጣን ክፍፍል፣የመሬት ይዞታ፣አገራዊ የስራ ቋንቋ(ዎች)፣የአዲስ አበባ ጉዳይና የባንዲራ ጉዳይ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። እነዚህ  ዋና ዋና ጉዳዮች ውሳኔ ሲያገኙ፣ለምሳሌ፣የፖለቲካ ሥርዓታችን መሰረት ዜግነት ሲሆን፣ክልሎችን ከቋንቋ ባሻገር ብዙና የተለያዩ መመዘኛዎችን አስቀምጠን እንደገና በአዲስ መልክ ስናዋቅር፣በፌዴራሉ መንግስትና በክልሎች መካከል ያለው ግኑኝነትና የስራ ሃላፊነት በግልጽ ሲቀመጥ፣አብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓትን ትተን ከተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት ዝርያዎች ውስጥ አንዱን ብንመርጥና የፓርላማ ሥርዓትን ትተን ፕሬዚደንታዊ ሥርዓትን ብንከተል፣ እነዚህ ለውጦች ከዛሬዋ ኢትዮጵያ ፍጹም የተለየች ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ለማድረጋቸው ምንም ጥርጥር የለውም። እነዚህ ለውጦች እውን ሲሆኑ የሽግግር መንግስቱ በአንድ በኩል ርዕሰ ብሔርም የመስተደድሩ መሪም የሆነውን ሰው (ፕሬዘደንቱን)፣በሌላ በኩል ደሞ የላይኛውንና የታችኛውን ምክር ቤት አባላት በአገር አቀፍ ደረጃ አስመርጦ ሥልጣኑን በምርጫ ለተመረጠ መንግስት ያስረክባል።  

የሽግግር መንግስት ምስረታን በተመለከተ፣ ብልፅግና ከተወገደ በኋላ ወይም ተሽመድምዶ መጥፊያው ሲቃረብ፣ ፋኖ ሃላፊነት ወስዶና የተለያዩ ባለድርሻዎችን አሰባስቦ የሽግግር መንግስት እንዴት ይቋቋማል በሚለው ሃሳብ ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ድርድር እንዲደረግ ማድረግ አለበት። እነዚህ የተለያዩ ባለድርሻዎች ቁጭ ብለው ሲደራደሩ/ሲወያዩ፣የድርድሩ የመጀመሪያው ዙር ማተኮር ያለበት የሽግግር መንግስት ምስረታው ላይ ሳይሆን የሽግግር መንግስት እንዴት ይመሰረታል፣ የሽግግሩን መንግስት ማን ይመሰርታል፣ የሽግግሩ መንግስት የሚሰራቸው ዋና ዋና ስራዎች ምንድናቸው፣ የሽግግሩ መንግስት ሥልጣንና ሃላፊነት ምን ይመስላል፣ በሽግግሩ ወቅት ውሳኔ የሚወሰነው እንዴት ነው፣ በሽግግሩ ወቅት ህግ እንዴት ይወጣል፣ የሽግግሩ መንግስት የስራ ዘመን ምን ያክል መሆን አለበት በሚሉ ሃሳቦች ላይ ነው። እነዚህ ጥያቄዎች የሽግግሩ መንግስት ከመመስረቱ በፊት መልስ ማግኘት አለባቸው፣የሚቋቋመው የሽግግር መንግስትም ስራ የሚጀምረው የሥልጣንና ሃላፊነት አድማሱን፣የስራ ዘመኑን፣ እንዴት ውሳኔ እንደሚወስንና እንዴት ህግ እንደሚያወጣ ባጠቃላይ የሥልጣን ገደቡን በውል ከተረዳ በኋላ መሆን አለበት።

ኢትዮጵያ ውስጥ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት አለ፣ የታጠቁ ኃይሎች አሉ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፣የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አሉ፣ሲቪክ ማህበራት አሉ፣ምሁራን አሉ፣ታዋቂ ወይም ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አሉ፣ወጣቶች አሉ፣የሙያ ማህበራት አሉ፣የሃይማኖት መሪዎች አሉ፣የተለያዩ ብሔሮች አሉ፣የአካል ጉዳተኞች አሉ፣ወታደራዊ ባለድርሻዎች አሉ፣ አካባቢያዊ ልህቅ አለ(Regional Elites)፣የሴቶች ማህበራት አሉ፣የእንዱስትሪና የንግዱ ማህበረሰብ አለ። የመጀመሪያው ቁልፍ ጥያቄ እነዚህን ባለድርሻዎች አስተባብሮ ወደ ጠረቤዛ ዙሪያ የማምጣቱን ሚና ማን መጫወት ይችላል የሚለው ጥያቄ ነው። ፕሮፌሰር መሳይም እምቢልታም በግልፅ እንዳስቀመጡት የፋኖ ሚና ጎልቶ የሚታየው እዚህ ላይ ነው፣በተለይ አንድ ማዕከላዊ የፖለቲካ አመራር ያለውና ዲሞክራሲያዊ አሰራርን ባህሉ ለማድረግ ለራሱና ለአገሩ ለኢትዮጵያ ቃል የገባና ወታደራዊ የበላይነት ያለው ፋኖ የተለያዩ ባለድርሻዎችን የማስተባበሩን ሃላፊነት መውሰድ ይችላል። የሽግግር መንግስት ምስረታን በተመለከተ ሁለተኛው ቁልፍ ጥያቄ እነዚህ የተለያዩ ባለድርሻዎች እንዴት ይሰበሰባሉ የሚለው ጥያቄ ነው። ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው ባለድርሻዎች ብዙዎቹ ድርጅታዊ መልክ ያላቸው ስለሆነ እነሱን ማሰባሰብ ብዙ አይከብድም፣ ለምሳሌ፣ የታጠቁ ኃይሎች፣የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ሲቪክ ማህበራት፣የሰራተኛ ማህበራትና የሃይማኖት ተቋማት ድርጅታዊ መዋቅር ያላቸው ስለሆነ እነዚህ ባለድርሻዎች በፋኖ አስተባባሪነት ለዚህ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ ተወካዮቻቸውን መርጠው እንዲልኩ ማድረግ ይቻላል። ይህ ከሆነ በኋላ እነዚህ ባለድርሻዎች ተሰባስበው የተቀሩትን ባለድርሻዎች(ምሁራን፣ወጣቶች፣ሴቶች፣ታዋቂ/ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች) ማሰባሰብ የሚችሉበትን ዘዴ ፈጥረው አንድ አገራዊ አካል መፍጠር ይችላሉ። ይህ አገራዊ አካል ነው ቁጭ ብሎ ተወያይቶና ተደራድሮ የሽግግር መንግስት መመስረት ያለበት። ይህ ስብስብ የሽግግር መንግስት ሲመሰርት፣የሽግግሩን መንግስት አባላት ከራሱ ከስብስቡ ውስጥና አገር ውስጥና ከአገር ውጭ ከሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻዎች መካከል ይህንን ትልቅ አገራዊ ሃላፊነት መሸከም ይችላሉ ብሎ የሚተማመንባቸውን ግለሰቦች መምረጥ ይችላል። በአንድ በኩል የሽግግሩ መንግስት አባል የሚሆኑ ግለሰቦች ከሌላ አገር ጋር የማይጋሩት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ሊኖራቸው ይገባል፣በሌላ በኩል ደሞ በሽግግሩ መንግስት ውስጥ በተለያየ ደረጃ የሚሳተፉ ግለሰቦች፣ ከሽግግሩ በኋላ በሚደረገው የመጀመሪያው አገራዊ ምርጫ ላይ ለውድድር መቅረብ እንደማይችሉ በግልፅ ሊነገራቸው ይገባል።

የኢትዮጵያን ፖለቲካ በንቃት በተከታተልኩባቸው ባለፉት 40 አመታት ኢትዮጵያ እንደ ጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ደካማ መንግስት ኖሯት አያውቅም፣ወይም እንደ ጠሚ አቢይ መንግስት ኢትዮጵያን ለአገር ውስጥ የርስበርስ ውጊያ ያጋለጠና ታሪካዊ ጠላቶቻችን አፍንጫችን ስር መጥተው እንዲሰፍሩ መንገድ ያመቻቸ መንግስት የለም። ዛሬ አማራ ክልል ሦስት አመት ያስቆጠረ ጦርነት አለ፣ትግራይ ክልል ይሁን ወይም እራሱን የቻለ አገር ምንም የሚታወቅ ነገር የለም፣ኦሮሚያ ክልል የታጠቁ ኃይሎችና መሳሪያ ያነገበ ሁሉ ያሰኘውን የሚያደርግበት ህግ አልባ ክልል ነው። ጋምቤላ ውስጥ ድንበር ዘለል ታጣቂዎች በተከታታይ እየመጡ ይገድላሉ፣ይዘርፋሉ ዜጎችን አፍነው ይወስዳሉ። ይህ የሚያሳየን ኢትዮጵያ ውስጥ የዜጎችን በህይወት የመኖር ዋስትና የሚያረጋግጥ፣ዳር ድንበር የሚጠብቅና ሉዓላዊነታችንን የሚያስከብር መንግስት ባለመኖሩ፣ እንደ አገር መቀጠላችን አደጋ ውስጥ መግባቱን ነው። ዛሬ ትልቁ ጥያቄ ይህንን የተደቀነብንን ትልቅ አደጋ አስቁመን ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ፣ነጻነት፣እኩልነትና ዲሞክራሲ የሰፈነበት የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት እንችላለን ወይ የሚለው ጥያቄ ነው። ለኔ ይህ ጥያቄ በደፈናው አዎ እንችላለን ወይም አንችልም የሚል መልስ ያለው አይመስለኝም። አንችልም ካልን አገር አልባ መሆናችን ነው፣ እንችላለን ካልን ደሞ “እንችላለን” ማለቱ ብቻ በቂ አይደለምና እንዴት እንደምንችል በተግባር ማሳየት አለብን።

ኢትዮጵያ ውስጥ አገራዊ አጀንዳ ያነገበ የህልውና ትግል የሚያደርግ ኃይል አለ፣የራሳቸውን ብሔር ነጻ ለማውጣት የሚታገሉ ኃይሎች አሉ፣አልገዛም ብሎ ከአቢይ አህመድ አምባገነን አገዛዝ ጋር ትንቅንቅ ውስጥ የገባ ህዝብ አለ። አላማችን ኢትዮጵያን ማዳንና ዲሞክራሲያዊ አገር ማድረግ ከሆነ ከእነዚህ ኃይሎች ውስጥ ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ያለውን ኃይል ከመቀላቀል፣ከመደገፍ ወይም ከመርዳት ውጭ ከዛሬው የአገራችን የፖለቲካ እውነታ አንጻር ሌላ አማራጭ የለንም። ዛሬ ወደድንም ጠላን ይህ ኃይል ፋኖ ነውና፣የፋኖ እንቅስቃሴ ወደ አንድ ማዕከል እንዲመጣና ፋኖ እራሱን በዲሞክራሲያዊ ስነምግባሮች እንዲያንጽ የተቻለንን ሁሉ እንዳድርግ!!!

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English

ኤክስ ፡ @zborkena

1 COMMENT

  1. The EPRDF – PP ethnocentric political system is at its peak, and it must be replaced with a new system, or it regresses and causes destruction. Abiy’s delusional grandeur is already causing the death of millions of Amharas. The regime of Abiy Ahmed must be replaced with a transitional government. The primary mission of the transitional government is to prepare a new constitution for Ethiopia. Ethiopia needs a federal system similar to that of the USA. The transitional government must request economic and military assistance from the USA. If agreed, the USA need to send American troops as advisors to assist the transitional government. The existing Police force must continue its duties during and after the transitional government. Ethiopia’s National Defense Forces must be replaced. Bloodshed cannot buy loyalty. Power through Ethnic allegiance, and governance through intimidation and terror must come to an end.
    – In the new constitution, Ethiopia must be governed by the principles of human rights.
    – The new constitution must guarantee justice, human rights, civil rights, and private ownership of land.
    – In the new constitution, Ethiopia needs to be restructured and modeled after the USA federal system.
    – In the new constitution, member states to the new Ethiopian federation must use Amharic and their local language equally without any discrimination and limitations as working languages of their state.
    – In the new constitution, Ethnic based political organizations must be prohibited by law.
    – In the new constitution, Oromo and Tigrian politicians must be prohibited by law from participating in any separatist activities globally.
    – The new constitution must guarantee private ownership of land.
    – …

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News