
ቦርከና ዜና
በአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻ በቁጥጥር ስር የዋሉትና የቬንዙዌላው ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀረበባቸው ክስ ለመከራከር ፍርድ ቤት ቀርበዋል። በሌላ በኩል በቅርቡ በእስራኤል የሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና የተሰጣት ሶማሊላንድ አሜሪካ በቬኔዙዌላ ላይ የፈፀመችውን ወታደራዊ ዘመቻ እንደምትደግፍ አስታውቃለች።
በኒዮርክ በሚገኘው ፍርድ ቤት የቀረቡት ማዱሮ፤ “በናርኮ-ቴረሪዝም፣ ኮኬይን ወደ አሜሪካ በማስገባት፣ በጦር መሳሪያ ሽያጭ እና በአጥፊ መሳሪያ ዝውውር” በአጠቃላይ አራት ክሶች ተመስርተውባቸዋል።
በቁጥጥር ስር በዋሉ በሶስተኛው ቀን ፍርድቤት የቀረቡት ማዱሮ የክስ ዝርዝሩን ካደመጡ በኋላ “እኔ ነኝ በደል የደረሰብኝ፣ ወንጀለኛ አይደለሁም” ሲሉ ተደምጠዋል። “አሁንም የሀገሬ ፕሬዚዳንት ነኝ” ያሉት ፕሬዝዳንቱ “ባለቤቴ ሲሊያ ፍሎሬስም የቬኔዙዌላ ቀዳማዊ እመቤት ናት” ሲሉ ተደምጠዋል።
የማዱሮ የወንጀል መርማሪ ግን ፕሬዝዳንቱ በፈረንጆች 2000 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በነበሩበት ወቅት ጀምሮ “በአደንዛዥ እፅ ዝውውር ተሳታፊ እንደነበሩ” ገልጿል።
ፍርድ ቤቱ ከአመጽ ቡድኖች ጋር በመሆን በኮኬይን ንግድ የመሳተፋቸውን ወንጀል ለመከታተል ለመጋቢት 17/2026 ቀጠሮ ሰጥቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ በእስራኤል የሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና የተሰጣት ሶማሊላንድ አሜሪካ በቬኔዙዌላ ላይ የፈፀመችውን ወታደራዊ ዘመቻ እንደምትደግፍ አስታውቃለች።
ሶማሊላንድ የፕሬዝዳንት ማዱሮን በቁጥጥር ስር መዋል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያቤት በኩል ባወጣችው መግለጫ አስታውቃለች።
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “አሜሪካ በቬኔዙዌላ ላይ የፈፀመችውን ወታደራዊ ዘመቻ በትክክለኛ መርህ ላይ የተመሰረተ ነው” ብላለች። ሚኒስቴሩ እርምጃው በቬኔዙዌላ “ህገመንግስታዊ ስርዓትን ለመመለስ እና ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ለመመስረት እድል ይፈጥራል” ሲል ገልጿል።
መግለጫው አክሎም “አሜሪካ በቀጠናው ካሉ አጋሮች ጋር ተባብራ ለአለማቀፍ የጋራ ደህንነት የወንጀል ቡድኖችን ለመዋጋት ትልቅ ሚና ይጫወትላታል” ብሏል። ሚኒስቴሩ አክሎም “በቬኔዙዌላውያን የሚመራ ተጠያቂነት ያለውና ለሰብዓዊ መብት መከበር የሚቆረቆር የሽግግር መንግስት እንድትመሰረት የሶማሊላንድ ፍላጐት ጭምር ነው” በማለት ገልጿል።
ሶማሊላንድ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ስር ማዋሏን የደገፈች ብቸኛ የአፍሪካ ሀገር ናት ተብሏል።
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ : ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






