
ቦርከና ዜና
ጥቃቱ የተፈፀመው በሦስት ሀገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ላይ ሲሆን ታጣቂዎቹ ባደረሱት ጥቃት የ6 ሰዎች ሕይወት አልፏል ተብሏል። በዚሁ ጥቃት ከ10 በላይ የሚሆኑት መንገደኞች ጉዳት ደርሶባቸው ለህክምና ወደ ሆስፒታል መላካቸውንና፣ ከ50 በላይ ሰዎች በታጣቂዎቹ ታግተው መወሰዳቸውን ቦርከና ከአካባቢው የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።
እገታው የተፈፀመው በትናንትናው እለት ታህሳስ 27/2018 ዓ.ም ሲሆን፣ የታጠቁ አካላት በኦሮሚያ ክልል በገብረ ጉራቻ ፊቼ በሚወስደው መንገድ “አሊደሮ” ተብሎ በሚጠራው ልዩ ቦታ በአገር አቋራጭ ተሽከርካሪ ሲጓዙ የነበሩ በርካታ ተሳፋሪዎችና ሾፌሮችን አግተው መውሰዳቸው ታውቋል።
ተሳፋሪዎቹ መነሻቸውን አዲስ አበባ በማድረግ ወደ ደብረ ማርቆስ ሲጓዙ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን፣ አንድ ኤፍኤም አውቶብስ አሊዶሮ ታግቶ መኪናው በጥይት መመታቱን ተከትሎ፤ ብዙ መኪናዎች ለመቆም ተገደዋል ተብሏል። ሌላ ኤፍኤም አውቶብስ መስታውቱ ተሰብሮ፣ በሹፌሩ በኩል በጥይት ተበሳስቷል ታይቷል።
በአሊዶሮ የደረሰውን ጥቃት በተመለከተ የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር ሾፌሮችና በአውቶብሱ የተሳፈሩ ሰዎች መታገታቸውን አስታውቋል። አሊዶሮ በተደጋጋሚ እገታ የሚፈጸምበት አስቸጋሪ ቦታ መሆኑን የጠቆመው ማህበሩ፣ ካለው ስጋት አንፃር ተሽከርካሪዎች በአጃቢ መሄድ ጀምረው እንደነበር አስታውቋል።
ከፍቼ ጎሀፂዮን መስመር የህዝብ አውቶብስ ተሳፋሪዎች በዘራፊዎች መታገታቸውን መረጃዎች ደርሰውናል ያለው የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር፣ አሁን የምንሰማው ግን እጅግ የሚያሳዝን ነው ብሏል።
“የሾፌሮች አንደበት” የተባለውና በየእለቱ አሽከርካሪዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን የሚያጋራው የማህበራዊ ትስስር ገፅ “በኦሮሚያ ክልል ከገብረ ጉራቻ ፊቼ መሀል ባለው የመንገድ ክፍል አሊደሮ ላይ የህዝብ አውቶብስ ተሳፋሪ የተወሰኑና ሌሎች ሾፌሮች በዘራፊ ወንበዴዎች ታፍነው ተወስደዋ” ሲል ስለክስተቱ የደረሰውን መረጃ አስፍሯል።
“የታጠቁ አካላት ተሽከርካሪ ላይ ተኩስ በመክፈት፣ ተሳፋሪን በመምታት የተወሰኑትን በማፈን፣ ሌሎች የከባድ መኪና ሾፌሮችንም በማገት ይዘው መሄዳቸውን መልዕክት ደርሶናል” ያለ ሲሆን “በአቅራቢያ የነበሩ ህግ አስከባሪዎች በቦታው ደርሰው የተኩስ ልውውጥ ቢያደርጉም ሌላው ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርሱ ከመከላከል ውጭ የታገቱትን ማስጣል አልተቻለም” ሲል አጋርቷል።
ከጥቅምት 1/2018 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ሶስት ወራት በዚህ መስመር የሚደረገው ጉዞ የፀጥታ ሃይሎች እጀባ ስለሆነ ካሁን ቀደም በተሳፋሪዎች ላይ ሲፈፀሙ የነበሩት ተመሳሳይ ወንጀሎች ቁመው እንደነበር ተጠቁሟል።
በአማራ ክልል እና በአዲስአበባ መካከል በትራንስፖርትና የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ የሚፈጸሙ እገታዎችንና ግድያዎችን ለመከላከል መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች ጸጥታ ኃይሎች እጀባ መጀመራቸውን ተከትሎ፣ ጉዞ ሲደረግ ከአማራ ክልል የሚነሱ ተሽከርካሪዎች ቀን 6:00 ሰዓት ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጎሐጽዮን ከተማ እንዲሁም ከአዲስ አበባ የሚነሱ ተሽከርካሪዎች ረፋድ 4:00 ሰዓት ላይ ፍቼ ከተማ ከተሰባሰቡ በኋላ፣ የጸጥታ ኃይሎቹ በየከተማው እየተቀባበሉ እጀባውን እንደሚያካሂዱ ተገልጿል።
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ : ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






