
በአበራ ገረመው
ታህሳስ 2018 ዓ.ም
ብዙዎቻችን በሀገራችን በተፈጠረው የሰላም እጦት፣የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣የህግ የበላይነት መሸርሸር፣የፍትህ መዛባትና ስርአተ አልበኝነት ፣ቅጥ ያጣ የፖለቲካ ጡዘት፣የሰበአዊ መብት ጥሰት…ወዘተ እና እነዚህን ተከትሎ የደረሰብንን ሰቆቃ፣ግፍና ተስፋ መቁረጥ ማብቂያው መቼና እንዴት እንደሆነ መላ ጠፍቶን ግራ ተጋብተን እንቆዝማለን፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ችግሮችን ለመፍታት በኢትዮጵያ ሽግግር መንግስት ማቋቋም መፍትሄ እንደሆነ አበክረው ያቀነቅናሉ፡፡አንዳንዶች ደግሞ በተለይም የገዢ ፓርቲና ደጋፊዎች አሁን ያለው የብልጽግና አገዛዝ በጥሩ መሰረት ላይ የተገነባና የወደፊቷ ኢትዮጵያ ተአምር የሚታይባት፤ ገነት የሆነች ሀገር ለማየት የሚስችል ፍኖተ ካርታ እንዳላቸው በመንገር ከያዙት የተሳሳተ ስሌትና መስመር ፍንክች ላለማለት ይተትራሉ፡፡
ተስፋ ቆርጦ መቆዘምም ሆነ የሽግግር መግስት ማቋቋም ሆነ ህዝብን ባዶ ተስፋ መመገብ ሀገራችንን ለገጠማት ቀውስ መፍትሄ አያመጣም፡፡ በአንጻሩ ለኢትዮጵያ ችግር በንጽጽር የተሸለ አማራጭ የሚሆነው በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ማሳለጥ እንደሆነ ይህ መጣጥፍ ያበስራል፡፡ የጸሃፊው አቋም የሽግግር መንግስት ማቋቋምን የሚያቀነቅኑ ግለሰቦችና ድርጅቶችን ለመኮነን ሳሆን ሃሳባቸው የተሳሰተና አዋጪ እንዳልሆነ ለማሳየት ነው፡፡ በሌላ በኩልም ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለማደን ካለው ፍላጎት ሳይሆን ጸሃፊው ልዩ ልዩ መጣጥፎችን በማገላበጥ.፣ያለፈውን የኢትዮጵያ ሽግግር መንግስት ልምድና የኢትዮጵያን ፖለቲካ ባህል በማጤን የደረሰኩበት ድምዳሜ ነው፡፡ በቅድሚያ ሽግግር መንግስትና በሽግግር ዴሞክራሲ መካከል ያለውን ትርጓሜና ልዩነቶች አብራርቼ ወደተነሳሁበት ነጥብ ድምዳሜ እሄዳለሁ፡፡
የሽግግር መንግስትና የሽግግር ዴሞክራሲ ምንነት
የሽግግር መንግስት ማለት አንድን ሀገር ሲያስተዳድር የነበረ አምባ ገነን መንግስት በጦርነት፣በአብዮት ወይም በቀውስ ምክንያት ሲገረሰስ መንግስቱን በገረሰሱ ሀይሎች ወይም በሌሎች ጥምረት አነሳሽነት ቋሚ መንግስት አስኪመሰረት የሚቋቋም ጊዚያዊ አስተዳደር ማለት ነው፡፡ የሽግግር መንግስት ዓላማው ሰላምና መረጋጋት ማምጣት፣ የዴሞክራሲ ስርአት ማሳለጫ ተቋማት መገንባት(ለምሳሌ አዲስ ህገ መንግስት መቅረጽ)፣የስልጣን ክፍፍል መወሰን እና ለምርጫ መዘጋጀት የሚጠቀሱ ዋና ዋና ተልዕኮዎች ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር የሽግግር መንግስት ዓላማው የሀገሪቱን መጻዒ ህልውና ለመበየን የአቅም፣የጊዜና የተልዕኮ ውስንነት ያለበት ነው፡፡ የሽግግር መንግስት በባህሪው ያልተረጋጋ ነገር ግን ዴሞክራሲ ስርአት ለመገንባት ያለመ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ስኬት የሚወስነው ግን የሀገሪቱ ፖለቲካ ባህል ይሆናል፡፡
የሽግግር ዴሞክረሲ ማለት ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ካልሆነ የአገዛዝ ስርአት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ጉዞ ሲሆን ሰፋ ያለ ዓላማና ሂደት ያለው አካሄድ ነው፡፡ በሽግግር ዴሞክራሲ ሂዴት የሚካተቱ ተግባሮች መካከል አዳዲስ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማቋቋም (ለምሳሌ የፖለቲካ ፓርቲዎች)፣ የዴሞክራሲ ሂደትን የሚያጎለብቱ ኣዳዲስ የህግ ማዕቀፎችን ማኖር የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የሽግግር መንግስት ለኢትዮጵያ ችግሮች መውጫ አይሆነም ሲል በምክንያት ነው፡፡
የመጀመሪያው የሽግግር መንግስት ከኢትዮጵያ አንጻር መንታ መንገድ ነው፡፡ ወደሚፈለገው ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሊያደርስ ወይም ወደ አምባገነናዊና ወደ ከፋ ቀውስ ሊያመራ ይችላል፡፡ በዋናነት ግን ወደ አምባገነንነት ሊያመራ እንደሚችል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል አመላካች ነው፡፡ ከላይ በሽግግር መንግስት ብያኔ ላይ እንዳስመጥኩት የሽግግር መንግስትን የሚያቋቋሙ ዋንኛ ሀይሎች በትጥቅ ትግል ወይም በነውጥ መንግስትን የገረሰሱ ሀይሎች ናቸው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያሉ የታጣቂ ኃይሎች መንግስትን ይገረስሱታል ወይስ አይገረሰሱትም የሚለው ሌላ ጥያቄ ሆኖ ገረሰሱት እንበለውና እነዚህ በጠመንጃ ስልጣን የተቆጣጠሩ ኃይሎች ልክ ወያኔ ኢህአዴግ አንዳደረገው ሁሉ የሀገሪቱን ፖለቲካ በብቸኝነት ላለመቆጣጠራቸው ምን ዋስትና አለ?
ዛሬ በፕሮግራማቸው ምንም የዴሞክራሲ መርሆዎችና ስርአት ግንባታ አላማ ሳያስቀምጡ መንግስትን መገርሰስ ብቻ አለማ አድርገው ፣የአባታችን ስልጣን እናስመልሳለን…ህልም ያላቸው ታጣቂዎች ስልጣኑን ቢቆጣጠሩ ብዕር ይዘው የሚታገሉ ፖለቲከኞች እንዴት ስልጣንን የብዙሃኑ ሊያደርጉት ይችላሉ? ገሚሱ ታጣቂ ደግሞ ግልጽ ያልሆነ ዴሞክራሲያዊ ፍኖተ ካርታና ዓላማ የሌለው ሽፍታ መሳይ ድርጅት እንዴት የሽግግር መንግስቱ ወደ ዴሞክራሲ እንዲመራ አቅምና ፍላጎት ከየት ሊያመጣ ይችላል?
ከሌግ ተቋም ውስጥ ሄለን ኢንስትትዩሽን አለምአቀፍ ጥናት እንደሚያስቀምጠው “የራስን ፍላጎት ለማሳካት የኃይል አማራጭን የሚያበረታታ ማህበረሰብ ለዴሞክራሲ የታደለ አይደለም፡፡ በተቃራኒው ለዴሞክራሲ ቁርጠኛ የሆኑና በድርጅታቸውና በንቅናቄያቸው ሰፊ ህዝባዊ ተቀባይነት ያላቸው መሪዎች ለዴሞክራሲ በተ ሻለ ሁኔታ ቅርብ ናቸው” ሲል ያስቀምጣል (Mainwaring, 1989)፡፡
በኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ዴሞክራሲን እንደማያረጋግጥ የ1981 ሽግግር መንግስት ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ያነ የነበረው ሽግግር መንግስት ገና ከጅማሩ ኦ.ነ.ግ የሽግግር መንግስቱን ረግጦ ሲወጣ ወያነ የሰራዊትና የፖለቲካ አቅም ስለነበረው መድረኩን ተቆጣጥሮ በሀገሪቱ ፖለቲካ ብቸኛ ተዋናይ ሆኖ መቆየቱና የማታ ማታ በዴሞክራሳይዘሽን ሂደት ላይ አደጋ ተጋርጦ ከ27 አመት የስልጣን ቆይታ በኋላ በለውጥ ፈላጊ ሀይሎች መገርሰሱይታወሳል፡፡
የሽግግር መንግስት አዋጪ አይደለም የሚያስብለው ሌላኛው ነጥብ አሁን ሀገሪቱ ያለችበት የፖለቲካ ሁኔታ ውስብስብነት ከ1981ዱ ይበልጥ የተወሳሰበ በመሆኑ ነው፡፡ በማህበረሰባችን ውስጥ የፖለቲካ ክፍፍሉ፣መናቆሩ እጅግ በጣም ሰፍቷል፡፡ቴክኖሎጂ ግጭቶችን የማባዛት ከፍተኛ ሚና የሚጫወትበት ዘመን ላይ ደረሰናል፡፡ የህብረተሰቡ የልማት፣የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር፣የፍትህ ፍላጎት እንኳን በሽግግር መንግስት በቋሚ መንግስትም ማሟላት አደጋች ሆኗል፡፡ ነውጠኝነት በዝቷል፡፡ የውጭ ጣልቃ ገብነት ሰፍቷል…ወዘተ ወዘተ፡፡ የሽግግር መንግስት መደበኛ ሰራዊት ፈርሶ መንግስቱን በገለበጡ ታጣቂዎች ጸጥታ ማስከበሩ ስለሚከናወን ሰላምና ጸጥታ ማስከበር ራሱ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል ይሆናል፡፡ የፈረሰው ሰራዊትና ካድሬ ተመልሶ ጫካ ገብቶ የቀውስ አዙሪትን እንደገና እንድጀምር ያደረጋል፡፡ መንግስት በመውደቁ ጥቅሙ የተነካበት ሁሉ የብቀላ በትሩን በማዘጋጀት የሽግግር መንግስቱን መጻረር ይጀምራል፡፡ የቀድሞ ደህንነቶችና ፖሊስ ሀይል ስራ ስለሚያጣ ሳቦታጅ ይስፋፋል…ወዘተ ወዘተ፡፡ እነዚህን ችግሮች የሚቋቋም ሽግግር መንግስት ማቋቋም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አቅም የሚታሰብ አይደለም፡፡ ሽግግር መንግስት ተንገዳግዶ ሲወድቅ ወይም ከቁጥጥር ውጪ ሲሆንበት እንደደቡብ ሱዳን ሀገሪቱ ወደ ብተና ጫፍ ከደረሰች በኋላ አለም አቀፍ ሰላም አስከባሪ ሀይል ተሰማርቶ ሀገሪቱን እንድያረጋጋ ማድረግ ኢትዮጵያን የመሰለ ትልቅ ህዝብና ሀገር የማይመጥን ነው፡፡
ከላይ በጠቀስኩት የሁኔታዎች መወሳሰብ ምክንያት ከሽግግር መንግስት ይልቅ የዴሞክራሲ ሽግግርን መጀመሩ ይሻላል፡፡
የት ያለው የዴሞክራሲ ሽግግር ነው ከተባለ አሁን ስልጣን ላይ ያለው የብልጽግና መንግስት የዴሞክራቲክ ሽግግር እንዲቀበለውና እንዲያሳልጥ መታገል ነው፡፡ ለምሳሌ የብሄራዊ ምክክር መድረክ ወደተሟላ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲመራን መታገል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲ ባህልና እሴቶችና ልምምዶች የሚጎለብቱበትን የህግ ማዕቀፍና ተቋማት እንዲገነቡ አለም አቀፍ ማህበረሰብና የፖለቲካ ኃይሎች በጥምረት ተጽእኖ ማሳደር የመሳሰሉ ትግሎችን ማካሄድ፡፡
የሽግግር መንግስት ምስረታን የሚያቀነቅኑ ሰዎች ለሽግግር መንግስት ምስረታ ወሳኝ ሀይል ነው ብለው ተስፋ የሚያደርጉት ወይም የሚተማመኑበት የታጠቁ ሐይሎች ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለመጣል ጫፍ ላይ ደርሰዋል ከሚል እሳቤ ነው፡፡ መንግስት በትጥቅ ትግል በአጭር ዘመን እንደማይወድቅ የራሴን ምልከታ ላሳይ ፡፡ ጦርነት የኳስ ጨዋታ አይነት 120 ደቂቃ የሚጫወቱበት ሜዳ አይደለም፡፡ ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች ያላቸውን አቅም በሙሉ ተጠቅመው የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት የመጨረሻ ፍልሚያ የሚያደርጉበት በህይወት መስዋአትነትና ቁሳዊ ሀብት ኪሳራ የሚሳካ አስከፊ ፊልሚያ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በርካታ ሪሶርስ ማንቀሳቀስ የሚችል አንድ መንግስት ውስን ሀብት ማንቀሳቀስ በሚችል ታጣቂ ኃይል እንዲሁ በቀላሉ ይፍረከረካል ፤ ይሸነፋል ማለት የጦርነትን ታሪክና ስትራቴጂ አለማወቅ ይመስለኛል፡፡ በሳምንት ውስጥ አራት ኪሎ እገባለው ያለው ፋኖ ለምን ሁለት አመት ፈጀበት? የአቅም ውስንነትና ጥሶ ማለፍ ያልተቻላቸው ቀጥሎ በዲያግራም የተቀመጡ የእሳት ቀለበቶች ስላሉ ነው፡፡ አሁን በያዙት ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስትራቴጂ ለወደፊትም እነዚያን ቀለበቶች በቀላሉና በአጭር ጥሰው አራት ኪሎ በመግባት የሽግግር መንግስት ማቋቋም በምናብ ካልሆነ በተግባር ያስቸግራል ባይ ነኝ፡፡

የሽግግር መንግስት ምስረታን የሚያቀነቅኑ ሰዎች ሌላኛው ተስፋ የሚያደርጉት በህዝባዊ አመጽ መንግስት በቀላሉ ይወድቃል ወይም ተገዶ የሽግግር መንግስት ምስረታን ይቀበላል ከሚል ነው፡፡ ያለፈውን ከ2010 በፈት የተካሄደው የቄሮና ፋኖ ህዝባዊ አመጽ ተምሳሌት አድርገው ከሆነ አሁን ያለው አውድ የተለወጠ ይመስላል፡፡ እንዲያ አይነት ንቅናቄ አሁን መፍጠር ይችላሉ ወይ የሚለው መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለህዝባዊ ተቃውሞ የተመቻቸ ሁኔታ አለ ወይ? ሰማኒያ አምስት ከመቶ የሚሆነው አርሶ አደርና የገጠሩ ህብረተሰብ እንዲሁ በቀላሉ በሀገራዊ አጀንዳ ዙሪያ ማነሳሳት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ አርሶ አደር ልጆቹ፤ሚስቱና መሬቱ ካልተነካበት በኑሮ ውድነት፣በዴሞክራሲ መብት፣የባህር በር ጥያቄ ምናምን የሚነሳሳ ማህበረሰብ አይደለም፡፡ መንግስትም ይህንን ስለሚያውቅ አርሶ አደሩን ችላ ብሎ በከተሜውና በሊህቃን ላይ አትኩሮ እየሰራ ነው፡፡ አስራ አምስት ከመቶ የሚሆነው ከተሜውና ሊህቃኑ ደግሞ በጎሳ፣ በአካባቢያዊነት፣ በሀይማኖት፣በጾታ፣ በማህበራዊ ክፍፍል፣ በዕድሜ ወዘተ የተከፋለ በመሆኑ ለአንድ ሀገራዊ አጀንዳ ሆ ብሎ መንግስትን ለመገርሰስ የሚነሳበት ሁኔታ የለም፡፡ይህን አይነት ሁኔታ የባለፈው የሀኪሞች አመጽ የከሸፈበት ሂደት አስረጂ ነው፡፡
ሌላኛው የሽግግር መንግስት ምስረታ የሚቀነቀንበት ምክንያት ገዢው መንግስት ከህዝብ ተነጥሏል፣ዕድሜ አይኖረውም የሚለው ይመስላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ህዝብ ሌላ አማራጭ በመታጣቱ ብቻ መንግስት በስልጣን ላይ እንዲቆይ የሚፈቅድበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በኢትዮጵያ ባለው የጽጥታና የሰላም መደፍረስ ሳቢያ ህዝቡ ለህይወቱና ለንብረቱ ሰግቷል፡፡ ለአለም አቀፍ የትጥቅ ግጭት ህግ የማይገዙ የኢትዮጵያ ሸማቂ ሀይሎች ሲቪሎችን እንዳሻቸው ከሚያደርጉ፤ሰበአዊ መብት ከሚገፉበት ሁኔታ ለመከለል አምባገነን መንግስትም ቢሆን ለሕይወቴና ለንብረቴ ጥላ ከለላ ይሆንልኛል የሚል እምነት ስለሚይዝ መንግስት አጥፊ እንደሆነና ዴሞክራቲክ እንዳልሆነ እያወቀ ለአመጽ ሳይነሳሳ ይቆያል፡፡ በርግጥ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በአንድ ግለሰብ ህልውናውን አስጠብቆ የቆመ ነው ማለት የተሳሳተ ድምዳሜ ነው፡፡ መንግስት በሺዎች የሚቆጠር የተማረና የስትራቴጂ ምክር የሚሰጡ ምሁራኖችን ግማሹን በጥቅማጥቅም ግማሹን በብሄር ቀጥሮ ወይም አባል አድርጎ እየተደገፈ ነው፡፡ ከደርግና ከወያኔ ኢህአዴግ የተሻለ የምሁራን ስብስብም ያለው ይመስላል፡፡ መንግስት በሀብታቸውና በገንዘባቸው በተራው ህዝብ ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ፈጥረው ዝም ማሰኘት የሚችሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትላልቅ ባለሀብቶችን አጋር አድርጎ የጥቅም ተጋሪ እንዲሆኑ በማድረግ በነሱ ተደግፎ ነው ያለው፡፡ መንግስት ኩዴታ አድርገው ሊያስወግዱት የሚችሉ ጀኔራሎችን ዳጎስ ያለ የከተማ መሬትና ሌሎች በርካታ ጥቅማጥቅሞችን በመለገስ በዚህ ቀውስ በነገሰበት ጌዜ ኩዴታ እንዳይከጅሉ የሚያስችል የኩዴታ መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ ነድፎ በእነሱ እየተደገፈ ነው፡፡ መንግስት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን አሁን ባለው የአለም አሰላለፍ የሀገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም ከኢትዮጵያ ለማግኘት በሚፈልጉ የውጭ ኃይሎችም ጭምር የቴክኖሎጂ፣የፋይናንስና የፖለቲካ ድጋፍ እያገኘ ነው፡፡ ስለሆነም መንግስት በአንድ ግለሰብ ሀይል የቆመ ነው የሚለውና በአንድ ግለሰብ ላይ አነጣጥሮ ፕሮፖጋንዳ መንዛት የመንግስትን ለውጥ አያፋጥንም፡፡
አንድ ዓላማ ካለስትራቴጂ ሊሳካ አይችልም፡፡ ስትራቴጂ አራት መሰረታዊ አለባዊያንን ካላሟላ አደጋ አለው፡፡ የመጀመሪያውና መቅደም ያለበት ግብ ነው፡፡ ቀጥሎ ግቡን ማሳኪያ አቅም ፤ሶስተኛው ግቡን ማሳኪያ ታክቲኮች ናቸው፡፡ አራተኛው እነዚህን አጣምሮ ከመስራት ጎን ለጎን የሚያጋጥሙ አደጋዎች(risks) መተንተንና ማስወገድ ናቸው፡፡ ሽግግር መንግስት አንድን አላማ ማሳኪያ ሂደት ሆኖ ሳለ እንደግብ የሚቀነቀንበት አካሄድ ስህተት ነው፡፡ የሽግግር ዴሞክራሲ ግን በራሱ ግብም ሂደትም ስለሆነ ለኢትዮጵያ ተመራጭ አካሄድ ይሆናል፡፡
ሽግግር መንግስት ማለት ሁሉም ነገር ከተንኮታኮቴ በኋላ፣አስካዛሬ ሀገሪቱ አነሰም በዛ ባሏት አነስተኛ ኢኮኖሚ የገነባቻቸው ደካማ የዴሞክራሲ ተቋማትና ህጎች በዜሮ ተባዝተው ከባዶ የሚነሱበት አካሄድ ስለሆነ ኢትዮጵያን ወደባሴ ቀውስና ትርምስ የሚያስገባ አማራጭ ነው፡፡ ለምሳሌ ህገ-መንግስቱ ዴሞክራቲክ በሆነ መንገድ ካልተሻሻለና ተቀዶ የሚጣል ከሆነ የሚፈጠረውን አደጋ እናስብ፤ የሀገሪቱን ጸጥታ ባለው ደካማ ፕሮፈሸናሊዝምም ቢሆን ጸጥታ በማስከበር ላይ ያለው መከላከያ ሰራዊት ፈርሶ በምትኩ አዲስ የሸምቅ ተዋጊዎች ጸጥታን ያስከብሩ ማለት በ1984 ዓም. በኢትዮጵያ የነበረውን ስርአተ አልበኝነት በባሴ ሁኔታ ማስቀጠል ነው፡፡ ስለሆነም የመከላኬያ ሰራዊት በዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሂዴት ገለልተኛና ከፖለቲካ ፓርቲ ቁጥጥር ውጪ የሚያደርግ ስራ በጥንቃቄ መሰራት አለበት አንጂ ማፍረስ አያስፈልግም፡፡ በተለይም ከተራ ወታደር አስከ መስመራዊ መኮንኖች ያለው ወታደር መፍረስ የለበትም፡፡ የታጠቁ ሀይሎች ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሂዴት በዲዲ አር መርህ መሰረት ሲስተናግዱ የፖለቲካ መሪዎቻቸው ደግሞ ወደ ፖለቲካው ይቀላቀላሉ ማለት ነው፡፡
ዴሞክራቲክ ሽግግር ፕሮሰስ ዛሬውኑ መጀመር ይቻላል ነገር ግን ሽግግር መንግስት መቼ እነደሚቋቋም፤ በዚህ እርግጠኝነቱ ይበልጥ በማይቻልበት ዘመን ማወቅና መወሰን አይቻልም፡፡ ነገር ግን የሽግግር ዴሞክራሲ አሁኑኑ መጀመር ስለሚቻል ዛሬውኑ መጀመር ይቻላል፡፡
የሽግግር መንግስት ምስረታና አፈጻጸም የረሱ ተግዳሮቶች እንዳሉት ሁሉ ወደዴሞክራሲ ሽግግርም በፈተናዎች የተሞላ ነው፡፡ የሽግግር ዴሞክራሲ ከአምባ ገነንነት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር በመሆኑ በርካታ ተግዳሮቶች የታጀበ ነው፡፡ በአለም ላይ በቀላል ውጣ ውረድ የዴሞክራሲያዊ ሽግግር ያሳለጠ ሀገር የለም፡፡ የዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት ግራ መጋባትና እርግጠኛ አለመሆን ያጋጥማል፡፡ በዴሞክሪሲ ሽግግር ወቅት አንዳንድ መጥፎ አጋጣሚዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የሽግግር መንግስት ከሚያስከፍለው ዋጋ የዴሞክራሲ ሽግግር የሚያስከፍለው ዋጋ የተሸለ ነው፡፡ ቢያንስ ሀገሪቱ እየታመመችም ቢሆን ህልውናዋን ታስቀጥላለች፡፡
የሽግግር ዴሞክራሲ ለማሳለጥ የሚያግዙ ቅድመ ሁኔታዎች፤
- በሊህቃን መካከል የሚደረግ ውይይትና ድርድር፤
- በመንግስትና በተቃዋሚ ሀይሎች መካከል የሚደረግ መስተጋብርና ድርድር፤
ከአምባገነንት ወደ ዴሞክራሲ ሚደረገውን ሽግግር ስኬት የሚወስኑ ጉዳዮች የሚከተሉ ናቸው፡-
- የህግ የበላይነት ተቀብለውና አምነው የሚንቀሳቀሱ ተቋማት መኖር፤
- ልዩ ልዩ ፍላጎቶች ያሏቸው ልዩ ልዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነትና ህግን መሰረት አድርገው መንቀሳቀስ፤
- ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚደረግ ድጋፍ፤
- በተጨማሪም በተለያዩ ማህበረሰብ ቡድኖች መካከል መቻቻልና፣ንግግር መኖር ግጭትን ለማስወገድ ወሳኝ ነው፡፡ እነዚህ ሲሟላ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር የተመቻቸ ይሆናል፡፡
- ሁሉም ሀይሎች ገዢ ፓርቲን ጨምሮ ከሴራ ትንተና የጸዳ ሃቀኛ ፖለቲካና ርዕዮተ አለም ማራመድ፤
ሳጠቃልል በኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ምስረታ ከማቀንቀን ይልቅ የሽግግር ዴሞክራሲን ማቀንቀን የተሻለ አማራጭ ነው፡፡ የሽግግር መንግስት እንመስርታለን ብሎ ዓላማ ነድፎ ከመንቀሳቀስ ይልቅ የዴሞክራሲ ሽግግርን ግብ አድርጎ መታገል ለሂደቱ የሚከፈል ዋጋ ቀላል ባይሆንም ተመጣጣኝና የሀገሪቱን ህልውና የሚያስቀጥል ይሆናል፡፡
የሽግግር ዴሞክራሲ እንዴት ይጀመር?
- በመንግስትና በተቋዋሚ ኃይሎች፣በመንግስትና በታጠቁ ኃይሎች መካከል ውይይትና ድርድር መጀመር፤
- በተቃዋሚ ኃይሎች መካከል በዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሂዴት የጋራ መግባባት መፍጠር የሚያስችል ውይትና ድርድር መጀመር፤
- በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁሉም አፈንጋጭ ቡድኖች ወደ ፖለቲከው አውድ ተመልሰው ሰላማዊ ትግል እንድጀምሩ ውይይትና ድርድር መጀመር፤
- የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር እውነተኛ የዴሞክራሲ ሽግግር የሚያሳልጥ እንድሆን የዴሞክረሲ መርሆዎችን መሰረት ያደረገ ውሳኔ ሃሳብ፤የተቋም ግንባታና የድርድር ሀሳቦች ማፍለቅ፤
- መንግስት ሆደ ሰፊ በመሆን ሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገር ያሉት የፖለቲካ ኃይሎች በዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሂደት ተሳታፊ እንዲሆኑ ማመቻቸት፤
- በውጪ ያሉና በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ኃይሎች መንግስት በሚያመቻቸው የዴሞክራሲ ሽግግር ተሳታፊ ለመሆን ዝግጁነትን ማሳየት፤
- የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ፣
- የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳይሸማቀቁ በድፍረት የዴሞክራሲ ሽግግርን መደገፍ፣መምራትና መሳተፍ አሁኑኑ የሚጀመሩ የሽግግር ዴሞክረሲ እርምጃዎች ናቸው፡፡
- የዲያስፖራው ማህበረሰብ የዴሞክራሲ ስርአት እሴቶች በተግባር እያየና እየኖረበት ያጣጣመ በመሆኑ የዴሞክራሲ ሽግግርን የሚያጠናክሩና የውይትና የንግግር ባህል እንዲጎለብቴ የሚያግዙ እርምጃዎችን መውስድና መደገፍ ይጠበቅበታል፡፡
አሁን የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሺዎች የሚቆጠሩ አጀንዳዎች የሰበሰበ ቢሆነም ሁሉም አጀንዳዎች በብሄራዊ ደረጃ የሚፈቱ ሳይሆኑ አብዛኛዎች በክልል፣በዞንና በማህበረሰብ ደረጃ እልባት የሚያገኙ ናቸው፡፡ እነዚህ አጀንዳዎች ተመርምረውና ተጨምቀው ውይይት ከተደረገ በኋላ በብሄራዊ ደረጃ የሚከተሉት ውጤት መገኘት መቻል አለበት፡-
- የሽግግር ዴሞክራሲን ማሳለጥ፣
- ዘላቂ ሰላም ማስፈን፤
- ለልማት እንቅፋት የሆኑ ሳንካዎች በማስወገድ ፈጥን ልማት ማረጋገጥ፤
- አስተማማኝ የህግ የበላይነት ማረጋገጥ፤
- ገለልተኛ የፍትህና የጸጥታ ተቋማት ማቋቋም፤
- በመግባባት ላይ የተመሰረተ ህገ መንግስታዊ ሪፎርም ማካሄድ፤
- የፌደራል ስርአት እንከኖች አርሞ ዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝምን ማጠናከር፤
- ለግጭት መነሻ የሆኑ የሰንደቅ ዓላማ፣ የፌደራል ቋንቋ ፣ብሄራዊ መዝሙርና የመንግስት መቀመጫ ዋና ከተማ ውዝግቦች ላይ መግባባት መፍጠር፤
- የትጥቅ ግጭት መነሻ የሆኑ ችግሮችን ፈትሾ በመፍታት የጠመንጃ አፈሙዝ ማዛቅዘቅ፤
- የሽግግር ፍትህን ማስፈን፤
- ደም በተቃቡ ህዝቦችና ቡድኖች መካከል እርቀ ሰለማ ማውረድና የመሳሰሉት ዋና ዋና ውጤቶች ሊሆኑ ይገባል፡፡
እነዚህ ውጤቶች ካልተገኙ ብሄራዊ ምክክሩ ትርጉም አልባ ልፋት ስለሚሆን በጥንቃቃ መመራት አለበት፡፡ የምክክር መድረኩን ውሳኔ ተቀብለው ለመፈጸም ገዢው መንግስትና ተቃዋሚ ሀይሎች በትጥቅ ትግል ላይ ያሉትንም ጭምር ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህን ውጤቶች ላይ ገንቢ ሚና የማይጫወት አካላትን አለም አቀፍ ማህበረሰብና ህዝቡ በመታዘብ መግሰጽ ይኖርበታል፡፡
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena







ያቀረብከው ፅሁፍ ረጅምና ውበትን የተላበሰ ከመሆኑም ባሻገር ፣ ለተለያዩ አንባቢዎች የተለያየ መልዕክትን ለማስተላፍ የተዘጋጀ ነው ።
ኦሮሞ በጦርነት አሸንፎ ስልጣን አልያዘም ። ኦሮሞን ወደ አዲስ አበባ ቤተ መንግህት ያመጣው ትግሬ ነው ። የትግሬና የኦሮሞ ህብረት መሰረቱ ለአማራ ያላቸው ጥላቻና የመገንጠል ፍላጎታቸው ነው ።
ተወደደም ተጠላም ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የሽግግር መንግስት ነው ። ይህንን የሽግግር መንግስት ፣ ብልጽግና እራሱ ማቋቋም ይችላል። የዴሞክራሲ ሽግግር ወይም የሽግግር ዴሞክራሲ ያልከው አካሄድ ፣ የኦሮሞን የበላይነት በማረጋገጥ ተጠናቋል ። በኢትዮጵያ የሚቋቋመው የሽግግር መንግስት ከሚሰራቸው ስራዎች አንዱ አዲስ ህገመንግስት ማዘጋጀት ነው ።
በኢትዮጵያ አዲስ ህገመንግስት :
– የኢህአዴጉ – ብልፅግና ህገመንግሥት ይታገዳል
– ኢትዮጵያ በአዲስ የፌደራል አደረጃጀት ትዋቀራለች። አማርኛ የፌደራሉ ቋንቋ ይሆናል ።
– በአዲሱ ፌደሬሽን የሚደራጁ ክልሎች ፣ አማርኛንና የክልላቸውን ቋንቋ በእኩልነት እና ባለማዳላት የክልላቸው የስራ ቋንቋ አድርገው ይጠቀሙበታል ።
– በጎሳ ወይም በብሄር የሚደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች በህግ ይታገዳሉ።
– አሁን ያለው የፌደራልና የክልል ፖሊሲ ስራውን ይቀጥላል ።
– ከ አንድ ብርጌድ የማይበልጥ የአሜሪካን ወታደር የሽግግር መንግስቱን በአማካሪነት እንዲያገለግል ጥያቄ ለአሜሪካን መንግሥት ይቀርባል
– የሀገር መከላከያ ሰራዊት ፈርሶ በአዲስ ይደራጃል
– የኦሮሞና የትግሬ ፖለቲከኞች ፣ በማንኛውም የመገንጠል እና የዘረኝነት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳይሳተፉ በህግ ይታገዳሉ።
– መሬት የግል ይዞታ እንዲሆን ይደረጋል
– …
ለህልውናው እና ኢትዮጵያን ለማዳን እየታገለ ያለውን የአማራ ህዝብ ፣ ተስፋ እንዲቆርጥ ወይም እንዲፈራ ለማድረግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች የሚያሳዩት ብልጽግና እራሱ መፍራቱን ነው ።