
ቦርከና ዜና
በጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር እና በጄነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ (ሔመቲ) ከሚመራው የቀድሞው የጃንጃዊድ ሚሊሺያ የአሁኑ የፈጥኖ ደራሽ ሀይል የገቡበት ጦርነት ሶስተኛ አመቱን ሊደፍን ሁለት ወራቶች ቀርተውታል።
ባለፉት 1000 ቀናት ውስጥ በከፍተኛ አውዳሚ ጦርነት የምትገኘው ሱዳን በአለም ላይ እጅግ አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ ያስተናገደች ሀገር ሁናለች ተብሏል።
ከ33.7 ሚሊየን በላይ ሰዎች፣ ወይም ከሶስት የሱዳን ዜጎች ሁለቱ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
ጦርነቱ ማህበራዊ ኑሮን እና አገልግሎቶችን መስተጓጎሉ ተገልጿል። ከ70 – 80 በመቶ የሚሆኑት ሆስፒታሎች ወድመዋል ተብሏል።
በጤና ተቋማት ላይ በደረሰው ውድመት 65 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ህዝብ ለጤና አገልግሎት ችግር ተጋላጭ ሁነዋል ተብሏል።
ሱዳን በአለም ላይ የምግብ ቀውስ ከተጋረጠባቸው ሀገራት የተመደበች ሲሆን፣ 21.2 ሚሊየን ህዝብ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋላጭ መሆናቸውንና የህይወት አድን እርዳታ ተጠባባቂ ሁነው እንደሚገኙ 13 የእርዳታ ድርጅቶች መግለፃቸውን አጂያንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።
ዘገባው አክሎም በጦርነቱ የተፈናቀሉ ሰዎች በጣም አጣብቂኝ ወደሆነና ደህንነታቸው ወዳልተጠበቀ ስፍራ ተፈናቅለዋል የተባለ ሲሆን፣ ይህም ለፆታዊ ጥቃት እና ለድንገተኛ ወረርሽኝ ተጋላጭ ሁነዋል ብሏል።
የተፈናቃዮችን ፍላጐት ለማሟላት የበጎ አድራጊ ተቋማት ድጋፍ በመቀነሱ በቂ እርዳታ ማዳረሱን አስቸጋሪ አድርጎታል። ስደተኞቹ መሰረታዊ ፍላጎት ማለትም በቂ ምግብ፣ መጠለያ እና የመጠጥ ውሃ እጥረት አጋጥሟቸዋል ሲል የእርዳታ ድርጅቶቹን መረጃ ዋቢ ያደረገው የአጂያንስ ፍራንስ ፕረስ ዘገባ ያመላክታል።
ወርልድ ቪዥን የማያስተዳድረውና በምስራቅ ዳርፉር የሚገኘው አል ናከል የስደተኞች ካምፕ ከ22,500 በላይ ተፈናቃዮችን የያዘ ሲሆን፣ ካምፑ መሰረታዊ ፍላጐች የተሟሉለት አለመሆኑ ችግሩ መባባሱን አስታውቋል።
በ1000 ቀናት ውስጥ በሱዳን ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች (GBV) በመበራከታቸው ጥቃቱ ለደረሰባቸው ታካሚዎች የህክምና ፍላጐት ከ2023 ወዲህ በ288% ጨምሯል ተብሏል።
በሱዳን የርስበርስ ጦርነት ባስከተለው ቀውስ የጦርነቱን ገፈት ያልቀመሰ ዜጋ የለም ሲል የዘገበው ደግሞ ስካይ ኒውስ ነው። ስካይ ኒውስ አሀዛዊ ሰነዶችን በመመርኮዝ ባወጣው ዘገባ ከ70 በመቶ በላይ የሱዳን ህዝብ እርዳታ ፈላጊ መሆኑን ጠቁሟል።
በዚህ ጦርነት በተለይ የፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች አሰቃቂ የጦር ወንጀሎችን እንደሚፈፅሙ ተገልጿል።ከተሞችን በቦምብ በመደብደብ በገበያ ስፍራዎች እና ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች በሚፈፅሟቸው የአየር ላይ ጥቃቶች ንፁሃን ዜጎች ህይወታቸው አልፏል ተብሏል።
ከዚህ ባለፈም ይህ ቡድን በመቶዎች የሚቅጠሩ ጋዜጠኞችን፣ የህክምና ባለሙያዎችን እና ፖለቲከኞችን አግቶ ወደማይታወቅ ስፍራ መውሰዱ ተገልጿል።
በሱዳን ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ቀውስ እያስከተለ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ቀጠናዊ፣ አህጉራዊ እና አለማቀፍ ተቋማት የበኩላቸውን ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካ ቀርቷል።
የአፍሪካ ህብረት የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ የገቡበትን ጦርነት እንዲያቆሙ ቢያሳስብም ጥሪው በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት አላገኘም። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ ያደረገው ስብሰባም የሱዳንን ጦርነት ማስቆም አልቻለም።
ተቋማቱ ተፋላሚ ሀይሎች ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንድደርሱና ለተፈናቃዮች ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም በጦርነት የሚገኙት ሀይሎች አወንታዊ ምላሽ አልሰጡም።
ጦርነቱ አድማሱን እያሰፋ የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ላለፉት ሶስት ወራት ኮርዶፋን ጨምሮ ሶስት ዋና ዋና ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን መቆጣጠር ችሏል። የሀገሪቱ ጦር በበኩሉ ዋና ከተማዋን ካርቱምን ከሁለት አመት በኋላ ከአማፂ ሀይሎች አስለቅቆ ዳግም መቆጣጠር ቢችልም፣ አሁንም መቀመጫውን ከፓርት ሱዳን አልቀየረም።
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ : ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






