
ቦርከና ዜና
ይህን ተከትሎ የሚኒሶታ ግዛት ገዥ ቲም ዋልዝ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የፌደራል ኃይሎችን ከግዛቱ እንዲያስወጡ ጥሪ አቅርበዋል። በአሜሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈፎች የስደተኞች አያያዝን በመቃወም አደባባይ ወጥተዋል።
በሚኒሶታ የቅዱስ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ቄስ ፉሮስ ቶልጋርድ፣ “ፖሊስ በሚኒሶታ 100 የሚጠጉ ሰልፈኞችን በቁጥጥር ስር አውሏል” ብለዋል። “በከተማዋ 700 የሚደርሱ የንግድ ሱቆችና ትምህርት ቤቶች በአመፁ ምክንያት ተዘግተዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
“የሀይማኖት አባቶች በአየር መንገድ ተገኝተን ስደተኞች እንዳይመለሱ ለመማጸን ነው የመጣነው” በማለት ገልፀዋል። “ሚኒሶታ አካባቢ የተፈጠረው ህሊና የማይፈቅደው ነገር ነው” ያሉት ቄስ ቶልጋርድ “በዚህ ሁኔታ መኖር ውስብስብ ችግር ፈጥሮብናል” ነው ያሉት።
ቄስ ቶልጋርድ “ፖሊስ ወደመጣንበት እንድንመለስ ቢጠይቀንም እኛ ከስደተኞች ጎን መቆማችንን ለማሳየት እዚሁ ድምፃችንን እያሰማን ነው፣ ለውጥ ካላየን አንመለስም” ብለዋል።
የኢምግሬሽን እና ከስተም ኢንፎርስመንት (ICE) ፖሊስ የሁለት እና የአምስት አመት ህፃን በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ስደተኞችን ይበልጥ ስጋት ላይ መደቀኑ ተገልጿል።
የአሜሪካ የፌደራል ኃይሎች በቀናት ልዩነት ከቅዳሜ ጀምሮ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ የሶስት ሰዎች ህይወት አልፏል።
ሚኒሶታ ውስጥ የምትገኘው ሚኒያፖሊስ ከተማ ነዋሪዎች እና አመራሮች ከፌደራል የጸጥታ አካላት ጋር ግጭት ውስጥ ገብተዋል ተብሏል። የሚኒሶታ ገዢ ቲም ዋልዝ፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሚኒሶታ ውስጥ ያሰማሯቸውን “3,000 ያልሰለጠኑ ኃይሎች” እንዲያስወጡ ጠይቀዋል።
ቅዳሜ ዕለት ከፌደራል ኃይል በተተኮሰ ጥይት የተገደለው አሌክስ ፕሪቲ የተባለው ግለሰብ የጽኑ ሕክምና ክፍል ነርስ እንደነበር ተገልጿል። የሚኒያፖሊስ ከተማ ነዋሪዎች የ3 ዓመቱን አሜሪካዊ ግድያ በመቃወም ሰልፍ ወጥተዋል።
ሰልፈኞቹ መጀመሪያ ላይ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተው የነበረ ቢሆንም ኋላ የተደረጉት ተቃውሞዎች ግን ሰላማዊ ሆነው ቀጥለዋል። ነዋሪዎች ከሰልፍ እና ተቃውሞው በተጨማሪ መንገዶች ላይ ሟቹን ግለሰብ የሚዘክሩ መታሰቢያዎችን እያኖሩ ነው።
የሚኒሶታ ግዛት እና የፌደራል ባለሥልጣን የግለሰቡን ሞት በተመለከተ በጋዜጣዊ መግለጫዎች የሚሰጧቸው ማብራሪያዎች አንዳቸው ከሌላው ጋር የሚጣረሱ ናቸው።
ሟቹ ግለሰብ ይዞት ነበር ከተባለው ሽጉጥ ጋር በተያያዘም የመሣሪያ መያዝ መብት ጉዳይ የሕግ አውጪዎችን አቋም ከፋፍሏል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር የሆኑት ክሪስቲ ኖም ፕሪቲ፤ ግለሰቡ የተተኮሰበት ሽጉጥ “እያወዛወዘ” ስለነበር ነው ሲሉ ከስሰዋል። ሽጉጡ በሕጋዊ መንገድ የተመዘገበ እንደሆነ የሚናገሩት የሚኒሶታ ግዛት ባለሥልጣናት ግን፤ ሟቹ መሣሪያውን እያወዛወዘ እንዳልነበረ እና የፌደራል ኃይሎች የተኮሱበት ሽጉጡን ከወሰዱ በኋላ መሆኑን ገልጸዋል።
በድርጊቱ ውስጥ የተሳተፉት የፌዴራል ኃይሎች አሁንም በሥራ ላይ ቢሆኑም ለደኅንነታቸው ሲባል ከሚኒያፖሊስ እንዲወጡ መደረጉን የድንበር ጥበቃ አዛዥ የሆኑት ግሬግ ቦቪኖ ተናግረዋል። የግለሰቡን ሞት በሚያሳዩት ቪዲዮዎች ላይ የታየውን ሁኔታ በሚመለከት ግን ቀጥተኛ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የሚኒሶታ ገዢ ቲም ዋልዝ በበኩላቸው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያሰማሯቸውን “3,000 ያልሰለጠኑ ኃይሎች” ከግዛቱ እንዲያስወጡ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል። “እኛ በሰላም እናምናለን፤ [የፌደራል ኃይሎች] ሌላ ሰው ከመግደላቸው በፊት ዶናልድ ትራምፕ እነዚህን 3,000 ያልሰለጠኑ ኃይሎች ማስወጣት እንዳለባቸው እናምናለን” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአንጻሩ የሚኒሶታ ባለሥልጣናት ግዛቱ ውስጥ የሚካሄደውን የፋይናንስ ማጭበርበር ምርመራ ጋር በተያያዘ “የወንጀል ሽፋን” ውስጥ ተሳትፈዋል ሲሉ ያለማስረጃ ከስሰዋል። የዋይት ሃውስ የፕሬስ ፀሐፊ ካሮሊን ሌቪትም የሚኒሶታ ገዢ “ዋልዝ ሁከትን ይፈልጋል” ወንጅለዋል። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ከዋልዝ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽም ሆነ የወሰዱት እርምጃ የለም።
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






