
ቦርከና ዜና
በአካባቢው ስላለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ እና የኮማንድ ፖስት መፍረስ ከፌደራሉም ሆነ ከአማራ ክልል መንግስት የተሰጠ ማብራሪያ የለም።
የህወሓት ታጣቂዎች በራያ እና አላማጣ የመንግስት መስሪያቤቶችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ አፈናና ዝርፊያ እየፈፀሙ ነው ተብሏል።
በአላማጣ ከተማ የነበረው ኮማንድ ፓስት ከተማውን ለቆ መውጣቱን ሁለቱም የከተማዋ የቀድሞ ከንቲባዎች እና ነዋሪዎች አረጋግጠዋል።
ከተማዋ በኮማንድ ፓስት ከመተዳደሯ በፊት ከንቲባ የነበሩት አቶ ኃይሉ አበራ በሰጡት ቃል አለማጣ ያለው ኮማንድ ፓስት ዛሬ ለቋል፤ ሰውም ሌሊቱን እየታፈነ ነው ያደረው ብለዋል።
ሀይሉ ሰው እንደአዲስ እየተፈናቀለ እግሩ ወደመራው እየሄደ ነው። ይህ የሆነው ሌሊት ላይ ነው ብለዋል። መከላከያና የፌደራል ፓሊስ የአላማጣ ከተማን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ፣ የህወሓት ታጣቂዎች ንጹሐን ሰዎችን አፍነው መውሰድ እና ማሰር እንደጀመሩ አብራርተዋል።
በተመሳሳይ መልኩ በቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ወቅት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ ተደርገው የተሾሙት አቶ ዝናቡ ደስታ “ጦርነትን ብቻ እንደመፍትሄ አድርጎ የሚወስደው የህወሓት ቡድን አሁንም ወደጦርነት ሊያስገባን ላይ ታች እያለ ነው” ሲሉ ወንጅለዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭት መቀስቀሱን የገለፁት ዝናቡ ለምሳሌ በወጀራት አካባቢ ዛሬ ጠዋት የመድፍና ሞርታር ተኩስ ልውውጦች ነበሩ። ይሄንን ትንኮሳ የጀመረው ሕወሓት የሚመራው ቡድን ሠራዊት ነው ብለዋል።
አቶ ዝናቡ አሁን በአላማጣ ለተፈጠረው ችግር ሶስት አካላትን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን፣
የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የህወሓት ድርጅት አመራሮች እና ከፍተኛ የሠራዊት አመራሮችን “እነዚህ ናቸው ትግራይ ላይ ጦርነት እንዲነሳ የሚፈልጉት” በማለት ከሰዋል።
እነዚህ ሶስት ወገኖች ከግጭቱ በፊት በነበሩ ቀናቶች ተሰብስበው የአላማጣ ኮማንድ ፓስት ኃይልን አፍነው ለማስቀረት ዝግጅት ሲያደርጉ መረጃው ደርሷቸው ነው መከላከያና የፌደራል ፓሊስ ሌሊት ላይ ሙሉ በሙሉ ከተማው ለቀው የሄዱት ሲሉ አስረድተዋል።
አቶ ዝናቡ የኮማንድ ፖስት አካላት
ከተማውን ለቀው በወጡበት ሰዓት ሌሊቱን ዝርፊያ ነው ሲካሄድ እንደነበር በመግለፅ የአቶ ሀይሉን ሀሳብ ተጋርተዋል። በኮማንድ ፓስት ሲጠበቅ የነበረው የመንግስት መስሪያ ቤት ተዘርፏል። የግለሰቦች ሀብትም እየተዘረፈ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
እንደ አቶ ዝናቡ ገለፃ የተለየ የፓለቲካ አመለካከት አላቸው ያሏቸውን ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውን አብራርተዋል። የህወሓት ታጣቂዎች በአካባቢው የጦርነት ወሬዎች እየተወሩ ነው ህዝቡ እንዲሸበር እና እንዲሸማቀቅ፣ ከተማውን ለቆ እንዳይወጣም ኬላዎች ተዘግተዋል ብለዋል።
ከፍተኛ የጦርነት ስጋት እንዳለ በመግለፅ፣ ብረት የታጠቁ ቀማኛዎች ተደራጅተው የፈለጉትን የሚያደርጉበት ድባብ ነው በከተማዋ ያለው፣ ህዝቡ ትልቅ ጭንቀትና ስጋት ውስጥ ነው። በተለይ ህፃናት፣ እናቶች፣ ሽማግሌዎች ሲሉ ከተማዋ ያለችበትን ሁኔታ አስረድተዋል።
በአካባቢው የሚስተዋሉ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በመንግስትና በህወሓት መካከል የለየለት ሌላ ዙር ጦርነት እንዳያስከትሉ ስጋት እንደፈጠረ፣ በትግራይ ክልል በተለያዩ ከተሞችም “እስራት፣ አፈና” እንደተበራከተ በመግለጽ፤ የፌደራል መንግስት አስቸኳይ መፍትሔ በመፈለግ ህዝቡን ከፊቱ ከተጋረጠበት ከባደሰ መከራ እንዲታደገው ጥሪ አቅርበዋል።
በተያያዘ መረጃ የህወሃት ታጣቂዎች ዛሬም በጠለምት በኩል በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጦርነት ሲያካሂዱ መዋላቸው
ተሰምቷል።
በዚህ ግጭት የሰው ህይወት ማለፉ የተገለፀ ሲሆን፣ የነዋሪው እንቅስቃሴ እንደተገደበና፣ የአማራ እና ትግራይ ክልሎችን የሚያገናኙት መንገዶች መዘጋጀታቸው ተረጋግጧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ ክልል ሲያደርገው የነበረው በረራ ዛሬም ለሁለተኛ ቀን ተቋርጧል ተብሏል። ከአዲስ አበባ ወደትግራይ ክልል ሁሉም ከተሞች የሚያደርገውን በረራ በትናንትናው እለት ያቆመው አየር መንገዱ እስካሁን በጉዳዩ ላይ ይፋዊ መግለጫ አልሰጠም።
በሌላ በኩል የክልሉ ነዋሪዎች ጦርነት ዳግም ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ከባንክ ብር ለማውጣት በመፈለጋቸው ረጃጅም ሰልፎች ተስተውለዋል ተብሏል። ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ስለገጠማቸው በካሽ ሲሰጡት ከነበረው 50 ሺህ ወደ 5 ሺሕ ዝቅ መደረጉን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English






