
ጋዜጣዊ መግለጫ
ከአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ የተላለፈ
አፋብን አረመኔው የብልፅግና አገዛዝ የአማራን ህዝብ ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል የጀመረውን ጦርነት ለማሳካት ይችል ዘንድ በርካታ አረመኔያዊ ተግባራትን ሲፈፅም መቆየቱ ይታወቃል ሲል ያስታወሰ ሲሆን፣ የአማራን ህዝብ ያለ ልዩነት ለመፍጀት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እየተጠቀመ ያለው አገዛዝ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጂኦ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶችን በማገልገል በፈጠረው የማውደም አቅም ተማምኖ በከፈተው ጦርነት ራሱ እየተለበለበበት ይገኛል ብሏል።
የአማራን ህዝብ ለማጥፋት ከሚጠቀምባቸው ስልቶች መካከል ነባሩን የብአዴን መዋቅር በመጠቀም ባሰባሰበው የምሊሻ እና የአድማ ብተና ኃይል ከፋኖ ጋር እንዲዋጋ እና ህዝባችን በሁለት ጎራ ተሰልፎ እንዲጠፋፋ የሞከረበት መንገድ አንደኛው ነው ያለው ቡድኑ፣ በአንድ ህዝብ መካከል እና በኢትዮጵያዊያን መካከል እንዲሁም ቀጠናዊ ጦርነቶችን በማስነሳት ለአፍሪካ ቀንድ የቀውስ ዘበኛ የሆነውን አገዛዝ በወንድማማችነት እና በጥበብ በማስወገድ የጋራ መንግስት መመስረት እንደሚገባን በተደጋጋሚ ጥሪወች ስናስተላልፍ የቆዬን መሆኑ ይታወቃል ሲል ገልጿል።
በተለይም ከሰሞኑ ደግሞ ጠላት በአንድ በኩል የህዝብ መገናኛ መስመሮችን በመዝጋት ንፁሃን ላይ ጭፍጨፋ እያደረገ በሌላ በኩል ደግሞ ብሔራዊ አጀንዳ ያለው እና ለሀገር ብሔራዊ ተልዕኮ የተሰለፈ በመምሰል የሚያደርገውን የማደናገሪያ ስልት በንቃት በመከታተል የፋኖ ሰራዊት በወሰዳቸው እርምጃወች ወራሪው የብልፅግና ኃይል ከፍተኛ ትርምስ ውስጥ ገብቷል ነው ያለው።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ መወለድ ያስገኘው የአንድነት መንፈስ ለተገኙ ወታደራዊ ድሎች ቁልፍ ሚና ተጫውቷል ካለ በኋላ፣ የድላችን ምስጢር ያለው አንድነታችን ላይ መሆኑም በተግባር ተረጋግጧል፣ ድርጅታዊ አንድነታችንን በጠበቀ መልኩ ከኢትዮጵያዊያን እና ከቀጠናው ኃይሎች ጋር የሚደረግ ትብብር አገዛዙን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ወሳኝ ሂደት መሆኑ ግልፅ ነው ብሏል።
ህዝባዊ ዓላማችንን የተጋራን ጋር በመርህ የምናደርገው ትብብር እና አንድነት የአረመኔውን አገዛዝ እድሜ ለማሳጠር ትልቅ ፋይዳ ያለው ጉዳይ ነው ያለው አፋብን፣ ይህንን ተከትሎ ባቀረብነው ወገናዊ ጥሪ በርካታ የአገዛዙ አገልጋይ የነበረ ምሊሻ፣ አድማ ብተና እና የመከላከያ ኃይል የወገንን ኃይል እየተቀላቀለ ይገኛል ሲል አስታውቋል።
ቡድኑ ባወጣው መግለጫ አገዛዙን በማገልገል ላይ ለምትገኙ የምሊሻ፣ የአድማ ብተና፣ የመደበኛ ፖሊስ፣ መከላከያ እና በሌሎች የአገዛዙ ታጣቂ አደረጃጀቶች ውስጥ ላላችሁ ተመሳሳይ ጥሪወችን እናስተላልፋለን ያለ ሲሆን፣ ይህንን ጥሪ ያስተላለፈው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ስራ አመራር በጉዳዩ ላይ በዝርዝር ተወያይቶ ጥሪዉን በመቀበል ወገናቸውን ለመካስ ለሚፈልጉ የአገዛዙ ሰራዊት አባላት እና የካድሬ መዋቅር የምህረት አዋጅ አውጇል ብሏል።
ለ) የምህረት አዋጁ የተላለፈላቸው የአገዛዙ መዋቅር አካላትን በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን፣ በየደረጃው የሚገኙ የብልፅግና አመራር አባላት፣ ምሊሻ፣ ሰላም አስከባሪ እና በሌላም ስያሜ ብልፅግና ያደራጃቸው ታጣቂወች፣ የክልል አድማ ብተና እና መደበኛ ፖሊስ አባላት፣ እንድሁም በሀገር መከላከያ ሰራዊት ስም በየቀጠናው የተሰማሩ እግረኞች እና የአገዛዙ መኮንኖችን ያካትታል።
አፋብን የምህረት አዋጁን ማውጣት ያስፈለገበት ምክንያት በተመለከተ በሰጠው ማብራሪያ፣ ሶስት ዓመታትን ሊደፍን ጥቂት ጊዜ በቀረው የጦርነት ሂደት በግልፅ መገንዘብ እንደሚቻለው የብልፅግና መዋቅር በአማራ ህዝብ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ድቀት ላይ ስልጣኑን ከማራዘም ያለፈ ለአማራ ህዝብ የሚጠቅም አንድም አጀንዳ የሌለው በመሆኑ የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ በተለያዬ ጎራ የተሰለፍን የአማራ ልጆችም እንደ የአንድ እናት ልጆች በመቀናጀት የህዝባችንን ህልዉና ማስጠበቅ ከእኛ የሚጠበቅ ተግባር ነው ብሏል።
በመሆኑም ለአማራ ህዝብ ሁለንተናዊ መብት እና ነፃነት እንጅ ለአብይ አህመድ ወንበር መፅናት የሚወድቅ የአማራ ወጣት መኖር ስለሌለበት፤ ህዝባችንን በጅምላ ለሚጨፈጭፍ አገዛዝ በማገልገል የዘቀጠ ታሪክ ውስጥ ራስን ከማግኘት ይልቅ ለነፃነቱ የሚዋደቅን ኃይል በመቀላቀል ደማቅ ታሪክ መፃፍ ታሪክ የጣለብን ግዴታ በመሆኑ፤ ህዝብን ታግሎ ያሸነፈ አገዛዝ እንደሌለው ሁሉ አብይ አህመድም የአማራን ህዝብ ማሸነፍ ስለማይችል እና በተሸናፊነት ለሚያጠናቅቀው ብልፅግና በመላላክ እና በራስ ወገን ላይ በመተኮስ የታሪክ፣ የህሊና እና የፍትህ ተጠያቂነትን ከማስተናገድ ለመዳን ሲባል እና አገዛዙን በጋራ ታግለን በማሸነፍ ለህዝባችን ሰላም ማምጣት የትውልዱ ግዴታ በመሆኑ፤ እንዲሁም የምንታገለው ለአማራ ህዝብ ህልውናና መዳን እንደመሆኑ መጠን የፋኖ ትግልም የአማራ ህዝብ ትግል ስለሆነ በሁሉም ጎራ ላሉ አማራዊ ወንድሞች ጥሪ ማድረግ እና ማታገል የድርጅታችን ተልዕኮ በመሆኑ፤ ይህንን የምህረት አዋጅ በአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ስራ አመራር ውሳኔ መሰረት ለህዝብ ይፋ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ነው ያለው።
የምህረት አዋጁ አተገባበርን በተመለከተም የምህረት አዋጁ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ካላይ የተዘረዘሩት የምሊሻ፣ አድማ ብተና፣ መከላከያ እና ሌሎች የታጠቁ የብልፅግና ኃይሎች እንዲሁም በየደረጃው ያሉ አመራሮች በየአካባቢያቸው ላለው የድርጅታችን መዋቅር እና ለዚህ ጉዳይ በተቋቋመው ግዜያዊ ግብረ ኃይል በአካል ቀርበው ሪፖርት ያደርጋሉ ያለ ሲሆን፣ ምህረት ጠይቀው ወገናቸውን ለመካስ የሚመጡ ግለሰቦች የአካል ደህንነት ዋስትና ይሰጣቸዋል፣ በተዘጋጀላቸው ማረፊያ የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል ሲል አስታውቋል።
ለትግል አገልግሎት ከሚዉል የጦር መሳሪያን ጨምሮ ማንኛውም የምህረት ጠያቂወች ንብረት በባለቤቶች እጅ እንደሚቆይ የገለፀዉ ቡድገዠኑ፣ ምህረት የተደረገላቸው ግለሰቦች ድርጅቱ ባዘጋጀው ፎርም መሠረት ለአማራ ህዝብ ነፃነት ሊሰሩ ካልተቻለም ከጠላት ወገን ላይሰለፉ ቃለ-መሃላ እንደሚፈፅሙ አመላክቷል።
አቅሙ እና ፍላጎቱ ያላቸው የምህረት ተጠቃሚወች የወገንን ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ መዋቅር ተቀላቅለው ለህልዉና ተጋድሎው የበኩላቸውን ድርሻ ይወጡ ዘንድ በሌላ ማናቸውም ለህዝብ ጠቃሚ በሚሆኑ ተልዕኮወች ላይ ይሰማሩ ዘንድ ድርጅቱ ሁኔታወችን ያመቻቻልም ብሏል።
ይህ የምህረት አዋጅ ከየካቲት 04 ቀ 2018 ዓ.ም ላሉት ተከታታይ 15(አስራ አምስት ቀናት) ብቻ ተፈፃሚ እንደሚሆን አስታውቆ፣ የምህረት አዋጁን በማስፈፀም የሰራዊታችን እና የድርጅታችን አመራር ግዴታ የምህረት አዋጁን አፈፃፀም ለመከታተል በማዕከል የተቋቋመው ግብረ ኃይል የመመሪያዉን አተገባበር ይከታተላል፤ መረጃወችን ይሰጣል፤ መፍትሔ ያስቀምጣል በማለት ገልጿል።
የድርጅቱ መዋቅር አመራር እና ሰራዊቱ ለምህረት ጠያቂወቹ የአካል ዋስትና መስጠትን ጨምሮ በእንክብካቤ በማስተናገድ በፍፁም ጨዋነት አዋጁን ይተገብራል ያለው አፋብን በአፈፃፀም ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ወዲያውኑ ለግብረኃይይሉ ያሳውቃል፣ የተሰጠዉን የመፍትሔ አቅጣጫ ይተገበራል፣ በግል ቂም ቁርሾ ወይም በሌላ ግላዊ እና ቡድናዊ ፍላጎቶች ምክንያት ከዚህ አዋጅ በተቃረነ መንገድ በማንኛውም ምህረት ጠያቂ ላይ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ማድረስ ወይም ንብረት መቀማት ፍፁም የተከለከለ ተግባር ነው ብሏል።
የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌወችን እና መርሆወችን እንዲሁም ዓለም አቀፍ የጦር ህግጋትን የተከተለ አሰራር ተገዥ እንደሚሆን ያነሳው ቡድኑ፣ ይህንን አዋጅ ጥሶ የተገኘ ማንኛውም የድርጅቱ አመራር እና አባል ወይም ሌላ አካል ከባድ ቅጣት እንደሚተላለፍበት አስታውቋል።
ሕዝቡ፣ የሀገር ሽማግሌወች እና የኃይማኖት በየቀጠናው ያለው ህዝብ፣ የሀገር ሽማግሌወች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን እና ሌሎች ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች በጠላት የፀጥታ እና የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ ያሉ ግለሰቦች በዚህ አዋጅ መሰረት አፈሙዛቸውን ወደ ዋናው ጠላት እንዲያዞሩ ካልሆነም ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲኖሩ እና የአማራው ኃይል ፍፁም ህብረት እንዲኖር የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ይጠበቃል በማለት ሚናቸውን አስቀምጧል።
አፋብን የአማራ ልጆች በጋራ ተባብረን ህዝባችንን ሊያጠፋ የተነሳውን ጠላት እናስወግድ ዘንድ አንድነት እና ህብረት ያስፈልገናል እና ወደ አማራ የምንተኩሰው ጥይት እንዳይኖር እና አንድ ጠላት ላይ ብቻ አነጣጥረን እናሸንፍ ሲል ጥሪውን አቅርቧል።
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






