Homeነፃ አስተያየት“ድሮኑ ቢቀር እንኳ…”

“ድሮኑ ቢቀር እንኳ…”

Advertisement
World Wide Travel Group
ሙሉጌታ ቢያዝን

       

(ከ18 ዓመት በታች የተከለከለ)

ሙሉጌታ ቢያዝን

ሰሞኑን የቱርኩ መሪ አዲስ አበባ መጥተው ነበር፡፡ ዠርጋዳው ኤርዶጋን የጦቢያን መሪ ከጎን አቁመው “ጦርነት ይብቃ ሰላም ይስፈን” ሲሉ ተደመጡ፡፡ ይህን የሰሙ ሁሉ ፈነጠዙ፡፡ ድሮን ስታቀብል የነበረችው ቱርክ ዛሬ “በቃ ማለት በቃ ነው”/Enough is enough/ አለች እያሉ ተንጫጩ፡፡ ጋዜጣው ዋና ርእስ አድርጎ አወጣው፡፡ የዩቲውብ ቻነሎች ሁሉ ተቀባበሉት፡፡ ሳቄ መጣ፡፡ ድሮን አልሸጥም ስትል አልተሰማችም፡፡ ወይስ ጆሮየ ነው፡፡  ግን ይህን መሰል ዜና ለመስማት የቋመጠ  ሁሉ ሲፈነጥዝ ሰነበተ፡፡አልፈርድበትም፡፡ ሰላምን አጥብቆ ቢናፍቅ ነው፡፡

እዚህ ላይ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ “ለዘለዓለም እንዴት እንኑር”/How to Live Forever/ በሚል አንድ ዶክመንታሪ ፊልም አንዲት መቶ ዓመት የደፈነችን የዕድሜ ባለጸጋ ሴት ጋዜጠኛው ይጠይቃል፡፡ 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

“በሕይወትሽ የተደሰትብሽበት ቀን የትኛው ነው? “

“የሰላሙን ቀን” ትለዋለች፡፡ የአንደኛው ዓለም ጦርነትን ያስቆመውን የ1918ቱ (እኤአ) ስምምነት የተፈረመበትን ቀን ማለቷ ነበር፡፡ 

“ለምን?” ሲል ጋዜጠኛው መልሶ ይጠይቃል፡፡ 

“ምክንያቱም ከንግዲህ በኋላ ጦርነት አይኖርም፡፡”

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ የትግራይ እናትም ቢጠየቁ እንዲህ ማለታቸው አይቀርም፡፡ ይሁንና ከ21 ዓመት በኋላ ቢያንስ 75 ሚሊዮን ነፍሳትን ቀርጥፎ የበላው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተለኮሰ፡፡ 

ጸሐፊው እንዲህ ይላል “There are many things in life that we think are true because we desperately want them to be true.”

ዕድሜ ሰጥቷቸው ከሰነበቱ እኒያ አዛውንት ዳግመኛ ቢጠየቁ ምን ይሉ ይኾን? ተሳስቼ ኖሯል?

የፖለቲካ መሪ በአደባባይ ሲናገር እንዳለ መውሰድ፣ መውሰድ ብቻ ሳይኾን ማመን የዋህነት አይኾንምን? ‘ጦርነቱን በዚሁ ቀጥሉ’ እንዲሉ መጠበቅስ ልጅነት ወይስ ጅልነት?

- Advertisement -

ምነው ጦርነት አንወድም ብለው አይደለም በጀርባ ጦርነት የሚጀምሩት? ሰላም ሰላም እየተጫወቱ አይደለም ጦርነት የሚለኩሱት? ‘ጦርነት ውስጤ ነው’ ብሎ ጦርነት የጀመረ ካለ ንገሩኝ፡፡ 

ቱርክ ድሮን ስታበድር ጭካኔም ሳታበድር አትቀርም፡፡ በብራዘርስ ካራማዞቭ (The Brothers Karamazov) መጽሐፍ የቱርክን ከአውሬ የከፋ ጭካኔዋን ኢቫን የተሰኘው አንድ ገጸ ባሕርይ ይናገራል፡፡ ይህ ገጸ ባሕርይ ሕፃናት ሰባት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ እንደ መላእክት ናቸው ይለናል፡፡ ዕፀ በለሱን ከቀረጠፉት ወላጆቻቸው ኃጢአትን የሚወርሱት የሰባት ዓመት ልደታቸውን ካከበሩ በኋላ ነው ዓይነት፡፡ እና እነዚህ ቱርኮች ከሸርካሺኖች(Circassians) ጋር በማበር በመላ ቡልጋሪያ ሕፃናት ላይ የፈጸሙትን ግፍ እንዲህ ይተርክልናል፡፡ 

የቱርክ ወታደሮች በፍርሃት የምትንዘፈዘፈውን እናት ይጠሯታል፡፡ ክፉና ደግ የማያውቀውን ጡት ያልተወውን ሕጻን በክንዶቿ ታቅፋለች፡፡ “ና እስኪ ማሙሽዬ” እያሉ በእቅፏ ያለውን ሕፃን ያጫውቱታል፡፡ ሕጻኑ ይፈነድቃል፡፡ በደንብ መፈንደቁን ጠብቀው ሽጉጡን ያስጠጉለታል (ከ18 ዓመት በታች የተከለከለ)፣ መጫወቻ ያገኘ መስሎት ሕፃኑ በሽጉጡ ለመጫወት ሲታገል ምላጩን ይስቡትና እርግብግቢቱ የሚቆጠረውን ለጋ ጭንቅላቱን እናቱ ፊት ይበረቅሱታል፡፡ 

ይህን ምን ይሉታል በሞቴ?

ሰዎች የአውሬ ጭካኔ ነው ሲሉ እሰማለሁ፡፡ ይህ ፍርደ ገምድልነት ነው፡፡ አውሬዎችን እንደመስደብ ያለ ነው፡፡ ነብር አድኖ መብላት ጥንተ ተፈጥሮው ነውና ያን ቢያደርግ በደል የለበትም፡፡ 

ጭካኔን ማበላለጥ ጭካኔ ቢኾንም በዱላ መቀጥቀጥን እኛ አውሮፓውያኖች ተክነንበታል፡፡አጥር ጋር ጆሮን በሚስማር አጣብቆ መምታት(መስፋት)ግን የሚታሰብ አይደለም፡፡እነሱ እኮ (ቱርኮችና ሸርካሺኖችን ነው) የጦር እስረኞቻቸውን ጆሮ በሚስማር ይመቱና በሚስማሩ እንደተጣበቁ እስኪነጋ ድረስ እዛው ይተዋቸዋል፡፡ ጎህ ሲቀድ አውጥተው ይሰቅሏቸዋል፡፡

እነዚህ ቱርኮች ሕጻናትን በማሰቃየት ልባቸው ውልቅ እስኪል ድረስ ‘ሐሴት’ ያደርጋሉ፡፡ ከእናት ማኅፀን ልጅ ቆርጠው ያወጡና ወደ ላይ አጉነው ሲመለስ በሳንጃ ይቀበሉታል፡፡ ልብ በሉ ይህን የሚያደርጉት ከእናት ፊት ነው፡፡ ይህን በማድረጋቸው እጅግ ይፈነጥዙ ነበር፡፡ሃሃሃሃ… /Doing it before the mothers’ eyes was what gave zest to the amusement/ ልክ ሰሞኑን ገበሬ ቤት ገብተው እህል እንደደፉት ጉዶች ዓይነት፡፡ ሃሃሃሃ…. “በዚህ ድፋው… አምጣው፣ አዎ እንደሱ ድፋው…… ሃሃሃ…. 

ነፍስ በሌለው እህል እንዲህ ከጨከኑ ነፍስ ያለው ቢያገኙ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ መገመት ጠንቋይ መኾን አይጠይቅም፤ተደርጓልም፡፡

የዜጎቿን ሆድ መሙላት የሰማይ ያህል የራቀባት ሀገር በእህል እንዲህ ስታጫወት እንደማየት ያለ ወለፈንዲነት የለም፡፡ ካናዳ ይሄን እንዳታይ እባካችሁ ወገኖቼ! አደራ፡፡ ኦ… ይቅርታ ለካ ከራሳችን አልፈን ስንዴ ወደ ውጭ መላክ ጀምረናል፡፡ ዘንግቼው ነው ይቅርታ!

ኢቫን እውነቱን ከኾነ ከቱርክ ድሮን ብቻ አይደለም ያስገባነው ጎበዝ፤ ጭካኔም ነው፡፡ እና ድሮኑ ባይገባ እንኳ ያስገባነውን ጭካኔ በቀላሉ ማስወጣት የምንችል አይመስለኝም፡፡

ያሰንበተን!

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English

ኤክስ ፡ @zborkena

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News