Homeነፃ አስተያየትየሽግግር መንግስት ለምንድነው የሚያስፈልገን፣ እንዴትስ ይመሰረታል?

የሽግግር መንግስት ለምንድነው የሚያስፈልገን፣ እንዴትስ ይመሰረታል?

Advertisement
World Wide Travel Group

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com) 

አገራችን ኢትዮጵያ ተከታታይ ሥርዓተ መንግስት ያላት፣ የረጂም ጊዜ ታሪክና የገናና ሥልጣኔ ባለቤት የነበረች አገር ናት። የዛሬዋ እንግሊዝ እንደ አገር ከመመስረቷ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የነበራት ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንደነበረች የሚያመለክቱ አያሌ የታሪክ ማስረጃዎች አሉ። እንግሊዞችና ሌሎችም የአውሮፓ አገሮች አስደናቂ ህንፃዎችንና  አብያተ ክርስቲያናትን ሲሰሩ ኢትዮጵያዊያንም ዓለም አቀፍ ዝና ያተረፉ የአክሱም ሃውልትን፣ ዕጹብ ድንቅ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትንና የጎንደር ቤተ መንግሥትን ሰርተዋል። 

የአውሮፓ ስልጣኔ መሠረት ከሆኑ ዕሴቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ብዙዎቹ የአውሮፓ አገሮች የሚጋሩት የላቲን ፊደል ነው። አገራችን ኢትዮጵያ የራሳቸው ፊደል ካላቸው ጥቂት የዓለም አገሮች ውስጥ አንዷ ናት። እነዚህ የታሪክ ማስረጃዎች የሚነግሩን አንድ ትልቅ እውነት አለ፣ እሱም በታሪክ ወደኋላ ስንሄድ በአንድ ወቅት እንግሊዞችና እኛ ኢትዮጵያዊያን በተመሳሳይ የስልጣኔ ደረጃ ላይ እንደነበርን ነው። ታዲያ እኛን ምን ነክቶን ነው ዛሬ እነሱ መጽዋች እኛ ተመጽዋች የሆነው? ለምንድነው እነሱ ጨረቃ ላይ መኖር ይቻል ይሆን ብለው ወደ ላይ ሲወጡ እኛ እዚሁ ምድር ላይ አብሮ መኖር ያቃተን? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ብዙ መጓዝ የለብንም። እንግሊዝ ውስጥ የዕድገትና ብልፅግና በር የተከፈተው፣ የእንግሊዝ ህዝብ በንጥቂያና ብዙኋኑን በማግለል ላይ የተመሠረተውን የፖለቲካ ሥርዓት አቃፊ በሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ሲቀይረው ነው። ይህንን እንግሊዞች በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምረው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያጠናቀቁትን የፖለቲካ ሂደት እኛ ኢትዮጵያዊያን ዛሬ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም አልጀመርንም። በትክክል የሚገባንና ቁጭት ውስጥ ከትቶን የሚያነሳሳን ከሆነ የድህነታችን፣ የተመፅዋችነታችን፣ የመራባችን፣ የኋላ ቀርነታችንና የእርስ በርስ መገዳደላችን ዋናው ምክንያት ለዘመናት አንቆ ከያዘን ነጣቂና አግላይ ከሆነ የኤኮኖሚና  የፖለቲካ ሥርዓት እራሳችንን ማላቀቅ አለመቻላችን ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፈው ግማሽ ምዕተ አመት ሦስት የተለያዩ መንግስታትን ከሥልጣን አስወግዷል፣ በ1967 ዓ.ም. የፊውዳሉን ሥርዓት፣በ1983 ዓ.ም.ወታደራዊውን አገዛዝ፣በ2010 ዓ.ም.ደሞ የህወሓትን የአንድ ብሔር አምባገነን አገዛዝ ከአራት ኪሎ ማባረር ችሏል፣ሆኖም መሰረቱን ፍትህ፣ነጻነት፣እኩልነትና ዲሞክራሲ ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት ባለመቻሉ የመጀመሪያውን የመንግስት ለውጥ ካደረገ ከ52 አመታት በኋላ ዛሬም አምባገነንነትን እየታገለ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ በ2010 ዓ.ም. በታሪካችን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እጅግ በጣም ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ አግኝቶ የመጣውና ብዙም ሳይቆይ እራሱን ወደ አንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭ አምባገነንነት የለወጠው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በግልጽ የሚታዩና ጥልቅ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች መፍታት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹን ቀውሶች የሚፈጥረው እሱ እራሱ ነው። ጠሚ አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ የወሰዳቸው ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ እርምጃዎች ኢትዮጵያንና ህዝቧን በቀላሉ መውጣት የማይችሉት አዘቅት ውስጥ ይዟቸው ገብቷል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ከዚህ በየቀኑ ጥልቀቱና ስፋቱ እያደገ ከሚሄድ አዘቅት ውስጥ በአስቸኳይ እራሳችንን የማናወጣ ከሆነ የኢትዮጵያ እንደ አገር ቀጣይነት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ይገባል። 

በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ  ስር የሰደደ የብሔር ፖለቲካ አለ፣የብሔር ግጭትና የርስበርስ ጦርነት አለ፣ሰላምና መረጋጋት የለም፣መንግስት ሊፈርስ ትንሽ ነው የቀረው(State Collapse)፣የዘር ማፅዳትና የጦር ወንጀል በየቀኑ ይፈጸማል፣ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ፣በህዝብ፣ በመንግስትና በፖለቲካ ተዋንያኑ መካከል መተማመን የለም፣ማዕከላዊው መንግስት ደካማ በመሆኑ አንዳንድ ክልሎች ከቁጥጥሩ ውጭ ሆነዋል፣የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በሚከተለው ፍጹም የተሳሳተ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ የተነሳ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በሁሉም አቅጣጫ እየከበቡን ነው፣ ከጎረቤቶቻችን ጋር በሰላም መኖር የማንችልበት ድረጃ ላይ ደርሰናል፣ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ አለ፣ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ ኢትዮጵያ የህልውና አደጋ ላይ ናት። ስለዚህ የኢትዮጵያን እንደ አገር ቀጣይነት ለማረጋገጥ፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና ባጠቃላይ ኢትዮጵያን ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመውሰድ የሽግግር መንግስት በጣም አስፈላጊ ነው።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

አለም አቀፉን ማህበረሰብ ጨምሮ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ በሽግግር ሂደት ውስጥ ማለፍ አለባት እያለ ሲወተውቱ፣የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ግን የብሔር ግጭትና የእርስበርስ ጦርነት በሚካሄድባት ኢትዮጵያ ውስጥ አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅቱን ጀምሯል። ትግራይ፣አማራና ኦሮሚያ ውስጥ ዜጎች እንኳን ምርጫ ጣቢያ ሄደው ተወካዮቻቸውን ሊመርጡ ገበያ ወጥተው ምግብ ለመሸመትም በህይወታቸው መቁረጥ አለባቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የመቃወም፣ የመሰብሰብና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የለም፣የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢሯቸው ውስጥ የቁም እስረኞች ናቸው። ኢትዮጵያ ከ4.5 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች የሚገኙባትና ከ5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርት ቤት መሄድ የማይችሉባት አገር ናት። እነዚህ በግልጽ በአይን የሚታዩ ሁኔታዎች አፍ አውጥተው የሚነግሩን ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ ሳይውል ሳያድር ሁሉን አቀፍ ወደሆነ የሽግግር ሂደት ውስጥ መግባት እንዳለባት ነው፣ይህ የማይሆን ከሆነ አደጋው መበታተን ሊሆን ይችላል። ይህንን የመበታተን አደጋ ለማዳንና፣ኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለመጀመር የግድ በሽግግር ሂደት ውስጥ ማለፍ አለብን፣በሽግግር ሂደት ውስጥ ማለፍ ካለብን ደሞ የሽግግር መንግስት ያስፈልገናል። 

ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ውድቀትን ለማስቀረት፣ሥር የሰደዱ የፖለቲካ፣ የብሔር እና የጸጥታ ቀውሶችን በቁጥጥር ስር ለማድረግ፣ሠላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ፣ በአምባገነንነትና በዲሞክራሲ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ፣ተቋማዊ ማሻሻያ ለማድረግ፣አገራዊ ዕርቅ ለማድረግና የጦር ወንጀልና የዘር ማጽዳት ወንጅል የፈጸሙ ኃይሎችን ተጠያቂ ለማድረግ የሽግግር መንግስት አማራጭ ሳይሆን አስፈላጊ ነው። ጠቅለል ባለ መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት የሚያስፈልገን በሚከተሉት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው-

  1. የኢትዮጵያን እንደ አገር ቀጣይነት ለማረጋገጥ- የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ፣ህዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው የሚል ኢትዮጵያን ተከታታይነትና ዘላቂነት እንዳላት አገር ሳይሆን፣ ብሔሮቿ ከፈለጉ የምትቀጥል ካልፈለጉ ደሞ ምንግዜም ልትበታተን የምትችል የብሔሮች ስብስብ አድርጎ የሚመለከት እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ አንቀጽ አለበት። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች የሚገኙባትና የማያቋርጥ የብሔር ግጭትና የርስበርስ ጦርነት የሚካሄድባት አገር ናት። በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት አይኑ በብሔር ፖለቲካ የታወረና ሁሉንም የፖለቲካ ልዩነቶች በጦርነት ብቻ ለመፍታት የሚሞክር ጦርነት ቀፍቃፊ መንግስት በመሆኑ፣ኢትዮጵያ ከብሔር ግጭት፣ከእርስ በርስ ጦርነትና ከመበታተን አደጋ ወጥታ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ማድረግ እንድትችል የሽግግር መንግስት ያስፈልጋል።
  2. በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚካሄደው ግጭትና ጦርነት ለማቆም- ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚካሄድ የትጥቅ ትግል አለ፣አማራና ኦሮሚያ ክልል በፌዴራል መንግስትና በታጣቂዎች ( ፋኖና ኦነግ-ሸኔ) መካከል የሚካሄደው ጦርነት የብዙ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፣በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከቀያቸው አናቅሏል፣በንብረትና መሰረተ-ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። የትግራይ ህዝብ የሁለት አመቱ ጦርነት ካደረሰበት ከፍተኛ ኤኮኖሚያዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ሳያገግም ሦስተኛ ዙር ጦርነት እየታወጀበት ነው። ጋምቤላ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች እንዳሻቸው እየመጡ ሰላማዊ ዜጎችን የሚገድሉበትና የሚዘርፉበት ክልል ከሆነ አመታት ተቆጥረዋል። በሥልጣን ላይ ያለው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት እነዚህ ችግሮች እንዲባባሱ ከማድረግ ውጭ መፍትሄ ሲፈልግ አይታይም። ይህ የሚያሳየን ኢትዮጵያ ውስጥ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ተደራድሮ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስና ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ ያለን ብቸኛ አማራጭ ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር መንግስት ብቻ መሆኑን ነው።
  3. ብሔር ተኮሩን ፌዴራል ሥርዓት ለማሻሻል- መሠረቱን ብሔርና ቋንቋ አድርጎ የተዋቀረው የኢትዮዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት ዛሬ በየቦታው ለሚታዩ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ምክንያት መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። የብሔር ኃይሎች ኢትዮጵያ “የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ናት” ብለው በተናገሩበት በቀኃስ ሥርዓት ውስጥም ሆነ የብሔር ነጻ አውጪዎች የ17 አመት ጦርነት ባካሄዱበት በደርግ ዘመንም ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔር ብሔረሰቦች ነበሩ፣ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ብሔሮች የግዛት ይገባኛል ሽኩቻ ውስጥ የገቡትና ከክልሌ ውጣልኝ በሚል እርስበርስ መገዳደል የጀመሩት ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ፌዴራሊዝም (Ethnic Federalism) ከተመሰረተ በኋላ ነው፣ ወይም ብሔር ብሔረሰቦች እራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ጀመሩ በተባለበት በህወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓት ውስጥ ነው — ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ደሞ የዚህ ሥርዓት ተቀጥላ ነው። የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት የፌዴራል ሥርዓቱን አወቃቀር ለማሻሳል ህገ መንግስታዊ ዕርምጃ መውሰድ የሚችስል ህዝባዊ ተአማኒነት የለውም፣ ደሞም ህገ መንግስት ማሻሻልን የመሰለ ትልቅ አገራዊ እርምጃ ለመውሰድ አገራዊ ሃላፊነት መሰከም ካቃተውና በአንድ ፓርቲ ከሚመራ አገዛዝ ይልቅ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የሚወክል የሽግግር መንግስት የበለጠ ተቀባይነትና ተአማኒነት ይኖረዋል።
  4. ህገ መንግስቱን ለማሻሻል- በ1987 ዓም በስራ ላይ የዋለውንና ዛሬ በስራ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ህገ መንግስት በተመለከተ ሁለት ነገሮችን ማለት ይቻላል፣ አንደኛ- ባለፉት 31 አመታት ህወሓት/ኢህአዴግ እንደጻፈው ህገ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ ለሁለት ከፍሎ ያከራከረ ሌላ ምንም ነገር የለም፣ሁለተኛ፣ይህ ህገ መንግስት ፌዴራል ዲሞክራሲያዊት ሪፑብሊክ ኢትዮጵያን ከፈጠረ ጀምሮ ኢትዮጵያ የአለማችን የብሔር ግጭት ተምሳሌት ሆናለች። ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በኢትዮጵያዊያን መካከል አጥር ሰርቶ የለያየን የብሔር ፌዴራሊዝም እንዲቀጥል የሚፈልግ መንግስት ስለሆነ እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደ አንድ አገር ህዝብ አብሮ የሚያኖረንን ማህበራዊ ኮንትራት እንደገና መጻፍ አለብን፣ይህንን ለማድረግ ያለን ብቸኛ አማራጭ ደሞ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ህገ መንግስቱ ይሻሻል ወይስ ይለወጥ የማለት ህዝባዊ መሰረት የሚኖረው ኢትዮጵያዊያን ተስማምተው የፈጠሩት የሽግግር መንግስት ሲኖር ብቻ ነው።
  5. አገሪቱን ያናጋት ኢኮኖሚያዊና ሰብአዊ ቀውስ እንዲያበቃ- ኢትዮጵያ በአንድ በኩል ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ጋር ተስማምታ ተግባራዊ ባደረገቻቸው የኤኮኖሚ ፖሊሲዎች የተነሳ፣በሌላ በኩል ደሞ የአሜሪካና የሌሎችም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እርዳታ በመቀነሱ የተነሳ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ቀውስና፣ ስፋቱና ጥልቀቱ በየቀኑ እየጨመረ የሚሄድ የረሃብና የድህነት አደጋ ውስጥ ገብታለች። ጦርነት በሚካሄድባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች ሁሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ተፈናቅሏል፣ የዞን፣የወረዳና የከተማ አስተዳደር ከጥቅም ውጭ ሆኗል፣የእርሻ ቦታዎች የጦርነት አውድማ ሆነዋል፣ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋሞች ተዘግተዋል ወይም ወድመዋል። የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ኢትዮጵያን ከዚህ ትልቅ ቀውስ ውስጥ ያወጣል ብሎ መጠበቅ የችግሩን ትክክለኛ ባለቤት አለመረዳት ነው። ስለዚህ ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ በፍጥነት ለመውጣት የሚያስፈልገን፣ትኩረቱን ትርጉም የለሽ ምርጫ ላይ ያደረገ መንግስት ሳይሆን፣ትኩረቱ ሰላም፣መረጋጋትና ሰብዓዊ ተደራሽነት ላይ የሆነ የሽግግር መንግስት ነው።
  6. ከቀን ወደ ቀን እየጠበበ የሚሄደውን የፖለቲካና ሲቪክ ምህዳር ለማስፋት- ኢትዮጵያ ጠሚ አቢይ አህመድ የሚፈልገው ነገር ሁሉ የሚሆንባት እሱ የማይፈልገው ከሆነ ግን ምንም ነገር የማይሆንባት አገር ከሆነች አምስት አመታት ተቆጥረዋል። አቢይ አህመድ የማይፈልጋቸው የአገር ውስጥና የውጭ ሜዲያዎች ታግደዋል፣ጋዜጠኞች ታስረዋል፣ከአገር ተባርረዋል ወይም ተሰድደዋል፣የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና ሲቭክ ማህበራት ፈቃድ ተሰርዟል። ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት ይቁም ብለው ሠላማዊ ሠልፍ የጠሩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ታስረዋል፣ባጠቃላይ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካና የሲቪል ምህዳር እየጠበበ ሄዶ እንኳን መናገር ማንንም የማያስተንፍስ ሆኗል። የፕሬስ ነፃነትን ዛሬ ካለበት ቦታ ዜጎች መንግስትን ከመቃወም ጀምሮ በነጻነት ማሰብና ያሰቡትን በነጻነት ማንሸራሸር የሚችሉበት ቦታ ላይ ለማድረስና፣የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት መንቀሳቀስ የሚችሉበት ምህዳር ለመፍጠር፣በተለይ ደሞ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ቁልፍ የሆኑ ተቋማትን(ምርጫ ቦርድና የፍትህ አካላት) በአዲስ መልክ ለመገንባት የሽግግር መንግስት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው።
  7. እውነተኛ ብሔራዊ እርቅ ለማስፈን- ኢትዮጵያ የቀይሽብር ወንጀል፣የጦር ወንጀል፣የዘር ማጽዳት ወንጀልና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባትና ዛሬም በየቀኑ የሚፈጸምባት አገር ናት። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በአገረ-መንግስቱ ግንባታ ሂደት፣ባለፈው የኢትዮጵያ ታሪክ፣በስራ ላይ ባለው ህገ መንግስት፣በፌዴራል ሥርዓቱ አወቃቀርና ባጠቃላይ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት በሚለው ጥያቄ ላይ የማይግባባ የፖለቲካ ልህቅ የሚገኝባት አገር ናት። በሥልጣን ላይ ያለው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ለእነዚህ ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያቀርብ ዕድል ተሰጥቶት ዕድሉን አለመጠቀሙ ብቻ ሳይሆን አንዳዶቹ ችግሮች እንዲባባሱና ይበልጥ እንዲወሳሰቡ አድርጓል። ካሁን በኋላ ኢትዮጵያ በአገራዊ ምክክር፣በሽግግር ግዜ ፍትህና በእውነትና እርቅ ሂደቶች ውስጥ እንድታልፍ ለማድረግ ቅቡልነቱም ህጋዊነቱም የሚኖረው ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ብቻ ነው።
  8. ተቋማዊ ማሻሻያዎች ለማድረግ– ኢትዮጵያ ነፃና ገለልተኛ ተቋሞች የሌሉባት አገር ናት። ፍርድ ቤቶች፣የፖሊስና የደህንነት ተቋሞች አራት ኪሎን የተቆጣጠረ ሁሉ ህዝብን ቀጥቅጦ ለመግዛት የሚጠቀምባቸው የማጥቂያ መሳሪያዎች ናቸው። ህዝብ በከፈለው ግብር የሚተዳደሩ ሜዲያዎች የገዢው ፓርቲ የፕሮፓንዳ መሳሪያዎች ናቸው። ምርጫ ቦርድ ገዢው ፓርቲ በየአምስት አመቱ እንዲመረጥ ለማድረግ የተቋቋመ ተቋም ነው። በሥልጣን ላይ ያለው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት እነዚህ ተቋሞች የሱን የሥልጣን ዘመን እስካረዘሙለት ድረስ ምንም አይነት መሻሻያ እንዲያደርጉና ዝህባዊ መልክ እንዲይዙ ማድረግ አይፈልግም። ስለዚህ ያለን ብቸኛ አማራጭ ነፃና ገለልተኛ ተቋማትን ያለምንም ጠልቃ ገብነት ህዝብንና አገርን እንዲያገለግሉ አድርጎ መገንባት የሚችል ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ማቁቋም ነው።

የሽግግር መንግስት እንዴት ይመሰረታል?

ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት እንዳይፈጠር ምክንያት ከሆኑ ነገሮች አንዱ፣የተለያዩ የፖለቲካና ማህበራዊ ባለድርሻዎች እርስበርስ የማይገናኙ መሆናቸውና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር መሃሉ ባዶ መሆኑ ነው፣ ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ የመሃል ፖለቲካ የሚያራምዱ ኃይሎች አለመኖራቸው ነው (Absnece of Centripetal political forces).። ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የመጀመሪያው ትልቅ ስራ እነዚህን- በአንድ ቤት ውስጥ ተራርቀው በየራሳቸው ክፍል የሚኖሩትን ባለድርሻዎች ተወያይተውና በመካከላቸው የሚገኙ ልዩነቶችን እጥብበው ወደ ሳሎን ክፍል እንዲመጡ ማድረግ ነው። እንዴት? ከታች ያሉትን 3 ሠንጠረዦች ይመልከቱ

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ሁለተኛ- እነዚህ ወደ መሃል የመጡ ባለድርሻዎቺ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ  ተወያይተው ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው

ሦስተኛ- ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት እንዴት መፈጠር አለበት በሚለው ጥያቄ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው 

አራተኛ- እነዚህ የተለያዩ ባለድርሻዎች የሽግግር መንግስት እንዴት መፈጠር አለበት በሚለው ጥያቄ ላይ ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የታጠቁ ኃይሎች (ህወሓት፣ፋኖ፣ኦነግ-ሸኔ፣ኦብነግ፣ጋህነግ እና ቤህነን) ጋር ንግግር መጀመር አለባቸው።

ኢትዮጵያ ዉስጥ የሽግግር መንግስት ሊፈጠር የሚችልባቸው ቢሆንሶች(Senarios)

- Advertisement -

አገራችን ኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ያስፈልጋታል ወይ በሚለው ጥያቄ ላይ አብዛኛው ተቃዋሚ ኃይልና የኢትዮጵያ እንደ አገር ቀጣይነት በሚያሳስባቸው ኢትዮጵያዊያን መካከል ልዩነት የለም፣ልዩነት ቢኖር እንዴትና በነማነው የሽግግሩ መንግስት የሚፈጠረው በሚለው ጥያቄ ላይ ነው። ጠሚ አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ የወሰዳቸው ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ እርምጃዎች ኢትዮጵያንና ህዝቧን በቀላሉ መውጣት የማይችሉት አዘቅት ውስጥ ይዟቸው ገብቷል። ከዚህ በየቀኑ ጥልቀቱና ስፋቱ እያደገ ከሚሄድ አዘቅት ውስጥ በአስቸኳይ እራሳችንን የማናወጣ ከሆነ የኢትዮጵያ እንደ አገር ቀጣይነት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ይገባል። ይህንን አደጋ ለመከላከል የመጀመሪያው እርምጃ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ነው።

ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ አመታትን ያስቆጠረ ሥርዓተ መንግስት ያላት አገር ብትሆንም፣ኢትዮጵያ ውስጥ በግልጽ የሚታየው የፖለቲካ ባህል ነፍጥን እንጂ ውይይትና ድርድርን የሚጋብዝ አይደለም። ባለፉት 50 አመታት በግልፅ እንዳየነው ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን ለመፍታት ጠመንጃ ተሸክመን ጫካ ገብቶ መታገል እንጂ በጠረቤዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ ተወያይቶና ተደራድሮ ልዩነቶችን መፍታት ምርጫችን ሆኖ አያውቅም። ዛሬ ላይ ግን ከአሮጌውና ከውጤት አልባው የጠመንጃ ባህላችን ተላቅቀን የውይይትና የድርድር ባህል እንድንለማመድ አገራችን ኢትዮጵያ የገባችበት  ውስብስብ ሁኔታ ያስገድደናል። ይህ ግዳጅ አገርን ለማዳን የሚደረግ ግዳጅ ነውና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሙሉ ልቡ ሊቀበለው ይገባል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በየቦታው የሚካሄደው ጦርንት እያፈናቀለ፣እየገደለና እያሳደደ ያለው ኦሮሞ፣አማራ፣ትግሬ፣ሱማሌ፣ሲዳማ፣ወላይታ፣ጋምቤላ ወዘተ ሳይል ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ነው። ጠሚ አቢይ አህመድ በፈጠራት ኢትዮጵያ ውስጥ በሥራ አጥነት፣በድህነት፣በኑሮ ውድነት፣በረሃብና በቤት አልባነት የሚሰቃየው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። ስቃዩ፣በደሉና መከራው ብሔር አይለይም፣ ከእነዚህ ሰው ሰራሽ ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ግን ለመገላገል የምናደርገው ጥረትም በብሔር ሊለያየን አይገባም፣አዎ በፍጹም አይገባም!!!

እኛ ኢትዮጵያዊያን የተሰራብንን የልዩነት ግድግዳ አፍርሰን አንድ ላይ ከቆምን ችግሮቻችን ከኛ በታች ናቸው። ሦስት የተለያዩ መንግስታትን ከሥልጣን አስወግደናል፣ለኛ የሚበጅና በምርጫ አምጥተን በምርጫ ማስወገድ የምንችለው መንግስት የሚገኝበትን የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር ግን አልቻልንም። በአስቸኳይ መወገድ ያለበትን የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት ከማስወገዳችን በፊት ግን ከዚህ ቀድም ያልሰራነውን አንድ ትልቅና ወሳኝ ሥራ መስራት አለብን፣ ይህ ወሳኝ ሥራ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ከመወገዱ በፊት ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ነው። በእርግጥ ዛሬ አገራችን በምትገኝበት ሁኔታ ውስጥ የሽግግር መንግስት ማቋቋም በጣም አስቸጋሪና ፈታኝ ስራ ነው፣ሆኖም ፈተናውና ችግሩ ይህንን ስራ ሳንሰራ ቀርተን እኛም አገራችንም ከሚደርስብን አደጋ በጣም ያነሰ ነው። 

በዛሬዋ የተለያዩ የታጠቁ ኃይሎች በሚገኙባትና በፌዴራሉ መንግስትና በእነዚህ የታጠቁ ኃይሎች መካከል ጦርነት በሚካሄድባት ኢትዮጵያ ውስጥ የታጠቁ ኃይሎችን ያላካተተ ወይም የእነሱን ሙሉ ስምምነት ያላገኘ የሽግግር ሂደት መጀመር አይቻልም። በተለይ አማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ኦነግ-ሸኔና ህወሓትን ከግምት ውስጥ ሳናስገባ ስለሽግግር መንግስት ማሰብ አንችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት እንዴት ይመሰረታል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ ቢሆንሶችን (Cenarios) አስቀምጠን መመልከት እንችላለን፣ነገርግን በእያንዳንዱ ቢሆንስ ውስጥ የታጠቁ ኃይሎችን ከግምት ውስጥ ካላስገባን የምናስቀምጠው ቢሆንስ ከምኞት ያለፈ አይሆንም። ለምሳሌ፣የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በትጥቅና በህዝባዊ እምቢተኝነት በሚካሄደው ትግል ግብአተ መሬቱ ሲደርስ፣ የተለያዩ ባለድርሻዎችን ጋብዞ ያንን በተደጋጋሚ አያስፈልግም ያለውን የሽግግር ሂደት ማስጀመር ይችላል፣ነገር ግን ከተጋበዙት ባለድርሻዎች ውስጥ የታጠቁ ኃይሎች ከሌሉበት እነዚህ ኃይሎች የሽግግሩን ሂዳት ከመጀመሩ በፊት ወይም ከተጀመረ በኋላ የማሰናከል ከፍተኛ ችሎታ አላቸው። 

ቢሆንስ አንድ-

የታጠቁ ኃይሎች ግንባር ፈጥረው ግንባሩ የተለያዩ ባለድርሻዎችን (ሲቪል፣ወታደራዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ) ያሰባስባል። ይህ የባለድርሻዎች ስብስብ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ከመውደቁ በፊት ተወያይቶ/ተደራድሮ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ያቋቁማል። ይህ የሽግግር መንግስት ነው ለጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት የድርድር ጥያቄ ማቅረብ ያለበት። ጥያቄው ተቀባይነት ካገኘና ድርድሩ ከተሳካ፣ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት የሽግግሩ አባል ይሆንና ለሽግግሩ መንግስት ሥልጣን ያስረክባል። ጥያቄው ተቀባይነት ካላገኘ ወይም ድርድሩ ካልተሳካ ግን የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ያለው ዕድል በኃይል መወገድ ብቻ ነው።

ይህ ቢሆንስ እውን እንዲሆን፣የታጠቁ ኃይሎች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ከማስወገድ ባሻገር ኢትዮጵያ ውስጥ መፈጠር ያለበት የሽግግር መንግስት የተለያዩ የአገሪቱን ባለድርሻዎች ማካተት እንዳለበትና እያንዳንዱ ባለድርሻ በሽግግር መንግስት ምስረታ ሂደት ውስጥም ሆነ፣በሽግግሩ መንግስት ውስጥ የሚኖራቸው ተሳትፎ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ለመሆኑ በሙል ልብ መቀበል አለባቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ በህዝባዊ እምቢተኝነትና በትጥቅ የሚደረገው ትግል የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረስ አለበት። ከዚህ በተጨማሪ ለጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት የድርድር ጥያቄ የሚያቀርበው የሽግግር መንግስት አካታችና የትኛውም ባለድርሻ በበላይነት የማይቆጣጠረው መሆን አለበት።

ቢሆንስ ሁለት

አገር ውስጥና ከአገር ውጭ የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻዎች ጥምረት ፈጥረው ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት እንዴት ይፈጠራል በሚለው ጥያቄ ላይ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ። እነዚህ ባለድርሻዎች ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ተገናኝተው በወደፊቷ ኢትዮጵያ ጉዳዮች፣ በሽግግር መንግስት አስፈላጊነትና እንዴት ይፈጠራል በሚለው ጥያቄ ላይ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ። የዚህ ስምምነት ውጤት የታጠቁ ኃይሎችና የሲቪል ባለድርሻዎች ጥምረት ይሆናል። ይህ ጥምረት ለጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት እሱ እራሱ ተሳታፊ የሚሆንበት የሽግግር መንግስት እንዲፈጠር ጥሪ ያቀርባል። መንግስት ጥሪውን ከተቀበለ ጥምረቱና መንግስት ሰፋ ያለውን ባለድርሻ ያካተተ የሽግግር መንግስት ይመስርታሉ፣መንግስት ጥሪውን ካልተቀበለ የሽግግር መንግስት መመስረቱ አይቀርም፣ይህ የሽግግር መንግስት የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በኃይል ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ ወደ ሥልጣን ይመጣል።

ይህ ቢሆንስ እውን እንዲሆን፣በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት እየተዳከመ ሄዶ የታጠቁ ኃይሎች ግልፅ የበላይነት ሊኖራቸው ይገባል።

ቢሆንስ ሦስት

ኢትዮጵያ ውስጥ የፌዴራል ኃይሎች ከአማራ ኃይሎች ጋር ጦርነት ውስጥ ከገቡ ሦስት አመት ተቆጥሯል፣ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሽምቅ ውጊያ ከተጀመረ አመታት ተቆጥረዋል፣አሁን ደሞ የኢትዮጵያ መንግስት ከትግራይ ኃይሎችና ከጎረቤት ኤርትራ ጋር ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብቷል። ይህ ውጥረት ከፈነዳ ሱዳን ውስጥ ከሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ጋር የአፍሪካን ቀንድ ባጠቃላይ ምስራቅ አፍሪካን ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ይዞ ሊገባ ስለሚችል፣ አለም አቀፉ ማህበረሰብ (አሜሪካ፣የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ህብረት) ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት እንዲፈጠር የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት ማስገደድ ይችላሉ። በተለይም ከኤርትራና ከትግራይ ጋር የሚደረገው ጦርነት የኢትዮጵያን ውስጣዊ ክፍፍል በፍጥነት ስሌሚያባብሰውና ከፍተኛ የዜጎች ሞት፣መፈናቀልና ስደት ስለሚከሰት፣አለም አቀፉ ማህበረሰብ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ አድርጎ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ተወግዶ የሽግግር መንግስት ሥልጣኑን እንዲረከብ ሊያደርግ ይችላል።

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English

ኤክስ ፡ @zborkena

1 COMMENT

  1. ወንድም ኤፍሬም፦

    የሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት ላይ ብዙ አስረድተሀል። ኢትዮጵያን ከልብ ከሚወዱት አንዱ መሆንህን አደንቃለሁ። ልብ ያለው ግሩም ድርሰትህን ልብ ይበለው። በሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት ላይ የሚጨመር የለኝም። አመሠራረቱ ላይ ግን፣ ጥቂት ማለት ይቻላል። ሌሎች ልሂቃንም በአመሠራረቱ ላይ ይበልጥ እንድትወያዩና ወደ ስምምነት እንዲደረስ እመክራለሁ።

    ቢሆነስ 3 ላይ፣ የውጭ አካል ጎትተን አምጥተን ይበልጥ እንዲፈተፍት መፍቀድ ራስን ለውርደት መዳረግ ስለሆነ፣ ሊታሰብ አይገባውም። ባለታሪክ ኢትዮጵያውያን የውስጥ ጉዳያቸውን ራሳቸው ሊያስተካክሉ ይገባል። አድሮ ጥጃነት አይመጥነንም።

    ቢሆንስ 2፣ መጀመሪያ የውስጥ ኃይሎች ትብብር አድርገው፣ ከዚያም የውጪዎቹ በራሳቸው ተባብረው፣ በመጨረሻ ሁለቱም ይተባበራሉ ብሎ ማለም ለዛሬይቱ የኢትዮጵያ ትውልድ የሚሆን አይደለም። ዳያስፖራው ዛሬ ያለበትን ሁኔታ የምናውቀው ነው።

    ቢሆንስ 1 የአገር ውስጥ ባለድርሻዎች ትብብር ፈጥረው ከመንግሥት ጋር አገርን ያስቀደመ ድርድር ማድረጉም ከአገዛዝ ባሕላችንና ዛሬም ካለው ክስተት ውጭ ነው። ከደርግ ጀምሮ እስከ ዛሬ እንዳየነው፣ መንግሥት ሰጥቶ መቀበል ስለማያውቅ፣ ሕዝብ የማክበር ባህልም ስለሌለው፣ እየተራብንና እየተጎሳቆልን በተገዛ መሣሪያ ያለማንም ከልካይና ሕጋዊ ገደብ እያሳደደ፣ እያቆሰለና እየገደለ ላምበርክካችሁ የሚል አውሬ-አከል ገዢ ነው። ስለዚህ፣ ሊሆን የሚገባው፣ የአገር ውስጥ የታጠቁ ቡድኖች የቡድን ሕልማችውን በአገራዊ የጋራ ሕልም ተክተው፣ ሀብታም አገራቸውን ለማዳንና በጋራ ለማበልጸግ ኃያል የሆነ ትብብር በመፍጠር መንግሥትንም ወደ ትብብሩ እንዲገባ አስገድደው፣ ሁሉም የታጠቁ ኃይሎችና መንግሥት እኩል የአገር ባለቤት ሆነው፣ በ 1986 ዓ.ም. ኔልሰን ማንዴላና ሌሎች የአፓርታይድ መንግሥት ተቃዋሚ መሪዎች ከአፓርታይዱ ገዢ ፓርቲ ጋር የሽግግር መንግሥት መሥርተው፣ በአገራቸው ዳር እስክ ዳር ሰላም አስከብረው፣ በሀቀኛ ድርድር ዲሞክራሲያዊ ደቡብ አፍሪቃን እንዳዋለዱ፣ በኢትዮጵያም ተግባሩና የሥራ ዘመኑም የተገደበ የሽግግር መንግሥት በታጠቁ ኃይሎችና በገዢው ፓርቲ በጋራ ቢመሠረት፣ ከ967 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ ያየነው አገርና ሕዝብ በሌለ የዲሞክራሲያዊ ወይም የፌደራል ስርዓት ቅዠት ማታለሉ አብቅቶ፣ የሁላችንም አገር ለሆነች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ልንበቃ እንችላለን።

    ባለፉት 34 ዓመታት በወያኔ ጦር ኃይል በጎሣ ተሸንሽነን፣ የኢትዮጵያ መሬቱም በጦረኞች የምርጥ ጎሣ ስም ስለተሰጠው አብረን በሰላም ለዘመናት የኖርነውን ዜጎች ሁሉ ያበጣበጠንን ክልላዊነትና ጠባብነት በስምምነት አፍርሶ፣ የዛሬውን የአንድ ጎሣ ቡድን ያነገሠውን ፌደራልም ሆነ ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ ሕገ መንግሥት በማስወገድ፣ በመንግሥት ቅርፅ ላይ ወስኖ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት መሆኑን ሕጋዊና ተቋማዊ ዕውቅና የሰጠና ሕገ ወጥና ስድ የሆኑ የመንግሥት መሪዎችም ሕግ ሲጥሱ የሚቀጡበትን ሥርዓት በግልጽ በሚደነግግ ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት መተካት ያሻል። እንዲሁም፣ የመንግሥት አካላትን የሥልጣን ክፍፍልና የዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን መከበር እንዳያሻማ አድርጎ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ አሟልቶ አውጆ፣ ነጻ ፍትሐዊ ምርጫና አስመራጭ የሚረጋገጡባቸውን ሕግጋት አውጥቶና ምርጫውንም ለዚያ ለማብቃት የሚያስችሉትን ተቋማት ባግባቡ በጥራት አደራጅቶና ተቆጣጥሮ፣ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያው ታሪካዊ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ማብቃት ይቻላል። የእስከ ዛሬ መሪዎች የሕዝብ አገልጋይነት ቀርቶ ጌታው መሆናቸው በአዲሱ ሕገ መንግሥት መሠረት በሚደራጁት ጠንካራና ነፃና ገለልተኛ የመንግሥት አስተዳደርና ቁጥጥር ተቋማት መሣሪያነትም ጭምር መቋረጥ አለበት ።

    ሕገ መንግሥቱን ሀቀኛ የሕዝብና የመንግሥት የመስተዳድር ውል ከማድረጉ ጋር፣ የሽግግር መንግሥቱ ተቆጣጥሮ በመራውና በመሰከረለት ነፃና ፍትሐዊ ዲሞክራሲዊ ምርጫ (የኢትዮጵያ ሕዝብ 80 በመቶው ጦርነት ላይ ሆኖ ሳለ፣ በ7ኛው የብልጽግና ፓርቲ የንግሥና ማጽደቂያ የምርጫ ክርክር በተባለ ቲአትር ላይ የብልጽግና ተወካይና የኦሮሞ ክልል ጦርነት አንዱ ዋና መሪ አቶ አዲሱ አረጋ የኑሮ ውድነቱ በተለያዩ አገሮች ባሉ ጦርነቶችና በዘይት (FUEL) ውድነት ምክንያት አቅርቦት መቀነሱን ሲያወሳ፣ በአገር ቤቱ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የትግራይ፣ የአፋር፣ የጋምቤላ፣ የቤኒሻንጉልና የደቡብ የእርስ በእርስ ጦርነት ባለበት፣ የአርሶ አደር የጤፍ ክምር በመከላከያ ሞርታር በመቃጠሉ፣ በጎታ የተቀመጠ የምግብ እህል በመከላከያ እየተዛቀ ከአፈር ጋር በመቀላቀሉም ለገበያ የሚቀርብ ትርፍ ምርት በመጥፋቱ፣ በጦርነቱ ምክንያት ብዙ መሬትም ጦም በማደሩና፣ የብልጽግና መንግሥት የግብርናና ገጠር ልማት ባጀት ድርሻም የኢሕአዴግ ዘመኑን ሲሶ ሆኖ ምንም ሌላ የመንግሥት ድጎማም ባለመኖሩ፣ በአርሶ-አደሩ ክህሎትና በኋላ ቀር የግብርና መሣሪያው ላይም የመንግሥት ድጋፍ እንደተለመደው ስለሌለ፣ የምግብ ምርትና አቅርቦት ተዳክሞ የኑሮ ውድነት ማሻቀቡን የብልጽግናው መሪ ካድሬም ሆነ አጃቢ ፓርቲዎች መሸፋፈን እንጂ ማመን አልደፈሩም።) በሕዝብ ለተመረጠው ፓርቲ አዲሱ ሕገ መንግሥት በደንገገው መሠረት የመንግሥትን ሥልጣን ማስረከብ የሽግግር መንግሥቱ የመጨረሻ ተግባር ይሆናል። ሕገ መንግሥት ማርቀቁ፣ እስከ ዛሬ የተለመደው ዓይነት የግልብ ምሑራን ግልበጣ ሥራ መሆኑ ቀርቶ፣ በአሜሪካ፣ በአውሮጳ፣ በእስያና በአፍሪቃም የታዩት የሕገ መንግሥት ድክመቶችም እንዳይደገሙና ኢትዮጵያዊ ወዙም እንዲጎላ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ የሚችሉ ብዙ ብቁ የሕግ ምሁራንና አስተዋይ የአገር ሽማግሌዎች በአገር ቤትና በውጭም በብዛት አሉን።

    እዚህ ላይ፣ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓአላዊነት፣ በዲምክራስያዊ ሥርዓት ግንባታና በአባቶች ደምና አጥንት በተጠበቁና ከአያሌ የአፍሪቃና አሜሪካ አገራት ጋር ቀለማቱን እንደተጋራነው ሰንደቅ ዓላማችን ባሉ የጋራ ቅርሶች ላይ ድርድር ሊኖር አይገባም። ዓለምን ተጋርተው እየበዘበዙ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን የገዙትን የእንግሊዝና የፈረንሳይ መንግሥታት ቋንቆዎች በደስታ የተቀበልን ሕዝቦች፣ በፈጠራ ትርክት ታውረን በአገር መግባቢያነቱና በመንግሥት ቋንቋነቱ ረጅም ታሪክ ያለውን አማርኛንም በዚያው ማስቀጠሉ አገር ቢያኮራና ዕድገትም ለማፋጠን ቢጠቅም እንጂ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት፣ ዕድገትና አብሮነት ሊጎዳ አይችልም። የቀሩትን ቋንቋዎቻችንንም በየአካባቢው በዲሞክራሲያዊ የሕዝብ ውሳኔ የመጠቀሙ ጉዳይ የሚያከራክር አይደለም።

    በትግራይ፣ ኦሮሚያና በሌሎችም በራሳቸው ጎሣ መሪዎች ለዓመታት በተገዙ አካባቢዎች የተከሰተው አስከፊ መፈናቀል፣ ስደት፣ ሞትና ውድመት፣ ነፃ አውጪ ነን ላሉትም “ያውላችሁ ምሩና አገር አሻሽሉ” ተብለው የመስተዳድር ፈላጭ ቆራጭ ቢሆኑም፣ የቡድናቸውንና የዘመድ አዝማድ ኪስ ከማሳበጥና ድሀውን በጦርነት በመማገድ ቀድሞ ከነቀፉት ንጉሣዊ አስተዳደር የባሱ ጨቋኝና አውዳሚ ሆነዋል። የሕወሀት ውድመትና ምዝበራ በትግሬ፣ የኦሕዴዱ ውድመትና ምዝበራ በኦሮሞ፣ የብአዴንም በአማራ የሚመሰክሩት የጎሣ፟ መር አገዛዝን ራስ ወዳድነት፣ ስግብግብነት፣ አውዳሚነትና አረመኔነት ነው።

    የአገር ባለውለታዎችንና አገር ተረካቢ ወጣቶችን ሲገድልና ለገንጣይና አስገንጣይ አገር ሲያመቻች ኖሮ የከሰመውን ደርግን እንተወውና፣ በተለይ የሕወሀት የጎሣ አገዛዝ፣ 1ኛ/ ለመሬትም የብሔር ስም ሰጥቶ ከልሎ፣ ከአማራም ወልቃይትን፣ ጠገዴን ጠለምትን፣ ሁመራን፣ ራያንና ሌላም አገር በኃይል ቀምቶ እርስ በእርስ በየአካባቢው አፋጅቶናል፣ 2ኛ/ ኤርትራን የቅጥፈት የኮሎኒ ትርክት ፈጥሮ አስገንጥሎ የወንድም ጠላት ፈጥሮልን ከመገዳደሉ ጋር ወደብ አልባም አድርጎናል፣ 3ኛ/ ለባለ 83 ጎሣዋ ኢትዮጵያ ቢበዛ የዘጠኝ ጎሣ ፈላጭ ቆራጭነት የነገሠባቸው 9 የጎሣ ክልሎች ፈጥሮ፣ የቀረነውን 74 ክልል-የለሽ ጎሣዎችን የባለክልሎቹ ዘጠኝ ጎሣዎች ተገዥ/ባሪያ አድርጎናል፣ 4ኛ/ ዲሞክራሲያዊነትም ሆነ ፌደራልነት ያልሸተተው፣ የሹም የሥልጣን ብልግና ምንምን መቆጣጠሪያ የሌለው የአገዛዝ ሕገ መንግሥት አውጆ፣ የአምባገነንነት ልክፍት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ እንዲሰፍን አድርጓል። ነገር ግን፣ በሕወሀት፟ መሩ የስግብግብ አገዛዝ ዘመን ለግብርና የተሻለ ድጋፍ የተሰጠበትና ኢኮኖሚውም የላቀ ዕድገት ያሳየበት ሆኖ ሳለ፣ በቂ የገንዘብ አቅም ሳይኖር፣ ከንጉሠ ነገሥቱ ዘመን 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ያነሰ ጥራት ያላቸው ከ 50 በላይ የክልል ዩኒቬርሲቲዎች ናቸው ብሎ ብቁ መምህራን፣ ማስተማሪያ መፃሕፍት፣ ላቦራቶሪ፣ የሎጂስቲክ ድጋፍና ቤተ መፃሕፍት ሳይኖሩ ግድግዳና ጣራ ብቻ አቁሞ መሐይም መፈልፈሉ፣ ዋና ዓላማው ትውልድና አገር ለማዘመንና ለመገንባት ሳይሆን የተለመደው የሕወሀት ቅጥፈትና የዋህ ሕዝብ የማታለል ሴራ ሆኖ ይታያል።

    በኢሕአዴግ-ኦንግ ሕገ መንግሥት ውስጥ፣ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ጭራሽ መኖራቸውም ተረስቶ ከሪፓብሊክ መንግሥቱ ውጭ ሆነው፣ በአንቀጽ 47 መሠረት የሪፓብሊኩ መንግሥት በዘጠኙ ጎሣዎችና የጎሣ ክልሎች ላይ ብቻ ተመሥርቶ፣ በአንቀጽ 62 መሠረት የክልል ባለሥልጣናት የማዕከላዊውን መንግሥት ፓርላማና ሥራ አስፈጻሚውንም ዘርፍ የማዘዝ እንዲሁም ሕገ መንግሥት የመተርጎም የበላይ ሥልጣን ይዘው (በቅርቡም የፌደሬሽን ም/ቤት ስለ ወልቃይትና ራያ የወሰነውን የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ማገዱ ሕገ መንግሥት ተብየው በመንግሥት አካላትም እንደማይከበር ምስክር ነው።) ፌደራልነቱም ውሸት ሆኖ፣ በዚህ የቅጥፈት ሥርዓት መሠረት የደረሰብንን የእርስ በእርስ መጋደል፣ ስደት፣ መፈናቀልና ሞት ለማስቆም፣ ጎሣ መሩን አውዳሚ ሥርዓት ማፍረስና በአውሮጳና አሜሪካ ብዙ ወገኖቻችን ተሰድደው በሰላም እንደሚኖሩባቸው ባለብዙ ጎሣ አገሮች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በሚያከብር፣ የሁሉን ኢትዮጵያውያን እኩልነትና ደህንነት በሚያረጋግጥና ኢትዮጵያም የጋራችን በምትሆንበት የሽግግር ሥርዓት መተካቱ ከዛሬው ራስ ወዳድ የአውሬ አገዛዝ ይገላግላል። ይቺን ሀብታምና ለምለም አገራችንንና ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ከወቅቱ ጎሣ መር የውድቀት አዘቅት የሚያወጣ የሽግግር መንግሥት አስፈላጊ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው።

    ለዚህ የሚረዳ “THE Small Miracle, edited by Steven Friedman and Doreen Atkinson, South African Review 7, Sigma Press (pty) Ltd., Pretoria. 1994.” ስለ ማንዴላዋ ደቡብ አፍሪቃ የ1986 ዓ.ም. ታሪካዊ የዲሞክራሲ ግንባታ ሽግግር ልምድ ማንበቡ ይጠቅማል። ከ1986 ዓ.ም. የደቡብ አፍሪቃ ስኬታማ ልሂቃን ጋር ሲተያዩ፣ የምንመኘውን የዲሞክራሲያዊ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ በማሳካቱ ላይ ኢትዮጵያውያንም ከማንም እንደማያንሱ የሚፈተኑበትና የሚያረጋግጡበት ወይም የሚወድቁበት የታሪክ አጋጣሚ ላይ ነን።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News