
ጠገናው ጎሹ
ከረጅሙ ዘመን
ከእኛው ከራሳችን
ከታሪክ አምዳችን
መማር ከተሳነን
በጎውን ተጠቅመን
ጎጅውን አርመን
መራመድ ካቃተን
ከቶም ይባስ ብለን
በሆነ ባልሆነው እየተጠላለፍን
መቀጠል ከፈለግን
ቁልቁለት መውረዱን
በአዙሪት መዞርን
ምርጫችን ካደርግን
የምናስብበት አእምሮ የሰጠን
የምንከውንበት ብቁ አካል ያደለን
ፈጣሪ ምን ያርገን?
መከራና ውርደት ያለማመደንን
የስድስት ዙር “ምርጫን”
ከምር በቃ ብለን
ሰባተኛ ዙሩን
በእውን ተፀይፈን
በአንድ ላይ አንድ ሆነን
ለጋራ አገር ብለን
በአርበኝነት ፀንተን
ለእውነተኛ ምርጫ መንገድ ካላበጀን
ፈጣሪ ምን ያርገን?
ምንስ ይሁንልን?
ፊደል መቁጠራችን
ማንበብ መጻፋችን
መፈላሰፋችን
ልሂቅነታችን
የክህሎት ሙያችን
መሆን ከተሳነው ብርቱ መሳሪያችን
ሰባብሮ መውጫችን
ከውድቀት አውዳችን
የነፃነት አገር እውን ማድረጊያችን
ምን ያርግ ፈጣሪያችን?
እናም ከእኩያን አገዛዝ መላቀቅ ካለብን
የፈጣሪን ድጋፍ ከምር እየጠየቅን
የሰጠንን አቅም ሥራ ላይ እያዋልን
የአያሌ ዘመናት ግፍና መከራን
እምቢ ይበቃናል ማለት ነው ያለብን።
የመከራ ምርጫን ምርጫችን ካደረግን
የሸፍጥ ፖለቲካ አጃቢዎች ከሆን
ለምን ድረስልን እያልን እንጮሃለን?
እንዴትስ ሊሰማን እንዴትስ ሊረዳን?
እናም እጅግ ብንዘገይም
ልብ እንበል አሁንም
የሰጠንን አቅም
ከምር እንጠቀም
ብሎም ነፃ እንውጣ እውን ይሁን ሰላም።
አዎ! ትንፋሽን ዋጥ አርገን
በስሜት መንጉዱን
ከምር ተቆጣጥረን
እንዲህ እንጠየቀው እኛኑ ራሳችን።
አእምሮን የሚያህል ማሰቢያ ሰጥተኸን
ሙሉ አካልን ያህል አበጅተህልን
እኛው ራሳችን
ከተሽመደመድን
ወደ ላይ ከመውጣት ቁልቁል ከወረድን
ከሌሎች ፍጡራን ልቀን ካልተገኘን
የባርነት ቀንበር ተሸካሚ ከሆን
ለምን ይገርመናል አንተስ ብትተወን?
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
ቦርከናን ይደግፉ :-እዚህ ገጽ ላይ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






