
ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
ሚያዚያ11፣2018
በአገራችንም ሆነ በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ያለው ትልቁና ዋናው ችግር የመንግስትን መኪና የጨበጠ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ሁሉ በአጋጣሚ ያገኘውን ዕድል ወይም የጨበጠውን የመንግስት መኪና በመጠቀም አንድን ህዝብ መጨቆኛ፣ የአገርን ሀብት መሸጪያና የመዝረፊያ መሳሪያ ማድረግ መቻሉ ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ በአገራችንም ሆነ በተቀሩት በተለይም በአፍሪካ አገሮች ውስጥ ከስራ-ክፍፍል፣ ከቴክኖሎጂ መዳበር፣ ከከተማዎችና መንደሮች መገንባት ጋር እየተያያዘ ከታች ወደ ላይ ያደገ የመንግስት መኪና ለመዋቀር አለመቻሉ ነው። የአገራችንም ሆነ የአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የመንግስት መኪና አወቃቀሮች ከየአገሮች የማቴሪያል መሰረት ጋር በመያያዝ እያደጉና እየተስፋፉ፣ እንዲሁም ቀልጣፋ በሆነ መልክ የተዋቀሩና ለተሟላ የአገር ግንባታ እንዲያገለግሉ ሆነው የዳበሩ ሳይሆን ከውጭ ኃይሎች ጋር በቀጥታ የተያያዙና የእነሱንም ጥቅም የሚያስጠብቁ ናቸው። የመንግስቱን መኪና የጨበጡና የሚጨብጡ ኃይሎች ስልጣን ላይ ሲወጡ ሆን ተበለው ተመርጠው ስልጣን ላይ ስለሚቀመጡና የሚሰሩትንም ነገር ስለማያውቁ ከውጭ የተዘጋጀላቸውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ በሁሉም አቅጣጫ ወደ ውስጥ የተዛባን ሁኔታ ይፈጥራሉ። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው ትውልድ በመተላለፍና እንደ ተራ ነገርም በመወሰድ ወደ ውስጥ ያተኮረና የሰፊውን ህዝብ ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል የተስተካከለና ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ይሆናል።
ወደ ካፒታሊስት አገሮች ስንመጣ አነሰም በዛም ከማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የመንግስትን ምንነትና ተግባሩንም በሚመለከት፣ እንዲያም ሲል ግለሰብአዊ ነፃነትና የህግ-የበላይነት አስፈላጊነት በሚገባ ተብላልተው ውይይት ስለተደረገባቸውና፣ አነሰም በዛም ጥቅሙን የሚያስጠብቅ የካፒታሊስት መደብ በመፈጠሩ የተነሳ የካፒታሊስት አገሮች መንግስታት ዋናው ተግባር ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ግንባታ ተግባራዊ ማድረግ ነበር። በዚያው መጠንም የሰራተኛው መደብ የራሱን ጥቅም የሚያስጠብቅለትን የሰራተኛውን ማህበር በመመስረት አነሰም በዛም የደሞዝና የስራ-ሰዓትን አስመልክቶ የመደራደር ኃይሉ ከፍ ሊል ችሏል። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ የሰራተኛው መደብ የመደራደር ኃይል በተለይም የፋይናንስ ካፒታል በአሸናፊነት ከወጣበት ጊዜ ጀምሮና፣ መንግስታትም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩበት፣ በተለይም ካለፉት 40 ዓመታት ጀምሮ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነስ መጥቷል ማለት ይቻላል። ስለሆነም የመንግስት ሚናና ተግባሩ አድሎአዊ እየሆነ የመጣበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ሰፊው ህዝብ በየአራት ዓመቱ ደስ የሚለውንና ጥቅሜን ያስጠብቅልኛል የሚለውን ፓርቲ ቢመርጥም፣ የሚመረጠው ፓርቲና ስልጣንን የሚጨብጠው ህዝብ የሰጠውን አመኔታ በመዘንጋት የካፒታሊስቶች ጉያ ውስጥ በመውደቅና የእነሱን ትዕዛዝ በመቀበል የሀብት ሽግሽግ ያደረገበትንና የሚያደርግበትን ሁኔታ እነመለከታለን። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተለይም ከአርባ ዓመት ጀምሮ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተቀባይነትን ካገኘበት ጊዜ ጀምሮና በተግባርም መመንዘር ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ መንግስታት ሳያወጡና ሳያወርዱ ይህንን የአንጀት አጥብቂኝ(Austerity Economic Policy)በመከተላቸው ሀብት ያላቸው የባሰውኑ ሀብታም ሲሆኑና ሲደልቡ፣ ኑሮውን ለማሸነፍ ላቡን እያንጠፈጠፈ በሚያገኘው ደሞዝ ብቻ የሚተዳደረው የሰራተኛ መደብ በጣም ደሀ እየሆነ የመጣበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በጣም ጥሩ በሆኑ መጽሀፎች በማስረጃ ተደግፈው በተጻፉት መሰረት በተለይም እነ ሚልተን ፍሪድማን፣ ወይም የቺካጎ ልጆች ተብለው የሚጠሩት የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች ፕሬዚደንት ሬገንና ሚስ ቴቸር ስልጣንን ከተረከቡበት ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ በኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካሪነት እንዲያማክሩ አመቺ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው ጊዜ ጀምሮ እስከ 1970ዎቹ መጨረሻ ድረስ በጥሩ ሁኔታ ላይ የነበረው የሰራተኛው መደብ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ያገኝ የነበረው ጥቅማ ጥቅሙ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ የተነሳ የራሱ መደጎሚያ ሊሆን የሚችል ሀብት ማፍራት እንዳልቻለ ማረጋገጥ ተችሏል። ሁሉም ነገር ለገበያው መለቀቅ አለበት በሚለው ሎጂካዊ ያልሆነና በሳይንስም የማይረጋገጥ አስተሳሰብ፣ መዛባትም ካለ ገበያው ራሱን በራሱ ያስተካክለዋል፣ ስለሆነም የመንግስት ጣልቃ-ገብነት አስፈላጊ አይደለም የሚለው የእነ ሚልተን ፍሪድማን ምክር ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በመሆኑ የተነሳ በኢኮኖሚው ውስጥ የበለጠ መዛባት ሊፈጠር ችሏል። በዚህም ምክንያት ከምርታማ መስኩ ይልቅ የፋይናንስ መስኩ በማበጡ የተነሳ ፋይናንስ ካፒታል ከምርታማ መስክ ወደ አየር ባየር የንግድ መስኩ እንዲሸጋሸግ በመደረጉ በዚያው መጠንም የሰራተኛው የመደረዳርና ሀብትም የማፍራት ኃይል በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ እያለ ሊመጣ ችሏል። የመንግስትን መኪና የጨበጡ ፕሬዚደንቶች፣ ወይም ጠቅላይ ሚኒስተሮች ራሳቸው በኢኮኖሚ ታሪክና ሳይንስ፣ እንዲሁም ቲዎሪ የሰለጠኑ ባለመሆናቸውና፣ በጠጨማሪም ስለሶስዮሎጂ ምንም የሚያውቁት ነገር ስለሌለ ሳያወጡ ሳያወርዱ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች የሚሰጧቸውን ምክር አሜን ብለው በመቀበልና በመተግበር በሰፊው ህዝብ ላይ ከፍተኛ በደል መፈጸም ችለዋል፤ እየፈጸሙም ነው። ይህም የሚያረጋግጠው መንግስት የሚባለው መኪና የሰፊው ህዝብ አገልጋይ መሆኑ ቀርቶ በሀብት በናጠጡ ጥቂት ባንኮችና ኢንዱስትሪዎች ቁጥጥር ስር እንደዋለ ነው። ሰሞኑን የቫቲካኑ ጳጳስ ሊዎ 14ኛው ይህንን ሁኔታ በመመልከት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ጦርነት የሀብታሞች እንደሆነ አመልክተዋል።
የካፒታሊዝምን ዕድገት ለመገንዘብ ከፈለግን ኋላ በመሄድ በትንሹም ቢሆን የተወሰነ ትንተና መስጠት ያስፈልጋል። የካፒታሊዝምን አጠቃላይና ሁለ-ገብ ዕድገት በደንብ የተከታተለ ሊገነዘብ የሚችለው በታሪክ ውስጥ በግለሰቦች ታታሪነትና ፈጠራ ብቻ ካፒታሊዝም በፍጹም አላደገም። ለካፒታሊዝም ዕድገት አመቺ ሁኔታዎች የተፈጠሩት የተለያዩ አገዛዞች ቀደም ብለው ከተማዎችንና መንደሮችን በዕውቅ እንዲገነባ በማድረጋቸውና፣ ወደ ውስጥ ያተኮረ ለካፒታሊዝም ዕድገት የሚያመች የጣልቃ-ገብነት(Interventionist Policy) በመከተላቸው ነው። ከዚህም በላይ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ መፈጠርና ዕድገት የሚያመቹ ዩኒቨርሲቲዎችንና፣ በኋላ ላይም የዕደ-ጥበብ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች በመንግስት በመቋቋማቸው ብቻ ነው። እንደሚታወቀው ካፒታሊስቶች ለትርፍና ከትርፍ አኳያ ብቻ ስለሚያመርቱ በራሳቸው ጥረት የሳይንስና የቴክኖሎጂ መመርመሪያና መፍጠሪያ ዩኒቨርሲቲዎችንና ኮሌጆችን ሊገነቡ በፍጹም አይችሉም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ለካፒታሊዝም ዕድገት የሚያመች የመመላለሻ መገናኛ እንደ ባቡር ሃዲድ የመሳሰሉት በመንግስት ጣልቃ ገብነትና የመዋዕለ-ነዋይ ፍሰት ብቻ ነው ካፒታሊዝም መፈናፈኛ ማግኘትና ለማደግ የበቃው። ባጭሩ እንደሚባለው በረቀቀው እጅ (Invisible Hand)አማካይነት በፍጹም ካፒታሊዝም ለማደግ ባልቻለ ነበር። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በተለይም የምዕራብ አውሮፓው ኢኮኖሚ ከፍተኛ ውድመት ስለደረሰበት፣ ቤቶችና የመገናኛ መስመሮች ስለተሰባበሩ፣ የውሃ ማጠራቀሚያና ቧንባዎች ስለወደሙ፣ እነዚህን የወደሙ ነገሮች በሙሉ የግለ-ሰብ ካፒታሊስቶች በራሳቸው ተነሳሽነት ሊጠግኗቸውና ለሰፈው ህዝብ ሊያቀርቡ አይችሉም። በቂም የፋይናንስ ምንጭና መሰረት ስለሌላቸው ይህንን ስራ ማከናወን የጀመረው መንግስት ነው ማለት ይቻላል። ይህንንም የኬይንስ የጣልቃ-ገብ ፖሊሲ በመባል ይታወቃል። ኬይንስ የሚባለው የእንግሊዙ ታላቅ ኢኮኖሚስት በተለይም በ1929 ዓ.ም የደረሰውን ትልቁን የኢኮኖሚ ቀውስ(The Great Economic Depression) በሚገባ ካጠና በኋላ የሰጠው ታላቅ ምክር የገበያ ኢኮኖሚ ራሱን በራሱ የማረምና የማስተካከል ኃይል ስለሌለው፣ በተለይም በካፒታሊስት ኢኮኖሚ ውስጥ የተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች ርስ በርሳቸው በተያያዙበት ሁኔታና፣ የሰራተኛው መድብም በስራ መስኩ ላይ የሚመካ በመሆኑ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ በሚፈጠርበት ጊዜ በፊስካል ፖሊሲ አማካይነት ጣልቃ በመግባት መንግስት ብቻ ነው እርማት ማድረግ የሚችለው በማለት አብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች መንግስታት ይህንን ምክር በመቀበልና ልዩ ዐይነት የክሬዲት ሲይስተም በመዘርጋት ኢኮኖሚው በአጭር ጊዜ ውስጥ በማንሰራራት የሰፊው ህዝብ የመግዛት ኃይል ከፍ ሊል ቻለ። በዚህም ምክንያት የተነሳ ኢኮኖሚው በሁሉም አቅጣጫ ማደግና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችም በመፈጠራቸው በአጠቃላይ ሲታይ ካፒታሊዝም በየአገሮቹ ውስጥ ብቻ ሳይወሰን ዓለም አቀፋዊ በመሆን የዓለምን ህዝብ ማስተሳሰር ቻለ።
ይሁንና ግን በተለይም በ1973 ዓ.ም በዘይት ዋጋ መወደድ የተነሳ ኢኮኖሚያዊ ቀውስና፣ በተለይም በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ ግስሽበት በመታየቱ እነ ሚልተን ፍሪድማን የሚባሉት የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች ለዋጋ ግሽበት መታየት ተጠያቂ ያደረጉት የመንግስትን በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ-ገብነትን ነው። ስለሆነም መንግስት የግዴታ ገበያውን ለካፒታሊስቶች ሙሉ በሙሉ ክፍት በማድረግ የዕቃዎች ዋጋ በአቅራቢና በጠያቂ(Supply & Demand) መወሰን አለበት የሚል ነው። በተለይም ከ1950 መጀመሪያ ጀምሮ እስከ 1970 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ ካፒታሊዝም በሚገባ ካደገ በኋላና የህዝቡም የመግዛት ኃይል በከፍተኛ ደረጃ መሻሻልን ቢያሳይም የተለያየ አመለካከት ባላቸው በኢኮኖሚስቶች መሀከል በተደረገ ትግል የተነሳ የኒዎ-ሊበራል አመለካከት ያላቸው ኢኮኖሚስቶች ቀስ በቀስ የበላይነትን በመቀዳጀታቸው የመንግስት ሚና ከ1979 ዓ-ም ጀምሮ እየቀነሰ ሊመጣ ቻለ። ስለሆነም መንግስትም በተዛዛዋሪ በባንኮችና በኢንዱስትሪዎች ቁጥጥር ስር በመውደቁ የተነሳ በተለይም ለካፒታሊስቶች የቀረጥ ቅነሳ በማድረግ እነሱን ሲያደልብ፣ በዚያው መጠንም የሰራተኛው መደብ እየተጎዳ መምጣት ቻለ። በሚያገኘው የወር ወይም የዓመት ደሞዝ ብቻ በመተማመን ለመደጎሚያ የሚሆነውን ሀብት ማፍራት አልቻለም። የራሱንም ቤት የመስራት ዕድል በፍጹም ሊያገኝ አልቻለም። በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግስት ጣልቃ-ገብነት በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ የካፒታሊስቶችን በሀብት መናጠጥ በጣም ከፍ ሲያደርገው በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀብትን የመቆጣጠር ዕድላቸው እየጨመረ ሊመጣ ቻለ። በተዘዋዋሪም ዓለም አቀፋዊ በሚባሉ ተቋማት ላይ ተፅዕኖ በማሳደር አብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች መንግስታት፣ በተለይም የአፍሪካ መንግስታትና አገራችንንም ጨምሮ አጠቃላይና ህዝባዊ ሀብትን ሊፈጥር የማያስችል የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ተገደዱ። በዚህም የተነሳ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮችና በአገራችንም ጭምር ፈጣሪ የሆነና ቴኮኖሎጂን የሚያዳብርና የሚያስፋፋ ሳይሆን በሀብት የደለበና ቅንጦትነት ያላቸውን የፍጆታ ዕቃዎች የሚጠቀም አዲስ የህብረተሰብ ክፍል በመፈጠሩ የተነሳ ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በተለይም የውጭ ንግድን መዛብት ሲያስከትል፣ በዚያው መጠንም አገሮች ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ከአይ ኤም ኤፍና ከዓለም ባንክ የሚበደሩት ብድር እየተቆለለና አገሮችም በየጊዜው መክፈል የማይችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ። በአገራችንም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ይህንን ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተል አለብን ወይ? የሚያመጣው ጥቅምስ ምንድን ነው? ጉዳቱስ ምንድን ነው? ተብሎ ውይይት ስለማይደረግ መንግስታት በጭፍን አስተሳሰብ በመመራት በተከታታይ ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን የሚያስፋፋ፣ እንዲያም ሲል የውጭ ንግድ ሚዛንን የሚያዛባና የውጭ ዕዳን እንዲቆለል የሚያደርግ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ተገደዱ። በአገራችን ምድር ብቻ ይህ ዐይነቱ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን የሚያስፋፋና ህዝባችንን አቅመ-ቢስ የሚያደርግ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለ36 ዓመታት በተከታታይ ተግባራዊ መሆን ችሏል። በአጠቃላይ ሲታይ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን በኃይል አስለላፍ ላይ ያሰከተለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ታች በሚከተለው አንቀጽ ላይ እንመልከት።
የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተቀባይነትን ማግኘትና ተግባራዊ መሆን የሚያረጋግጠው በተለይም ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ካፒታሊስት አገሮች ውስጥ የኃይል አሰላለፍ እንደተለወጠና መንግስት የሚባለው የጠቅላላው ህዝብ አገልጋይ ሳይሆን እጅግ በረቀቀ መንገድ በጣም ጥቂት የሚሆነውን የህብረተሰብ-ክፍል በሀብት እንዲደልብ በማድረግ ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነውን ህዝብ ደግሞ አቅመ-ቢስ እንዳደረገው እንመለከታለን። በተለይም እንደ አሜሪካ በመሳሰሉት የካፒታሊስት አገሮችና በተቀሩትም የምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ መንግስታት ከሚሊተሪ-ኢንዱስትሪ ውስብስብ (Military Industrial Complex) ጋር በመቆላለፍና ለህዝብ የሚውለውንና ድህነትን ሊቀርፍ የሚችለውን ከፍተኛ ባጀት ለጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች በመመደብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነትን እንዲያካሂዱ ተገደዋል። ይህም ጦርነት በአንድ በኩል ጥንታዊ ታሪክ ያላቸውን አገሮችና ባህላቸውን ማፈራረስ ሲሆን፣ በዚያው መጠንም ህዝቡ ሲበታተንና አለኝታ ሲያጣ ያለውን የጥሬ-ሀብት፣ ዘይትና ጋዝ ለመዝረፍ ነው። ይህም ጉዳይ በሊቢያ በግልጽ የሚካሄድ ሲሆን፣ ዘረፋውንም የሚያካሂዱት በተለይም የአሜሪካንና የፈረንሳይ የዘይት ትላልቅ ኩባንያዎች ናቸው። ጠለላውን የሚሰጧቸውም ወይም እንደፈለጋችሁ ዝረፉ የሚሏቸው ደግሞ ስለጠን፣ የፓርሊሜንተሪ ዲሞክራሲ አለን፣ በተለይም በህግ የበላይነት የምንተዳደርና፣ በዚህም የምናምን ነን በሚሉ የካፒታሊስት አገሮች መንግስታት አማካይነት ነው። ይህ ጉዳይ ለአብዛኛዎቹ በፖለቲካ ዓለም ውስጥ በመሳተፍ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል በሚሉት ኢትዮጵያውያን ምሁር ነን ባዮች ዘንድ በፍጹም ግልጽ አይደለም። በእነዚህ ፖለቲከኛ ነን ባዮች ዕምነት በካፒታሊስት አገሮች በመንግስታትና በኢንዱስትሪዎች ተግባራዊ የሚሆነው ፖሊሲ ሁሉ ቅዱሳዊ ሲሆን፣ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮቹ በማን አለኝበት እየተነሱ የዓለምን ህግ በመጣስ የሚያካሂዱት ጦርነትና ህዝብን እንዳለ መጨፍጨፍ፣ እንዲያም ሲል ጥንታዊ የታሪክ ቅርስ የሆኑ ህንፃዎችን ማውደምና ቅርሳቸውንም መዝረፍ፣ የቀረው ህዝብ ደግሞ ጠዋሪ አጥቶና ግራ-ተጋብቶ መንከራተት በኢትዮጵያውያን የፖለቲካ አክቲቪስቶችና ሚዲያውን በሚቆጣጠሩት ጋዜጠኖች ነን ባዮች ዘንድ አሜሪካንና ግብረ-አበሮቿ የሚያካሂዱት ጦርነት ፍትሃዊና ቅዱሳዊ ነው። ይህንን የአሜሪካኖችንና የተቀረውን የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊቶችን ሚና፣ በተጨማሪም እንደ ሲአይኤ የመሳሰሉት የስለላ ድርጅቶች የሚያቀርቡትን የተሳሳተ መረጃ፣ እንዲሁም በእየአገሩ እየገቡ አንድን መንግስት እንዳለ መገርሰስና ህዝብን መጨፍጨፍ አስመልክቶ ራሳቸው ክሪቲካል አመለካከት ያላቸው የአሜሪካንና የምዕራብ አውሮፓ ምሁራን በሰፊው የሚያትቱትና በመጽሀፍም መልክ የሚያቀርቡት ነው። አንድ ቦታ ስብሰባ ላይ ተቀምጠን ከተወሰኑ ሰዎች ጋር ይህንን ጉዳይ አስመልክት ስናወራ፣ ወዳጄ አለኝ አንዱ፣ ዛሬ የዓለምን ሁኔታ ለመረዳት አንድ ሰው የግዴታ ማርክሲስት ወይም ኮሙኒስት መሆን አይጠበቅበትም፤ ሁሉም ነገር በግልጽ የሚታይና ሰበቦችን እየፈለጉ ጦርነትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማካሄድ በህግ-መንግስቱ ያልተፈቀደና የየመንግስታቱም ተግባር የየአገራቸውን ደህነንት መጠበቅ፣ ኢኮኖሚውን ፍትሃዊ-በሆነ መልክ ማስተካከልና ህዝቡም በስምምነት የሚኖርበትን ሁኔታ ብቻ መፍጠር ነበር ያለኝ በጣም ልቤን ነካው። በእርግጥም በማንኛውም አገር ውስጥ አንድ ህዝብ አንድን ፓርቲ ስልጣን እንዲጨብጥ ሲመርጠው በስነ-ስርዓት እንዲያስተዳድረው እንጂ በየቦታው እየገባህ ጦርነትን ማካሄድ አለብህ፣ ህዝቡ ከአገሩ እየተፈናቀለ ሲመጣ እዚሁ መጠለያ ስጥ በማለት አይደለም። ራሳቸው ፓርቲዎችና የመንግስት ሰራተኞች፣ የጦር መኮንኖችና ፕሬዚደንቶችና ሚኒስተሮች ህዝብ እየሰራና ቀረጥ እየከፈለ ገቢ በሚያስገባው ገንዘብ ስለሚተዳደሩ ከህገ-መንግስትና ከየፓርቲዎች ፕሮግራማቸው ውጭ አገራቸውንና ህዝባቸውን የሚበድል፣ እንዲሁም የሚያዘበራርቅ ነገር ማድረግ የለባቸውም። የመንግስትን ተግባር በሚመለከት(The Theory of the State) ከግሪክ ፈላስፋዎች ጀምሮ እስከ 19ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ በእንግሊዝና፣ በተለይም በጀርመን ፈላስፋዎች በሚገባ ተጽፎና ተተንትኖ ቀርቧል። በተለይም የጀርመነን ክላሲኮች ጥበባዊ የሆነ መንግስት ምን መምሰል አለበት? ሚናውስ ምንድን ነው? በሚል በሚገባ ተወያይተው ያቀረቡት በአንድ አሜሪካዊ ምሁር በሚገባ ተተንቶኖ ቀርቧል። በኋላ ላይም በተለይም በ1950ዎቹና ከዚያም በኋላ በእነ ፖላንትሳዝ የመንግስትን ተግባር አስመልክቶ በሚገባት ተተንትኖ ቀርቧል። አስቸጋሪው ነገር ግን በተለይም ነገሮችን በጥቁርና በነጭ እየሳሉ ለማየት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኛ ነን ባዮች ሳያውቁት የፋሺስቶቶችን አስተሳሰብ እያንፀባረቁ ነው። ከምሁራዊ ብስለት እጦት የተነሳና በጣምም ሰነፍ ስለሆኑ ወደ ኋላ በመመለስ ነገሮች ሁሉ እዚህ ደረጃ ላይ እንዴት ሊደርሱ ቻሉ? ምክንያቶቻቸውስ ምንድን ነው? ብለው የመጠየቅ ባህልና ችሎታ የላቸውም። ለማንኛውም ሁሉም ነገር በቲዎሪና በኢምፔሪካል ደረጃ ተጽፎና ተረጋግጦ ቀርቧል።
ነገሩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ መንግስትን እንደመቅደስ እያመሳሰልን ከአገራችን ሁኔታ በመነሳት አንዳንድ ነገሮችን እንበል። በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት በአጠቃላይ ስለቤተክርስቲያንና፣ በተለይም ደግሞ ስለመቅደስ ምንነት ያለውን ትምህርታዊ መሰረተ-ሃሳብ ግንዛቤ ያላችሁ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው መቅደስ ውስጥ ማንኛውም ሰው አይገባም። ቄስ፣ ዲያቆንና ጳጳስ ብቻ ናቸው ገብተው መቀደስ የሚፈቀድላቸው። ደብተራና ያፈረሰ ቄስም መቅደስ ውስጥ በፍጹም መግባት አይፈቀድላቸውም። ቄስና ዲያቆን፣ እንዲሁም ጳጳስ ቤተመቅደስ ውስጥ የሚገቡት መንፈሳቸውም በጣም ንጹህ ነው ተብሎ ስለሚታመንበት ነው። ከእግዚአብሔርም ጋር ልዩ ዐይነት ግኑኝነት ያላቸው ሰዎች በመሆናቸው ማንኛውንም ሰው የሚጎዳ፣ ወይም የሚያስቀይሞ ነገር በፍጹም አያደርጉም። ሰውን የሚጎዳ፣ ቤተክርስቲያንን የሚያጎድፍ ስራ የሚሰሩ ከሆነ ይቀሰፋሉ ይባላል። ይህ የቱን ያህል ዕውነት እንደሆነ ማረጋገጥ ባይቻልም ሰውን የሚጎዳ ወይም ቤተክርስቲያንን፣ በተለይም ቤተመቅደስን የሚያጎድፍ ስራ የሚሰራ ቄስ የሰራው ወንጀል ትዝ ሲለው ተዝናንቶ አይንቀሳቀስም፤ የመንፈስም ዕረፍት አያገኝም። ስለሆነም መቅደስም ውስጥ የሚገቡ ቄሶችና ዲያቆኖች ሆነ ቤተ-ክርስቲያን ሄደው ቅዳሴ ለማዳመጥ ወይም ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ በዓልን የሚያከብሩ በተቻለ መጠን ለህሊናቸው ተገዢና እግዚአብሄርንም የሚፈሩ መሆን አለባቸው። አስቸጋሪው ነግር ግን አባዛኛዎቹ ወደ ቤተክርስቲያን አዝወትረው የሚሄዱ ዕምነት አለን ብለው ከመሄድና ከመፀለይ በስተቀር መጽሀፍ ቅዱስንም በሚገባ በማንበብና በመረዳት መደረግ ያለባቸውን መደረግ ከሌለባቸው ጋር በማነፀፃር እንደዚህ የመሰሉ ሰውን የማይጎዱ ነገሮችን ብቻ ነው ማድረግ ያለብኝ በማለት ከመንፈሳቸው ጋር በማዋሃድ በዚያው አይመሩም። አንድ ወጥ ሃይማኖት ከመፈጠሩ በፊት ፍልስፍና የበላይነትን በተቀዳጀበት ከክርስቶስ ልደት በፊት ስነ-ምግባርንና ሞራልን በሚመለከት በፈላስፋዎች ዘንዱ ስፊ ጥናት ተካሂዷል። በሶክራተስና በፕሌቶ ዕምነት የሞራልና የስነ-ምግባር ብቃትነት የሌለውና፣ በተጨማሪም አንድን አገር ለማስተዳደር የሚያስችል የጠለቀና ሳይንሳዊ ዕውቀት የሌለው ሰው ፖለቲከኛ ሊሆን አይችልም፤ የመንግስትንም መኪና መጨበጥ የለበትም የሚል ነው። ይህም ማለት አነሰም በዛም ስነ-ምግባርንና ግብረ-ገብነትን በሚመለከት በፍልስፍናና በሃይማኖት መሀከል ይህንን ያህልም ልዩነት የለም። አስቸጋሪው ነገር አብዛኛውን ጊዜ ሃይማኖት እንደ ዕምነት ስለሚወሰድ ሰው ደፍሮ በቂ ምርምር አያደርግም። በሳይንስ ዓለም ውስጥ ግን ሁሉም ነገር መረጋገጥ አለበት። በሌላ ወገን ደግሞ ሳይንስንና ቴክኖሎጂን የፈጠሩ ሰዎች የሰውን ልጅ ከጨለማ ለማውጣት በማለት እንጂ የኋላ ኋላ ላይ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ወደ መጨቆኛ መሳሪያነት በመለወጥ ጦርነትም የሚካሄድባቸውና የሰውም ልጅ ሊገደልባቸው ነው በሚል አስበው አይደለም። ጋሊሊዮ፣ ሬኔ ዴካ፣ ኒውተንና ላይብኒዝ፣ አንዲሁም አያሌ የሳይንስ አፍላቂ ምሁራን ሳይንስን ሲፈጥሩና ለቴክኖሎጂ መፈጠርና መዳበር መሰረት ሲጥሉ ዋናው አስተሳሰባቸውና ዓላማቸው የሰውን ልጅ ከጨለማ በማውጣት የተሰተካከለና የማያስጨንቅ ኑሮ እንዲኖር በማሰብ ብቻ ነው። ይሁንና በዘመነ ካፒታሊዝም ሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ማጥፊያ የጦር መሳሪያዎች መስሪያነት በመለወጥ ስልጣንን የጨበጡና በተለይም የተወሳሰቡ የጦር መሳሪያዎችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ከትርፍ አንፃርና ሀብትን ከመቆጣጠር አኳያ በማየት ብቻ የዓለምን ህዝብ ከፍተኛ ጭንቅት ውስጥ ከተውታል ማለት ይቻላል። በዚህ ላይ እናቁምና በመንግስትና በመቅደስ መሀከል ምን ዐይነት ግኑኝነት ሊኖረስ ይችላል? ብለን እንጠይቅ ይሆናል። ሁለቱም የተለያዩ ተቋማት ስለሆኑ ሁለቱንም ማመሳሰል አይቻልም፤ ተገቢም አይደለም ብለን እንናገር ሊሆን ይችላል፣ ትክክልም ነው። ተግባራቸው የተለያየ ስለሆነ ማመሳሰሉ ትክክል አይደለም ልንል እንችል ይሆናል። በሌላ ወገን ግን እንደሜታፈር አድርጎ መጠቀሙ ስለፖለቲካና ስለመንግስት ያለንን የተሳሳተ ግምት ጥራት ሊሰጠው ይችላል የሚል ዕምነት አለኝ።
ለማንኛውም ነገሩን መልክ ለማሲያዝ ጠጋ ብሎ ማየት ተገቢ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን አብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገር ሰዎች፣ ኤሊቱንም ጨምሮ ስለፖለቲካና ስለመንግስት ተግባርና ምን ዐይነትስ ሰዎች የመንግስትን መኪና መቆጣጠርና ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው የተሳሳተ ግምት አለን። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት በትምህርት ቤቶችና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የመንግስትን ምንነትና ተግባር፣ በፓለቲካ ዓለም ውስጥም ምን ዐይነት ሰዎች መሳተፍ እንዳለባቸው ሳይንሳዊ በሆነ መልክ በትምህርት መልክ አይሰጥም፤ በጋዜጦችና በመጽሄቶች ላይም ነገሮችን በማንሳት በጥናት መልክም ክርክር አይደረግም። ካላንዳች ማውጣትና ማውረድ ዐይናችንን ጨፍነንና አንገታችንን ደፍተን መንግስትንና ፖለቲከኞችን እናመልካለን። አንድ አገዛዝ የመንግስትን የመጨቆኛ መሳሪያ በመጠቀም የፈለገውን ያህል አረመኔያዊ ተግባር ቢፈጽምም፣ አገር ቢያፈራርስም፣ የአገሩንም ሀብት ለውጭ ከበርቴዎች ለሚባሉት ቢቸበችብም፣ ባህልን ቢያውድምና ግብረሰዶማዊነትንም ቢያስፋፋም፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከሚባሉት ጋር በመስማማትና በመታዘዝ በመሠረቱ ድህነትን የሚያስፋፋ ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ሲያደርግ ዝምብለን እንመለከታለን። እንደዚህ ዐይነቱን አገር አውዳሚ አገዛዝ መንግስት ብለን እንጠራዋለን። ስለሆነም አንድ አገርና ህዝብ ማንም ዱርዬ እየተነሳ ስልጣንን ጨብጦ አገር ሲያተራምስ መሪ ወይም ጠቅላይ ሚኒስተር እያልን እንጠራዋለን፤ እንሰግድለታለን።
ከሁለት ሺህ ዓመት ተኩል ጀምሮ የፖለቲካንና የመንግስትን ጉዳይና ሚና አንስተው ይከራከሩና ይጽፉ የነበሩ ፈላስፋዎች ግልጽ አመለካከት ነበራቸው። በእነሱ ዕምነትና ሳይንሳዊ ግንዛቤ መንግስት ጨቋኝና ጦረኛ ሳይሆን ፍትሃዊ መሆን ያለበት ነው። በተጨማሪም መንግስት የአንድ ቡድን ወይም ግለሰብ የግል ሀብት ሳይሆን ህዝባዊ ባህርይ ያለውና አንድን ህዝብ በስነ-ስርዓት ማስተዳደር ያለበት አካል ነው። ባጭሩ የህዝብ አገልጋይ የሆነና ከህዝብም በላይ ሊሆን የማይችል ነው። አንድ ቡድን ስልጣንን የሚይዘው ላልተገደበ ጊዜ ሳይሆን የግዛት ዘመኑ ገደብ ያለው ነው፤ መሆንም አለበት። ህዝብን የሚመለከቱ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ከሰራና ፍትሃዊነትንም ካነገሰ በተደጋጋሚ የመመረጥ ዕድል አለው። በሌላው ወገን ግን ህዝብ የሰጠውን አደራ የሚጥስና አገርን የሚያምስ፣ እንዲሁም አጠቃላይ ጦርነት በማካሄድ ህዝብን የሚፈጅና የአገርንም ሀብት ለመልቲ ናሽናል ኩባንያዎች የሚያዘርፍ ከሆነ ይህ ዐይነቱ አገዛዝ አንድም ወር ስልጣን ላይ የመቆየት መብት የለውም።
ለማንኛውም የመንግስትን ስልጣን አስመልክቶ በቀጥታ ከህዝብ፣ ከአገር፣ ከታሪክና ከባህል ጋር በቀጥታ ግኑኘነት ያለው ሰለሆነ ስልጣን ላይ የሚወጡት፣ ወይም መውጣት ያለባቸው ፈላስፋዎች መሆን ሲገባቸው፣ ይህ የማይቻል ከሆነ ደግሞ ፖለቲከኛ የሚባሉት የግዴታ በፈላስፋዎች የሚመከሩ መሆን አለባቸው። ስልጣን ላይ የሚወጡትም ከልጅነታቸው ጀምረው ጭንቅላታቸው በደንብ የተኮተኮተ መሆን አለበት። በሌላ አነጋገር፣ ማንም ስልጣን ላይ በመውጣት ፖለቲከኛ ነኝ ሊል በፍጹም አይችልም። ይህ የሚሆን ከሆነ የመንግስት ሚናና ትርጉሙ ይቃወሳል። በተለይም በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን ምድር ያለውን ሁኔታ በጥብቅ የምንከታተል ይመስለኛል። ዶናልድ ትረምፕ የሚባል አንድ ፕሬዚደንት ህገ-መንግስቱንና ህዝብ የሰጠውን ኃላፊነት በመጣስ የራሱን ህዝብ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከትቶታል፤ በተለይም የማይሆን ሰበብ በመፈለግና በእስራኤሉ ጠ/ሚኒስተር ኔታንያሁን ትዕዛዝ በመቀበልና ግፊትም ስለተደረገበት በኢራን ሁዝብ ላይ ጦርነትን እያካሂደ ነው። ዋናው ምክንያት ደግሞ ኢራን አቶም ቦምብ ለመስራት የሚያስችል በቂ ዩራኒዩም አዘጋጅታለች፤ ይህም ለእስራኤልም ሆነ ለእኔ ለአሜሪካን መንግስት አደጋ ነው በማለት ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ለአሜሪካንም ሆነ ለእስራኤል፣ እንዲሁም ለተቀሩት የአቶም ቦምብ ባለቤት አገሮች እናንተ ብቻ ናችሁ መስራት የሚፈቀድላችሁ የሚል በተባበሩት መንግስታት ቻርተር ተቀባይነት ያለው ህግ የለም። በመሰረቱ አቶም ቦምብን በመሰራት ለመጀመሪያ ጊዜ በማንአለኝበት ሂሮሽማና ናጋሳኪ ላይ ከመቶ ሺህ ህዝብ በላይ የሚቆጠር በራዲይ አክቲቭ ጨረር በማቃጠል የፈጀችው አሜሪካን ነች። መወንጀልና መከሰስም ያለባት አሜሪካን ነች። ከዚህ ስንነሳ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚያክል ህዝብ ያላት እስራኤልና ወደ ሶስት መቶ ሚሊዮን በላይ የሚቆጠር ህዝብ ያላት አሜሪካ በስምንት ቢሊዮን የዓለም ህዝብ ላይ እንደፈለጋቸው ሊጨማልቁና ሊደነግጉ በፍጹም አይችሉም። የአቶም ቦምብ አስከፊ መሳሪያ በመሆኑና፣ የእግዚአብሄርንና የተፈጥሮን ህግ የሚጥስ በመሆኑ ማንኛውም አገር የመስራት መብት የለውም። በዓለም አቀፍ ህግ መከልከል ያለበት መሳሪያ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን የሰውን ልጅ የማይጠቅሙና ለምርት ስራ የማያገለግሉ የጦር መሳሪያ ፋብሪካዎች በሙሉ መዘጋት አለባቸው። የዓለም ህዝብ ኃያላን ነን፣ እንደፈልግንም በዓለም ህዝብ ላይ እየጨፈርንና እያስፈራራን እንኖራለን በሚሉት መሰቃየት የለበትም። እግዚአብሄር የሰውን ልጅ ሁሉ በአምሳሉ የፈጠረ በመሆኑ አንደኛው ከሌላኛው የሚበልጥበት ምንም ምክንያት የለም። የዓለምን ኢኮኖሚና የጥሬ-ሀብትን በሚመለከት ፍትሃዊነት ባለው መንገድ በተገለፀለት መልክ ለስምንት ቢሊዮን ህዝብ በሚስማማ መልክ ማምረትና ፍትሃዊነት ባለው ዋጋ በስምምነት መሽጥ ይቻላል። ሁሉም ነገር ገደብ ስላለው ገደብ እየታየ መሰራት አለበት። ገደቡን የለቀቀ ሀብትና ስልጣን ለሰው ልጅ በጣም አደገኛ ናቸው። አንድ ሰው የፈለገውን ያህል ሀብታም ቢሆንም´አንድ ሺህ ዓመት በዚህች ዓለም ላይ በፍጹም ሊኖር አይችልም። በሌላ አነጋገር፣ ማንኛውም ሰው ገደቡን ማወቅ አለበት። ሀብታም ስለሆንኩና ስልጣንም ስላለኝ የፈለግሁትን ማድረግ እችላለሁ፣ ሌላውን ዝቅ አድርጌ መመልከት እችላለህ፣ ደካማውንና ደሀውን እንደ ቆሻሻ አየዋለሁ የሚል ከሰው ልጅ መነፈስ ውስጥ መውጣት አለባቸው። አስቸጋሪው ነገርና በጥናትም እንደተረጋገጠው ስልጣንን የያዙና ሀብታሞችም በህይወታቸው ውስጥ ምንም ችግር ያላዩና ከሌላው ዝቅ ብሎ ከሚታየው የህብረተሰብ ክፍል ጋር ከልጅነታቸው ጀምረው እየተጫወቱ ያደጉ አይደሉም። በተለይም ይህንን በሚመለከት የስካንዲኔቪያን ሶሻል ሳይንቲስቶች በሞዴል መልክ በማዘጋጀትና በማጥናት አረጋግጠዋል። የህብታም ልጆችን አስተዳደግ በሚመለከትና ባህርያቸውንም አስመልክቶ በፊልም መልክ ተስርቷል። ፊልሙም የሚያረጋግጠው ከሀብታም ቤተሰብ የተወለዱና ያደጉ ምንም ዐይንተ ርህራሄ የሌላቸውና፣ ሰው መሆናቸውንም የማይገነዘብ ናቸው። ለመኖርና ለመባለግ የተፈጠሩ የሚመስላቸው ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ የማንኛውም ሰው ልጅ ባህርይ በመጥፎም ሆነ በጥሩ መልክ ሊቀረጽ የሚችለው በጣም ልጅ ሆኖ ካለበት ጊዜ ጀምሮ በሚደረግለት ጥሩ እንክብካቤም ሆነ ቅጥ ያጣ አስተዳደግ ነው። በነገራችን ላይ ታላላቅ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች በሙሉ፣ እንዲሁም የማቲማቲስክ ሰዎች በችግር ውስጥ ያደጉና አንዳንዶችም፣ በበሽታ የሚሰቃዩ ነበሩ። ስንትና ስንት ስቃይን እያዩና በማዕክለኛው ክፍለ-ዘመንም መረን የለቀቀ ጦርነት እየተካሄደ ነው ምርምር ያደርጉና የመጨረሻ መጨረሻም ለቴክኖሎጂ መሰረት የሆነውን ሳይንስን መፍጠር የቻሉት። ታላቁ ሶክራተስ እንደሚለን በፈተና ያልተፈተነ ህይወት ህይወት አይደለም እንደሚለው ህይወቱ ያልተፈተነ ሰው በአጋጣሚ ስልጣን ላይ ሲወጣና ሀብትም ሲቀዳጅ የሚሆነውን የማይሆነውን ማድረግ ይጀምራል። በአጠቃላይ ሲታይ እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች ናቸው በተለያየ መልክ በውስብስብ ሁኔታ ውስጥ በመግባትና የበላይነትን በመቀዳጀት ለጦርነት ምክንያት የሚሆኑት።
ለማንኛውም ወደ አገራችን ስንመጣ በተለይም ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በአገራችን ምድር ስልጣንን የተቀዳጁ ኃይሎች በልክስክስ ዕውቀት የሰለጠኑ ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ ሰው ሆነው እንዲያስቡ የሰለጠኑና ኃላፊነታቸውን እንዲገነዘቡ ተደርገው የታነፁ አይደሉም። በተለይም ባለፉት 36 ዓመታት አገራችንን ሲያስተዳድሩ የነበሩትና አሁንም የሚያስተዳድሩት እልም ያሉ ዱርዬዎችና የውጭ ኃይሎች አገልጋዮች ለመሆን የበቁት ከልጅነታቸው ጀምረው መንፈሳቸው በጥሩ ዕውቀት ያላታነፅ በመሆኑ ነው። ጭንቅላታቸው እንዳለ የወላለቀ ነው። ምንም ይነት የማሰብ ኃይል የሌላቸው ናቸው። በፍጹም የታሪክ ግንዛቤ የላቸውም። የአንድን አገር ታሪክ በጥቁርና በነጭ በመጻፍ አንድን ህዝብ ርስ በርሱ እንዲጠላላ ለማድረግ በቅተዋል። ቅዱስ የሆነውን ፖለቲካና የመንግስት መኪና እንዳለ ወደ ተንኮል መሸረቢያ መሳሪያነት ለውጠውታል። ስራቸው ሁሉ የሰይጣን ስራ ሆኗል። ይህ ዐይነቱ ሰይጣናዊ የፖለቲከኛ ነን ባዮች ድርጊት ትክክል እንደሆነ በሁላችንም ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቷል። ጠቅላይ ሚኒስተር ነን የሚሉት አስፈሪ የጦር መሳሪያ በታጠቁ መኮንኖች ወይም ወታደሮች ተከበው ሲንጎራደድ ሲታዩ ሰፊው ህዝብ መሸማቀቅ ይጀምራል። በተለይም ወደ ሴተኛ አዳሪነት የተለወጡ ሸርጋጅ የወንድ ፖለቲከኛ ነን ባዮች አንድን ጠቅላይ ሚኒስተር ባይ አጋኖ በማየትና በማድነቅ ልዩ ፍጡር እንደሆነ ለማቅረብ ይሞክራሉ። በፓርሊያሜንት ውስጥ የተቀመጡትም ሆነ በሚኒስተርነትም ደረጃ የሚያገለግሉት በሙሉ በሳይንሳዊ ዕውቀት የሰለጠኑ ስላልሆኑ መንፈሳቸው በሚገባ ያልተገራ በመሆኑ ከመታዘዝ በስተቀር በራሳቸው ህሊና የማይገዙና ይህም ነገር መደረግ የለበትም ብለው በግልጽ በድፍረት የሚናገሩ አይደሉም። በሳንይንም ሊረጋገጥ የማይችል መሆኑን ማስረዳት አይችሉም። ዝም ብለው ብቻ የጠቅላይ ሚኒሰተሩንና የዓለም ተዋንያን ድርጅቶችን ትዕዛዝ በመቀበልና ተግባራዊ በማድረግ አንድን ምስኪን ህዝብ ፍዳውን ያሳዩታል። የሚያሳዝነው ነገር ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ተማርን፣ የዶክትሬት ዲግሪ ጨብጠናልም በሚሉት ዘንድም ተቀባይነትን ማግኘቱ ነው። አንዳንዶችም የአገዛዙን አምባገነንነት የተቃወሙ ቢያስመስሉም የመንግስትን አወቃቀርና የፖለቲካኛ ነን ባዮችን ድርጊት ክሪቲካል በሆነ መልክ አይመለከቱም። ይህ ዐይነቱ የአገዛዝ መዋቅር ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር በሺህ ድሮች በመተሳሰር ለህብረተሰብአዊ ዕድገትና ለሰላም መኖር ትልቅ እንቅፋት እንደሆነ ሊገባቸው በፍጹም አይችልም። ይህ ዐይነቱ የአገዛዝ መዋቅርና አስተሳሰብ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው ትውልድ በመተላለፍ ህዝባችን በዘለዓለማዊ ድህነት ውስጥ እንዲኖር እንደሚያደርገው ምንም ዐይነት ግንዛቤ የላቸውም፤ የለንም። ድህነትንና ኋላቀርነትን እንደልማድና እንደባህል አድርገን በመቀበላችን ህዝባችን ተራበ አልተራበ፣ ተጠማ አልተጠማ ደንታ አይሰጠንም። ይህንንም አስተሳሰባችንና ዕምነታችንን በፍጹም መቀየር አይቻልም። ለማንኛውም እያነሱ መወያየቱ ክፋት የለውም። በዚህ ቁልፍ ጥያቄ ላይ በቂ ግንዛቤ ካለን ብቻ ነው መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት የምንችለው። በተለይም የመንግስትን ምንነትና ሚና፣ እንዲሁም ፖለቲካ ማለት ምን ማለት ነው? በሚለው ላይ በቂ ጥናት ካላደረግንና ግንዛቤም እስከሌለን ድረስ ከመቶ ዓመት በኋላም የተከታታዩ ትውልድ ህይወት በፍጹም አይለወጥም። መልካም ግንዛቤ!!
fekadubekele@gmx.de
www.fekadubekele.com
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena
መነበብ ያለባቸው መጽሀፎች፤
1. Agleitta, Michel; A Theory of Cpitalist Regulation: The US Experience, London, 197
2. Binyamin Appelbaum; The Economists’ Hour: False Prophets, Free Markets, And the Fracture of Society, New York, 202
3. Bob Jessop; The Capitalist State, Oxford. 1982
4. The Future of Market Economy, Münster 1991
5. Josef Chytry; The Aesthetic State: A Quest in Modern German Thought, California, 1989
6. Nicos Poulantzas, States Theory, Political Construction, Ideology, and the Theory of Socialist Democracy, Frankfurt, 1 1977
7. Robert Kuttner; Can Democracy Survive Global Capitalism? London, 2018
ማሳሰቢያ፤ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በመሰለ አገር መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣትና የተሟላም ሰላም ለማስፈን የግዴታ
የጠለቀና ሰፊ ጥናት ማካሄድ በጣም አስፈላጊ ነው። አንድን አገር በተሟላ መልክ መገንባትና ማስከበርም
የሚቻለው በዕውቀት አማካይነት እንጂ በቀረርቶና በሽለላ አይደለም። ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ በማለትም የትም
መድረስ በፍጹም አይቻልም። እንደምናየው ጥቂት አገሮች፣ በተለይም የካፒታሊስት አገሮች የዓለምን ህዝብ
አስተሳሰብ አንድ ወጥ ለማድረግና የተለያዩ ባህሎችን ለመደምሰስ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው። ይህ ዐይነቱ
አካሄድም እጅግ አደገኛና የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ የሚፃረር ነው። ተፈጥሮ እንደ ተፈጥሮ ለመኖር
የምትችለው በአንድ ዛፍና በአንድ ሰብል አማካይነት ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ ዛፎች፣ በተለያዩ አትክልቶች፣
ፍራፍሬዎች፣ በተለያዩ እንስሳዎችና በዱር አራዊቶችና በተለያዩ ዐይነት እንሴክቶችም አማካይነት ብቻ ነው።
ከእንሴክቶችም ውስጥ ንብ ከፍተኛውን ቦታ ትይዛለች። ስለሆነም ተፈጥሮን ተፈጥሮ የሚያሰኛት እነዚህ
የተለያዩ ፍራፍዎችና ሰብሎች፣ እንዲሁም ዛፎችና አራዊት በስምምነት ሲኖሩ ብቻ ነው። የሰው ልጅም
በእዚህ አማካይነት ብቻ ነው ለህይወቱ አስፈላጊ የሚሆኑ ነገሮችን ማግኘት የሚችለው። ስለሆነም
የሰውንም ልጅ በጠቅላላው በአንድ አስተሳሰብ መቅረጽ አይቻልም፤ ተገቢም አይደለም። የካፒታሊስት
አገሮች ዋና ዓላማ የሰው ልጅ አስተሳሰብ በሙሉ ገንዘብ በማግኘትና የፍጆታ ዕቃዎችን በመጠቀም ብቻ
በዚያ እንዲሽከረከር ማድረግ ነው። በሌላ ወገን ግን የሰው ልጅ ከማቴሪያል ሁኔታዎች ባሻገር መንፈሳዊ
ነገሮች ያስፈልጉታል። እርስ በርሱም በመገናኘት መጫውትና መዝፈን አለበት። መጨፈርም አለበት። ይህ
ሲሆን ብቻ ሰው መሆኑን ይገነዘባል፤ ከሌላው ጋርም መገናኘትንና ሃሳብ ለሃሳብ የመለዋወጥን ጥቅሙን
ይረዳል። ባጭሩ ዝም ብሎ መነዳቱ ትክክል አይደለም። ይህንን ካልኩን በኋላ እንደዚህ ዐይነት ጽሁፍ የአንድ
ሰው ስራ ብቻ መሆን የለበትም። ሌሎችም ጊዜን በመውሰድና በመሰዋት የራሳቸውን አስተዋፅዖ ማድረግ
አለባቸው። ካለበዚያ መበላታችን አይቀርም። በተረፈ ግን እንደዚህ ዐይነት ሳይንሳዊ ጽሁፍ በተከታታይ
እንዲወጣ የምትፈልጉና ትምህርትም ለመቅሰም የምትሹ የግዴታ እንደዚህ ዐይነትን አቀራረብ በሞራልም ሆነ
በቁሳቁስ መርዳት ያስፈልጋል። እስካሁን ድረስ በሞራልና በታሪካዊ ግዴታ የተነሳ በግለሰብ ተነሳሽነት
አስፈላጊውን አስተዋፅዖ ለማድረግ ችያለሁ። ይህ ዐይነቱ የአጻጻፍ ስልትንባ ትንተና እንዲቀጥል ከተፈለገ
ድረ-ገጼን ማገላበጥ አስፈላጊውን ዕርዳታ ማድረግ ትችላላችሁ። ፕሮፈሽናሊታና ተከታታይነት ያለው ጽሁፍ
ማዘጋጀት የሚቻለው የራስን ጊዜ በመሰዋት ነው። ይህም ማለት ሌላ ጥቅም የሚገኝባቸውን ነገሮች ወደ ጎን
በመተው ነው። በሌላ ወግን ግን የምንኖረው በካፒታሊዝም ዓለም ውስጥ ነው። ይህንን ሎጂክ መረዳት
በጣም አስፈላጊ ነው። ለማንኛውም የድረ-ገጹ ላይ አስፈላጊው መረጃዎች ተቀምጠዋል።







Well, it is truly informative ! But the very problem of our intellectuals is the problem of making their writings very long and academically philosophical instead of making them reasonably brief and strongly relevant to the tragic political, socio-economic, moral , ethical and spiritual crises of the century????
Dear Mr. TG,
I would like to appreciate you for reading my article and for your friendly comment. Sometimes it is very difficult to write Short articles when the title is very interesting. Any way I will try to write as short as possible. If you are intersted you can visit my Website. http://www.fekadubekele.com is the name of the Homepage.
Fekadu Bekele
I sincerely appreciate and would like to extend my heartfelt gratitude for your not just response but a response with a very polite, reasonable, and a real sense of professionalism/ intellectualism!
Thank you!!