Homeነፃ አስተያየትማመስገን፣ መመስገንና መመሰጋገን በእጅጉ መልካም ነገር ነው! ነገር ግን...

ማመስገን፣ መመስገንና መመሰጋገን በእጅጉ መልካም ነገር ነው! ነገር ግን…

Advertisement
World Wide Travel Group

ጠገናው ጎሹ

ከሁሉም በፊት ይህንን ሂሳዊ አስተያየት የማቀርበው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከአገራችን ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ጋር ስለሚያያዝ እንጅ አዘጋጆችም ሆነ ታማኝ በየነ  ያመኑበትንና የሚፈልጉትን የመሆናቸውና የማድረጋቸው ጉዳይ እንዳልሆነ ግልፅ ይሁንልኝ ።

ከሰሞኑ የኪነ ጥበብ አካል  የሆነው የሙዚቃ ዘርፍ ወገኖች ባዘጋጁት የማመስገንና የመመሰጋገን አውድ ላይ ታማኝ በየነ ያደረገውን በእጅጉ ስሜታዊነት የተቆጣጠረው አጭር ንግግር በተመስጦና በተደበላለቀ ስሜት ተከታተልኩት።

ይህንን በተመለከተ አንድ ሰው በድህረ ገፅ (ቦርከና) ላይ የፃፈውን የወንድምነት ምስጋና እና ጥሪንም አነበብኩት ። የአድናቆትና የሙገሳ ተገቢነት እንደተጠበቀ ሆኖ ገንቢ የሚሆን ሂሳዊ  አስተያት/ምክር የሌለበት መሆኑ ግን የተሟላ ሆኖ አላገኘሁትም። ለምን? ቢሉ የመማርና የመማማር ወይም የማረምና የመተራረም እጅግ አስፈላጊነት/ጠቃሚነት  የሚጎድለው መሆኑን በወቀሳነት ሳይሆን በገንቢ አስተያየትነት መግለፅ ትክክል ይሆን ነበር የሚል እምነት ስላለኝ ነው። ከዘመናት የመከራና የውድቀት ፖለቲካ መማርና የእውነተኛ ለውጥ መሪዎችን አምጠን ለመውለድ እየተሳነን በሥልጣነ መንበር ላይ የሚፈራረቁ  ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች በሚያዘጋጁልን በስሜት የመነዳት ክፉ ልማድ እየተጠለፍን ይኸውና አሁንም የመከራው ዘመን  እየተራዘመብን በእጅጉ ተቸግረናል። ታዲያ ታማኝ በየነም ስሜትን ከተሞክሮና ከተጨባጭ ሁኔታ ጋር አገናኝቶ የማሰብ፣ የመወሰንና የሚበጀውን የማድረግ ክፉ ደካማነት ተጠልፈን ከወደቅነውና እንደ አቢይ አህመድ አይነት የሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች ሰለባዎች ከሆነው መካከል አንዱ ነበርና “እንደ አብዛኛው ሰው በወቅቱ መስሎኝ ነበር” ቢል እንኳ “ቢያንስ ግን ብዙ ጊዜ ሳልወስድ  ቆም ብየ ማሰብና የፀረ አምባገነንት አክቲቪስትነቴን  መቀጠል ነበረብኝ እና አሁንም ጨርሶ አልመሸም ” ከማለት ይልቅ  “የአክቲቪስት  ውለታ ቢስ ሆንኩኝ” የሚል መበከነከን ውስጥ ገባ? የሚል ጥያቄ ማንሳት የእውነተኛ ወገንነት እንጅ ውለታ ቢስ አድራጊነት ሊሆን አይችልም።

የተመስጦዬ ምክንያት እንዲህ አይነት አጋጣሚዎችን/መድረኮችን እያዘጋጁ በመገናኘት በየእውቀታችን፣ በየሙያችንና በየክህሎታችን ስላደረግነው በጎ ተፅእኖ ፣  እያደረግን ስላለነው አሁናዊ ጥረት እና  ወደ ፊትም ማድረግ ስለሚኖርብን ሁለገብ አገራዊ/ህዝባዊ በጎ/ገንቢ አስተዋፅኦ መምከር፣ መመካከር፣ ማመስገንና መመሰጋገን በእጅጉ አስፈላጊና አበረታች የመሆኑ እውነትነት ነው።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ለተደበላለቀው ስሜት  ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ለማሳያነት ያህል በጥያቄ መልክ ግልፅ ላድርግ ፦

ማመስገኑና መመሰጋገኑ እንደ ተጠበቀ ሆኖ  እንዲህ አይነት ግንኙነቶች/ ዝግጅቶች ሲዘጋጁ  አዘጋጆች ፣ተጋባዥ እንግዶች ወይም ተናጋሪዎች እና ራሳቸው ተመስጋኞች  ለዘመናት ስለመጣንበትና አሁንም እጅግ አስከፊና አሳፋሪ በሆነ ደረጃ ስለምንገኝበት ፖለቲካ ወለድ አጠቃላይ ማለትም የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚያው፣ የሞራላዊ፣ የሥነ ልቦናዊ፣ የሥነ ምግባራዊ፣ የባህላዊ እና የሥነ ሥነ ጥበብና  የኪነ ጥበብ ቀውስ/ውድቀት  እንደ ፖለቲከኛነት ሳይሆን እንደ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣  ሰላምና የጋራ እድገት/ልማት ፈላጊ ወገን ወይም ባለሙያ ሃሳባቸውንና አስተያየታቸውን  በተገቢው የስሜት ሃይል ለማስተላለፍ የሚያስፈራቸው ምንድን ነው?

የምንወደውን ሙያ  ጨምሮ ታላላቅ አገራዊ/ህዝባዊ አስተዋፅኦ ያላቸው የማህበራዊና ባህላዊ እሴቶች  ልኩን በሳተና መሬት ላይ ካለው ግዙፍና መሪር እውነታ ጋር በእጅጉ በተራራቀ ስሜታዊነት ምክንያት የሸፍጥ፣ የሴራ፣ የብልግና እና የጭካኔ  ፖለቲካ ሥርዓት መጫወቻ ሲሆኑ እያየን ምንም እንዳልሆነ አመስግነን፣ ተመሰጋግነን እና ፎቶ ግራፍና ተንቀሳቃሽ ምስል ቀርፀንና ተቀራርፀን መሰነባበት እና እወቁንና እወቁልን ማለት የት ያደርሰናል?

ለመሆኑ የአገራችን አክቲቪዝም የስኬት ማሳያ ሳይሆን የመቀንጨርና የውድቀት ሰለባ እየሆነብ የተቸገርነው ለምንድን ነው?

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

 ከምርና ከቅንነት በሚመነጭ ሃሳብና ድርጊት ተገቢውንና ወቅታዊውን ፍኖተ መፍትሄ ማፈላለግ ግድ የሚለን ሆኖ ሳለ የብሶታችን  ስሜት መቆጣጠር ተስኖን ለዘመናት ከመጣንበትና አሁንም ተዘፍቀን ከምንገኝበትን አስከፊ ሁኔታ ጋር እየተለማመድንና  የሰበብ ድሪቶ እየደረትን  ከየት ወደ የት ነው የምንሄደው ? እስከ የትስ ነው የምንሄደው?

እንደ ሰው እንደ ሰው ተከብሮና ተከባብር እና እንደ መልካም ዜጋ የአገር ኩራት ሆኖ ይኖር ዘንድ  የህልውናው  ጉዳይ ፈፅሞ ለድርድር እንደማይቀርብ  ለአያሌ ዓመታት ለእኩያን ገዥዎች  ሲያሳውቅና ሲያስገነዝብ የኖረው መከረኛ የአገሬ ህዝብ ያገኘው ምላሽ  ጨርሶ የማጥፋት እርምጃ መሆኑ በእጅጉ ያሳሰባቸው ዜጎች/ሃይሎች የጀመሩትንና እያካሄዱ ያሉትን የህልውና/የነፃነት/የፍትህ  አገርን እውን የማድረግ ተጋድሎ  ገንቢ በሆነ ሂሳዊ  ድጋፍ እየደገፍን የኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ነፃነትን ጨምሮ  የሁሉም መሠረታዊ መብቶቻችን የሚከበርበትን ሥርዓተ ፖለቲካና አስተዳደር እውን የምናደርግበትን እለት/ጊዜ ከማፋጠን ይልቅ በየአጋጣሚው  እየተሞጋገስንና እየተላቀስን የቀጠልንበትን ክፉ ልማድ በፍፁምነት ለማስቀረት ባንችል እንኳ በተገቢው ደረጃ ለመቆጣጠር የተሳነንና የሚሳነን ለምንድን ነው?

ለሩብ ምዕተ ዓመት የህወሃት/የኢህአዴግ ህሊና ቢስ አገላጋዮች/አሻንጉሊቶች የነበሩት ቡድኖች (የአሁኖቹ ብልፅግና ተብየዎች) በስሜት ፈረስ ከመጋለብና የውድቀት አዙሪት ሰለባ ከመሆን ሊታደገው የሚችል የፖለቲካ ሃይል/ድርጅት ለማግኘት  ያልሆነለትን መከረኛ ህዝብ በስሜት እየጋለቡና እያስጋለቡ  ፈጣሪያቸውንና ጠርናፊያቸውን (ህወሃትን) ከቤተ መንግሥት አባረው ያንኑ እኩይ የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ለማስኬድ ሲዘጋጁ  ለምን? በነማን? ለነማን? እንዴትና ወዴት? ብለን ያለመጠየቃችንና ትርጉም ያለው ግንዛቤ በማግኘት ወቅታዊ እርምጃ ያለመውሰዳችን ውድቀት አሁንም አላስተማረንም/አልመከረንም እንዴ?

 የህወሃት  ከዘውድ መባረርን ብቻ በማየት “የህዝብ መከራና ውርደት በዘመናችን ሙሴ አበቃለትና የአገር ትንሳኤ ትንቢት ተፈፀመ “  እያልን ራሳችንን ወደ ቂሎች ተራ ያወረድንበት ጊዜና ሁኔታ የገንቢ ፀፀትንና የእርምት እርምጃ የመውሰድ ጥበብንና ቁርጠኝነትን ለምንና እንዴት አላስተማረንም?

- Advertisement -

 “ከሙሴው” የእግር ጫማ ስር የተገኘንበትን እና ከራሳችን አልፎ መከረኛውን ህዝብ ጨምረን ያነሆለልንበትን መሪር እውነት  ገንቢ በሆነ ሂስና ግለ ሂስ አርሞና ተራርሞ ወደ ፊት ከመገስገስ ይልቅ  “አይ እንደማነኛውም ለውጥ ፈላጊ እውነት መስሎኝ እኮ ነው፤ ይኸ እኮ ማንም ሰላም ፈላጊ የሚያደርገው ነው፤ እነ አቢይ አህመድ እኮ በአፍዛዥና አደንጋዥ የፕሮፓጋንዳ አንደበት/ዲስኩር ጠልፈውኝ ነው፣ እንደዚህ መሆኑን ባውቅማ ኖሮ … ወዘተ  ”  ከሚል እጅግ ደምሳሳና የወረደ አስተሳሰብ ሰብሮ ለመውጣት የሚያስችል ጥረት ከማድረግ ይልቅ “ለምን ተሳስተሃል/ተሳስተሻል  ብርቱ ወቀሳ ደረሰብኝ? እዚህ ሁሉ ነገር ቢቀርብኝስ?” እና ወዘተ እያሉ ገንቢነት በሌለው ስሜታዊነት መብከንከን የት ያደርሰናል? ከየትስ ወደ የት ይወስደናል? 

እናም አሁንም ቢሆን ያደረግነው በጎ አስተዋፅኦ  የማይካድና  አርአያነት የነበረው የመሆኑ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ እውነትም የህዝብ/የአገር መከራና ውርደት ህሊናችንን ረፍት የሚነሳን ከሆነ እንኳንስ ተሳስተን ሳንሳሳትም የሚቀርብብንን ትችት/ሂስ በቅጡ ማስተናግድ ይኖርብናል።   ራሳችንን ከልክ ካለፈ ስሜታዊነት እየተቆጣጠርን በትክክል የሚቀርበውን ሂስ “አዎ በዚህና በዚያ ምክንያት ተሳስቻለሁና ለማረምና ለመታረም ዝግጁ ነኝ” የሚል እና ትክክለኛ ያልሆነውን ደግሞ “በዚህና በዚያ ምክንያት ትክክል አይደለምና  እውነትን እውነትና ሃሰትን ሃሰት በሚል ቅንና  ሚዛናዊ ህሊና ማየት ይኖርብናል ” የሚል የፖለቲካና የሞራል ልዕልና ሊኖረን ይገባል። ምክንያቱም እንዲህ አይነቱ ፖለቲካዊ፣ ሞራላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ሥነ ምግባራዊ፣ ወዘተ አርበኝነት ብቻ ነው ከዘመን ጠገብ ፖለቲካ ወለድ የግፍ አሟሟትና የቁም ሟችነት ወደ  የነፃነት፣ የፍትህ፣ የሰላም፣ የእኩልነትና የጋራ እድገት/ልማት አገር ምሥረታ የሚውስደን።   

ስለሆነም ቅን፣ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ልብ/ህሊና ያለው የአገሬ ሰው ልብ ይበል!!!

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

Ethiopian News–Borkena English

ኤክስ ፡ @zborkena 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News