
Nu 8/6/2026/010
በጭፍጨፋው 5 ግለሰቦች እና ሌሎች በገለልተኛ ዓለም አቀፍ አጣሪ በድን እንዲመረመሩ ጥሪ እናቀርባለን !!!
ሰኔ 2፣ 2018 ዓ ም
ግንቦት 23 እና24 ቀናት 2018 ዓ ም በምስራቅ እርሲ ዞን ሶስት ወረዳዎች ባሉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ንፁሃን ላይ በተከፈተ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ቁጥራቸው ከ52 በላይ የሚሆኑ ንፁሃን በግፍ ተግድለዋል፣ ከ47 በላይ ቀላልና ከባድ ቆስለኛ ሆነዋል፣ 190 በላይ ደግሞ እስካሁን ድረስ ደብዛቸው አልተገኘም። በተጨማሪም፣ ሁለት አቢያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ ከ310 በላይ ቤቶች የተቃጣሉ ሲሆን፣ ከ500 በላይ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ለመሸሽ ተገደዋል።
ጭፍጨፋው በተፈጸመ አምስተኛ ቀን ላይ አገዛዙ ባወጣው መግለጫ፣ ፋኖ እና ኦነግ/ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሰራዊት (OLA) ተጣምረው በጋራ የፈፀሙት ነው በማለት የገለፀ ሲሆን፣ “አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ” እንዲሉ “አጣሪ ቡድን” ያለውን ወደ ስፍራው መላኩንም ምክር ቤታችን ማረጋገጥ ችሏል። “አጣሪ ቡድን” የተባለው ዶክመንተሪ እየሰራ መሆኑንም ለማወቅ ችለናል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ስለጭፍጨፋው አውነተኛ ገፅታ የሚናገሩት ድምፅ እንዳይሰማ እንደ እነ ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ ካሳን የመሳሰሉ ዜጎችን አስሯል። ይህን የአገዛዙን የተለመደ አምባገነናዊ ድርጊት የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት በጥብቅ ያወግዘዋል።
አገዛዙ “ጭፍጨፋው የተፈጸመው በአማራ ፋኖ እና ኦነግ/ሸኔ ነው” ብሎ የገለፀ ቢሆንም፣ በድርጊቱ ተሳትፈዋል ብሎ የዞኑን ፖሊስ ኮሚሽነርን ጨምሮ ወደ አምስት የሚጠጉ የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮችን ለሚዲያ ፍጆታ ብሎ አስሯል። ይህም፣ የአገዛዙን የተምታታ እና በውሸት የተበተበ አካሄድ ፍንትው አድርጎ ያሳየ ብቻ ሳይሆን፣ የራሱም እጅ አለበት ብሎ እንደሚያምን የሚያጋልጥ ነው።
የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት በምስራቅ እርሲ ዞን በትርፈጸመው አረመኔያዊ የግፍ ጭፍጨፋ ጉድይ በጥልቀት ያደረገውን ልዩ እና እውነትን ማዕከል ያደረገ የምርመራ ውጤት፣ ለመላው የኢትዮጲያ ሕዝብ እና ብሎም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደሚከተለው ይፋ ያደርጋል :-
1ኛ- በምስራቅ አርሲ ዞን ሶስት ወረዳዎች ውስጥ በሚኖሩ ንፁሃን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ በተፈጸመው ጭፍጨፋ ተጠያቂ አካላትንን በተመለከተ :-
በምስራቅ አርሲ ዞን በአሰኮ ወረዳ፣ በሸካ ወረዳ እና በእንዶሌ ዋቤ ወረዳዎች ውስጥ በሚኖሩ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ በሆኑ ንፁሃን ላይ ግንቦት 23 እና ግንቦት 24 መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ የታጠቁ ኃይሎች ጥምረት ጭፍጨፋ መፈፀሙን ምክር ቤታችን በቀጥታ ከስፍራው በደረሰው መረጃ ማረጋገጥ ችላል።
በዚህ ጭፍጨፋ በአገዛዙ በኩል ሽመልስ አብዲሳ፣ ደምመላሽ ገብረሚካኤል፣ አራርሳ መርዳሳ፣ ኮ/ል አበበ ገረሱ እና ስንታየሁ ጥላሁን በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ በሰጡት ትዕዛዝ ወይም በሚመሯቸው ተቋማት ተሳትፎ በኩል ተጠያቂዎች እንደሆኑ እና ዝርዝር ተሳትፏቸው በገለልተኛ ዓለም አቀፍ አጣሪ ቡድን ተጣርቶ ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸው ምክር ቤታችን ያምናል፣ በዚህ አጋጣሚ ጥሪም ያቀርባል።
በተጨማሪም፣በመንግሥት መዋቅሮች እየታገዘ በንፁሃን ደም ታሪኩ የጨቀየው “ኦነግ/ሸኔ” የተባለው ታጣቂ ኃይል፣ በእለተ እሁድ ግንቦት 23 እና 24 2018 ጭፍጨፋ መፈፀሙን ከነዋሪዎች እና ከጭፍጨፋ ሰለባዎቹ አንደበት መስማት የቻልን በመሆናችን፣ ጉዳዩ በገለልተኛ ዓለም አቀፍ አጣሪ ቡድን መጣራት እንዳለበት ምክር ቤታችን ያምናል፣ በዚህ አጋጣሚ ጥሪም ያቀርባል። ።
2ኛ- በአርሲ በ2018 ብቻ አራት ግዜ የጭፍጨፋ ጥቃት ተፈፅሟል።
ግንቦት 23/24 ቀን 2018 በምስራቅ አርሲ ሶስት ወረዳዎች የተፈፀመው ጭፍጨፋ በዓይነቱ የመጀመሪያው ሳይሆን፣ በ2018 ብቻ አራት ግዜ መጠነ ሰፊ የጭፍጨፋ ዘመቻዎች የተፈፀሙ ሲሆኑ፣ የጭፍጨፋዎቹ ዋና ዓላማም ድፍን ኦሮሚያን ከኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እና ከነገደ አማራ የማፅዳት መንግስታዊ እቅድ አካል መሆኑን እና በጫካ ውስጥ ያለው እና ኦነግ/ሸኔ እየተባለ የሚጠራው ታጣቂ ኃይልም በፍቃዱ የሚሳተፍባቸው ዘመቻዎች እንደሆኑ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም።
የአርሲ ጭፍጨፋ በወለጋ፣ በባሌ፣ በሐረር፣ በሸዋ፣ በጅማ እና በመላ ኦሮሚያ የሚኖሩ ኢትዮጲያዊያን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እና የነገደ አማራ ተወላጆችን ለማፅዳት የተከፈተ የመንግስታዊ እና የፅንፈኞች የጄኖሳይድ ዘመቻ አካል እና ቀጣይነት ያለው በመሆኑ፣ ፍትሕን በትግል እንጂ በልመና ማግኘት የማይቻል በመሆኑ መላ የሀገራችን ህዝብ ለፍትህ እና ዘለቄታዊ ሰላም ቆርጦ መታገል አለበት። በዚህ ትግል ምክር ቤታችን ከህዝብ እና ከእውነት ጋር ያለውን ውገና አጠናክሮ ይሰለፋል።
ስንተባበር ፣ እንጠነክራለን፣ እናሸንፋለን!!!
የአዲስ አበባ ሚዲያ ምክር ቤት፣
ሰኔ 2፣ 2018።
ግልባጭ :-
ለተባበሩት መንግሥታት
ለአፍሪካ ህብረት
ለአሜሪካ መንግሥት
ለአውሮፓ ህብረት
ለለጋሽ ሀገራት + 2 (ሩሲያ፣ ቻይና)
ለአመንስቲ ኣንተርናሽናል
ለሂውመን ራይትስ ዋች
ለጄኖሳይድ ዋች
_
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkenaየቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena






