
ጠገናው ጎሹ
ይህ ጥያቄ በቀላሉ አዎን ወይም አይሆንም በሚል የሚመለስ እንዳልሆነና እንደማይሆን በሚገባ እረዳለሁ። በእውን እንደ ሰው ሰው እና እንደ መልካም ዜጋ የነፃነት፣የፍትህ፣ የመተባበር፣ የአንድነት ፣ የሰላምና የጋራ እድገት/ልማት/ሥልጣኔ አገር ባለቤቶች ሆነን ለመኖር የምንሻ ከሆነ እንዲህ አይነት እጅግ ፈታኝ ጥያቄዎችን መጋፈጥንና ትክክለኛ (ውጤታማ ) መልሳቸውን አምጦ መውለድን ግድ ይለናል። የትም የማያደርስ የዲስኩር፣ የሰበካ እና የትንታኔ ድሪቶ እየደረትን ለአያሌ ዓመታት ያሳለፍነውን ራሳችንን የማታለል የዘመን መለወጫ ልማድ ከምር መመርመርና የእውነተኛ ፍኖተ ህይወት መገለጫ የሆነውን ራስን ብቻ ሳይሆን ትውልደ ትውልድን የመታደግ ሃላፊነትን መወጣት ይኖርብናል። ከሞት በኋላ ተስፋ ለምናደርገው ህይወትም ከዚህ መሠረታዊና የተቀደሰ ምንነትና ማንነት በላይ ዋስትና የለውምና።
የአምባገነንት የሥልጣን ዘመናቸው በለመዱት የጡጫና የማታለል ዘዴያቸው እንደማይቀጥል ሲያውቁ የሴራና የሸፍጥ ፖለቲካ ማምረቻና ማከፋፈያ ቤተ መንግሥታቸውን ለባለ ተረኛ እያስረከቡ መከረኛ የአፍሪካ ህዝብ በርሃብ ጠኔና በበሽታ ሰለባነት እየማቀቀ እንዲከፍል በሚገደድበት የግብርና መሰል ክፍያ ቀሪ የጡረታ እድሜያቸውን እየተንፈላሰሱ መኖሩ (መኖር ከተባለ) አልበቃቸው ብሎ በህዝብ ላይ መከራና ውርደትን በከፋ ሁኔታ ካራዘሙትና እያራዘሙ ካሉት እኩያን ገዥዎች ጋር በመሞዳሞድ/መሻረክ ልክ የሌለው የከርስ ተገዥ የሆኑ ግለሰቦችንና ቡድኖችን መታዘብ አዲስ ነገር ባይሆንም አሁን የደረስንበት ደረጃ ግን ከህሊና የመረዳት አቅም በላይ ሆኗል።
እኩያን የአፍሪካ ገዥዎች በአፍሪካ ህዝብ ስም የተቋቋሙት እንደ የአፍሪ ህብረት እና ኢጋድ የመሳሰሉ ድርጅቶችን እጅግ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ለአምባገነናዊ አገዛዞች መሸፈኛነት እንዲያገለግሉ የማደረጋቸውን መሪር ሁኔታ ከምር በሆነ ቁጭትና ሂሳዊ እይታ የሚታዘብ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ሰው ህሊናውን ምን ያህል እንደሚረብሸው ለመገመት የሚከብድ አይመስለኝም።
የአፍሪካ አገራት ገዥዎች ሲያሻቸው በዴሞክራሲና በአገር ልዑላዊነት ስም እያታለሉና ሲፈልጉ ደግሞ ጨካኝ የጭቆና ሰይፋቸውን እየተጠቀሙ ለመቀጠል አለመቻላቸውን ሲያውቁ ሥልጣነ መንበራቸውን ሳይወዱ በግድ እያስረከቡ በጡረተኝነት በመሰናበት በህዝብ ግብርና መሰል ክፍያዎች ተዝናንተው የሚኖሩበት የጡረታና ሌላም ጥቅማጥቅም አልበቃቸው ብሎ በሰላም መልክተኝነት እና በምርጫ ተብየ ታዛቢኝነት ስም የአገሬን ህዝብ ጨምሮ በመከረኛው የአፍሪካ ህዝብ ፖለቲካ ወለድ የመከራ ቁስል ላይ እንጨት እየሰደዱ መከራውን ይበልጥ አስከፊ ያደርጉበታል። እንዲህ አይነቱን የጭካኔ ፖለቲካ ጨዋታ ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ በቃ ለማለት ከተሳነን መጭውን አዲስ ዓመት/የዘመን መለወጫ የምንቀበለው የዘመን ቀመር ቁጥርን እየቆጠርንና በእኩያን ገዥዎች የባርነት ቀንበር ሥር እየማቀቅን መሆኑን ከምር መገንዘብ ይኖርብናል።
የአፍሪካ ህብረትንና እና ኢጋድን የመሳሰሉ አህጉራዊና ቀጠናዊ ድርጅቶች በሰላም መልእክተኝነትና በምርጫ ታዛቢነት ስም እየመለመሉና እየሾሙ ከሚያሰማሯቸው ግለሰቦች የሚያገኙትን የሃሰት ሪፖርት/ድርሰት እንደ መልካምና ውጤታማ የምርጫ ሂደትና ውጤት ማረጋገጫ/መገለጫ እንደሆነ እያደረጉ በመከረኛው ህዝብ ላይ እጅግ ርካሽና አደገኛ የእከክልኝ እንዳክልህ ፖለቲካ ጨዋታ ሲጫወቱ መታዘብ ህሊናውን የማይረብሸው ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ህሊና ያለው ሰው የሚኖር አይመስለኝም። እናም ይህንን አይነት እኩይ አስተሳሰብና ተግባር በቀጥታና ገንቢ በሆነ ይዘትና አቀራረብ ከባድ ነውር ነውና ይታረም ለማለት ወኔው የሚያጥረን ከሆነ ከፍተኛ ችግር እንዳለብን ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል።
የአፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ የሚሰኙ የስመ መልካምነት/የስመ ገናናነት መገለጫ ስያሜዎች በተግባር የአምባገነኖች ክለባት/አውዶች እንዲሆኑ በመደረጋቸው ይኸውና መከረኛው የአህጉሩ ህዝብ ከቀጥታ ቅኝ ተገዥነት/ባርነት ማብቃት ከ6 አሥርተ ዓመታት በኋላም በገዛ ወገኖቹ እኩይ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ምክንያት የሚገኝበትን ግዙፍና መሪር ሁኔታ ለመረዳት የሚጠይቀው ቅንና ሚዛናዊ ህሊናን እንጅ ግልፅና ግዙፍ ስለሆነው እውነታ የመረጃና ማስረጃ ጋጋታ መደርደርን አይደለም።
ለአያሌ ዘመናት ሥር የሰደደው የሸፍጠኞች፣ የሴረኞች እና የጭካኔ አገዛዝ አራማጅና ጠርናፊ ገዥ ቡድኖች የሚጫወቱት “የእከክልኝ እንዳክልህ” እጅግ አስቀያሚና አደገኛ የፖለቲካ ጨዋታ ሰለባ የሆነው የአገሬ ህዝብም ትርጉም ያለው ማለትም በእውነተኛ ነፃነት፣ ፍትህ ፣እኩልነት፣ አንድነት፣ ሰላምና የጋራ ብልፅግና የታጀበ የዘመን መለወጫን/አዲስ ዓመትን የሚቀበለውና የሚያከብረው መቼና እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ ህሊናችንን ረፍት ካልነሳው እና ተገቢውንና ወቅታዊውን መልስ አምጠን እንድንወልድ ካላስገደደን ከደመ ነፍስ ፍጡራን በምን የተሻልን እንደሆን የየራሳችንን ውስጠ ነፍስ/ህሊና መጠየቅ አለብን።
ከብዙ ጊዜ “የእባካችሁ በገዛ አገራችን አታሳዱንና አትግደሉን” ተማፅኖ በኋላ “በቃ ማለት በቃ ነው” በሚል ቆራጥና ፈፅሞ ወደ ኋላ በማይመለስ የህዝብ የነፃነት ንቅናቄ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ የመቸለሱ አስቀያሚና አደገኛ አዙሪት/ልማድ በአግባቡና በወቅቱ እስካልተገታና በመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ አራማጅነት እስካልተተካ ድረስ የዘመን መለወጫ/የአዲስ ዓመት ቀመርን እየተከተልን እንኳን አደረሰንና የከርሞም ሰዎች ይበለን መባባል በራሱ ብቻ በፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ቀንበር የጎበጠውን (የተሽመደመደውን) የገሃዱ ዓለም እኛነታችንን ፈፅሞ አይቀይረውምና ከምር ሊያሳስበንና ተገቢውን ጥረት ሁሉ እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል ።
ሰሞኑን በአፍሪካ ህብረት በተመለመለው/በተመደበው የቀድሞው የኬንያ ፕሬዘደንት ኡሁሩ ኬንያታ እና በኢጋዱ ወርቅነህ ገበየሁ ጠርናፊነት የተመራው የታዛቢዎች ቡድን አገራችን ኢትዮጵያ የነፃና የዴሞክራሲያዊ ምርጫን ለ7ኛ ጊዜ የማካሄዷን “የምሥራች አብስሮናል” ። ታዲያ ይህ አይነት የቀድሞና የአሁን የአፍሪካ መሪዎች ተብየዎች በህዝብ መከራና ውርደት የመሳለቅ ክፉ የፖለቲካ ጨዋታ ለአያሌ ዓመታት የመጣንበትንና አሁንም በባሰ ሁኔታ የምንገኝበትን አገራዊ ፣ ቀጠናዊና አህጉራዊ ፖለቲካ ወለድ አዙሪት/ዝቅጠት በግልፅ ካላሳየን ሌላ ምን አይነት የውርደት ማሳያ ነው የምንጠብቀው? እንዲህ አይነቱ እጅግ አሳዛኝ (tragic) አገራዊ፣ አሀጉራዊና ቀጠናዊ የፖለቲካ ጨዋታ ቁርጠኛና ዘላቂ ለሆነ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ይበልጥ ካላዘጋጀንና ነፃነት ወይም ሞት ለሚል ፅዕኑ ተጋድሎ ካላነሳሳን ሌላ ምን?
እግሩ ወደ መቃብር እየተጠጋ በመሄድ ላይ ያለው የቀድሞው የናይጀሪያ ፕረዝደንት ኦባሳንጆ ከአሁን በፊት ሁለቱን የህወሃት/ኢህአዴግ አጃንጃዎች (ህወሃትንና ብልፅግናን) ለማግባባት/ለማስታረቅ ያደረገው ሙከራ ፋይዳ ቢስ መሆኑ ትምህርት አልሆነው ብሎ ዛሬም የአራት ኪሎውን ቤተ መንግሥት ለተቆጣጠረው አንጃ/ብልፅግና መልካም ዜና አበስራለሁ በሚል ይመስላል ወደ ትግራይ እንደተጓዘ ሰምተናል ። የአገሬ ህዝብ መጭውን ዓመት/ዘመን የሚቀበለው ከእንዲህ አይነት አስቀያሚና ጨካኝ የፖለቲካ ጨዋታ ጋር እንዳይሆን አበረታችና ተስፋ ሰጭ የሆነውን የፋኖነት/የአርበኝነት ተጋድሎ ሁለገብና ሂሳዊ በሆነ ድጋፍ/ተሳትፎ ይበልጥ ማጠናከርና የመከራውን ጊዜ ማሳጠር ይኖርበታል ።
ከኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባህላችን ላይ የእኩያን ገዥ ቡድኖች ሸፍጥ፣ ሴራና ጭካኔ ሲጨመርበት ሊያሳድር የሚችለው ፈታኝ ሁኔታ ብስለትና ጥበብ የተሞላበት እቅድና አካሄድ የመጠየቁ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ ከአገራችን የትጥቅ ወይም የሁለገብ ትግል ታሪክ አንፃር ሲታይ በምክንያታዊነት ጥንካሬው እና በተጋድሎ መርህና ሥነ ምግባር እጅግ አበረታች በሆነ ሁኔታ በፋኖዎችና ይህንኑ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎን በሚጋሩ ሌሎች ወገኖች ግንባር ቀደም ተፋላሚነት በመካሄድ ላይ የሚገኘው ተጋድሎ ትክክለኛ ግቡን እንዲመታ ማስቻልን የግድ ከሚል ጊዜና ሁኔታ ላይ ነው የምንገኘው። ይህንን ታሪካዊ ተልእኮ ሂሳዊ በሆነ ድጋፍ (ተሳትፎ) በማጠናከር ከዘመን ጠገቡ፣ ከአስከፊውና አስፈሪው ፖለቲካ ወለድ አገራዊ መከራና ውርደት ሰብሮ ከመውጣትና የጋራ ነፃነትን በጋራ ተጋድሎ እውን ከማድረግ ውጭ ሌላ የተሻለ ፍኖተ ነፃነት የለም። ይህንን ሆነንና አድርገን ለመገኘት ከተሳነን የማንም እኩይ ገዥ/ፖለቲከኛ እና የምንም አይነት መከራና ውርደት ሰለባዎች ሆነን ብንቀጥል ከቶ ሊገርመን አይገባም።
ለዘመናት የመጣንበትና አሁንም በባሰ አኳኋን ተዘፍቀን የምንገኝበት እጅግ ፈታኙ ጥያቄ ከታሪክ ሂደት በመማር ጎጅውን እያረምንና እና በጎውን ለማያቋርጥ ሥልጣኔና የጋራ ብልፅግና ግብአትነት እየተጠቀምን ወደ ፊት ከመገስገስ ይልቅ በሥልጣነ መንበር ላይ በሚፈራረቁ ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ባለጌ፣ ፈሪና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች እየተጠለፍን በመውደቅ ቀመሩን እየጠበቀ የሚመጣውን የዘመን መለወጫ/አዲስ ዓመት አሜንና አሜን ወይም ይሁንና ይሁን በሚል ራስን የማታለል ልማዳዊ ምንነትና ማንነት እየተቀበልን የመቀጠላችን ጉዳይ እንዴትና መቼ ነው ፍፃሜ የሚያገኘው? የሚለው ነው።
ይህ ፈታኝ ጥያቄ ከፊታችን በሚጠብቀን አዲስ ዓመት ፍፃሜ ካላገኘ ወዮ ለእኛው ለራሳችን በእኛው በገዛ ራሳችን እኩያን ገዥ ቡድኖች ከሰብአዊ ፍጡራን በታች ሆነን ለመቀጠል ለፈቀድነው! አዎ ወዮ ለእኛው ለራሳችን ከማሰቢያ ረቂቅ አእምሮና ከብቁ የማከናወኛ አካል ጋር የመፈጠራችን ዓላማ ዋጋ እያሳጣን ከመከራና ከውርደት ጋር መለማመድን ልማድ ላደረግነው!
ቁመን ያስገደልናቸው እጅግ አያሌ ቁጥር ያላቸው ንፁሃን ወገኖችና የነፃነትና የፍህ አርበኞች እንደ እኛ ለአዲስ ዓመት ያልደረሱት በፈጣሪ አድሏዊ ውሳኔ ይመስል “ስንቶች ሲለዩ እኛ ለዚህ በመድረሳችን ምስጋና ይድረሰው፤ እንኳን አደረሰን” እያልንና እየተባባልን የመቀጠላችንን አስቀያሚ ልማድ ከምር በሆነ ይዘትና አቀራረብ ካላረምነው እጅግ አስፈሪ ሁኔታ ላይ ነንና ከልብ ሊያስጨንቀን ይገባል።
አዎ! ለዚህ ነው እየተቃረበ ያለውን አዲስ ዓመት የዘመን ጠገብ ፖለቲካ ወለድ አስከፊና አደገኛ አዙሪትን ሰብሮ በመውጣት በነፃነት አገር በነፃነት ኗሪዎች እንሆን ይሆን ወይንስ ከተጠናወተን መከራና ውርደት ጋር ይበልጥ እየተለማመድን እንቀበለው ይሆን? የሚለው ጥያቄ ህሊናችንን ሊያስጨንቀውና ትክክለኛውን መልስ አምጦ እንዲወልድ ሊያስገድደው ይገባል ብሎ በግልፅና በቀጥታ መነጋገር ጊዜ የማይሰጥ ጉዳያችን መሆን ያለበት።
አዲስና የማይጠበቁ ወይም ያልነበሩና ያልሆኑ ባይሆኑም ከሰሞኑ የተከታተልናቸውና የታዘብናቸው የእኩያን ገዥዎች የሸፍጠኝነት፣ የሴረኝነት፣ የብልግና እና የጭካኔ አስተሳሰብና አካሄድ የወለዳቸውን የመከራ ምርጫ ተውኔቶች በተለመደው ድርጊት አልባ ትንተና እና የራስን ሃላፊነት ወደ ፈጣሪ እየገፈተሩ እግዚኦ ባይነት እንኳንስ ለማስቆም ፋታ በሚሰጥ አኳኋን ለማስታገስም ፈፅሞ አይቻለንምና ከምር ልብ እንበል ።
እርግጥ ነው እያንዳንዱ ትውልድ በየራሱ ዘመንና ተጨባጭ ሁኔታ የሚለካና የሚወሰን የውድቀት ወይም የስኬት እጣ ፈንታ ያጋጥመዋል። የእኛ ትውልድ ግን እጅግ ዘመን ጠገብ ከሆነ ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ዶፍ በኋላም እንኳንስ ለአገር መሪነት የራሳቸውን እንጡራ ነፍስ/ህይወት በቅጡ ለመምራት የሚያስችል እውቀት፣ ክህሎት፣ ቀናነት፣ እውነተኝነት፣ ሞራላዊ ልእልና፣ ሥን ልቦናዊ ብርታት፣ ሥነ ምግባራዊ ስምረት፣ የበጎ መንፈስ እሴት ፣ ሰብአዊ ሩህሩህነት ፣ ወዘተ ባህሪ የሌላቸው መሪ ተብየዎች መሳለቂያ ሲሆን መስማትና ማየት ህሊናን በእጅጉ ይረብሻል። ለዚህም ነው በመካሄድ ላይ ያለውን ህልውና፣ ነፃነት ፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ሰላም፣ ፍቅር፧ አንድነትና የጋራ ብልፅግና የሚረጋገጥባትን አገር እውን የማድረግ ተጋድሎ በሁለንተናዊ ድጋፍ መጠናከር ማጠናከር ያለበት።
ይህ ትውልድ አስከፊውን ትውልዳዊ የውድቀት አዙሪት ተጋፍጦ ራሱን ነፃ በማውጣት ነፃነትና ፍትህ የሚረጋገጥበትን ሥርዓተ ፖለቲካ እውን ካላደረገ በስተቀር የግፍ ሞት ሰለባ የሆኑ የሚሊዮኖች ወገኖቹን አስከሬን እየቆጠረ፣ የራሱን የቁም ሟችነት ይበልጥ እየተለማመደ ፣ የእኩያን ገዥዎች መሳለቂያነቱን እንደ መልካም ነገር አሜን ብሎ እየተቀበለ ፣ ራሱን ከደመ ነፍስ ፍጡራን በታች ማግኘቱን እንደ ፀጋ/በረከት እየተቀበለ ፣ ከዚህ የባሰ አታምጣብኝ እያለ እና ሳይኖር እየኖርኩ ነው በሚል ራሱን በራሱ እያቄለ ይቀጥላል። በእጅጉ አያስፈራም? ተገቢ ፍርሃትን በተገቢው መንገድ ካስተናገዱት ከመከራ የማውጣት ሃይል ሲኖረው ልኩን ያለፈ የተሸናፊነት ፍርሃት ግን ለመከራ ቀንበር ተሸካሚነት አሳልፎ ይሰጣል።
ለዘመን ጠገቡና ለአስከፊው ሁለንተናዊ ውድቀታችን ዋነኛ ምክንያት የመሆንና በሃላፊነት የመጠየቅ ጉዳይ የእኩያን ገዥዎች መሆኑን እነርሱ ራሳቸውና የቅርብ ግብረ በላዎቻቸው ካልሆኑ በስተቀር ለማስተባበል የሚሞክር ባለ ጤናማ ህሊና ወገን የሚኖር አይመስለኝም።
በሌላ በኩል ግን ከየራሳችን ልክ የሌለው የውድቀት አዙሪት ራሳችንን ነፃ የማድረጉ ሃላፊነትና ግዴታ ትኩረት ሊነፈገው እንደማይገባ ግልፅና ግልፅ መሆን አለበት።
የሃይማኖታዊ እምነት መሪነትንና አማኝነትን በቃል ከማነብነብ ግልብ ልማድ አውጥቶ በፈጣሪ ፈቃድ ለትልቅ ዓላማ የተሰጠን የማሰቢያ ረቂቅ አእምሮና ብቁ የማከናወኛ አካል በመጠቀም የፈጣሪን እገዛ እየጠየቁ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓተ ፖለቲካንና አስተዳደርን እውን በማድረግ የሃይማኖታዊ እምነት ነፃነትን ጨምሮ ሁሉም ሰው የመሆን መሠረታዊ መብቶች በሚረጋገጡበትና በሚከበሩበት ሁኔታ ሥር የመኖሩ ጉዳይ ፈፅሞ ለድርድር መቅረብ ያለበት ጉዳይ መሆን የለበትም ።
ቁጥራቸው የሚያኮራ ባይሆንም የሃይማኖታዊ እምነት ተልእኳቸውን ለመወጣት የሚጥሩ የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች/አስተማሪዎች መኖራቸው እውነት ቢሆንም ከላይ ከአናት ጀምሮ እስከታች ያለው እና በተለይም በከሞችና በከተሞች አካባቢ የሚገኘው አብዛኛው የሃይማኖት መሪ፣ ፣ ጳጳስና ሊቀ ጳጳስ ፣ ሊቅና ሊቀ ሊቃውንት፣ መምህርና ሰባኪ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ ፓስተር፣ ነቢይ ተብየ ፣ ሸህ፣ ወዘተ በአድርባይነት ክፉ ልክፍት የተለከፈ እና ከዚህም አልፎ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለእኩያን ገዥዎች የቤተ መንግሥት ፖለቲካ ራሱን አሳልፎ የሰጠ የመሆኑን ግዙፍና መሪር እውነትነት የገዛ ራሳችንን የውድቀት አዙሪት ላለመቀበል ወኔው እየሸሸን ካልተቸገርን በስተቀር ልንከደው የምንችል ጉዳይ አይደለም።
አስከፊውን 7ኛ የምርጫ ጨዋታ/ድራማ በላቀ ንቃተ ህሊና፣ በተቀነባበረና በተባበረ አደረጃጀት እና የተሸናፊነትንና የፍርሃትን ደዌ በሚቀርፍ አቋምና ቁመና በመታገል ከባለጌ፣ ከሸፍጠኛ፣ከሴረኛና ከጨካኝ የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኛ ገዥ ቡድኖች ራስን ነፃ በማውጣት ዴሞክራሲያዊትና ለዜጎቿ ሁሉ ምቹ የምትሆን ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ ውጭ ሌላ ምርጫ/አማራጭ ፈፅሞ የለም። አይኖርምም።
ለዚህ ነው እኩያን ገዥ ቡድኖች መከረኛውን ህዝብ ፖለቲካ በወለደው ሁለንተናዊ የመከራና የውርደት ዶፍ ሰለባ እያደረጉ በቀጠሉበት ግዙፍና መሪር እውነታ ውስጥ ሁሉንም ራሱ ካላደረገውና ስለ ሁሉም ነገር ራሱ ካልተናገረ/ካላላዘነ የአገር መሪ የሆነ በማይመስለው ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየ አማካኝነት ራሳቸው ያከናነቡንን ዘመን ጠገብ አገራዊ ቀውስ/ውድቀት ደስታና ክብር እንዳጎናፀፉን እያደረጉ ገልብጠው ሊያስነብቡንና ሊያሳምኑን ሲሞክሩ እያየንና እየሰማን ምንም የማናደርግ ከሆነ የእነርሱው መሳለቂያዎች/መጫወቻዎች እንደሆን መጭውን ዓመት/ዘመን የምንቀበለው የመሆናችን ግዙፍና መሪር እውነታ በእጅጉ ሊያሳስበንና ተገቢውን ሁሉ እንድናደር ከመቸውም ጊዜ በላቀ ሊያነሳሳን የሚገባው ።
እናም ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ህሊና ያለው ወገን ሁሉ ልብ ይበል!!!
____
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






