
ጠገናው ጎሹ
“የጠቅላይ ሚኒስር አብይ አህመድ ስትራቴጂያዊ ትዕግሥት ሻቢያን፣ ህወሃትንና ጀሌዎቻቸውን እያሽመደመደና እያደቀቀ ወደ ፊት ቀጥሏል ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ወደ ፊት”
ይህ ከአንድ የብልፅግና የሚዲያ ሠራዊት አባል ከሆነ የማህበራዊ ሚዲያ (Abera Delelo) የተወሰደ ውዳሴና መፈክር ነው። ምንም እንኳ ለዘመናት ከመጣንበትና አሁንም በባሰ አኳኋን ከምንገኝበት ፖለቲካ ወለድ ቀውስ/ውድቀት አኳያ/አንፃር አሳዛኝ እንጅ አስገራሚ ባይሆንም እንዲህ አይነት ከባለ ህሊና ሰብአዊ ፍጡርነት በታች የሚያወርዱ እና የመከረኛውን ህዝብ መከራና ውርደት የሚያራዝሙ የፖለቲካ እብደቶችን ፣ድንቁርናዎችንና የሞራል ጉስቁልናዎችን/ዝቅጠቶችን አካፋን አካፋ በሚያሰኝ ይዘትና ደረጃ ካልተጋፈጥናቸውና ካላሸነፍናቸው ፋይዳ የሌለው የአልቃሽነትና የአስለቃሽነት ደዌ ሰለባዎች እየሆንና ሳንኖር እየኖርን እንደሆነ ራሳችንን እያቄልን/እያታለልን እንቀጥላለን።
እንደሚከተለው የምገልፃቸው የሂሳዊ አስተያየቴ ነጥቦችም ከዚሁ መሠረታዊ የአገር/የህዝብ ጉዳይ የሚነሱ እንጅ ግለሰባዊ ህይወትን ወይም ምንነትንና ማንነትን መነሻና ዒላማ የሚያደርጉ እንዳልሆኑ ግልፅ እንዲሆን እያስገነዘብኩ ወደ ነጥቦቼ ልለፍ፦
1) የአብይ የተለየ የጥንቆላ/ የቡና ስኔ አተላ ቅሬትን የመተርጎም “ጥበብ” ነው ካልተባለ በስተቀር ማነኛዋም ልጇን የምትወድ እናት ለልጇ የንጉሥነት ወይም የንግሥትነት መልካም ምኞት የመግለጿ ነገር ያልተለመደና እውነት ነው በሚል ቅዠት ውስጥ የሚያስገባ ፈፅሞ አይደለም። አብይ ግን ገና ከለጋ ወጣትነቱ በዚህ ክፉና አደገኛ ቅዠት ተለክፎ አደገ፣ ጎረመሰ/ጎለመሰ እና ዛሬ እየሆነና እያደረገ ያለውን የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሴራና ሸፍጥ አገዛዝን እያገለገለ ባለበት ወቅት ይቃዠበት የነበረውን “የ7ኛ ንጉሥነት” ቀደም ብሎ የተዘጋጀ ህዝባዊ/ዴሞክራሲያዊ ሃይል ባለመኖሩ በግልብ ስሜት ይጋልብ የነበረውን የህዝብ ንቅናቄ ተጠቅሞ የቤተ መንግሥት ፖለቲካውን በመቆጣጠር “በልጅነቴ የተተነበየልኝ ትንቢት እውን ሆኗልና አሻጋሪያችሁ እኔና እኔ ብቻ ነኝ ብሎን አረፈ። ምሁር ነኝ ባዩን ጨምሮ አብዛኞቻችንም ሙሴነትን ጨመርንበት “አዎ! የኢትዮጵያ የትንሳኤ ሙሴ አንተ ነህ” አልንና በመማር/ፊደል በመቁጠር የሚገኘውንና ነገሮችን በአግባቡ የመቃኘት ፣ ሰብሰብ አድርጎ የማደራጀት፣ በጥሞና የመዳሰስ፣ በጥልቀት የመረዳትና ጊዜ ወስዶ የመወሰን (የማድረግ ወይም ያለማድረግ) ታላቅ ጥበብ አውልቀን ጣልንና ራሳችንን ብቻ ሳይሆን መከረኛውን ህዝብ ትንሽ እንኳ የእፎይታ ጊዜ ሳያገኝ የእኩያን ገዥዎች ሰለባ ሆኖ እንዲቀጥል አደረግነው።
2) አዎ! አስፈላጊ በመሆኑ በሌላ አገላለፅ ልድገመውና ሴረኛ፣ ሸፍጠኛና ጨካኝ ገዥዎች ያደነቆሩት መከረኛ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ሳይማርና በፖለቲካ ወለድ ችጋር እየተገረፈ በሚከፍለው ግብር ተምረዋልና ተመራምረዋል የተባሉት እና በሙያም ሆነ በሥራና በእድሜ ተሞክሮ አንቱ ያልናቸው አብዛኛዎቹ ምሁራን/ልሂቃን “የዘመናችን ሙሴ ተገለጠ፣ ይህ ከፈጣሪ እንጅ ከሰው አይደለም፣ የኢትዮጵያ ትንሳኤ እውን ሆነ ፣ ወዘተ” በሚል ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የመማርንና የመመራመርን ሰፊና ጥልቅ ትርጉም/እሴትነት አቧራ ላይ አውርደው አጎሳቆሉት። ከእነዚህ ምሁራን/ልሂቃን ተብየዎች መካከል አንዳንዶቹ ዛሬም በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪነት፣ በኮሚሽነርነት፣ በምርጫ ቦርድ መሪነት ፣ ወዘተ ስም የአሻንጉሊትነት ሥልጣን ተሰጥቷቸው የብልፅግናን እና የጠርናፊውን የአብይ አህመድን ዙፋን የማገልገልና የማስጠበቅ ወራዳና ትውልድ አዋራጅ ተልእኮንና ሃላፊነትን በመወጣት ላይ የሚገኙ ናቸው። ከዚህ የከፋ የመማርንና የመመራመርን ሰፊና ጥልቅ ትርጉም/እሴትነት የማጎሳቆልና የትውልድ ማፈሪያ/መሸማቀቂያ የመሆን አሳፋሪና አስፈሪ ምንነትና ማንነት ይኖር ይሆን?
3) ብልፅግና ተብየው ገዥ ቡድን የፈጣሪን/የክርስቶስን ሃያልና የተቀደሰ ምንነትና ማንነት በሚናገረው/በሚያስተምረው ታላቁ መጽሐፍ ቀዱስ/ወንጌል ውስጥ ፈፅሞ የሌለውንና በኑሮ/በቁስ መበልፅግንና ይህንን ለማድረግ ደግሞ መሠረታዊ የሰብአዊ ፍጡርነት መገለጫ ስለሆኑት ርህራሄ፣ ሃዘኔታ ፣ እውነተኝነት፣ ቅንነት፣ ፍቅር፣ ሰላም ፣ወዘተ ሃይለ ቃላት ደንታ ቢስነትን እና እውነተኛና ህዝባዊ በሆኑ የሰብአዊ ልማትና ሥልጡኔ ሥራዎች ሳይሆን እጅግ ብልጭልጭና ግልብ ስሜትን በሚስቡ ነገሮች መጠመድን፣ በፖለቲካ ወለድ ጨካኝ ሰይፍ ስለተሰየፉት እጅግ አያሌ ንፁሃን ቢያንስ አዝናለሁ/እናዝናለን ማለትን እንደ የብልፅግና/ቁሳዊ ሃብት አደናቃፊነት መቁጠርን፣ ወዘተ እጅግ አስከፊና አስፈሪ የ7 ዓመታት አስተሳሰብና አካሄድ አሁንም “ወይ ፍንክች” በሚል ሁኔታ መቀጠሉን መታዘብ ጤናማና ቅን ህሊና ባለው የአገሬ ሰው ላይ የሚያሳድረውን የህሊና ስቃይ በበቂ ቃላት መግለፅ የሚቻል አይመስለኝም።
4) ይህ እጅግ ግዙፍና መሪር አገራዊ የመከራና የውርደት ዶፍ በወረደበትና እየወረደ በቀጠለበት ግዙፍና መሪር እውነታ ውስጥ “የጠቅላይ ሚኒስር አብይ አህመድ ስትራቴጂያዊ ትዕግሥት ሻቢያን፣ ህወሃትንና ጀሌዎቻቸውን እያሽመደመደና እያደቀቀ ወደ ፊት ቀጥሏል ፤ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ወደ ፊት” በሚል እጅግ ወራዳ ፣ ርካሽና ጨካኝ ፕሮፓጋንዳ ነፃነት ፣ፍትህ ፣ እኩልነት፣ መተሳሰብ፣ መተዛዘን፣ ሰላም፣ እና የጋራ ልማት/ሥልጣኔ በሚረጋገጥባትና በሚከበርባት አገር ውስጥ ልኑር ብሎ በጠየቀ ህዝብ ላይ መሳለቅ ይህንን ትውልድ ከምር ካላስጨነቀውና ለዘመናት እጣ ፈንታውን ያበላሹበትን እኩያን ገዥ ቡድኖች አስወግዶ ስኬታማ እጣ ፈንታውን እውን የሚያደርግበትን ሥርዓተ ዴሞክራሲ አምጦ እንዲወልድ ካላስገደደው/ካልገፋፋው ሌላ ምን ሊሆንና ምን ?
5) እስካሁን ለመጣንበትና አሁንም ተዘፍቀን ለምንገኝበት እጅግ አስከፊ የፖለቲካ እብደት/ቅዠት ፈፅሞ የማያወላዳውና ትክክለኛው መልስ/ፍኖተ መፍትሄ አንድና አንድ ብቻ ነው። እየጀመሩ መላልሶ የመጨንገፍን/የመውደቅን ጋግርታም የፖለቲካ ባህል/ልማድ ሰብሮና ሰባብሮ በመውጣት ትውልድ ተሻጋሪ የሆነ የነፃነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የአንድነት፣ የሰላምና የጋራ ልማት/እድገት (የዴሞክራሲያዊ) ሥርዓትን አምጦ መውለድ !!!
6) ለዚህ ደግሞ ኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባህላችን ከእኩያን ገዥ ቡድኖች የሴራ፣ የሸፍጥና የጭካኔ አገዛዝ ላይ ተጨምሮ በሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ ምክንያት የተፈጠሩና ሊፈጠሩ የሚችሉ ፈታኝ ሁኔታዎች እንዳሉ ሆኖ መሠረታዊ ተልእኮው፣ ዓላማው፣ መርሆውና ግቡ/መዳረሻው ህልውና፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ መተሳሰብ፣ አንድነት፣ ስላምና የጋራ ልማት/ሥልጣኔ የሚረጋገጥባት አገርን/ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መተኪያ የሌለውን ህይወታቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ የሚያስገድዳቸውን ተጋድሎ በማካሄድ ላይ ያሉትን ፉኖዎችንና ሌሎች የዓላማቸውና የተጋድሏቸው ተጋሪ የሆኑ ወገኖችን ገንቢ በሆነ ሂሳዊ ድጋፍ/ተሳትፎ ለድል ማብቃትን ይጠይቃል።
7) ያኔም ነው የመከራና የውርደት አገዛዛቸውን የእፁብ ድንቅ ትዕሥተኝነትና ልማታዊነት እያስመሰሉ ገልብጠውና ዘቅዝቀው ከሚያስነብቡንና ከሚሳለቁብን እኩያን ገዥዎች የምንገላገለውና እንደ ሰው ሰው እና እንደ መልካም ዜጋ ለሁላችንም የምትመች አገር ባለቤቶች ሆነን ለመኖር የምንችለው።
እናም ነፃነትን፣ ፍትህን፣ እኩልነትን፣ ሃቀኝነትን፣ ሰላምንና የጋራ ልማትን/ሥልጣኔን በእውን የሚፈልግ ልብ ያለው ወገን ሁሉ ልብ ይበል!!!
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






