
ቦርከና ዜና
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ አስተዳደር 023 ቀጅማ ቀበሌ ቀሰማ ተብላ በምትጠራ ጎጥ ‘በድንገት’ በተቀሰቀሰ የእሳት አደጋ ከ53 በላይ ቤቶች እና በአንድ መስጅድ ወድሟል ተብሏል።
የሀብሩ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ባወጣው መግለጫ፣ እስካሁን በተገኘው መረጃ መሰረት ከ54 በላይ አባውራና እማውራ፣ በአጠቃላይ ደግሞ ከ163 በላይ የቤተሰብ አባላት የጉዳቱ ሰለባ ሆነዋል ሲል ገልጿል።
ኮሚኒኬሽኑ አክሎም፤ አደጋው የተከሰተው ሁለት ህፃናት ከአገዳ ክምር አጠገብ እሳት በማያያዝ ሲጫወቱ በተፈጠረ እሳት ነው ብሏል።
የወረዳው አስተዳደር ምክር ቤት በማህበረሰቡ ላይ የደረሰውን የእሳት አደጋ ተመልክቶ ለዜጎቹ መደረግ ያለበትን ድጋፍ መለየት የሚያስችል አቅጣጫ እንዲያስቀምጡ የሀብሩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና ውሃና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደምሌን እና የወረዳው ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃን ጌትነትን ወደ ስፍራው ልኳል ተብሏል።
መግለጫው፤ ሁለቱም ኃላፊዎች አደጋው ወደደረሰበት ቦታ አቅንተው ጉዳቱን ተዘዋውረው ካዩ በኋላ ተጎጂዎችን በአካል አግኝተው በደረሰባቸው ከፍተኛ ጉዳት እጅግ ማዘናቸውን ገልጸዋል ሲል አክሏል።
በተጨማሪም ተጎጂዎችን ከዕለት ድጋፍ ጀምሮ በዘላቂነት ለማቋቋም እንዲቻል የጉዳቱን መጠን በትክክል ሊያጠና የሚችል የቴክኒክ ቡድን ተዋቅሮ ወደ ስፍራው እንዲሄድ መደረጉ ተጠቅሷል።
የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ የተቋቋመው የቴክኒክ ቡድን የጀመረውን ስራ አጠናቆ ሲጨርስ ተጨማሪ መረጃዎች ይፋ እንደሚደረጉ ገልጸዋል።
በዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመታደግ በመንግስት በኩል ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ያሉት ኃላፊው፤ በጎ አሳቢ ግለሰቦች፣ በጎ አድራጊ ማህበራት፣ ወጣቶች፣ የወረዳው ህዝብ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ግብረሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






