
ቦርከና ዜና
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እነዚህን ጥያቄዎች እንደ ግብዓት በመያዝ፣ አሰባሳቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሊሠሩ እንደሚገባ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአገራዊ ምክክሩ የተነሱ የሐሳብ ልዩነቶችን በንግግር መፍታት ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል።
ምክር ቤቱ ባለፉት 4 ዓመታት በአገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት አብሮ ሲሠራ፣ በርካታ ሐሳቦችን በገለልተኝነት ማንሳቱንም አስታውቋል።
የምክር ቤቱ አመራር አቶ መላኩ ስብሐት፤ ምክር ቤቱ በአጀንዳ አሰባሰብ ሂደቱ መረጃዎችን ከማደራጀት በተጨማሪ በማማከርና በመታዘብ ሰፊ ሥራ መሥራቱን ተናግረዋል።
በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ባሉ ግጭቶች ምክንያት ሰለባ ይሆናሉ ተብሎ የሚታሰቡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት፣ ከ5 ሺህ በላይ ማኅበራትን በማሳተፍ መሠራቱንም አብራርተዋል።
ምክር ቤቱ ተሳታፊዎቹ የሚያነሷቸው ሐሳቦች ከፋፋይ፣ አሉታዊ ስሜት የሚፈጥሩ እንዲሁም ለግጭት የሚዳርጉ እንዳይሆኑ ቀደም ብሎ መሥራቱንም አስታውቋል።
በምክክሩ ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና የወጣቶች ተወካዮች እንዲሁም የተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ወቅት በተወሰኑ ክልሎችና በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ባሉ ተወያዮች በኩል ግጭት ቀስቃሽ ሐሳቦች ገጥመውናል ያሉት በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ፍሬሰናይ ገበየሁ፤ የሲቪል ማኅበራት የጋራ መግባባት ላይ በሚያደርሱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ምክር ቤቱም በማማከር ረገድና በውይይቱ ላይ በመሳተፍ እገዛ ማድረጉን አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን ጀምሮ እንደሚካሄድ መግለጹ ይታወቃል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






