
ቦርከና ዜና
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ “በመላው ኢትዮጵያ የሰላም ጠንቅ የሆነውና በስልጣን ላይ ያለው ኃይል፣ ኢትዮጵያን ከመበታተን እንዲገታና ተጽዕኖ እንዲደረግበት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስናሳውቅ ብንቆይም፣ ምላሽ አለመገኘቱን” አስታውቋል፡፡
የህወሓት የጽህፈት ቤት ኃላፊ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በበርካታ ጉዳዮች ላይ የፓርቲያቸውን አቋም ያንጸባረቁ ሲሆን የፌደራሉን መንግስት ደግሞ ደጋግመው ከስሰዋል፡፡
ለሦስት ዓመታት ከስምንት ወራት በላይ የዘላቂ ግጭት ማቆም የፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈርሞ፣ ጊዜያዊ አስተዳደር ተመስርቶ የነበረ ቢሆንም፣ በትግራይ ህዝብ ላይ የሚፈጸመው “የዘር ማጥፋት” በረቀቀ መንገድ መቀጠሉን አመልክተዋል፡፡
የጽ/ቤት ኃላፊዋ በመግለጫው “ተኩስ ለተወሰነ ጊዜ ቢቆምም፣ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ላይ የድሮን ጥቃት በመፈጸሙ” ስምምነቱን ሲጥስ ቆይቷል ሲሉ ወንጅለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ከምዕራብ ትግራይ እስከ ምስራቅ ትግራይ ያለውን ሰራዊቱን በሙሉ በማሰባሰብ ለጦርነት እየተዘጋጀ ነው ሲሉ መናገራቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል፡፡
ብሔራዊ ክህደት ፈጸሟል የሚሉትና በዋናነት በስምረት ፓርቲ ውስጥ የሚገኙቱን የቀድሞው የፓርቲው አመራሮችን በተመለከተ ሲናገሩ ደግሞ “በትግራይ ላይ ጦርነት እንዲቀሰቀስ፣ በትግራይ ህዝብ ትግል እንዲዳከምና እንዲናቅ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን” አስረድተዋል፡፡
ፈትለወርቅ ሲቀጥሉ፤ በጀትን፣ ነዳጅንና ሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦችን በመከልከል በትግራይ ላይ ጦርነት ለመክፈት የሚዘጋጀውን ኃይል ትተው፣ አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት በህወሓት ላይ ያወጡት መግለጫ በዳዩ እያለ በተበዳዩ አካል ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ያለመና ትክክል ያልሆነ ነው በማለት በብርቱ ተቃውመዋል፡፡
የትግራይ ህዝብ እና የህወሓት ድርጅት ጥያቄ ህዝባችን እራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር፣ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን ነው የሚሉት የሥራ አስፈጻሚ አባሏ ይህንን ጥያቄ በመጠየቁ መቀጣት የለበትም፤ አሁንም በትግራይ ህዝብ መሰረታዊ ጥቅሞች ላይ አንደራደርም ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ላለፈው አንድ ወር በተደረገ ዘመቻ ዓለምአቀፍ ተቋማት ህወሓት የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እያካሄዱ መሆኑን የሚገልጹ ሪፖርቶችን ሲያወጡ እንደከረሙ ይታወቃል፡፡
ፈትለወርቅ ይህን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፤ ሆን ተብሎ በትግራይ እየተካሄደ ያለውን ትግል ሌላ የፍርሃትና የሽብር ድባብ ለመፍጠር የታለመ መሆኑን በመጥቀስ የትግራይ ህዝብ ህልውና እንዲቀጥል ሁሉም ሊታገል ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በከባድ ችግር ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች በማንኛውም መንገድ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ማግኘት እንዳለባቸው የገለጹት አንጋፋዋ የህወሓት ከፍተኛ አመራር ፈትለወርቅ፣ የትግራይ ህዝብ ህልውናን ለማረጋገጥ በትግራይም ሆነ ከትግራይ ውጪ ላለው ተወላጅ ያለው አማራጭ ታግሎ ማሸነፍ በመሆኑ አንድነቱን አጠናክሮ እንዲታገል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






