Homeአበይት ዜናጄነራል ታደሰ ወረደ ታግተው እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ

ጄነራል ታደሰ ወረደ ታግተው እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ

Advertisement
World Wide Travel Group
ታደሰ ወረደ
ታደሰ ወረደ

ቦርከና ዜና

ታደሰ በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጫና ከመኖሪያ ቤታቸው እንዳይወጡና ከውጭ ሰዎች ጋር እንዳይገናኙ መታገዳቸውን የቤተሰቡ የቅርብ ሰው ተናግረዋል። ረቡዕ ዕለት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ወደ መቀለ መጓዛቸውን ተከትሎ ሌተናንት ጄነራል ታደሰ በምን ሁኔታ እንደሚገኙ ለማወቅ ተጨማሪ ጥረት ተደርጓል።

ለመጀመሪያ ጊዜም ከቅርብ ቤተሰቦቻቸው ተጨባጭ መረጃ ማግኘት ተችሏል። በደኅንነት ስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ቅርብ ቤተሰባቸው እንደገለጹት፤ አምባሳደር ማሲንጋ ከሌተናንት ጄነራል ታደሰ ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው ከአዲስ አበባ ወደ መቀለ ተጉዘዋል። አንድ የጄነራሉ የቅርብ ሰው በእርግጥ አምባሳደር ማሲንጋ ጄነራል ታደሰን ለማግኘት የሞከሩት አሁን ብቻ አይደለም። ከዚህ በፊትም ሞክረው አልተሳካላቸውም ብለዋል።

የጄነራሉ የቅርብ ዘመድ ከዚህ ቀደም የተያዘው ቀጠሮ መሰረዙን ተናግረዋል። በዚህ ሳምንት ረቡዕ የተያዘው ቀጠሮ ሁለተኛ ሙከራ እንደነበርም መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል። “የትናንቱ ቀጠሮ ከተያዘ በኋላ ‘ይገናኛሉ’ የሚል ተስፋ ነበረን። ቀጠሮው ከቀኑ 5 ሰዓት ነበር። እሳቸውም ቀጠሮ እንዳላቸው ያውቁ ነበር። አምባሳደሩ መቀለ እንደገቡም ያውቁ ነበር። ከዚያ ግን 4 ሰዓት ገደማ ለዋና የደኅንነት ኃላፊው ስልክ ተደውሎ ትዕዛዝ ተላልፏል” ብለዋል።

“ምንም ዓይነት አጀባ አታድርጉ፤ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አታካሂዱ፤ ተሽከርካሪዎች አይንቀሳቀሱ፤ ይህንም ለራሱ [ለጄነራል ታደሰ] አሳውቁት” የሚል ትዕዛዝ እንደተሰጠ ገልጸዋል። በተጨማሪም “ይህ ትዕዛዝ ከተላለፈ በኋላ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ብታደርጉ ሊያስቆማችሁ የሚችል ሌላ ኃይል አለ። ስለዚህ ምንም ችግር እንዳይፈጠር ማንኛውንም ዓይነት እንቅስቃሴ አታድርጉ” የሚል ትዕዛዝ መተላለፉን አክለዋል።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ይህ መመሪያ ለሌተናንት ጄነራል እንዲሁም ለአሽከርካሪዎቻቸው እና ረዳቶቻቸው እንዲነገር ትዕዛዝ ተሰጥቷል። የጥበቃቸው ኃላፊ ይህን ትዕዛዝ ለሌተናንት ጄነራል ታደሰ ካሳወቃቸው በኋላ ጄነራሉ ትዕዛዙን እንዳልተቀበሉት እና “እኔ ራሴ መኪና ነድቼ እሄዳለሁ” ማለታቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ይህም በጥበቃ አባሎቻቸው እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረ የቅርብ ዘመድ ገልጸዋል። በተለይም ቤተሰቦቻቸው “እባክህ ተወው፤ ባለው ሁኔታ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አይታወቅም” በማለት እንደለመኗቸው እና እንዳይወጡም እንዳሳሰቧቸው ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ከሌተናንት ጄነራል ታደሰ ጋር ለመገናኘት ተስፋ አድርገው እንደነበር ጠቅሰውም፤ ሌተናንት ጄነራል ታደሰ የቤተሰባቸውን ምክር ተቀብለው ከቤት ሳይወጡ እንደቀሩ ተናግረዋል። ያለውን ሁኔታ ለአምባሳደር ማሲንጋ ደውለው እንዳስረዱም ገልጸዋል። ይህ የስልክ ውይይት “20 ደቂቃ እንደወሰደ” ቢገልጹም የውይይቱ ይዘት ምን እንደነበር ለማወቅ አልተቻለም።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ “ይህ ክስተት አንድ ክልል ሲመሩ የነበሩ ጄነራል የመናገር መብታቸው፣ ሰዎችን የማግኘት መብታቸው እና የመንቀሳቀስ መብታቸው በተግባር እንደታገደ ያሳያል” ሲሉ ገልጸዋል። “ቢወጡ ኖሮ ምን ያጋጥማቸው ነበር?” ሲሉም ጥያቄ ሰንዝረዋል።የተላለፈውን ትዕዛዝ በመጣስ የሌተናንት ጄነራል የጥበቃ አባላት “ብቻዎትን አንልክዎትም፤ አብረን እንሄዳለን” ቢሏቸው ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እስካሁን ድረስ እንደሚያሳስባቸው አክለዋል።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English

ኤክስ ፡ @zborkena 

1 COMMENT

  1. ሲጀመር ታደሰ ወረደ ከአሜሪካው አምባሳደር ጋር ተገናኘ አልተገናኘ የሚያስገኘው አንድም ለውጥ የለም። በቅርቡ ካይሮ ላይ ግብጽንና ኤርትራን ያማከረው የአሜሪካን ተልኮ ምን እንደሆነ ሰው ለይቶ ሊረዳው አይችልም። አሜሪካን ማመን ውሃ መዝገን ነው። ያኔ ወያኔ በጄ/ጻድቃን በኩል ጦርነቱ አልቋል ከማን ጋር ነው የምንደራደረው በሚልበት ወቅት የሳተላይትና የ3ኛ ሃገር የጦር መሳሪያ ማጓጓዣ አየር መንገድ በመጠቀም ወያኔን አሜሪካ ትደግፍና ታስታጥቅ እንደነበረ ግልጽ ነው። ስለሆነም እንኳን አሁን ከደቂቃዎች በፊት የተናገረውን የሚሽር ጉረኛና ራስ አፍቃሪ ፕሬዝደንት ባለበት ጊዜ ያኔ መሪዎቻቸው ሰው ሰው ሲሸቱም ነገራቸው ሁሉ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ እንደነበር ያለፈ ታሪካቸው ፍንትው አድርጎ ያሳያል። እዚህ ላይ አሳዛኙ ነገር የታደሰ ወረደ የቁም እስረኛ መሆን ነው። በሰፈሩት መስፈሪያ መሰፈር የማይቀር ሆነና እንሆ ከበረሃ እስከ ከተማ ወያኔ ራሱን እየበላና እያስበላ አልፎ ተርፎም የትግራይን ህዝብ ለመከራና ለስቃይ እየዳረገ ዛሬም ይነግድበታል። እኔ የሚያሳዝነኝ ጀጋኑ/ጀግና እየተባሉ ሲጠሩ ነው። በሃበሻ ምድር ውስጥ ጀግና የለም። ቢኖርማ 17 ዓመት ሙሉ አንድ ፈላጭ ቆራጭ ወታደራዊ መሪ ትውልድ ባልፈጀም ነበር። በትግራይ ጀግና ቢኖር 50 ዓመት ሙሉ በህዝቡ የሚነግድበትን የፓለቲካ አተላዎች መክላት በቻለ ነበር። የእኛ ሃገር ጀግኖች የጀግንነታቸው መለኪያ እጅና እግሩን የታሰረ ማሰቃየትና በጥይት ደብድቦ መግድል ብቻ ነው። ህፍሽፍሽ በሚለው መጽሃፉ ላይ ግርማይ ለማ እንደሚነግረን የራሳቸውን የትግራይ ልጆች ማጭድ አግለው የሚጠብሱ አረመኔዎች እንንደሆኑ ነው። ወያኔ በጅምላ አስተሳሰብ ሰውን ያሰረ፤ ከራሱ ህልውና ውጭ ለሌላው የማያስብ፤ በውጭ እጆች የሚነዳ ለመሆኑ በቅርቡ ደብረጽዪን በይፋ ጽምዶን ከኤርትራ ጋር አብረን የፈጠርነው ብልጽግናን ከስልጣን ለማውረድ ነው በማለት ሲናገር ተደምጧል። ችግሩ 27 ዓመት በስልጣን ቁንጮ ላይ የነበረው ወያኔ በ 27 ዓመታት ውስጥ ለትግራይ ህዝብ ያደረገው በጎ ነገር ምንድን ነው? ዛሬ የትግራይን ልጆች ማግዶ መልሶ ስልጣን ቢይዝ ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለመላ ሃገሪቱ ከሻቢያ ጋር ሆኖ መና ከሰማይ ያወርዳል ብለው የሚጠብቁ የቁም ከብቶች ካሉ የቂል ስብስቦች ብቻ ናቸው። ሻቢያና ወያኔ በታሪካቸው ሲተቃቀፉ፤ ሲጣሉ፤ ሲዋጉ፤ ሲካሰሱ የኖሩ እኩይ ሃይሎች ናቸው። የዛሬ መጨባበጥ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል እንጂ ሻቢያና ወያኔን አንድ የሚያደርጋቸው ተንኮላቸው ብቻ ነው። ሌላ አንድነት ኖሯቸው አያውቅም።
    አንድ በተስፋዬ ገብረአብ ከተጻፈ መጽሃፍ ላይ ያገኘሁት ነጥብ ትውስ አለኝ። ተስፋዬ ከአንድም ሳይሆን እሬትና ማርን እየደባለቀ እንደጻፈና እንደተናገረ ናይሮቢ ላይ እንዳሸለበ እናውቃለን። የቲራቮሎ ዋሻ በተሰኘው መጽሃፉ ላይ (በነገራችን ላይ የመጽሃፍቱ አርዕስትና ውስጡ ከአንድ ምዕራፍ በስተቀር አይገናኙም) ከእቃው መጠቅለያው ይሉሃል ይሄ ነው። ግራም ነፈሰ ቀኝ በዚሁ መጽሃፍ ላይ ዳህላክ ዴሴት ሂዶ መቃብሮችን ሲመለከት አንዳንድ መቃብሮች የተተከለላቸ ነገር በስፍራው የለም። እንዲህ ይላል ኢትዮጵያዊያን አፍርሰውት ወይም ወስደውት ይሆናል ይለናል። ሌላ ስውርና ግልጽ መርዙን በዚህና በሌሎች መጽሃፍቶቹ ውስጥ ይዘራል። አዎን እንዴት ሟች ትወቅሳለህ ትሉ ይሆናል በቁም እያለም ነው የእኔ ወቀሳ የነበረው። ደግሞም ሟች ወቃሽ መሆን አያስፈልግም የሚባለው ወግ ሊቀር ይገባዋል የሞተም ሆነ የቆመ በሥራው ሊመሰገን ወይም ሊወቀስ ይገባልና። ታዲያ ይህ ከታደሰ ጉዳይ ጋር ምን አገናኘው ይል ይሆናል አንባቢ። ታደሰ ከወያኔ ጋር ሊጥ አቡክቶ የጋገረ፤ እልፎች ሲገደሉ ያየ። ዘረፋና የሰው ልጆች መብት ሲደፈር ያልተነፈሰ በመሆኑ አሁን ላይ ኡኡታ ቢያሰማ ማን ይደርስለታል? መልሱ ማንም ነው! ዘገየም ፈጠነም ኢትዮጵያን ያጣጣለ፤ ደሙ በሰው እጅ የተነከረ ሁሉ አወዳደቁ የሮም ነው የሚሆነው።
    ባጭሩ በዚህም በዚያም እያሳበብን መገዳደላችን ይቀጥላል። እውቁ ፊታውራሪ ተክለሃዋሪያት ተክለማሪያም (የህይወቴ ታሪክ) በተሰኘው መጽሃፋቸው ላይ ስለ ተፈሪ መኮነን እንዲህ ይላሉ …በዙሪያቸው ከንቱዎች እና ግብዝ ሰዎች እየበዙ ሄድ። እድላቸው እየተቃና ጊዜው ሲያመቻቸው የበለጠ ወደ ስህተት አመሩ። በማለት ስለ ንጉስ ሃይለስላሴ ጅማሮ ይነግሩናል። አክለውም ማፍረስና እርስ በእርስ መፋጀትንም ልማድ አድርጎታል ይሉናል ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ ያላቸውን እይታ ሲነግሩን። በመጨረሻም “በታሪካችን ውስጥ ጎልቶ የሚታየው እርስ በእርስ መጠቃታትና መዛረፍ ነው” በማለት የዘመኑ ትዝብታቸውን አስፍረዋል። ይህ አሁን ያለንበትን ጊዜ አይመስልም? ስናሳዝን። የታደሰ ወረደ የቁም እስርም ሆነ በአዲስ አበባና በሌሎች ክልሎችና ከተሞች ዙሪያ እንበለ ፍርድ ተቆልፎባቸው የሚገኙ የሃገሪቱ ዜጎች ሁሉ የዚህ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የፓለቲካ የወረርሽኝ በሽታ ሰለባዎች ናቸው። ግን ማቆሚያው መቼ ይሆን? አላውቅም!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News