
ሙሉጌታ ቢያዝን
አንበሳው በሽቦ በታጠረ ስፍራ ተቆልፎበታል፡፡ ሦስት ቀን ሙሉ እህል ባፉ አልዞረም፡፡ ረሃብ ጊዜ አይሰጥምና ተንገበገበ፤ዐሥሬ ማፋሸግ ያዘ፡፡ የሚላስ፣የሚቀመስ ያገኝ ይመስል ወዲያ ወዲህ ጎርደድ፣ ጎርደድ ሲል ድንጉጧን አጋዘን በዚያ ስታልፍ ይመለከታል፡፡
“አጋዘን እርጂኝ እባክሽ ከዚህ ወጥመድ ገላግዪኝ” ሲላት “ትበላኛለህ ልረዳህ አልችልም” ብላ ከፊቱ ተሰወረች፡፡ ቀጥሎ ጅብ እያነከሰ ሲያልፍ ይመለከትና ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀርብለታል፡፡ ጅብም “አንተ ራስ ወዳድ፣ይሉኝታ ቢስ ነህና ይገባሃል ጭራሽ እርዳኝ ትላለህ? አልችልም” ብሎ እያሽካካ በቆመበት ጥሎት ይሔዳል፡፡
ጥቂት ቆይቶ ከዛፍ ዛፍ የምትዘለዋን ጦጣ ሲመለከት፣ ጎሮሮውን ስሎ ድምፁን አቅጥኖ ለማሳዘን እየሞከረ፡- “ጦጢት? ጦጢት? እረ ጦጢት?” ሲል ተጣራ፡፡ ጦጢት ‘ሰለለ እንጂ ይሄን ድምፅ የት ነው የማውቀው?’ እያለች ዞር ብትል እንኳን ሰንዝሮ ሲያገሳ ምድር የምትርድለት አንበሳ ኾኖ አገኘችው፡፡ ‘እንዴ አንተም በወጥመድ ትያዛለህ? አንተም ቀን ይጎድልብሃል?’ እያለች በሆዷ ስታጉረመርም “ጦጢትዬ?” ሲል አቋረጣት፡፡ ‘እኔን ነው ወይስ ሌላ?’ ብላ ዞር ስትል “አዎ አንቺን ነው… እባክሽን ምግብ ከበላሁ ሦስት ቀኔ ነው ክፈችልኝና ልውጣ” ሲላት “ምን?” አለችው ባለማመን “የምሬን ነው” አለ፤ ድምፁን ለማለስለስ እየሞከረ፡፡ “ሞኝህን ፈልግ… ጅብ የማያውቁት ሀገር ሔዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ አሉ(ወደ ጅብ እየተገላመጠች)፣ ለማያውቅህ” ብላ እያሽካካች ተሰወረች፡፡
አንበሳ በብስጭት ጠጉሩን እየነጨ ወዲያ ወዲህ ጎረደድ ጎርደድ ሲል በግ ‘በበበበበበ’ እያለች ስታልፍ ያያታል፡፡ በግንም ከበፊቱ ይበልጥ ድምፁን አሳዝኖ /በአራራይ ቅኝት/ ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀርብላታል:: በግም:- “እንደምትባላ ቀዬው ሲያወራ ሰምቻለሁ …ብትበላኝስ?” ትለዋለች፡፡ ‘እህ’ ብላ ስትሰማው አንበሳ የልብ ልብ ተሰማው፡፡ “…ዓላወቁልሽም እንጂ እንዳንቺ ብልህና ጠቢብ አንስሳ በምድር ከቶ አይገኝም…ይሄው ጊዜ ሰጥተሸ ሰማሽኝ…ጥበብ ከመስማት ይጀምራል… ረሃቡ ስለጠናብኝ ሣር ቢኾን ካንቺ ጋ እግጣለሁ፤ ደግሞም ካመት እስካመት ሣር የማይነጥፍበትን መስክ አሳይሻሁ፤አሁኑኑ እንዳሳሁሽ ቁጠሪው (ታድያ ለማንም እንዳትነግሪ) እባክሽ” ሲል ተማጠናት፡፡
እንደ አንበሳ ባለ ኃያል፣በእንስሳዎች ሁሉ አለቃ ፣ ‘ብልህና ጠቢብ’ መባሏ ልቧን አሞቀው፤በውዳሴው ሰከረች፡፡ ‘ደግሞ ዓመት እስከ ዓመት ሣር የማይነጥፍበት መስክ ከቶ የት ነው? ገነት መኾን አለበት’ እያለች…
አመነችውና መሸጎሪያውን ነካ አድርጋ ከፈተችለት፡፡
ከታሰረበት ወጥመድ መውጣቱን ሲያረጋግጥ “በግ ሆይ ልበላሽ ነው ምንም ማድረግ አልችልም” ይላታል፡፡ “እንዴ አልበላሽም አላልክም እንዴት ቃልህን ታጥፋለህ?” ስትለው “ቃል መጠበቅ ለበጎች እንጂ ለተራበ አንበሳ አይደለም፡፡ ለመኾኑ አንበሳ ከመቼ ወዲህ ነው ሣር ሲግጥ ያየሽው?” ሲል መልሶ ይጠይቃታል፡፡ በግም ደንግጣ:- “ነውር ነው” አለች፣ በበግ አእምሮዋ ለማምለጥ እያሰበች፡፡አንበሳውም ‘በግ ካመረረ፣የጨዋ ልጅ ካመረረ’ እንደማይመለስ ስለገባው እንደ መርግ ጫንቃዋ ላይ ተጭኖ አላሰናዝር አላት፡፡
ወዲያው አንበሳ እንዲህ አለ:- “ይልቅ ሃሳብ አለኝ፡፡ አንቺን መብላቴ ቢርበኝ ነውና ወንጀል አይደለም፡፡ ቢኾንም በሦስት እንስሳ እናስመስክርና ‘ተሳስተሃል’ ካሉኝ እተውሻለሁ፤ ‘አንተ ልክ ነህ’ ካሉኝ እንግዲህ ምን ማድረግ ይቻላል?” ይላታል የሰብቅ ፈገግታው እንዳይታይበት እየታገለ፡፡ በግም ትስማማለች፡፡
ፍርድ አደላዳይ ሲያስሱ እባብን ያገኙታል…አንበሳ ጉሮሮውን ሞርዶ:-” እባብ ሆይ፣ ከዕለታት ባንዱ ቀን ከሞት የታደገኝን እንስሳ በራበኝ ጊዜ ብበላው ከኩነኔ ይቆጠርብኛል?” እባብም፡- “አንተ ምንም አላጠፋህም ኩነኔም የለብህም” ይለዋል. ወደ ጉድጓዱ ለመግባት እየቸኮለ፡፡.ጥቂት ምዕራፍ እንደተጓዙ በራባት ጊዜ የገዛ ዘሯን የማትምረዋን ንስርን ያገኙና ያንኑ ጥያቄ አንበሳ ያቀርባል፡፡ “ምንም ጥፋት የለብህም፤እኔም ቢርበኝ ያንኑ ነው የማደርገው(Nature allowed us to do so. Don’t hesitate)” አለች ለማምለጥ ክንፏን እንደመፈተሸ እያለች..
በመጨረሻ ኤሊን ያገኛሉ፡፡ ‘አጥብቆ ዝምታ ለበግም አልበጃት፤ዐሥራ ሁለት ኾና አንድ ነበር ፈጃት’ን ተርታ ‘እስታሁን ባለመናገሬ አይደለ ፍርዱ ለአንበሳው ማጋደሉ?’ ብላ ትንፋሽዋ እየተቆራረጠ) “ኤሊ ሆይ አንበሳን ከወጥመድ ያወጣሁት እኔ ነኝ፡፡ ከወጥመዱ ከመውጣቱ በፊት ግን እንደማይበላኝ የገባውን ቃል አጥፎ ረሃቤን ላስታግስብሺ እያለኝ ነው፡፡ ይህ መልካም ነውን?” ስትል በግ አቤቱታዋን አሰማች፡፡
ኤሊ የበጓን ዐይን ስታይ አዘነችላት፡፡ ለበግ ብታደላ የራበው አንበሳ እሷን እንደማይምር ገብቷታል፡፡ እናም አንድ ዘዴ ብልጭ አለላት፡፡ “በግ ሆይ ያልሽውን በጥሞና ሰምቻለሁ፡፡ፍርድ ለመስጠት ግን መጀመሪያ ሁሉም ነገር ከጀመረበት ስፍራ መነሣት ያስፈልጋል” ስትል አንበሳ ከአፏ ላይ ለቅሞ “መልካም ሀሳብ ነው” ብሎ ወደታሰረበት ስፍራ ሰተት ብሎ ሲገባ ኤሊ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፡- “በግ ዝጊበት (lock him up!)” ስትላት፣ በግ ፈጥና በሩን ከርችማ መሸጎሪውን ጠመዘዝችው፡፡
አንበሳ ግን ተስፋ አልቆረጠምና ምራቁን እየዋጠ፡- “በግዬ የኔ ፍቅር….በግዬ በግዬ… ነውውው…?ነው? ነው? እረ? ነው? አመረርሺ ማለት ነው? ብልህነትሽ ወዴት አለ?” በግ መለሰች፡- “ብልህነቴን ለኤሊ አውሻት ነበር እንድል ትጠብቅ ይኾናል…. ርግብነቴ እየተጫነኝ እንጂ እባብነትም እኮ አለኝ” አለችው፡፡ “ሁለት ጊዜ የምትነክሰኝ እኔ ምንድን ነኝ?”
የኛ ነገር እንደ በጓ ያለ ነው፡፡እየራበን ‘ጠግበሃል’ ስንባል የምናምን…ነፃ አውጪ እስኪመጣ ለመበላት የተዘጋጀን…ጠላትና ወዳጃችንን የማንለይ፣ ጠላት የነገረንን ልባችንን ከፍተን አህ ብለን የምንሰማ…
የኛ ነገር እንደ በጓ ያለ ነው፡፡ ሲኦል በኾነች ምድር እየኖርን በገነት እንደምንኖር ራሳችንን ያሳመንን..
የኛ ነገር እንደ በጓ ያለ ነው፡፡ ‘አድገሃል’ ስንባል አዎን ‘እውነት ነው’ የምንል፣ ‘በ2030 ከዓለም ኃያላን ሀገራት መካከል አንዷ እንኾናለን’ ስንባል፣ሥልጣን ማራዘሚያ መኾኑ ሮኬት ሳይንስ ኾኖብን የልቡና ዐይናችንን ጨፍነን ‘አሜን! የእግዚአብሐር ሰው የምንል’ …
ብስክሌት ወደፊት እንዲጓዝ ሁለቱ ፔዳል በእኩል መረገጥ ግድ እንደሚለው፣ ‘እንደ ርግብ የዋህ፣እንደ እባብ ብልህ ኹኑ’ ብንባልም የዋህነትን አጥብቅን ይዘን ፈቅ ማለት ከቶ እንዴት ያቻለናል?!
የኛ ነገር እንደ በጓ ያለ ነው፡፡ አንበሳ ወጥመድ በያዘው ቁጥር ‘እህ’ ላለው እንስሳ ሁሉ ተመሳሳይ ውዳሴ እንደሚያዘንብ መገመት የማንችል…
በሥልጣኑ አስፈራርቶ ውሽማ ያደረጋትን ሴት ለመዳራት የውሻው ጩኸት ያስቸገረው ሰውዬ፣ በተወደደ ሥጋ ለውሻው ክትፎ አሠርቶ መወርወሩን የወሬ አርእስተ ርእስ ወይም አጀንዳ የምናደርግ ፣…..እኛ በየ ሚዲያው ስለክትፎው ስንተነትን፣ እናታችንን ማነወሩ ትዝ የማይለን…የማያንገበግበን…ጥቃት የማይገባን…መብራት ጠፍቶ ከርሞ ሲመጣ ‘ለምን ጠፋ? ዓባይ መገደቡ አባይ ኖሯል?’ ብሎ ከመጠየቅ ‘ሆሆ’ ብለን የምንፈነጥዝ…ከቃል አባይ እውነተኛ ቃል ኪዳን የምንጠብቅ ተላሎች…
ነነ…ነነ…ነነ…ነነ…
ደላላው ወዳጄ ዘመኑ ከሌላ ሴት፣ ሴት ልጅ ወልዶ ‘ወይን ያስተፈሥህ ልበ ሰብ’ እንዲል የወይን ጠጅ ይዤ ‘እንኳን ደስ ያለህ’ ልለው ወደቤቱ ጎራ ብየ ነበር፡፡ የባጥ የቆጡን ስናነሣ ስንጥል ቆይተን ልወጣ ሳኮበኩብ “ምነው ማን እንዳልኳት ሳትጠይቀኝ?” አለኝ (ይህ አነጋገር ሰርቄ ስለወለድኳት ነው የሚል ስውር ቅሬታ ቋጥሯል)፡፡ “እረ ይቅር በለኝ… ለመኾኑ ማን አልካት?” ስለው ካፌ ላይ ነጥቆ ‘ኮሚሽን’ አለኝ፡፡ “እከከከከከ ኮሚሽን ዘመኑ?” ስለው “ኋላሳ!” አለ በይምሰል ፈገግታ ደምቆ፡፡
ምስኪኗ በግ በኤሊ ብልህነት ከአንበሳው መንጋጋ/ከሞት/ አመለጠች፡፡
ሙሉ ለሙሉ በግ ለኾነ ኤሊን ያዝለት ይኾናል፡፡ የበግ ለምድ የለበስን ተኩላ ኾነን ይኾን፣ መከራችን ለአፍታ ተግ የማይለው?’ እንደ ኩኮ ወፍ (cuckoo bird) በሌላው ትክሻ ለውጥን መናፈቅ! በሌላው ደም ምቾት መጋገር! በሌላው አጥንት ሕንፃ ማቆም! በሌላው ላብ እጅን ታጥቦ መቅረብ! በሌላው መጎስቆል ወዝ ለመጭለፍ መቋመጥ! ውቅያኖስ ለሚጠይቀው ለውጥ አንድ ኩባያ ውኃ ለማውጣት የምንሰንፍ ወይም የምንነፍግ!
ለውጥ እንፈልጋለን ግን ቀድሞ የሚጎሳቆልልን እንሻለን፡፡ሕይወት እንሻለን ግን ቀድሞ የሚሞትልን እንቀላውጣለን፡፡ መዳን እንፈልጋለን ግን የሚሰቀልልን ‘ዳግማዊ ክርስቶስ’ እንዲመጣ እንመኛለን፡፡ ሁሉም የራሱን ‘መስቀል’ ለመሸከም ይሰቀቃል፡፡ በ ‘እነክሽ እነካ ዘፈን ረሃብ አይጠፋም’ ነበር ያለው ወዲ ዜናዊ? ወዳጄ ልቤ ‘እየመጡ ነው’ በሚል ዘፈን ለውጥ አይመጣም፡፡
በሰው ትክሻ ተንጠልጥሎ ለመሻገር መቋመጥ ጊዜው ሳያልፍበት አይቀርም፡፡ በደንብ መጉረስ ካማረን፣ በደንብ ማረስ! አለያ “እንዲህ ሲጎርሱ፣ የማያርሱ?” የሚል ለመነኩሴ እንኳ በማይራራ ክፉ ዐይን ብንገረፍ መደነቅ የለብንም፡፡
ብቻ…የኛ ነገር ይገርመኛል…
በጃፓናዊው ደራሲና ገጣሚ ጦማሬን ልቋጭ፡- ” Individually we are one drop. Together, we are an ocean”- Ryunosuke Satoro.
ያሰንብተን!
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






