የአብይ አህመድ የብልፅግና አገዛዝ አስከፊነት ለሕወሓት የጥፋት ወጥመድ እጅ የመስጫ ምክንያት ይሆናልን?
(የአማራ ሕልውና ትግል እና የ«ጽምዶ» እውነተኛ ገጽታ)
የፖለቲካና ስትራቴጂያዊ ጥናት

በዶ/ር ሶስና ታደሰ
የትንተናው ዋና መንደርደሪያ (Executive Summary)
ከአማራ ሕዝብ ጥቅምና ሕልውና አኳያ፣ በፋኖ፣ በTDF (ሕወሓት) እና በOLA (ኦነግ ሸኔ) መካከል ሊደረግ የሚታሰብ ማንኛውም ዓይነት ጥምረት ጥልቅ መዋቅራዊና ሞራላዊ ውድቅነት ይገጥመዋል። የዚህ ዓይነት አጋርነት የአማራን ሕዝብ ደህንነትና ታሪካዊ ጥያቄዎች በጊዜያዊ ወታደራዊ ስሌት ለውጦ አሳልፎ የሚሰጥ «የሕልውና ቅራኔ» (Existential Contradiction) ነው የሚሉ በርካታ ምክንያቶች አሉ፦
- የሰማዕታት ደም ክህደትና ታሪካዊ ጠባሳ፦ ጥምረቱ በሕወሓት እና ኦነግ ሸኔ ኃይሎች በአማራ ንጹሐን ላይ ለተፈጸሙ የጅምላ ጨፍጨፋዎች (እንደ ወለጋ፣ ኮምቦልቻ፣ ማይካድራና ጭና ያሉ) ተጠያቂ ለሆኑ አካላት ያለምንም ፍትህ ያለ ዋጋ ይቅርታ መስጠት በመሆኑ፣ የትግሉን ሞራላዊ መሠረት ያፈርሰዋል።
- የርስትና ማንነት ጉዳይ (የወልቃይትና ራያ አጥር)፦ ሕወሓት ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ የትግራይ ግዛቶች ናቸው ብሎ በሚያምንበት፣ ፋኖ ደግሞ የአማራ ታሪካዊ ርስቶች ናቸው በሚልበት ሁኔታ ጥምረት መፍጠር፤ ወልቃይትና ራያን ለሕወሓት አሳልፎ መስጠትን ይጠይቃል—ይህ ደግሞ የሕልውና ትግሉን ዓላማ ሙሉ በሙሉ መካድ ነው።
- የተቃረነ የፖለቲካ ራእይ፦ የኦነግ ሸኔ አጀንዳ “የኦሮሚያ ሪፐብሊክን” መመሥረት፤ የሕወሓት የፖለቲካ ግብም “ታላቋ ትግራይ” ን እውን ማድረግ ሲሆን፣ የሁለቱም ኃይሎች ግብ በአማራ መቃብር፣ በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ እንዲሳካ የሚፈልጉት ነው፡፡ የፋኖ ዓላማ ደግሞ የአማራን ሕልውና በማስከበር የተረጋጋችና ፍትሐዊት ኢትዮጵያን መገንባት ነው። እነዚህ ሁለቱ ራእዮች ሙሉ በሙሉ የሚጋጩ ናቸው።
- የሕዝባዊ ቅቡልነት ማጣት፦ የአማራን ሕዝብ በብሔሩ ለይተው በቀጥታ ሲያጠቁ ከነበሩ ኃይሎች ጋር መሰለፍ ፋኖ የነበረውን ሕዝባዊና ሞራላዊ የበላይነት የሚያሳጣው ከመሆኑም በላይ፣ በየአካባቢው ባሉ የፋኖ ክንፎች መካከል ጥልቅ ክፍፍልን ይፈጥራል። አሁንም ፈጥሯል፡፡
- የስልታዊ መጠቀሚያነት አደጋ፦ ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ ፋኖን ማዕከላዊ መንግሥቱን ማዳከሚያ መሳሪያ አድርገው ከተጠቀሙበት በኋላ፣ ዓላማቸው ሲሳካ መልሰው የተበተነውን የአማራ ክልል እንደሚያጠቁት ግልጽ ነው።
የ«እባብ» እና የ«ጅብ» ምስላዊ ፍተሻ (Visual Truth Test)
«አንድ ሰው ከጀርባህ ስላለው ተናዳፊ እባብ ቢያስጠነቅቅህ፣ ከፊትህ ወዳለው ጅብ እየሳበህ ነው ማለት ነው? ሁለቱም ከፍተኛ ጉዳት ባደረሱ ሁለት ተላላፊና አዳኝ ኃይሎች መካከል ለምን የተሳሳተና (False dichotomy) የግዴታ ምርጫ እንድናደርግ ይፈለጋል? የዚህ አጀንዳ ባለቤት ማን ነው? ሕወሓት? ኤርትራ? ወይንስ ግብፅ?»
ክፍል 1፦ ታሪካዊ ሥርወ-መንስኤና የብልፅግና ውላጅነት
በፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አንድ ሕዝብና ሀገር ለደረሰበት አጠቃላይ ቀውስና የሕልውና አደጋ መፍትሔ ለማግኘት፣ የመከራውን ሥርወ-መንስኤ (Root Cause) በጥልቀት ማወቅና መተንተን ግዴታው ነው።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ፣ በተለይም በአማራ ሕዝብና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት፣ የርስት መነጠቅና ሀገር አልባ የማድረግ ዓላማ ያለው ጦርነት የተከፈተው፤ በድንገት ከአየር ላይ የወደቀ ወይም በቅርብ ጊዜ የተፈጠረ አይደለም። ይልቁንም ሕወሓት በደደቢት በረሃ ከፃፈው ማንፌስቶ ጀምሮ ድኀረ-1983 ሲተገብረው የነበረው የጥላቻ ፖለቲካ እና የፈጠረው ህገ-መንግስታዊ ስርአት ቀጥተኛ ፍሬ ነው።
የአማራ ሕዝብ በዘመናዊ ታሪኩ ከፋሽስት ጣሊያን በኋላ እንደ ሕወሓት አቅዶ የሰራበት ስርዓተ-ጠላት አላጋጠመውም። የአሁኑ ዘመን የኦሕዴድ ብልጽግና የጥፋት ምዕራፍ መሠረቱ የተጣለው በዘመነ ሕወሓት ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት አማራን የገጠሙት ጠላቶች ለመገንጠል ካርታ አስምረው፣ የሰው ልጅ ሕይወት በጅተው፤ ሕዝብ ጨርሰው “ሀገር እንሆናለን” ብለው የሚያልሙ ፋሽስቶች ናቸው፡፡ ይህ እውነታ የገባቸው ጥቂት የአማራ ልሂቃን፣ ይህ የሕልውና ትግል ውስብስብና ግንባረ-ብዙ መሆኑን በተደጋጋሚ ይናገራሉ፡፡
ባለፉት 6 ዓመታት ብቻ እንኳን እንደታዘብነው፣ አማራን ለማጥፋት ጦር የሰበቁ ጠላቶች በዓለም ፊት ራሳቸውን ሲገልጹ፦
- ሕወሓት፦ “የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን እንደሚታገል”፤
- ኦሕዴድ ብልጽግና፦ “የሕግ የበላይነትን ለማስከበር“ የሚያደርገው ትግል እንደሆነ አድርገው ይሰብካሉ።
በአንጻሩ አማራው ራሱን ከጥፋት ለመከላከል የሚያደርገውን በይዘቱ ልዩ የሆነውን ፍትሃዊ የሕልውና ትግል፣ ለዓለማቀፉ ማኀበረሰብ በአግባቡ ማስረዳት አልቻለም፡፡
የቀጠናው ጂኦ-ፖለቲካዊ ቁማር እና የ«ጽምዶ» እውነተኛ ገጽታ
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ በተቃርኖ የተሞሉ ኃይሎች “ጽምዶ” (Tsimdo) በሚል አወዛጋቢ ቀጣናዊ የኃይል አሰላለፍ ፈጥረዋል፡፡ ይህ የሕወሓት፣ ኤርትራ እና ሱዳን ኃይሎች ጥምረት ከአማራ ሕዝብ መሠረታዊ የትግል ዓላማ እና መዳረሻ ግብ አኳያ አንድም የጋራ ፍላጎት የሌለው፣ ይልቁንም በዘላቂ የአማራ ጥቅሞች ላይ በተቃርኖ የሚቆሙ ኃይሎች የሞሉበት ስብስብ ነው፡፡
«ጽምዶ» የአማራ ሕዝብ የፖለቲካ ጥያቄም ሆነ የፋኖ የትግል ግብ አይደለም፤ ከቃሉ መጠሪያ ጀምሮ በስያሜም ሆነ በገቢር የአማራ የሆነ አንዳችም ነገር የለውም። ይህ አጀንዳ የራሱ የሆነ ጂኦ-ፖለቲካዊ መነሻና መድረሻ ያለው የፖለቲካ ገበያ ሸፍጥ የፈጠረው የቀጠናዊ ቁማር አካል ነው። ለዚህም ነው ሦስቱ አካላት ጥምረቱን ለራሳቸው ጥቅም ብቻ የሚፈልጉት፦
የቀጠናው አካላት ስትራቴጂያዊ ድብቅ ፍላጎት (Strategic Interest)፦
- ጽምዶ – ለኤርትራ መንግሥት፦ በኦሕዴድ መራሹ ብልፅግና ላይ የተፈጸመበትን ክህደት ለመበቀል ሲል ጦርነቱን ቢፈልገውም፣ ጦርነቱ ወደ ግዛቱ እንዳይመጣበት የጦርነት ሜዳውን ወደ ኢትዮጵያ የሚገፋበት (Strategic Depth) ስልታዊ መሳሪያው ነው።
- ጽምዶ – ለሱዳን ወታደራዊ መንግሥት፦ ኦሕዴድ/ብልፅግና በሱዳን የውክልና ጦርነት እጁን ማስገባቱን ተከትሎ፣ ተፋላሚ ኃይሉን (RSF) ለማጥፋት የኢትዮጵያን ክፍል ለማጥቃት፣ ብሎም በአማራ በኩል ያለውን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መሬት (አልፋሽጋ) ጠቅልሎ ለመውሰድ ያቀደው ነው።
- ጽምዶ – ለሕወሓት፦ የእነዚህን ከላይ የተጠቀሱ ሁለት ሀገራት አቅሞች በመጠቀም፣ የአማራ ታሪካዊ ርስቶችን እነ ወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያን በመጠቅለል የሁመራ ኮሪደርን ለመያዝ እና የዘመናት ቅዥቱ የሆነውን “ታላቋ ትግራይ”ን እውን ለማድረግ የተጠቀመበት ነው።
“ጥቅምን በሚስጥር መያዝ” በሚል የማደንዘዣ ቃል፣ የአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል፣ ከመሠረታዊ እና ዘላቂ ጥቅሞቹ በተቃርኖ ከተሰለፉ ኃይሎች ጋር በትብብር ስም በመሰለፍ የአማራን ሕዝብ ደምና መስዋዕትነት በግልጽ ለሽያጭ ያቀረበ አደገኛ ስሌት በአደባባይ እየተነገረ ነው።
ፋኖን በሱዳን ጦርነት ልክ እንደ “አርሚ 70” (አርሚ 70 ማለት የቀድሞው ሳምሪ ወይም በማይካድራ ላይ ጭፍጨፋ የፈጸመው ገዳይ ቡድን ማለት ነው) በቅጥረኛነት የማሰለፍ ድብቅ ዕቅድ በትብብር ስም ቀርቧል፡፡ በቀጣይም እነዚህ ሦስት ቡድኖች የፋኖን የወል ስም በመጠቅለል፣ ያለምንም ሕጋዊ ውክልና ‘የወታደራዊ ስምምነት’ በሚል አደገኛ የቁማር ጥምረት የመጫወቻ ካርድ ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ሞጋች ጥያቄ 1፦ ታሪካዊ ወንጀልንና የሕዝብ ደምን የመሸጥ አጣብቂኝ
«የ«ጽምዶ» አራጋቢዎች፤ ሕወሓት ላለፉት 40 ዓመታት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶና በአማራ ሕዝብ ላይ ለፈጸመው የዘር ማጥፋት፣ ላለፉት 27 ዓመታት የዘረጋው ስርአታዊ ማግለል፣ የማዕከላዊ እስር ቤት ሰቆቃ፣ የወልቃይት/ ጠለምትና የራያ አፓርታይድ ጭቆናና የርስት ወረራ፣ የሰሜን እዝን በመምታት በአማራ ሕዝብ ላይ በከፈተው ጦርነት ያደረሰው አሰቃቂ ውድመት፣ አንድም ይፋዊ ይቅርታ ሳይጠይቅና ላደረሰው ወንጀል ፍትሕ ሳይቀበል፣ ዛሬ አብይ አህመድን ስለተቃወመ ብቻ ከሕወሓት ጋር በጥምረት ስም መሻረክ—በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ሰማዕታትን ደም አሳልፎ ለፖለቲካ ቁማር መሸጥ ነው ወይስ አይደለም?
መልሳችሁ ‘አዎ’ ከሆነ ትግሉንም የአማራን ሕዝብም ከድታችኋል፤ ‘አይደለም’ ካላችሁ ደግሞ ሕወሓት የፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል አጥባችሁ ለፍትሕ እንዳይቀርብ ነጻ እያወጣችሁት እንደሆነ ለሕዝቡ አደባባይ ላይ አረጋግጡ!?»
- የደደቢት ማንፌስቶ፦ የአማራና የኦርቶዶክስ አከርካሪን የመስበር ስትራቴጂ
ሕወሓት ገና በደደቢት በረሃ ትግል ሲጀምር ባወጣው ማንፌስቶ ላይ አማራን የትግራይ ሕዝብ ዋና ታሪካዊ ጠላት አድርጎ ፈርጇል። ኢትዮጵያዊነትን እና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ደግሞ የትምክህትና የጨቆና ተቋማት አድርጎ በመፈረጅ፣ “አከርካሪውን እንሰብራለን” በሚል የጥላቻ ርዕዮተ-ዓለም ተነሥቷል። ይህ ማንፌስቶ ላለፉት 40 ዓመታት በስርዓት ሲተገበር የነበረ ከሕወሓት ወደ ኦሕዴድ/ብልፅግና የተላለፈ የፖለቲካ ፕሮግራም ነው። ሕወሓት ራሱ በ1968 ዓ.ም. በማንፌስቶ ያስቀመጠውን ፀረ አማራነት በሀገር ሕገ-መንግሥት ደረጃ በማስቀጠል፣ ፀረ አማራነት ሀገራዊ ቅርፅ አስይዟል፡፡
- በወልቃይትና ራያ የተፈጸመው የአፓርታይድ ስርዓት
ሕወሓት በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ በወልቃይትን፣ ጠገዴ፣ ጠለምት በኃይል ወረራ ሲፈጽም፣ የተገበረው የለየለት የአፓርታይድና የዘር ማጥፋት ስርዓት ነው። የአማራ ግዛቶችን ወደ ትግራይ ከጠቀለለ በኋላ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆችን በጅምላ በመጨፍጨፍና በማፈናቀል፣ በቦታቸው ከትግራይ በመጡ ሰፋሪዎች የመተካት የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጽዳት ወንጀል ፈጽሟል። የአማራ ሕዝብ አማርኛ የመናገር፣ የባህልና የማንነት መብቱን በመንጠቅ ከአካላዊ ዘር ማጥፋት እስከ ባህል ማጥፋት (Cultural genocide) ድረስ ፈጽሟል፡፡
በሕወሓት ፋሽስታዊ ጭካኔ ለአርባ ዓመታት በጅምላ የተጨፈጨፉ ወገኖቻችንን አፅም ዛሬም ድረስ ለቅመን በክብር አላሳረፍንም፡፡ ያረፈብን የታሪክ ጠባሳ ገና አልሻረም፤ አሁንም የወገኖቻችን ትኩስ ደም እየፈሰሰ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ከሕወሓት ጋር ”ጽምዶ” በሚል መጠመድ ታሪካዊ ክህደት ነው፡፡
- የማዕከላዊ እስር ቤት ዘግናኝ ወንጀሎች
ሕወሓት በ27 ዓመታት የግፍ አገዛዙ፣ ሀገሪቱን በጥቁር ሽብርና በሰቆቃ ምድርነት ቀይሯት ነበር። በስሙ «ማዕከላዊ» ተብሎ በሚጠራውና በሌሎች ምስጢራዊ እስር ቤቶች ውስጥ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን፣ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ እና ሞጋች ጋዜጠኞችን፣ የአማራና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምሁራንንና አባቶችን በማሰር ወንድ ሴት ሳይመርጥ የእጅና የእግር ጥፍር በመንቀል፣ በጨለማ ክፍል ውስጥ ለአመታት ዘግቶ ማስቀመጥ እና ሰብአዊ ክብርን የሚያዋርዱ ማሰቃያዎችን መተግበር የሕወሓት መለያዎች ነበሩ።
- ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ፦ አማራን ሀገር አልባ የማድረግ የጥፋት መረብ
ሕወሓት በ1987 ዓ.ም የዘረጋው ህገ-መንግስት፣ ኢትዮጵያዊነትን በማፍረስ በዘርና በብሔር ላይ የተመሰረተ የታሪክ ጥፋት ነው። ከሁሉ በላይ ይህ ህገ-መንግስት አማራውን በገዛ ሀገሩ “መጤ”፣ “ነፍጠኛ” እና “ጨቋኝ” አድርጎ በመፈረጅ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለተፈጸሙትና ዛሬም ለሚፈጸሙት የጅምላ ጭፍጨፋዎችና መፈናቀሎች ህጋዊና ፖለቲካዊ ሽፋን የሰጠ ሰነድ ነው። ዛሬ የአማራ ሕዝብ ህልውናውን እንዳይጠፋ፣ ማንነቱን አስከብሮ የሀገር ባለቤትነቱን ለማስመለስ በመታገል ላይ ያለው፣ በሕወሓት ተተክሎ በኦሕዴድ የጥፋት ዕድገቱ የጨመረውን ጸረ-አማራ መርዛማ የሥርዓቱን ፍሬ ለማምከን ነው፡፡
- ሞጋቹ እውነታ፦ የአብይ አህመድ አገዛዝ የሕወሓት/የስብሃት ነጋ የዘር ውላጅ ነው!
አሁን ላይ ያለው የኦሕዴድ ብልፅግና/የአብይ አህመድ አገዛዝ ከባዶ አየር የመጣ ወይም አዲስ አገዛዝ አይደለም፤ ይልቁንም ሕወሓት ያረገዘው፣ ያሳደገውና የወለደው ቀጥተኛ የዘር ውላጅ ነው። አብይ አህመድና የኦሕዴድ ብልፅግና አመራሮች ሙሉ በሙሉ በሕወሓት የደህንነት፣ የጦርነትና የፖለቲካ ትምህርት ቤት (ኢህአዴግ) ውስጥ ሰልጥነው ያደጉ ናቸው። ሕወሓት በህገ-መንግስቱ ያስቀመጠውን “የአማራና የኦርቶዶክስ አከርካሪ የመስበር” አጀንዳ፣ አብይ አህመድ በድሮን ጥቃት፣ በታጠቁ ኃይሎች የጅምላ ጭፍጨፋ እና ስልታዊ ጥቃቱን ከገዳማት እስከ ሲኖዶሱ ድረስ hard እና soft power በመጠቀም በፍጥነት እያስፈጸመው ይገኛል።
ክፍል 2፦ የ«ጽምዶ» ወጥመድ እና ስትራቴጂያዊ መውጫ መንገድ
በማንኛውም ሀገርና የማኀበረሰብ ቡድኖች ውስጥ በሚካሄዱ የሕልውናና የፖለቲካ ትግሎች፣ የጋራ ጠላትን ለመመከት በሚል ስም የሚደረጉ ጥምረቶች የሚመሩት በጋራ መከባበር፣ በግልጽ ስትራቴጂያዊ ጥቅም እና በእኩልነት ላይ ተመሥርቶ ነው። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በሕወሓት እና በአፋብን (AFNM) ጥቂት አመራሮች መካከል እየተራገበ ያለው «ጽምዶ» በአማራ ሕዝብ ላይ የተቃጣ ስውር ሴራ እና ለአጠቃላዩ የአማራ ፋኖ ሰራዊት የተዘጋጀ ‘የባርነት ካምፕ’ ነው!
ሕወሓት ከ27 ዓመታት አምባገነናዊ አገዛዝ በኋላ እንኳ ለራሱ ለትግራይ ሕዝብ ያተረፈለት ስደት፣ ያልተቋረጠ ጦርነት እና በሌሎች ወንድም ሕዝቦች ዘንድ መጠላትን ብቻ ነው። ታዲያ የሕዝባዊ፣ የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ መሠረቱን ሙሉ በሙሉ ካጣ የከሰረ መርዛማ ብራንድ ቡድን ጋር እንዴት ጥምረት ይታሰባል?
ሞጋች ጥያቄ 2፦ የተሳሳተው ምርጫ (False Dilemma) እና የባርነት ካምፕ
««የሕወሓትን ወጥመድ ከተቃወማችሁ የአብይ አህመድ ደጋፊዎች ናችሁ» የሚለው የከሰረ ትረካችሁ የሚያሳየው የፖለቲካ ድርቀታችሁን ነው። ለመሆኑ የአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል በራሱ እግርና መርህ ቆሞ ሁለቱንም የዘር ማጥፋት አበጋዞች (ሕወሓትንና ብልፅግናን) እኩል መታገል አይችልም ብላችሁ ታምናላችሁ?
ወይስ የአማራ ሕዝብ ነፃነት የሚረጋገጠው ሁልጊዜ በአንዱ በዳይ ጫማ ስር ወድቆ ዳግማዊ ኢሕዴን በመሆን ብቻ ነው ብላችሁ ነው የምታስቡት?»
1. የሕወሓት ያልተለወጠው የበላይነት አቋም እና የአመራሮቹ የትርክት ውድቀት
ሕወሓት በየመድረኩ የአማራን የሕልውና ጥያቄ በግልጽ እያጣጣለ ነው፡፡ ዛሬም ለአማራ ሕዝብ የትግል መነሻ የሆኑ የወሰንና ማንነት ጉዳዮችን በሚጨፈልቅ ፍላጎት ላይ ተቸክሏል፦
- የሕወሓት ቃል አቀባይ የአቶ ሚካኤል ይፋዊ ንግግር፦ በአደባባይ ወጥቶ፦ “እኛ እንደ ብልፅግና በሌላ ኃይል አንተማመንም፤ ‘በዚህ ግባ፣ በዚህ ውጣ’ ብለን የምንጋብዘውና የምንጠራው ኃይል የለም! በራሳቸው ፍላጎት ከመጡ የራሳቸው ጉዳይ ነው” በማለት ፋኖን እንደ አቻ ኃይል ሳይሆን “ተገዢና ተላላኪ” አድርጎ እንደሚመለከተው አረጋግጧል።
- የፈትለወርቅ (ሞንጆሪኖ) የጦርነት መፈክር፦ የሕወሓት ከፍተኛ አመራር ፈትለወርቅ (ሞንጆሪኖ) በመድረክ ላይ ወጥታ፦ “ሕልውናችን በጠላቶቻችን መቃብር ላይ ይረጋገጣል!” እና “የሰማዕታት አደራ የሆነው መሬት — ወልቃይትና ራያ — አንዲት ስንዝር እንኳ አትቆረስም!” እያለች በየመድረኩ መፈክር ስታሰማ ታይቷል።
ሞጋች ጥያቄ 3፦ የተንበርካኪነትና የክህደት ፍተሻ
«የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል ‘ማንንም አልጠራንም፣ በራሳቸው ፍላጎት ከመጡ የራሳቸው ጉዳይ ነው’ ብሎ አናቁቷችሁ እያለ፤ የሕወሓት አመራሯ ሞንጆሪኖ ደግሞ ‘ወልቃይትና ራያ አትቆረስም፣ ሕልውናችን በጠላቶቻችን መቃብር ላይ ይረጋገጣል’ እያለች በየመድረኩ እየፎከረች፦
ጥቂት የአፋብን (AFNM) አመራሮች የሕወሓት ጥገኞችና ተንበርካኪዎች ከመሆናችሁ ውጭ፣ ይሄን ያፈጠጠ ውርደት ለሕዝቡ ‘ስትራቴጂያዊ አጋርነት ነው’ ብላችሁ ለማስረዳት የምትጠቀሙበት የሞራል ልዕልና ከየት ልታመጡ ነው?»
2. ፋኖ የሕዝብ ልጅ እንጂ የጥቂቶች የግል ንብረት አይደለም!
በአፋብን ውስጥ ባሉ ሰብሳቢውን ጨምሮ እጅግ ጥቂት ግለሰቦች የሚመራው የ«ጽምዶ» ቅዠት መገንዘብ ያቀተው ዋናው እውነታ፦ ፋኖ የጥቂት አመራሮች የግል ንብረት ሳይሆን፣ ሕዝባዊ መሠረት ያለው የአማራ ሕዝብ ልጅና የነፃነት ታጋይ መሆኑን ነው!
የአማራ ሕዝብ ልጆቹን ያስለፈውና ደሙን ያፈሰሰው በየጊዜው ለሚለዋወጡ የፖለቲካ ቁማርተኞች መጫወቻ እንዲሆን ወይም ዳግማዊ ኢሕዴን ተፈጥሮ ወደ ሕወሓት የባርነት ካምፕ እንዲነዳ አይደለም።
ጥቂት የፋኖ አመራሮች የወጡለትን ሕዝባዊ አደራ ረስተው ለመንበርከክ ቢጣደፉም፣ መሬት ያለው እውነተኛው ፋኖ እና መላው ሕዝብ ይህንን የቅዠት ጥምረት ውድቅ ማድረጋቸው የትግሉን ሕዝባዊነት ያረጋግጣል። ምክንያቱም የአማራ ፋኖ ትግል የጀመረውን በሕዝባዊ ጥያቄ መሠረት እንጂ በጥቂት የጥቅም ቡድን ፍላጎቶች አይደለም፤ የአማራ ፋኖ የጥቂት አመራሮች የግል ንብረት አይደለም፤ ምክንያታዊና ሕዝባዊ መሠረት ያለው የአማራ ሕዝብ ልጅና የነፃነት ታጋይ ነው!
ሞጋች ጥያቄ 4፦ የመሬት ላይ እውነታ እና የ«ሚስጥር ኪስ» ቁማር
«መሬት ላይ ያለው እውነተኛው ፋኖ (እንደ ጎንደር ፋኖ ያሉት መዋቅሮች) የ«ጽምዶ»ን ሴራ በፅናት ውድቅ አድርገውት እያለ፤ የሕዝቡ የደም ዋጋ የሆነው የወልቃይት፣ የራያ የርስት ጉዳይ፣ የደብረብርሃን ተፈናቃዮችና የወለጋ አማራዎች ጭፍጨፋ የፍትሕ ጥያቄ ‘በሚስጥር ኪስ’ የሚያዝ ሸቀጥ ሊሆን አይችልም እያሉ ባለበት ሁኔታ፦
ጥቂት የ«ጽምዶ» የደም ነጋዴዎች የሕዝቡን አደራ ሽጣችሁ የሕወሓት መጠቀሚያ ከመሆን ውጭ፣ መሬት ላይ ያለው ፋኖና ሕዝቡ ከጎናችሁ አለ ለማለት የምታቀርቡት አንድም መሬት ጠብ የሚል እውነት የላችሁም?! ካላችሁ እስኪ አሳዩን?»
ክፍል 3፦ የትግሉ ስትራቴጂያዊ መውጫ መንገድ (The Strategic Way Forward)
የአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል ከነባሩና ከአሁኑ ስርዓት የጥፋት አዙሪት ወጥቶ አሸናፊ ይሆን ዘንድ የሚከተሉትን 4 መሠረታዊ ስትራቴጂያዊ እርምጃዎች መውሰድ ይኖራበታል፦
- የ«ድርብ መከላከል» (Double Defense) ስትራቴጂን መተግበር፦
የአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል በአንድ ጊዜ በሁለት ተቃራኒ ግን እኩል አደገኛ በሆኑ ኃይሎች መሃል የተካሄደ «ባለ ሁለት ግንባር ፍልሚያ» (Two-Front Battle) ነው። በአንድ በኩል የአሁኑ የብልፅግና አገዛዝ በመንግሥታዊ መዋቅርና በኃይል ሰፊ የዘር ማጥፋትና ጥቃት እያደረሰ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሕወሓትና የቀጠናው ስትራቴጂያዊ አጋሮቹ («ጽምዶ») ትግሉን የመጠለፍ፣ ታሪካዊ ርስቶችን የመንጠቅና የአማራን የትግል አቅም ለራሳቸው ቀጣናዊ ቁማር የመጠቀሚያ መሳሪያ የማድረግ ድብቅ አጀንዳ አላቸው። ስለሆነም ስትራቴጂያዊው የመውጫ መንገድ—በአንዱ ጠላት ቀጥተኛ ጥቃት ምክንያት ለሌላኛው አድፍጦ ለሚጠብቅ ኃይል ጀርባን አሳልፎ አለመስጠት፣ በታክቲክ ደረጃ ከሁለቱም ወገን የሚመጡ ስጋቶችን በንቃት እየተቆጣጠሩ በስትራቴጂ ደረጃ ደግሞ ዘላቂ ጥቅምን፣ ማንነትና ርስት የማስከበር ዓላማን ሳይቀይሩ በራስ መርህ ላይ ጸንቶ ሁለቱንም አደጋዎች እኩል የመመከት «የድርብ መከላከል» መስመር መያዝ ነው።
- የፖለቲካና የወታደራዊ ነፃነትን በራስ አቅም ማረጋገጥ፦
ትግሉ የማንኛውም ሌላ ኃይል መጠቀሚያ ወይም የቀጠናው ቁማር የኪሳራ ከላላ (Buffer) ከመሆን ሙሉ በሙሉ ነፃ መውጣት አለበት። የትግሉ የጀርባ አጥንት በፅኑ ማማ ላይ መገንባት ያለበት በአማራ መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ ባጠነጠነ በራሱ በሕዝቡ መሪነትና መስዋዕትነት፣ በራሱ ድርጅታዊ ጥንካሬ፣ በራሱ የትግል ግብና ራእይ ላይ ብቻ ነው።
- የመሬት ላይ እውነተኛና መርህ-ተኮር አንድነትን መፍጠር፦
የአማራ ሕዝብ ባለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን የደረሰበትን መከራ የተረዱ፣ ይህን መዋቅራዊ የጥቃት መሠረት ከጥፋት ጥንስሱ (ሕወሓት) እስከ ውርስ አስቀጣዩ (ኦሕዴድ) ድረስ ያሉ ጠላቶችን ጠንቅቀው የተረዱ እውነተኛ የአማራ ፋኖዎች መሬት ላይ ያሉ የሕዝብ መዋቅሮች የ«ጽምዶ»ን ወጥመድ ውድቅ ማድረጋቸው እንደ ትልቅ ጥንካሬ የሚወሰድ ሲሆን፤ የውስጥ አንድነትን በመርህ ላይ ተመሥርቶ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ባለፈው ሐምሌ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. የጎንደር ፋኖዎች ያወጡት የአቋም መግለጫ እውነተኛ የአማራ የሕልውና ትግል መንፈስ የተንጸባረቀበት ነው፤ ይህ መንፈስ በሁሉም ቀጠና መታየት አለበት፡፡
- የማይደራደሩበት መርህ-ተኮር ዲፕሎማሲን መከተል፦
ከማንኛውም ቀጣናዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ ኃይል ጋር የሚደረግ ንግግርና ግንኙነት የሚቻለው፣ የሕዝቡ የሕልውና፣ የርስትና የፍትሕ ጥያቄዎች በይፋ፣ በቅድመ-ሁኔታና ያለምንም መሽኮርመም ሙሉ በሙሉ ሲቀበሉ ብቻ መሆን አለበት።
እንደመውጫ፦ ሞጋች ጥያቄ 5፦ (የጎንደር ፋኖን ተጋድሎና እውነታ የሚያሳይ)
«የ«ጽምዶ» አራጋቢዎች፤ የጎንደር ፋኖና መሬት ላይ ያለው እውነተኛው ሰራዊት ዛሬም በየግንባሩ ከአገዛዙ ሰራዊት ጋር ደሙን እያፈሰሰ፣ ሕይወቱን እየገበረና ውድ መስዋዕትነት እየከፈለ ይገኛል!
መሬት ላይ ያለው እውነታ ይህ ሆኖ እያለ፦
- በየቀኑ ከብልፅግና ጦር ጋር ሀይለኛ ተኩስ ውስጥ ያለን የሕዝብ አርበኛ፣ ‘ከሌላኛው ጸረ-አማራና ጸረ-ኢትዮጵያ ኃይል (ከሕወሓት) ጋር አልሰለፍም’ ስላለ ብቻ ‘የብልፅግና ደጋፊ’ ብሎ መፈረጅ—የራሳችሁን የፖለቲካ ውድቀትና ተንበርካኪነት ለመሸፈን የምታደርጉት የከሰረ የፕሮፖጋንዳ ሸፍጥ አይደለምን?
- ለመሆኑ በግንባር ከአገዛዙ ሰራዊት ጋር የሚዋጋው የጎንደር ፋኖ ‘የአብይ ደጋፊ’ ከተባለ፤ በአዲስ አበባ ምቾት ውስጥ ሆኖ የሕወሓትን ወንጀል የሚያጥበውና የሕዝቡን የደም ዋጋ ‘በሚስጥር ኪሱ’ ይዞ የሚነግደው ጥቂቱ ቡድን ደግሞ የማን ቅጥረኛና ተልእኮ አስፈጻሚ ሊባል ነው?”
ማጠቃለያ
የአብይ አህመድ የብልፅግና አገዛዝ አስከፊነት ለሕወሓት የጥፋት ወጥመድ እጅ የመስጫ ምክንያት ሊሆን አይችልም። ከአማራ ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም አኳያ ሕወሓት በአደባባይ አጋርነቱን ሳይሆን ጠላትነቱን ነው ዛሬም እያሳየ ያለው፡፡ በአማራ ጉዳይ ነባር አቋሙን ሳይቀይር፣ የፍረጃ ስም እየለዋወጠ የጠላቶቹን መቃብር እየተመኘ በሚፎክርበት አደባባይ፤ በትብብር ስም የትግሉን አደራ ለሕወሓት አሳልፈው ለመስጠት የሚሮጡ ጥቂት አመራሮች የሕዝቡን መስዋዕትነት በግልጽ የካዱ ናቸው!
የሕወሓትን ወንጀል ማጠብ እና የፍርሃት ጦርነት በፕሮፖጋንዳ መልቀቅ የአማራ ሕዝብን ልዕልና መናቅ ነው፡፡ የአፋብን ሰብሳቢ ዘመነ ካሴ፣ በአንድ ንግግሩ አማራውን ብቻውን ለማቆም ሩጫ አለ፣ ካልተባበርን “ግብግቡ በሚያስነሳው ማዕበል ውስጥ ይሰጥማል” የሚል የሕልውና ስነ-ልቦናዊ ፍርሃት ለመፍጠር ያለመ የፕሮፖጋንዳ ንግግር መናገሩ ይታወሳል፡፡
ይህ ንግግር ፈጽሞ የተለጣፊነት ባህሪ መለያ ከመሆኑ ባሻገር የሕወሓትን የጥፋት ታሪክና የአሁኑን ወታደራዊ ዝግጅት በይፋ “የማጠብ” ስልታዊ ማለማመጃ ወንጀል ነው።
ሕወሓት ወልቃይትና ራያ ላይ የደቀነውን ወታደራዊ ወረራና የቀጠና ፍላጎት ሆን ብሎ በቃላት በመሸፈን፣ ጠላትን አብይ አህመድ ላይ ብቻ ለመገደብ የሚደረገው የፕሮፖጋንዳ ሸፍጥ፣ የአማራ ሕዝብን የአስተሳሰብ ልህቀት እንደ ሕዝብ የመናቅ ሥርየት የለሽ ወንጀል ነው፡፡
“ብቻችንን ከቆምን እንሰጥማለን” የሚል ስነ-ልቦናዊ የፍርሃት ጦርነት በፋኖው ውስጥ በመልቀቅ፣ ከዘር አጥፊዎቹ ከሕወሓትና ከኦነግ ጋር መሻረክን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ማቅረብ ዳግማዊ ኢሕዴንን የማዋለድ የታሪክ ክህደትና የተንበርካኪነት መንገድ ነው፡፡
የአማራ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት እየታገለው ያለው ለፍትሕ፣ ለሕልውናው መረጋገጥ፣ ለታሪካዊ ርስቶቹ መከበር፣ ለሰብአዊ መብቱ መከበር እና የሀገር ባለቤትነቱን በዘላቂነት በማጽናት እኩልነትን ለማረጋገጥ እንጂ የሌሎች ገንጣይ እና አስገንጣይ ቀጣናዊና ውስጣዊ ኃይሎችን የትርክት ፍጆታ ለማስፈጸም አይደለም።
በጥቅሉ የአማራ ሕዝብ አሸናፊ የሚሆነው አንዱን በዳይ በሌላው በዳይ ለመተካት ሲሮጥ ሳይሆን፤ በራሱ የእውነትና የፍትሕ ጥያቄ፣ በራሱ የአማራዊ መርህ እና በራሱ የተስተካከለ ድርጅታዊ ጥንካሬ ላይ ጸንቶ ሲቆም ብቻ ነው!!
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena







well, as any person has or may have his or her own perspective with regard to our political culture of very background, complicated and sadly enough deadly in this 21st century , the article is understandable.
It is quite right to any person who is well informed about political groupings like the ones mentioned in the article that it was because of their terrible political agenda and policies that contributed a lot to the the most dangerous political situation we’re facing.
But this desperately needs a very careful and extremely challenging way of doing things in order to change what terribly went wrong to what is right.
When we talk about the making of cooperation and coordination among political groups who have very different backgrounds and objectives before , the question must be how much or to what degree they have changed their political thoughts and practices , and how they are serious about it .
As far as our political culture and actions are concerned, it is much better to break the very ugly political thinking of never coming closer to each other again . The most important thing is the question of on what base/ condition the idea of cooperation and coordination should be built ? How those parties of cooperation and coordination are honestly and realistically serious about it?
I strongly believe that it is the right thing to critically assess the situation and advice those groupings to do things in the right way that will make what people want to see and how they want to live in peace and productive political system a reality.
I am sorry to say but I have to say that making a very generalized and absolutely negative assertions and conclusions is not helpful at all ! It is not helpful to the people whom we are concerned about! The very ideas never room for consultation , discussion , cooperation is not the right way to deal with our age-old and extremely messed up political culture and practice!
Let’s thing big and wide , but seriously and productively!!!
I don’t agree with her thesis. First, Fano is entering into a loose cooperation with other entities against the regime. Once the regime is removed, Fano will be in a much stronger position to emerge as a formidable force. It would have greater political legitimacy than TPLF, which continues to be viewed negatively by many Ethiopians, and OLA, which has less political capital than most other political actors in the country.
She focuses on the intentions of OLA, TPLF, and Eritrea. However, the issue is not that these entities pursue their own interests—we already know they do. The more urgent concern is that the Abiy regime is inflicting far greater damage than these groups could realistically cause in the future. In my view, the destruction caused by the current regime in just eight years exceeds what TPLF did during its 27 years in power by many times over.
The regime is dismantling Ethiopia at an extraordinary pace. The country is moving toward fragmentation with such speed and determination that, if this continues, Ethiopia itself could cease to exist within a year or two. From that perspective, the Wolqait and Raya disputes are of secondary importance. My greater concern is that the Amhara people could be systematically weakened and destroyed if the current regime remains in power much longer.
There are also significant strategic advantages to cooperation. It forces the regime to divide its military and political attention across multiple fronts, reducing its ability to concentrate exclusively on Amhara areas and giving Fano valuable breathing space.
As long as Fano maintains its unity, I believe it can deal with any other political or military actor. In my view, there is no greater threat to the Amhara people—or to Ethiopia as a whole—than the Abiy regime. The mass killings, daily bombings, and artillery shelling of villages have caused immense destruction. I believe the scale and pace of the damage under Abiy’s eight years in power surpass that of previous adversaries, including Fascist Italy and TPLF.
• በመሠረቱ እንኳንስ እንደ የአገራችን አይነት በዋናነት በመንበረ ሥልጣን ላይ በሚፈራረቁ እኩያን ገዥ ቡድኖች ምክንያት ረጅምና አስከፊ በሆነ ቀውስ ውስጥ የሚገኝን የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ሌላ ንዑስ የጋራ ጉዳይን በተመለከተም አንድ አይነት እይታ/አስተሳሰብ/አመለካከት ይኖራል ብሎ መጠበቅ የገሃዱ ዓለም እውነታ አይደለም። ከላይ የቀረበው ጽሑም ከዚህ እውነታ አንፃር ነው መታየት ያለበት እንጅ እንዴት እንዲህ ይሆናል በሚያሰኝ አግራሞት አይደለም ።
• በፅሁፉ ውስጥ የተገለፁትና የጋራ አገርን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከማድረግ ይልቅ በተሳሳተና አደገኛ በሆነ የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ አመለካከትና አካሄድ ያራምዱ የነበሩ ወገኖች/ቡድኖች ( OlA and TPLF) አሁን ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ ገምግመውና ተረድተው ከተገቢው ገንቢ የእርምት አቋም ጋር ወደ ሃቀኛና ዘላቂ ፍኖተ የጋራ መፍትሄ እንዲመጡ ገንቢና ቀጥተኛ ሃሳብ የመስጠቱ ጉዳይ አጠያያቂ አይደለምና ባለፈው ከተፈፀመ ስህተት ላይ ተቸክሎ በእኔ/በእኛ ቅድመ ሁኔታ ብቻ ካልሆነ ከእገሌ ወይም ከነ እገሌ ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ ቢሆንም አልነጋገርምና ከስህተት የታረመ ትብብር አላደርግም ማለት ፈፅሞ ትክክለኛ የፖለቲካ እሳቤ አይደለም።
• ከ3+ ዓመታት ወዲህ ደግሞ እኩያን ገዥ ቡድኖች በመንበረ ሥልጣን ላይ ለመቆየትና ያሻቸውን ለማድረግ ይመቻቸው ዘንድ የአማራን ህዝብ የጥላቻና የጥቃት ዒላማ የማድረጋቸውን አስከፊና አደገኛ ፖለቲካ እንዲያቆሙና ለሁሉም ዜጎቿ ምቹ የምትሆን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንፍጠር የሚለውን መሠረታዊና የተቀደሰ ጥሪ አንቀበልም ከማለት አልፈው ጦርነት በማወጃቸው ምክንያት ህልውናን ከማስጠበቅ ተነስቶ በጋራ ጥረት ለምትመሠረት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን መሆን እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ በማካሄድ ላይ የሚገኙትን ፋኖዎችና የትግል ተጋሪዎችም ትብብሩንና የቅንጅቱን ሂደትና ውጤት በተመለከተ ግልፅ የሆነና ሃላፊነት የተሞላበት አያያዝን እንዲከተሉ ግልፅና ገንቢ አስተያየት የማቅረብ አስፈላጊነት አያጠያይቅም።
• በዚህ ሂደት ውስጥ ፈፅሞ መረሳት የሌለበት ጉዳይ እንኳንስ ለዘመናት በዘለቀ የፖለቲካ ብልሹነት ምስቅልቅሉ በወጣ አገር ውስጥ በተወሰነ ወቅት በሚነሳ ግጭት ምክንያት የሚፈጠርን ፈታኝ ሁኔታ ለመፍታት መሠረታዊ/ዋነኛ ከሆኑ የጋራ ጉዳዮች ( fundamental national issues) ስኬት ጋር የማይጣረሱ ጉዳዮችን አጥንቶና ተረድቶ ስምምነት ላይ መድረስን ግድ ይላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ትኩረት የሚያሻው ሌላው ጉዳይ የእንደኛን አይነት ዘመን ጠገብ፣ ውስብስብና አስከፊ ፈታኝ ሁኔታ ለመፍታት የሚያስችል የጋራ መፍትሄ ለማምጣት ጥረት ስናደርግ የስህተቱ መጠንና ክብደት ይለይ እንደሆነ እንጅ አንዳችን ከሌሎቻችን ተለይተን ፍፁም ወይም እንከን የለሽ ፍጡሮች አድርገን ማቅረብ ትክክል አይሆንም የሚለው ነው።
ከዚህ መሠረታዊ የገሃዱ ዓለም የፖለቲካ እሳቤና አካሄድ ውጭ የሚካሄድ ፖለቲካን ጤናማና ገንቢ ሊያደርግ የሚችል መስተጋብር አይኖርም፤ ቢኖርም አየፀናም።
ሃሳቡ የተሰነዘረው በአማርኛ በመሆኑ የእኔው ሃሳብም በዚሁ ቋንቋ ይሆናል። አንዴ ሻቢያ አንዴ ወያኔ ከዚያም በሲያትልና በደቡብ ሱዳን አልፎ ተርፎም በንግድ ዓለም ራሱን ያሳለፈው የያኔው የኤርትራ ክፍለ ሃገር ተወላጅ የማነ ጃማይካ (የማነ ኪዳኔ መሰለ).. ሁሉን አይቶ ከሰከነ በህዋላ አልበገሬነት በሚለው የግጥም መድበሉና Jamaica, a Memoir በሚለው መጽሃፉ ላይ ስለ ጦርነትና ግጭት፤ ስለ ፓለቲካ አሰላለፍና አስተሳሰብ ከንቱ መሆኑ እንዲህ ሲል ይነግረናል።
እኔ እቃወማለሁ ከንቱ ደም መፋሰስ እኔ እቃወማለሁ
ህይወት መባከኑን እኔ እቃወማለሁ
ትክክል ያልሆነ ጦርነት አልሻም….ወዘተ እያለ ይቀጥላል
የሻቢያ/የወያኔ/የፋኖ/የኦላ ጥምረት የመጠፋፋት ጥምረት እንደሆነ ማንም ቢሆን የሚገምተው ነው። አበው እንደሚሉት የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል እንዲሉ ከአሁኑ ሞንጀሪኖ የምትነግረን፤ ጦርነት ጠማቂው ድብረጽዪን የሚለው ሁሉ ጭራሽ ጥምረትን የሚያጠናክር ሳይሆን የሚያጠራጥርና የሚያስበረግግ ነው። ወያኔ በአማራ ህዝብ ላይ የፈጸመው በደል ሰማይ ጠቀስ ሆኖ እያለ የአማራን ህዝብ እንወክላለን የሚሉት ታጣቂዎች ከዚህ የቁም ሙት ድርጅት ጋር ቂጥ ለመግጠም ማሰባቸው የፋኖን ያልጠራ አላማ ግልጽ አድርጎ ያሳያል። ወያኔ ከብልጽግና ጋር በከፈተው ቀዳሚ ጦርነቶች የፈጸመው በደል በድምጽና በቪዲዪ የተያዘና ሰው ዞር ብሎ ሊመለከተው የሚገባ በመሆኑ በአማራ ህዝብ ላይ በማይካድራ ከሰሩት በደል በላይ በወሎ በጎንደር በሽዋና በአፋር የፈጸሙት አሳፋሪ ተግባር ለታሪክ ተቀምጧል። እርሻ ውለው ማጭድንና የምሳ መያዣቸውን አንጠልጥለው ሃገር ሰላም ነው ብለው ወደ ቤታቸው የሚመለሱ ገበሬዎችን አስበርክከው የረሸኑ፤ ዘርፎ ወደ መቀሌ ለመውሰድ ያልተመቻቸውን በቁም ያቃጠሉ፤ የቁም ከብቶችን በጥይት ደብድበው የገደሉ፤ በትምህርት ቤቶችና በህዝብ መገልገያ ተቋማት ያሉ እቃዎችን ጭነው የወሰድ አልፎ ተርፎም በቀይ ቀለም በየግድግዳው ፉከራና ስድብን የለጠፉ ከዘርና ከቋንቋቸው ውጭ ሌላው ሁሉ ጉድፍ የሆነባቸው ጉዶች ጋር ነው ፋኖ እጣመራለሁ የሚለው። ሲጀመር እኔም እንደ ጃማይካ ጦርነትን እጠላለሁ። ለዚያውም የብሄርተኝነት እሳትን። ብሄርተኝነት በተደጋጋሚ እንደምለው የአፓርታይድ አንድ ገጽታ ነው። በብሄሩ አስቦና ታግሎ ሃገር ያቆመ፤ ሁሉን ሰው ያስተረፈ አንድም ድርጅት በዓለም ላይ የለም። ብሄርተኝነት በሽታ ነው።
በሃገራችን የፓለቲካ ትርምስ ውስጥ ከመገዳደልና ከሰቆቃ ውጭ ያልተሄደበት መንገድ የሰላሙ መንገድ ብቻ ነው። ሌላውን ዝንተ ዓለም ነጉደንበታል። ስንጋደል ስንገድል ስናሳስር ስንታሰር ስናሳድድ ስንሰደድ አይተነዋል። የፓለቲካ ጠበብቶች ጦርነት ንፋስ ነው ይሉናል። አቅጣጫውን የሚቀያይር፤ የሚሸከመውን አራግፎ ሌላ አቧራ የሚያስነሳ ባጭሩ እንቦለሌ ዟሪ ነው። ይህ ለሚገባው ይገባዋል። በሰዎች እንባና ደም ለሚነግድ ግን ስሜት አይሰጠውም። ለምን ግን ሃበሻ ከፓለቲካ ውጭ የሚቆረጥመው ነገር አጣ? ለምን ፓለቲካችን አኞ ሆነ? ከትውልድ ትውልድ ለሃገርህ አሁን ደግሞ ለክልልህ ወይም ለብሄርህ እየተባለ እሳት ውስጥ ይማገዳል? ለምን ካለፈው የፓለቲካ ስህተታችን ለመማር ተሳነን? ስናሳዝን
ህዝባችን በዚህ በዚያም ነፍሴ አውጭኝ እያለ በዓረብና በነጭ መንጋ ሃበሳ ሲቆጥር፤ ሌላውም በሰራውና ባልዋለበት አንገቱ ሲቀላ ድምጽ የማያሰማው ሃበሻ ትግራይ ትጸርይ ይልሃል። ከሚሊዪን በላይ ህዝብ ገብሮና አስገብሮ ከዘመናት የነፍስ አባቱ ከሻቢያ ጋር ሆኖ ለዳግመኛ ጦርነት ራሱን እንደገና ያዘጋጃል። ይህ እብደት አይደለም የሚሉ ሁሉ ራሳቸው ያበድ የቁም ሙቶች ናቸው። አማራ ብልጽግና ይህን በድሎን ያን አድርጎ ይላል። ራሱ ተመልሶ ግን የአማራ ህዝብ ጠላት ሆኖ ገፋፊና ዘራፊነቱ በሰፊው ይወራል። አላማው ባልጠራ፤ የጦርነቱ ማብቂያ በማይታወቅ ማጥ ውስጥ የአማራን ህዝብ ከቶ ከላይና ከታች ህዝቡ በመንግስት ሃይሎችና በፋኖ በሚደረግ ፍልሚያ ሟችና ተፈናቃይ ሆኗል። ታዲያ ወያኔና ሻቢያ ከፋኖ ጋር እንጣመር ማለታቸው ውጊያው በአማራ ክልል ብቻ ተወስኖ እንዲቀር እንደሆነ እንዴት መገመት ያቅታቸዋል? አማራ ክልል የጦርነት ቀጠና፤ አስመራና መቀሌ ደጀን መሆናቸው ነው? መሳቂያ ፓለቲካ። የመንፈቅ ልጅ እንኳን የወያኔን ሴራ ያውቃል እንኳን ተምረናል በቅተናል የሚሉት ቀርቶ!
ጽምዶ ወያኔና ሻቢያ ከግብጽና ከሱዳን ጋር የገመድት የፋኖ ማነቂያ ገመድ ነው። የአንድን ድርጅት ባህሪ ለመረዳት ያለፈበትን መንገድ መመልከት ተገቢ ይሆናል። በታሪካቸው ወያኔና ሻቢያ የራሳቸውን ሰዎች እየረሸኑና እያስረሸኑ፤ ለዚያውም በተኙበት እየገደሉና እያስገደሉ፤ ወገናቸው በጋለ ማጭድ እየጠበሱ ነው ዛሬ ላሉበት የፓለቲካ ጡረታ ላይ የደረሱት። እነዚህ ቡድኖች ገድለው በስምህ ት/ቤት ያቆማሉ፤ መንገድ ይሰይማሉ። አፍነው ወስደው አፋላጊ ሆነው አብረው ይሰለፋሉ። ገድለው ቀብረው ሃዘን ላይ የእዝን ንፍሮ አብረው ከሃዘንተኛው ጋር ይዘግናሉ። ባጭሩ ከሂትለር ገስታፓ አይሻሉም። ከላይ የተጠቀሰው የማነ ጃማይካ የአባቱን ምክር አልሰማ ብሎ ለትምህርት ወጥቶ በዚህ በዚያም ተቅበዝብዞ ሻቢያን ከአሜሪካ ሂዶ ተቀላቅሎ በህዋላም ወያኔን እንዲሰልልና ለሻቢያ ሪፓርት እንዲያደርግ በወያኔ ውስጥ ከእነ ስብሃት ነጋ ጋር በመሆን የኤርትራን መቆረስ ካፋጠኑት አንድ ነው። ግን በመሸ ጊዜው ሁሉን ዞር ብሎ ሲያየው ከንቱ የከንቱ ከንቱ መሆኑ በውል ተርድቶታል። ለዚህ ነው ሰላም ከጦርነት እንደሚሻል ዛሬም ወደፊትም በሃሳብ የምንታገለው። የኤርትራ/የትግራይ/ሽራፊዋ ኢትዪጵያም ከጦርነት የምታተርፈው አንድም ነገር የለም። ስለዚህ በፈጠራ የታሪክ ትርክት ራስን አስክሮ የሌላውንም የጠራ ሃሳብ አደፍርሶ ሁልጊዜ እኔን ምሰሉ ማለቱ ለማንም አይበጅም። ቢቻል ግንፍል ሃሳብን ገድቦ በሃሳብ ተከራክሮ ነገሮችን ተቀብሎና አካፍሎ ተቻችሎ ከመኖር የበለጠ ምንም ነገር አይኖርም። ሻቢያ ለኤርትራዊያን ወያኔ ለትግራይ ህዝብ ከምሲን እንዳላስገኙለት ሁሉ የአማራውም ሆነ የኦሮሞው ስብስብ በጦርነት ተቀናጀም አልተቀናጀም የህዝባችን መከራ ከማባባስ ሌላ የሚፈጥሩት አንድም ማለፊያ ነገር አይኖርም። ስለሆነም በሁሉም መንገድ ጦርነት ይቁም። ብልጽግናም ፉከራና ሽለላህን ትተህ እንበለ ፍርድ ያጎርካቸውን ፍታ። ለሰላም በር ክፈት። ያለዚያ አወዳደቅህ ከደርግና ከወያኔ የከፋ ይሆናል። የቅርብ ጊዜ ታሪካችን የሚያሳየን ይህኑ ክስተት ነውና! ፋኖም ከመንግስት ጋር በጠራ መንገድ ተደራድረህ በውል ለህዝብና ለሃገር ሲባል ትጥቅ በማውረድ ወደ ሰላም ኑሮ ተመለሱ። የጽምዶ ጥምረት ለእናተም ለአማራ ህዝብም ለመላው ኢትዮጵያ አይጠቅምም። የጠላቶቻችን መገልገያ መሳሪያ አትሁኑ!