
ከአሰፋ አበበ
በኢትዮጵያ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች አጀንዳዎችን በመሰብሰብ በአጀንዳዎቹ ላይ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በማዘጋጀት ምክረ ሀሳቦችን እንዲያቀርብ በ2014 ዓ/ም በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ባዘጋጃቸው ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ከሐምሌ 8/2018 ጀምሮ 4,000 ሰዎች ለሶስት ሳምንታት ያህል ይመካከሩበታል የተባለው የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል:: ለምክክሩ የተቀረጹ አጀንዳዎች ይፋ ከሆኑበት ቀን ጀምሮ በጉዳዩ ላይ ከምክክር መድረኩ ውጭ የሞቀ ውይይት በማድረግ ላይ ካሉት ቡድኖች ውስጥ አንዱ የኦሮሞ ማህበረሰብ ቡድን ነው::ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ያመጣል ብለው ውጤቱን በተስፋ የሚጠብቁ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ ምክክሩ ችግሮቹ እንዲወሳሰቡና እንዲባባሱ ከማድረግ ውጭ መፍትሔ አያመጣም ብለው የሚያናንቁ ወገኖችም አሉ::
የ1966ቱ አብዮት በገጠር መሬት፥ በከተማ ቦታና ቤት ውርስ የአማራውን ወገብ ለመስበር የመጣ ነው፥ የ1983ቱ ለውጥም አማራ ጨቋኝ ነው በማለት አማራውን አንገት ለማስደፋት ነበር፥ የ2010 የመንግሥት ለውጥም የትግራይ የበላይነትን በኦሮሞ የበላይነት ለመተካት ነው፥ ስለዝህ አማራ ወደ አባቶቹ ቤተመንግሥት ተመልሶ ሥልጣን ይዞ፥ የአባቶቹ አጽመ-ርስት የተባሉትን መሬቶች በጉልበቱ መልሶ ተቆጣጥሮ በአማራው ፍላጎትና ሁኔታ (terms & conditions) የሚመራ መንግሥት፥ ሥርዓትና አገር እመሰርታለሁ ብሎ የትጥቅ ትግል በማድረግ ላይ ያለው የአማራ ፋኖ (አፋብን) የአማራ ጥያቄ የሚመለሰው በምክክር ሳይሆን ወልቃይትንና ራያን በጉልበት እንዳስመለስነው በክንዳችንና በጉልበታችን በትጥቅ ትግል ነው የሚል አቋም አለው:: ኦነግ- ኦነሠም በጉልበት ያጣነውን መብታችንን የምናስመልሰው በጉልበት ነው በማለት በትጥቅ ትግል ላይ ይገኛል:: ሕወሐት በበኩሉ የትግራይ ችግር በሰላምና በፕርቶሪያ በተደረገው ስምምነት ልፈታ አልቻለም፥ በማለት በትግራይ ውስጥ የምከታ ፕሮግራም ቀርጾ፥ ከትግራይ ውጭ ደግሞ ጽምዶ የሚባል ጥምረት ፈጥሮ ችግራችን የሚፈታው በኃይል ጠላቶቻችንን በመቅበር ነው በማለት ለጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን እየገለጸ ነው::
በተመካካሪዎቹ ነጻነት ላይም ጥያቄ የሚያስነሱ ዘገባዎች እየቀረቡ ነው:: ለምሳሌ ምክክሩ ከተጀመረ በኋላ ገዥው ብልጽግና ፓርቲ በዋና ዋና የምክክር አጀንዳዎች ላይ በምክክሩ ላይ የሚሳተፉ አባላቱ ሊከተሉት የሚገባቸውን አቋም አስመልክቶ አቅጣጫ መስጠቱ: ከአቅጣጫው ወጣ ያለ እንቅስቃሴ ለሚያደርጉትና ከፓርቲው አቋም ለሚያፈነግጡ ተመካካሪ አባላቱ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ በሰፊው ተዘግቧል:: የብልጽግና ፓርቲ ለድርድር ወይም ለምክክር እንዳይቀርቡ አቋም ይዞባቸዋል ከሚባሉት ጉዳዮች ውስጥም አንዱ አሬንጓዴ፥ ቢጫ እና ቀይ ቀለሙ የኢትዮጵያ ባንዲራ መደብ ለውጥ ጉዳይ ነው ተብሏል:: በሰዓሊ መስፊን ሀብተማሪያም ዲዛይን ተደርጎ የተሰራው በባንድራው መሐል ላይ የተቀመጠው ባለአምስቱ ጫፍና ባለጨረሩ ሰማያዊ ኮከብ እንጂ አሬንጓዴ፥ ቢጫና ቀይ ቀለም የባንዲራው መደብ እንዳይለወጥ እንዲከላከሉ፥ በምክክር ማሳመን ካልቻሉም በባንዲራው መደብ ለውጥ ላይ የሚደረገውን ምክክር ረግጠው እንዲወጡ የምክክሩ ተሳታፊ ለሆኑ የብልጽግና ፓርቲ አባላት ጥብቅ መመሪያ መሰጠቱ በሚዲያዎች ተዘግቧል:: ሌሎቹ በብልጽግና ፓርቲ ጥብቅ አቅጣጫ የተሰጠባቸው አጀንዳዎች የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ጉዳይ፥ የፌዴራሊዝሙ ቅርጽና የመሬት ጉዳይ እንደሆነ ተገልጿል::የፓርቲ፥ የቡድን ወይም ሌላ ውክልና ይዞ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የተገኘ ተመካካሪ የወከለውን ቡድን አቋም ማራመዱ፥ የሀሳብ ልዩነቱን ማስመዝገቡና የወከለውን ቡድን ጥቅም በእጅጉ የሚጎዳ ውሳኔ የሚወሰን ከሆነ የውሳኔው አካል ላለመሆን ስብሰባውን ረግጦ ቢወጣ ዴሞክራሲያዊ መብት ነው የሚል እምነት አለኝ:: ነገር ግን ከተቻለ መቶ በመቶ፥ ካልተቻለ ከሰባአምስት በመቶ በላይ መግባባት ይጠበቃል በሚባልበት በዝህ ምክክር ላይ የዝህ ዓይነቱ ዴሞክራሲያዊ መብት የመጠበቅ ዕድሉ ጠባብ ይመስላል:: በመሆኑም የሀሳብ ልዩነት ያላቸው ተመካካሪዎች አስቸጋሪ ሁኔታ ልገጥማቸው ይችላል ተብሎ ይገመታል::
የሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ተሳታፊዎች ዓላማና የእርካታ ደረጃም ይለያያል:: ለምሳሌ በሱማሊና ኦሮሚያ ክልሎች ድንበር አከባቢ የሚኖሩ የዱቤ ማህበረሰብ ተወካይ የሆኑት አቶ አብዲ ኡመር የተባሉ ተመካካሪ እጅግ የተገለለና አናሳ ያሉትን የዱቤ ማህበረሰብን ወክለው በሀገራዊ ምክክሩ ከኦሮሞና ሱማሌ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ እኩል ለምክክር መቀመጣቸው ከፍተኛ እርካታ እንደሰጣቸው ገልጸዋል:: የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕ/ር መስፊን አርአያ መኖሩን ለመጀመሪያ ጊዜ አሁን ሰማሁ ያሉት መኒት ብሔረሰብን ወክሎ የተገኘው ተወካይም የዱቤ ብሔረሰብ ተወካይ ያለውን በተሳትፎ ብቻ የመርካት ስሜት ልኖረው ይችላል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድም የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ተሳታፊዎችን ቢትጠይቃቸው አብዘኞቹ በዝህ መድረክ ላይ መገኘቴ ብቻ ከበቂ በላይ ነው ይላሉ ብለዋል:: ይህ ጉዳይ ምክክሩ ችግሮችን በዘላቂነት ከመፍታት ይልቅ በተሳትፎ ላይ ያተኮረ ያስመስለዋል::
ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ የሕዝብ ቁጥራቸው ግንዛቤ ውስጥ ሳይገባ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በእኩል የተሳታፊ ቁጥር በክልል ተወካዮች ቡድን የመወከላቸው ጉዳይ ነው::በምክክር ጉባኤው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እያንዳንዳቸው 22 ተወካይ አባላት እንዲኖራቸው ፤ በፌዴራል ደረጃ የሚወከሉ ባለድርሻ አካላትም 22 ወኪሎች እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡ እነዝህ ከ12 ክልሎች፥ ከሁለት የከተማ አስተዳደሮችና ከፌዴራል ደረጃ የሚወከሉ 330 የጉባኤ አባላት አካራካሪ እና ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች መቋጫ እንዲያገኙ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ ለእነርሱ ውሳኔ የሚቀርበውም ጉዳይ ቢያንስ 3 ክልሎች ጉዳዩ በክልል ተወካዮች ጉባኤ እንዲታይና እንዲወሰን ግልፅ የሆነ ጥያቄ ለኮሚሽኑ ሲያቀርቡና ኮሚሽኑ ጉዳዩ የሕዝቦችን እሴት፣ ማንነት እና ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑ ሲይምንበት ነው:: ይህ አሰራር ትልቁን የኦሮሚያ ክልል እና ትንሹን የሐራሪ ክልል በእኩል ደረጃ ላይ ያስቀመጠ ከመሆኑም በላይ ጥቅሜ ተነካ ያለ ክልል ወይም ማህበረስብ የሶስት ክልሎች ድጋፍ ካላገኘና ኮሚሽኑ ካልደገፈው ጉዳዩ ለክልል ተወካዮች ቡድን አይቀርብለትም::ይህ የሕዝብ ቁጥርን ዋጋ የሚያሳጣና መሰረታዊ የዲሞክራሲ መርህን የሚጻረር አሰራር ነው::
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎች ለመቅረጽና ይፋ ለማድረግ በተሰጠው ስልጣን መሠረት ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችን ቀርጾ ሐምሌ 8/2018 ለተጀመረውና 4,000 ተሳታፊዎች ላሉት የምክክር ጉባዔ አቅርቧል:: የአጀንዳዎች አሰባሰብ፥ ልየታ፥ መረጣ፥ቀረጻና ቅደም ተከተል ማስያዝን አስመልክቶ የምክክር ኮሚሽኑ በይፋው ድህረ ገጹ ላይ የሚከተለውን ብሏል::
“በብዙዎቹ በምክክር ባለፉ ሀገራት ምክክር የሚደረግባቸው አጀንዳዎች አስቀድመው ተለይተውና ታውቀው በአጀንዳዎቹ ላይም እነማን እንደሚመካከሩ ተለይተው ሂደቱ የቀጠለበት አግባብ አለ፡፡ አጀንዳዎች አስቀድመው ተወስነው የሚደረግ ሀገራዊ ምክክር በውስን አጀንዳዎች ላይ ብቻ የሚያተኩር ሲሆን ተሳታፊዎቹም ውስን የህብረተሰብ ክፍሎች በአብዛኛውም ሊሂቃንና የፖለቲካ መሪዎች የሚሆኑበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡…..
በኢትዮጵያ በሂደት ላይ ያለው ምክክር አጀንዳዎቹ አስቀድመው የተወሰኑ ባይሆኑም መርሆዎች ግን ተቀምጠውለታል፡፡ ምክክር እንዲካሄድባቸው የሚቀረጹ አጀንዳዎች እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው፣ የአለመግባባት መንስዔዎችን በትክክል በሚዳስስ አጀንዳ የሚያተኩሩ እና ጥልቀትና አግባብነት ያላቸው መሆን እንዳለባቸው መርሆዎች ተቀምጠውለታል፡፡…
…በኢትዮጵያ ያሉ የአለመግባባት ወይም የሀሳብ ልዩነቶች የሚታይባቸው ጉዳዮች እጅግ መሰረታዊና ሀገራዊ እንደመሆናቸው መጠን በአጀንዳዎቹ ላይ በራሱ አለመግባባቶች ይታያሉ፡፡ ለተወሰነው ሰው አጀንዳ የሆኑ ጉዳዮች ለሌላው አጀንዳ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ አልፎ አልፎም ጉዳዮችን አይነኬ ለማድረግ የሚሞክሩ አመለካከቶችም አሉ፡፡
….የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በህግ የተሰጠውን ሀላፊነት መሠረት በማድረግ አጀንዳዎችን ከምክክር ሂደቱ ተሳታፊዎች፣ ከተለያዩ ጥናቶች፣ ግለሰቦች ወይም ተቋማት ከሚሰጧቸው የአጀንዳ ሀሳቦች በማሰባሰብ የመለየት፣ የመቅረጽ እንዲሁም ቅደም ተከተል በማስያዝ ምክክር እንዲደረግባቸው ያደርጋል፡፡”
ይህ የሚያሳይው አጀንዳዎች የተሰሰቡትና የተቀረጹት በኮሚሽኑ ከተዘጋጁ የውይይት ስብሰባዎችና የጥናት መድረኮች ላይ ከተነሱ ሐሳቦች፥ ከግለሰቦች እና ተቋማት ለኮሚሽኑ ከቀረቡ የአጀንዳ ሐሳቦች ነው:: በኮሚሽኑ የውይይትና የጥናት መድረኮች ላይ የመሳተፍ ዕድል ያላገኙ ወይም ያልፈለጉ፥ ከኮሚሽኑ ጋር በመገናኘት ይህ ጉዳይ በምክክር አጀንዳነት ይያዝልን ብለው ያልጠየቁ አካላት ሐሳብ፥ ጥያቄና ጉዳይ በአጀንዳነት የሚያዝበት አግባብ የለም ማለት ነው::
በሰላማዊ መንገድ ለኦሮሞ ሕዝብ መብት እንታገላለን የሚሉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ፤የኦሮሞ ነጻነት ግንባር- የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነግ-ኦነሠ)፥ የትግራይ ሕዝብ ነጻነት ግንባር (ትሕነግ)/ሕወሐት፥ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ)፥በዘመነ ካሴ የሚመራው አማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) እና በእስክንድር ነጋ የሚመራው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ተዋህደው የፈጠሩት የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) የመሳሰሉ ድርጅቶች በኮሚሽኑ የአመሰራረት ሂዴት ላይ፥ በኮሚሽኑ አባላት አሰያየምና ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ስላለንና በምክክሩ ሂዴት ላይ እምነት ስለለለን በምክክሩ አንሳተፍ በማለት ራሳችውን ከምክክሩ ስላገለሉ አጀንዳ አላስያዙም ማለት ነው::ይህ ከሆነ ሀገራዊ ምክክሩ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና በባለድርሻ አካላት መካከል ያሉ የሀሳብ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን አካታችና አሳታፊ መሆነ ምክክር ሙሉ በሙሉና በዘላቂነት ለመፍታት መቻሉን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል::
በተጨማሪም አንድ ጉዳይ በአጀንዳነት ይያዝልን ተብሎ ስለተጠየቀ በአጀንዳነት ይያዛል ማለት አይደለም:: በአጀንዳነት የሚያዙት እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚተኮሩ፥ የአለመግባባት መንስዔዎችን በትክክል የሚዳስሱ፥ እና ጥልቀትና አግባብነት ያላቸው ጉዳዮች ናቸው ተብሏል:: አንድ ጉዳይ እነዝህን መመዘኛዎች ወይም መርሆች አሟልቷል ብሎ በአጀንዳነት የሚይዝ ወይም አላሟላም ብሎ የሚጥል ደግሞ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ነው:: ለዝህ ነው የምክክር ኮሚሽኑ አባላት ማንነትና ገለልተኝነት ወሳኝ የሚሆነው:: የኮሚሽኑ አባላት ብቻ ሳይሆን የውይይቱን ሂደት ለማስተባበር ኮሚሽኑ የመደባቸው 160 አመካካሪዎች እና 156 የቃለ ጉባኤ ጸሐፊዎች ማንነትና ገለልተኝነትም ወሳኝ ነው:
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ ለመቅረጽ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የተለያዩ ግብአቶችን ተጠቅሞ የሚከተሉትን ስምንት አጀንዳዎች ቀርጾ ለምክከር አቅርቧል::
- የሀገር ግንባታ (ለምሳሌ የማንነት እና የሀገር ባለቤትነት ጉዳዮች: የአስተዳደር ጉዳዮች: የቋንቋ ጉዳዮች)
- የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ እንዲሁም የፖለቲካ ሥርዐት፣የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ስርአት (ለምሳሌ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት : የክልል አስተዳደር እና ወሰኖች፤ የአዳዲስ ክልሎች አመሠራረት: ሕገ መንግሥትን የመተርጎም ሥልጣን: የሕገ መንግሥት ማሻሻያ:)
- የፌደራል ከተሞች (ለምሳሌ አዲስ አበባና ድሬዳዋ : አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ያለው ግንኙነት : የድሬዳዋ የወደፊት አስተዳደራዊ ሁኔታና ከኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ጋር ያላት ግንኙነት)
- የሃይማኖት ጉዳዮች፣ታሪካዊ ቅሬታዎች እና እርቅን የሚመለከቱ ጉዳዮች
- ተቋማት ግንባታ፣ የህግ የበላይነትና ሰብአዊ መብቶች
- ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች
- ሙስና እና መልካም አስተዳደር
- ሰላም ግንባታ
በምክክሩ ላይ የሚሳተፈው ሰው ብዛት 4,000 ሲሆን በእያንዳንዱ አጀንዳ ላይ 500 ተመካካሪዎችን ያካተተ ዐቢይ ምክክር ቡድን የሚመካከር ሲሆን (500 ተመካካሪ X 8 አጀንዳ=4,000 ) : እያንዳንዱ ዐቢይ ቡድን ደግሞ 50 ተመካካሪዎች ባሉባቸው 10 ንዑስ ቡድኖችን የያዘ ይሆናል:: በአጠቃላይ 4,000 ተመካካሪዎች እያንዳንዳቸው 50 ተመካካሪ በያዙ 80 ንዑስ ቡድኖች ተመድበው ይመካከራሉ ተብሏል:: ምድቡ የተመካካሪውን ፍላጎት፥ ሙያ፥ ዕውቀትና ችሎታን ያገናዘበ ይሁን አይሁን ግልጽ አይደለም:: አንዳንድ የሚወጡ መረጃዎች ግን የዝህ ተዛምዶ ችግር መኖሩን ይገልጻሉ::
የኦሮሚያ ክልል፡ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎችን ሁሉ የሚወክል እንጂ የኦሮሞ ሕዝብን ጥቅም ብቻ የሚወክል አይደለም:: የብልጽግና ፓርቲም የአባላቱንና አገራዊ የሆነውን የድርጅቱን ጥቅም የሚወክል እንጂ የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም በተለየ ሁኔታ የሚወክል አይደለም:: በመሆኑም ለኦሮሞ ሕዝብ መብትና ጥቅም እንታገላለን የሚሉና የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም ይወክላሉ የተባሉት ኦነግ፥ ኦፌኮ፥ ኦነግ-ኦነሠ እና የእነርሱ ዓላማ ደጋፊዎች ባልተሳተፉበት ምክክር የኦሮሞ ጉዳይን የሚወክል አጀንዳና ጥቅሙን የሚጠብቅ ሀሳብ በአግባቡ አልተንሸራሸረም የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ አሉ::
አንዳንድ የኦሮሞ መብት ተቆርቋሪዎች ሀገራዊ ምክክሩን እንደ ዕድል ሳይሆን እንደ ስጋት ያያሉ:: ምክክሩ ለኦሮሞ ሕዝብ ተጨማሪ መብት የሚያስገኝ ሳይሆን ሕዝቡ በዘመናት ትግሉ ያገኛቸውን መብቶች መልሶ እንዲቀማ መደላድል የሚፈጥር፥ መብት ቀናሽና መብት ወሳጅ እንቅስቃሴ ነው ይላሉ:: ምክክሩ የኦሮሚያ አካል የሆኑ የፊንፊኔ እና የድሬ ዳዋ ከተሞች ከኦሮሚያ እንዲነጠሉ ለማድረግ ነው፥ መሬት የግል ንብረት ሆኖ እንዲሸጥና እንዲለወጥ በማድረግ በታሪክ አጋጣሚ ሀብት ያከማቹ ሰዎችና ቡድኖች መሬት እንዲቆጣጠሩ ለማድረግ ነው፥ አፋን ኦሮሞ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንድሆን የቀረበውን ጥያቄ ሌሎችም የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ መሆን የምገባቸው አሉ በሚል ሰበብ ጥያቄውን ለመድፈቅና የኦሮሚያ ክልል ፈርሶ የኦሮሞ ሕዝብ በተለያዩ አስተዳደር ክፍሎች ተከፋፍሎ እንዲዳከም ለማድረግ ነው: አሁን በሥራ ላይ ያለውን የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ሥርዓት (Majoritarian Electoral System) ወደ ተመጣጣኝ የውክልና ምርጫ ሥርዓት (Proportional Representation Electoral System) በመለወጥ የኦሮሞ ህዝብ በቁመቱና በወርዱ (በቁጥሩና በስፋቱ ልክ) ተወክሎ ሥልጣን እንዳይይዝ ለማድረግ ነው: የመንግሥት ቅርጽና ሥርዓትም አሁን ካለው ፓርላሜንታሪ ወደ ፕሬዝዳንታዊ መለወጥ የተፈለገው ከኦሮሞ ባሕል ጋር ከሚጣጣመው ከቡድን ውሳኔ ስጭነት ወደ አማራ የንጉሥነት ባሕል የሚጠጋው የግለሰብ ውሳኔ ስጪነት የሚጎላበትን ሥርዓት መልሶ ለማስፈን ነው: በማለት ይከራከራሉ::
የድሬ ዳዋ ከተማና አከባቢዋ በሕገ መንግሥቱ ከኦሮሚያ ተነጥሎ ዕውቅና ባይሰጠውም የኦሮሚያና የሱማሊ ክልሎች የይገበኛል ጥያቄ የሚያነሱበት በመሆኑ በፌዴራል መንግሥት ሥር መተዳደር ይኖርበታል የሚል መከራክሪያ ይነሳበታል:: ነገር ግን የአማራና የትግራይ ክልሎች ይገባኛል ብለው የተዋጉበት ወልቃይት በፌዴራል መንግሥት ሥር እንድተዳደር ለምክክር አልቀረበም::ይህም የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ጉዳይ ብቻ ከሌሎቹ የይገባኛል ክርክር ከሚነሳባቸው መሬቶችና ከሌሎቹ ትልልቅ ከተሞች ተለይተው ለምምክር የማቅረብ ዓላማ በኦሮሞ ልህቃን ዘንድ ጥርጣሬን ፈጥሯል:: የኦሮሞ ልህቃኑ ለእነዝህ በኦሮሞ ሕዝብ መብት ላይ የተደቀኑ አደጋዎች ናቸው ላሉትም መፍትሔ ነው ብለው የሚያቀርቡት የኦሮሞ ሕዝብ አንድ ሆኖ የሀገራዊ ምክክሩ ውሳኔም ሆነ ምክረ ሀሳብ ተፈጻሚ እንዳይሆን መታገል ነው ይላሉ:: ይህ አቋም የኦሮሞ ሕዝብ በትግል አዙርት ውስጥ መሽከርከር እንዲቀጥልና ሀገሪቷም ችግር እፈታለሁ ብላ ወደ ሌላ ችግር እንድትሸጋገር ያደርጋል::
እንደእኔ ሐሳብ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችና ኤልቶች ከመጀመሪያው ጀምሮ የሀገራዊ ምክክሩ ሙሉ ተሳታፊ ቢሆኑ እመርጣለሁ:: በአንድ በኩል የሀገሪቷ ችግሮች ለውይይት ቀርበው በምክክር ሊፈቱ ይገባል እየተባለ በሌላ በኩል ደግሞ ሰበብ እየደረደሩ ከምክክሩ ራስን ማግለል ተገቢ አይደለም እላለሁ:: በ1984 የኦነግ ከሽግግር መንግሥቱ መውጣት ኢሕአዴግ የ1988ቱን ሕገመንግሥት ያለኦነግ ተሳትፎ ከማውጣት እንዳላቆመው ሁሉ የኦነግ፥ ኦፌኮ፥ ኦነግ-ኦነሠ ከሀገራዊ ምክክሩ ራሳቸውን ማግለል ሕገ መግሥቱን ያለእነርሱ ተሳትፎ ከመለወጥ አያስቀርም:: የተስተካከለና ምቹ ሁኔታ በቀላሉ ልገኝ ስለማይችል በተገኘው ጠባብ ቀዳዳ ተጋፍቶ ገብቶ ይበጃል ያሉትን አጀንዳ ለማስያዝ መታገል፥ በምክክሩ ላይ መከራከርና ካልተሳካም ከውስጥ ሆኖ ባገኙት መረጃ ሂዴቱን አጋልጦ መታገል ተገቢ ነበር እላለሁ:: በምክክሩ መሳተፍ ማለት የምክክር ውጤቱን ወይም ውሳኔን በግድ መቀበል ማለት ልሆን አይችልም:: በመሆኑም የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችና ኤልቶች የድሮውን ታሪክ እያኘኩ ባለፈው የተፈጸመው በደል ካልተቀለበሰ ወይም ካልተካሰ እያሉ ከውይይት መራቅ የለባቸውም፡፡ ያለፈውን ታሪክ አሁን በቀላሉ መቀልበስ ስለማይቻል ያለፈው የታሪክ ጠባሳ ለአሁኑ ውይይት እንቅፋት መሆን የለበትም፡፡ ኦሮሞ ራሱን ለውይይት ካላዘጋጀ፥ ከአገራዊ ፕሮጀክቶችና እንቅስቃሴዎች ራሱን ካገለለ ተጎጅ ይሆናል፥ ሀሳብና አጀንዳ ሰጪ ሳይሆን ተቀባይ ሆኖ ይቀጥላል:: በመሆኑም የራስን ሀሳብና ጥያቄ በማደራጀት በምክክሩ ላይ መሳተፍ ያስፈልግ ነበር እላለሁ::
ለማጠቃለል የሀገራዊ ምክክሩ የሚያቀርበው ምክረ ሁሳብ እንጂ አስገዳጅነት ያለው የሕግ ድንጋጌ ባለመሆኑ ኦሮሞን የሚጎዱ ምክረ፡ሀሳቦች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ለሕዝበ ውሳኔ ስቀርቡ የሕግ ድጋፍ እንዳያገኙ በሰላማዊ መንገድ መታገልና ከገዥው የብልጽግና ፓርትና መንግሥት ጋር መነጋገርና መደራድር ያስፈልጋል:: ለዝህ ደግሞ ጠንካራና ተከታታይነት ያለው በጉዳዩ ላይ ሕዝብን የማንቃትና የማስተማር የሚዲያ ሥራ መሰራት ይኖርበታል::
በሕዝብ ቁጥር ብዛቱ ከኢትዮጵያ በቀዳሚ ደረጃ ላይ የሚገኝ፥ ከአፍሪካ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የኦሮሞ ሕዝብ ሁሌ ከድርጊት በኋላ የሚያለቅስለት፥ የተወሰደበት መብት እንዲመለስ የሚጮህለት፥ ከተጎዳ በኋላ ስለጉዳቱ የሚተርክለት እንጂ በቁጥሩ ልክ የሚመጣውን ችግር ቀድሞ አይቶ የሚከላከልለት፥ አጀንዳ ሰጪ እንጂ ተቀባይ እንዳይሆን የሚረዳው፥ ከሚጎዳው ይልቅ የሚጠቅመው ፖሊሲ እንዲወጣለት፥ ለመብቱና ለጥቅሙ በቁርጠኝነት የሚቆሙ በቂ ብልህና አዋቂ ሰዎችን (ኤልቶችን) ማፍራት አለመቻሉ ያሳዝናል:: በመሆኑም የኦሮሞ ምሁራን ከግድየለሽነትና ከአድርባይነት ወጥተው ለሕዝባቸው መብትና ጥቅም በቁጭት መሥራት ይኖርባቸዋል:: እራሳቸውን ወደ ዳር ከመግፋትና ከማግለል ወደማዕከሉ ተጠግተው፥ ተሳታፊ ሆነው የውሳኔ ስጭነት ቦታ ላይ መሥራት ይኖርባቸዋል:: አጀንዳዎቹ ለምክክር ቀረቡ እንጂ ገና አስገዳጅ የሕግ ኃይል አልተቀዳጁም:: በመሆኑም ተስፋ ባለመቁረጥ የኦሮሞን ጥቅም የሚጎዱ ምክረ-ሀሳቦች ሕጋዊ ኃይል አግኝተው እንዳይተገበሩ ለማድረግ በሰላማዊ መንገድ መታገል ያስፈልጋል::
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena







በመሠረቱ እንደ ኢንፎርሜሽን ካልሆነ በስተቀር ኮሚሽን ተብየው እንኳንስ ፊደል የቆጠረና ቅን ህሊና ያለው ወገን በእኩያን ገዥዎች ምክንያት ፊደል የመቁጠር እድል ያላገኘው እጅግ አብዛኛው ህዝብ የብልፅግና ተብየዎችን ርካሽና አደገኛ የፖለቲካ አጀንዳ ሊያስፈፅም ከዚያው ከብልፅግና ማህፀን ተወልዶ ተልእኮውን እያስፈፀመ መሆኑን በመስማት ሳይሆን በመኖር አሳምሮ የሚያውቀው መሪር ሃቅ ነው ።
እንደ ኢንፎርሜሽን ሊኖረው የሚችለው አስተዋፅኦ እንደተጠበቀ ሆኖ አስቀያሚው የፖለቲካ ተውኔተ ጉባኤና መሰል የፖለቲካ አስተሳሰቦችና አካሄዶች ፍፃሜ እንዲያገኙና ለሁሉም የምትመች ዴሞክራሲያዊት አገር እውን እንድትሆን ምን መደረግ አለበት? እንዴት መደረግ አለበት? የትና መቸስ መደረግ አለበት? የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ከሚሞክር አቀራረብ ጋር ካላያያዝነው ግልፅና ግልፅ የሆነውን ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ከመደጋገም አልፈን ወደ ፊት ለመራመድ እንቸገራለን።