
ኤፍሬም ማዴቦ
(emadebo@gmail.com)
ባለፉት አስር ወራት በኢትዮጵያ ማህበራዊ ሜዲያና የፖለቲካ መድረክ ላይ በስፋት ከሚደመጡ ጽንሰ-ሃሳቦች ውስጥ አንዱ “ፅምዶ” የሚለው የትግርኛ ቃል ነው። “ፅምዶ” ቃል ለቃል ወደ አማርኛ ሲተረጎም “መጣመር”፣ “መተሳሰር” ወይም “መቀናጀት” ማለት ነው። ይህ ማለት ደሞ በዛሬዋ ኢትዮጵያ አውድ ፅምዶ ማለት ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የታጠቁ ኃይሎች፣ ወይም ሌሎች የተለያዩ ሲቪክና ማህበራዊ ባለድርሻዎች ልዩነቶቻቸውን አቻችለው፤ በጋራ ዓላማ ዙሪያ ኃይላቸውን አስተባብረው የሚሰሩበት ስልታዊ ቁርኝት ነው። ፅምዶ ለፍትህ፣ለነፃነትና ለዲሞክራሲ የሚደረገውን ትግልና ባጣቃላይ ከአምባገነን ሥርዓት ወደ ዲሞክራሲ የሚደረገውን ሽግግር በጋራ ለመምራት የሚደረግ የአላማ አንድነት ነው፣ወይም ኃብትና ጉልበትን አስተባብሮና አቅምን አቀናጅቶ አፋኝ ሥርዓትን ወይም የፖለቲካ ተግዳሮቶችን በጋራ መጋፈጥ ነው። ፅምዶ የእያንዳንዱ የጥምረቱ አባል ድርጅት ድርጅታዊ ህልውና እንዳለ ሆኖ፣ በብሔራዊና በህልውና ነክ ጉዳዮች ላይ በጋራ መሰለፍ ነው።
“ፅምዶ” የሚለው ቃል ከቃል ለቃል ትርጉሙ ባሻገር በኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ውስጥ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚ ኃይሎች የሚሰጡት ፖለቲካዊ ትርጉም በጣም የተለያየ ነው። ገዢው ፓርቲና ደጋፊዎቹ ፅምዶን እንደ አገር ክህደት፣ ፅምዶን የሚያራምድ ኃይልን አንደ አገር ጠላት፣ የፅምዶን አስተሳሰብ ደሞ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት እንደሚያፈርስ አስተሳሰብ አድርገው ነው የሚመለከቱት።ተቃዋሚዎች ግን በተቃራኒው ፅምዶን ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አማራጭ አድርገው ነው የሚመለከቱት። ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ-
ገዢው ፓርቲ፡ ራሱን በምርጫ ህዝባዊ ሥልጣን እንዳገኘ ህጋዊ መንግስት አድርጎ ይመለከታል። ስለዚህ ማንኛውም ሽግግር ወይም የ “ፅምዶ” ሃሳብ ህገ-መንግስታዊ ማዕቀፉንና የአገሪቱን ህግ ጠብቆ በመንግስት መሪነት የሚካሄድ ሂደት መሆን አለበት ብሎ ያምናል
ተቃዋሚ ኃይሎች፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሂደት መዋቅራዊ ችግሮች እንዳሉበትና አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ሁሉን አቀፍ ውክልና የሌለው እራሱን በራሱ የመረጠ መንግስት ነው ብለው ይከራከራሉ። ስለሆነም “ፅምዶ” ሲባል የተበታተነውን ትግል በማስተባበር፣የኢትዮጵያን ችግሮች የሚፈታና በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ የተለያዩ ባለድርሻዎችን ተሳትፎ የሚያረጋግጥ ቁልፍ መዋቅራዊ ኃይል ነው ብለው ያምናሉ።
ገዢው ፓርቲ፡ የአገሪቱ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በህገ-መንግስቱ ማዕቀፍ ውስጥ፣ በምርጫና በህግ ማስከበር ሂደት ነው ውስጥ ነው ብሎ ያምናል፣ የፖለቲካ ልዩነቶች ቢኖሩም መፍትሄው በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት አጠናክሮ ማስቀጠል ነው ብሎም ይከራከራል።
ተቃዋሚ ኃይሎች፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ የመዋቅርና የሂደት ችግር በመሆኑ፣ አሁን ባለው የፖለቲካ መዋቅር ብቻ የሚፈታ አይደለም ይላሉ። ስለዚህ “ፅምዶ” የሚባለው ጽንሰ-ሀሳብ ሥርዓት ወለድ ውዝግቦችን ለመፍታት የሚያስችል አዲስ መግባባት (National Consensus) የሚፈጠርበት መድረክ መሆን አለበት ብለው ያስባሉ።
ገዢው ፓርቲ፡ ማንኛውም የንግግር ወይም የውይይት ሂደት መንግስት በባለቤትነት በሚመራቸው እንደ «አገር አቀፍ ምክክር ኮሚሽን» ባሉ ተቋማት ማዕቀፍ ውስጥ መከናወን አለበት ብሎ ያምናል። የውይይቱ ወሰንና ፍጻሜም በህግ ማዕቀፍ ውስጥ መገደብ አለበት የሚል አቋም አለው።
ተቃዋሚ ኃይሎች፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ወይም ገዢው ፓርቲ ራሱ የችግሩ አካል ስለሆነ፣አገራዊ ምክክር ጉባኤን መምራትም ሆነ በጉባኤው ላይ ብቸኛ ወሳኝ አካል መሆን የለበትም፣እንዲያውም አገራዊ ጉባኤው በገለልተኛ አካላት የሚመራ፣ ሁሉን አቀፍና የአገርን የፖለቲካ አቅጣጫ በጋራ የሚወስን መሆን አለበት ብለው ያምናሉ።
ለመሆኑ ፅምዶ ለኢትዮጵያ ይጠቅማል?
የዛሬዋን በእርስ በርስ ጦርነት፣በብሔር ግጭት፣በኤኮኖሚ ውድቀትና በተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የምትታመሰውንና የህልውና አደጋ ውስጥ የገባችውን ኢትዮጵያ ስንመለከት፣ጥምረት ፈጥሮ እነዚህን ችግሮች በጋራ መጋፈጥ ወይም “ፅምዶ” የሚከተሉት በጎ ጎኖች ይኖሩታል-
- ጥምረት የተበታተነ አቅምን ያሰባስባል- በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቁ ችግር ህዝባዊ ትግሉ የተበታተነ መሆኑ ነው። ፅምዶ የተበታተነ ትግልን ያሰባስባል፣የተቃዋሚውን ጎራ ድምፅ ከፍ ብሎ እንዲሰማ ያደርጋል
- ጥምረት የድርድርና የውይይት አቅም ይፈጥራል- ብሔራዊ ውይይቶች ወይም የሽግግር ሂደቶች ሲኖሩ ጠንካራ ድርጅታዊ ፅምዶ ያላቸው አካላት ጠንካራ የመደራደር አቅም ይኖራቸዋል
- ጥምረት የህዝብን ተስፋ ያነቃቃል- የፖለቲካ ኃይሎች ሲቀናጁ ህብረተሰቡ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ አፍራሽ ትርክቶችንና መበታተኖችን አይቶ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ፣ የመተማመን ስሜት ያድርበታል
አንድ በፍጹም መርሳት የሌለብን ነገር ቢኖር ፅምዶ ችግሮችም ሊኖሩበት ይችላል፣የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፣
- አለመተማመንና የቅንጅት አለመኖር- ከዚህ ቀደም የነበሩ የፖለቲካ ጥምረቶች በፍጥነት የመፍረስ ታሪክ ስላላቸው፣ በድርጅቶች መካከል ጥልቅ የሆነ የመተማመን ቀውስ ሊፈጠር ይችላል
- የርዕዮተ ዓለምና የስትራቴጂ ልዩነት- በድርጅቶች መካከል ያለው የረጅም ጊዜ ግብና የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች ሳይፈታ ለጊዜያዊ ስልት ብቻ የሚደረግ ፅምዶ ዘላቂነት የሌለውና በቀላሉ የሚናጋ ሊሆን ይችላል
“ፅምዶ” የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ ዛሬ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በተደጋገሚ እንዲነሳ ያደረገው በአንድ በኩል የችግራችን ብዛትና ውስብስብነት ሲሆን፣በሌላ በኩል ደሞ እነዚህን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት የሚደረገው ትግል የተበታተነ በመሆኑ ነው። ፅምዶ ማለት በተለያዩ ድርጅቶች መካከል ያለውን ልዩነት አጥፍቶ ድርጅቶቹን ማዋሃድ ማለት ሳይሆን፣ በሚጋጩ አጀንዳዎች መካከል የጋራ ጉዳይን መለየት፣ በጋራ አጀንዳዎች ዙሪያ መተባበርና የተበታተነ ኃይልን ለጋራ ዓላማ ማስተባበር ማለት ነው። የፅምዶ መሰረታዊ ጥያቄ “ልዩነታችንን እንዴት እናስወግድ?” ብቻ ሳይሆን “ልዩነታችን እያለ ለጋራ ጉዳይ እንዴት አብረን እንስራ?” የሚለው ቁልፍ ጥያቄ ነው።ነገር ግን እንዲህም ሆኖ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ታሪካዊ አውድ ውስጥ ፅምዶን እንደ ሁነኛ የፖለቲካ ስምምነት ብቻ መመልከት አደገኛ ነው። ማን ከማን ጋር እንደሚጣመር፣ በምን የጋራ አጀንዳ እንደሚጣመር፣ ጥምረቱ የሚያመራበት የፖለቲካ አቅጣጫ ምን እንደሆነና ከመንግስት ለውጥ በኋላ ለምትኖረው ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ራዕይ እንዳለው መጠየቅ ያስፈልጋል። አለበለዚያ ዛሬ የተጣመሩ ኃይሎች ነገ የበለጠ ክፍፍልና ግጭት የሚያመጡበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
ጥምረትን በተመለከተ ከላይ የተቀመጡትን የተለያዩ ሃሳቦች ስንመለከት፣እኛ ኢትዮጵያዊያን ፅምዶ የሚባለውን ቃል በፅንሰ-ሃሳብ ደረጃ ከመቀበል ውጭ ሌላ አማራጭ ያለን አይመስለኝም። መጠየቅ ያለብን ፅምዶ ለምን ያስፈልጋል የሚለውን ከላይ መልሱ በግልፅ የተቀመጠውን ጥያቄ ሳይሆን፣በፅምዶ ስም እነማናቸው የሚጣመሩት የሚለውን ቁልፍ ጥያቄ ነው። እነማናቸው የሚጣመሩት የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት የዛሬዋን ኢትዮጵያ ወጥረው የያዟት ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን እንመልከት-
ፖለቲካዊ ችግሮች
- የፖለቲካ አለመተማመንና የስልጣን ትግል
- በመንግሥትና በተቃዋሚ ኃይሎች፣ እንዲሁም በተለያዩ ብሔራዊና ክልላዊ ቡድኖች መካከል ስር የሰደደ አለመተማመን አለ
2. የእርስበርስ ጦርነትና የብሔር ግጭት
አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ጋምቤላና ቤንሻንጉል-ጉሙዝ ውስጥ የሚካሄዱ የእርስበርስ ጦርነቶችና የብሔር ግጭቶች የኢትዮጵያን እንደ አገር መቀጠል እየተፈታተኑ ነው
3. በአገር ግንባታና በህገ-መንግሥት ላይ የጋራ ስምምነት አለመኖር- ኢትዮጵያ ውስጥ በአገረ-መንግስት ግንባታ፣በአገራዊ ማንነት፣በፌዴራል ሥርዓቱ አወቃቀር፣ በሥልጣን ክፍፍል፣ በታሪክና በባንዲራ ጉዳይ ጥልቅ አለመግባባት አለ
2. ኢኮኖሚያዊ ችግሮች
1. የኑሮ ውድነትና የገንዘብ ዋጋ መቀነስ
ኢትዮጵያ ውስጥ የኑሮ ውድነቱ ማህበረሰቡ መሸከም ከሚችለው በላይ ሆኗል፣የብር የመግዛት አቅም እያሽቆለቆለ ሄዶ ዛሬ አፍሪካ ውስጥ በጣም ከወደቁ ገንዘቦች አንዱ ሆኗል
2. ሥራ አጥነትና የወጣቶች የሥራ እድል እየተመናመነ መሄድ
ኢኮኖሚው በፍጥነት እያደገ ለሚሄደው የህዝብ ብዛት በተለይ ለወጣቱ በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር አልቻለም
3. የጦርነት፣ የዕዳና የኢንቨስትመንት ጫና
ጦርነት ምርት ማምረትን፣ማከፋፈልንና ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳል። ምርት ካልተመረተና ካልተከፋፈለ፣መንግስት ግብር መሰብሰብ አይችልም፣መንግስት ግብር ካልሰበሰበ ደሞ የአገር ውስጥና የውጭ ዕዳ እየተቆለለ ይሄዳል
3. ማህበራዊ ችግሮች
.1 ድህነት፣ ረሃብና የምግብ ዋስትና ችግር
የአለም የምግብ ድርጅት በ2018 ወደ 15.8 ሚሊዮን ሰዎች ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንደሚገጥማቸው አስጠንቅቋል
2. መፈናቀልና የመሠረተ ልማት/የህዝብ አገልግሎት መቋረጥ
ጦርነትና ግጭት ሚሊዮኖችን ከቀያቸው አፈናቅሏል፤ የአለም የምግብ ድርጅት ወደ 4.4 ሚሊዮን የሚጠጉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን እንዳሉ በማስረጃ አስደግፎ ተናግሯል
3. የጤና፣ የትምህርትና የሰብዓዊ አገልግሎት ችግር
ግጭት፣ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የምግብ እጥረትና የኢኮኖሚ ጫና ተደራርበው በጤና፣በትምህርትና በሌሎችም መሠረታዊ አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች አንዳንዶቹ ባለፉት አርባ አመታት ከሥርዓት ወደ ሥርዓት እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮች ናቸው፣ አንዳንዶቹ ችግሮች ደሞ ለምሳሌ፣ትግራይ፣አማራና ኦሮሚያ ውስጥ የሚካሄደው ጦርነትና የአለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት ፖሊሲ ተከትሎ የመጡ የኤኮኖሚ ቀውሶች የጠሚ አቢይ አህመድ የተበላሸ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች የፈጠሯቸው ችግሮች ናቸው። እነዚህ ችግሮች በረጂም ግዜ ሂደት የተፈጠሩና ብዛት ያላቸው ውስብስብ ችግሮች ሰለሆኑ፣ችግሮቹን ለማስወገድ በአንድ በኩል ግዜ ያስፈልጋል፣ በሌላ በኩል ችግሮቹን ለማስወገድ ፈቃደኛ የሆነና ህዝብን የሚሰማ መንግስት ያስፈልጋል።
ዛሬ በሥልጣን ላይ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በአንድ በኩል በችግር ላይ ችግር መፍጠር እንጂ የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት ፍላጎቱም ቁርጠኝነቱም ያለው መንግስት አይደለም፣በሌላ በኩል ደሞ ጠሚ አቢይ ሁሉንም እኔ አውቃለሁ፣ወይም የሁሉም ችግር መፍትሄ ከኔ ነው የሚመነጨው የሚል ሰው ስለሆነ፣ከህዝብ የሚመጣን የተለየ ሃሳብ የሚሰማ ሰው አይደለም። ይህ ማለት ደሞ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች የማስወገድ ሂደት የሚጀምረው ጠሚ አቢይ አህመድን በማስገደድ ወይም በማስወገድ ነው ማለት ነው፣ማስገደድና ማስወገድ ደሞ የተለያዩ ኃይሎችን መጣመር የግድ ይላል።
ከላይ ከፍ ሲል ፅምዶን ወይም ጥምረትን ስንመለከት፣የተበታተነ ትግልን ለማሰባሰብና የድርድር ጡንቻን ለማጎልበት ጥምረት አስፈላጊ መሆኑን አብረን ተመልክተናል። የኢትዮጵያን ዋና ዋና ችግሮች ስንመለከት ደሞ የአገራችንን ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች የማስወገድ ሂደት የሚጀምረው ጠሚ አቢይ አህመድን በማስገደድ ወይም በማስወገድ እንደሆነና፣ማስገደድና ማስወገድ ደሞ የተለያዩ ኃይሎችን መጣመር የግድ እንደሚል ተመልክተናል። እነዚህ ሁለት እውነቶች ላይ ቆመን ነው እነማናቸው የሚጣመሩት የሚለውን ቁልፍ ጥያቄ መመለስ ያለብን።
ከሰሞኑ በብዙ ሜዲያዎች እንደሰማነው ኢትዮጵያ ውስጥ የትብብሩ ውጤት በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን እየተነገረ ነው፣ከተለያዩ ተባራሪ ዜናዎች እንደምንሰማው ደሞ የሚጣመሩት ኃይሎች አማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ህወሓት፣ኦነግ-ሸኔ፣ኦብነግና የጋምቤላና የቤንሻንጉል-ጉሙዝ ታጣቂዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ በስፋት ይደመጣል። ለመሆኑ እነዚህ ድርጅቶች ኢትዮጵያን በተመለከተ ምን የጋራ አጀንዳ አላቸው? የእያንዳንዱ ድርጅት አነሳስና የትግል አላማ ምንድነው? ለምሳሌ፣ኦብነግና ኦነግ-ሸኔን፣ህወሓትና አማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄን፣ኦነግ-ሸኔና የቤንሻንጉል ነፃነት ግንባርን ብንመለከት በሱማሌና በኦሮሚያ፣በትግራይና በአማራ፣በኦሮሚያና በቤንሻንጉል-ጉሙዝ መካከል ስር የሰደደ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ አለ። የኦነግ-ሸኔ፣የህወሓትና የኦብነግ ንቅናቄ የተጀመረው ኦሮሚያን፣ትግራይንና ኦጋዴንን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ታጣቂ ድርጅቶች ውስጥ ብዙዎቹ መሠረታዊ የርዕዮተ ዓለም፣ የፖለቲካ ግብና የታሪክ ልዩነት አለባቸው፣አንዳንዶቹ እርስ በርስ የሚፈላለጉ ናቸው፣ደሞም የተመሰረቱት በኢትዮጵያዊ አጀንዳ ዙሪያ ሳይሆን፣የኔ ነው የሚሉትን ግዛት ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ነው። ታዲያ እነዚህ ድርጅቶች በምን የጋራ አጀንዳ ዙሪያ ነው ጥምረት የሚፈጥሩት?
ዛሬ “ፅምዶ” የሚለውን ቃል ጭራሽ መስማትም የማይፈልግ የማህበረሰብ ክፍል አለ፣በኔ ዕምነት ይህ የጤና አይመስለኝም፣”ፅምዶን” በአይነ ቁራኛ የሚመለከትም አለ፣”ፅምዶን” በአይነ ቁራኛ መመልከት የጥንቃቄ ምልክት ነውና ሊበረታታ ይገባል፣ግን እነዚህ ሰዎች ፅምዶን” በአይነ ቁራኛ ከመመልከት ባሻገር በተለያዩ የታጠቁ ኃይሎች መካከል ጥምረት እንዲፈጠር ምን መደረግ አለበት የሚለውን ጥያቄ መመለስ ቢጀምሩ ጥምረቱን ማፋጠን ይችላሉ። በሌላ በኩል ደሞ ምንም ይሁን ምን የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት እስካስወገደ ድረስ ፅምዶ አስፈላጊ ነው የሚሉም አሉ።ለኔ ይህ የየትም ፍጪው፣ዱቄቱን አምጪው አመለካከት ታሪክን በተለይ የራሳችንን አገርና የአንዳንድ አፍሪካ አገሮችን የቅርብ ግዜ ታሪክ ያላገናዘበ ጭፍን አመለካከት ነው። ባለፉት ሃምሳ አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በወታደራዊ መኮንኖች፣በታጠቁ ኃይሎች ጥምረትና ድርጅታዊ ቅድመ ዝግጅት ባሌለው ህዝባዊ ንቅናቄ የተመሩ የመንግስት ለውጦችን ተመልክተናል፣ሶስቱም የመንግስት ለውጦች ከድጡ ወደ ማጡ ወሰዱን እንጂ ህዝብ የታገለለትንና የተሰዋለትን አላማ አላሳኩም። ስለዚህ ዛሬ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ይወገድ ስንል፣የህንን መንግስት ማን ይተካዋል ለሚለው ጥያቄ በቂ መልስ ሊኖረን ይገባል። አንጎላን ከፖርቱጋል ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት ሦስት ድርጅቶች የትጥቅ ትግል አካሂደዋል። ከእነዚህ ሦስት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ዩኒታ በሚል ምህጻረ-ቃል የሚታወቀው ድርጅት ነው። በብሔራዊ ደረጃ ተደራጅቶ ከሌሎች ሁለት አጋር ድርጅቶች ጋር ለአንጎላ ነጻነት ከፖርቱጋል ቅኝ ገዢዎች ጋር ለ8 አመት የተፋለመውና በዮናስ ሳቪምቢ የሚመራው ዩኒታ፣ አንጎላ ነጻነቷን ስትቀዳጅ ሥልጣን መያዝ ያለብኝ እኔ ነኝ በሚል ከብሔራዊ ደረጃ ወርዶ በብሔር ተደራጅቶ ከአንጎላ ማዕከላዊ መንግስት ጋር ለ27 አመት ተዋግቷል። ይህ ዛሬ በብሔር የተደራጁ፣ እንደ አሸን የፈሉና ምንም አይነት አገራዊ አጀንዳ የሌላቸው የታጠቁ ኃይሎች ለሚገኙባት ኢትዮጵያ ትልቅ ትምህርት ሊሆን ይገባል።
በፖለቲካ ቋሚ ወዳጅም ሆነ ቋሚ ጠላት የለም፤ የሚኖረው “የጋራ ጠላት” ወይም ጊዜያዊ ስልታዊ ጥቅም ነው የሚል አባባል አለ። ይህ አባባል እንደየሁኔታው አንዳንዴ ሊሰራ አንዳንዴም አደገኛ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ በ1970ዎቹ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ በሚል አንዳንድ ኢትዮጵያዊ ኃይሎች ከዚያድ ባሬ ወራሪ ኃይል ጋር ተሰልፈው ኢትዮጵያን ወግተዋል። ህወሓትን ከመሳሰሉ ኃይሎች ጋር ጥምረት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል የምንል ሰዎች እንደዚህ አይነት ተጨባጭ ምክንያቶች ስላሉን ነው።
ህወሓትና ኦነግ-ሸኔ በተለይ ህወሓት 360 ዲግሪ ዞሮ ርዕዮተ አለማዊና የአላማ ለውጥ ለማድረግ ዝግጁ ካልሆነ በቀር እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ለዘለቄታው አጋር ለመሆን የሚያስችል የጋራ አገራዊ አጀንዳ የላቸውም፤ ይባስ ብሎም በወደፊቷ ኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያላቸው አመለካከትና ባጠቃላይ አገርን የመምራት ወይም የመገንባት ራዕያቸው ከብዙ ኢትዮጵያዊያን አገራዊ ራዕይ ጋር የሚጋጭ ነው። በኔ አመለካከት እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ጥምረት እንፍጠር የሚሉት ኢትዮጵያን ከጥፋት ለማዳን ሳይሆን፣ ዛሬ ላይ ካሉበት ፖለቲካዊና ወታደራዊ አጣብቂኝ ለመውጣት የሚያደርጉት ግዜያዊና ስልታዊ ጥምረት (Tactical Alliance) ነው።
ይህንን ጽሁፍ የሚያነብ አንባቢ ሁሉ አንድ ልብ ሊለው የሚገባ ጉዳይ አለ፣ እኔ እያልኩ ያለሁት ከላይ ስማቸው በተጠቀስ ድርጅቶች መካከል ጥምረት መፈጠር የለበትም አይደለም። የኔ ትልቁ ጥያቄ፣ እነዚህ ድርጅቶች ጥምረት ሲፈጥሩ፣በመካከላቸው ያለውን ስር የሰደደ ልዩነት እንዴት እንዳስወገዱ፣የመገንጠል ጥያቄ ያነሱ ድርጅቶች ይህንን ጥያቄያቸውን ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ መተዋቸውንና የሚፈጥሩት ጥምረት የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት ከማስወገድ ባሻገር የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች የሚለውን ጥያቄም አብሮ የሚመልስና፣ጥምረቱ በሂደት የተለያዩ የሲቪል ባለድርሻዎችን የሚያካትት መሆኑን ለጉዳዩ ባለቤት ለኢትዮጵያ ህዝብ በማያሻማ ቋንቋ መግለጽ አለባቸው። በተለይ ከተፈጠረ ገና አመት ያልሞላው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ልምድ ካላቸውና፣ባለፉት ሃምሳ አመታት አማራን እንደ ጨቋኝና የበደሎች ሁሉ አባት አድርገው ከሳሉት ህወሓትና ከኦነግ-ሸኔ ጋር ከመጣመሩ በፊት፣የእነዚህ ሁለት ድርጅቶች ሃሳብና አጀንዳ ብቻ ሳይሆን፣የሃይል ሚዛናቸውም ስጋት በማይፈጥር መልኩ መለወጡን ማረጋገጥ አለበት፣ወይም የሚለወጥ ለመሆኑ ዋስትና ሊኖረው ይገባል።
በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት በፍጹም ኢትዮጵያን በመሰለ የህልውና አደጋ ውስጥ በገባ አገር ውስጥ ጎን ለጎን መኖር የማይገባቸው ሁለት ትልልቅ በገሃድ የሚታዩ ኩነቶች አሉ።
አንደኛ- ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት ሁኔታ በዘመናዊ ታሪካችን ውስጥ በፍጹም ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነው። በሦስት ግንባሮች የሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት፣የህዝብን ጀርባ ያጎበጠ የኑሮ ውድነትና በየቀኑ እየተባባሱ የሚሄዱት ወንጀል፣መፈናቀል፣ስደት፣የሞራል መላሸቅ፣ በራስ አለመተማመን፣ምን አገባኝ፣ ዋልጌነት፣ ግድ የለሽነት፣ሥርዓት-አልበኝነት፣ ሙሰኝነትና ሱሰኝነትን የመሳሰሉ ማህበራዊ ችግሮች ኢትዮጵያን የህልውና አደጋ ውስጥ ከትተዋታል።
ሁለተኛ- የረጂም አመት የታሪክ ባለቤት የሆነችና በቅኝ ግዛት ያልተገዛች አገር አለችን እያልን የምንኩራራ እኛ ኢትዮጵያዊያን የኩራታችን ምንጭ የሆነችው አገራችን የህልውና አደጋ ውስጥ ገብታ በአይናችን እያየን፣አገራችንን ከዚህ የመከራና የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንዴት ነው የምናወጣት ለሚለው ጥያቄ ችግሩ በግልጽ መታየት ከጀመረ ከግማሽ ምዕተ አመት በኋላ ዛሬም መልስ የለንም፣እንዳውም ይባስ ብሎ እርስበርስ መገዳደልና መተላለቅ የየቀኑ ስራችን ሆኗል።
የዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ይህንን ፍጹም አደገኛ የሆነ ሁኔታ ለውጦ የራሱን የወደፊትና ባጠቃላይ አገሩን ኢትዮጵያን ከጥፋት ካልታደገ፣”ኢትዮጵያ የምትባል አገር ነበረች” እያልን የምናወራበት ግዜ ሩቅ ላይሆን ይችላል።
በመጨረሻ አንድ ነገር ግልጽ መሆን ያለበት ይመስለኛል፤ ዛሬ ኢትዮጵያ የምትፈልገው በተበታተነ መልኩ የሚካሄድ የፖለቲካ ትግል ሳይሆን፣ ለልዩነቶች እውቅና ሰጥቶ በጋራ አገራዊ ጥቅም ዙሪያ የሚሰባሰብ ሰፊ የፖለቲካና የማህበረሰብ ኃይል ነው። ስለዚህ “ፅምዶ” የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ በራሱ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው። ነገር ግን ፅምዶ የሚለው ቃል ብቻውን መፍትሄ አይደለም፤ ትልቁ ቁምነገር የተለያዩ ኃይሎችን የሚያጣምረው አጀንዳ፣ የሚጣመሩት ኃይሎችና ጥምረቱን ተከትሎ የሚመጣው አገራዊ ራዕይ ነው።
የኢትዮጵያ ችግር የአንድ መንግሥት ወይም አንድ ድርጅት ብቻ የፈጠረው ችግር አይደለም። የፖለቲካ አለመተማመን፣ ጦርነት፣ የብሔር ግጭት፣ በአገር ግንባታና በህገ-መንግሥት ላይ ያለው አለመግባባት፣ የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት፣ ድህነት፣ መፈናቀልና የመሠረታዊ አገልግሎት ችግሮች ተያይዘው በረጂም ግዜ ሂደት የተፈጠሩ ችግሮች ናቸው። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የጠሚ አቢይ አህመድን መንግሥት መለወጥ ብቻ በቂ አይደለም፤ ይህ መንግስት ከተለወጠ በኋላ የሚመጣው የፖለቲካ ሥርዓት፣ የሽግግር ሂደት፣ የህገ-መንግሥት ስምምነትና የአገር ግንባታ አቅጣጫ አብረው መታሰብ አለባቸው።
የታጠቁ ኃይሎች የሚፈጥሩት ጥምረት የጠሚ አቢይን መንግሥት ለማስወገድ ብቻ የሚፈጠር ጊዜያዊ ወይም ስልታዊ ጥምረት ከሆነ ኢትዮጵያን ከአደጋ ማዳን አይችልም። የኛ የራሳችን የቅርብ ግዜ ታሪክ ፍንትው አድርጎ የሚያሳየን ይህንኑ እውነት ነው። ስለዚህ በፅምዶ ስም የሚጣመሩ ኃይሎች የዛሬውን ጠላት ብቻ ሳይሆን የነገዋን ኢትዮጵያም አርቀው ማሰብ አለባቸው። በተለይም በርዕዮተ ዓለም፣ በአገር አተያይ፣ በግዛት ጥያቄና በወደፊቷ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ላይ ጥልቅ ልዩነት ያላቸው ኃይሎች ከመጣመራቸው በፊት አንድ በግልጽ መመለስ ያለባቸው ጥያቄ አለ፤እሱም “አብረን የምንታገለው ምን ለማስወገድ ነው፣ ምንስ ለመገንባት ነው?” የሚል ቁልፍ ጥያቄ ነው። የጋራ ጠላት ሊያጣምር ይችላል፤ ጥምረቱን ዘላቂና አገርን የሚጠቅም የሚያደርገው ግን የጋራ አገራዊ ራዕይ ነው። ስለዚህ ፅምዶን መቃወምም ሆነ በጭፍን መደገፍ በቂ አይደለም። ትክክለኛው አቋም ፅምዶን በጥንቃቄ መመልከት፣ የጋራ አጀንዳውን መጠየቅ፣ የተሳታፊዎቹን የፖለቲካ ዓላማ መመርመር፣ ከመንግስት ለውጥ በኋላ የሚኖረውን የአገር አቅጣጫ በግልጽ መጠየቅና የኢትዮጵያ ህዝብ የሂደቱ ባለቤት መሆኑን ማረጋገጥ ነው። ለኔ የፅምዶን በተመለከተ ትልቁ ፈተና “ፅምዶ” የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት ማስወገዱ መቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ የጠሚ አቢይን መንግስት ካስወገደ በኋላ ለምትመሠረተው ኢትዮጵያ ያለውን የጋራ ራዕይ ከወዲሁ ማሳየት መቻሉ ላይ ነው። ይህ ካልሆነ “ፅምዶ” በሃምሳ አመት ወስጥ አራተኛው ከድጡ ወደ ማጡ የሥልጣን ለውጥ ሊሆን ይችላል። ለዚህ ነው እንደ አማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ አይነቶች ከራሳቸው ብሔር ባሻገር የወደፊቷ ኢትዮጵያ ጉዳይም የሚገዳቸው ድርጅቶች ፅምዶን በከፍተኛ ጥንቃቄ መመልከት አለባቸው እያልን በነጋ በጠባ የምንወተውተው!
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






