Homeነፃ አስተያየትአዲስ አበባ ፡ የዘውጌ ማንነት ማቅለጫ ጋን “ፊንፊኔ ኬኛ” እና  “በራራ የእኛ” 

አዲስ አበባ ፡ የዘውጌ ማንነት ማቅለጫ ጋን “ፊንፊኔ ኬኛ” እና  “በራራ የእኛ” 

Advertisement
World Wide Travel Group

በደረጀ ይመር
ንደፈ ሐሳባዊ ስንቅ


ታዋቂው የሥነ ማኅበረሰብ ፈላስፋው ቱርካዊው ዱርካይም፣ ከተሜነት የዘውጌ ማንነት ማቅለጫ ጋን (melting pot) እንደሆነ ያብራራል፡፡ እንደ ልሂቁ አባባል፣ የከተማ መስፋፋት ከኢንዱስትሪ አብዮት መፈንዳት ለጥቆ የሚመጣ ኹነት ነው፡፡ ይኽ ነባራዊ ኹኔታ ደግሞ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካውና በኢኮኖሚ ረገድ የፋፋ ዘመናዊ ማኅበረሰብን ለዐይነ ሥጋ በማብቃቱ ረገድ ድርሻው የላቀ ነው፡፡ በዚህ አውድ ውስጥ የተፈጠረ የዳበረ ማኅበረሰብ ለዘውጌ ማንነት ፊት አይሰጥም፡፡ አጠቃላይ የግለሰቦች የእርስ በርስ ግንኙነት በላቀ ኅላዌ (ኦርጋኒክ ሶሊዳተሪ) የሚገለጽ እንደሆነ ከፈላስፋው ሐተታ እንረዳለን፡፡

በአንጻሩ የዘመናዊነት መዳፍ ያልዳበሰው ኋላ ቀር ማኅበረሰብን ያስተሳሰረው የግንኙነት መረብ፣ ከአምክንዮ በተራቆተ የደቦዋዊ ቅኝት፣ ማለትም በወንዝ ልጅነት፣ በእምነት፣ በባህል ወይም በትውፊት የሚገለጽ ይሆናል፡፡ እሴቶቹ በመወለድ ብቻ የምንላበሳቸው ቆሞ ቀር የማንነታችን መገለጫዎች ናቸው፡፡ የእኛን ማውጣት ማውረድ /Rational endeavor/ ወይም የአእምሮ ፍሬ የሚጠይቁ አይደለም፡፡ እነዚህ ኋላ ቀር የትስስር ዘረ-መሎች ዘመናዊነት በሚፈነጥቃቸው ዕድገቶች ምክንያት በሌላ ውስብስብ መስተጋብር ደብዛቸው ይጠፋል፡፡

በሌላ አነጋገር የዘውጌ ፖለቲካ በጽኑ የሚሻው ባህላዊ ንጣፍ፣ ከተሜነት በሚያመጣው ዕድገት የተነሳ ጠፍ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ባህላዊውን ማኅበረሰብ እንደ ወጋግራ ያቆመው ከምክንያት ይልቅ፤ ለስሜት ቅርብ የሆነው የጋራ ማንነት፣ ዝመና የሚፈጥረውን ልህቀት መቋቋም ተስኖት ሥፍራውን ለሌላ ገዢ መስተጋብር መልቀቁ ግዴታ ይሆናል፡፡ ከተሜው በሐሳብ የበላይነት እንጂ፤በቋንቋ ማንነት ወይም በወንዜ ልጅነት ልቡ ሊሸፍት አይችልም፡፡

አዲስ አበቤ ጠሉ ሕገመንግሥታዊ ሰነድ 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

በሥራ ላይ ያለው ሕገመንግሥት እንደ አዲስ አበባ ሕዝብ ያጎደለው የለም፡፡ የከተማዋ ነዋሪ ባለፉ ሦስት ዐሥርተ ዓመታት የፖለቲካ ውክልና ተነፍጎት፤ የፖርቲ ሹመኞች እንዳሻቸው ሲቀልዱበት ነው የኖሩት፡፡የኢሕአዴግ ግንባርን የመሠረቱት አራቱ የዘውጌ ድርጅቶች፣በመዋጮ ከተማዋን ሲያስተዳድሯት እንደኖሩ ይታወቃል፡፡

ሕገ መንግሥቱ አዲስ አበባን ብሔር፣በሔረሰብ ወይም ሕዝብ አይደለሽም ብሎ የፖለቲካዊ ውክልና ነፍጓታል፡፡በፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተማዋ መቀመጫ የላትም፡፡ ምክር ቤቱ ወደ 12 የሚጠጉ ሀገራዊ አጀንዳዎችን መወሰን እንዲችል፤ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን ለግሶታል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ትልልቅ ርዕሰ ጉዳዮች፣ የአዲስ ሕዝብ የበይ ተመልካች እንዲሆን ተፈርዶበታል፡፡ 

ሕወሓት/ኢሕአዴግ በምርጫ 97 በቅንጅት የደረሰበትን አሸማቃቂ ሽንፈት ተከትሎ፣በጊዜው የሕወሓት ደንገጡር ለነበረው ኦህዴድ በተላለፈለት ቀጭን ትዕዛዝ መሠረተ፣የክልሉን መቀመጫ ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ ለማዛወር በቅቶ ነበር፡፡በዚህም የተነሳ፣ከተማዋ ድርብ ድርብርብ ችግሮችን ልትሸከም ችላለች፡፡ ለአብነት ያህል፣መዲናዋ ለኦሮሚያ ክልል ተቋማት መገንቢያ መሬት ባልተጻፈ ሕግ እንድታቀርብ የተገደደችበትን አሻጥር ዋቢ አድርጎ ማንሳት ይቻላል፡፡ ይህ አይነቱ  የመዲናዋን ሕዝብ ጀርባ የሚያጎብጥ አግላይ ሥርዓት እንዲተከል ምክንያት የሆነው ደግሞ በሕገ መንግሥታዊ ሰነድ የተደገፈው እና መዋቅራዊ ሥጋ የለበሰው የማንነት ፖለቲካ ነው፡፡ 

 የማንነት ፖለቲካ በባሕርይው ከተሜ ጠል ነው፡፡ፖለቲካ የሚለው ጽንሰሐሳብ ጥንስሱ ፖሊስ ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ቃሉ በዋንኛነት ከከተማ ዜጎች መብት እና ግዴታ ጋር የተቆራኘ ነበር ፡፡ስለዚህ ፖለቲካን ገና ከጅምሮ አንስቶ ከከተሜነት ወይም በዜግነት ከሚገኝ ማንነት ማዕቀፍ ውጪ መመልከት የሚቻል አይደለም፡፡ በዚህ ንድፈሐሳባዊ ማዕቀፍ የሀገራችንን የከተሜ ጠል ፖለቲካን ዘፍጥረት ከመረመርን ትርጉም ያለው መደምደሚያ ላይ ለመድረስ እንችላለን፡፡ አምባገነናዊውን የደርግ ሥርዓትን ገርስሶ የሥልጣን መንበሩን የተቆናጠጠው ሕወሓት/ኢህአዴግ ከከተማ ሥነልቦና ጋር በተፋቱ የክፍለሀገር ልሂቃን የሚመራ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ እነዚህ ልሂቃን አዲስ አበባንም ሆነ ሌሎች ዘውጌ-ዘለል(meta-ethinic) ከተማዎችን ያገለለ የፖለቲካ ሥርዓትን ለዐይነ ሥጋ ለማብቃት የ1987ቱቱን ሕገ መንግሥታዊ ሰነድን ቀርጸው በተግባር አውለዋል፡፡

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

የዘውጌ ብሔርተኝነትና  አዲስ አበቤነት

አዲስ አበቤነት በዘውጌ ማንነት ኪሳራ የተቀለሰ የላቀ ሰብእና ነው፡፡ የአዲስ አበባን ውሃ ጠጥቶ ያደገ “አዲስ አበቤ” እንደው በቀላሉ የቤተሰቡን የዘውጌ ውርስ እንደ ካባ አንስቼ ላጥልቅ ቢል አይቻለውም፡፡ አዲስ አበቤነት የደም ውርስ አይደለም፤ ከግለሰቡ አቅም በላይ በሆነ ማኅበራዊ ስሪት/ሶሻል ኮንስትራክሽን/ በጊዜ ሒደት የሚዳብር ማንነት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፣ ከሐሳብ ይልቅ በዘውግ ፖለቲካ ላይ መሕልቃቸውን ለጣሉ ብሔርተኛ ድርጅቶች መርዶ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ አዲስ አበባ የዘውግ ፖለቲካ ማቅለጫ ጋን (ሜልቲንግ ፖት) ናት፡፡ በአዲስ አበባ ዜጎች በደቦ በሚቧደኑበት ዝግ ማንነት (ቋንቋ እና ዘረመል) ምትክ ከተሜነት በወለደው ሁሉን አቃፊ በሆነ፣ ሥልጡን መስተጋብር እርስ በርሳቸው ሳይነጣጠሉ የተቆራኙ ናቸው፡፡ 

አዲስ አበባን አዲስ አበባ ያደረጋት መሬቷ አይደለም፤ ላለፉት መቶ አመታት የሀገራችን ሕዝቦች በከተማዋ ላይ የፈጠሩት ውስብስብ ማኅብራዊ መስተጋብር ነው፡፡ ይህን መስተጋብር በአንድ ብሔር ጥላ ሥር ለመቀንበብ መሞከር በፖለቲካ ፊት እንደአላዋቂነት የሚያስቆጠር ተግባር ይሆናል፡፡ እርግጥ ነው፣ የአማራና የኦሮሞ ብሔረተኞች፣ በመዲናይቱ ላይ ታሪክ እያጣቀሱ የይገባኛል ጥያቄ እንደሚሰነዘሩ ይታወቃል፡፡ በተለይ ከሰሞኑ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያሉት የኦሮሞ ብሔረተኞች በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ አዲስ አበባን በሚመለከት ያራመዱት አቋም ቆፈን ውስጥ የሚከት ነው፡፡

ምክክሩ ሕወሓት/ኢህአዴግ ለተከለው ከፋፋይ የፖለቲካ ዘረመል የመፍትሄ አማራጭ ያመላክታል ተብሎ ቢጠበቅም፤ የተሳበውን ያህል ርቀት ሳይሄድ እንደቀረ ምልክቶችን ማስተዋል ጀምረናል፡፡ ከዚህ ይልቅ፤ ላለፉት ሦስት ዐሥርተ ዓመታት ሀገረ መንግሥቱን ሲያመሰቃቅል የኖረውን የጎሳ ፌዴራሊዝም የበለጠ ለማጽናት ተሳታፊዎች በብርቱ ሲዋጁ ተስተውለዋል፡፡ አዲስ አበባን ለመቀራመት የቋመጡት የኦሮሞ ብልጽግና ልሂቃን የምክክሩ ጥቅል ግብ በአግላይ የብሔረተኝነት አጀንዳ ዙሪያ ብቻ እንዲቀነበብ ሲታትሩ ታዝበናል ፡ ፡(እዚህ ጋር የምክክሩ ተሳታፊ የነበሩትን የኦሮሞ ብልጽግና ተወካዮች መዲናዋን በተመለከተ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያጋሯቸውን ጦማሮች ዋቢ ማድረግ ይቻላል)፡፡ ይህም አሻጥራዊ ሩጫ በአማራ ልሂቃን ዘንድ ተቀዛቅዞ የነበረው “የበራራ ታሪክ” ዳግም እንዲያንሰራራ ምክንያት ሆኗል፡፡      

”በረራ የእኛ”  እና “ፊንፊኔ ኬኛ” 

የአማራ ብሔርተኞች፤ የአዲስ አበባንና የበራራ ታሪክን ለማስተሳሰር፣ ወደ ኋላ ሩቅ ሄደው በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረውን ኹነት ያጣቅሳሉ፡፡ ይህንን በተመለከተ የኒውጀርሲ ስቴት ዩኒቨርስቲ መምህሩ ፕ/ር ሐብታሙ ተገኝ ሰፊ ጥናት ሠርተዋል፡፡በተለይ በራራ- ቀዳሚት አዲስ አበባ በሚል ርዕስ ለሕትመት ብርሃን ያበቁት መጽሐፋቸው ቀዳሚ ተጠቃሽ መሆን ይችላል፡፡ ጥቂት ከመጸሐፉ፡- 

- Advertisement -


በኦሮሞ ብሔርተኞች የሚቀነቀነው የአዲስ አበባ ታሪክ በፈጠራ የታጀለ ነው፡፡ የአዲስ አበባ የጥንት ስም በረራ ነው፡፡በረራም የኢትዮጵያ የነገሥታቱ ዋና መቀመጫ በመሆን ከአጼ ዳዊት ቀዳማዊ (1380-1413) ጀምሮ እስከ አጼ ልብነ ድንግል (1508-1540) ከመቶ ዓመት በላይ አገልግላለች፡፡ በረራ ወረብ በሚባል አውራጃ ትተዳደር እንደ ነበር የታሪክ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ በ16ኛው ክ/ዘመን ይኖሩ የነበሩ ብዙ የውጭ ሀገሮችን የጎበኙት አባ ዳንኤል የተባሉ ኢትዮጵያዊ መነኩሴ ወረብን በኢየሩሳሌም መስለው ጽፈዋል፡፡


በአንጻሩ የኢምሬት ፕሮፌሰሩ ሙከሪያ ቡልቻ፤ “Greater Addis Ababa in the making: Stop them or Perish” (ታላቂቷ አዲስ አበባ እየመጣች ነው፤አቁሟቸው አሊያም ዝም በሉና ጥፉ) በሚለው ሐተታቸው የተለመደውን የታሪክ ትንታኔ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ የሐተታቸው የጊዜ ምሕዋር የሚሽከረከረው ግን፣ የቅርቡን የ19ኛው መቶ ክ/ዘመንን የታሪክ ውጣ ውረድ ታሳቢ አድርጎ  ነው፡፡ በርግጥ ታሪክን ለትንታኔ ከሚመቸን የጊዜ ውቅያኖስ ጨልፎ መውሰድ አመክኖአዊ አይሆንም፡፡ ለማንኛውም ልኂቁ በከተማዋ ዙሪያ ካሰፈሩት በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል እነሆ፡-

አጼ ምኒልክ ወደ ኦሮሞ መሬት መስፋፋት እንደ ጀመሩ የፊንፊኔን ውብ ሜዳና ሸለቆ ሊያሳይ በሚችለው እንጦጦ ተራራ ላይ ቤተ መንግሥታቸውን መገንባት ነበር፡፡ አንጦጦ በዛን ጊዜ ላልገበረው ፊንፊኔም ሆነ ዙሪያ መለስ ለሚገኙ አካባቢዎች፣ እንደ ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ቦታ የሚያገለግላቸው መሆኑ በንጉሡ ዘንድ ተመራጭ አድርጎታል፡፡ 1880ዎች አጋማሽ ወረራውን በድል ፈጽመው ከእንጦጦ ወደ ፊንፊኔ በመውረድም ቤተመንግሥታቸውን ገነቡ:: የአካባቢውን ስምም ወደ አዲስ አበባ ቀየሩ፡፡ በመቀጠል ምኒልክ በዙሪያቸው ለሰፈሩት መሳፍንት እና ወታደሮች መሬት ሲከፋፍሉና ከተማዋ እየሰፋች ስትሄድ በሺዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ተፈናቅለዋል::

እነዚህን የኋላ ኹነቶች በዚህ ዘመን ላይ ቆሞ የንትርክ አጀንዳ መፍጠር፣ በታሪክ ፊት የዋኽ የሚያስብል ተግባር ነው፡፡ አዲስ አበባ መመዘን ያለባት አሁን ባለው አጠቃላይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማእቀፍ ብቻ ነው:: ታሪክን የኋሊት ተጉዞ ከተማዋ ላይ ያለ ሥሪቷ ባእድ ማንነትን ለመጫን የሚያደረገው ሩጫ ማሳረጊያው ጥፋት እንደሚሆን ለመገመት ሊቅ መሆንን አይጠይቅም፡፡

“ኬኛ” አንብሮ  እና “የእኛ” ተቃርኖ

የ“ኬኛ” እና “የእኛ” ፖለቲካዊ ትርክት አራማጆች የቆሙበት መደላድል ከከተሜ መሠረታዊ ባሕርይ ጋር ፈጽሞ የሚሄድ አይደለም፡፡ ዳር እና ዳር ሆነው የሚጓተቱት እነዚህ ኃይሎች ድጋፋቸው፣ከተሜነት የወለደው ውስብስብ ነባራዊ ሁኔታ ሳይሆን በሩቁ ዘመናት የተከሰቱ ታሪካዊ ኹነቶች ናቸው፡፡ ሽኩቻቸውን ጤናማ ማድረግ ይቻላል፡፡ ቅራኔያቸው ዲያሌክቲካል (የተሻለ ነባራዊ ሁኔታን የሚወልድ ፍጭት) መሆን ከቻለ ግን ውጤቱ መልካም ይሆናል:: “የኬኛ” ትርክት በአንብሮ (thesis) መልክ ማዶ ላይ ቆሞ በሌላ ጫፍ ቆሞ ከሚገዳደረው “የእኛ” ትርክት /antithesis/ ጋር በሚፈጥሩት ሰላማዊ የሐሳብ ፍጭት ሁሉን አቃፊና ሰብሳቢ የሆነው አዲሰ አበቤነት በአስተጻምሮ /synthesis/ ደረጃ መወለድ ለሁሉም የሀገራችን ዜጋ ብሥራት ነው የሆነው፡፡ ይህን ገቢራዊ ለማድረግ ስክነት የተሞላበት የሐሳብ ሙግትን የሚያስተናግድ ከተሜው በበቂ ሁኔታ የሚወከልበት አቃፊ ምህዳር መፈጠር ይኖርበታል፡፡

ማሰሪያ

የቤልጂየሟ ዋና ከተማ ብራስልስ በብዙ ረገድ ከአዲስ አበባ ጋር የሚመሳሰል ታሪካዊ እና ማኅብራዊ ነባራዊ ሁኔታ አላት፡፡ ቤልጄየም በሰሜን 59 በመቶ  ፊሊሚሽ ተብለው የሚጠሩ የደች ተናጋሪዎች ፣በደቡብ ዋሎንስ ተብለው የሚጠሩ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች እና በምሥራቅ 1 በመቶ የሚሆኑ ጀርመንኛ ተናጋሪዎች ውህድ ሀገር ናት፡፡መዲናዋ ብራስልስ የፊሊሚሾች ወይም የደች ተናጋሪዎች ይዞታ እንደሆነች ቢታወቅም የከተማዋ አብዛኛው ነዋሪ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ነው፡፡ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በመጣፍ የሀገሪቱ ልሂቃን የከተማዋን ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ መወስን የሚያስችል አቃፊ ፖለቲካ ሥርዓትን ለመትከል በቅተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ብራስልስ የታሪካዊ ባለቤቶቹ ፊሊሚሾች ( ደች ተናጋሪዎች )በመሆን ፈንታ፣  የነዋሪዎቿ ማለትም የፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ልትሆን ችላለች ፡፡ ይህንን የከተማ ዳይናሚክስ ከኢደስ አበባ አንጻር በቅጡ ከገመገምነው ብዙ ትርጉም የሚሰጥ ተሞክሮን መቅሰም እንችላለን፡፡ 

ብራስልስ የብራስልሳዊያን ናት እንደሚባለው ሁሉ፣ የአዲስ አበባም የባለቤትነት ጉዳይ በዚህ አውድ ውስጥ ነው መበየን ያለበት፡፡ በርግጥ አዲስ አበባ፤ የአዲስ አበቤዎች ነች የሚለው ትርክት ከተተከለው የፖለቲካ ሥርዓት ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ ይኽ እውነታ ሕገ መንግሥታዊ እውቅና ተነፍጎታል፡፡ የሉአላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች  ስለሆኑ፣ ከዚህ ክበብ ውጭ የሆነ በዜግነት ወይም በአዲስ አበቤነት የተገኘ ማንነት የሚስተናገድበት ምንም ማእቀፍ የለም፡፡ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ከዚህ የሕወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓት ውርስ የምንላቀቅበትን የተሻለ ምክረ ሐሳብ ይዞልን ይመጣል ብለን ስንጠብቅ፤ጭራሽ ያለውን ሥርዓት የሚያጠናክር ጉንጭ አልፊ ንትርክን ለአውደ ርዕይ ሊያቀርብልን ችሏል፡፡

በጥቅሉ የምክክሩ ተሳታፊዎች  በብሔር ፌደራሊዝም እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ያስተጋቧቸውን አቋሞች  ከግምት ከጣፍን ፖለቲካችን አሁንም በሕወሓት/ኢህአዴግ የሙት መንፈስ እየተመራ እንደሆነ ይገባናል፡፡ ሕወሓት ሕያው ነው፡፡ ተሸንፎ መቀሌ ቢገባም የተከለውን ሥርዓት የሚቀናቀን የልሂቃን ስብስብ ወይም የፓርቲ መስመር በብልጽግና ውስጥ በአጥጋቢ ደረጃ እንዳልጎለበተ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ እውነተኛ የአዲስ አበቤነት መንፈስ ወይም የዜግነት ፖለቲካ ከበባውን ሰብሮ እንዲወጣ ከተፈለገ፣ ተቋማዊ ዋስትና ያለው፣ የሐሳብ ሙግት የሚያስተናግድ የተለቀቀ ምህዳር ለከተማዋ ነዋሪ ሊመቻችለት ይገባል፡፡ወደፊትም ቢሆን፤ የመዲናዋ ዕጣፈንታ ከከተማ ሥነልቦና ጋር በሚቃረኑ የክፍለሀገር ልሂቃን እጅ ላይ እስከወደቀ ድረስ ከችግሩ አዙሪት(vicious circle) የምንወጣበት ዕድል በእጅጉ የተመናመነ ይሆናል፡፡

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena 

2 COMMENTS

  1. አቶ ዸረጀ ይመር

    ገብተዉ መፈትፈት የጀመሩት በማያውቁት ታሪክ ነው፡፡ ታሪክ አዋቂ ከሆኑ ትክክለኛው ታሪክ የቱ እንደሆን ይንገሩን፡፡ ዶ/ር ሐብታሙ ብዙ ምርምር አድርገውና በመረጃ እያስደገፉ ጽፈዋል፡፡ የጻፉት ስህተት ከሆነ እንደርሳቸው ጽፈው በመረጃ ያሳዩን፡፡ ፊንፊኔ የኦሮሙ መሆንኑ የሚያሳይ ታሪካዊ መዝገብ አንድም አላየንም፡፡ ካላ ያሳዩን፡፡ አለዚያ በማያውቁር ነገር ገብቶ መፈትፈት ወይም መካሪና አስታሪቅ መምሰል የእብድ ገላጋይ ወይም አለሁ ባይ ያሰኛል፡፡ መስሎት ነው እንጅ እንደዚህ አይነቱ ግልብ አስተሳሰብ ወይም ማለባበስ ሰላም አያመጣም፡፡

  2. አቶ ዸረጀ ይመር

    ገብተዉ መፈትፈት የጀመሩት በማያውቁት ታሪክ ነው፡፡ ታሪክ አዋቂ ከሆኑ ትክክለኛው ታሪክ የቱ እንደሆን ይንገሩን፡፡ ዶ/ር ሐብታሙ ብዙ ምርምር አድርገውና በመረጃ እያስደገፉ ጽፈዋል፡፡ የጻፉት ስህተት ከሆነ እንደርሳቸው ጽፈው በመረጃ ያሳዩን፡፡ ፊንፊኔ የኦሮሞ መሆኑን የሚያሳይ ታሪካዊ መዝገብ አንድም አላየንም፡፡ ካላ ያሳዩን፡፡ አለዚያ በማያውቁት ነገር ገብቶ መፈትፈት ወይም መካሪና አስታሪቅ መምሰል የእብድ ገላጋይ ወይም አለሁ ባይ ያሰኛል፡፡ መስሎት ነው እንጅ እንደዚህ አይነቱ ግልብ አስተሳሰብ ወይም ማለባበስ ሰላም አያመጣም፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News