Homeነፃ አስተያየትኦሕ Dead ምን ላይ ነው? በአዲስ አበባ አይግረማችሁ! (ክፍል ፪)

ኦሕ Dead ምን ላይ ነው? በአዲስ አበባ አይግረማችሁ! (ክፍል ፪)

Advertisement
World Wide Travel Group


                                           

ክፍል ፪

በአቶ ሙሉዓለም ገብረመድኀን

ከሚውጠው በላይ የሚያላምጠው ኦሕዴድ
እና ቀጣናዊ ሁኔታዎች …

የኦሕዴድ ብልጽግና ኢምፓየር ዕቅድ የኢትዮጵያን ‹state formation› እንደገና የመከለስ፣ የመሸንሸን፣ የመፐወዝ ፕሮጀክት ነው፡፡ ኦሕዴድ በአፉ ‘ኢትዮጵያ’ ቢልም፣ በኦሮሚያ ‹state formation› ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት ላይ ነው፡፡ ቡድኑ የሁለት ሀገረ መንግሥት መንታ ልብ ነው ያለው!

ከራሱ ኃይል ውጭ ሌሎች ኢትዮጵያውያን እና የአገር-ግዛቶቻቸውን ከኦሕዴድ ብልጽግና የግዛት ፍላጎት የሚተርፉ ጥቅም አልባ የማድረግ ፖለቲካዊ ፍላጎት አለው፡፡
እነ ዐቢይ አህመድ ይዘውት ያለው የፖለቲካ ፕሮጀክት ከሌሎች ክልሎች ተነጥቀው ወደኦሮሞ በሚጠቃለሉ ግዛቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ የፖለቲካ ፍላጎት፦ ከኢትዮጵያ አጎራባች የሆኑ አገራት ለምሳሌ ሶማሊያ፣ ሶማሌላንድ፣ ጅቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን ፣ እና ሌሎችም ጋር ከኢትዮጵያ አንፃር ሳይሆን ከኦሕዴድ ብልጽግና ኢምፓየር አኳያ በሚኖራቸው ፋይዳና ተጎራባችነት የማመቻቸት ማለትም የመስፋፋት፣ የመጠጋጋት እና የመጠቅለል ፖለቲካ ይዘው እየሰሩ ነው።

በመሆኑም ስጋትነታቸው ለኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ለቀጠናው ጭምር ነው፡፡

በዚህ የማይወሰነው ይህ ኃይል፣ ኤርትራን ‘ባሬንቱ ኬኛ’ ይል ጀምሯል። በባህር በር ስም በኤርትራ ላይ ሊከፍት ያሰበው የጦር ወረራ፣ ወታደራዊ ዝግጅቱ ከአገራዊ ራዕይ አንጻር ሳይሆን፣ ከሚያልመው የሥልጣን ኢምፓየር ፍላጎት፣ ከጦረኛ ፖሊሲው የሚመነጭ ጉዳይ ነው፡፡

ይህ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የክፍለዘመኑ የተለየ ገጠመኝ ነው፡፡ ይህ አድማሳዊ ቀውስ ከኦሕዴድ ብልጽግና የሀገር-ምስረታ ፍላጎት የሚነሳ በኢትዮጵያ እና በቀጣናው ላይ የኢምፓየር ዓላማ ያለው ፕሮጀክት ነው፡፡

ይህን ለማሳካት ክልሎችን ከማስገበር አልፎ የአካባቢውን አገራት በኦሕዴድ ብልጽግና ሰዎች የመቆጣጠርና የመከታተል ስምሪቶቹ ለዚህ ዓላማው አስረጅ ሆኖ ይቀርባል፡፡

➽ ኬንያ ላይ ባጫ ደበሌ (ኦሮሞ)

➽ ጅቡቲ ላይ ለገሰ ቱሉ (ኦሮሞ)

➽ ሶማሊያ ላይ ሱለይማን ደደፎ (ኦሮሞ)

➽ ደቡብ ሱዳን ላይ ነቢል መሀዲ (ኦሮሞ)

➽ በኡጋንዳ እነ ሜጀር ጀኔራል ኩምሳ ሻንቆን
በወታደራዊ አታሼነት በመመደብ፣ በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አገራት በፖለቲካና ወታደራዊ አታሼነት ስም የራሱን ሰዎች አሰማርቶ የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያው አድርጓቸዋል፡፡

እንዲህም ሆኖ አገር መምራት ባለመቻሉ ዲፕሎማሲያዊ ቀውሶችን አስከትሏል፡፡ የአገዛዙ ኪሳራዎች ዘርፈ ብዙ ቢሆኑም ሁለት ዐበይት ጉዳዮችን እንመልከት፡-

❶. ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት
የላትም

ከኤርትራ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ ጋር በኃይል ፉክክርና በጣልቃ ገብነት የተሞላ፤ ሰላም የራቀውና የተረበሸ ሁኔታዎች ይታያሉ።

ደቡብ ሱዳን በጋምቤላ በኩል፤ ሱዳን በአማራ በኩል የኢትዮጵያን ግዛት በኃይል ወርረው ይዘዋል፡፡

ኬንያ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ድክመት ከፍተኛ ቀጣናዊ ብልጫ ይዛ የአካባቢው ተመራጭ አገር ‹East Africa’s diplomatic and business centre› ሆናለች፡፡

❷. ከጎረቤት አገራት ጋር ወደጦርነት የሚያስገባ አደገኛ
ጣልቃ ገብነት አለ

በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ዐቢይ አሕመድ ለአንድ ወገን አድልቶ በጎረቤት አገር የውስጥ ጉዳይ እጁን አስገብቶ የጦርነት ተዋናይ ሆኗል፡፡ ይህ የሆነው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ሳይሆን ከተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች ፍላጎት በሚነሳ ነው፡፡

130 ሚሊየን ሕዝብ ያላት በአፍሪካ ሁለተኛ ግዙፏን አገር የመምራት ዕድል እጁ ላይ የገባው ዐቢይ አሕመድ ዋነኛው የኢሜሬቶች የንጉሣዊ ቤተሰብ አገልጋይ ሆኖ በሱዳን ቀውስ ውስጥ እጁን አስገብቶ ይገኛል፡፡

በአገር ውስጥ የገጠመውን የቅቡልነት ቀውስ በተለይም የአማራ ሕዝብ የኀልውናን ትግል ለመቀልበስ መሳሪያም ሆነ ገንዘብ ለመለመን ‘የአረብ ቅምጥ’ ሆኖ የአካባቢው አገራትን በመረበሽ የእጅ አዙር ጦርነቶችን እንደሚያስቀጠል፣ የሱዳን ቀውስም ከዚህ በከፋ ሁኔታ እንደሚቀጥል ይገመታል፡፡

ሶማሊያ በዐቢይ አሕመድ የሉዓላዊነት ትንኮሳ (2024) በመበሳጨት፡- ግብጽ ላለፉት አርባ ዓመታት ሞክራው ያልታሳካለት ወታደራዊ ስምሪት በሶማሊያ ቀንቷታል፡፡ ይህም የአገዛዙ ቀጠናዊ ውድቀት የካይሮን የከበባ ስትራቴጂ ሙዝ የመላጥ ያህል ቀላል አድርጎላታል፡፡

አጠቃላይ በዚህ ዘመን እንደአገር የነበረን ቀጠናዊ ተሰሚነታችን ጠፍቶ፣ ኢትዮጵያ ጎረቤቶቿን በጥባጭ አገር ተደርጋ እየተሳለች ነው።

የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ዘንድ የነበራት ተጽዕኖ ወደዜሮ ወርዷል።

ኦሕዴድ ብልጽግና ባልተጻፈ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው፡- በኤርትራ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ ላይ የሚራምደው የጣልቃ ገብነት ፖሊሲ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ በሆነች አገር ገዥው ፓርቲ በሕብረቱ አባል አገር ላይ አመጽን የትግል ስልቱ ያደረጉ ኃይሎችን በይፋ ሲደግፍ መታየቱ ለቀሪ አባል አገራቱ መልዕክቱ ‹ግጭት ደጋሽነት› ነው፡፡

በተለየ ሁኔታ በኢጋድ አባል አገራት ቀጠና፡- በአግባቢነት ስራ፣ ሰላምን በሚያረጋግጡ ተልዕኮዎች፣… ላይ በመሳተፍ አርዓያ መሆን የሚገባትን አገር (ኢትዮጵያን) የሚመራው የኦህዴድ አገዛዝ የራሱን ፍላጎት በሱዳን (RSF እና SPLM-N በመደገፍና በማስታጠቅ) በኤርትራ (ከ10 በላይ የታጠቁ እና የንቅናቄ ቡድኖችን በመደገፍና ማደራጀት) በሶማሊያ (ሶማሌላንድን ገንጥሎ ዕውቅና በመስጠት ሂደት) የግዛት አንድነቷን አደጋ ላይ በመጣል የቀጠናው ረባሽ ሆኗል፡፡

‹ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ የሚሰጥ› የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አለኝ የሚል አገዛዝ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ሰፊ መስተጋብር ያላቸውን ጎረቤት አገራት ሉዓላዊነት የሚንድ፤ ጸረ-ሥርዓት እንቅስቃሴን የሚደግፍ ሆኖ መገኘቱ ዲፕሎማሲያዊ ውድቀቱን አጉልቶ ያሳያል፡፡

ወሳኝ የሚባሉ ዓለማቀፍ ተቋማት፣ በደህንነት ስጋት መቀመጫቸውን ከአዲስ አበባ ወደናይሮቢ ኬንያ እያዞሩ ይገኛል፡፡

ይህ ሁሉ ውድቀት የዲፕሎማሲ ቀውሱ የወለደው፤ የአገዛዙ ኪሳራዎች ናቸው፡፡ይህ ሁሉ ውድቀት ከሚውጠው በላይ በሚያላምጠው ኦሕዴድ ጦረኛ ፖሊሲ የተነሳ ነው።

አጠቃላይ ሰሜን ኢትዮጵያን የጦርነት አውድማ በማድረግ ሌላ ዳርፉር በመፍጠር፣ ደቡብን ከአምስት በትኖ ሊውጥ ያሰፈሰፈ፣ የምስራቁ በር ከሆነው ከሶማሌ ጋር አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በሚሻገር ወሰን ከ 400 በላይ ቀበሌ የተፋጠጠ፣ ከምዕራቡ መስኮት ቤኒሻንጉል ጉምዝ አንድ ሙሉ ዞን (ካማሽን) ሊጠቀልል የሚያሳድድ፣ አሶሳ ላይ የሚያዛጋ፣ መተከል ላይ ዐይኑን የተከለ፣ የደቡብ-ምዕራብ አቅጣጫ ተዋሳኝ ጎረቤቶቹን ልዋጣችሁ በሚል የሚያስበረግግ፣ ቀይ ባህርንም፣ ፖርት ሱዳንንም በርበራንም እኩል የሚያልም፣ መስፋፋቱን ያልጨረሰ፣ የቀውስ ነጋዴ፣… ነው!!

አዲስ አበባን “ከበናታል” ሲል በኢትዮጵያዊያን መከበቡን የዘነጋ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ የገዛ ሕዝቡን (የኦሮሞን) አንድነት ያናጋ፣… የግጭት ትርክት አምራች፣… መውረስ እንጂ መስራት የማያውቅ፣ ለድርድር ሲቀመጥ አቻነትን ሳይሆን የአቻዎች አውራነትን የሚያልም፣ mine is mine and yours is negotiable ባይ ስግብግብ የፖለቲካ ኃይል ነው…!!

ባለፉት ስምንት ዓመታት የታየው እውነታ ኦሕዴድ ብልጽግና ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በቀጣናው ላይ ላሉ አገራትም ስጋት መሆኑን ነው፡፡

ይህ አገዛዝ ለዓላማው ማስፈጸሚያ አድርጎት በሚከተለው የጦርነት ፖሊሲ አጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔረሰብ በዚህ አስከፊ አገዛዝ በተናጠል ከመበላት አይድንም፡፡ ቀጠናውም አሁን ካለበት የቀውስ ምዕራፍ ወደከፋ ሁኔታ ይሻገራል።

ዘላቂው መፍትሔ ይህን ኃይል ከራሱ ውስጣዊ አቅም ጭምር ባሳተፈ መልኩ ነቅሎ መጣል ነው!!

__

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News