Homeነፃ አስተያየትሃይማኖታዊ እምነት የሴራና የሸፍጥ ፖለቲካ ተውኔተ ጉባኤ ሰለባ ሲሆን!

ሃይማኖታዊ እምነት የሴራና የሸፍጥ ፖለቲካ ተውኔተ ጉባኤ ሰለባ ሲሆን!

Advertisement
World Wide Travel Group
ሃይማኖታዊ እምነት የሴራና የሸፍጥ ፖለቲካ

ጠገናው ጎሹ

ይህንን ሂሳዊ አስተያየት በሃተታ መልክ ከማቅረብ ይልቅ ሃሳቤን በአጭሩ በሚገልፅና የሚያነብ አንባቢም ሃቁን በራሱ ግንዛቤና አረዳድ መርምሮ መልስ ሊሰጥበት በሚችልበት ጥያቄያዊ አቀራረብ ያቀረብኩት መሆኔን እየገለፅኩ ወደ የርዕሰ ጉዳዬ ነጠቦች  ልለፍ።

ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው የሚለው መርህና ህግ ሁለቱም ለየራሳቸው የተሰጠ የሃላፊነትና የአሰራር ድንበር ስላላቸው  አንደኛው በሌላው ሃላፊነትና አሰራር ጣልቃ ልግባ ሲል የሚፈጠረው ሥርዓተ አልበኝነት ስለሚሆን እንጅ ሁለቱንም የሚያገናኝ ጉዳይ የላቸውም ማለት እንዳልሆነ የፖለቲካ እውቀት ሀሁ መሆኑን የማይረዳ ፊደል ቆጣሪ ይኖር ይሆን?

መንግሥት በሃይማኖት ስም የሚፈፀምን ወንጀል ወይም የግልም ሆነ የማህበረሰብ መብት ጥሰት የሃይማኖት ጉዳይ ነው በሚል ማለፍ ወይም ከምር አለመውሰድ እንደሌለበት ሁሉ የሃይማኖታዊ እምነት ተቋማትም እንኳንስ በእረኝነት እንዲጠብቁት የተሰጣቸውና እንደየራሳቸው ሥርዓተ እምነት የሚመሩት ተከታያቸው ማነኛውም ሰብአዊ ፍጡር የመንግሥት (በተለይም የእኩያን ገዥዎች) የመከራና የውርደት ዶፍ ሰለባ  ሲሆን የመንግሥት/የፖለቲካ ጉዳይ ነው በሚል ሰንካላ ሰበብ ባይቆጡና ያገባናል ከማለት አልፈው አስፈላጊም ከሆነ መስዋእትነትን ሊያስከፍል እስከሚችል ደረጃ ድረስ ለመሄድ ወኔው ቢከዳቸው የእረኝነታቸው ምንነትና  እንዴትነት ከባድ ጥያቄ ላይ የመውደቁ መሪር እውነታ ይገርመን ይሆን?

ታዲያ በኮሚሽን ተብየው ተውኔተ ጉባኤ ላይ እንዲታደሙ  የተጋበዙ/የተመለመሉ የዛሬዎቹ የእኛ የሃይማኖታዊ እምነት መሪዎች፣ ምሁራንና ሰባኪዎች  እኩያን ገዥዎችን ሲሆን የ8 ዓመታት ሁለንተናዊ መከራን ታሳቤ ባደረገና ባልዘገየ አቀራረብ እና ቢያንስ ግን “ምክክር ተብየው የመከራና የውርደት ቀንበራችሁን ከመከረኛው ህዝብ ላይ ለማንሳትና ብሎም እውነተኛ፣ ፅዕኑና ዘላቂ የሆነ ህልውና፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ መከባበር፣ አንድነት፣ ሰላምና የጋራ ልማት/እድገት የሚረጋገጥበትን ሥርዓት እውን ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ እየተካሄደ ስላልሆነና ይህ ደግሞ ከተከታዮቻችን አልፎ  በእረኝነት የሾመንን/ያሾመንን ፈጣሪን ጨምሮ በእጅጉ ማስቀየም ነውና ለማቋረጥ እንገደዳለን”  የማለት ወኔ/ህሊና ሲከዳቸው መታዘብ ለዘመናት ከመጣንበትና አሁንም ተዘፍቀን ከምንገኝበት ውድቀት አንፃር ባያስገርምም በእጅጉ አያስፈራም?

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

የትኛውንም ሃይማኖታዊ ስብከት፣  ጥቅስ፣ ዝማሬ፣ እግዚኦታ፣ ፆምና ፀሎት ፣ ወዘተ ብናዥጎደጉድ መከረኛው የአገራችን ህዝብ ለዘመናት ከኖረበት (መኖር ከተባለ) እና ከ8 ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ  ከሚገኝበት የምድር ላይ ሲኦል ግዙፍና መሪር እውነታ ጋር እያገናኘን በመማር፣ በማስተማር እና የተሳካ (ትርጉም ያለው)  ህይወትን ለመኖር በሚያስችል ሁኔታ ካልተጠቀምንበት በስተቀር  ከመከራና ከውርደት ሰብሮ መውጫ መንገዱ የትኛው ነው? ይህንን ግዙፍና መሪር ሃቅ የሰበብ ድሪቶ እየደረትን ዙሪያውን በመዞር ወይም በመሸሽ የምንወርሰው ሰማያዊ ህይወት/ገነት/ከሞት በኋላ ህይወት ይኖራል እንዴ? ከሞት በኋላ ህይወት መውረሻው ከትውልድ፣ በትውልድና ለትውልድ የሆነንና የሚሆንን በጎ ሥራ (መልካም አገር) እየሠሩ ማለፍ ካልሆነ ባዶ (ድርጊት አልባ) የእናምናለን መነባንብና ትውፊታዊ ትዕይንት በራሱ እንዴት ሊሆን ይችላል?

 የሃይማኖታዊ እምነት መሪነት፣ ሊቅነት/ምሁርነት፣ ሰባኪነት፣ አገልጋይነትና አማኝነት/ተከታይነት የማይናወፅ ምንነት ፣ ማንነት፣ ለምንነት፣ እንዴትነትና ወዴትነት መሠረታዊ መገለጫው ዘመናትን ያስቆጠረውና በአሁኑ ወቅት ደግሞ የምንገልፅበት ቃል እስከሚቸግረን ድረስ አስከፊ ሆኖ የቀጠለው የእኩያን ገዥወች ጨካኝ ሰይፍ  ሰለባ እየሆነ ያለውን መከረኛ ህዝብ ለመታደግ ካልሆነ ሌላ ምንና ለምን  ሊሆን ነው? 

ክርስቶስ ምስኪኖች በነበሩበት ቦታና ሁኔታ  ሁሉ እየተዘዋወረ ያስተማረው፣ የግፍ ገዥዎችን “ህዝቤን ልቀቁ” ብሎ የገሰፀው/የተቆጣውና በመጨረሻም በግፈኞች እጅ የቁም ሰቆቃን ተቀብሎና መስቀል ላይ ተሰቅሎ የነፍስም ሆነ የሥጋ መዳኛ/ዋስትና ስለሆነው እውነተኛነት፣ ቅንነት፣ ሰላም፣ ፍቅርና የጋራ ህይወት ስኬት ያሳየን ይህንኑ ጥልቅና ፈታኝ ጥያቄ በብቃትና በፅዕናት እየመለስን ለነፍስም ሆነ ለሥጋ የሚበጅ ህይወትን ለመኖር እንድንችል አይደለም እንዴ?

 ክርስቶስ ያስተማረው፣ የፆመው፣ “አባት ሆይ” ብሎ የፀለየው፣ በየበርሃው፣ በየሸንተረሩ፣ በየተራራው፣ በየመንደሩ ፣ እና በአጠቃላይ በክፉ ገዥዎች  የመከራ ቀንበር ሥር የሚማቅቁ ምስኪኖችን እያፅናና በማስተማር እና ክፉ ገዥዎችንም “ህዝቤን ልቀቁ” ብሎ እየገሰፀ/እያወገዘ በመጨረሻም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ፍቅርና ሰላም የሚያስከፍሉትን ዋጋ አሳየን  እንጅ እንደ ዛሬው የእኛ እረኝነት/የሃይማኖት አባትነትና ሰባኪነት ራሱን መሬት ላይ ካለው መሪር እውነታ ጋር በማይገናኝ የስብከት፣ የፆምና ፀሎት፣ የዝማሬ፣ የእግዚኦታ፣ ወዘተ ግብዝነት ፈፅሞ እንዳልነበረ ለመረዳትና ለማስረዳት መሠረታዊ እውቀትን እንጅ የተለየ ሊቅነትን ይጠይቃል እንዴ?

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ለመሆኑ ለዘመናት ያሰማነውና እያሰማነው ያለነው እግዚኦታ፣ የፀለይነውና እየፀለይን ያለነው ፀሎት  ፣ የዘመርነውና እየዘመርን ያለነው ዝማሬ፣ የፆምነውና እየፆምን ያለነው ፆም፣ ያካሄድነውና እያካሄድን ያለነው ሱባዔና ምህላ፣ ዓለም ተደነቀ በሚል ያካሄድነውና እያካሄድን ያለነው ክብረ በዓል፣ በየአዳራሹና በየመናፈሻው የታደምንበትና እየታደምንበት ያለው የሃይማኖታዊ እምነት ሙዚቃዊ ትርኢት፣ በየመስጊዱ ያስቆጠርነውና እያስቆጠርነው ያለው ሶላት/ስግደት፣ ወዘተ ዘመን ጠገብ ከሆነው ፣ እጅግ አስከፊ ሆኖ እየቀጠለ ካለውና ከሰብአዊ ፍጡርነት በታች እያዋለን ካለው የመከራና የውርደት ዶፍ ያልታደገን ለምንና እንዴት እንደሆነ ከምር ጠይቀን እናውቃለን?

መልሳችን “አዎ ጠይቀን እናውቃለን” ከሆነ ታዲያ ይህንን በማለታችን ያገኘነው ትክክለኛ መልስ ምንድን ነው? አዎ ካልሆነ ደግሞ ታዲያ የሃይማኖታዊ እምነት እሴትነት እንዲህ አይነት ሰፊ፣ ጥልቅና ፈታኝ ጥያቄዎችን በአግባቡ፣ በአጥጋቢነትና በዘላቂነት ለመመለስ ካላስቻለን ሌላ ምን ?

እንደዚህ አይነት ጥያቄዎችን የተግባርና የቃል ውህደትን መሠረት ባደረገ አቀራራብና ይዘት ለማስተናገድ የማያስችል የሃይማኖታዊ እምነት መሪነት/እረኝነት/ምሁርነት/ ሰባኪነት እና አማኝነት የትም እንደማያደርስ በግልፅና በቀጥታ መናገርና መነጋገር የፅድቅ እንጅ የኩነኔ/የእርግማን መንገድ ነው እንዴ? በእንዲህ አይነት እውነታ ላይ መናገርንና መነጋገርን የሚከለክልና የሚቆጣ አምላክ (ፈጣሪ) አለ እንዴ? ወይንስ እኛው ራሳችን ከመሪሩ እውነታ ለመሸሽ የሰበብ ድሪቶ እየደረትን በራሳችን አእምሮ ላይ የምናሳርፈው የፈሪነትና የአስመሳይነት መንፈስ  ነው ያስቸገረንና የእኩይ ገዥዎች ሰለባዎች ያደረገን?

የሃይማነታዊ እምነት  መሪዎች ወይም ምሁራን ወይም ሰባኪዎች ሁሉን አቀፍና አሳታፊ በሆነ ፍኖተ መፍትሄ እውን መሆን ያለበትን ነፃነትና ዘላቂ ሰላም ከማዋለድ ይልቅ ባርነትንና መከራን ለማረዘም በተፈጠረና ተልእኮ በተሰጠው ኮሚሽን ተብየ ተውኔተ ጉባኤ ላይ መገኘታቸው ሲያሳዝነን ሴረኛና ሸፍጠኛ ገዥ ቡድኖች በፈለጉት መንገድ የስብሰባ ጉልቻነት ማሟያዎችና የርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ አሻንጉሊቶች ሲያደርጎቸው መታዘብ  ህሊናውን የማይረብሸው  የሃይማኖታዊ እምነት ተከታይ/አማኝ ለምንና እንዴት ብሎ መጠየቅን እንደ ሃጢአትና እንደ ነውር የሚቆጥር ከሆነ  አማኝነቱ የማስመሰልና የዘልማድ ነው ቢባል እውነት እንጅ ውሸት ይሆናል እንዴ?

- Advertisement -

የጨካኝ ገዥዎች የካድሬነት ደዌን በተሸከመ ፣ የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካን በክቡር/ቅዱስ መስቀል “በሚባርክ” እና የሃይማኖታዊ እምነት ተልእኮውን የመከረኛውን ህዝብ መከራና ውርደት ለማሳጠርና እውነተኛ እፎይታን እውን ለማድረግ የሚታገሉ  ወገኖችን በሰላምና በራሱ በፈጣሪ ስም  ጠልፎ  የእኩያን ገዥዎች ሰለባዎች ለማስደረግ  የተካሄደውንና እየተካሄደ ያለውን የሃይማኖታዊ እምነት መሪዎችና ሰባኪዎች ያልተቀደሰ ተልእኮ እውን ከምር  ለማወቅና ለመረዳት ሞክረን የምናውቅ ስንቶቻችን እንሆን?

ፈጣሪ ከረቂቅ የማሰቢያ አእምሮና ከብቁ የማከናወኛ አካል  ጋር ፈጥሮና ለዚሁ የምትመች ምድርን አዘጋጅቶ በሰላም፣ በነፃነት፣ በመከባበር፣ በመተሳሰብ ፣በመረዳዳት  እርሱን (ፈጣሪን) እያመሰገንና የማያቋርጥ እርዳታውን  እየጠየቅን እንደ ሰው ሰው እና እንደ ዜጋ የመልካም አገር ባለቤቶች ሆነን መኖር ሲገባን በመሬት ላይ ያለው እኛነታችንና እንዴትነታችን ግን የአስመሳይነት፣ የአድርባይነት፣ የእኩይ ፖለቲካ አሽቃባጭነት፣ የመርጦ አዛኝነት/አልቃሽነት፣ የመርጦ ድግስ/ሰርግ አድማቂነት፣ የፍርሃት ልክፍተኝነት፣ እና በአጠቃላይ የሰው ባህሪ የሚያስከትለው ፈተና  ነው ከሚባለው በላይ በከፋ አኳኋን የወደቅነውና እየወደቅን ያለነው ለምንድን እንደሆነ ከምር ጠይቀን እናውቃለን?

እናም ከዚህ አይነት ዘመን ጠገብና እያደር በእጅጉ እየተሸረሸረ ከሄደው የድርጊት አልባነት፣ የአስመሳይነት፣ የአድርባይነት፣ የግብዝነት፣ የነጋዴነት፣ እና ትውልድን ያለመታደግ የሃይማኖታዊ  እምነት መሪነት፣ ሰባኪነት፣ ተከታይነት በአስቸኳይ ለመላቀቅና ወደ ትክክለኛው ፍኖተ ህይወት ለመመለስ እልህ አስጨራሽ የጋራ ጥረት ማድረግን ግድ ይለናል ። ለፍቶና ጥሮ አዳሪው መከረኛ ህዝብ  የእኩያን ገዥዎች ጨካኝ ሰይፍ ሰለባ ሲሆን  ሰማእትነትን በሚጠይቅ ደረጃ ይቅርና  ከምር ለመቆጣት እና ነውር ነውና በቃ ለማለት ወኔው እየከዳን በተቸገርንበት መሪር እውነታ ውስጥ የምናዥጎደጉደው ስብከት፣ ጥቅስ፣ ሰማእትነት፣ ፃድቅነት፣ ዝማሬ፣ ፀሎተ ሃይማኖትና ፆመ ድነት፣ ወዘተ የውስጠ ነፍስ እሴትነት የለውምና ፈጥነን ራሳችንን በመጠየቅ ትክክለኛውን የመዳኛ ፍኖተ ህይወት ፈልገን ማግኘት ይኖርብናል ።

ያ መንገድ ደግሞ  ክርስቶስ ያሳየን የአርነትና የጋራ ብልፅግና  መንገድ ነው።መከረኞችን የማፅናናት፣ የመደገፍና የመታደግ እና በነፃነት ፣ በፍትህ ፣ በሰላምና በመተሳሰብ መኖር የሚችሉበትን ፍኖተ ሥርዓት የማሳየትና ለድል የማብቃት መንገድ ነው። አዎ! ክፉ/እኩያን ገዥዎችን  “መከረኛ ህዝባችንን/ወገናችንን ልቀቁት!” የሚል የሃይማኖታዊ እምነት የአርበኝነት ተጋድሎ  መንገድ ይኸው ነው!

ዋናው ችግር/ፈተና ሃይማኖትታዊ እምነትን የእውነተኛ (የቃልና የሚጨበጥ ተግባር መፍለቂያና ማሰራጫ) ከማድረግ ይልቅ የፍርሃት፣ የአስመሳይነት፣ የአድርባይነት፣ የነጋዴነት/የቢዝነስ አሳዳጅነት ፣ የሙስና፣ የአጭበርባሪነት፣ የዘልማድ ጥገኝነት ፣ ወዘተ መደበቂያ/መመሸጊያ የማድረግ አደገኛ ሁኔታ ነው። እርግጥ ነው በትክክል ብንጠቀምበት የሰው ልጅ የጨካኝ አውሬነት ባህሪው ተገዥ እንዳይሆን የሚጫወተው ሚና በዋጋ የሚተመን አይደለም (it is priceless) ለዚህ ነው እኛም በዚህ ረገድ ያለብንን ፈተና ከመሪሩ የገሃዱ ዓለም ግዙፍና መሪር እውነታ ጋር እያመሳከርንና ተጨባጭ ከሆነ ውጤት አንፃር እያስተያየን ካልተጠቀምንበት አሁን በምንገኝበት አያያዛችን ለዛሬው ብቻ ሳይሆን ለነገው እጣ ፈንታችን የበለጠ አደጋነት አለውና ዛሬውኑ ተገቢውን እርምጃ እንውሰድ ብሎ መናገርና መነጋገር ከትክክልም ትክክል የሚሆነው።

  ከኮሚሽን ተብየው ተውኔተ ጉባኤ ሂደትና ውጤት የተረዳነው መሪር ሃቅም ይህንኑ በግልፅ የሚያሳይ ነው ።

እናም  የምንወስደው እርምጃም የሃይማኖታዊ እምነትን ጨምሮ ሁሉንም የሰው ልጆች/ዜጎች ነፃነትና መብት የደፈጠጠውንና እየደፈጠጠ ያለውን የእኩያን አገዛዝ አስወግዶ የጋራ የሆነች ዴሞክራሲያዊት አገርን አምጦ የመውለድ ታሪካዊ/ትውልዳዊ ሃላፊነት ነውና ልብ ያለው ልብ ይበል!

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena 

1 COMMENT

  1. Whenever I Ethiopian elite tries to invoke religion of God on the suffering of our people. The thing that comes to my mind is a statement by an American lady asked where God was on September 11! She said “he was standing behind looking because we have already told him we don’t want him in our Affairs” that’s what our list did since the 1960 Revolution. They tried to destroy religion in our country by attacking the believers for years. Now some of them become religious leaders.(pretend to be.) . how can they stand for the truth or for the people that is a great problem

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News