
በሲሳይ ሙሉ (ዶ/ር)
መግቢያ
የአፋብን እና የህወሓት ጥምረት ጉዳይ በተመለከተ የሚደረጉ ክርክሮች አብዛኛውን ጊዜ በታሪካዊ ቁስሎች እና በስሜታዊ ቅሬታዎች ላይ የተንተራሱ ናቸው። የአማራ ሕዝብ በህወሓት የተፈፀመበት መዋቅራዊ በደል፣ የዘር ፍጂት፣ መፈናቀል፣ የአስተዳደር በደል እና የእርስት እና ማንነት ነጠቃዎች ዛሬም ድረስ ያልሻረ ቁስል ነው። እነዚህ ጠባሳዎች እውነተኛ እና አሁናዊ ሀቆች ከመሆናቸው አንጻር የትኛውም በሳል የፖለቲካ ውይይት የአማራ ሕዝብ ይህንን መራራ ሀቅ እንዲረሳው ከመጠበቅ መነሳት የለበትም።
ሆኖም ግን የታሪክ በደል እና ቅሬታ ብቻ አንድ ፖለቲካዊ ወይም የትጥቅ ትግል ጥምረት ለመፍጠር ብቸኛ መስፈርት አይደለም። የበፊቱን በደል የሚያካክስ ጥምረት ከተፈጠረ እና ታሪካዊ ጠባሳዎችን በዘላቂነት እንዲሽሩ ለማድረግ ሚያስችል መንገድ ከተሰራ ጥምረቶች እንደሁኔታው እየተፈተሹ ቅቡልናቸው ሊመዘን ይችላል። ስለዚህ ከታሪካዊ ዳራዎች በተጨማሪ የፖለቲካ ጥምረትን ስናስብ ሚዛን ሚደፋው ጥያቄ «ቀደም ሲል ማን ማን ላይ በደል ፈፀመ?» ብቻ አይደለም። «ዛሬስ እያንዳንዱ ወገን ከጥምረቱ ምን ያተርፋል? ምንስ አሳልፎ ይሰጣል? የዛሬው ችግር አልፎ ነገ ሌላ የፖለቲካ መድረክ ላይ ሲደረስ ይሄ ጥምረት ይጸናል? ማን ምን ድረስ ነው አብሮ ሚሄደው? በጥምረቱ የበላይነት ድርሻ የሚኖረው ማን ነው?» በሚሉት ጥያቄዎች ላይ ተመስርቶ ነው። የፖለቲካ ጥምረት ማለት ወቅታዊ ችግራችንን ብቻ ታሳቢ አድርገን ምንገባት ቀላል ስሌት ሳይሆን የነገውን የኃይል ሚዛን፣ የድርድር አቅም እና የሕዝብ ዕጣ ፈንታ የሚቀርጽ ውሳኔ ምንወስንበት ነው።
ስለሆነም ዋናው የፖለቲካ ጥያቄ ፋኖ እና ህወሓት ወቅታዊ የጋራ ጠላት አላቸው ወይ የሚለው ብቻ ሳይሆን «ከዚህ ግንኙነት አማራ የሚያገኘው ተጨባጭ፣ ዘላቂ እና ሕጋዊ ማረጋገጫ ያለው ጥቅም ምንድን ነው? ህወሓትስ ምን ያተርፋል?» የሚለው ነው።
ህወሓት በአሁኑ ወቅት ጥምረት የሚፈልገው ለምንድን ነው?
ህወሓት ከአፋብን ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ያነሳሳውን መንስኤዎች ለመርመር ህወሃት በትግራይ ክልል ውስጥ ያጋጠመው ቅቡልና መሸረሸር፣ ከፌደራል መንግሥት ጋር ያለውን ውጥረት፣ እና በቀጣናው እየተባባሰ የመጣውን አለመረጋጋት በአንድነት ማየት ያስፈልጋል። በአንድ ወቅት አሁን የብልጽግና አገዛዝ የነገሰበትን ስርዓት በጠነከረ ክንድ በበላይነት ይመራ የነበረው ህወሃት ዛሬ የቀደመ ጥንካሬው እጅግ የወረደ እና ደካማ ድርጅት ሆኗል። ከብልጽግናው አገዛዝ ጋር ከገባበት ጦርነት ማብቃት በኋላ በትግራይ ውስጥ የሚታየው የስልጣን፣ የሕዝብ ውክልና እና የቅቡልና ፉክክር፣ የድርጅቱን ውስጣዊ ድክመት አጋልጦታል። የቀደሙ ህወሃት የፖለቲካ መዋቅሮች በከፊል መመለሳቸው ክልሉን በፊት ወደነበረው የተረጋጋ የፖለቲካ መስመር አላስገባውም። ይልቁንም ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ትግራይን ማን ይወክላል? ስልጣንስ እንዴት ይያዝ? ከፌደራል መንግስቱ ጋር ያለን ግንኙነት ምን ይምሰል? ክልሉስ ወዴት ያምራ በሚሉት ነጥቦች ላይ የህወሃትን ውስጣዊ ክፍፍሉን አጠናክሮታል።
ለህወሓት አሁን እጁ ላይ ያለችው ዋና የመጫወቻ ካርዱ የፕሪቶሪያ ስምምነት ቢሆንም እሱም አፈፃፀሙ ህወሃት በሚፈልገው መልኩ እና ለትግራይ ህዝብ ቃል በገባው መልኩ እየሄደ ስላልሆን ተጨማሪ ውዝግብ አስነስቷል። የፌደራል በጀት፣ አስተዳደራዊ መዋቅሮች፣ ተፈናቃዮችን መመለስ እና የግዛት ቁጥጥርን የመሳሰሉ ሌሎች ዋና ዋና ጉዳዮች እስካሁን ህወሃት በሚፈልገው መልኩ እልባት አላገኙም። ይሁንና ዛሬም ህወሓት ለደጋፊዎቹ የፕሪቶሪያን ስምምነት እንደ ዋቢ በማንሳት በወልቃይት፣ በራያ እና በሌሎች አካባቢዎች ላይ የያዘውን አቋም ለማስፈጸም እና ተፅዕኖውን ለመመለስ ይሞክራል። በአንጻሩ፣ በአማራ በኩል እነዚህ ጥያቄዎች በፖለቲካም ሆነ በታሪክ ፍጹም ተቀባይነት የሌላቸው እንደሆነ ህወሃት ቢረዳም በትግራይ ላይ ያለውን ሽራፍራፊ ቅቡልና ለማስቀጠል ዛሬም ያንን ዋና አጀንዳ አድርጎ ማራገቡ ተጠባቂ ነው። ይህ የርስት እና ማንነት ጥያቄ ጉዳይ ለይደር ሚቆይ ቀላል ልዩነት ሳይሆን፣ በህወሓት የፖለቲካ ግቦች እና በአፋብን መሠረታዊ የትግል ዓላማዎች መካከል ያለ ጥልቅ እና ቀጥተኛ የጥቅም ግጭት ነው።
በሌላ በኩል ህወሓት ሙሉ በሙሉ እንደተዳከመ ወይም ዳግም የማንሰራራት አቅም እንደሌለው አድርጎ መውሰድም ስህተት ነው። የኢትዮጵያ ወቅታዊ አለመረጋጋት ለህወሓት ፈተና ብቻ ሳይሆን አዳዲስ እድሎችንም ፈጥሮለታል። የፌደራል መንግሥቱ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልሎች ውስጥ የሚታዩትን ግጭቶች ለመቆጣጠር ከመወጠሩ ባሻገር ከኤርትራ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ግብፅ እና ከቀይ ባህር ፖለቲካ ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ የቀጣናው ውጥረቶች ተወጥሯል። እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ የብልጽግናውን አገዛዝ ስሌት ማወሳሰብ የሚችል የትኛውም አካል የፖለቲካ ትርፉን በፍጥነት ይጨምራል። ህወሓት በትግራይም ላይ ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የቆየውን የበላይነት ሙሉ በሙሉ ሳይመልስ እንኳ አገዛዙ ለሚያደርገው የማረጋጋት ወይም የፖለቲካ ድርድር ጥረት ራሱን ተጽእኖ ፈጣሪ አካል አድርጎ ለማቅረብ የሚያስችለውን አቅም ማግኘት ይፈልጋል።
ከአፋብን ጋር የሚደረግ ማንኛውም አይነት ግንኙነት ህወሓት ይህንን አላማውን እንዲያሳካ ያግዘዋል። ስለሆነም የአማራ ህዝብ ከህወሃት ጋር ሚያደርገውን የትኛውንም አይነት ጥምረት ከማሰቡ በፊት ሊጠይቀው የሚገባው ዋና ጥያቄ «ህወሓት ፍጹም ተዳክሟል ወይ?» የሚለውን ሳይሆን «አፋብን፣ ህወሓት አሁን ያለበትን ውጥረት እና ድክመት ወደ አዲስ የድርድር አቅም ለማሳደግ መሳሪያ መሆን አለበት ወይ?» የሚለውን ነው።
ህወሓት ከጥምረቱ ሚፈልገው ምንድነው?
ለህወሓት ከአፋብን ጋር የሚደረግ ግንኙነት ከውጊያ ቀጠና አመቺነት ባሻገር ትልቅ የፖለቲካ ማገገሚያ እርምጃ ነው። ከጦርነቱ፣ ከውስጣዊ ክፍፍሉ እና በፌደራል ደረጃ ከተዳከመ ተፅዕኖው በኋላ፣ ህወሓት ራሱን በአንድ ክልል ብቻ የተወሰነ አካል አድርጎ ከመቅረብ ይልቅ፣ የኢትዮጵያን የወደፊት የፖለቲካ እድል የመቅረፅ አቅም እንዳለው ኃይል አድርጎ ማሳየት ይፈልጋል። ከአፋብን ጋር የሚደረግ አነስተኛ ቅንጅት እንኳ ይህንን ምስል ለመገንባት ይጠቅመዋል። ከዚህ ቀደም በአብዛኛው የአማራ የፖለቲካ ሀይሎች ጽኑ ተቃውሞ ሚደርስበት የነበረ ድርጅት፣ ዛሬ እንደድሮው ከትግራይ ክልል ውጪ ካሉ ኃይሎች ጋር ተነጋግሮ ጥቅሙን ማስከበር የሚችል አቅም እንዳለው ለማስመስከር ያስችለዋል። ይህን ትርፍ በአራት ተያያዥ መስመሮች መመልከት ይቻላል።
- የቅቡልነት መልሶ ግንባታ:- ከአማራ የፖለቲካ ወይም የትጥቅ ኃይሎች ጋር የሚደረግ ትንሽም ቢሆን ግንኙነት ህወሓት ከትግራይ ውጭ ያሉ ሀይሎችን በማሰባሰብ ዛሬም ሀገራዊ የፖለቲካ ተዋናይ ነው የሚለውን ምስል ለማደስ ሊረዳው ይችላል። በተለይም በጣላትነት ከሳለው እና ዛሬም ድረስ በጥልቅ ግጭት ውስጥ ካለው ከአማራ ማኅበረሰብ እና ከአማራ የፖለቲካ ኃይሎች ጋረ መጣመሩ ለህወሃት ትልቅ ትርፍ ነው። የግንኙነቱ ፋይዳ አንድን ተጨባጭ ስምምነት ከማስፈጸም በላይ “ህወሓት ሙሉ በሙሉ ተገልሎ አልቀረም” የሚል የፖለቲካ መልእክት መፍጠሩ ነው። ይህ ምስል የድርጅቱን የውስጥ ቅቡልነት ለማደስ እንዲሁም በፌዴራል ሀይሎች ወይም በሌሎች ሀገራዊ ተዋናዮች ዘንድ ዛሬም እንደቀላል ሊታይ ማይገባው ኃይል አድርጎ ለማቅረብ ያግዘዋል።
- ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለሚያድርገው የጀርባ የድርድር ጫና መፍጠር፦ ህወሓት ከአፋብን እና ከሌሎች የታጠቁ ኃይሎች ጋር መቀራረብ እንደሚችል ማሳየቱ በብልጽግናው አገዛዝ ዘንድ የሚኖረውን የድርድር ክብደት ሊጨምር ይችላል። ብልጽግና በአገር ውስጥ ግጭቶች እና በቀጣናው ውጥረቶች ተወጥሯል። ህወሓት የደህንነት ሁኔታውን ማወሳሰብ ወይም ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋር ሊሰለፍ እንደሚችል የሚያሳይ ማንኛውም ምልክት፣ የብልጽግናው አገዛዝ ከህወሓት ጋር ለመስማማት የሚያደርገውን ጥረት ያፋጥነዋል። ነገር ግን ይህ ስምምነት በምንም መልኩ የአማራን ሕዝብ ጥቅም የሚያስጠብቅ ላይሆን ይችላል። ህወሓት ያገኘውን የተሻለ የድርድር አቅም ተጠቅሞ በፕሪቶሪያ ስምምነት፣ በፌደራል በጀት፣ በአስተዳደር እና በሌሎችም ጉዳዮችም ላይ የራሱን ጥቅም ያረጋግጣል።
- በትግራይ ውስጥ ያለውን ቅቡልና ማደስ፦ የህወሓት መሪዎች ከክልሉ ውጭ ካሉ ኃይሎች ጋር መነጋገር ወይም መቀራረብ መቻላቸውን ለደጋፊዎቻቸው እንደ ድርጅታዊ ብቃት አድርገው ማቅረብ ይችላሉ። ህወሃት ለደጋፊው ህዝብ “ከጦርነቱ በኋላ ትግራይ ላይ ብቻ ተገድቦ የቀረ አካል ሳይሆን የሀገሪቱን እጣ ፋንታ ለመቅረጽ ዛሬም እንደትናንቱ ተጽዕኖ አለው” የሚል መልእክት ማስተላለፍ ይፈልጋል። በተለይም አሁን በውስጣዊ የፖለቲካ ፉክክር እየትናጠ ላለው ህወሃት ይህ ዓይነት ምስል መፍጠሩ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። የውጭ ግንኙነት በመፍጠር የውስጥ ድክመቱን ለመሸፈን እና የመሪነት ጥያቄዎችን ለማርገብ ሊጠቀምበት ይችላል። ስለዚህ ከፋኖ ጋር መቀራረብ ለህወሓት ውጫዊ የፖለቲካ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን፣ በትግራይ ውስጥ የራሱን ቦታ ለማጠናከር የሚጠቅም መሣሪያም ሊሆን ይችላል።
- ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ተደማጭነት ፦ ምንም እንኳን የህወሃት ቅቡልና እና ተደማጭነት ከጊዜው ወደጊዜ እያሽቆለቆለ የመጣ እውነታ ቢሆንም ከፋኖ እና ሌሎች ሀይሎች ጋር ሚያደርገው ጥምረት በውጭ ተዋናዮች ዘንድ “የሰሜን ኢትዮጵያ መረጋጋት ያለ ህወሓት ተሳትፎ ሊመጣ አይችልም” የሚል ክርክር እንደገና ሊጠናከር ይችላል። ህወሓት በሰሜን ኢትዮጵያ የደህንነትና የፖለቲካ ሂደቶች ላይ አሁንም ተጽዕኖ የሚያሳድር ኃይል መሆኑን የሚጠቁም ሆኖ ሊቀርብ ይችላል። ይህ ደግሞ የዲፕሎማሲ አካላትን፣ የአስታራቂዎችን እና የውጭ ባለድርሻ አካላትን ትኩረት ድጋሜ ለመሳብ ሊረዳው ይችላል። ይሁንና ይህ ማለት የውጭ ተዋናዮች የህወሓትን ሁሉንም ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ይቀበላሉ ማለት አይደለም። ነገር ግን በውይይት ጠረጴዛ ላይ መታየት፣ ተሰሚነት ማግኘት እና የችግሩ መፍትሔ ውስጥ አስፈላጊ ተዋናይ መሆን በራሱ የድርድር አቅም ሚያሳድግ የፖለቲካ ካፒታል ነው።
ለፋኖ ትልቁ አደጋ ህወሓት ምንም አይነት ይፋዊ ጥምረት ሳይገባ ወይም ምንም አይነት የፖለቲካ መስዋዕትነት ሳይከፍል ይህንን የፖለቲካ ትርፍ ማፈሱ ነው። ይፋዊ የጥምረት እና ትብብር ሀሳቦችን በአደባባይ ማራመድ፣ ጥምረቱን ሚያሳነሱ ተቃውሞች ሲነሱ የማስተካከያ መግለጫዎችን መስጠት ወይም ጥምረቱን ይፋዊ ለማድረግ ተደጋጋሚ ውይይቶችን ማድረግ እና በደጋፊው ዘንድ የመወያያ አጀንዳ ማድረግ ብቻ እንኳ ህወሓት አገር አቀፍ ተቀባይነቱን እንዲመልስ እንደሚያግዘው እርግጥ ነው። ለዚህ ማሳያው ሰሞኑ የተለያዩ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ በተደጋጋሚ የሚሰጡት መግለጫ እና የኦባሳንጆ ተከታታይ ጉዞዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡
ስለሆነም ፋኖ መጠየቅ ያለበት «እኔ የኔ አስተዋፅኦ እኔ በማላተርፍበት ድርድር ላይ ህወሃት እና ብልጽግና መጠቀሚያ የሚሆኑበትን የፖለቲካ አቅም ለመገንባት ነው ወይ?» የሚለውን ነው።
ፋኖ ከጥምረቱ ሊያገኝ የሚችለው ጊዜያዊ ጥቅም አለን?
በአፋብን በኩል ያሉ የጥምረቱ ደጋፊዎች ፋኖ ከተወሰነ ግንኙነት አጭር ጊዜያዊ ጥቅሞችን ሊያገኝ ይችላል ብለው ሲከራከሩ ይሰማል። ይህ አመለካከት በዋናነት ሦስት ሐሳቦች ላይ ይመሰረታል፦ 1) በግጭት ቀጠና ውስጥ ውይይት መኖሩ ያልታሰበ የጎንዮሽ ግጭትን ሊቀንስ ይችላል፤ 2)ከጥምረቱ የሚገኝ ድጋፍ እና የመረጃ ልውውጥ ሊጠቅም ይችላል፤ 3) በተጨማሪም አሁን አማራውን በስፋት አያጠቃ ያለው የብልጽግናው አገዛዝ ስለሆነ ከህወሃት ጋር መተባበሩ በፌደራል መንግሥት ላይ ተጨማሪ ጫና በመፍጠር ውድቀቱን ያፋጥናል የሚል መከራከሪያ ይቀርባል።
ሆኖም ከዚህ ውስን የመረጃ እና አቅርቦት እገዛ እንዲሁም አላስፈላጊ ግጭትን ማስወገድ ወደ ሰፊ የፖለቲካና የወታደራዊ ጥምረት መሻገር ፈጽሞ የተለየ ውሳኔ ነው። የመጀመሪያው የአላስፈላጊ ግጭት ቅነሳ ተደርጎ ቢወሰድ ሁለተኛው ግን የረጅም ጊዜ የኃይል ሚዛንን የሚቀይር የፖለቲካ ውል ነው። ሁለቱን አንድ አድርጎ መመልከት ጊዜያዊ እፎይታን ከስትራቴጂያዊ ድል ጋር ማደባለቅ ነው።
የጋራ ጠላትን ለመጣል ሲሉ ብቻ መሠረታዊ የፖለቲካ አላማን አሳልፎ መስጠት፣ የዛሬን ጫና በነገው የህልውና አደጋ ለመተካት የመወሰን ያህል የዋህ ውሳኔ ነው። ከዚህም በላይ፣ የህወሓትን የፖለቲካ አጀንዳ መጋራትና ህወሃትን በቀጥታ ከሚመለከቱ የአማራ ህዝብ ወሳኝ ጥያቄዎች ዙሪያ የተያዘውን ቀይ መስመር ማለስለስ፣ ፋኖ ለህወሓት ነፃ የፖለቲካ ማገገሚያ ሽፋን እየሰጠ የራሱን የህልውና መሰረት በገዛ እጁ እንዲያፈርሰው ያደርገዋል።
አፋብን ሊያገኘው የሚችለው ምናልባት ውስን የሎጂስቲክስ ድጋፍ፣ የመስክ መረጃ ወይም በፌዴራል መንግሥት ላይ ጊዜያዊ ጫና ሊሆን ይችላል። ህወሓት ግን ከተመሳሳይ ግንኙነት ዳግም የሀገር አቀፍ ቅቡልነት፣ የውጭ ተደማጭነት፣ ከአገዛዙ ጋር የተሻለ የድርድር አቅም እና በውስጥ ፖለቲካው የተጠናከረ አዲስ ቅቡልና ሊያገኝ ይችላል። በመሆኑም የፋኖ ጊዜያዊ ጥቅም ከህወሓት ሊያገኘው ከሚችለው ዘላቂ የፖለቲካ ትርፍ ጋር ሲነጻጸር እጅግ የተገደበ ነው።
ከዚህም በላይ፣ የሎጂስቲክስ ድጋፍ ሁልጊዜ ነጻ ጥቅም አይደለም። ለአንድ አካል ሕልውና ወይም የእንቅስቃሴ አቅም በሌላ አካል ምንጮች ላይ ተመስርቶ ሲቆም ጊዚያዊ ጥቅሙ በቀላሉ ወደ ዘላለማዊ ጥገኝነት ይለወጣል። ጥገኝነት ደግሞ የዕዝ ነፃነትን ያዳክማል፤ ራስን ችሎ የፖለቲካ ውሳኔ የመወሰን አቅምንም ይገድባል። እንዲሁም በብልጽግና መንግሥት ላይ የሚፈጠር ጫና ድርድር ሲጀምር በተሻለ ሁኔታ ለተደራጀውና የራሱን አጀንዳ በግልጽ ለማራመድ ለሚችለው አካል እንዲውል የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው።
ስለሆነም በዚህ ጥምረት ውስጥ ፋኖ ሊያገኛቸው የሚችላቸው ጥቅሞች በጥብቅ መመዘን አለባቸው፡፡ ጥቅሙ ተጨባጭ እና ሊረጋገጥ የሚችል ነው ወይ? ይህ ጊዚያዊ እፎይታም ሆነ በዘላቂነት ሚገኝ ጥቅም ካለ ጥቅም የሚገኘው በህወሓት በኩል ብቻ ነው ወይ? ወቅታዊው ውጥረት ካለፈ በኋላ ጥቅሙ ዘላቂ ሆኖ ይቀጥላል ወይ? ፋኖ ለዚህ ጥቅም ሲል ምን አሳልፎ ይሰጣል? ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ይህ እርምጃ የአማራን ሕዝብ ደህንነት፣ የፖለቲካ ህልውና፣ የግዛት ጥቅም እና ዘላቂ የራስ እድልን በራስ የመወሰን መብት በግልጽ ያረጋግጣል ወይ? የሎጂስቲክስ ድጋፍ ጥገኝነትን ይፈጥራል፡፡ በብልጽግና ላይ የሚደረግ ጫና ደግሞ ድርድር ሲጀመር በደንብ ለተደራጀው አካል ጥቅም ይውላል።
ጊዜያዊ ግንኙነት እንዴት ዘላቂ ዋጋ ያስከፍላል?
የዚህ ጥምረት ከባዱ አደጋ በውስጡ የሚፈጠረው ግንኙነት ጊዜያዊ ቢሆንም፣ የሚያስከትለው የፖለቲካ ውጤት ግን ጊዜያዊ አለመሆኑ ነው። ፋኖ ከህወሓት ጋር የፈጠረው ግንኙነት ምንም እንኳ ውይይት፣ ትብብር ፤ ጽምዶ ፤ ጥምረት ፤ የጋራ ጠላትን መዋጋት ፤ ጠላትነት መቀነስ እያለኡ የተላያየ ስም ቢሰጡትም በፍሬው ሲመዘን ግን ለህወሓት ከሚሰጠው የፖለቲካ ትርፍ አንጻር በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከሁሉም በላይ ደግሞ በጥምረቱ ውድቀትና ስኬት ውስጥ ሁለቱ አካላት የሚሸከሙት አደጋና የሚያገኙት ትርፍ ፍጹም ያልተመጣጠነ ነው። ለህወሓት ጥምረቱ ቢሳካ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ቅቡልና ያገኛል፤ የዲፕሎማሲ በሩ ይከፈትለታል፤ ከአዲስ አበባና ከፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ያለውን የድርድር አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል። ጥምረቱ ቢፈርስ ወይም ዓላማውን ማስካት ባይችል እንኳ ህወሃት አሁን ካለው የተለይ የሚያጣው ይሄ ነው ሚባል ነገር የለውም።
በአንጻሩ ፋኖ በጥምረቱ ስኬትም ሆነ ውድቀት ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ ይከፍላል። ጥምረቱ ቢሳካ እንኳ ከህወሓት ጋራ በመጣመሩ የሚያገኘው ተጨባጭ የፖለቲካ ጥቅም ምን እንደሆነ እስካሁን በግልጽ አይታወቅም፡፡ የሚያተርፈው ነገር ቢኖር ጥገኝነትን የሚያስከትል እርግጠኛ ያልሆነ የሎጂስቲክስ ድጋፍና ያልተጨበጠ ተስፋ ብቻ ነው። ጥምረቱ ቢፈርስ ግን የፋኖ ትግል በውስጥ ክፍፍል እና የሕዝብ እምነት እስከማጣት ድረስ የሚዘልቅ አደጋ አለው። የውስጥ ክፍፍልን እና የሕዝብ እምነት መሸርሸርን ሊያስከትል የሚችልን አደጋ ያዘለ ጥምረት የተዘረዘረ እና ሚታወቅ ጥቅም እንኳን ቢኖረው እንደ ጥሩ የስትራቴጂ አማራጭ ሊወሰድ አይገባም፡፡ የትግሉን ዓላማ ለማሳካት ተበሎ ትግሉን ራሱ አደጋ ውስጥ ሚጥል እርምጃ መውሰድ የፖለቲካ የዋህነት ነው። አፋብን ይሄንን ችላ ብሎ ወደጥምረቱ ሲገባ ያን ተከትሎ የሚመጣውን ሕዝባዊ አመኔታና የስትራቴጂ ነፃነት ዳግም ለመመለስ ከባድ ዋጋ መክፈሉ አይቀሬ ነው። ስለሆነም ዋናው ጥያቄ «ግንኙነቱ ዛሬ ምን ያስገኛል?» የሚለው የየዋሃን ስሌት ሳይሆን፤ «ግንኙነቱ ነገ ለማን ዘላቂ የድርድር አቅም ይፈጥራል? የማንንስ አቅም ያዳካማል?” የሚለው መሠረታዊ የህልውና ጉዳይ ነው።
በአጠቃላይ ፋኖ ከተሳካለት ጥገኝነትን የመፍጠር አደጋ ያላቸው እና እርግጠኛ ያልሆኑ የሎጅስቲክስ ድጋፎችን ቢያገኝም ህወሓት ግን በትግራይ ደረጃ እንዲሁም በአገር አቀፍ እና ዓለማቀፍ ደረጃ ጣውን ተቀባይነትን፣ የዲፕሎማሲ እድልን እና የድርድር አቅሙን አሁን ካለው በብዙ እጥፍ ለማሳደግ ያስችለዋል። የአማራ ፋኖም አንድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አጭር ጊዜያዊ ጥቅሞችን ብች አስቦ ስትራቴጂካዊ ነፃነቱን አሳልፎ መስጠት የለበትም፡፡ በተለይ ደግሞ ሌላኛው ወገን ያንን አጋጣሚ ተጠቅሞ በአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥቅሞች ላይ ዘላቂ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችልበት እድል በሰፊው የሚፈጥርለት ከሆነ ጉዳቱ በጣም የከፋ ነው።
ማጠቃለያ
የፋኖ–ህወሓት ጥምረትን ለመቃወም የሚቀርበው መከራከሪያ የኋላ ታሪክን ብቻ በማስታወስ ላይ የተመሠረተ መሆነ የለበትም። ምንም እንኳ ታሪካዊ በደሎችና ያልተፈቱ ቅሬታዎች ትልቅ ቦታ ቢኖራቸውም ዋናው ነጥብ ማንኛውም ጥምረት ሊመዘን የሚገባው “ዛሬ ምን ያስገኛል? ነገስ ምን ለማድረግ ያስችላል?” የሚሉትን ጥያቄዎችም ታሳቢ በማድረግ መሆን አለበት። በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የውስጥና የቀጠና ውጥረት ህወሓት ከፋኖ ጋር ግንኙነት እንዲፈጥር እንደገፋፋው ብዙ ምልክቶች አሉ። ህወሃት ከፋኖ ጋር በሚፈጥረው ጥምረት ለህወሓት አዲስ ተቀባይነትን፣ ሰፊ የፖለቲካ ተደማጭነትን፣ የተሻለ የድርድር አቅም እና ከብልጽግና ጋር በሚኖረው ግንኙነት እንዲሁም በፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ የላቀ የመደራደር አቅም ሊሰጠው ይችላል።
በተቃራኒው ፋኖ ከዚህ ጥምረት የሚያገኘው ጥቅም እንደ ህወሓት ዘላቂና አስገዳጅ በሆነ መልኩ ሊረጋገጥ የሚችል አይደለም። ፋኖ የሚያተርፈው ጊዜያዊ የሎጂስቲክስ ድጋፍ ወይም በብልጽግና አገዛዝ ላይ የሚፈጥረውን ጊዜያዊ የፖለቲካ ጫና ብቻ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ጊዜያዊው የሎጂስቲክስ ድጋፍ ፋኖን በህወሓት ላይ ጥገኛ ከማድረጉ ባሻገር በብልጽግና አገዛዝ ላይ የሚኖረው ጫናም ቢሆን ህወሓት ጥምረቱን ለራሱ ስትራቴጂያዊ አጀንዳ እስከፈለገበት ጊዜ ድረስ ብቻ የሚዘልቅ ሊሆን ይችላል፡፡
እነዚህ ጊዚያዊ ጥቅሞች ወይም ያልተረጋጋጡ ተስፋዎች የአማራን የግዛት እና የርስት ጥያቄዎች ለማስመለስ ሚጨምሩት ፋይዳ የለም፡፡ የፋኖን የዕዝ እና አደርጃጀት ነፃነት ህወሓት ላይ ጥገኛ እንዲሆን ያደርጋል ወይም በወደፊት ሊፈጠር በሚችል የፖለቲካ ስምምነት ላይ ፋኖ የአማራን ህዝብ አጀንዳዎች በሚመጥን መልኩ ተጽዕኖ እንዲኖረው አያደርጉም። ይልቁንም ይህ ግንኙነት በፋኖ ውስጥ ክፍፍልን ሊያባብስ፣ ስትራቴጂያዊ ነፃነቱን ለአደጋ ሊያጋልጥ እና የህወሓትን የድርድር አቅም ግን ሊያጠናክር ይችላል።
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena







ምሁራን አንዳንድ እሳቤዎችን ለተራው ህዝብ በሚገባ ቋንቁና በድፍረት ብትጽፉ ብታስተምሩን መልካም ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያን መከላከያ ሃይል ያረደ የወልቃይት ተወላጅ ለማሳሳት ያለምንም ርህራሄ ያረደ ያሰደደ ለተክልና ለእንሰሳ ያላዘነ በክፋቱ ወደር የማይገኝለትን የትግሬን የጥፋት ሃይል ወልቃይትና የተቀረው የአማራ አካባቢ ተቀብሎ የሚያኖርበት በምን እዳው ነው? ከወለጋ ከአሩሲ በኦነግና በነዚሁ ትግሬዎች እርዳታ አማራው ይፈናቀላል ይታረዳል ወደ ቦታው ይመለስ የሚል እንቅስቃሴ ግን አይሰማም አይታይም፡፡ በአጠቃላይ ትግሬዎችን እሽሩሩ ለማለት ካልሆነ በስተቀር ከተከዜ መልስ ሰው በዘሩ ከተሸነሸነ ትግሬ ምን ይሰራል፡፡ ትግሬ በጥንቱ በኢትዮጵያ እሳቤ መጥቶ ሰርቶ ይመለስ ይሆን እንጅ ምድሩ የረገጠውን ሁሉ የኔ ነው የሚለው አባዜውን ማስተናገድ አይገባም፡፡ መሬት ከፈለገ በኤርትራ የተቀማው መሬት ስላለ እሱን ይጠይቅ፡፡ አማራው አጽመ እርስት ላይ ትግሬን ምን አንጠለጠለው? የአማራ ምሁራን ማሽሞንሞናችሁን ትታችሁ ሃቅ ሃቁን ጻፉ ትግሬ ከደብረ ጽዮን እስከ ጳጳሱ በአንድ እስትንፋስ በአንድ እሳቤ ለአንድ አላማ ሲሰሩ አዲስ አበባን በተበላሸ ባህል ሲንጡት ተው ያልተባሉበት ነገሩ ምንድነው? መሃል አዲስ አበባ ላይ የህዝብ አጥንት ግጠው ከባንክ ተበድረው የተበላሸ ብድር ተብሎ በመለስ ዘራዊ በስብሃት ነጋ ተሰርዞላቸው ያ ሳያንስ ዛሬ የትላልቅ ህንጻዎች የወርቅ ቤቶች የንግድ ድርጅቶች ባለቤት ሁነው በወንጀል ባገኙት ገንዘብ ህብረተሰቡን ይበክላሉ ያዋክባሉ ያለውን መንግስትም በዘረጉት መረብ ጢብ ጢብ ይጫወቱበታል፡፡ ስለዚህ ምሁራን ስትጽፉልን ደፈር አድርጋችሁ የምታውቁትን ጻፉ፡፡ አብረሃም በላይ ሚኒስቴር ሁኖ ታሪክ ያፋልሳል ጌታቸው ረዳ ያንን ሁሉ ጥፋት አድርሶ ዛሬም በአቋሙ ላይ ነው፡፡ አረጋዊ በርሄ፤ጻድቃን ገ/ተንሳይ፤ሰየ አብረሃ የህወአት ወታደር የበላይ አዛዥ ሁነው ለገደሷቸው ዜጎች እስከ አሁን ተጠያቂ አልሆኑም፡፡ ፍትህ እስኪመጣ ስማቸው በህዝብ አእምሮ ውስጥ ይቀመጣል የሌላው እናት አልቅሳ አትቀርም፡፡