Homeነፃ አስተያየትአገራዊ አንድነትን እና የዜጎች ሰላምን የማስከበር አካል ለሆነው የዐማራው የኅልውና ትግል  አጋር...

አገራዊ አንድነትን እና የዜጎች ሰላምን የማስከበር አካል ለሆነው የዐማራው የኅልውና ትግል  አጋር ማነው? ትብብር ለምን ዓላማ እና ልዕለ-ግብ? በምን ሁኔታ እና ከማን/ከነማን ጋር?  

Advertisement
World Wide Travel Group
አያልሰው ደሴ

አያልሰው ደሴ
የግል አስተያየት 
ነሐሴ ፳፻፲፰ ዓ/ም 

ሀ. መንደርደሪያ፤-  

ጥንታዊቷ አገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪቃ አኅጉራዊ ቀጠና እነሆ ላለፉት ፵ ዓመታት አስተማማኝ ሰላምን እና መረጋጋትን ተነፍጎ፣ የየአገሩ ዜጎች ለእብሪተኛ እና ስግብግብ አምባ-ገነኖች የጭቆና አገዛዝ እና ለተወሳሰበ የቀውስ አዙሪት ጥንውት የተዳረጉበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን። የቀጠናው አገሮች ከሚገኙበት የተመሰቃቀለ ውስጣዊ ችግሮች በተጨማሪ የየግላቸውን ጥቅሞች ለማስከበር ትኩረት ሰጥተው ጥረት የሚያደርጉ እና አበክረው የሚሠሩ የቅርብ እና የሩቅ ኃይሎች ለተፈጥሮ ጥሬ-ሃብት ቅርምት የሚረዳቸውን የፖለቲካ ተጽዕኖ-አሳዳሪ የቁጥጥር አድማሳቸውን ለማስፋት በሚከተሉት ሽሚያ አንዱ ለሚደግፈው ክፍል ሌላው የራሱን ዓላማ ደጋፊ ቡድን በመርዳት የቀጠናውን አገሮች የኃይል አሠላለፍ ቢያንስ የእጅ-አዙር ጣልቃ-ገብነት ሁኔታን ሊጋብዝ ለሚችል አደጋ ተጋላጭ ሆነዋል። መሪ የተባሉትም ቅድሚያ የሚሰጡት ለሕዝባቸው ደኅንነት እና ለአገራቸው እድገት ሣይሆን በተጭበረበረ ምርጫም ቢሆን እንደ ምንም ሥልጣን ላይ ሙጭጭ ማለት ስለሆነ፤ የጥቅም-ተጋሪ የሆኑበትን ይኽን የባዕዳን ድርጊት እንዳላዬ እያዩ ከማለፍ ያለፈ የአገር ተቆርቋሪነት ተግባር ቢያንስ በይፋ በሚታወቅ መልክ ሲያሳስባቸው አይታይም። 

አሣፋሪው ነባራዊ ሁኔታ ይኽ በመሆኑም በቀጠናው አገሮች የአስተማማኝ ሰላም መኖር አለመኖር እና ያም ለአዎታዊ ለውጥ የሚደረግ ትግል ላይ የሚያስከትለው ተግዳሮት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አገራችን ኢትዮጵያ ዜጎቿ በከፈሉት ክቡር መስዋዕትነት የቅኝ-ገዥዎችን እና የተስፋፊዎችን ሙከራ ሁሉ አሣፍራ በመመለስ ነፃነቷን እና አንድነቷን አስከብራ መኖር መቻሏ ለእኛ የሁልጊዜ ኩራታችን ቢሆንም፣ በነባሮቹም ይሁን በአዲሶቹ ተቀራማቾች ዘንድ ግን በአኅጉሩ ላይ ያሏቸውን ፍላጎቶች ለማሳካት እንደ-እንቅፋት እንደሚመለክቷት አያጠራጥርም። በመሆኑም፤ የየግላቸውን ጥቅም ለማጋበስ ባልቦዘኑ ባዕዳን ዘንድ ትኩረት የሚሰጡት ለአገራችን ምትክ የሌለው ዋነኛ አቅሟ የሆነውን አንድነቷን አጥታ እንድትከፋፈል፣ ቢያንስ እነሱ  እንደፈለጉ ለሚቆጣጠሩት ለማያባራ የውስጥ ነውጥ እንድትዳረግ ማድረግ እንደሚሆን መገመት ችግሩን ከሚገባው በላይ አጋንኖ ማዬት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። በተለይም አገራችን ላይ የተጫነው ሕዝብን ክፋፋይ ኋላ-ቀር የፖለቲካ ሥርዓት ዋነኛ መንግሥታዊ የአገዛዝ መርኆ በሆነበት እና ሥር እንዲሰድ ተደርጎ የውስጥ አንድነታችን እየተሸረሸረ ባለበት፣ ሐይማኖትን ተገን ያደረጉ አክራሪ ቡድኖች ንጹኃን አማኝ ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል በሕዝባችን መኻል ልዩነትን ለመፍጠር እየኳተኑ ባሉበት፣ ወዘተ… እጅግ አደገኛ አሁናዊ ሁኔታ ለዚኽ የባዕዳን መሠሪ መተናኮል ተጋላጭ አይደለንም ማለት ሲሰማ የሞተን እያየ ቅበረው የተባለው ይሆናል። አይሆንንም ትተሽ ይሆናልን አስቢ እንደሚባለው፤ እንደ-አገር ለማንኛውም ምናልባታዊ አደጋ ተጋላጭ የሆንባቸውን ጎኖች የምር መፈተሽ እና ያ ስጋት እውን እንዳይሆን ከወዲኹ ቢያንስ የተቻለውን የሥነ-ልቦና ቅድመ-ዝግጅት ከማድረግ የሚመጣ ጉዳት አይኖርም። 

 ስለሆነም፤ በዚኽ አዙሪቱ በበዛ ተጨባጭ እና ምናልባታዊነቱ በማያጠራጥር የቀውስ ድባብ በሠፈነበት አደገኛ ሁኔታ የሚፈጠር የኃይል አሠላለፍ ዋነኛ መሥፈርቱን በደፈናው ‘የጋራ ጠላትን ለማስወገድ ’ ከሚል ነጠላ እሳቤ ላይ መሠረት ያደረገ ሊሆን ከቶ አይገባም። አዎ፣ በዓላማም ሆነ በግብ ሆድ-እና-ጀርባ አልፎም አጥፊ-እና-ጠፊ የሆነ መሠረታዊ አቋም ወይም እምነት ያላቸው ኃይሎች ለየቆሙበት ዓላማ እውን መሆን እንቅፋት አድርገው የሚያዩት እና እንዲወገድላቸው የሚፈልጉት አንድ ክፍል/ኃይል ሊኖራቸው መቻሉ የሚያጠያይቅ አይሆንም። ቁልፉ ቁም-ነገር እንዲወገድ ወይም እንዲለወጥ የሚፈለገው ክፍል/ኃይል ጠላት ሆኖ የተቆጠረበት መሠረታዊ ምክንያት ብቻ ሣይሆን ከዚያስ ለሚለው የልዕለ-ግብ ጥያቄ ከወዲኹ አጥጋቢ መልስ እንደሚያስፈልገው ጠንቅቆ መረዳቱ ላይ ነው። 

ለ. የኃይል/የኃይሎች አሠላለፍ ለምን ዓላማ? ልዕለ-ግቡስ?  

ከወዲኹ ቀውስ እያስተናገደች ያለችው አገራችን በዚኽ ያልተረጋጋ ውስብስብ ጅዖ-ፖለቲካዊ ድባብ በሠፈነበት ነባራዊ ሁኔታ የሚፈጠርን የኃይል/የኃይሎች አሠላለፍ የጋራ ጠላትን ማስወገድ ከሚል ስንጥር አመክንዮ ባለፈ የሚያስከትለውን መዘዝ እጅግ በጥንቃቄ መመርመር አስፈላጊም፣ ተገቢም ይሆናል። የዚኽ አጭር ማስታወሻ ዓላማም አፍጥጦ ለመጣው ለዚኽ አደገኛ ጉዳይ የሚገባው ትኩረት እንዲሰጠው በአክብሮት ለማሳሰብ ነው። 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

በአገራችን ኢትዮጵያ ትግላችን አንድን ኢትዮጵያዊ ማኅበረ-ሰብ ነፃ ለማውጣት ነው ብለው የተደራጁ እና ለዚያም ዓላማ የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ነፃ-አውጭ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመሩ እነሆ ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ ሆኗል። በአንድ አገር ያሉ ዜጎች እኩልታቸውን የሚያረጋግጥ ፍትኀዊ ሥርዓት ሲጠፋ፣ መሠረታዊ መብቶች ካልተከበሩ እና በነገዳዊ ማንነትም ይሁን በመንፈሣዊ እምነታቸው ምክንያት አድልዖ ሲኖር የጋራቸው በሆነች አገራቸው የተነፈጉ መብቶቻቸውን ለሚያስከብር ርእታዊ ሥርዓት እውን መሆን ትግል ማድረጋቸው የሚጠበቅ ብቻ ሣይሆን ተገቢም፣ አስፈላጊም ነው። አገራዊ አንድነትን እና የሕዝብን ሰላም በአስተማማኝ ማረጋገጥ የሚቻለው የዜጎች ሁሉ እኩልነት እና ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩበት ፍትኃዊ ሥርዓት እውን ሲሆን በመሆኑ፤ ለዚኽ የሚጠበቅ እና አስፈላጊ የአርነት እንቅስቃሴ ድጋፍ ሊቸረው የሚገባው በስሙ እንቅስቃሴ /ትግል/ በሚደረግለት የሕዝብ ክፍል /ማኅበረሰብ/ ብቻ ሣይሆን በፍትኅ-ወዳድ፣ ሰላም  እና አገራዊ-አንድነት ፈላጊ ዜጋ፣ አልፎም ኅሊና ባለው ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ሊሆን ይገባል። ለዚኽ ፍትኃዊ ጥያቄ የሚሰጥ ድጋፍ መታዬት ያለበት ጥያቄውን ላነሳው የኅብረተሰብ ክፍል የሚከፈል ውለታ ተደርጎ ሣይሆን በተገቢነቱ ሊሆን ያስፈልጋል። ተገቢነቱም የአንድ አገር አንድነትም ሆነ ዕጣ-ፈንታቸው የተሳሠረ ዜጎችን እኩልነት የሚያረጋግጥ ፍትኃዊ ሥርዓት በአስተማማኝ እውን ማድረግ የሚቻለው የማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ብሶት የጋራ ሆኖ ሲታይ እና በተግባር ሲደገፍ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። ወደ-ኋላ ሲታይ ከበጎ ምኞት ባሻገር በአብዛኛው ከልምድ እና ከግንዛቤ እጥረት የተነሣ አንዳንድ ያልታሰቡ ችግሮች የተስተዋሉበት መሆኑ ቢነገርም፣ ኢትዮጵያውያን በአገራዊ-ዜግነታቸው ተደራጅተው የሕዝብን ብሶት መሠረት ላደረጉ ክቡር ዓላማዎች ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ የሕይዎት መስዋዕትነት የተከፈለባቸው ትግሎች ማድረጋቸው ይታወቃል። አገራዊ አንድነትን እና የሕዝብን ሰላም በአስተማማኝ ማረጋገጥ የሚቻለው  አድልዖ የሌለበት እና የዜጎች እኩልነት የሚከበርበትን ፍትኃዊ ሥርዓት እውን ማድረግ ሲቻል ብቻ መሆኑ  ሊታወቅ ያስፈልጋል። ለዚኽ ልዕለ-ግብ የሚደረግ የጋራ ትግል ሁሉንም አትራፊ-እና-ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑም የሚያጠራጥር አይሆንም። 

ሕወሓት ለሚከተለው ፀረ-አንድነት ዓላማ ተግባራዊነት ሕጋዊ ሽፋን እንዲያስገኝለት በሕገ-መንግሥት ስም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጫነውን መዘዘ-ብዙ እና መሠሪ ኋላ-ቀር የፖለቲካ ሥርዓት ያስቀጠለው እና የሱው ፍጡር የሆነው ኢሕአዴግ-ወለዱ በዐብይ አሕመድ የሚመራው የብልጽግና ድርጅት ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ቀደም-ሲል በሕወሓት ሲካሄድ የነበረውን እና ላለፉት አርባ ዓመታት ያላባራውን ዐማራን የማጥፋት፤ ታሪኩን፣ ባኅሉን እና እሴቱንም የመፋቅ ዘመቻውን በገሃድ አውጆ፤ ተቀዳሚም ዋናም ተልዕኮው የአገርን ዳር-ድንበር ማስከበር የሆነውን መከላከያ ሠራዊት በማዝመት ጭምር እነሆ ላለፉት ሦስት የመከራ ዓመታት ሁለ-ገብ ጦርነት በማካሄድ ላይ ይገኛል። የብልጽግናው አገዛዝ በሚያካሂደው በዚኽ አረመኔኣዊ ጦርነት በዐማራው ላይ የተቃጣውን መንግሥት-መር የኅልውና አደጋ በእጅጉ አባብሶታል። የዐማራ ሕዝብም በኅልውናው ላይ የተዘመተበትን ይኽን ቀጣይ የጥፋት ዘመቻ ለመቋቋም ተባብሮ መነሣት አማራጭ የሌለው ግዴታ ሆኖበታል። አለኝታው በሆነው በፋኖ አደረጃጀት በሚያደርገው እራስን ከጥፋት የመከላከል እና የማዳን መራር ትግል የአገዛዙን ታሪክ ይቅር የማይለው እኩይ ጥረት እያከሸፈ፣ ድርጅታዊ ይዞታውን እያጠናከረ እና የሕዝብ አለኝታነቱን በክቡር መስዋዕትነቱ እያስመሰከረ ይገኛል። 

በአካባቢው የሚታየው የፖለቲካ ድባብ፣ የኃይሎች አሠላለፍ በፋኖ የቀን-ተቀን፣ የአጭር ጊዜ እና የረዥም ጊዜ አካሄድ አጠቃላይ ዕቅድ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ ግልጥ ነው። በዚኽ የኅልውና ተጋድሎ ያለው የኃይሎች አሠላለፍ በአገር ውስጥ ባሉ ተዋናይ ተፋላሚዎች የተገደበ አይደለም። የዐብይ አሕመድ የብልጽግና አገዛዝ፣ የበጥባጯ ኤምሬትስ እና የደጋሎ ሱዳን በአንድ በኩል፤ ከጀርባ ግብፅ እና የአልቡርሃን ሱዳን በአጋርነት እንዳሉበት የሚነገርለት ኤርትራ እና ሕወሓት የፈጠሩት “ፅምዶ” የተባለው ጥምረት/ኅብረት በሌላ በኩል፣ ባልተረጋጋው እና ብዙ ቀውሶችን እያስተናገደ ባለው ምሥራቅ-አፍሪቃ፣ በተለይም በተለምዶ የአፍሪቃ ቀንድ በሚባለው የቀይ-ባሕር እና የሜዲተራኒያ አዋሣኝ ቁልፍ ቦታዎች፣ በቅርብ ጊዜ ባልታዬ ሁኔታ የግብፅ፣ የቱርክ እና የእስራኤል አዳዲስ የጦር ሠፈሮች መኖር፣ በተጨማሪም ልዕለ-ኃያሏ አገር አሜሪካ እና እስራኤል ግንባር-ቀደም ተሣታፊ የሆኑበት ክኢራን ጋር በሚካሄደው ጦርነት ምክንያት ያሉ እና ሊኖሩ የሚችሉ መዘዞች አጠቃላይ የኃይሎች አሠላለፍ እና ያም ሊያስከትል የሚችለው ሁኔታ በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል። በአገሮች መኻል የነበረው የኃይሎች አሠላለፍ ባለበት ላይቀጥል እና የተደበላለቀ ሁኔታን ሊያስከትል  እንደሚችልም በጥሞና መገምገም ተገቢ ይሆናል።  

በቅርብ ይሁን በሩቅ ባሉ ኃይሎች መካከል የነበሩ እና በአዲስ መልክ የሚከሰቱ አሠላለፎችን ሁሉም ለውጥ-ፈላጊ ክፍል፣ በተለይም ለዐማራ ኅልውና እየተፋለመ ያለው ፋኖ በሚያካሂደው ትግል ላይ ሊኖረው የሚችለውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ጎኖች የሚገባውን ትኩረት ሰጥቶ በጥንቃቄ ሊመረምር እና ሊከታተል ያስፈልጋል። ከዚኽ ጋር በተያያዘ የብልጽግናውን አገዛዝ ተቃውመው የትጥቅ ትግል በማድረግ ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎች ከ”ፅምዶ” ጋርም ሆነ ውጭ እና ውስጥ ካሉ ከሌሎች ኃይሎች ጋር እና መኻል ያለውን ትሥሥር ወይም የግንኙነት ባኅሪ እና ይዘት በጣም በጥንቃቄ መታየት የሚገባው ጉዳይ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይሆንም።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ከዚኽ አኳያ አንደኛው በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው፣ ሌሎችንም እንደጨመረ የሚነገርለት በኤርትራ እና በሕወሓት መካከል የተደረገው ”ፅምዶ” የተባለው ትብብር ነው። ይዘቱ በግልጥ የታወቀ ባይሆንም ሱዳን እና ግብፅ የዚኽ ትብብር አካል እንደሆኑ ይነገራል። ሁለተኛው በይፋ እየተነገረ ያለው በሕወሓት፣ በዐፋብን፣ በኦነሠ እና ተመሣሣይ አደረጃጀት፣ ዓላማ እና አቋም ያላቸውን ሌሎች ታጣቂ ኃይሎች ጨምሯል የሚባለው ትብብር ነው። በቀጠናው ካለው የተወሳሰበ ነባራዊ ሁኔታ እኳያ በእነዚኽ ኃይሎች መኻል የተፈጠሩ ትብብሮች በዐማራው የኅልውና ትግልም ሆነ በአገራችን በኢትዮጵያ ላይ የሚኖረው ጦስ የሰከነ ግምገማን የሚጠይቅ፣ ከፍተኛ ጥንቃቄም የሚያስፈልገው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።  

በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ እንደሚስተዋለው ጉዳዩን በዝምታ ማየት ወይም አንዴ  ሆኗልና የተለየ አቋም መያዝ አያስፈልግም የሚል ለዘብተኛ አቋም መያዝ ወይም ተስፋ ቆርጦ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ተገቢ አለመሆን ብቻ ሣይሆን እጅግ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ከመሆን የተለዬ ሆኖ ሊቆጠር አይችልም።  

በአንዳንድ ቅን-አሳቢ ወገኖች ዘንድ በአሁኑ ጊዜ የተፈጠረው ትብብር/ግንባር በብልጽግናው አገዛዝ የኅልውና አደጋ በተጋረጠባቸው አልፎም በተዘመተባቸው ኃይሎች መኻል ስለሆነ፣ ይኽን የጋራ ኅልውና በጋራ ትግል ማስወገድ ተገቢ ነው የሚል የማሳመኛ አቋም ይቀነቀናል። ይኽን በበጎ አለማየት ተገቢ አለመሆን ብቻ ሣይሆን ለኅልውና አደጋ የተጋለጡትን ማኅብረሰቦች ችግር አለመረዳት እና አልፎም ግፈኛውን ብልጽግናን ከመደገፍ ተለይቶ የማይታይ ድርጊት ነው እስክማለትም የደረሰ ደፈናዊ ትችትም በጥሬው ሲሰነዘር ይሰማል። ይኽ ዓይነት ላይ-ላዩን ብቻ ያዬ አመለካከት በአብዛኛው የዐብይ አሕመድ የብልጽግናው አገዛዝ በሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን አረመኔኣዊ ጭፍጨፋ እና ግፍ ለማስቆም ካለ ቀና ፍላጎት የመነጨ መሆኑ ባይካድም፤ የአገዛዙን የወንጀል ድርጊት ለማስቆም የሚደረግ በማን እና ምን መዘዝ እንደሚያስከትል በጥሞና ማየትን እንደሚጠይቅ የሚያዘናጋ እና ተገቢውን ግንዛቤ እንዳናይ ግርዶሽ ሊሆን አይገባም። እንደዚያ ዓይነት ደፈናዊ አስተሳሰብ በቀና መንፈስ የሚሰነዘር ሊሆን ቢችልም ዱባ እና ቅልን አንድ አድርጎ ከማየት ያልተለዬ ሲበዛ ግልብነት የተጠናወተው ድምዳሜ ከመሆን አያልፍም። የባዕዳንን ጥቅም-አስክባሪ የሆነውን የዐብይ አሕመድን ፀረ-ሕዝብ አገዛዝ እና የኢትዮጵያ አገራዊ-አንድነትን እኩል በአንድ ሚዛን ማስቀመጥ ደግሞ ተገቢ ስሌት አይሆንም። መቸም ቢሆን ጣራ አፈሰሰ ተብሎ ወይም ትኋን አለ ተብሎ ቤት፣ ያውም በክረምት አይቃጠልም እና መወገድ ያለበትን አገዛዝ እና መደፈር የሌለባቸውን አገራዊ አንድነት እና የሕዝብን ሉዓላዊነት  አንድ-እና-አንድ አድርጎ ማየት ቢያንስ ጤና-ቢስነት ይሆናል።  

ማንኛውም ኃላፊነት የሚሰማው ድርጅት በተለይም ለአገር እና ለሕዝብ መታገልን ዓላማው ያደረገ ድርጅት፤ ከእነሱ ውጭ ካሉ ሌሎች ድርጅቶች ጋር በሚደረግ የኃይል አሠላለፍ እንኳን አባል ደጋፊ ለመሆንም ሆነ  ላለመሆን የሚወሰነው የሌላው/የሌሎቹ ኃይል/ኃይሎች እሱ ከሚታገልለት መተክላዊ ዓላማ፣ ግብ እና ልዕለ ግብ ጋር ከሚኖረው መሠረታዊ አዎንታዊነት ወይም አሉታዊነት አኳያ በጥንቃቄ ተመዝኖ ሊሆን ግድ ነው። ያ ደግሞ የጋራ ጠላትን ለመታገል የሚል ሩቅ የማይወስድ ነጠላ መመዘኛን የሚመለከት አይሆንም። በዓላማም በግብም ሆድ-እና-ጀርባ የሆኑ ኃይሎች የጋራ ጠላት ሊኖራቸው ይችላል። ያ የጋራ የሚያሰኘው ግን የመነሾው ምክንያትም ሆነ እንዲለውጥ የሚፈለግበት መሠረታዊ ዓላማ እና ግቡ ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ የሰከነ ግምገማ እና ሃቀኛ ምላሽ ያስፈልገዋል። 

- Advertisement -

እዚኽ ላይ አንድ ብዥታ የበዛበት እና በተገቢ ግልጥ መሆን ያለበት ጉዳይ አለ። ይኸውም ትብብር ፈጠሩ በተባሉት ኃይሎች ላይ ተደቀነ የተባለውን የኅልውና አደጋ የሚመለከት ይሆናል። መሠረታዊ ጥያቄው የኅልውና አደጋው በታጣቂ ኃይሎቹ ላይ ነው ወይስ እንወክለዋለን በሚሉት ማኅበረሰብ ላይ? የሚለው ይሆናል። ታጣቂ ኃይሎቹ የተደራጁት እና የሕይዎት መስዋዕትነት የሚክፍሉት በስሙ ለተደራጁበት ማኅብረሰብ ሰብዓዊ መብት እና ክብር መሆኑ የማያሻማ እውነታ ነው። ይኽ ደፈናዊ እውነታ እንዳለ ሆኖ በተለይ አሁን ትብብር ፈጠሩ በተባሉት ኃይሎች በኩል ያለውን ነባራዊ እውነታ ቀረብ ብሎ መፈተሽ አስፈላጊ ይሆናል። ሦስቱም (ፋኖ፣ ትሕነግ/ሕወሓት እና ኦነሠ/የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት) ምናልባት የይዘት ልዩነት ሊኖር ቢችልም በዐብይ ከሚመራው የብልጽግና አገዛዝ ጋር ጦርነት ላይ መሆናቸው የሚያጠያይቅ አይሆንም። የብልጽግናው አገዛዝ ታጣቂዎቹ የሚዋጉላቸው ማኅበረሰቦች (ዐማራ፣ ተጋሩ እና ኦሮሞ) ላይ የዘመተባቸው የጦርነት ባኅሪ ተመሣሣይ ነው? የኅልውና አደጋው በደፈናው እነዚኽ ኃይሎች ወክለው በሚታገሉለት ማኅበረሰብ እንደ-ማኅበረሰብ ነው ወይስ በታጣቂዎቹ ላይ? አሳማኝ ማስረጃው ምንድን ነው? ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ያስፈልጋል። ሆን-ተብለው የሚደረጉ ማንነት-ተኮርም ሆነ እምነት-ተኮር ጥቃቶች መታዬት እና መመዘን የሚኖርባቸው በድርጊቱ/ በጥቃቱ ዋነኛ ምክንያት እንጅ በምን ያኽል ሰው ላይ ወይም ንብረት ላይ ተፈጻሚ በመሆናቸው ሊሆን አይገባም። 

 በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም በአገራዊ ሥልጣን ላይ በሚገኘው በዐብይ አሕመድ የሚመራው የብልጽግና አገዛዝ በዐማራ ኅልውና ላይ የተዘመተበትን ሁለ-ገብ ጦርነት የሕይዎት መስዋዕትነት እየከፈለበመታገል ላይ በሚኘው ፋኖ እና በሕወሓት/ትሕነግ እና በመሰሎቹ ነፃ-አውጭ ታጣቂ ድርጅቶች ተደረገ፣ የሚባለው የጋራ ትብብር/ግንባር፣ ወዘተ… መፈጠር ዋነኛ መስፈርት የጋራ ጠላትን በጋራ ለመታገል እንደሆነ ይነገራል። 

ትግሌ የተወሰነ ማኅበረ-ሰብን ነፃ ለማውጣት ስለሆነ በዚያ ማኅበረ-ሰብ ስም መደራጀት እና ያንን ዓላማ እውን ለማድረግ ነው የትጥቅ ትግል የማደርገው የሚሉ ደርጅቶች ነፃ የሚኮነው ከማን ነው? የሚለውን ማዬት ተገቢ ይሆናል። በነፃ-አውጭ እንቅስቃሴ እና በአርነት እንቅስቃሴ መኻል ያለው ልዩነት ላይ ብዥታዎች እንዳሉ ግልጥ ነው። በአንድ ሉዓላዊ አገር ውስጥ ባሉ ልዩ-ልዩ ማኅበረ-ሰቦች ላይ ወይም በአንድ አገር ምልዓተ-ሕዝብ የሚደርስን የፍትኅ-መጓደል እና አድልዖ የተሞላበት ሥርዓት ለመለወጥ እና ሰብዓዊ መብትን፣ የዜጎች እኩልነትን፣ ፍትኅን፣ ወዘተ… ለማረጋገጥ የሚደረግ ትግል የአርነት እንቅስቃሴ ነው። እንቅስቃሴው ወይም ትግሉ በደል አደረሰ፣ ጨቆነ፣ ወዘተ.. ከተባለው ሥርዓት ጋር እንጅ ዜጋ ከሆኑበት  የራሣቸው አገር ጋር አይደለም። በአንፃሩ ለአንድ ማኅበረ-ሰብ ወይም ሕዝብ በነፃ-አውጭነት መደራጀት ዓላማው እና ግቡ በአንድ አገር ከሚኖር ሕዝብ መኻል አንድን የማኅብረ-ሰብ ክፍል ገንጥሎ የራስን አገር ማቋቋምን ዓላማ እና ግቡ ያደረገ እንቅስቃሴ ነው። ይኽ በተገቢ ግልጥ ሊሆን ያስፈልጋል። በመሆኑም፤ የዜግነት መብቴን ተነፈግሁ፣ ጭቆና እና በደል በዝቶብኛል፣ ፍትኅ እና እኩልነት ይረጋገጡልኝ ብሎ የአርነት  ጥያቄዎችን አንስቶ በዳይ ሥርዓትን በሚታገል እና ችግሬ ሥርዓተ-መንግሥቱ ጋር ሣይሆን ከአገር ጋር ነው፣  መፍትኄውም የራሴን አዲስ አገር መመሥረት ነው፤ ምናልባት ከዚያ ዝቅ-ካለም በሉዓላዊ አገሮች መኻል  በሚደረግ ኅብረት /በኮንፌደሬሽን/ መልክ የመሆን ዕድል ይኖር ይሆናል በሚል ስሌት የተቃኘ ትግል ነው። ያ ደግሞ ለምሣሌ እንደ ትሕነግ/ሕወሓት እና ኦነግ፣ ወዘተ… ያሉ ነፃ-አውጭ ድርጅቶች እንመሠርታለን የሚሉት አዲስ አገር ውስጥ ማካተት የሚፈልጓቸውን የአገር ክፍሎች ከወዲኹ አስምረው ይዘዋል፣ እንደ ሉዓላዊ አገር የራሣቸውን ሲኖዶስ እስክማቋቋም ሄደዋል። ታዲያ በዚኽ ሰልቃጭ እቅዳቸው ስንቱ ኢትዮጵያዊ  ከትውልድ ቀየው ማንነትን መሠረት ባደረገ የጅምላ ፍረጃ መጤ፣ ሠፋሪ፣ ወዘተ… እየተባለ ለዘግናኝ  ጭፍጨፋ፣ ቢያንስ ለጅምላ መፈናቀል እንደሚዳረግ ማሰብ ያስፈልጋል።  

እዚኽ ላይ አንድ በበቂ ግልጥ መሆን ያለበት ጉዳይ ሊጠቀስ ይገባል። እሱም በስሙ ነፃ-አውጭ ነን ብለው አገርን የሚታገሉ ድርጅቶችን/ቡድኖችን እና ያ ነፃ ልናወጣህ ነው የሚሉትን ማኅበረ-ሰብ/ሕዝብ የግድ አንድ እና-አንድ አድርጎ ማየት ተገቢ አለመሆኑን ነው። አዎ፣ ማንም ሰው ያለ-ምክንያት ሕይዎቱን ለመስጠት ጭምር ብድግ ብሎ መሣሪያ አንስቶ ዱር-ቤቴ አይልም። በተለይ ማንነት እና ሐይማኖትን መሠረት ያደረጉ በደሎች እና የመገለል ብሶቶች አጥንት ሰብረው የሚገቡ፣ በተለዬ መልኩ ስሜትንም የሚኮረኩሩ በመሆናቸው፣ እንኳን በአሁኑ ጊዜ እየደረሰብኝ ነው ብሎ ለሚያምን፣ እውነትም ይሁን አይሁን ድሮ ክትውልዶች በፊት ደርሶ ነበር ተብሎ የሚሰበክ ትርክት ጭምር ልብ ያሻክራል፣ ያ ደግሞ ብዙዎችን ለተደራጁ ክፍሎች ቅስቀሳ ሰለባ ያደርጋል። ስለሆነም፣ በማንነቴ ወይም በእምነቴ በደል ደርሶብኛል ብሎ ሕይዎቱን መስዋዕት ለማድረግ የተሰለፈን ወገን እንዲሁ በደፈናው ማውገዝ ተበድያለሁ በሚለው ወገን በኩል ለጤናማ ውይይት በር ሊዘጋ ይችላል። በአንድ አገር ዜጎች መኻል በወል ማንነት ዙሪያ የሚከሰቱ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት እስከተቻለ ድረስ ሰላማዊ መንገድን መጠቀም የተሻለ ይሆናል። በመሆኑም፣ ከታጠቁ ክፍሎች በፊት ማኅበረ-ሰብ-ለማኅበረ-ሰብ በሚደረግ ውይይት የተሻለ የመግባቢያ  አውድ ለመፍጠር በቅድሚያ በአገር ሽማግሌዎች እና ሠፋ ያለ አመለካከት ባላቸው ምኁራን በኩል መጀመሩ  ተመራጭ ይሆናል። መፍትኄው ለምን ተበደልኩ አልክ የሚል ስሜትን በማይፈጥር ክልብ በመነጨ መንፈስ  በደልህ በደሌ፣ ብሶትህ ብሶቴ ነው፤ መፍትኄው የማንኛውም ዜጋ ሰብኣዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች እኩል  የሚከበሩበት ለሁላችንም የሚበጅ ፍትኃዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን ተባብረን እና ተደጋግፈን መታገል ነው  ብሎ በቀና መንፈስ ለመረዳዳት መሞከር ያስፈልጋል። ባለፉት ግማሽ ምዕተ-ዓመታት የተከተልናቸው ማንነት በሚሉት ልዩነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካችን ግን ይኽንን ዕድል ስላኮሰሰብን፣ የሕዝብ ዕጣ-ፈንታ በማንነት ዙሪያ በተደራጁ ታጣቂ ኃይሎች ይሁንታ እንዲበየን የሚያደርግ አሉታዊ ጎኑ የበዛ የፖለቲካ ባኅል ሥር እንዲሰድ ተደርጓል። ዕጣ-ፈንታው እንደተሣሰረ የአንዲት አገር ሕዝብ በአስተማማኝ ሰላም ለመኖር እንዲችል እና ቀጣይ ትውልዶች የተሻለ ሕይዎት እንዲኖራቸው አሁን ክምንገኝበት ማንነት ከሚሉት ቁልቁል ከሚያይ አደገኛ የፖለቲካ አባዜ ልንላቀቅ ያስፈልጋል። 

በየትኛውም የአገራችን ክፍል ያለ ሕዝብ ለሚያነሳቸው ብሶት የወለዳቸው እና አግባብነት ያላቸው ጥያቄዎች ሁሉ ሰላማዊ ሕዝብን ጨምሮ ጭፍጨፋ ማካሄድ ተቀዳሚ ምላሹ የሆነው ዐብይ-መሩ የብልጽግና አገዛዝ ለፋኖም ሆነ ለእነዚኽ ታጣቂ ኃይሎች ጠላት ተብሎ መፈረጁ የሚገርም አይሆንም። ጥያቄው ያለው ለፋኖም ሆነ ለሌሎቹ ብልጽግናን ጠላት ብሎ ለመፈረጅ መሠረታዊ የሆኑ መተክላዊ አመክኔዎቻቸው ምንድን ናቸው? የሚለውን በጥሞና መመልከቱ መልካም ነው። ለዚኽም፣- 

ሀ/ ፋኖ በተደራጀ መልክ መታገል የተገደደበት መሠረታዊ ምክንያትም ሆነ ኢትዮጵያን እንደ-አገር ሕዝቧንም  እንደ-ሕዝብ የሚያይበት አቋም እና እምነት እነዚኽ ታጣቂ ነፃ-አውጭ ድርጅቶች ከያዙት እና ከሚታገሉበት ዓላማ እና ግብ ጋር ያለው መሠረታዊ የፖለቲካ እንድነት እና ልዩነት ምንድን ነው? 

ለ/ ያስ በብልጽግና እና በፋኖ መኻል ካለው በምን ይለያል? 

ሐ/ የሕወሓት/ትሕነግ እና የመሰሎቹ ነፃ-አውጭዎች ድርጅታዊ የፖለቲካ እምነት ምንድን ነው? ዓላማ እና ግባቸውስ? በሥራ ላይ የሚገኘው እና የኢትዮጵያውያንን መሠረታዊ የዜግነት መብት የነጠቀው እጅግ ኋላ ቀር እና መርዘኛ የፖለቲካ ሥርዓትን በተመለከተ አቋማቸው ምንድን ነው? ያስ ከፋኖ አቋም ጋር ይጣጣማል ወይስ ይጣረሳል? 

መ/ በ ሐ በተጠቀሰው ላይ በፋኖ እና በነዚኹ ታጣቂ ነፃ-አውጭ ድርጅቶች መካከል የመነሻ-እና-መዳረሻ መሠረታዊ የፖለቲካ አቋም ላይ አንድነት ከሌለ፤ የጋራ ጠላት የተባለው ዐብይ ስለተወገደ ብቻ ሕይዎታችንን እንሰጣለን ብለው የተደራጁበትን እና የሚታገሉለትን ዓላማ እርግፍ አድርገው ሊተዉ የሚችሉበት ተኣምራዊ አሳማኝ ምክንያት ይኖራል ወይ? 

ሠ/ ከበጎ ምኞት እና ከቅን አስተሳሰብ ወጣ እንበልና፣ ከላይ የተጠቀሰው አሳማኝ ምክንያት ከሌለስ ከዚያ በኋላ ለሚከሰተው አይቀሬ ፍልሚያ መልሱ ግዴለም ይዋጣልናል ነው? ለዚያ አይቀሬ ጠብ-በቀጠሮ ሥነ ልቦናዊም ሆነ ድርጅታዊ ቅድመ-ዝግጅት አለ? ከሌለስ? ያ ዓይነት ብቻ የጋራ ጠላት ይወገድ እንጅ ሌላው  የጋራ ጠላት የሆነው ብልጽግና ከተወገደ በኋላ ይደርሳል የሚል ግልብ ስሌት በቅድሚያ ዐማራን ክወዲኹ  መሸክም ላቃተው ለባሰ ተደራራቢ መከራ እና ሰቆቃ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብም ማሰብ ለሚዘገንን የችግር  አዙሪት፣ የጋራ እገራችን ኢትዮጵያንም አገራዊ አንድነቷን ለትርምስ ሊዳርግ አይችልም ብሎ ማሰብ ይቻላል? ለእንደዚያ ዓይነት ማሰብ እንኳ ለሚዘገንን ውጤት በሚዳርግ እንቅስቃሴ ፋኖ አባራ-ተባባሪም አስቻይ ሚና ተጫዋችም ሊሆን ይችላል፣ ይገባልስ?  

ረ/ ከፋኖ እና ከእነዚኽ ኃይሎች ማነው በቅርብ እና በሩቅ ካሉ መንግሥታት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች/ተቋማት ድጋፍ ያለው? ለምን?  

ለሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች የሰከነ ግምገማን ግድ የሚሉ ሃቀኛ ምላሾችን ይሻሉ። 

የቅርብ-ጊዜ ፍላጎትን ወይም ዓላማን ለማሳካት የሚወሰዱ ወይም ተግባራዊ ለሚሆኑ የቅርብ-ጊዜ /ታክቲካዊ/ ትልሞች የሚቀዱት እና መሠረት የሚያደርጉት ከተተለመው የእንቅስቃሴው/የድርጅቱ ልዕለ-ግብ /ስትራተጅ/ እንጅ የተገላቢጦሽ አለመሆኑ ምን-ጊዜም እና በማኛቸውም ሁኔታ ሊዘነጋ አይገባም። በመሆኑም፤ የጋራ  ጠላትን ለመታገል በሚል ከማንኛውም ድርጅት ጋር የሚፈጠር ትብብር/ግንባር፣ ወዘተ… የሚወሰነው ከዚኽ  እኳያ ተመዝኖ ብቻ ሊሆን ይገባል። ከዚኽ መሠረታዊ መርኅ ውጭ የሚፈጠር ግንባርም ሆነ የሚደረግ  ትብብር ፀፀት የማይመልሰው መዘዘ-ብዙ ጉዳትን የሚያስከትል ይሆናል። የልዕለ-ግብ-አስጨባጭ /የስትራተጂያዊ/ የግንባር ይሁን የኅብረት ፈጠራ የዓላማ እና የግብ የመርኅ አንድነትን ግድ የሚል መሆኑም ሊታወቅ ይገባል። 

ወደ ትብብሩ በመግባት “የተሻለ አቅም አገኛለሁ፣ ለዚኽ እስከረዳኝ ድረስ የምጠላውን ከጠላልኝ ጋር ተሠልፌ በጋራ ጠላት ላይ ዘምቸ የጋራ ጠላቴን አስወግዳለሁ” በሚል በጥሞና ያልታሰበበት እና ከሌላው ወገን የሚነገረውን ወይም የተገባውን ቃል እንዳለ በጥሬው በመውሰድ ተባብረን መጣል እንችላለን ከሚል ቀና ከሚመስል ነጠላ እምነት እና እሳቤ በመነሳት የሚደረግ ትብብር፣ ግንባር፣ ወዘተ… ምኞታዊ እና የማይጠቅም  

ብቻ ሣይሆን መርኅን የጣሰ ወዶ-እና-ፈቅዶ አንገት-አስደፊ ሽንፈትን ለመቀበል ፈቃደኛ ከመሆን የተለዬ  አይሆንም። ነፃ-አውጭ ነን ብለው ከተሰለፉ ኃይሎች ጋር በአንድ መሥመር ለመሠለፍ መከጀል ቢያንስ፣ ቢያንስ የኢትዮጵያውያንን መሠረታዊ የዜግነት እና የአገራቸው የሉዓላዊነት ብቸኛ የባለቤትነት መብትን የነጠቀ፣ ለዚኽ ሁሉ ክፍፍል፣ መከራ እና ቀውስ የዳረገን የክልል ሥርዓት አሜን ብሎ ለመቀበል፣ የክልል ሥርዓትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ወድዶ እና ፈቅዶ ክመወሰን የተለዬ አይሆንም። 

በፋኖ በኩል ከእነዚኽ እና መሰል አቋም ካላቸው ጋር ለመተባበር ቢታሰብ እንኳ፣ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን በሚመለከት በሚነሱ መሠረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ በሚኖር የአቋም ልዩነቶች ምክንያት ለሚፈጠር አይቀሬ አለመግባባት ለሚያስከትለው ማናቸውም ሁኔታ በፋኖ በኩል ከወዲኹ በጥንቃቄ የታሰበበት ሥነ-ልቦናዊም ሆነ አስተማማኝ ድርጅታዊ ቁመና እና የተሟላ ቁሣዊ ዝግጅት አለ? ከሌለ ሁኔታው ለሚጠይቀው አስቀድሞ በተዘጋጀው ሊመታ መቻሉ የሚያጠራጥር አይሆንም። የኅልውና ትግል የሚያካሂደው ዐማራ ባለፉት አርባ ዓመታት ያሳለፈውን ሰቆቃ፣ ለደረሰበት የኅልውና አደጋ መዳረግ ምክንያት የሆኑ፣ ትናንት በዐማራ ላይ ጦርነት አውጀው የገደሉ እና በጅምላ ያፈናቀሉ፣ አሁንም ከዚኽ ተልዕኳቸው ያልተቆጠቡ እና የያዙትን ድርጅታዊ መተክላዊ አቋማቸውን ሙጥኝ ያሉ መሆናቸው የታወቀ 

ነው። እምነት እስከሞት እንዲሉ ነውና ዐማራውን ለኅልውና ትግል የዳረጉ እምነቶችን ሙጥኝ ካሉ፣ አለን ለሚሉት ችግር ሁሉ ኢትዮጵያን እንደ-አገር ተጠያቂም ጠላትም አድርገው ከሚቆጥሩ፤ ለዚኽ ደግሞ ዋነኛው ተጠያቂ ዐማራው እንደ-ሕዝብ/ማኅበረሰብ ነው ብለው በዋና ጠላትነት ከፈረጁ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደ ሕዝብ እና አገራዊ አንድነትንም ከማያምኑ እና ከማይቀበሉ፣ በኢትዮጵያ መቃብር ላይ የየራሣቸውን አገር መመሥረት ዓላማቸው መሆኑን ያለ-አንዳች መሽኮርመም በይፋ ከሚሰብኩ፣ ለዚኽ እውን መሆንም በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሚደገፉ እና ዓላማቸውን ለማሣካት ለነዚኽ ባዕዳን ተልዕኮ ተላላኪ ከመሆን የማይመለሱ፣ ወዘተ… ጋር መተባበር ምን ለማሣካት ነው? ብሎ መጠየቅ እና ሃቀኛ ምላሽ ማግኘት ያስፈልጋል። 

ለጊዜው በአገራዊ ሥልጣን ላይ መገኘቱ ካልሆነ በዐብይ አሕመድ ኦሕዴድ-ብልጽግና እና በእነዚኽ ድርጅቶች መኻል ያለው መሠረታዊ የፖለቲካ ቅኝት እና እምነት ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ለእነዚኽ ድርጅቶች  መሠረታዊ በሆኑ የፖለቲካ እቋሞች እና እምነት ፋኖ ነው ወይስ ብልጽግና የሚቀርባቸው? በዐብይ አሕመድ  ብልጽግና እና በእነዚኽ ድርጅቶች መኻል ያለው መሠረታዊ ልዩነት ምንድን ነው? በብልጽግና እና በፋኖ  መኻልስ? ለሚሉት ማጠየቂያዎች የሚሰጠው ምላሽ ለጊዜው ፊት-ለፊት ከሚታየው የዐብይ አሕመድ ብልጽግና በላይም ማዶም አሻግሮ ማየትን ይጠይቃል። ከምንም በላይ በራሱ የውስጥ ቅራኔ እየተንገዳገደ  ያለን ብልፅግና ለማስወገድ በሚል ቅንጭብ ስሌት ላይ በተመሠረተ አካሄድ የሚፈጠር ትብብር፣ ግንባር፣  ወዘተ… የዐማራን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎችም ሆነ የአገር ሉዓላዊነትን እና አንድነትን የሚያክሉ ወሣኝ  ጉዳዮችን ለአደጋ አሣልፎ ከመስጠት የተለዬ አይሆንም።  

በአሁኑ ጊዜ ከሌሎች ታጣቂ ኃይሎች ጋር ተፍጥሯል የሚባለው ትብብር፣ ግንባር፣ ወዘተ… ያቀፈው አንድም የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸውን፣ ኢትዮጵያን እንደ-አገር፣ በተለይም ዐማራን እንደ-ማኅበረሰብ በጠላትነት  የፈረጁ ብቻ ሣይሆኑ፣ በዚኽ የደነደነ አቋማቸው ምክንያት የባዕዳን ሁለንተናዊ ድጋፍ ያልተለያቸው በመሆኑ፣  ሁለተኛ በድርጅት ቁጥር ፋኖን ከመሰሉ በራሣቸው ላይ የታወጀባቸውን የኅልውና አደጋ ከማስወገድ ማዶ  ለኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት እና ለምልኣተ-ሕዝቧ ሉዓላዊነት ከሚታገሉ ኃይሎች ጨርሶ ስለማይመጣጠን፣  በጋራ በሚፈጠር የጋራ ትብብር፣ ግንባር፣ ወዘተ… በሚወሰን ማንኛውም የጋራ ውሣኔ የሚኖራቸው ድምፅ  ነጠላ ቁጥር ነውና በሌሎቹ አብላጫ ድምፅ የመገዛት ግዴታን ከወዲሁ የያዘ መሆኑም ሊዘነጋ አይገባም። ያ ደግሞ ከአሁን በፊት አገር-አቀፍ ነኝ ብሎ የጀመረው እና እራሱን የትግራይ ሕዝብ ነፃ-አውጭ ብሎ የሰየመው ታጣቂ ድርጅት የትሕነግ/ሕወሓት አብሪ /መንገድ-መሪ/ ሆኖ አዲስ-አበባ ያደረሰውን የኢሕዴንን አሣፋሪ ታሪክ መድገም ይሆናል። እንደሚታወቀው ትሕነግ/ሕወሓት አዲስ አበባ የሽግግር መንግሥት ሲያቋቁም ዋነኛ ዓላማው በቋሚነት የያዘውን ተገንጥሎ የራሱን አገር የመመሥረት ልዕለ-ግብ ያሳካልኛል ያለውን የፖለቲካ ሥርዓት ቢያንስ እሱ በበላይነት የሚቆጣጠረው ሥርዓት እውን ማድረግ ነበር። ለዚኽም ተግባራዊነት እንዲያመቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ በታሪካችን ታይቶ-በማይታውቅ ሁኔታ ቋንቋን መሠረት ባደረገ ማንነት ከፋፍሎ ሲያዋቅር፣ በመንገድ-መሪነት ያገለገለውን አገር-አቀፉን ኢሕዴንን ብአዴን በሚል አዲስ ስያሜ የዐማራ ተወካይ አድርጎ በመሾም ያሰበውን እና የቆመበትን ዓላማ ለማሳካት ታማኝ አገልጋዩ አድርጎ ተጠቅሞበታል። ያለ-ኢሕዴን/ብዐዴን እና ለኦሮሞ ሠፊ ሕዝብ በአብዛኛው በጦርነት በተማረኩ የሠራዊት አባላት እና ወዶ-ገብ ምሑር-ቀመሶች የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራቲክ ድርጅት /ኦፒዲኦ/ በሚል ስያሜ ያደራጀው አጃቢነት እና ተላላኪነት፤ ሕወሓት/ትሕነግ/ወያኔ ለአገራዊ ሥልጣን መብቃትም ሆነ እስልቶ ያቀደውን እና እስካሁን ለመከራ-አዙሪት የዳረገንን የጎሣ ማንነትን መሠረት ያደረገ እጅግ ኋላ-ቀር የፖለቲካ ሥርዓት በማቋቋም በኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዓላዊነት እና በአገራዊ አንድነት ላይ ጊዜ-ጠብቆ የሚፈነዳ አደገኛ ፈንጅ ማጥመድ አይችልም ነበር።  

ፍላጎቱን ለማስፈጸም ያደራጀው እና የብዙ ታጋይ ኢትዮጵያውያንን መስዋዕትነት ባስከፈለ ትግሉ በትሕነግ/ሕወሓት የታዘዘውን ሁሉ በታማኝነት በመፈጸም ያገለገለው ብዐዴን፤ የዐማራ ብልጽግና በሚል አዲስ ስያሜ በዚያው የአገልጋይነት ጥንውት የዐብይ አሕመድ “ኦሮሙማ” ተላላኪ ሆኖ እወክለዋለሁ በሚለው ዐማራ ላይ የተከፈተውን ዘግናኝ ፍጅት ግንባር-ቀደም አስፈጻሚ ሆኗል። መለስ ብለን ይኽን አሣፋሪ ክስተት ማስታወስ ያስፈለገው የኃይል-አሠላለፍ ምን-ያኽል በቀና መንፈስ ቢታይ እና ፊት-ለፊት ገዝፎ  

የሚታየንን ጠላት ለመታገል ያስገኛል ተብሎ የሚታሰበውን ጊዚያዊ ጥቅም ብቻ እንዲሁ በጥሬው ታሳቢ  በማድረግ የምጠላውን ከጠላልኝ እና የምታገለውን ከሚታገልልኝ ጋር ቆሜ ዓላማዬን አሳካለሁ ማለት ለምን  ዓይነት ዘለቄታዊነት ያለው ችግር እንደሚዳርግ ለማስገንዘብ ነው። 

ለዜጎች እኩልነት፣ ለማኅበራዊ ፍትኅ፣ ለሕዝብ ሉዓላዊነት እና ለአገራዊ አንድነት በሚታገሉ እና በደልን እና ቂምን ቋጥረው፣ መነሻም መዳረሻም አድርገው በሚቆጥሩ ክፍሎች መኻል መሠረታዊ የአመለካከት እና የፖለቲካ መተክላዊ ልዩነት እንዳለ ምን-ጊዜም ሊዘነጋ አይገባም። መቸም ቢሆን በአንድ አገር የሚኖር

ማኅበረሰብ እንደ-ማኅበረሰብ፤ በዚያው አገር ከሚኖር ሌላ ማኅበረሰብ ወገኑ ላይ የጅምላ በደል አደረሰ የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ የገዘፈ ስህተት ከመሆን አይዘልም። በእርግጥ እራሱን ከአንድ ማኅበረሰብ የሚቆጥር የገዢ ክፍል፣ እንደ-ገዢ በሌላ ማኅበረሰብ ወገኑ ላይ የጅምላም ባይሆን በተለያዩ ምክንያቶች በደል ሊፈጽም አይችልም አይባልም። ማኅበረሰብን እንወክላለን ብለው በነፃ-አውጭ ስም የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ታጣቂ ክፍሎች ግን በደል አደረሰ ለሚሉት ሥርዓት ተጠያቂ የሚያደርጉት ገዥውን ክፍል በተናጠል ሣይሆን ያ ገዥ ያሉት ክፍል አባል ነው የተባለውን ማኅበረሰብ በጅምላ በጠላትነት በመፈረጅ መሆኑ የታወቀ ነው። በተለይም በሕዝብ ያልተመረጠ ገዢ-አካል በሚፈጽመው በደል በዳይ የተባለው የወጣበት ማኅብረሰብ በጅምላ ተጠያቂ የሚሆንበት አንዳችም ጤናማ ምክንያት ሊኖር አይችልም። የዚያ ዓይነት ጥላቻ የወለደው የጅምላ ፍረጃ ምን-ያኽል ርቀት ወደ-ኋላ ሄደን ማን በማን ላይ ምን በደል አደረሰ የሚል የወል መጠፋፋትን የሚጋብዝ የታሪክ ክለሳ ወደፊት አያራምድም። 

ኢትዮጵያውያን ዕጣ-ፈንታችን እንደተሣሰረ ሕዝብ የምንኮራበት በጎውም ሆነ የማንኮራበት መጥፎው ያለፈ  ታሪካችን የጋራችን መሆኑን መቀበል ብቻ ሣይሆን፣ ትኩረት ሰጥተን መረባረብ የሚኖርብን ቀጣይ ትውልዶች  አንገታቸውን ቀና አድርገው እና በራሣቸው/በማንነታቸው ኮርተው በሰላም፣ በአንድነት እና ከኛ በተሻለ  ሕይዎት እንዲኖሩ የሚያስችል ሁኔታን ለመፍጠር ሊሆን ይገባል። ያንን ማድረግ የወል ግዴታችን አድርገን  ካልተቀበልን፣ በተለይ በአሁኑ ጊዜ አገራችን ከምትገኝበት አደገኛ ሁኔታ፣ በነውጥ እየተናጠ ካለው የቀጠናችን  እና ካልሰከነ ዓለም-አቀፍ ይዞታ አኳያ አሁን ያሉ ችግሮቻችንን መፍታት የማይታሰብ ብቻ ሣይሆን፤ ማንም  አትራፊም፣ ተጠቃሚም መሆን የማይችልበትን የጋራ ጥፋት አሜን ብሎ ለመቀበል ከመወሰን ተለይቶ ሊታይ  አይችልም።  

ሐ. መደምደሚያ፤-  

 በአሁኑ ጊዜ ባለው አሉታዊ ጎኑ በበዛ ነባራዊ ሁኔታ በራሱ የውስጥ ቅራኔ እየተንገዳገደ ያለን ብልፅግናን ለማስወገድ በሚል ቅንጭብ ስሌት ላይ በተመሠረተ አካሄድ የሚፈጠር ትብብር፣ ግንባር፣ ወዘተ… የሰከነ ግምገማን ይጠይቃል፣ በተገቢ የታሰበበት አሳማኝ ምላሽም ያስፈልገዋል። ከእነዚኽ ድርጅቶች ጋር ኅብረት ቀርቶ ጊዚያዊ ትብብር ለመፍጠር ከመከጀል በፊት ለእነዚኽ መሠረታዊ ጥያቄዎች የምር መልስ መስጠት ያስፈልጋል። አዎ፣ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ እነዚያ ድርጅቶች እንወክለዋለን በሚሉት ማኅበረሰብ ላይ ደረሰበት/አለ የሚሉትን ፍትኅን የሚጠይቅ ብሶት በቀና መንፈስ በመውሰድ ከነሱ ጋር መተባበር ተገቢ ነው ከሚል እምነት በመነሣት መሆኑ የሚያጠያይቅ አይሆንም። ፋኖ የሚታገለው በማንነቱ ምክንያት በመሠረታዊ ኅልውናው ላይ ጦርነት ለተከፈተበት ለዐማራው ብቻ ሣይሆን፣ የሱ መብቶች በአስተማማኝ  እና ዘለቄታዊነት ባለው ሁኔታ የሚከበሩት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ሙሉ ነፃነት እና እኩልነት  

ሲከበሩ፣ ፍትኅ ሲሰፍን መሆኑን የሚያምን፣ ለዚያ እውን መሆንም የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ያለ-አንዳች  ማመንታት ከመታገል ወደ-ኋላ እንደማይል የታወቀ ነው። ስለሆነም፣ የራሱን ኅልውና በማረጋገጥ ተመሣሣይ  እምነት ካላቸው ወገኖች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያውያን በነፃነት እና በእኩልነት የሚኖሩባት አገር እንድትሆን  ማድረግ የትግሉ ልዕለ-ግብ መሆኑ ሊታወቅ ያስፈልጋል። 

ከዚኽ ውጭ የዐብይን የብልጽግና አገዛዝ መቃወምን ብቻ እንደ-መመዘኛ በጥሬው በመውሰድ በፖለቲካ  እምነትም፣ በዓላማም ሆነ በግብ ዓይን-ለዓይን ከማይተያዩ ኃይሎች ጋር ለመተባበር መወሰን፤ የዐማራውን  ሕዝብ ኅልውና ለማስከበር የሚደረገውን ትግል ለታመለት ግብ ማብቃት እንዳይችል የሚያደርጉ እክሎችን  ከማትረፍ ባለፈ፣ ለዚኽ የተቀደሰ ዓላማ ተሠልፈው በየጦር-ግንባሩ ምትክ-የሌላት ሕይዎታቸውን የሰዉ  ሰማዕታትን ክቡር መስዋዕትነት የሚያረክስ ተግባር ከመሆን ይቆጠራል።  

ተፈጥሯል በሚባለው የዚኽ ግንባር/ስብስብ አባላት ዘንድ – ቢያንስ በአንዳንዶቹ – ከፋኖ ጋር መሠለፍ  የሚፈልጉበት አንዱ ምክንያት የዐብይን አገዛዝ ለማስወገድ በሚደረገው ዘመቻ በሚኖረው አስተዋጽዖ ላይ  ብቻ የተወሰነ ሣይሆን፤ አንድም ለቆሙበት ፀረ-ኢትዮጵያ አንድነት ዓላማ እውን መሆን ለኢትዮጵያ አገራዊ  አንድነት የማያወላውል አቋም ያለውን ፋኖ በዚኽ የጋራ-ጠላትን ለማስወገድ በሚል ዘመቻ ተሣታፊ ሲሆን  ክልሉ ዋነኛ የጦርነት ሜዳ እንዲሆን በማድረግ ከአሁን በፊት ሕወሓት ካደረሰው ጉዳት በላይ  እንዲያስተናግድ፣ እዚያው-በዚያው የፋኖ ኃይል እንዲዳከም፣ ከሕዝብም እንዲነጠል፤ ብልጽግና ሲወገድም  የአገሪቱ የወደፊት እጣ-ፈንታ የሚወሰነው ፋኖን በመሰሉ የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነት አጥብቀው በሚሹ  ሣይሆን በፀረ-አንድነት ኃይሎች ፍላጎት እና ፈቃድ እንዲሆን ያስችላል ከሚል መርዘኛ ስሌት አይደለም  ማለት፣ ቢያንስ ድርጅቶቹ እና የባዕዳን ደጋፊዎቻቸው የኢትዮጵያን አንድነት ምን ያኽል እንደሚጠሉት  ካለመገንዘብ የመነጨ የበዛ ግብዝነት ይሆናል። በአንዳንድ ጎረቤት አገሮች እና ግብፅን በመሰሉ ትንሽ ራቅ  ባሉት ጭምር የኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት፣ ልማት እና እድገት መረጋገጥ የእነሱን ጥቅም ብቻ ሣይሆን  ኅልውናቸውን የሚጋፋ አደጋ አድርገው እንደሚቆጥሩት ምን-ጊዜም መረሳት የለበትም። 

በአሁኑ ጊዜ ፋኖን ጨምሮ ተፈጠረ በሚባለው ትብብር ውስጥ አሉ የሚባሉት ኃይሎች ጋር ፋኖ አባል ከሆነ የሚከትሉትን በታሪክም፣ በኃላፊነትም የሚያስጠይቁ ችግሮች እንደሚያስከትል ከወዲኹ ማወቁ አስፈላጊ ይሆናል።  

ሀ. በፋኖ ኃይሎች መኻል ካለመግባባት አልፎ ለእርስ-በርስ ደም-አፋሳሽ ሁኔታ ለሚያደርስ ልዩነት ይዳርጋል፤ ለ. ፋኖ በአሁኑ ጊዜ በሕዝብ ዘንድ ያለውን መሰል-የሌለው ተቀባይነት ያሳጣዋል፤ ሐ. በአገዛዙ ሥር የሚገኘው እና እየተሰላቸ ባለው የመከላከያ ሠራዊት ተቋም ሥር ያሉ የጦሩ አባላት፤ በተለይም ዓማራ በሆኑ እንዲሁም ፋኖን በኢትዮጵያዊ አቋሙ የሚያምኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወደ-ፋኖ እንዳይቀላቀሉ ሰበብ ይሆናል፤ 

መ. በአገር-አንድነት እና በሕዝብ ክብር እኩሪ ታሪክ ያለውን ፋኖ በተፈጥሮ ባኅሪውም ሆነ በታሪኩ የማይታወቅበትን ከፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች፣ አልፎም ከባዕዳን ጋር ተባባሪ ሆነ የሚል ስም-አጥፊ እና ታሪክ አጉዳፊ አዲስ ልጥፍ ሊያስከትልበት እና ያም ቶሎ የማይሽር ያልታሰበ የውስጥ ችግርን ሊፈጥርበት ይችላል፤ ሠ. ይኽ ዓይነት አርቆ-ያላዬ ትብብር በተለይ የዐማራውን ክፍል /ክልል/ ወታደራዊ ፍልሚያ የሚደረግበት ዋነኛ የጦር ቀጠና ስለሚያደርግ በቀላሉ ለማገገም አዳጋች ለሚሆን የመሠረታዊ አገልግሎት-ሰጪ ተቋማት ውድመትን ሊያስከትል፣ ከወዲኹ መኖር የከበደውን ሕዝብም ሊሽከመው ለማይችል ለባሰ ችግር ሊዳርግ ይችላል፤ 

ረ. አገርን በቀላሉ ለማይበርድ እና ኅልውናዋን አጥብቆ ለሚፈታተን የቀውስ-አዙሪት ይዳርጋል፤ ሰ. ከዚኽ ዓይነት መርኅ-የለሽ የኃይል አሠላለፍ በፖለቲካውም ሆነ በወታደራዊ መስኩ አትራፊዎቹ1- ሰ. ሀ/ በኢትዮጵያ ኪሣራ የራሣቸውን አዲስ አገር መመሥረትን ግባቸው ባደረጉ፣ ወይም ሕዝብን ከፋፋዩ እና ፀረ-አንድነቱ የክልል ሥርዓት እንዳይነካ ብቻ ሣይሆን ይበልጥ ይገባናል የሚሉትን ክፍል አካትቶ እንዲቀጥል የሚፈልጉ በነፃ-አውጭ ስም የተደራጁት ታጣቂ ኃይሎች፤ 

ሰ. ለ/ ከዚኽ ዓይነት ትብብር የየራሣቸውን ጥቅም ለማስከበር በሚሹ እና ለዚያ እውን መሆን የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነት እና ሰላም እንደ-እንቅፋት የቆጠሩ እና የተከፋፈለች ቢያንስ የውስጥ ሰላሟን ያጣች እንድትሆን አጥብቀው የሚፈልጉ እና ለዚያም እውን መሆን አበክረው ሲጥሩ የነበሩ፤ ተቃዋሚዎችን በማሰልጠን፣ በማስታጠቅ እና ከለላ በመስጠት የሚታወቁ የቅርብም የሩቅም ባዕዳን፤ ይሆናሉ። 

ሁሉም ባይሆኑ ከእነዚኽ ድርጅቶች መኻል ብዙዎቹ እንወክለዋለን የሚሉትን ማኅበረሰብ በትክክል  ይወክላሉ ብሎ መውሰድ ያንን ማኅበረሰብ መናቅ ይሆናል። አንዳንዶቹ እንወክለዋለን የሚሉትን ማኅበረሰብ  እንወክላለን የሚሉ ሌሎች ቡድኖች እንደሚኖሩ የታወቀ ነው። አንዳንዶቹም እንወክለዋለን በሚሉት  ማኅበረሰብ ለደረሰ ችግር ጠተያቂ የሚሆኑ ናቸው። ዞሮ-ዞሮ ዐማራን ከተዘመተበት የኅልውና አደጋ ለመታደግ  የሕይዎት መስዋዕትነት በመክፈል እየታገለ ያለው ፋኖ ዓላማውን ለማሳካት ከአሁን በፊት በማንነቱ ምክንያት  በዋና ጠላትነት ፈርጀው ከዘመቱብት፣ ካፈናቀሉት፣ ወዘተ… ብቻ ሣይሆን አሁንም ወደፊትም ከዚያ እኩይ  እና ኋላ-ቀር አስተሳሰብም እምነትም ካልተላቀቃቸው ኃይሎች ጋር አብሮ ለመሠለፍ መከጀል ቢያንስ  ጊዜውም ሆነ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚጠይቅም፣ የሚያስፈልግም አይደለም። ያ እንዲሆን መፍቀድ ደግሞ  የእነዚያን ድርጅቶች ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም እና ዓላማ እውቅና ከመስጠት እና አቋማቸው ትክክል መሆኑን  እንዲገፉበት፣ አልፎም ወደ-ኋላ መመለስ የማያስችል ሕጋዊ ዋስትና ከመስጠት የማይተናነስ አሉታዊ ወሣኝነት ያለው አሣዛኝ ድርጊት ይሆናል።  

ይኽን መሰል ጠጣር እውነታ ባለበት ሁኔታም ቢሆን የዐማራውን የኅልውና ትግል በማካሄድ ላይ ያለው ፋኖ  በቂ አቅምም፣ ኃይልም አለው። ፋኖ አግላይነት የሌለው እና ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ፍትኅን የሚጠይቅ  እንቅስቃሴ በመሆኑ ከዐማው አልፎ የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነት በሚደግፉ ሌሎች ወገኖች ጭምር በተስፋ  የሚታይ እና ድጋፍ ያለው መሆኑም አሌ የሚባል አይደለም። ስለሆነም፤ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነት  ላይ የጠራ እምነት ያለው ፋኖ ይኽን አቅሙን እና ኃይሉን በቅድሚያ ያልተጠቃለሉ የፋኖ ኃይሎችን  በማካተት እና በሌሎች ቀጠናዎች የሚገኙ እና በኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት ላይ ብዥታ የሌላቸውን ወገኖች  በማስተባበር ጥረት ላይ ሊያውለው በተገባ ነበር። የጋራ ጥላትን በጋራ ለመታገል በሚል እሳቤ በተከበረው  ፋኖ ስም ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ላይ የጠራ አቋም ከሌላቸው ሌሎች ኃይሎች ጋር ለመተባበር  የሚደረግ ማናቸውም ሙከራ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት እንደሚሆን ከወዲኹ ግልጥ ሊሆን ያስፈልጋል።  

ፋኖ ሙሉ ትኩረቱን መስዋዕት እየከፈለበት ባለው ሕዝባዊ ትግል የዐማራን ኅልውና ከማስከበር አልፎ የአገርን አንድነት እና የዜጎችን መብቶች ማስከበር የሚችል ፍትኃዊ መንግሥታዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን መሰል እምነት ካላቸው ኢትዮጵያውያን ጋር እንጅ ዓላማ እና ግባቸው ዐማራን እንደ-ማኅበረ-ሰብ እና ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን በጠላትነት ከፈረጁ ኃይሎች ጋር ሊሆን ጨርሶ ተገቢ አይሆንም። አዎ፣ እነዚያ ዐማራን እና ኢትዮጵያን በጠላትነት ፈርጀው የቆሙ ኃይሎች በያዙት አቋም ላይ ልዩነት ቢኖርም፣

ወደ-መኻል እንዲመጡ እና ይችን የጋራ አገራችንን ቢያንስ ለቀጣይ ትውልዶች ሰላም፣ እኩልነት እና ፍትኅ የሰፈኑባት፣ የሚቸገሩባት ሣይሆን ወድደው የሚኮሩባት አገር እንድናስረክባቸው የሚያስችል ሁኔታን እውን ለማድረግ ከእልህ እና ከባዕዳን በቀር ማናችንንም አትራፊ-እና-ተጠቃሚ ከማያደርግ የእርስ-በርስ መተላለቅን ከሚጋብዝ ይዞታ ይልቅ ለውይይት እና ምክክር ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግ ሁሉም በቀና መንፈስ እንዲረዳው ያስፈልጋል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ እና የኅልውና ትግሉ ወሣኝ ምዕራፍ ላይ ፋኖ ከፀረ አንድነት ኃይሎች ጋር ለመተባበር አይደለም እነሱን ለመቃወም የሚያጠፋው/የሚያባክነው ጊዜ ሊኖረው  አይገባም።  

 የሕይዎት መስዋዕትነትን ጨምሮ ፈርጀ-ብዙ ዋጋ እያስከፈለ ያለው የፋኖ እና የሌሎች ኢትዮጵያውያን  ትግል ልዕለ-ግቡን አሳካ የሚባለው አስተማማኝ አገራዊ አንድነትን የሚያስከብር እና የዜጎችን ሰብዓዊ፣  ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መብቶችን የሚያረጋግጥ ፍትኅዊ፣ ዴሞክራሲያዊ-ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እውን  ማድረግ ሲቻል ብቻ ይሆናል። ይኽ እውን መሆን የሚችለው ደግሞ በምኞት ሣይሆን በጊዜው መንግሥታዊ  ሥልጣን ላይ ያለውን አካል ምን-ያኽል እንዲለውጥ ብንሻ እና መወገድ እንዳለበትም አስፈላጊነቱ  የሚያጠያይቅ ባይሆንም፣ በሕዝብ ዘለቄታዊ ሰላም እና በአገር አንድነት ኪሣራ ሊሆን ክቶ አይገባም። መቸም  ቢሆን መንጋቱ ለማይቀር ሌሊት፣ ቤቴ ጨለመ ተብሎ ቤት አይቃጠልም።  

የጠላቴ-ጠላት ወዳጅ ይሆናል የሚል ጥሬ እሳቤን መሠረት አድርጎ የጋራ-ጠላትን በጋራ ለመታገል በሚል ግልብ ፈሊጥ ኢትዮጵያን እንደ-አገር እና ኢትዮጵያዊነትን እንደ-እሴት ችግራቸው አድርገው በመቁጠር በነፃ አውጭ ስም ከሚታገሉ እና ያንን ዓላማ ለማሳካትም በቀጥታ ጭምር በኢትዮጵያ ላይ ወረራ እስከመፊጸም ከሄዱ፣ በቻሉት መንገድ ሁሉ ከመተነኳኮስም ካልቦዘኑ ባዕዳን ጋር ትሥሥር ካላቸው እና እርዳታ ከሚቸራቸው ኃይሎች ጋር ትብብር/ግንባር፣ ወዘተ.. ለመፍጠር መከጀል፣ የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች ከሚባል ከከንቱነት ያለፈ ተግባር ይሆናል። ስለሆነም፤ በአገር-ውስጥ ካሉም ሆነ መቸም ቢሆን ቅድሚያ የሚሰጡት ለራሣቸው ጥቅም ብቻ ከሆነ ባዕዳን ኃይሎች ጋር የሚፈጠር/ሩ የኃይል/የኃይሎች አሠላለፍ በተለይ ለፋኖ ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ ማስተዋል የጎደለው፣ አደገኛ መዘዝ-ጎታች እና ታሪክ አጉዳፊ አሳፋሪ ድርጊት ከመሆን ተለይቶ የማይታይ ከባድ ስህተት ይሆናል። 

ለጊዜው በመንግሥታዊ ሥልጣን ላይ የሚገኘውን፣ አንዳችም የኃላፊነትም የተጠያቂነትም መንፈስ  ያልፈጠርበትን፣ ከነግሳንግሱም መወገድ ያለበትን የብልጽግና አገዛዝ እና፤ መሠረታዊ የሆኑትን የአገርን  አንድነት እና የሕዝብን ሰላም የሚያኽሉ የገዘፉ መተክላዊ ዓላማዎች በአንድ ተመሣሣይ ሚዛን ላይ ማስቀመጥ  ተራ ስህተት ሣይሆን ማስተዋል የጎደለው አደገኛ የእብደት ተግባር ይሆናል። በትግሉ ሂደት ከሌሎች ኃይሎች ጋር የሚፈጠር የኃይል-አሠላለፍ አስፍላጊነትም፣ ጠቀሜታም የሚኖረውን ያኽል፤ ከማን/ከነማን ጋር እና ለምን ልዕለ-ግብ ለሚሉት ጥያቄዎች በጥንቃቄ የታሰበበት እና ተገቢ መልስ ከሌለው፣ ፀፀት የማይመልሰው ዘለቄታዊነት የሚኖረው ጉዳትን እና ጥፋትን ሊያስከትል እንደሚችልም በጥብቅ መታሰብ ይኖርበታል። ለዚያ አደጋ ተጋላጭ የሚያደርገው ደግሞ የተለያዩ ጊዚያዊ ጥቅማ-ጥቅሞችን ለማግኘት ሲባል በአመራር ላይ ባሉ ወይም ለእነሱ ቅርብ በሆኑ ቡድኖች/ግለሰቦች የተሣሣተ ግንዛቤ ላይ የተመረኮዘ አርቆ-ያላዬ ውሣኔን ተከትሎ ተግባራዊ እንዲሆን ሲፈቀድ ነው። መሠረታዊ መርኅን የሚጥስ ያ ዓይነት ተግባር የግፍ ሰለባም የትግሉ ደጋፊም የሆነውን ሕዝብ ብቻ ሣይሆን በትግሉ የታቀፉትን እና መስዋዕት እየከፈሉ ያሉትን የፋኖ አርበኛ ታጋዮች አሳብ ለማካተት ዕድል ያልሰጠ ስለሚሆን፣ የውስጥ አንድነትን የሚሸረሽር እና ለከባድ ችግር የሚዳርግ ልዩነትን የሚያስከትል መሆኑ ከወዲኹ መታውቅ አለበት። ያን መሰል ከባድ ታሪካዊ ስህተት ደግሞ ፋኖ የቆመለት እና የሚታገልለት ዐማራን ከተደቀነበት የኅልውና አደጋ ከመታደግ ባለፈ ለዜጎች ሁሉ አንድነት እና እኩልነት፣ ለኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት እና ለኢትዮጵያዊነት እሴቶች ባለው የማያወላውል አቋሙ በበጎ የሚመለከተው ብቻ ሣይሆን የሚደግፈውን እና በተስፋም የሚጠብቀውን ኢትዮጵያዊ ወገኑን የሚያስክፋ እንደሚሆን የሚያጥራጥር አይሆንም። የድርጊቱ ተስፋ-አጨላሚነትም በስማቸው ነፃ እናወጣችኋለን የተባሉ ማኅበረ-ሰቦችንም ከነዚኽ ቅን-አሳቢ እና አገር-ወዳድ ወገኖች ጎራ የሚጨምር እንደሆነ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል። 

ድል ለፋኖ!! 
ፍትኅ ለኢትዮጵያውን ሁሉ!!!  
ኢትዮጵያ አንድነቷ ተከብሮ በነፃነት ትኑር!!!! 

አገራዊ አንድነታችን ለጋራ ኅልውናችን መሠረት እና ምትክ-የሌለው ዋስትና ነው!!!!! 

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News