
ከ፦ የታሪካዊና የህልውና ትግሉ ተቆርቋሪ (በዶ/ር ሶስና ታደሰ)
ለ፦ በጎንደርና በመላው አማራ ምድር መሬት ላይ ላላችሁ እውነተኛ የፋኖ አበጋዞችና ታጋዮች
የተከበራችሁ የአማራ የሕልውናችን አጥርና በተለይም የጎንደር ወታደራዊ አቅም ማዕከል የሆናችሁ ታጋዮች፤
ከዚህ በፊት የ«ፅምዶ»ን አደገኛነት በተለይም «ፅምዶ ፋኖን ለሕወሓት ተራ እግረኛ ቅጥረኛ ወታደር ያደርገዋል፤ ከዚህ አሰላለፍ ወጥታችሁ የድርጅት ነፃነታችሁን አስከብሩ፤ ወይም ይህንን ማድረግ ካልቻላችሁ በአስቸኳይ ከዚህ አፋብን ከሚባል መዋቅር ራሳችሁን በማግለል በራሳችሁ ዕዝና ነፃ ድርጅት ቁሙና መልሳችሁ ያጣችሁትን የሕዝብ ተቀባይነት አግኙ» የሚል ተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጋችን ይታወቃል።
ይሁን እንጂ እናንተ አንድም እርምጃ ሳትወስዱ፦
- መስከረም 10 ቀን 2019 ዓ.ም. የድርጅታችሁ መሪ ተብዬው ዘመነ ካሴ መቀሌ ላይ ሆኖ የፅምዶን ፀረ-አማራ የትብብር ኃይሎች መግለጫ ሲያነብ በትግራይ ቴሌቪዥን ከእናንተ እኩል ተመልክተናል!
- መስከረም 17 ቀን 2019 ዓ.ም. የድርጅታችሁ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ሄኖክ ኪዳኔ በሰጠው የሚዲያ ማብራሪያ፣ በራያ ዘብና በተከዜ ዘብ ዙሪያ በተነሳለት ጥያቄ ላይ፦ «የራያ ዘብም ሆነ የወልቃይት ዘብ ከሥርዓቱ ጋር ትጥቅ ይፈታል፤ የሚያስጠይቀው ወንጀል ካለ በወንጀል ይጠየቃል» ብሎ የማንነታቸውን፣ የርስታቸውንና የሕልውናቸውን አስጠባቂ የአማራ የቁርጥ ቀን ልጆችን ትጥቅ አስፈትቶ በወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ የተዘጋጁ መሆኑን በግልጽ ተናግሯል!
የዚህ ንግግርና የፖለቲካ አቅጣጫ ዋና ትርጉም፦
የሄኖክ ኪዳኔ ንግግር ዋና ዓላማ በግልጽ እንደወረደ ሲተረጎም፦ ሕወሓት በአማራ ሕዝብ ላይ በተለይም በሸዋ፣ በጎንደር (ወልቃይት/ጠገዴ/ጠለምት) እና በቤተ-አማራ ወሎ (ራያ) ሕዝብ ላይ የፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለማጠብና ከወንጀሉ ነፃ አድርጎ፣ የወልቃይትና የራያን አማራ ሕዝብ ትጥቅ አስፈትቶ ለጠላት አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጀ የፖለቲካ ወጥመድ ነው! ይህም በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ የተሰጠበት አሁን ግን በይፋ የተገለጠ አስነዋሪ ሴራ መሆኑን መላው ሕዝብ ተገንዝቦታል።
ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ የይስሙላ የወሰን ውዝግብ ሳይሆኑ የአማራ ሕዝብ፣ የአማራ ህልውናና የጎንደርና የወሎ ቤተ-አማራ የፖለቲካና የወታደራዊ አቅም ማዕከላዊ ደም ስሮች ናቸው!
ጎንደር የታሪክ፣ የጀግንነትና የነፃነት አምባ እንጂ የጠላት ማስፈጸሚያና የባርነት ካምፕ ሆና አታውቅም! ታዲያ እናንተ የዚህ ታሪካዊ ውርደትና የወልቃይት/ራያ ርስት አሳልፎ ለመስጠት የሴራ እቅድ አካል ሆናችሁ በዝምታ የምትቀጥሉት እስከመቼ ነው?
የሚቆረቆርላችሁን ማህበረሰብ ምክር ጆሮ ዳባ ልበስ ብላችሁ እንዳሳለፋችሁ ይታወቃል። ቢያንስ ግን አሁን የራሳችሁ የምትሏቸው መሪዎቻችሁ ከእናንተ ዓላማና የትግል ግብ ውጭ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን በተግባር እያያችሁ ነው! የሊሐቃኑን ምክር ለመስማት ቢከብዳችሁ እንኳ ያላችሁበትን ሁኔታ አይቶ የሚንቃችሁ የጠላት ስብስብ እንዳለ ካወቃችሁ ሊያነቃችሁ ይገባል።
- ትብብር በሚል የዳቦ ስም የፅምዶ የባርነት ካምፕ ውስጥ ተደፍቃችሁ እስከመቼ ተራ ቅጥረኛ የሕወሓት ወታደር ሆናችሁ ታደፍጣላችሁ?
- እስከመቼ ከወጣችሁበት የትግል ዓላማ፣ ከጎንደር የጀግንነት ሌጋሲና ከራያና ከወልቃይት የአማራነት ጥያቄ ጋር ተጣልታችሁ ታዘግማላችሁ?
- እስከመቼ ደጀን ከሆናችሁ ማህበረሰብ ጋር ተራርቃችሁ ትዘልቃላችሁ?
ይህ አፋብን የሚባል ፀረ-አማራ ስብስብ ለተከዜ ዘብ የማይራራና ትጥቅ አስፈታለሁ እያለ ሲፎክር ማን ማለት እንደሆነ ልብ ማለት ይገባል፣ እናንተም በተከዜ ዘብ መነጸር የምትታዩ የአማራ ዘቦች ናችሁ! ስለዚህ እንደ ሄኖክ ኪዳኔ አገላለጽ በፀረ-ሕወሓት ትግል ላይ በመሳተፋችሁ ትጥቅ ትፈታላችሁ፣ ብሎም የወንጀል ተጠያቂ ትሆናላችሁ ማለት ነው! ምክንያቱም አብዛኞቻችሁ የምትታወቁት ሕዝባችሁን ለመታደግ በፀረ-ፋሽስት ሕወሓት ትግል ላይ በመሰለፋችሁ ነው። ስለሆነም የአፋብን የትግል መስመር ፀረ-አማራ ብሎም የሕወሓት የሴራ ወጥመድ አስፈጻሚ መሆኑን በግልጽ ካያችሁ፣ ያላችሁበት የትግል ማዕቀፍ የጠላቶቻችሁ ወጥመድ መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
ጥሪያችን፦
እውነታውን ተቀበሉ! የከፈላችሁትን ከባድ መስዕዋትና የመጣችሁበትን የትግል መስመር አስቡ! የወጣችሁለትን ታሪካዊ የትግል መስመር መሳቱን በድጋሚ መርምሩ፣ ከሐሰት ፕሮፕጋንዳ ራሳችሁን በማራቅ በዙሪያችሁ ያለውን የሕዝብ ትርታ አድምጡ! ተከዜ ዘብ በሕወሓት የሚመጣውን አውዳሚ ጦርነት ገድቦ የያዘ ለአማራ ሕዝብ ብሎም ለናንተ ቁጥር አንድ ጠባቂያችሁ ነው! ስለሆነም ከደጀኑና ከጠባቂው ማህበረሰባችሁ ጋር ተጣልታችሁ የጠላቶቻችሁን የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ ካርድ ከመሆን በጊዜ እንድትቆጠቡ እና በጎንደር ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ሐምሌ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. ያወጣችሁትን መግለጫ መሠረት በማድረግ ግልጽ አማራዊ አቋማችሁን እንድታስፈጽሙ በጥብቅ እናሳስባለን! ከፋሽስት ወራሪ ሕወሓት ነፃ የሆኑ የአማራ ርስቶች በአማራነት በደምና በአጥንት የተገነባ የነፃነት ምድሮች እንጂ በፅምዶ ደላሎች ስምምነት የሚደራደሩበት የንግድ እቃ አይደሉም!
የአማራ ሕልውና፣ የፍትሕና የርስት ጥያቄ በፀረ-አማራና በፀረ-ኢትዮጵያ ደላሎች ቁማር አይሸጥም! ነፃነትን የሚያፃና ታጋይ ሁኑ!!
ድል ለአማራ ሕዝብ!
ፍትሕ፣ እኩልነትና ነፃነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena







መቸም አንድን ሰው አንድን ነገር ለምን በተረዳኸውና/ሽውና በራስህ/ሽ ግልፅ በሆነ ምክንያት በተቀበልከው/ሽው መጠን ለምን ታስተጋባለህ/ሽ ማለት ትክክል አይደለምና ከላይ ያለው ፅሁፍና የፀሐፊው ጉዳይ መታየት ያለበትም ከዚሁ መሠረታዊ አቀራረብ ነው።
ፀሐፊዋ በተከታታይና በተደጋጋሚ ለምንና እንዴት ከእነገሌ ጋር ትብብር ይታሰባል? ከፀረ አማራ ሃይሎች ጋር …? ወዘተ የሚል ጥያቄ ማቅረባቸው በራሱ ተገቢ እንጅ ክፋት የለውም። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን የትብብሩ መሠረታዊ ተልእኮና ዓላማ የእኩያን ገዥዎችን የጭካኔ አገዛዝ አስወግዶ በሽግግር ፍትህና በመሸጋገሪያ መንግሥት አማካኝነት እውነተኛና ዘላቂ የጋራ ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ለማድረግ ይቻል ዘንድ ከፍተኛ ጥንቃቄና/አያያዝና እልህ አስጨራሽ እርብርብን ግድ ይላል የሚል ሂሳዊ ሃሳብ/ትንታኔ መሰንዘር ተገቢና ገንቢ ይሆን ነበር ።
በመሠረቱ በመንበረ ሥልጣን ላይ በተፈራረቁና በሚፈራረቁ ሴረኛ ጨካኝ ገዥዎች ምክንያት ኋላ ቀርና ጋግርታም በሆነው የፖለቲካ ባህላችን ምክንያት ለዘመናት ስንጠላላና ስንገዳደል ከኖርንበት የፖለቲካ አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት ይቻለን ዘንድ ካለፈው ታሪካችን ተምረንና እየተማርን እናም ከልብ እየተፀፀትን በመተባበር ትውልዳዊ ሃላፊነትንና አደራን እንወጣ የሚል ገንቢ የሆነ ሂሳዊ አስተያየት/ትችት ከመለገስ ይልቅ እንዴት ከእገሌ/ከእነገሌ ጋር ? የሚል ዘመቻ ተምሮ ከመገኘት/ከምሁርነት መሠረታዊ ትርጉም () ጋር ፈፅሞ አይገጥምም።
ዘመነ ካሴን በፖለቲካ ህይወቱና ተሳትፎውን እንጅ በግል አላውቀውም። እንከን የለሽ ፖለቲከኛ እንዲሆን እየጠበቅንበት ከሆነ እንኳንስ በእኛ አይነት የፖለቲካ ባህልና ታሪክ በአንፃራዊነት ዘምኗል በሚባልም እንከን አልባነት የሚጠበቅ አይደለምና ትክክል አንሆንም። ከዚህ አንፃር ሂሳዊ ትችትን ገንቢ በሆነ ይዘትና አቀራራብ መግለፅ ሲቻል “የድርጅታችሁ መሪ ተብየው ዘመነ ካሴ” የሚል የጥላቻና የንቀት አአነጋገር ግን ዝቅ የሚያደርገው ዘመነን ወይም የትግል ጓዶቹን ወይም ተባባሪ ሃይሎችን ሳይሆን ትችት ሰንዛሪዎቹን እኛኑ ነው።