Homeነፃ አስተያየትምንድነው የመጀመሪያ ምርጫችን? ጦርነት ወይስ የፖለቲካ ስምምነት?

ምንድነው የመጀመሪያ ምርጫችን? ጦርነት ወይስ የፖለቲካ ስምምነት?

Advertisement
World Wide Travel Group
ፋይል

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com) 

የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ሥልጣን ላይ በቆየባቸው ባለፉት ስምንት አመታት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የግጭትና የእርስበርስ ጦርነት ምልክት ሆና ቆይታለች። ኦሮሚያ ውስጥ የትጥቅ ትግል ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፣በአማራ ክልልም ውጊያ ከተጀመረ ከሦስት ዓመት በላይ ሆኖታል። ትግራይ ውስጥ ከ2013 እስከ 2015  እልህ አስጨራሽ አውዳሚ ጦርነት ተካሂዷል፣ የትግራይ ህዝብ ይህ አውዳሚ ጦርነት ጥሎበት ካለፈው ጠባሳ ሳይድን ሌላ ጦርነት ታውጆበታል። “ትብብር ለህልውና” የሚባል የታጣቂዎች ጥምረት ከተፈጠረ ገና አንድ ወር ሳይሞላ አዲስ አበባ፣ደብረዘይት፣ኮምቦልቻና ባህርዳር ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። ነገሮች በዚህ ከቀጠሉ መዳረሻችን የት ይሆን? ለመሆኑ በዚህ ጦርነት አሸናፊና ተሸናፊ ይኖራል? ደሞስ ተሸናፊው ወገን መሸነፉን ተቀብሎና ጦርነት ውስጥ እንዲገባ ያደረጉትን ምክንያቶች ሁሉ ረስቶ ሠላማዊ ኑሮ መኖር ይጀምራል? ባለፉት ሃምሳ አመታት እኛ ኢትዮጵያዊያን የተጓዝነው እያንዳንዱ ምዕራፍ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየን፣ አንድ ወገን በወታደራዊ ኃይል ሌላውን አሸንፎ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት የሚችልበት ዕድል በጣም ጠባብ እንደሆነ ነው። ጦርነት ኢትዮጵያን ከድጡ ወደማጡ ይወስዳት እንደሆነ ነው እንጂ፣ ለአገር የሚበጅ ሰላም በፍጹም አያስገኝም። ለምንድነው ሥልጣን ላይ ያለው መንግስትም ሆነ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉት የኢትዮጵያ ፓለቲካ ልህቃን ባለፉት ሃምሳ አመታት በተደጋጋሚ ከሰሩት ስህተት የማይማሩት? 

ጠሚ አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን እንደመጣ ህወሓቶችን ከማግለልና እንደ ዕድፍ በሚቀፍ ስም ከሚጠራቸው መሄድ የሚችለውን ርቀት ያክል ሄዶ ወደ መሃል እንዲያመጣቸውና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የድርሻቸውን ያክል ተሳታፊ እንዲሆኑ በተደጋጋሚ ምክር ቀርቦለታል። ለዚህ አገራቸውን የሚወዱና ለአገራቸው የሚጨነቁ ሰዎች ለሰጡት ምክር የአቢይ አህመድ ምላሽ “ተዋቸው የትም አይደርሱም” የሚል እንኳን ከአገር መሪ ከአንድ ተራ ሰውም የማይጠበቅ ምላሽ ነበር። ይህ አርቆ አስተዋይነት የጎደለው ምላሽ ኢትዮጵያን ምን ያክል ዋጋ እንዳስከፈለ ወደ ኋላ ሄዶ የሰሜኑ ጦርነት በሰው ህይወት፣በመሰረተ ልማት፣በገንዘብና በማህበራዊ ትስስር ላይ ያደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት ማየቱ ይበቃል።  ጠሚ አቢይ አህመድ በኢትዮጵያ ላይ ያደረሰው ከፍተኛ ጉዳት የሰሜኑ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ከተቋጨ በኋላ ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ ትንሽም ቢሆን ይካሳል የሚል ዕምነት ነበር፣የሆነው ግን በተቃራኒው ነው። እንደ አውሎ ነፋስ ከጥፋት ወደ ጥፋት የሚበረው አቢይ አህመድ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለአገር ጥቅም ከመጠቀም ይልቅ የራሱን የግል ፋላጎትና የሥልጣን ጥማት ለማርካት በመጠቀሙ ዛሬ የፕሬቶሪያው ስምምነት ፈርሶ ህወሓትና የፌዴራል መንግስት ሌላ ዙር ጦርነት ውስጥ ገብተዋል። 

ብልፅግና ፓርቲና ተከፋይ ዲጂታል ሜዲያው ከሰሞኑ የፌዴራል ኃይሎች ወደ መቀሌ እየሄዱ ነው በሚል ሠርግና ምላሹን ተያይዘውታል። የኢትዮጵያን ፖለቲካ በሚገባ ለሚረዳ ለማንም ሰው ግልፅ መሆን ያለበት አንድ ትልቅ እውነት አለ፣ እሱም የፌዴራል ኃይሎች ባለፈው ጦርነትም መቀሌን ተቆጣጥረው ህወሓትን እንደ ዱቄት አመስነው ሲሉን ነበር፣ሆኖም ይህን ካሉ ሶስት ወር ሳይሞላ ነው የትግራይ ኃይሎች ደብረሲና የደረሱት። አሁንስ የፌዴራል ኃይሎች መቄሌን ቢቆጣጠሩ ህወሓትን ወሳኝ በሆነ መልኩ አሸንፈው የትግራይ ህዝብ ለአመታት የናፈቀውን ሰላም ለማምጣታቸው ምን ዋስትና አለ? ደሞስ የአቢይ አህመድ መንግስት ትግራይ፣አማራና ኦሮሚያ ክልል የሚያካሄደውን ጦርነት በአሸናፊነት የመወጣት ችሎታው አለው? ማነው በፌዴራል መከላከያ ውስጥ ተሰልፎ በእነዚህ ሶስት ክልሎች ውስጥ ካሉት አማጺያን ጋር የሚዋጋው? ትግራይ፣አማራና ኦሮሚያ ከ60% በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖርባችው ክልሎች ናቸው፣በቆዳ ስፋትም ከግማሽ በላይ የሆነውን የኢትዮጵያ ክፍል ይሸፍናሉ።ታድያ በእነዚህ ክልሎች ውስጥ በጦርነቱ የተነሳ ምርት ካልተመረተና ግብር ካልተከፈለ የፌዴራሉ መንግስት ገንዘብ ከየት አምጥቶ ነው ሌሎች መስራት ያለበትን ስራ ሁሉ ሰርቶ የጦርነቱን ወጪ የሚሸፍነው? 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

“ትብብር ለህልውና’ ከመፈጠሩ በፊት አንከር ሜዲያ ላይ ቀርቤ የትብብሩን መምጣት በተመለከተ ያለኝን አመለካከት ምንም ሳልደብቅ ተናግርያለሁ። አንከር ሜዲያ ላይ ከመቅርቤ በፊት በማህበራዊ ሜዲያ ላይ ለህዝብ ያጋራሁት ጽሁፍ ቃል ለቃል ይህ ነበር –

“በቅርቡ የአፋብን ሊ/መ አርበኛ ዘመነ ካሴ Le Temps ከተባለ የሲዊዘርላንድ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ አፋብን የትግራይ ኃይሎችን ጨምሮ ከተለያዩ የታጠቁ ኃይሎች ጋር ትብብር ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑንና ትብብሩ በቅርብ ግዜ ውስጥ ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን ተናግሯል። እንደ አርበኛ ዘመነ ካሴ አባባል የትብብሩ ዋና አላማ የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት ማስወገድ ነው። ገዳይና አገር አጥፊ የሆነው የጠሚ አቢይ መንግስት መወገድ አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ እኔን ጨምሮ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚስማማ ይመስለኛል። የኔ ትልቁ ጥያቄ በቀድሞዋ፣በአሁኗና በወደፊቷ ኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ምንም ስምምነት የሌላቸውና የሚጋሩት አገራዊ አጀንዳ የሌላቸው ድርጅቶች ህብረት የአቢይ አህመድን መንግስት ካስወገደ በኋላ ኢትዮጵያ ምንድነው የምትሆነው? የታጠቁ ኃይሎች ትብብር ለመፍጠር እየተወያየን ነው ሲሉ፣ውይይቱ የአቢይን መንግስት ከማስወገድ ባሻገር፣ከአቢይ አህመድ መንግስት በኋላ መምጣት ያለበትን የሽግግር ሂደትና መፈጠር ያለበትን የሽግግር መንግስት ያጠቃልላል?

ህወሓት ሃምሳ አንድ አመት ያስቆጠረ፣ለሃያ ሰባት አመት የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግስት የተቆጣጠረና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የታጠቀ ሠራዊት ያለው ድርጀት ነው።ኦነግ-ሸኔ ሃምሳ ሦስት አመት ያስቆጠረና የብዙ አመታታ የፖለቲካ ልምድ ያለው ድርጀት ነው። አፋብን ግን ገና የሦስት አመት ጎረምሳ ነው። ህወሓትና ኦነግ-ሸኔ ሲመሰረቱ ጀምሮ አማራን እንደ ዋና ጠላት አድርገው ሲመለከቱ የነበሩና አማራው ኢትዮጵያ ውስጥ በሌሎች ማህበረሰቦች እንዲጠላ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ድርጅቶች ናቸው። ዛሬ ላይ ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር ለሚፈጠረው ጥምረት ወደኋላ ሄደን ቂም መያዝ አለብን ብዬ ባላስብም፣ይህ የጠላትነት አመለካከትና እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ከአማራ ጋር ያላቸው የግዛት ይገባኛል ጥያቄ ትብብሩ ከመፈጠሩ በፊት ሁሉንም ወገኖች የሚያስማማና አሰተማማኝ ዋስትና ያለው መልስ ማግኘት አለበት። ይህ ከመሆኑ በፊት የአቢይ አህመድን መንግስት ለማስወገድ ብቻ የሚደረግ ሩጫ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊብስ ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላትና የምስራቅ አፍሪካ ትልቋ አገር ኢትዮጵያ በምንም ተዓምር መንግስት አልባ (Stateless) የምትሆንበት ሁኔታ መፈጠር የለበትም። እውነቱን ለመናገር ለኔ መንግስት አልባ አገር ከምንሆን አቢይ አህመድ ቢቀጥል ይሻላል”

በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቀው ሃሳቤ አሁንም አልተለወጠም። አንከር ሚዲያ ለቃለመጠይቅ የጋበዘኝ ይህንን ጽሁፍ ከተመለከተ በኋላ ነበር። አንከር ሜዲያ ላይም ቀርቤ ይህንኑ ሃሳቤን ነው ያንጸባረኩት እንጂ፣ትብብሩን እደግፋለሁም እቃወማለሁም አላልኩም። እነ በግልፅ የተናገርኩት ትብብሩ የአቢይ አሀመድን መንግስት ከማስወገድ ባሻገር ዘላቂ የሆነ አላማ ካለው ይንገረንና እሱን ከሰማሁ በኋላ ልደግፈው ወይም ልቃወመው እንደምችል ነው። በቃለመጠይቁ ላይ ትብብሩን ልደግፍ የሚችልባቸውን ሶስት ቅድመሁኔታዎች አስቀምጬ ነበር፣ እነሱም ትብብሩ የሲቪክና የፖለቲካ ባለድርሻዎችን መጋበዝ እንዳለበት፣የአቢይን መንግስት ካስወገደ በኋላ ሁሉን አቀፍ የሽግግር ሂደት ማስጀመር እንዳለበትና ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉን አቀፍ አገራዊ ምክክር ጉባኤ ለመኖሩ ቃል እንዲገባ ነበር። ይህንን ከተናገርኩ ከሁለት ሳምንት በኋላ ትብብሩ ሲፈጠር ባስቀመጣቸውና ከዚያም ቀጥሎ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ውስጥ ከላይ የጠቀስኳቸውን ሶስት ነገሮችና በተደጋጋሚ የጮሁኩለትንና አሁንም የምጮህለትን የሽግግር ፍትህ ሂደት በግልጽ በማስቀመጡ ለትብብሩ ድጋፌን ሰጠሁ። አንዳንድ ታዋቂ ፖለቲከኞችን ጨምሮ አንብበው የማይረዱ ወይም የሰሙትን ገልብጠው የሚረዱ ሰዎች፣ትብብሩን አልደግፍም ያለው ኤፍሬም ወር በማይሞላ ግዜ ውስጥ ትብብሩ ሲፈጠር፣ሃሳቡን ለውጦ ትብብሩን ደገፈ ሲሉ ተደምጠዋል። እኔ አንከር ሜዲያ ላይ ቀርቤ ቃለመጠይቅ ከሰጠሁ በኋላ ትብብሩ ሲፈጠር የለወጥኩት ምንም ሃሳብ ስለሌለ ይህ አባባል ፍጹም ከእውነት የራቀ አባባል ነው። አንከር ሜዲያ ላይ የሰጠሁትን ቃለመጥይቅም ይኸውላችሁ እንደገና በጥሞና ስሙና ፍርዱን ለእናንተ እተዋለሁ። 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ትብብሩን ከፈጠሩ ኃይሎች ውስጥ አንዳንዶቹ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በተለያየ ጫፍ ላይ የቆሙ፣ የተለያየ ርዕዮተ አለም የሚያራምዱና የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት ለሚለው ጥያቄ የሚሰጡት መልስ በጣም የሚቃረን ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፣ዛሬ በእያንዳንዳቸው ላይና እንወክለዋለን በሚሉት ህዝብ ላይ የብልፅግና አገዛዝ እያደረሰ ያለው የህልውና አደጋ ግን ተመሳሳይ ነው፣ብልፅግና መራሹ የአቢይ አህመድ መንግስት ትግራይም፣ኦሮሚያም አማራም ውስጥ ጦርነት ከፍቶ እየተዋጋ ነው። ታዲያ እነዚህ ሶስት ኃይሎች በተለያየ የኢትዮጵያ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ ሌሎች ኃይሎች ጋር ሆነው አንድ ላይ ከምንጠፋ አጥፊያችንን በጋራ መክተን የኢትዮጵያ ህዝብ በወደፊት ጉዳዩ ላይ የራሱን ውሳኔ ይወስን ብለው ትብብር ቢፈጥሩ ጥፋቱ ምኑ ላይ ነው? እነዚህ ኃይሎች ትብብር ፈጠሩም አልፈጠሩ ጦርነት መካሄዱ አልቀረም፣የጎንዮሽ እየተላተሙ የነሱን መጥፋትና የህዝባቸውን ውድቀት ከሚያፋጥኑ ትብብር ፈጥረው ይህ አውዳሚ ጦርነት ዕልባት እንዲያገኝ ቢያደርጉ ምንድነው ችግሩ? ደሞስ ለኢትዮጵያ የሚበጀው እነዚህ ኃይሎች ትብብር ፈጥረው ኢትዮጵያን ወደ ሽግግር ሂደት ቢወስዱ ነው ወይስ ምንም የሚያገናኘን ነገር የለም ብለው እራስ በርስም ከብልፅግና ጋርም መዋጋት ነው? ትብብሩን በፍጹም አንደግፍም የሚሉ ሰዎች ወደ ኋላ መለስ ብለው እነዚህን ጥያቄዎች ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር እያገናዘቡ ቢመልሱ መልካም ይመስለኛል። የትብብሩ ዋና ግብ የጠሚ አቢይን መንግስት ማስወገድ ቢሆንና፣ከአቢይ አህመድ በኋላ የምትኖረውን ኢትዮጵያ በተመለከተ ያለውን አላማና ግብ ባይነግረን ወይም ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ምንም ደንታ ባይኖረው ኖሮ፣እኔ ኤፍሬም ትብብሩን መቃወም ብቻ ሳይሆን መኖር የማይገባው ትብብር ነው ብዬ ለትብብሩ መጥፋት ቀንና ማታ ማድረግ የምችለውን ሁሉ አደርግ ነበር። 

“ትብብር ለህልውና” ሲመሰረትና ከተመሰረተ በኋላ በሰጠው የመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በጣም ጠቃሚና የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት ሃምሳ አመታት አራት ኪሎን የተቆጣጠሩ መንግስታትን ሁሉ የጠየቃቸውን የሽግግር ሂደት፣አገራዊ ጉባኤና የሽግግር ፍትህን የመሳሰሉ ሶስት መሰረታዊ ጥያቄዎች የነሱም አላማና ግብ እንደሆነ በማያሻማ ቋንቋ አስቀምጧል። ይህንን እናደርጋለን ብለው ለኢትዮጵያ ህዝብ የገቡትን ተስፋ ያደርጋሉ አያደርጉም እራሱን የቻለ ትልቅ ጥያቄ ነው፣ግን የኛ ስራ መሆን ያለበት እነዚህ ትብብሩ ያስቀመጣቸው ሶስት ትልልቅ ግቦች እውን እንዲሆኑ የየራሳችንን ድርሻ መወጣትና በትብብሩ ላይ ግፊት ማድረግ ነው እንጂ፣ትብብሩ ውስጥ ያሉት ኃይሎች እሳትና ጭድ ናቸው እያልን ገና ከጅምሩ ትብብሩን መቃወም አይደለም። በሚገባ ካሰብንበትና መስራት የሚገባንን ከልባቸን ከሰራን እሳቱን ማጥፋት ጭዱንም ለምንፈልገው ጠቃሚ ጉዳይ ማዋል እንችላለን። ጠቅለል ባለ መልኩ ትብብሩ የሰላምና ድርድር በር ከከፈተ፣የሲቪክና ፓለቲካ ባለድርሻዎች ጋር በእኩልነት አንድ ላይ ለመስራት ቃል ከገባ፣  ከጦርነት በኋላ አካታች የሽግግር መንግሥት ለመመስረት ሙሉ ፈቃደኛ ከሆነና አገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትህ ሂደቶችን ለማስጀመር ቃል የሚገባ ከሆነ አገር ውስጥም በውጭ አገሮችም የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የትብብሩ ጥረት እንዲሳካ የየራሱን ጥረት ማድረግ ይኖርበታል ባይ ነኝ። እንደዚህ ሲባል ግን ሙሉ ልባችንን ትብብሩ ላይ ጥለን የሚሰራውን ስራ ሁሉ እንደግፋለን ማለት አይደለም። ትብብሩ ለኢትዮጵያ ህዝብ አደርጋለሁ ብሎ ቃል የገባውን ስራ ትቶ ሌላ ነገር ውስጥ ከገባ፣ከህዝብ ጋር ቆመን ይህንን አንቀበልም ብለን በትብብሩ ላይ ጫና መፍጠር አለብን። ባጠቃላይ የኛ ትልቁ ኃይል ህዝብ ነውና ምን ግዜም ከህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ጋር መቆም አለብን።

እኛ ኢትዮጵያዊያን የሚያዋጣን ሌላ ዙር ጦርነት ሳይሆን ከጦርነት ወደ ፖለቲካዊ ውይይት፣ ከጥላቻ ወደ መተማመን፣ ከግለሰብና የድርጅት ፍላጎት ወደ ጋራ አገራዊ ጥቅም መሸጋገር ነው። በቅርቡ የተፈጠረው ትብብር ለህልውናም ቢሆን ጦርነት የመጨረሻ  እንጂ የመጀመሪያ አማራጩ ሊሆን አይገባም። በሚገባ ታስቦበት ከተሰራ ትብብሩ ኢትዮጵያን ወደ ሰላምና መረጋጋት ለመውሰድ አይኑና ልቡ በጦርነት ከተጋረደው ከጠሚ አቢይ አህመድ የተሻለ ዕድል አለው ብዬ አምናለሁ። ይህንን ታሪክ ያደለውን ዕድል ተግባራዊ ለማድረግ ግን የመጀመሪያ አማራጩ የሰላም መንገድ መሆን አለበት። ለምሳሌ፣ትብብሩ በሂደት ለመንግስት ተከታታይ የሠላም ጥሪ ማድረግ አለበት። በውጭ አገሮች በተለይ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መንግስት የቀረበለትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበል አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያደርግበት የማያቋርጥ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት አለባቸው። አገር ቤት የሚገኙ የሲቪክና የፖለቲካ ድርጅቶችም መንግስት የሠላም ጥሪውን እንዲቀበልና ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር በእኩልነት እንዲደራደር የማያሰልስ ህዝባዊ ግፊት ማድረግ አለባቸው። እኔ እርግጠኛ ነኝ መንግስት በጦር ሜዳው፣በህዝባዊ እምቢተኝነትና በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሚደርስበት ጫና እያየለ በሄደ ቁጥር ሳይወድ በግዱ የቀረበለትን የሠላምና የድርድር ጥሪ ይቀበላል። እንደ ውኃ የሚያጥለቀልቅ ኃይል አለን እያለ ድርድርን አልቀበልም ብሎ የተኮፈሰው ደርግ በመጨረሻ ለንደን ላይ ለድርድር የቀረበው ህወሓትና ሻዕቢያ ያስቀመጡትን የድርድር ቅድመ-ሁኔታዎች ተቀብሎ ነው።

የፖለቲካ ስምምነት ላይ መድረስ ዘመን ያስቆጠሩ የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት ሁነኛው መንገድ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፣ሆኖም የፖለቲካ ተዋንያኑ መሃሉን ትተው በተቃራኒ ጫፍ ላይ በቆሙባት ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ስምምነት ላይ መድረስ ቀላል አይደለም። በተለይ በፖለቲካ ተዋንያኑ መካከል  የረጅም ጊዜ አለመተማመንና የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ቡድኖች መካከል ያለውን ቁስልና የታሪክ ጠባሳ ፈውሶ ወደ ስምምነት ለመምጣት ረዘም ያለ ግዜ፣ ትዕግስት፣አስተዋይነትና መደማመጥን ይጠይቃል።

- Advertisement -

የኢትዮጵያን ፖለቲካ በተከታተልኩባቸው ረጅም ዓመታት ውስጥ በግልጽ የተረዳሁት አንድ ትልቅ እውነት አለ፤ እሱም ወታደራዊ ድል ጊዜያዊ መረጋጋትን ሊያመጣ ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ተፋላሚዎች ተደራድረው ፖለቲካዊ ስምምነት ላይ እስካልደረሱ ድረስ፣ በጦርነት የተገኘ ድል አዲስ የቂምና የበቀል ዑደት ከመፍጠር ባለፈ የህዝብን ፍርሃትና የፖለቲካ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ሊፈታ እንደማይችል ነው። ዛሬ ላይ ወደድንም ጠላን “ጦርነቱን ማን ያሸንፋል”?» ከሚል ጥያቄ ይልቅ “ኢትዮጵያን ከዚህ የውድቀት ዑደት እንዴት እናወጣታለን’?» የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ እራሳችንን መጠየቅ የሚገባን ግዜ ላይ የደረስን ይመስለኛል። 

በአለማችን በብዙ አገሮች ውስጥ ጦርነቶችና ግጭቶች ነበሩ፣በብዙዎቹ አገሮች ውስጥ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት የተፈጠረው አንዱ ሌላውን በጦርነት ባሸነፈባቸው አገሮች ውስጥ ሳይሆን፣ጦርነቶችና ግጭቶች በፓለቲካዊ ስምምነት በተቋጩባቸው አገሮች ውስጥ ነው። እኛም አገር ውስጥ ቢሆን፣የሰሜኑ ጦርነት ያንን ያክል ጉዳት ካደረሰ በኋላ ለግዜውም ቢሆን የተቋጨው በፕሪቶሪያው ስምምነት ነው። የተለያዩ አገሮች ታሪክ እንደሚያስተምረን የኃይል እርምጃዎች ጊዜያዊ መረጋጋትን ሊያመጡ ይችሉ ይሆናል፣ የቆሰሉ ልቦችንና የተበላሹ ማህበራዊ ትስስሮችን መጠገን የሚቻለው ግን አሳታፊ በሆነ የሰላም ሂደት ብቻ ነው። የብዙ ኢትዮጵያዊያንን ህይወት ከቀጠፈው ከአሰቃቂው የሰሜኑ ጦርነትና ከፕሪቶሪያው ስምምነት መማር የሚገባን ትልቁ ትምህርት ቢኖር፣ የፖለቲካ  ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድና በንግግር ለመፍታት ቁርጠኝነቱ ሊኖረን እንደሚገባን እንጂ፣ የሚቃወሙንን ነገር ግን የራሳችንን አገር ዜጎች በማጥፋት ዘላቂ ድል ማግኘት እንደማንችል ነው።

“ጦርነትን ማሸነፍ” እና “ግጭትን መፍታት” በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ወታደራዊ ድል ግዜያዊ አላማን ሊያሳካ ይችል ይሆናል፤ ግን በተፋላሚዎቹ መካከል የፖለቲካ ስምምነት እስካልተደረሰ ድረስ፣በጦርነት የተገኘ ድል በራሱ ጦርነቱን ያመጡትን የፖለቲካ፣ የሥልጣን፣ የመብትና የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች መመለስ አይችልም። የተለያዩ የአለም ባንክ ጥናቶች እንደሚያሳዩን ግጭትና ጦርነትን በዘላቂነት ለማቆምና አስተማማኝ ሠላም ለማምጣት፣አሳታፊ የፖለቲካ ተቋማት፣ ሥልጣን መጋራት፣ የግ ህየበላይነትና ተዓማኒ የፖለቲካ ሂደት ወሳኝ ናቸው። እነዚህ ወሳኝ እሴቶች ደሞ የፖለቲካ ስምምነት ውጤቶች ናቸው። ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያዊያን ማድረግ ያለብን “እኔ አሸንፌያለሁ፣ አንተ ተሸንፈሃል” ብለን ታሪክን ለመዝጋት መሞከር ሳይሆን፣ሁላችንንም አሸናፊ የሚያደርገንን መንገድ መከተል ነው። ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የምትፈልገው ሌላ ዙር ጦርነት ሳይሆን ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት ነው፣ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት ደሞ የፖለቲካ ስምምነት ውጤት ነው።

ዛሬ ላይ ትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያ ውስጥ የቀጠሉ ግጭቶች ኢትዮጵያን እጅግ በጣም አስከፊ ወደሆነ የጥፋት አዘቅት ውስጥ እየገፏት ነው። የጦርነት ጉዞ ለኢትዮጵያ የሚበጅ መፍትሄ ይዞ እንደማይመጣ ካለፉት ሃምሳ አመት ታሪካችን ልንማር ይገባል። በመሆኑም መፍትሄው ሌላ ዙር ጦርነት ውስጥ መዘፈቅ ሳይሆን፤ የታጠቁ ኃይሎችን፣ የፖለቲካ ድርጅቶችንና የሲቪል ባለድርሻዎችን ያሳተፈ ሁሉን አቀፍ አገራዊ የፖለቲካ ስምምነት መፍጠር ነው። የ“ትብብር ለህልውና” መፈጠርም በዚህ አይነቱ የመፍትሄ አውድ ውስጥ ነው መታየት ያለበት። ትብብር ለህልውናን በተመለከተ ዋናው ጥያቄ የጠሚ አቢይ አህመድን መንግሥት ማስወገድ መቻሉ ብቻ ሳይሆን የአቢይ አህመደ መንግስት ከተወገደ በኋላ ኢትዮጵያን ወዴት ይወስዳታል የሚለው ጥያቄ ነው። ስለዚህ ማንኛውም የፖለቲካ ወይም የታጣቂ ኃይሎች ትብብር የአገሪቱን የወደፊት የፖለቲካ ሥርዓት፣ የሽግግር ሂደትና የህዝብ ውሳኔ በግልጽ የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ ሊኖረው ይገባል። ይህ ማለት ደሞ የትብብሩ ዋና መለኪያ የወታደራዊ አቅሙ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን ከጦርነት ወደ ሰላም፣ ከግጭት ወደ ፖለቲካዊ ውይይትና ከመከፋፈል ወደ አገራዊ ስምምነት ማሸጋገር መቻሉ ላይ  መሆን አለበት። “ትብብር ለህልውና” ጦርነትን እንደ መጀመሪያ አማራጭ መውሰድ ያለበት አይመስለኝም።

የዚህ ጽሑፉ ዋና አላማ ማን ጦርነቱን ያሸንፋል የሚለው ጥያቄ ላይ ከማተኮር፣ አብዛኛውን ግዜያችንን ማጥፋት ያለብን እንዴት ነው የፖለቲካ ልዪነቶቻችንን ከጦርነት ውጭ ማስወገድ የምንችለው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ መሆን አለበት የሚል ነው።ይህ ጥረት የታጠቁ ኃይሎችን፣ የፖለቲካ ድርጅቶችንና የሲቪል ባለድርሻዎችን ያሳተፈ አገራዊ የፖለቲካ ስምምነት፣ ሁሉን አቀፍ የሽግግር ሂደት፣ አገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትhን የሚያካትት መሆን አለበት። “ትብብር ለህልውና” እነዚህን እሱ እራሱ እንደ አላማና ግብ ያስቀመጣቸውን እሴቶች በተግባር ማሳየት ከጀመረና ጦርነትን እንደ መጀመሪያ አማራጭ ሳይሆን እንደ መጨረሻ አማራጭ ከተመለከተ፣የአገራችን ኢትዮጵያ ትንሳኤ ሩቅ አይደለም።

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News