Homeነፃ አስተያየትበፈተና ላይ የወደቀው የፕሮፌሸናሊዝም ምሰሶ፦ የመከላከያ ሰራዊት ተቋማዊ ቀውስ፣ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት...

በፈተና ላይ የወደቀው የፕሮፌሸናሊዝም ምሰሶ፦ የመከላከያ ሰራዊት ተቋማዊ ቀውስ፣ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እና የስትራቴጂካዊ ውድቀት ዋጋ

Advertisement
World Wide Travel Group
መከላከያ ሰራዊት
ፋይል

በአበራ ገረመው
(መስከረም 2019 ዓ.ም)  

መግቢያ

የማንኛውም ሀገር የመከላከያ ሰራዊት ፕሮፌሸናሊዝም (የሙያ ብቃት) የሚለካው በግዢ በሚፈጸሙ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ወይም በካምፕ ግንባታዎች ብቻ አይደለም። ይልቁንም ሀገራዊ ስጋቶችን በብቃት የመገምገም፣ የተቀናጀ ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ እቅድ የማውጣት፣ ሰራዊቱን በሁለገብ ስነ-ልቦና፣ አካዳሚ፣ ስነ-ምግባር እና የታሪክ ቅርስ የታነጸ የማድረግ እንዲሁም የፖለቲካዊ ገለልተኝነትን የመጠበቅ አቅሙ ነው።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚታየው ተደራራቢ የትጥቅ ግጭት፣ የጸጥታ መበላሸት እና ተቋማዊ አለመረጋጋት የመከላከያ ሰራዊቱን የወታደራዊ ፕሮፌሸናሊዝም ደረጃ እና የስትራቴጂ አፈጻጸም ጥልቅ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ሆኗል።

1. የሃርድዌር እና የሶፍትዌር ግንባታ መዛባት፦ የተረሱት ተቋማዊ መሰረቶች

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

በቅርብ ዓመታት በሰራዊቱ ውስጥ ለድሮን ቴክኖሎጂ ግዢ፣ ለወታደራዊ ካምፖች ግንባታ እና ለአየር ኃይል ማጠናከር ከፍተኛ ትኩረትና በጀት ተመድቧል። ነገር ግን ወታደራዊ ፕሮፌሸናሊዝም የመሳሪያ ስብስብ ብቻ አይደለም። ከነዚህ የሃርድዌር ስራዎች ባሻገር የሰራዊቱን ወታደራዊ ስነ-ምግባር፣ ባህልና ማህበራዊ መሰረት የሚገነቡ “የሶፍትዌር“ ስራዎች ሙሉ በሙሉ ችላ ተብለዋል፦

  • የወታደራዊ መሬት ይዞታዎች መወረርና የአካባቢ ጥበቃ ክፍተት፦ የሰራዊቱ የነበሩ ወታደራዊ መሬቶችና ይዞታዎች በህገ-ወጥ መንገድ እየተወረሩና እየጠበቡ መጥተዋል። በተጨማሪም ካምፖችንና የወታደራዊ ይዞታዎችን አረንጓዴ የማልማት፣ ደን የማልማትና ውብ የማድረግ ስራዎች እጅግ በመዳከማቸው፣ ሰራዊቱ ከአካባቢ ጥበቃና ከተቋማዊ ስነ-ስርዓት አንጻር የነበረውን አርአያነት ቀናንሶታል።
  • የወታደራዊ ባል (ክበባት) እና የባህል ማዕከላት መቅረት፦ ቀደም ሲል የሰራዊቱን ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ አንድነት የሚገነቡ የወታደራዊ ባል (የመኮንኖችና የሰራዊት ክበቦች) እና የባህል ተቋማት አገልግሎት የማይሰጡበት ወይም ለመገንባት የተደረገ ጥረት አነስተኛ የሆነበት ሁኔታ ይስተዋላል።
  • የስፖርታዊ ውድድሮች መቋረጥ፦ የሰራዊቱን አካላዊ ብቃት፣ የቡድን መንፈስና ወታደራዊ አንድነት የሚያጠናክሩ ውስጣዊና ሀገራዊ የስፖርት ውድድሮች በመቅረታቸው የሰራዊቱ ማህበራዊ ትስስር ተዳክሟል።
  • የወታደራዊ ቅርሶች መውደም እና የሙዚየም አለመኖር፦ በሀገሪቱ ረጅም ወታደራዊ ታሪክ ውስጥ የተፈሩ በርካታ ወታደራዊ ቅርሶች እየወደሙና እየተበተኑ ይገኛሉ። እነዚህን ሰብስቦ ለትውልድ የሚያስተላልፍና የወታደራዊ ታሪክና ጥናት ማዕከል የሚሆን ዘመናዊ ወታደራዊ ሙዚየም አለመገንባቱ ተቋማዊ ማስታወሻ ማጣትን አስከትሏል።
  • የዶክትሪን እና የአካዳሚክ ስልጠና መዳከም፦ ሰራዊቱ በምን ዓይነት ግልጽ የወታደራዊ ዶክትሪን እንደሚመራና እንደሚሰለጥን ግልጽ አይደለም። ሰራዊቱን በአካዳሚክ እስከ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ የማብቃትና የስትራቴጂካዊ ትንተና አቅሙን የማሳደግ ስራዎች በመዳከማቸው፣ በተለይም በሀገር ውስጥ ግጭቶች ወቅት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲከሰቱና የህዝብ አመኔታ እንዲሸረሸር ምክንያት ሆኗል።

2. የጥቅም ትስስር እና የአመራሩ የሙያዊ ምክር እጥረት

በወታደራዊ ፕሮፌሸናሊዝም መርሆዎች መሠረት፣ የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራር ለሙያዊ ጥራት፣ ለግዳጅ ስኬትና ለሰራዊቱ ደህንነት ታማኝ በመሆን ለፖለቲካው አመራር ግልጽና ወታደራዊ ሳይንስን መሠረት ያደረገ ሙያዊ ምክር ማቅረብ ይኖርበታል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት፦

  • የጥቅም ትስስር እና የቁሳቁስ ማታለያ፦ ለከፍተኛ ጀኔራሎች በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ከተሞች እስከ 1,000 ካሬ ሜትር የሚደርስ መሬት እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች መሰጠታቸው በፖለቲካው አመራር እና በሰራዊቱ ከፍተኛ አመራር መካከል የጥቅም ትስስር እንዲፈጠር አድርጓል።
  • ዳተኝነት እና የሙያዊ ምክር እጥረት፦ ይህ የጥቅም ትስስር ሰራዊቱ በግዳጅ አፈጻጸም በሚያሳያቸው መዳከሞች እና ከ3 ወር እስከ 3 ዓመታት በተራዘሙ ያልተሳኩ እቅዶች ላይ አመራሩ በፖለቲካው አካል ላይ ጠንካራ ትችት እንዳይሰነዝር አድርጎታል። ለኢታማዞር ሹሙም ሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ግዳጆች ለምን ውጤታማ እንዳልሆኑ ጥናታዊ እና ገለልተኛ ምክር የመስጠት አቅምና ፍላጎት እንዲዳከም አድርጎታል።

3. የሕግ አውጪው ተዋስኦ፣ የመከላከያ ሚኒስቴር እና የፓርቲ የመሆን አደጋ

- Advertisement -
Advertise here _ borkena
  • ተደጋጋሚ የሕግ ማሻሻያ፦ ከ2010 ዓ.ም የለውጥ ማግስት ጀምሮ የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ለአምስተኛ ጊዜ እንዲሻሻል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡ (በየአንድ ዓመት ተኩል ገደማ አዋጁ የሚቀየርበት ሁኔታ) ተቋማዊ ጥናትና ረጅም ጊዜን ያቀደ ስትራቴጂ አለመኖሩን የሚያሳይ ነው። ይልቁንም የፖለቲካ አመራሩ የራሱን ወቅታዊ የፖለቲካ ፍላጎቶችና ውሳኔዎች በሰራዊቱ ላይ ለመጫን የሚያደርገው ህጋዊ ሽፋን የመስጠት ሙከራ እንደሆነ ይተቸዋል።
  • የሚኒስትሮች ተደጋጋሚ መለዋወጥ፦ ከለውጡ ወዲህ አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ አቶ ለማ መገርሳ፣ አይሻ መሐመድ፣ ዶክተር ቀነአ ያደታ፣ ዶክተር አብርሃም በላይ እና እንደገና አይሻ መሐመድ እያለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስድስት ጊዜ የመከላከያ ሚኒስትሮች መለዋወጣቸው በሲቪል-ወታደራዊ ግንኙነት ላይ ትልቅ ጥያቄ ያነሳል፤ ዘላቂ የፖሊሲ ቀጣይነትንም ያጠፋል።
  • የቅጽል ስም (Stigma) ዝንባሌ እና ገለልተኝነት ማጣት፦ ሰራዊቱ የሀገርና የህዝብ መከላከያ ከመሆን ይልቅ በየስርዓቱ ለሚመጡ የፖለቲካ ኃይሎች መጠቀሚያ ተደርጎ በመወሰዱ በደርግ ዘመን “የደርግ ሰራዊት”፣ በኢህአዴግ ዘመን “የወያኔ ሰራዊት”፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ “የብልጽግና ወይም የኦህዴድ ሰራዊት” የሚል ቅጽል ስም ይሰጠዋል። ይህ አካሄድ ሰራዊቱ ህገ-መንግስታዊ ተቋማዊ ገለልተኝነት እንደሌለው እና የፕሮፌሸናሊዝም ክፍተት እንዳለበት የሚያሳይ ግልጽ ማሳያ ነው።

4. የፕሮፌሸናሊዝም እጥረት ያስከተላቸው አደገኛ ውጤቶች

እነዚህ ተደራራቢ የወታደራዊ ስትራቴጂ፣ ተቋማዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በሀገሪቱና በሰራዊቱ ላይ አደገኛ ውጤቶችን አስከትለዋል፦

  • የአውደ ውጊያ ድክመት እና የሰው ኃይል መበታተን፦ በስትራቴጂና የታክቲክ ብቃት ማነስ ምክንያት በሰራዊቱ ውስጥ በገፍ የመክዳት፣ በገፍ ለታጣቂዎች እጅ የመስጠት እና ያለአግባብ አላስፈላጊና ግብረ-ገባዊ ያልሆነ መስዋዕትነት የመክፈል ሁኔታዎች ጎልተው ይታያሉ።
  • በህዝቡ ላይ የሚደርስ ሰብአዊና ማህበራዊ እንግልት፦ በትጥቅ ግጭት ቀጠናዎች ውስጥ ባለው ህዝብ ላይ በታጣቂዎችም ሆነ በመንግስት ኃይሎች የሚደርሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ እንግልቶች እና የማህበራዊ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎል የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ ጥለዋል።
  • የግብር ከፋዩ ህዝብ አላስፈላጊ ኪሳራ፦ ህዝቡ የሚከፍለው ግብር ለመከላከያ የሚመደበው ሰላምና ደህንነት እንዲሰፍን ቢሆንም፣ የጸጥታው ሁኔታ በፍጹም ሊረጋጋና የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከእስራት ማስፈታት አልተቻለም።
  • የህዝብ አመኔታ ማጣት፦ ወታደሩ በስትራቴጂካዊ ክፍተቶች ምክንያት የሚከፍለው ዋጋና የጸጥታው አለመረጋጋት ህዝቡ በሰራዊቱ ችሎታ፣ ብቃትና ገለልተኝነት ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር አድርጎታል።

5. ለተፈጠሩት ክፍተቶች ተጠያቂ አካላት (Accountability Analysis)

ለእነዚህ ተደራራቢ ችግሮችና ተቋማዊ ውድቀቶች ቀጥተኛና ተዋረዳዊ ተጠያቂነት የሚወስዱት አካላት የሚከተሉት ናቸው፦

- Advertisement -
  1. የፖለቲካ አመራሩ (የሀገሪቱ የፖለቲካ መሪዎችና የሚኒስትሮች ምክር ቤት)፦ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ጥያቄዎችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ወታደራዊ ኃይልንና አስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን እንደ ዋና መፍትሔ በመጠቀማቸው፤ ሰራዊቱን በቦታና በጥቅማጥቅም የማሸነፍ አካሄድ በመከተላቸው፤ እንዲሁም አዋጆችንና ሚኒስትሮችን በተደጋጋሚ በመቀያየር ተቋማዊ አለመረጋጋት በመፍጠራቸው።
  2. የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራር (ኢታማዞር ሹም፣ የመከላከያ ኮማንድ ፖስት እና የጦር ጀኔራሎች)፦ ለፖለቲካ አመራሩ ወታደራዊ ሳይንስን መሠረት ያደረገ ገለልተኛና ደፋር ሙያዊ ምክር ከመስጠት ይልቅ ለጥቅማጥቅም ዳተኛ በመሆናቸው፤ ያልተጠኑ አጫጭር እቅዶችን አውጥተው የሰራዊቱን ህይወት ለከንቱ መስዋዕትነት፣ ለገፍ መክዳትና እጅ መስጠት በመዳረጋቸው፤ እንዲሁም የወታደራዊ ዶክትሪን፣ የታሪክ፣ የቅርስና የይዞታ አስተዳደር ስራዎችን ችላ በማለታቸው።
  3. የፖለቲካ ፓርቲዎች (ተፎካካሪና ተቃዋሚ ቡድኖች)፦ በሀገሪቱ በሚደረጉ የፖለቲካ ውይይቶች፣ የምርጫ ቅስቀሳዎች እና የመድረክ ክርክሮች ወቅት የመከላከያ ሰራዊትን ፕሮፌሸናሊዝም፣ ገለልተኝነት፣ የበጀት አጠቃቀም እና ተቋማዊ ማሻሻያ (Defense Reform) ዋና አጀንዳ አድርገው በመከራከር እና አማራጭ ፖሊሲዎችን በማቅረብ ረገድ ትልቅ ክፍተት በመኖሩ።
  4. የመከላከያ ሚኒስቴር፦ ሰራዊቱ በህገ-መንግስታዊ ወሰን ውስጥ እንዲንቀሳቀስ የማድረግና የሲቪል ቁጥጥር ሚናውን መወጣት ባለመቻሉ፤ እንዲሁም የሚኒስትሮች ተደጋጋሚ መለዋወጥ ተቋሙ የረጅም ጊዜ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዳይኖረው በማድረጉ።
  5. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፦ በመከላከያ በጀት፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች አፈጻጸም እና ተደጋጋሚ የአዋጅ ማሻሻያዎች ላይ ጥልቅ የማጣራትና የቁጥጥር ስራ ሳይሰራ በይፋ በማጽደቁ።
  6. የታጠቁ አማጺ ኃይሎችና ተቃዋሚ ቡድኖች፦ ሰላማዊ የፖለቲካ አማራጮችን ውድቅ በማድረግ ወደ ትጥቅ ትግል በመግባታቸው፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ሰብአዊ ጥሰቶችን በመፈጸማቸው እና የመሰረተ ልማትና የኢኮኖሚ ውድመት በማስከተላቸው።
  7. የወታደራዊ የፍትህና የህግ ማስከበር ስርአት፦ በአውደ ውጊያና በህዝብ መካከል የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችንና የዲሲፕሊን ግድፈቶችን ገለልተኛ በሆነ መንገድ መርምሮ ተጠያቂ የማድረግ ክፍተት በመኖሩ።

ማጠቃለያ እና የፖሊሲ አቅጣጫዎች

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና ፕሮፌሸናል የመከላከያ ሰራዊት ለመገንባት ከቁሳቁስና መሳሪያ ስብስብ ባሻገር ጥልቅ ተቋማዊ ማሻሻያ ያስፈልጋል፦

  1. ሁለገብ ተቋማዊ ግንባታን ማጠናከር፦ የወታደራዊ መሬት ይዞታዎችን ማስከበር፣ ካምፖችን አረንጓዴና ውብ ማድረግ፣ የወታደራዊ ባል (ክበባት) ማዕከላትን መገንባት፣ የስፖርት ውድድሮችን ማነቃቃት፣ ቅርሶችን በመጠበቅ ዘመናዊ ወታደራዊ ሙዚየም መገንባት እንዲሁም ሰራዊቱን በአካዳሚክና በግልጽ ዶክትሪን ማብቃት።
  2. ተቋማዊ ገለልተኝነትና የጥቅም ትስስርን ማስወገድ፦ የሰራዊቱን አመራር በጥቅማጥቅም ማሸነፍን ማስቆም፤ ሰራዊቱ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ መጠቀሚያ ሳይሆን የሀገርና ህዝብ መከላከያ እንዲሆን ገለልተኝነቱን ማስከበር።
  3. የሕግ እና የአመራር መረጋጋት፦ የወታደራዊ አዋጆችን ለፖለቲካ ፍላጎት በየዓመቱ ከመቀያየር መቆጠብ እና የመከላከያ ሚኒስቴርን በሲቪል መሪዎች ማረጋጋት።
  4. የፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳ ማድረግ፦ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰራዊቱን ከፖለቲካ ነጻ የሚያደርጉና ፕሮፌሸናሊዝሙን የሚያረጋግጡ አማራጭ ፖሊሲዎችን በፖለቲካ መድረኮች አጀንዳ አድርገው ማቅረብ።
  5. ፖለቲካዊ መፍትሔዎችን ማስቀደም፦ ወታደራዊ ኃይልን የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ለማንበርከክ ከመጠቀም ይልቅ ለፖለቲካዊ ድርድርና ንግግር ምቹ ሁኔታ መፍጠሪያ ማድረግ።

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News