Homeነፃ አስተያየት  አምና እና ዘንድሮ(ጠገናው ጎሹ)

  አምና እና ዘንድሮ(ጠገናው ጎሹ)

Advertisement
World Wide Travel Group
አምና እና ዘንድሮ  _ ጠገናው ጎሹ

ጠገናው ጎሹ

ባለፈው  የአዲስ ዓመት ዋዜማ  “ዘንድሮና ከርሞ : የዘመናት እንቆቅልሾቻችንን ለመፍታት የምንችልባቸው የዘመን ክፍሎች ይሆኑ ይሆን?”  በሚል ርዕስ ረጅምና እልህ አስጨራሽ ከሆነ በገዛ አገራችን የአታሳዱንና የአትግደሉን ተማፅኖ በኋላም የእኩያን ገዥዎች  ምላሽ ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ በመቀጠሉ ምክንያት ተገደው የነፃነት ወይም ሞት ተጋድሎ ላይ የሚገኙ ወገኖች ትግልም ከአገራችን የትጥቅ ትግል ታሪክ አንፃር አስደናቂ በሆነ የውጊያ ብቃትና ዲሲፕሊን እየታጀበ መቀጠሉን ዋቢ በማድረግ የገለፅኩበትን ፀሁፍ አስታውሳለሁ። የያኔው ዘንድሮ  በአምና  እና የያኔው ከርሞ ደግሞ በአሁኑ ዘንድሮ ተተክቷል።  

 ይህ ዓመት (ያኔ ከርሞ ያልኩትና የአሁኑ ዘንድሮ ) ዘመን ጠገብና በእጅጉ አስከፊ የሆነው ፖለቲካ ወለድ እንቆቅልሻችን በታሪካዊነት የሚፈታበትና የድል ብሥራት የሚበሰርበት ዓመት የመሆኑ እውነታ ከመቸውም በላይ ግልፅና ግልፅ እየሆነ በመሄድ ላይ የሚገኝበት ዓመት ነው። ይህ ግዙፍና ጥልቅ እውነታ ለእኩያን ገዥዎች፣ ለወራዳ ግብረ በላዎቻቸውና ቁጥራቸው ቀላል ላልሆነ የአድርባይነት ልክፍተኞች ካልሆነ በስተቀር የነፃነት፣ የፍትህ ፣የሰላምና የጋራ ልማት  አገር ባለቤት ለመሆን ለሚመመኝና የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ለሚፈልግ የአገሬ ሰው ሁሉ ግልፅና ግልፅ ነው።

አዎ! እንኳንስ በእኛ አይነት በሥልጣነ መንበር ላይ በሚፈራረቁ እኩያን ገዥዎች  ምክንያት እጅግ ኋላ ቀርና ጋግርታም የሆነ የፖለቲካ ባህል በአንፃራዊነት በተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል በሚባል አገርም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ሊኖሩ የመቻላቸው እውነትነትን ተቀብሎ በአግባቡ የመስተናገድ አስፈላጊነት  ሳይዘነጋ ይህ ዓመት (ዘንድሮ) የታላቅ ታሪካዊ/ትውልዳዊ የሆነ የዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ሥርዓት መሠረት የሚጣልበት ዓመት በመሆኑ በእውቀት፣ በጥበብ ፣ ይበልጥ በመተማመንና በመተባበር ላይ በተመሠረተ ፖለቲካዊ አያያዝ/አመራር እና ከዚሁ በሚመነጭ የመከላከያና የደህንነት መዋቅር የሚመራ መሆን ስላለበት ከምር ሊወሰድና አስፈላጊው ክትትል ሊደረግበት ይገባል።     

በሥልጣነ መንበር ላይ እየተፈራረቁ መከረኛውን ህዝብ የአስከፊ  ድንቁርና፣ ለመግለፅ የሚከብድ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ  ጉስቁልና እና  የግፍ አሟሟትና የቁም ሞት ሰለባ ያደረጉት  ክፉ ገዥዎች  እያካሄዱት ያለውን የሥልጣን ማስጠበቂያ ጦርነት ከዓመታት በኋላም አደብ ገዝተው ወደ ትክክለኛው የሰብአዊ ፍጡርነት ህሊናቸው ለመመለስ ፈፅሞ ፈቃደኞች ሆነው አልተገኙም ። እንዲያውም ይባስ ብለው ተገደው የህልውና እና የነፃነት ተጋድሎ ላይ የሚገኙትን ወገኖች ወደ እውነተኛ የፖለቲካ መፍትሄ ድርድርና ምክክር መድረክ ከመጋበዝ ይልቅ “እጅ እየሰጣችሁ በእኛ አጀንዳ አቅራቢነት (ቅድመ ሁኔታ ወሳኝነት) በሚዘጋጅላችሁ ጠረጴዛ ዙሪያ ለመታደም ፈቃደኛ ካልሆናችሁ ከምድረ ገጽ እናጠፋችኋለን” በሚል ርካሽና ጭራቃዊ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ እንደተጠመዱ ቀጥለዋል።  በሌላ በኩል ከህዝብ ተወልዶ በህዝብ ድጋፍ የጎለበተው ህልውና፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ ሰላም፣ የጋራ ልማትና ሥልጣኔ የሚረጋገጥባትን አገረ ኢትዮጵያ ለማዋለድ የሚካሄደው ተጋድሎ እጅግ አበረታችና አስደናቂ በሆነ ቅርፅ፣ ይዘትና ፍጥነት ወደ ፊት በመገስገስ ላይ ይገኛል።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

አምና (ያለፈው ዓመት) ኋላ ቀርና ጋግርታም  ከሆነው የፖለቲካ ባህል በሚመነጩ ፈተናዎች ምክንያት አንድ ተልእኮና ዓላማ አለን በሚል ህይወትን ጨምሮ ከፍተኛ  ዋጋ በሚያስከፍል የትግል ሜዳ ላይ የተገኙ ፋኖዎች በሁለት ጎራ ተከፍለው ትግሉን እየጎዱ የነበሩበትንና  የጨካኝ ገዥዎችን እድሜ እያራዘሙ የመሆናቸውን መሪር እውነት ተገንዝበው እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) በሚል  ወደ አንድነት  የመጡበት ዓመት ነበር። ይህ የእውነተኛ ፋኖነት/አርበኝነት የትግል ውጤት የገዥዎችን ተልእኮ ወይም የየራሳቸውን ደካማ ባህሪ ተሸክመው  ፋኖን የተቀላቀሉ ግለሰቦች ራሳቸውን ግልፅ በማድረግ  የገዥዎች ርካሽና አስከፊ የቤተ መንግሥት ፖለቲካ መጫወቻ ካርዶች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ።  ይህ ደግሞ በትግሉ ሂደት ውስጥ ማን ምን እንደሆነ እና ከየት እስከ የትና እስከ መቸ ድረስ ሊዘልቅ ወይም ላይዘልቅ  እንደሚችል ይበልጥ ግልፅ በማደረግ ረገድ ከፍተኛ ትምህርት ሰጥቷል።

ለዚህም ነው ድንቅዬ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ታጋዮች እኩያን ገዥዎች የጦር መሣሪያን ከርካሽ ፕሮፓጋንዳ ጋር እያስታቀፉ የሚልኩትን ሥልጣን አስጠባቂ ሠራዊት እምቢ ያለውን በማስወገድ እና የሚማረከውንና ፈቅዶ እጅ የሚሰጠውን ደግሞ በሚያስደንቅ የሰብአዊነት አያያዝ  በማስተናገድና ወደ ፊት በመገስገስ አሁን ከደረሱበት ደረጃ ላይ የደረሱት።

 ተረኛ እኩያን ገዥ ቡድኖች እጅግ ከከፋውና ከከረፋው  የፖለቲካ ድንቁርናቸው ፣ የሞራል ዝቅጠታቸው፣ የሥነልቦና ድህነታቸው፣ የሥነ ምግባር ብልሹነታቸው፣ ልክ ከሌለው የሥልጣን አፍቃሪነታቸው  በሚመነጭ  ጨካኝነታቸው ቢቀጥሉም መከረኛው ህዝብ በታጋይ ልጆቹ መሪነትና አስተባባሪነት በአልገዛም ባይነት ተጋድሎ ፀንቶ በመቆም ይኸውና የድል ብሥራት ዋዜማ ላይ እና የዴሞክራሲያዊት አገር ምሥረታ ታላቅ (ታሪካዊ) ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

ከሰሞኑ ለበርካታ ዓመታት በነበራቸው ፈፅሞ ይታረቃል በማይባል የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምና ዓላማ ይታወቁ በነበሩ ድርጅቶች/ቡድኖች መካከል ስምምነት ላይ ተደርሶበት ወደ ተግባር የተገባበትና ከእኛ የፖለቲካ ትግል ታሪክ እይታ አንፃር በእጅጉ አበረታች አስደሳች የሆነው “የትብብር ለህልውና” እውን መሆን ካለፉት ሦስት ዓመታት የትግል ፅዕናትና ስኬታማነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ የዘንድሮ ወርቃማ የድል ፍሬ ነው።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

የሁሉም ነገር የራሱ የሆነ መነሻ ምክንያት እንዳለው ሁሉ የፖለቲካ/የሥርዓተ መንግሥት መፈጠር መሠረታዊው ምክንያትም የሰው ልጅ ተያይዞ ከመጥፋት/ከመጠፋፋት ይልቅ አብሮ መዳንና መኖርን በመምረጥ መብትና ግዴታውን በህግ ጥላ ሥር ለሚያስተዳድርለት አካል (መንግሥት) ለመስጠት መምረጡና መስማማቱ  ነበር። በአሳዛኝ መልኩ  ይህንን መሠረታዊ የፖለቲካ/የሥርዓተ መንግሥት ሃላፊነትና ተግባር የሚጥሱ /የሚደፈጥጡ ገዥዎች በማጭበርበር ወይም በሌላ ክፉ ዘዴ (by hook or crook) ሥልጣን ላይ እየወጡ እንዳልነበረ ሲያደርጉት ማየት/መታዘብ  ከአገር ውስጥ አልፎ በዓለማችንም በእጅጉ የተለመደ የታሪክ አካል ነው።

ግዙፍና መሪሩን እውነታ ተጋፍጠን ትክክለኛ ሥርዓተ መንግሥትን/ሥርዓተ ፖለቲካን  መመሥረትና ማሠራት ተስኖን የጥላቻና ተያይዞ የመጥፋት አደገኛ አስተሳሰብንና አካሄድን እንደ የሥልጣን መወጣጫና ማስጠበቂያ ለተጠቀሙና ለሚጠቀሙ እኩያን ገዥዎች አሳልፈን እየሰጠንና የመንግሥትና የህግ ያለህ  የሚል እጅግ አሳፋሪ ተማፅኖ በመማፀን  የግፍ አሟሟትና የቁም ሞት ሰለባዎች ከሆን ይኸውና ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ አስቆጠርን። እንዲህ አይነቱ መሠረታዊ መብትን ለሸፍጠኛ፣ ሴረኛና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች  አሳልፎ እየሰጡ መልሶ እነርሱን ከማሰቢያ አእምሮና ከማከናወኛ አካል ጋር በፈጠረ አምላክ ስም ከመማፀን የከፋ እንደ ሰውም ሆነ እንደ ዜጋ እጅግ  አሳፋሪና አስፈሪ ጉዳይ የለም። በተለይ ደግሞ በዓለማዊው ወይም በሃይማኖታዊው ወይም በሁለቱም  ፊደል ቆጥሬያለሁ (ተምሬያለሁ) ለሚል የህብረተሰብ ክፍል ።

እናም ይህንን የአሁኑን ህልውና ፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ሰላም ፣ የጋራ ልማትና ስልጣኔ አገር ባለቤት የመሆን ተጋድሎ ከእኩያን ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ቀንበር ተሸካሚነት አንፃር ካላየነውና አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ  ለድል እንዲበቃ ካላደረግነው ችግሩና ተጠያቂነቱ የእኛ የራሳችን እንጅ የሸፍጠኛ፣የሴረኛና የጨካኝ ገዥ ቡድኖችና የግብረ በላወቻቸው አይሆንም።

ስለሆነም ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ሰላም፣ የጋራ እድገትና ስልጣኔ የሚረጋገጥባት አገር ባለቤት የመሆን ብርቱ ፍላጎት ያለው ወገን ሁሉ ልብ ይበል! 

- Advertisement -

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News