

አንዱ ዓለም ተፈራ
መስከረም ፳ ፬ ቀን ፳ ፻ ፲ ፱ ዓ. ም.
አሁን በአገራችን ያለው የጦርነት ሁኔታ፤ ግልጥና የማይታበል ነው። ይሄን በአገራችን ውስጥ የሚካሄድ ጦርነት፤ በኛ አገር ብቻ የተወሰነና ሌሎችን የማይነካ አድርገን አንወስደውም። በዓለም ላይ ያለ የፖለቲካ ሁኔታ፤ የተያያዘና የተሳሰረ ነው። ታሪክን ስንመረምር፤ ሰዎች በኑሯቸው፣ ዛሬን ነገ ለማድረግ፣ ብዙ ተግባራትን ያካናውናሉ። ይሄም፤ ፉክክርና አንዱ የሌላውን ንብረት መቀማትን ያካትታል። አልፎ ተርፎም መጠፋፋትን እንደሚጨምር፤ ታሪክ አስቀምጦልናል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ሰዎች በአንድነት በሚኖሩበት ወቅት፤ የግለሰብ ህልውናቸውን ለስብስቡ የአንድነት ህልውና ተገዢ በማድረግ፤ የጋራ ጥረታቸው ጠንክሮ፤ በራሳቸውና በሌሎች ስብስቦች መካከል አጥር አበጅተው፤ “እኛ!” እና “እነሱ!” የሚል ክፍፍል በመፍጠር፤ እኛ ለሚሉት ህይወት ህልውና፤ ለግል ህልውና የሚያደርጉትን ጥረት ያድሉታል። በዚህ ስሌት፤ አረቦችም ሆኑ አውሮፓዊያን፤ በአፍሪካዊያን ላይ ያካሄዱትን ያባሪያ ንግድ፤ መመልከቻ መነፅር እናገኛለን። ከዚያም፤ የቅኝ ግዛት መስፋፋትን እናጤንበታለን። ቀጥሎም፤ ቀደም ሲል የተካሄደውን በቅኝ ግዛት ምክንያት በአፍሪካዊያን ላይ የደረሰውን እናስብበታለን። ወደ አገራችን ስናተኩር ደግሞ፤ ከማንነታችን መገለጫ አንዱ የሆነው፤ ከውጪ የተደረጉብንን ወረራዎች መመከታችን ነው። አርበኞቻችንን ስንዘክር፣ የመልክዓ ምድራችንን አጥር ስናጠብቅ፣ መዝሙራችን፣ ፉከራችን፣ ሙዚቃችን፣ ቅኔያችን ስንመረምር፤ ይህ ራሳችንን እና ጎጆ፣ ትዳርና ንብረታችንን መጠበቅ፤ የህልውናችን ዋና ጉዳይ ሆኖ፤ ማዕከላዊውን ቦታ ይዞ እናገኘዋለን። ይሄ አሁን በአገራችን እየተካሄደ ያለው ጦርነት፤ የኛ ብቻ ሳይሆን፤ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ሂደትም አካል ነውና፤ በዓለም ዙሪያ የፖለቲካ እሳቤ፤ የራሱ የሆነ ቦታ አለው። በዚህ ሂሳብ፤ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ወደ ውጪ ሆኗል። በአገራችን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በመመርመር፤ ውጪው ዓለም የፖለቲካ ግንዛቤ፤ ማን ዓይነት ምልከታን እየፈጠረ ነው! የሚለውን ጉዳይ እናስተባቃለን።
እንግዲህ ለዚህ ሁሉ መሠረታዊ መነሻችን፤ አገራችን ያለችበት የመልክዓ ምድር አቀማመጥ ነው። አገራችን የአባይ ምንጭ መነሻ መሆኗና ይህ ወንዝ ለሌሎች ወሳኝ የሆነ የህይወት ሚና ተጫዋች በመሆኑ፤ በሱዳንና በግብፅ በኩል፤ የረጅም ዘመን በዓይነ ቁራኛ የመታያ ዒላማ አድርጎናል። ለቀይ ባህር ያለን ቀረቤታ፤ በዚያ ባህር ለሚደረገው የንግድና ወታደራዊ እንቅስቃሴ፤ ጥርስ ውስጥ አስገብቶኗል። አገራችን የአፍሪካ የፖለቲካ ክንውን ማዕከል መሆኗና የአፍሪካ አንድነት ጽሕፈት ቤት ከአውሮፓ ኮሚሽን ጋር መቀመጫ ሆና መገኘቷ፤ ሌሎች በቅናትም ይሁን በእገዛ፤ የተሯሯጡበትን ሁኔታ ፈጥሮብናል። በታሪካችን ደግሞ፤ በክርስትናና በእስልምና መፈጠርና መስፋፋት የተጫወትነው ድርሻ፤ የሌሎችን ትኩረት ስቧል። ለቅኝ ግዛት መንኮታኮት ያደረግነው አስተዋፅዖ፤ የምዕራባዊያንን ኩርፊያ አስከትሎብናል። እናም ታሪካችን፤ አሁን ላለንበት የጦርነት ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፤ ላለንበት የፖለቲካ ሀቅ፤ ሌሎች ላላቸው የፖለቲካ አመለካከት ዋና ባለቤት ነው። ከዚህ በላይ ደግሞ፤ በአገራችን ውስጥ ሊኖር የሚችለው እምቅ የሀብት ክምችት፤ ሌላው ጉዳይ ነው። ይሄን እዚህ ላይ ካስቀመጥኩ በኋላ፤ በአገራችን እየተካሄደ ያለውን፤ ራሱን ጦርነቱን እንመልከት።
አሁን በአገራችን ያለው ጦርነት፤ መሠረታዊ ምክንያቱ፤ በግለሰብ ኢትዮጵያዊ እና በኢትዮጵያዊነት ላይ የተማከለ ነው። በቀጥታ ሳቀርብው፤ ይህ ጉዳይ፤ እኔ ነኝ ኢትዮጵያዊው! ወይንስ በደፈናው በዐማራነቴ ነው ዐማራ ኢትዮጵያዊ የሚል ዜግነት ያገኘሁት! በሚለው ላይ የተቆለፈ ነው። ይህ ጉዳይ፤ በተለያዬ መነፅር እየታዬ፤ የተለያዩ የፖለቲካና የማንነት እምነቶችን ፈጠረ። ከዚያ ተነስተው፤ የፖለቲካ ድርጅቶች የየራሳቸው ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያዎችን በመቅረጽ፤ መሪዎቻቸው ሕዝቡን ወደየራሳቸው ወገን ለማሰለፍ ተጠቀሙበት። ወዲያና ወዲህ ያጠሯቸውን አካላት በማስኮልኮል፤ የፖለቲካ ጉልበት ባለቤቶች፤ ራሳቸውን የአገራችን የግል ሥልጣን ባለቤት ለማድረግ፤ የርስ በርስ ጦርነት አወጁ። ኢትዮጵያዊ ጠፍቶ፤ ትግሬ፣ ዐማራ፣ ኦሮሞ፣ አፋር፣ ሲዳማ፣ ጉራጌ፣ ሶማሊ፣ ወላይታ፣ አኙዋክ፣ ኑሬ፣ አደሬ፣ ጋሞ አልፎ ተርፎ ደግሞ፤ ትርጉማቸው አስቸጋሪ የሚሆን፤ አዲስ አበቤ፣ ድሬ የሚሉ የፖለቲካ ማንነቶች ወደ ፖለቲካው መድረክ፤ ዓይኖቻቸውን አፍጥጠው መጡ። ይህ እየሰፋ የሄደ የመከፋፈያ አጥር፤ በያንዳንዱ ክፍል ትርጉሙና ጥንካሬው እየጎለበተ፤ ለማያባራ የብዙዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆነ። ይሄንን መመርኮዣ በማድረግ፤ ከአጠቃላይ ዕይታ ወርደን፤ በተጨባጭ የአገራችን የጦርነት ሁኔታ ላይ እናተኩር።
ለአንድ ግለሰብ። የማንነት መሠረቱ፣ የግለሰቡ ህይወት ነው። የግለሰቡ ህይወት ለማንነቱ ማጠንጠኛ ነው። ከዚያ ቀጥሎ፤ ከሌሎች ግለሰቦች ጋር በሚኖረው የኑሮ ግንኙነት፤ ሌሎች ማንነቶችን ይላበሳል። በርግጥ የተፈጥሮ ማንነቱን፤ እናትና አባቱ የሠጡት ነው። የፀጉሩን ቀለምና ጥንካሬ፣ የቁመቱን ርዝመት ወይንም እጥረት፣ የቆዳውን ቀለም እና የመሳሰሉትን ያገኘው፤ ከወላጆቹ ነው። ይሄ የመጀመሪያው መሠረታዊ የማንነቱ መነሻ ነው። በዘመናዊው የኅብረተሰብ አኗኗር ደግሞ፤ ይሄ ማንነት፤ በወላጆቹ የአገር ባለቤትነት የቆመ ነው። ይሄ የአገር ባለቤትነት፤ ቅደም ተከተል ያለው ሳይሆን፤ በቀጥታ ከትውልድ ማንነቱ ጋር አብሮ የተሳሰረ ነው። በወላጆቹ ዜጋ፤ የርሱም ዜግነት ይወሰናል፤ አድጎ በምርጫው የሌላ አገር ዜጋ ልሁን! እስካላለ ድረስ። አብዛኛውን የበለፀጉ አገሮች፤ በአገራቸው የተወለደን ግለሰብ፤ ሙሉ የዜግነት መብት በመሥጠት፤ የአገሪቱ ሕጋዊ ዜጋ ያደርጋሉ። ይህ ግለሰብ፤ ከሌሎች ጋር የአገሩ ባለቤት በመሆኑ ደግሞ፤ በኢትዮጵያዊነቱ ተመርኩዞ፤ ዐማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ እያልን የምንጠራዉን፤ በደሙ ይዘት የተመሠረተ የዘር ማንነት፤ ያለብሰዋል።
በመጀመሪያ፤ ራሱን “የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር!” ብሎ የጠራው ቡድን፤ ይሄንን ከላይ ያሰመጥኩትን፤ በደም ይዘት ላይ የተመረኮዘ የመከፋፈል ጉዳይ፤ በአገራችን ላይ አስቀመጠ። ዋናው ላለንበት የጦርነት ሀቅ፤ ባለቤቱ ይሄ ነው። ይሄ ጉዳይ፤ በሂደት ተጋልጦና ተቀባይነት አጥቶ፤ ሕዝቡ በያለበት፤ “አትከፋፍሉን! በቃን! ኢትዮጵያዊያን ነን! አጥሩን አንቀበልም! ያንዳችን ደም የሌላችንም ደም ነው!” በማለት፤ (በጎንደር ሕዝቡ ተሰልፎ፤ “የኦሮሞ ደም የኛም ደም ነው!” ማለቱን ልብ ይሏል) ይሄንን ጠባብ ደርጅት አባረረው። ድርጅቱ ቢባረርም፤ የፖለቲካ ፍልስፍናው፣ የአስተዳደር መመሪያውና በቦታው ያስቀመጠው ሕገ መንግሥትና የክልል አጥር፤ እንዳለ ቀጠለ። የዚህ ምክንያት፤ ሥልጣኑን ለመውሰድ አስፍስፈው በዙሪያው የነበሩት፤ ዋና ጉዳያቸው፤ ሥልጣኑን ከትግሬ ባለቤትነት ወደ ኦሮሞ ባለቤትነት መቀየር እንጂ፤ የነበረውን አገር አፍራሽ ስርዓት መለወጥ አልነበረምና ነው። እናም አሁን በአገራችን ያለው ጦርነት መንስዔው እና እያሳደገው ያለው ጉዳይ፤ ይሄ ነው። በትክክል ይሄ ሊያቆምና እንደ አገር ልንቀጥል የምንችለው፤ ይሄ ሂደት ሲከስም ብቻ ነው።
በሥልጣን ላይ ያለው አብይ መራሹ የአክራሪ ኦሮሞ ገዢ ቡድን፤ “የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ተግባርን እያከናወንኩ ነው!” የሚል ትርክት ይዞ ነው፤ ዐማራውንም ሆነ ሌሎች ወገኖችን በድሮንና በከባድ መሳሪያ እያጋዬ ያለው። ሕዝቡን በማውደም አገር ማስተዳደር! ታጋዮቹ ደግሞ፤ “በማንነታችን ለሚደርስብን የመጥፋት አደጋ፤ ህይወታችንን እንሠጣለን!” በማለት ነው፤ ትጥቅ አንስተው ትግላቸውን የቀጠሉት። ገዢው ቡድን እያደረገ ያለው ጦርነት፤ ኢትዮጵያዊነትን እናም ኢትዮጵያን አጥፍቶ፤ ቡድኑ ለሚመኘው አዲስ ማንነትና አገር እውነታ ነው። በዚህም ምክንያት፤ ይህ ቡድን እስካልተወገደ ድረስ፤ አገራችን ከዚህ ጦርነት ልትወጣ አትችልም። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ይሄንን ገዢ ቡድን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን፤ ስርዓቱንም ከፖለቲካ ፍልስፍናው፣ ከሕገ መንግሥቱና ከአስተዳደር መመሪያው ጋር ለማፍረስና፤ በቦታው ኢትዮጵያዊነትን ለማንገሥ የማይደረግ ትግል፤ ኢትዮጵያን ከጦርነት ሊያስወጣት አይችልም። ይህ በንድፈ ሃሳብ ትክክለኛና መደረግ ያለበት ጉዳይ ነው። ያለንበት የፖለቲካ ሁኔታ ግን፤ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ሳይሆን፤ በተጨባጩ በመሬት ላይ ባለ ሀቅ ነው የሚገዛው። እናም በቦታውና በየደረጃው ያሉ የመንግሥቱ መዋቅር አባላት፣ በየቦታው ያሉ የታጠቁ ኃይላት እና ጉዳዩ አስጨንቋቸው ለውጡን በማገዝ ያሉት በሙሉ፤ አስበውበትና እውነተኛ መፍትሔ ለማምጣት ቆርጠው ሲነሱ የሚደርሱበት ውሳኔ፤ ኢትዮጵያዊነትን በማንገሥ፤ ጦርነቱን ያከትመዋል። ካለንበት እውነታ ወደዚህ ሃሳብ ለመሸጋገር ግን፤ ከባድ ተራራ ከፊታችን ተጋርጧል።
መረዳት ያለብን፤ ይህ ጦርነት፤ ሕዝቡን የበለጠ እየከፋፈለ፣ ድህነትን እያስፋፋ፣ እያጨራረሰን ነው። ከፖለቲካው ጉዳት በላይ፤ የብሩ ዋጋ ማሽቆልቆል፣ ረሃብና የአቅርቦት እጥረት፣ የሕዝብ ኅብረተሰባዊ እንቅስቃሴ ጉድለት፣ የተፈናቃዮች መብዛት፣ የእርሻ በወቅቱ አለመከናወን፣ አብይ እውቅና ለማግኘት የሚሄድበት ርቀት፣ ሕጋዊ ነኝ! ለማለት የሚያደርገው መፍጨርጨር፣ የሚሰግዱለትን ፍለጋ መሯሯጡ፣ ፍርድ ቤቱን የራሱ በትር ማድረጉና ሌሎች ተግባራቱ፤ ራሱን ዘለዓለማዊ ገዢ ለማድረግ ዐማራን መፍጀት፣ ማፈናቀል፣ እህል ማጋየት፣ ትምህርት መንፈግ፣ ኅብረተሰባዊ እንቅስቃሴን ማገት፣ ጦርነቱን ግዴታ ወደፊት እንዲገፋው እያደረገው ነው። ይህ በአገራችን ውስጥ ያለ ሀቅ ነው። ጦርነታችን ከሌሎች አገራት የፖለቲካ ሂደት ጋር የተያያዘ በመሆኑ፤ ሌሎች ይሄንን በኛ አገር እየተካሄደ ባለው ጦርነት፤ ምን እየተጫወቱ ነው? እንዴትስ ያዩታል! ወደሚለው እንሸጋገር።
ከላይ እንዳስቀመጥኩት፤ የአገራችን የመልክዓ ምድር ቦታና ታሪካችን፤ በዓለም የፖለቲካ አስላለፍ፤ ግልጥ ቦታ አለው። ያ ቦታ የሌሎችን ትኩረት ስቧል። ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ፤ አገራትና የውጪ ኃይላት፤ በአገራችን ውስጥ ግራና ቀኝ የተሰለፉትን ወገኖች በማበረታታትና በመደገፍ፤ የጦርነቱ አካል ናቸው። የተዋጊዎችም ጥንካሬና እድገት ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። ሌሎች ምን ያህል እጃቸው ዘልቆ ገብቷል? የሚለው፤ ራሱን የቻለ ጉዳይ በመሆኑ፤ እዚህ ላይ ጊዜ አናጠፋበትም። ነገር ግን፤ በግንዛቤያችን እንያዘው። ለምንፈልገው የነገ ኢትዮጵያዊነትና ለምንፈልጋት የነገ ኢትዮጵያ፤ አሁን እየተካሄደ ያለው ጦርነት፤ ለሌሎች አገራትና ኅይላት ምን ግንዛቤ ሠጥቷል? ምን መልስስ አግኝቷል? የሚለውን እንመለከት።
ባሁኑ ሰዓት፤ ሱዳን በእርስ በርስ እየታመሰች ስለሆነ፤ እንደ አንድ የሆነች ሱዳን አገር፤ በአገራችን ጦርነት በቀጥታ ባትሳተፍም፤ ሁለቱ ተዋጊ ወገኖች፤ በአገራችን በሚካሄደው ጦርነት፤ በቀጥታ ተጫዋቾች ናቸው። የአብይ መራሹ ገዢ ቡድን በቀጥታ በአረብ ኤሚሬትስ በመታዘዝ የሚቲን ቡድን ደግፎ ጣልቃ መግባቱ፤ ሱዳንን በጦርነታችን ቀጥታ ተሳታፊ አድርጓታል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር፤ ከኤርትራና ግብፅ ጋር በማበር፣ የቡርሃንን ቡድን ደግፎ በሰሜናዊ ክፍሉ አብሮ መሰለፉ፤ የሱዳንን የእርስ በርስ ጦርነት፤ የራሳችን ጦርነት አካል እንዲሆን አድርጎታል። በሶማሊያ በኩልም ቢሆን፤ ምንም እንኳን አገሪቱ በራሷ የርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች ቢሆንም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚደረገው ጦርነት፤ ወገን በመለየት፣ ተሳፊዎችን በማገዝ ተሳታፊ ሆናለች። ኤርትራ፤ ከአብይ ገዢ ቡድን ጋር የህልውና ጦርነት እያንዣበበባት በመሆኑ፤ ጦርነቱ ኤርትራ ከሚሆን ይልቅ፤ በትግራይና በዐማራ መሬት እንዲሆን፤ ድጋፏን በነዚህ አካባቢዎች ላሉ ታጋዮች እየለገሰች ነው። እንግዲህ ከፊታችን ወለል ብሎ የሚታየው፤ ሌሎች በጦርነቱ ሂደት እጃቸውን በቀጥታ በማስገባት፣ ጦርነቱን ለራሳቸው የፖለቲካ ግኝት እየመሩት መሆኑን ነው። አስላለፋቸው ይሄን ይመስላል። አረብ ኤሚሬትስ፤ ከማንም በበለጠ፤ ለራሷ የምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ፖሊሲ ስትል፤ የአብይን ገዢ ቡድን፤ በከፍተኛ ወጪ እየደገፈች ነው። ለኢትዮጵያ ብላ አይደለም። ለራሷ የአገር ጥቅም ስትል ነው። እህል ከኢትዮጵያ ለማምረትና የውሃና መሬት እጥረቷን በኢትዮጵያ ጉዳት ለማካካስ፤ በቀይ ባህር የንግድ መስመር ላይ የፖለቲካ ሚና ለመጫወት፣ በሶማሊያ ለምታደርገው ጣልቃ ገብነት እና በሱዳን ለምታደርገው የጣልቃ ገብነት ጦርነት፤ በኛ የርስ በርስ ጦርነት ጣልቃ ገብታ፤ ጦርነቱን ወደምትፈልገው ግብ ለማድረስ እየተጠቀመችበት ነው። ቻይናም ሆነች ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ፣ ሩስያም ሆነች አውሮፓ ዩኒየን፤ የሩቅ ታዛቢዎች አይደሉም። እያንዳንዳቸው በየፊናቸው እየተጫወቱ ያለው ሚና አለ። ትናንት ዶናልድ ትራምፕ፤ በኤርትራ ላይ ተጭኖ የነበረውን እቀባ ሲያነሳ፤ በቀይ ባህር ላለው የመስመሩ እንቅስቃሴ እንዲረዳው እንጂ፤ ለኤርትራ አስቦ አይደለም።
ከላይ በዝርዝር ያስቀመጥኩት፤ በአገራችን ላይ እየተካሄደ ያለው ጦርነት፤ ምን ያህል የውስጣችን ብቻ ሳይሆን፤ የውጪ ኃያላትን እንዳማከለ ማሳያ ነው። ይህ፤ ጦርነቱን ለማቆምም ሆነ የአንዱ ወገን አቸናፊ ሆኖ የሚወጣበትን ውጤት ለማስገኘት፤ ባለቤቶቹ እኛ ብቻ እንዳልሆን ያመላከታል። ሆኖም ግን፤ የራሳችን ነገ ባለቤቶቹ እኛው እንደሆን ማሰረገጥ አለብን! ይህ የኛና የኛ ጉዳይ ነው! ይህንን ማድረግ የምንችለው ደግሞ፤ ኢትዮጵያዊያን ወጣ ገቡን ተመልክተን፣ መሠረታዊ የትግሉን አስኳል ጠንቅቀን አውቀን፣ የያንዳንዳችንን ሚና ለይተን፤ ለሚቀጥለው ትውልድ ያለንን ኃላፊነት ተገንዝበን፤ ድርሻችንን ስንወጣ ነው። በርግጥ ከአሳማ ጋር ጭቃ ውስጥ አትግባ! የሚል ነገር አለ። ጭቃ ውስጥ ጨምሮ ያጨማልቃልና ነው። የአገር ጉዳይ ግን፤ የማንነታችን እና የህልውናችን ጉዳይ ነው። ዝምታና የራስን የዛሬ ጥቅም ከማሳደድ በላይ ነው። ውግንናቸውን ከገዢው ክፍል የደረቡ፤ ልያስቡበት የሚገባ ጉዳይ አለ። ከሚሰምጥ መርከብ መግባት፤ ሆን ብሎ ራስን መግደል ነው። አብይ መራሹ የአክራሪ ኦሮሞ ገዢ ቡድን፤ እየፈራረሰ ነው። ይህ የምኞት ጉዳይ ሳይሆን፤ ተጨባጩ የአገራችን የፖለቲካ ሀቅ የደነገገው ነው። ዛሬ በወታደራዊ ኃይሉ፤ ያንን ቦታ ወይንም አካባቢ ሊቆጣጠር ይቻላል። ነገም አስፍቶ፤ በድሮንና በጀት፤ አንድን አካባቢ ሊያወድም ይችላል። መሠረታዊ የአገራችንን የፖለቲካ እውነታን ግን፤ አሁን በያዘው መንገድ፤ ምንም አደረገ ምንም፤ ሊቀይረው አይችልም። ኢትዮጵያዊነትን በጉልበቱ ቀይሮ የራሱን ፍላጎት ሊያሟለበት አይችልም።
በጦርነቱ እየተሳተፉ ያሉት ተቃዋሚ ኃይላትም፤ ዋናው መሠረታዊ ግባቸውና አካሄዳቸው፤ በኢትዮጵያዊነት ላይ ቢተከል እወዳለሁ። ያለውን ስርዓት ቢያፈርሱት ሁላችንንም በኢትዮጵያዊነታችን የሚቀበል አገር መልሰው ቢያቋቁሙ እወዳለሁ። አሁን ካሉበት የትግል ግንዛቤ ተነስተው ወደዚህ እሳቤ ለመሸጋገር፤ ከባድ እንደሚሆንባቸው ይገባኛል። ተጨባጩ ሀቅ ደግሞ፤ በምኞትና በመግለጫ ሳይሆን የተመረኮዘ ሳይሆን፤ አሁን ባሉበት እውነታና በሚወስዱት እርምጃ የተወሰነ ይሆናል። በአሁኑ ሰዓት የተፈጠረውን የትብብር ለህልውና ሂደት፤ በዚህ መነፅር እመለከተዋለሁ። ይሄን ስርዓት ማፍረስና የምመኘው ኤትዮጵያዊነት እውነት እንዲሆን፤ የግድ አንድ ቦታ መጀመር አለበት። በምንም ምክንያት ሆነ በምንም፤ አሁን ያለንበት ሂደት ተጀምሯል። ይሄንን ወደ ምንፈልገው ግብ እንዲሄድ መጣር፤ የያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው። “የለም! በምፈልገው ዓይነት አልተቀረጽም!” በማለት ያለውን እውነታ መቃወምና ማውገዝ፤ ማንንም አይረዳም፤ ከጠላታችን ከገዢው ቡድን በስተቀር። የኔ አቋም ይሄ ነው። የምጥረውም ለመጨረሻው ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ ነው።
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






‘Whistle Blower REVEALS Truth About West’s War Obsession | Kolja Spöri
Neutrality Studies
Link = youtube.com/watch?v=lA3Pw1q7ZLk
ዓይናችን ይገለጥ!!!
=========
የአገራችን በጦርነት መታመስ ምንጩ ፤ የጪው ዓለም አቦላት (አሜሪካና አውሮፓ) ናቸው።
Be well.