Homeነፃ አስተያየትየአማራ ብሔረተኝነትና ኢትዮጵያዊነት (ክፍል ሦስት)

የአማራ ብሔረተኝነትና ኢትዮጵያዊነት (ክፍል ሦስት)

Advertise Here
Advertise here
የአማራ ብሔረተኝነት

በአበበ ኃብተሥላሴ  

…ካለፈው የቀጠለ ክፍል ሦስት 

መስከረም 29 2019  

የአማራ ብሔረተኝነትን የሚያቀነቅነው ጋዜጠኛ አንሙት ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ ያለውን አቋም ግልጽ ያደረገበት የሚከተለው ተጨማሪ አባባሉ ነው። 

“በዚህ [በአማራ ትግል] ውስጥ ሚና እንዲኖረው የሚፈልግ ሰው በዚህ ውስጥ ሚና እንዲኖረው የሚሻ አካል ዛሬ ገና አማራው ተደራጅቶ ተነሳ ብሎ ትናንት ከተሸነፈበት መድረክ ፈቀቅ ብሎ ዛሬ ደግሞ እዚህ መጥቶ የትናንት የሽንፈት ውርሱን ይዞ መጥቶ በአማራ ትግል  ውስጥ አምጥቶ ተመልሶ እንወቅላችሁ የሚለው አካሄድ አያዋጣም ነው። የዛ አርባን (ከተሜ) ብሔረተኛና የአርሶ አደር አማራ  ብሔረተኝነት ግጭት ነው አሁን እየተካሄደ ያለው። The two faced Amhara Identity የሚል አንድ ሰውዬ አለ። ጽሁፉን እልክልሃለሁ፡ በዚህ ጽሁፍ አርባን አማራ ብሄረተኛ የሚባለው በጎሳ አማራ ያልሁኑ ጭምር ያሉበት በፖለቲካ አስተሳሰቡ ኢትዮጵያኒስት፣ የዜግነት የአንድነት የፖለቲካ ሃይል የሚባለው ከአርሶ አደር አማራ ብሔረተኛ ጋር እንዴት ሳይጋጭ እንዴት ቅራኔ ሳይፈጥር ይሂድ የሚለውን መረዳት ይገባ ነበር። ነገር ግን ምን መሰለህ አሁን የመጣው ይሄ [የአማራ] ብሔረተኛ እንደ ትግራይ ብሔረተኛ እንደ ኦሮሞ ብሔረተኛ ሊሆን ስለሆነ ይዞት የመጣውን ትግል በዛ መንገድ ይዞ የሚቀጥል ከሆነ ኢትዮጵያን ያፈርሳታል የአማራ ብሔረተኛ ለኢትዮጵያ ስጋት ነው ብሎ እየተመለከተ ነው ይሄ አርባን አማራ ብሔረተኛ ማለት። ይሄ ከሆነ ደግሞ ዞር በል ነው እየተባለ ያለው። ይሄ ከሆነ በራስህ  ሜዳ ሄደህ ተጫወት ነው እየተባለ ያለው”1። 

እዚህ ላይ አንሙት ስላነሰው ጽሑፍና ጸሐፊ ምንነትና ማንነት ማለት ተገቢ ይሆናል። የዚህ ጽሁፍ ርዕስ The Two-Faced Amahara  Identtity2የሚል ሲሆን ጽሑፉ እ.አ.አ በ2005 የተጻፈና ፀሐፊውም ዶ/ር ሴግፍሪድ ፖስዋንግ (Siegfried Pausewang) የሚባል የዶክትሬት ማዕረግ ያለው ግለሰብ ነው። ይህ ፀሐፊ ኢትዮጵያን በተመለከተ የተለያዩ ጽሑፎችን የጻፈ፣ በ1960ዎቹና 1970 መጀመሪያ አካባቢ ኢትዮጵያ ውስጥ የኖረ ሰው ነው። ከ1967 እስከ 1971 ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሽዮሎጂ ትምህርት ረዳት ፕሮፌሰር ሆኖም የሰራ ሰው ነበር። ከ1983 ወዲህም ለኢትዮጵያ ቤተኛ የነበረ ሰው መሆን የቻለውም የትሕነግን የጎሳ ፖለቲካ እሳቤ በእጅጉ የሚገዛው ስለነበር ነው። ይህ ግለሰብ በዚህ በተባለው ጽሑፍ ውስጥ የአማራ ማህበረሰብን በሁለት ጎራ ከፍሎ እንደሚከተለው ይገልጻቸዋል። በጽሑፉ ገጽ 286 ላይ አንደኛው ወገን ይላል ጸሐፊው “እራሳቸውን ኢትዮጵያዊና አማርኛ የጋራ ቋንቋቸው ያደረጉ ነገር ግን ከተለያየ የጎሳ ማንነት የተሰባሰቡ ከተሜዎች ሲሆኑ ሌላኛው ከነዚህ የሚለይ ወገን አብዛኛው የአማራ ገበሬ ሕዝብ ነው።3”  

ግለሰቡ በጽሑፉ ውስጥ በብዛት ያተተው ስለዚህ እራሱን አማራም ኢትዮጵያዊም ብሎ ስለሚጠራና እሱ የከተሜ አማራ ብሎ ስለሚጠራው ወገን ሲሆን የአርሶ አደሩ የአማራ ብሔረተኛ ስለሚለው ወገን ግን ያለው እጅግ በጣም ውሱን ነው። በተጨማሪም ስለከተሜ አማራው ብዙ ቢያትትም ይበልጥ ያተኮረው ግን አስተሳሰቡንና ፍላጎትን በመንቀፍ ነው። በጽሁፉ ገጽ 280 ላይ እንዲህ ይላል። 

“ይህ የከተማ ኗሪ፣ የተማረ፣ ከተለያየ ማንነት የተውጣጣ እራሱን ተራማጅ ልሂቅ አድርጎ የሚቆጥርና በኢትዮጵያ የመሪነቱን ሃላፊነት መውሰድ የሚገባው አድርጎ ነው። ይህ ወገን እ.አ.አ ከ1975 በተለይም እ.አ.አ ከ1991 በኋላ በኢትዮጵያ የማዕከላዊ አስተዳደር ፖለቲካዊ እሳቤ ተቀባይነት ማጣትና እየገነገነ ከመጣው የጎሳ ፖለቲካ እሳቤ በተቃራኒ እራሱን ኢትዮጵያዊ አድርጎ ለመግለጽ ጠንካራ ዝንባሌ ያደረበት ነበር”4። 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

እንግዲህ በተለይ ከ1983 በኋላ ከሕዝብ ፈቃድ ውጪ ጥቂት ጽንፈኞች ያዘጋጁትና በግድ የተከሉት አድሏዊ ሥርዓትን ተከትሎ የጎሳ ፖለቲካ የሁሉ ነገር መዘወሪያ በመደረጉ በማንነት ብቻ እራስን መግለጽ እንደ ፋሽን እራስን ኢትዮጵያዊ አድርጎ መግለጽ ደግሞ እንዲኮሰምን ጥረት ቢደረግም መሬት ላይ ያለው ሃቅ የሚመሰክረው ግን ኢትዮጵያዊነት ተቀባይነት ያጣው በጥቂት ጽንፈኞች እንጂ በአብዛኛው ሕዝብ አለመሆኑን ነው። ይህ የጸሐፊው አባባል ግን ይህንን ሃቅ የካደ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት በአብዛኛው ሕዝብ ልብ ውስጥ የነበረና እስክሁንም ድረስ ታፍኖ ያለ ነገር ግን ደንድኖ የኖረና ሁኔታዎች ሲመቻቹ የሚፈነዳና አገሩን የሚያጥለቀልቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት መገለጫ ነው። ለዚህ አንድ ማሳያ የሚሆነው ጸሐፊው ይህንን ጽሑፍ ከጻፈበት እ.አ.አ ከ2005 በፊትና በኋላም ኢትዮጵያዊነት እየተጠቃ ቢኖርም በ2010 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ መንግሥት ሥልጣን ሲመጣ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ በማለቱ የሚገፈልገውን መሪ ያገኘ መስሎት የተለያየ ማንነት ያለው አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠው ታይቶ የማይታወቅ ድጋፍ ነው። 

ምንም እንኳን ኢትዮጵያዊነት እንዲዳከምና እንዲሞት ጭምር ለብዙ አሥርት አመታት ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም እንደሚፈለገውና እንደተጠበቀው በቀላሉ የሚበን እንዳልሆነ ያረጋገጠው ይህ የ2010 ድጋፍ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ፣ በአገሩ ተከባብሮና ተግባብቶ በአንድነት ለመኖር የሚፈልግ እንጂ ጽንፈኞቹ እንደሚደክሙለትና ለማሳመን እንደሚጥሩት በአድሏዊ የጎሳ ፖለቲካ በቀለኛ እሳቤ ማንነቱ ከኢትዮጵያዊነቱ በልጦበት ተለያይቶ እንዲባላ፣ ሰላሙን እንዲያጣ፣ ለማያባራ ጦርነት ሰለባ እንዲሆን የማይፈልግ በመሆኑ ነው። ሆኖም ግን ዶ/ር ፖስዋንግም ሆኑ የአማራ አርሶ አደር ብሔረተኛ ነን ባዮች ይህንን ሊቀበሉ የማይፈልጉበት ምክንያት አላቸው። ጸሐፊው ምን ያህል በጎሳ ፖለቲካ ያበደ፣ ለእሳቤው ጥልቅ ፍቅር ያለውና ትሕነግን አፍቃሪ መሆኑን ከሚያሳዩት አባባሎቹ ውስጥ አንደኛው በጽሑፉ ገጽ 280 ላይ ያለው ነው። እንዲህ ይላል ጸሐፊው፣ 

“ኢሕአዴግ [በትሕነግ የሚዘወረው] እ.አ.አ በ1991 ኢትዮጵያን በጎሳና በቋንቋ መስፈርት ለመከለል እንዲወስን ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ እየገነገነ በመጣው የጎሳ ፖለቲካ ላይ መሰረት ያደረገ የእምቢተኝነት ትግል ነው። ኢሕአዴግ ምንም ምርጫ አልነበረውም።

እ.አ.አ በ1991 የመንግሥት ሥልጣን የመያዝ ቅቡልነት ለማግኘት ከተፈለገ እየገጎለበቱ ለመጡ በጎሳ ማንነት መስፈርት ለተደራጁ አካላት ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ማለትም በተቻለ መጠን ቢያንስ የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን የሚረዳ መብት መስጠት ግዴታ ነበር”5። 

- Advertisement -

ለዚህ የባንዳ ስብስብ ለሆነው የትሕነግ ፀረ-ኢትዮጵያ፣ ፀረ-ሕዝብና ፀረ-ልማት ሥርዓት ተከላ አስፈላጊነት እንደ ምክንያት የተወሰደው ይህ አባባል ትክክል የማይሆነው እንደሚታወቀው በጊዜው የነበሩና በማንነት ላይ መሰረት ያደረገ አደረጃጀትን ይዘው የነበሩ አብዛኛዎቹ አካላት በሕዝብ ግፊትና ትግል የተወለዱ አለመሆናቸው ነው። በጊዜው ተፈልፍለው የነበሩ አብዛኛዎቹ ድርጅት ተብዬዎች የሕዝብ ብሶትና ፍላጎት የወለዳቸው ሳይሆን በፀረ-ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት አገራት የሚታገዘው ትሕነግ ወደ መሃል አገር በቀላሉ እንዲገሰግስ ለመርዳትና ላነገበው አገር የማዳከም ፀረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ ስኬት ሲባል የፈጠራቸው ናቸው። እነዚህ እየጎለበቱ የመጡ የሚባሉት ድርጅቶች ትሕነግ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ እንዲረዳው የተለያየ ማንነት ያለው ሕዝብ የሚኖርባቸው የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ ያለኮሽታ መግባት እንዲችልና ወደ መዲናዋ ለመድረስ የተለያየ ማንነት ያላቸውንና በምርኮ ይዞታ ሥር የነበሩ ግለሰቦችንና ሌሎችን በማስገደደም በማግባባትም የፈጠራቸውና ከሥልጣን በኋላም ለከፋፍለህ ግዛ ስልት የተጠቀመባቸው ናቸው። በጊዜው ማለትም ከ1983 በፊት የሚታወቁት ትሕነግ፣ ኦነግና ኦብነግ ሲሆኑ ሌሎቹ በማንነት መስፈርት የተፈጠሩና የኢሕአዴግ ድርጅቶች የሚባሉት የሕዝብ ፍላጎትና ትግል የወለዳቸውና በዚህም ምክያት እየፈረጠሙና ጥያቄያቸውም በስፋት ተቀባይነት ያገኘ እንዳልሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚነገረው አይደለም። 

ከሥልጣን በኋላም ትሕነግ እንዴት ቆሜለታለሁ የሚለውን ሕዝብ ሳይሆን ኦሕዴድን እየተጠቀመ የተለያየ ማንነት ያለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አፍኖ መንግሥታዊ ምዝበራ በማካሄድ የጥቂት ባለሥልጣናቱን ጥቅም ሲያስጠብቅና ድርጅታዊ ኃብት ሲያፈራ እንደነበር ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚነገረው አይደለም። ሆኖም ግን ለዚህ ከሕዝብ ፈቃድና ይሁንታ ውጪ በትሕነግ በግድ ለተተከለና በሕዝብ ላይ የማያባራ መቅሰፍት ላወረደ አድሏዊ፣ አጥፊ፣ የዜሮ ድምር ላስከተለና ሁሉንም ለጎዳ የጨለማ ዘመን እሳቤ ለሚገዛው ሥርዓት ተገቢነት የጸሐፊው በዚህ ደረጀ ወርዶ ምክንያት ፈላጊ መሆን የሰውዬውን አቋም ግልጽ ያደረገ ነው። ይህ ግለሰብ ምን ያህል ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነ የትሕነግ አቋምን አራማጅ እንደሆነ የሚከተለው አባባሉ ተጨማሪ ምስክር ነው። በጽሑፉ ገጽ 281 እና 282 ላይ ኢትዮጵያዊም አማራም ነኝ ስለሚለውና የከተሜ አማራ ብሎ ስለሚገልጸው ወገን እንዲህ ይላል።  

“ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል የሚለው አዲስ የፖለቲካ ጥያቄ የመነጨው ኢትዮጵያዊያንን አንድ ከሚያደርግና እየጎለበተ ከመጣ የኢትዮጵያዊነት ርዕዮተ-ዓለም ነው። ይህ ጥያቄ የተነሳው እ.አ.አ በ1999 በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል እየተደርገ የነበረውን ጦርነት ተከትሎ ነው። … ኢትዮጵያ ልትጠይቅ የምትችለው ብቸኛ የባህር በር አሰብን ሲሆን አሰብ ደግሞ እ.አ.አ ከ1991 በኋላ በተባበሩት መንግሥታት ታዛቢነትና በኢትዮጵያ በጎ ፈቃድ የራሷን ሉዓላዊ አገር የመሰረተችው የኤርትራ ግዛት ነው። … ይህ [የባህር በር ጥያቄ] የማይረባ የፖለቲካ ጥያቄ ነው። በተለይ አሁን ባለው በበይነ መረብና በተስፋፋው ዓለም አቀፋዊ የአየር መስተንግዶ ዘመን ማንም አገር የባህር በር አያስፈልገውም። ስዊትዘርላድ፣ ኦስትሪያና የቼክ ሪፑብሊክ በምጣኔ ኃብትና በፖለቲካውም ሃያል የአውሮፓ አገራት መሆን የቻሉት ያለ ባህር በር ነው”6። 

እዚህ ጋ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ በጊዜው ከኤርትራ ጋር የነበረውን ጦርነት (ምንም እንኳን ትሕነግ እውነት ለኢትዮያና ለሕዝቧ ጥቅም ብሎ ባይሆንም) የኢትዮጵያ ሕዝብ ግልብጥ ብሎ የደገፈውና መስዋዕትነትም የከፈለው በታሪክ በአገሩ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ተደራድሮ የማያውቅ ኩሪ ሕዝብ በመሆኑ ነው። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ያህል የአገር ጉዳይ ሲነሳ ቀፎው እንደተነካ ንብ ተሞ የሚነሳ ሕዝብ መሆኑን ያሳየ አንድ ተሞክሮ ነው። ለማስታወስ ያክል ኢትዮጵያን በተመለከተ እ.አ.አ በ1991 በለንደን ከተማ ትሕነግ፣ ኦነግና የደርግ ባለሥልጣናት በተገኙበት ኢትዮጵያን ለትሕነግ አሳለፎ የሰጠ ስምምነትን ያደራደረው በአፍሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሃላፊ የነበረው አሜሪካዊው ሄርማን ኮህን በድርድሩ ላይ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት ያለባህር በር መቅረት አይገባትምና ኤርትራን ማሳመን ስለማያስቸግር አሰብን መጠየቅ ይቻላል ማለቱ ይታወቃል። ሆኖም ግን በወቅቱ ትሕነግን ወክሎ የቀረበው መለስ ዜናዊ ሃስቡን ውድቅ ያደረገው አሰብ የኤርትራ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ ናትና ይህን መጠየቅ የኤርትራን ሉዓላዊነት መጋፋት ነው በማለት እንደነበር ለሚያስታውስ ይህ ጸሐፊም ከላይ ያለው አባባል መለስ ያለውን እንዳለ የተቀበለ፣ የሚያምንበትና ኢትዮጵያን በተመለከተም ያለውን አቋም ያሳየ ነው። ስለዚህ አደጉ ተመነደጉ የሚባሉ የአውሮፓ አገራትን ከኢትዮጵያ ጋር በማነፃፀር አንደኛ የባህር በር ጥያቄ የማይረባ ነው የሚለውን አባባል ዝም ብሎ የሚቀበል ሊኖር ይችላል ነገር ግን ይህ አባባል የሳተው ሃቅ ኢትዮጵያና የተጠቀሱት አገራት ያሉበት ሁኔታ በእጅጉ የሚለያይ በመሆኑ ለአንዱ የሰራ ለሌላውም ይስራል የሚለውን ድፍን አባባል ተቀባይነት እንዲያጣ ያደርጋዋል። ይህም ማለት በኢትዮጵያና በተጠቀሱት አገራት መካከል ያለው ነባራዊ ሁኔታ በተለይ ያላቸው ምጣኔ ኃብታዊ አቅም፣ የቴክኖሎጂ ልቀት፣ የተማረ ሕዝብ ብዛት፣ የአማራር ብቃት በመሳሰሉት አንኳር አንኳር ጉዳዮች በእጅጉ የተለያዩ በመሆናቸው ለአንዱ የሰራ ለሌላውም ይሰራል ብሎ ለመደምደም የማያስችሉ ናቸው። 

ሁለተኛ ሲጀመር ከላይ የገለጻቸው የባህር በር የሌላቸው አገራት እንደ ኢትዮጵያ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደተባለው ሕዝባቸውን በማንነት ሸንሽነውና ይህ ይኔ መሬት ነው ያ ያንተ አይደለም በመባባል ብሎም ቋንቋዬን ደፍጥጠሃል፣ መሬቴን ቀምተሃል፣ ጡት ቆርጠሃል እየተባባሉ፣ እርስ በርስ እየተገዳደሉና በአገራቸው ላይ ሰላም አጥተውና ሕዝብ ወጥቶ መግባቱን ብርቅ አድርገው አይደለም የሚመሰገን ምጣኔ ኃብታዊና ፖለቲካው ውጤት ማስመዝገብ የቻሉት። አድሏዊ የጎሳ ፖለቲካ ሥርዓት በግድ መተከሉን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን የተለያየ ማንነታቸውን ይዘው በዜግነት ፖለቲካ እንደ አንድ አገር ዜጋ እራስቸውን ቆጥረው ለዕድገትም ለልማትም እንዳይጥሩ ሆነ ተብሎ የተሰራ ፀረ-ኢትዮጵያ ሴራ እንዳለ ይታወቃል። በመሆኑም ለልማት እጅግ በመሰረታዊነት ተፈላጊ የሆነ በሰላም ወጥቶ መግባትን የነፈገና በማንነትና በቋንቋ ክልል ፈጥሮ የኢትዮጵያ ሕዝብን በመለያየት ለተከታታይ አመታት ለንጹሃን መገደል ምክንያት የሆነ ሥርዓትን እየደገፉ ስለልማት ማውራት ወይም የባህር በር ጥያቄን በዚህ መልኩ ለመንቀፍ መጣር ምን ያህል እርስ በርሱ የሚጣረስ እንደሆነ እየተባባሰ የሄደው የኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት ቀውስና በከፋ የኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ያለው ሕዝብ በቂ ምስክር ናቸው።

ሦስተኛ አንድ አገር ለማደግና ለመልማት የሚያደርገው ጥረት ላይ ከሰላም መስፈን ባሻገር የባህር በር መኖር አለመኖር ምን ያህል ልዩነት እንዳለው በጥናት ያረጋገጡ ማለትም የባህር በር ያለውና የሌለው አገር ለማደግና ለመልማት በሚያደርገው ጥረት ላይ የባህር በር የሌለው አገር ምን ያህል እንደሚጎዳ በርካታ ጥናታዊ ትንታኔዎችን ያዘሉና ተቀባይነት ያገኙ ምሁራዊ ጽሁፎችን ማየት ተገቢ ግንዛቤ ያስጨብጣል። ስለዚህ ከዚህ ግንዛቤ በመነሳት ይህ የባህር በር ጥያቄን በተመለከተ አገርንና ሕብረተሰብን መለወጥ የሚችል ዕድገትንና ልማትን እውን ለማድረግ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያለ እጅግ ኋላ ቀርና በድህነትና መሃይምነት ተጠፍንጎ አቅሙ የተሽመደመደ አገርን በተሻለ ሁኔታ ላይ ካለና በአውሮፓ ውስጥ ከሚገኝ አገር ጋር ከላይ በተገለጸው መልኩ ማነፃጸር ትርጉመ-ቢስ የሚሆነው ከሃቅ ጋር የሚጣረስ በመሆኑ ነው። 

ይህ ፀሐፊ ኢትዮጵያዊነትን በሚያቀነቅን ወገን ላይ ያለው አመለካከት ምን ማለት እንደሆነ የሚያሳየው ደግሞ በገጽ 283 ላይ ሂትለር የጀርመን ብሔረተኝነትን ለፋሺዝም እሳቤ ተጠቅሞ ጀርመኖች ምርጥ ዘር/ሁሉንም የሚበልጥ ዘር መሆናቸውን ለማስረጽ የተጠቀመበትን ታሪካዊ ዳራ በማንሳት ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነትን የሚያቀነቅነው ወገንም ፋሺስታዊ መንገድን እየተከተለ ነው ያለው አባባል ነው። በእርግጥ እንደተጠቀሰው ሂትለር አገራዊ ብሔረተኝነትን ተጠቅሞ ውጤቱ አገርንና ሕዝብን የጎዳ ቢሆንም በብዙ አገራት ደግሞ ጠቃሚ የሆነ ውጤትንም እንዳስከተለ መረዳት ይገባል። አገራዊ ብሔረተኝነት በሌሎች አገራት ያለው ጠቃሚ ተሞክሮ እንዳለ ሆኖ ማለትም ሉዓላዊነታቻውን ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለአገራዊ ዕድገትና ልማት ሕዝብን በአንድነት ማሰለፍና ድህነትንና መሃይምነትን መርታት እንዳስቻለ ይታወቃል። 

በኢትዮጵያ ታሪክም ኢትዮጵያዊነት የሕዝብን አንድነት፣ ነፃነትና ክብር ብሎም የአገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ እንደረዳና የተለያዩ የቅኝ ገዢዎችን ወረራ ለመመከትና በድል ለመወጣት ማስቻሉ አገራዊ ብሔረተኝነት በአግባቡ ማለትም ለአምባገነን ገዢዎች ፍላጎት ሳይሆን ለሕዝብና ለአገር ጥቅም ማስጠበቂያነት ብሎም ለአገራዊ ዕድገትና ልማት ሕዝብን ለማነሳሳት ቢውል ጥቅሙ እጅግ የላቀ እንደሆነ ታሪክን ማገላበጥ በቂ መልስ ይሰጣል። በተቃራኒው ግን በተለያዩ አገራት የተሞከረው የጎሳ ፖለቲካ ምን ያህል ጥፋት እንዳስከተለ የሚታወቅ ሲሆን በኢትዮጵያ ከ1983 ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለአገራዊ ኃብት መውድም፣ ለሰላም እጦት፣ ለሰው ሕይወት መጥፋት፣ መፈናቀልና ለሥነ-ልቡና ቀውስ መዳረግ ምክንያት መሆኑን መካድ አይቻልም። በተጨማሪም ለምጣኔ ኃብታዊ ድቀት፣ ለፖለቲካዊ ቀውስ፣ ለወንጀሎች መበራከት፣ ለሙስናና ለአስተዳደራዊ ብልሹነት ምክንያት እንደሆነና ይህንንም ተከትሎ ምን ያህል የኑሮ ውድነት ሕዝቡን ለሰቆቃ ኑሮ እንደዳረገ የሚታወቀውን ሃቅ በመሸምጠጥና ሂትለርን በመጥቀስ ኢትዮጵያዊነትን በአገራዊ ብሔረተኝነት ሰበብ ፋሺስታዊ ብሎ መደምደም የሕዝብ አንድነት ፀር መሆንና የጎሳ ፖለቲካ አፍቃሪነትን ያሳበቀ ሆኗል። 

በተጨማሪ ይህ ጸሐፊ ምን ያህል የጎሳ ፖለቲካ አፍቃሪ ብቻ ሳይሆን በእሳቤው የታወረ እንደሆነ የሚመሰክረው ሌላው አባባሉ ደግሞ የሚከተለው ነው። በጽሁፉ ገጽ 282 ላይ እንዲህ ይላል። 

“በአፍሪካ አሁን ላይ ለሚታየው አገራዊ ብሄረተኝነት የአሮፓውያኑ ፍላጎትና እጅ አለበት። … አውሮፓውያኑ አሁን ያለውን የአገራት ድንበር በሚያካልሉበት ወቅት የተለያየ ማንነት ስላለው ሕዝብ ምንም ደንታ ስላልነበራቸው የተፈጠሩት አገራት የተለያየ ማንነት ያላቸው አፍሪካውያንን ያካታቱ ነበሩ። …የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም የተለያየ ማንነት ላለው ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን መብት ከመስጠት ይልቅ የቅኝ ገዢዎቹን አከላለል የተቀበለ ሆኗል”7። 

ከዚህ የጸሐፊው አባባል መረዳት የሚቻለው አፍሪካውያን አሁን ካላቸው 54 አገራት በላይ በማንነት ተሸንሽነውና አቅመ-ቢስ ሆነው መፈጠራቸው የሚፈለግ መሆኑን ነው። ይህን የመሰለ አፍሪካውያን በጎሳ ማንነታቸው መሰረት ደካማና አቅመ-ቢስ የሆኑ ሉዓላዊ አገራትን ስለመፍጠር የተያዘው እሳቤ ተቀባይነት የማያገኘው ባለው አድሏዊ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ምክንያት ነው። ይህም የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎቹ ኃብታም አገራት የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ ምን ያህል የአፍሪካ አገራት በድህነትና በኋላ ቀርነት ሥር እንዲቆዩ እንደሚፈለጉ ከሚያስረዳው የጥገኝነት ፅንሰ ሃሳብ በመነሳት ነው። ይህ ፅንሰ ሃሳብ የሚያብራራው የቀድሞ ቅኝ ገዢዎቹ ወይም የአሁኑ እጅ አዙር ቅኝ ገዢዎችና በለፀጋ የሚባሉት አገራት የተለያዩ ማለትም ግልጽና ድብቅ አሰራሮችን በመጠቀም ኋላ ቀርና ድሃ አገራት የማዕድንና የእርሻ ውጤቶችን ብቻ እንዲያመርቱና በርካሽ ለበለጸጉ አገራት እንዲሸጡ ነገር ግን የቴክኖሎጂ ዕውቀት የሚሹና ውድ የፋብሪካና የእንዱስትሪ ምርቶችን ድሃ አገራቱ ማምረት እንዳይችሉ ነገር ግን ከነዚያው ባለፀጋ አገራት እየገዙ የነሱ ጥገኛ ሆነው እንዲኖሩ እንደሚያስገድዷቸው ነው። 

በመሆኑም ድሃ አገራት የሚያመርቷቸው የማዕድንና የእርሻ ምርቶች ዋጋቸው በጣም እርካሽ በመሆኑ ባለፀጋ አገራቱ ደግሞ እነዚህን እርካሽ ምርቶች ከድሃ አገራት ገዝተው ያላቸውን የቴክኖሎጂ ልቀትና ዕውቀት ተጠቅመው ወደ ፋብሪካና እንዱስትሪ ምርትነት ለውጠው እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ መልሰው ለድሃ አገራቱ በመሸጥ የድሃ አገራቱ ገቢና ወጪ እንዲዛነፍና ምንጊዜን በዕዳ ተዘፍቀው እንዲኖሩ የሚያስገድድ አሰራር የሚከተሉ ናቸው። ይህ እንዲሆን ደግሞ ገቢና ወጪያቸው እየተዛነፈ ለሚቸገሩ ድሃ አገርት የገንዘብ ብድር የሚሰጡ እንደ ዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ ያሉ የዓለም የገንዘብ ተቋማትን ወጪ የሚሸፍኑት ጥቂት የበለፀጋ አገራት የተቋማቱ ፖሊሲና አሰራር ላይ ተፅዕኖ እንዲፈጥሩና በድሃ አገራት ኪሳራ እነሱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቱ በዚህ መልኩ የተዋቀረ ነው። ይህንን አሰራር ተከሎ የተለያዩ ድሃ አገራት ብድር በሚጠይቁበት ወቅት የዓለም የገንዘብ ተቋማቱ አንድ ወጥ የሆነ አሰራር በመከተል ድሃ አገራቱ ለበለፀጉ አገራት አገር ዘለል አምራች ድርጅቶች በራቸውን በመክፈት በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ አምራች ወይም አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶቻቸውን ወደ ግል ባለቤትነት እንዲያዛውሩ፣ የመገበያያ ገንዛባቸውን ዋጋ እንዲያረክሱ፣ ሕግና ቁጥጥርን እንዲያላሉ የመሳሰሉ ግዴታዎችን እንዲተገብሩ ስለሚገደዱ በነሱ ኪሳራ ባለፀጋ አገራቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ። 

እንግዲህ ይህንን የመሰለ አሰራር ተከትሎ ነው አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ነፃ ከወጡ እ.አ.አ ከ1960ዎቹ አንስቶ እስካሁን ድረስ አገራቱ ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝና ከዕዳ መላቀቅ ባለመቻላቸው አብዛኛው ሕዝባቸው በድህነትና መሃይምነት ተጠፍንጎና በበለፀጋ አገራት በሚደገፉ አምባገነን ገዢዎቹ መዳፍ ሥር ወድቆ እየማቀቀ ያለው። እንግዲህ የአፍሪካ አገራት ለብዙ አሥርት አመታት ያህል ጊዜ አሁን ባለው ሃምሳ አራት አገራት ይዞታ እንኳ የሚደርስባቸውን ተጽዕኖ መቋቋም እንደተቸገሩና ከጊዜ ወደ ጊዜ ለባሰ ችግር እንደተዳረጉ መሬት ላይ ያለው ሃቅ እየመሰከረ በመሆኑ ጭራሽ በማንነት መበጣጠቃቸውና የበለጠ አቅመ-ቢስ ሆኖ መገኘት ለአስከፊ ባርነት የሚዳርጋቸው እንጂ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ለመገንዘብ የግድ ዲግሪ መጫን አይፈልግም። ስለዚህ የአፍሪካ አገራት ድንበራቸውን አፍርሰው እንደ አንድ አገር መቆምና በአንድ ፖሊሲ በመመራት እራስን መርዳት የሚያስችል አቅም መፍጠር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ግንዛቤ መያዙና ለትግበራውም መጣር የህልውና ጉዳይ እየሆነ መጥቷል። ቀደም ብለው ይህንን የተገነዘቡ የአፍሪካ መሪዎች ምስጋና ይግባቸውና ከ1950ዎቹ መጨረሻና ከ1960ዎቹ አንስቶ የአፍሪካ አገራት አንድ እንዲሆኑ አበክረው መጣራቸው ሰሚ ባያገኝም አሁን አሁን ግን የአፍሪካውያን የብዙ አመታት ሰቆቃ ለምን እንደሆነ በቅጡ የተረዱ አፍሪካውያን አፍሪካ እንደ አንድ አገር ሆና መቆም እንዳለባት በስፋት እየመከሩ ይገኛሉ። አፍሪካ በተፈጥሮ ኃብት የበለፀገች፣ በቂ የሚታረስ መሬትና ውሃ ያላት፣ በተፈጥሮ የተለያዩ ውድ ማዕድናት በከርሰ ምድሯ ያካበተች፣ ጥሩ መሪ ብታገኝ አገር መለወጥ የሚችል ወጣት ሕዝብ ያላት መሆኗና ከጥገኝነት ፅንሰ ሃሳብ ትንተና አንፃር እየደረሰባት ያለው መከራ የአንድነቱን ጥያቄ የበለጠ የሚፈለግ አድርጎታል። ምክንያቱም አፍሪካውያን ነፃ ከወጡ ጀምሮ አድሏዊ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት እያደረሰባቸው ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ በመመከት ከድህነትና መሃይምነት መላቀቅ ያልቻሉት አቅመ-ቢስ በመሆናቸው ስለሆነ ከዚህ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አንድነትና አቅምን አጎልብቶ መገኘት እንጂ ጭራሽ መበጣጠቅ መፍትሔ ሳይሆን እራስን ለቀንበር ማዘጋጀት በመሆኑ በምንም አመንክዮ አሳማኝ መሆን አይችልም። 

ስለዚህ የአፍሪካ ሕዝብ አሁን እየደረሰበት ያለው መከራና ስቃይ በመሰረቱ እጅግ በጣም ጥልቅ በሆነ ድህነትና መሃይምነት ተጠፍንጎ የተያዘ በመሆኑና ይህም ሁኔታ እንዳይለወጥ የቅኝ ገዢዎቹ ፍላጎት እንደሆነ ለብዙ አመታት ሲከተሉ የኖሩት ፖሊሲ ለድሃ አገራት ጎጂ እንደሆነ በግልጽ አሳይቷል። የአፍሪካ ሕዝብ ያለውን የኋላ ቀርነት፣ የድህነትና የመሃይምነት ችግሮችን 54 አገራት ሆኖ እንኳን መለወጥ አለማቻሉ እየታወቀ የበለጠ በማንነት አንሶና ተበጣጥቆ አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሔ መጠበቅ ድንጋይን ወደላይ ወርውሮ አየር ላይ እንዲቀር መጠበቅ ስለሚሆን ያለው ብቸኛ አማራጭ አፍሪካ እንደ አንድ አገር አንድ የመገበያያ ገንዘብ፣ አንድ የውጭ ፖሊሲ፣ አንድ የመከላከያ ሠራዊት የመሳሰሉት እንዲኖራት ማስቻል ነው። ይህም ሲሆን ነው የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎችን ባለፀጋ አገራት ተፅዕኖ መቋቋም የሚቻለው። እንደሚታወቀው አፍሪካ ተፈጥሮ የለገሳት የተለያዩና ባለፀጋ አገራቱ እጅግ በጣም የሚፈልጓቸውና ካለነሱ መኖር የማይችሉባቸው የማዕድን ኃብት አላት። በዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ብቻ ከ$30 ትሪልየን ዶላር በላይ የሚገመት የማዕድን ክምችት እንዳለ ይታወቃል። 

ስለዚህ እስካሁን እንዳለው ሳይሆን በተገላቢጦሽ አንድ ሆና የቆመቸው አፍሪካ ለምታካሂደው ድርድርም ሆነ የንግድ ግብይት በመላ አሁጉሩ ያለ እምቅ የማዕድን ኃብትን እንደ አቅም በመውሰድ እነዚህን ማዕድናት ለእንዱስትሪና ፋብሪካ ምርቶቻቸው በእጅጉ የሚፈልጉ የቅኝ አዙር ገዢዎች ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር የምትፈልገውን ጥቅም ማግኘት ስለምትችል ከዚህ በፊት የሚደርስባትን የተለያዩ ጎጂና ጥገኛ ያደረጓትን የባለፀጋ አገራት ተፅዕኖ እምቢ ለማለት አቅም ይኖራታል። እንግዲህ ከዚህ ክርክር በመነሳት የተለያየ ማንነት ያለው ሕዝብ ያላቸው አገራት የተለያየ ማንነታቸውን ይዘው እንድ አንድ አገር ዜጋ ደግሞ ተሰባስበውና በአንድነት በመቆም ነው ያለባቸውን ድህነትና መሃይምነት መገላገል የሚችሉት እንጂ ኃይልና አቅምን በሚስልብ፣ ደካማ በሚያደርግና ለጥቃት በሚያጋለጥ ማንነት ብቻ በመቆም አይደለም የሚባለው። ይህንን ደግሞ አፍሪካውያን እ.አ.አ ከ1950ዎቹ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ምን እንደደረሰባቸው ግልጽ ያደረገው ተሞክሯቸው ያረጋገጠው ሀቅ ትምህርት ሰጪ በመሆኑ ነው የአፍርካ አገራት አንድነት የበለጠ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደረገው። 

በዚህ ሁኔታ የአፍሪካ አገራት ጭራሽ ከነበሩበት 54 አገራት የበለጠ በማነስ፣ አቅመ ደካማና ለጥቃት ተጋላጭ በሚያደርጋቸው በጎሳ ማንነት ተበጣጥቀው አገራት መሆን በረከት ሳይሆን የበለጠ መቅሰፍት ሊያስከትል እንደሚችል የአንዳንድ ከነበሩበት አገር ተገንጥለው ‘ነፃ የወጡ’ አገራት ተሞክሮ ጥርት አድርጎ የመሰከረው ሃቅ ነው። ምክንያቱም እንደ ጸሐፊው ፖስዋንግ ከሆነ አፍሪካ በማንነት መስፈርት ተበጣጥቃ አገራትን ትፍጠር ከተባለ እንደሚታወቀው አፍሪካ ቢያንስ ቢያንስ ከሦስት ሺ በላይ በጎሳ መስፈርት የሚመደብ ሕዝብ ያላት በመሆኑ ሦስት ሺ አቅመ-ቢስና ደካማ አገራት በየራሳቸው እንዴት የጠንካራና የበለፀጋ አገራትን ተዕዕኖ መቋቋም፣ ከድህነትና መሃይምነት መላቀቅና ሕዝብን ከሰቆቃ ኑሮ መገላገል እንደሚችሉ ማሰብ ጉም እንደመዝገን ስለሚቆጠር ነው። ስለዚህ የሚፈለገው ነገር ሕዝብ በማንነት ታውቆና ሉዓላዊ አገርም መስርቶ ብሎም በዚህ ተኩራርቶ ነገር ግን ለዕድገትና ልማት ጠንቅ ለሆነ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ሰለባ ሆኖ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በድህነትና በመሃይምነት ተጠፍንጎ መኖር ወይስ በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ያለው ይኸው ሕዝብ የሚደርስበትን ተፅዕኖ ተቋቁሞ የአንድነት እምቅ ኃይልን ተጠቅሞ ከድህነትና መሃይምነት እንዲገላገልና የማንነቱን መገለጫዎችም አስጠብቆ እንዲኖር ማስቻል ነው?  

እሩቅ ሳይኬድ ከኢትዮጵያና ከሱዳን የተገነጠሉትን የኤርትራንና የደቡብ ሱዳንን ሕዝብ ሁኔታ ማጤን ብልህነት ይሆናል። ለሚያስታውስ ኤርትራውያን የአፍሪካ ሲንጋፖር እንሆናለን ብለው ነበር ደቡብ ሱዳኖችም የነዳጅ ዘይት ስላለን ከሱዳን ጋር ከነበረን የተሻለ ኑሮ መኖር እንችላለን ብለው ነበር። ነገር ግን ሁሉም እንደሚወራው ቀላል ያልሆነው ከምንም ሳይሆን ባለው አድሏዊ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ማንም አቅመ ደካማ አገር እንደሚፈልገው በማደግና በመልማት ሕዝብን ከድህነትና መሃይምነት ለመገላገል የሚቸገር መሆኑን ነው። አላየሁም አልሰማሁም ካልተባለ በስተቀር። ስለዚህ በአንድ ሕበረተሰብ ውስጥ ያለ ችግርንና በደልን ለመገላገል ሲባል እራስን በማንነት አውርዶ መገኘትና ሲከፋም አገር ለመሆን ማሰብ የሚጠበቅ በረከትን ሳይሆን የሚያስከትለው ዳፋ እጅግ በጣም የከፋ የመሆን ዕድሉ እጅግ በጣም ሰፊ በመሆኑ ለሕዝብ የሚታሰብ ከሆነ በረጋ መንፈስ የተለያዩ አማራጮችን ማየትና መፈተሽ ብልህነት ይሆናል። ምክንያቱም በተለይ በጎሳ ፖለቲካ መስፈርትና እሳቤ ላይ በመንተራስ የሚወሰድ ስሜታዊ ውሳኔ ዞሮ ዞር ፍትሃዊነት የሚጎድለው፣ ምክንያታዊነትን የማይቀበል፣ መርህ የለሽ ለአገራዊ ዕድገትና ልማትም እንቅፋት የመሆን ዕድሉ የሰፋ እንጂ የተሻለ ሁኔታን እንደማያመጣ ከኢትዮጵያም ከሌሎች አገራት ተሞክሮም መረዳት በመቻሉ ነው። 

እንግዲህ ወደ አንሙት አባባል ስንመለስ “የትናንት የሽንፈት ውርሱን ይዞ መጥቶ በአማራ ትግል ውስጥ አምጥቶ ተመልሶ እንወቅላችሁ የሚለው አካሄድ” የሚለው አባባል ያው ከላይ እንዳለው ኢትዮጵያነትን እንደከሸፈ የወሰደ በመሆኑ በአማራው ብሔረተኛ እሳቤ ኢትዮጵያዊነት ስለማያዋጣ በአማራ ትግል ውስጥ እንደማይፈለግ ያረጋገጠ ነው። አንሙት እዚህ ጋ እና ከዚህ

በፊት ከላይ ካላቸው አባባሎች በመነሳት መረዳት የሚቻለው ኢትዮጵያዊነት የከሸፈ ስለሆነ ለአማራ ሕዝብ የሚያዋጣው የዜግነትና የአንድነት ፖለቲካ ሳይሆን በተፈጥሮው አድሏዊ፣ ከፋፋይና በቀለኛ እሳቤን በሚሰብክ የጎሳ ፖለቲካ መሰረት ማንነትን ማስቀደም እንደሆነ ነው። ለዚህም ነው አንሙት ከላይ እንዳለው “የኢትዮጵያ አንድነት ለኔ ከአማራ ህልውና በታች ነው” በሚለው እሳቤ መሰረት አማራነቱን ከኢትዮጵያዊነት በላይ አድርጎ የሚቀበል አማራ በሚያካሂደው ትግል ውስጥ ኢትዮጵያዊም አማራም ነኝ የሚለውም ሆነ ሌላው ምንም ሚና ሊኖረው ስለማይገባ “ዞር በል” ከፈለግህ “በራስህ ሜዳ ሄደህ ተጫወት” እያለ ያለው። በዚህ የአማራ ብሔረተኝነት (የአርሶ አደር አማራ ብሔረተኛ) እሳቤ የዜግነት ፖለቲካን ወይም ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅን “ዞር በል” ብቻ ሳይሆን እያሳደደ መግደሉን ለሚያስታውስ ይህ የ“ዞር በል” አባባል ምን ያህል ጥላቻ የበከለው እንደሆነ መረዳት ይቻላል። እንግዲህ ይህ እንደ አቋም በመያዙ ነው ኢትዮጵያ የሚለውን የፋኖ ታጋይ እያሳደዱ መግደል ስራዬ ተብሎ የተያዘው ብሎም ኢትዮጵያዊነትን በመጠየፍ የትሕነግንና የኦነግን መንገድ በመከተል ከእነዚህ ፀረ-ኢትዮጵያ፣ ፀረ-አንድነትና ፀረ-ሕዝብ ኃይሎች ጋር ደግሞ ሕብረት ለመፍጠር ስምምነት ላይ መድረስ የተቻለው። ታዲያ ከዚህ የበለጠ ኢትዮጵያን መጠየፍ አለ እንዴ? ከዚህ የበለጠ ፀረ-ኢትዮጵያዊነትና ፀረ-አንድነት አለ እንዴ? ከዚህ የበለጠ ለኢትዮጵያና ለሕዝብ ስጋት አለ እንዴ? ተብሎ ቢጠየቅ የሚገርመው ማን ይሆን? 

በተጨማሪም ይህ የአማራ ብሔረተኛ “እንደ ትግራይ ብሔረተኛ እንደ ኦሮሞ ብሔረተኛ ሊሆን ስለሆነ ይዞት የመጣውን ትግል በዛ መንገድ ይዞ የሚቀጥል ከሆነ ኢትዮጵያን ያፈርሳታል” ብሎ የሚያስበውን “ዞር በል” ብሎም “በራስህ ሜዳ ሄደህ ተጫወት” ማለትስ የሚናገረው ስለአገርና ሕዝብ መጨነቅን ወይስ አገር ቢፈርስም አለመጨነቅን? ይህንን ማለትስ ከሰላሳ አመታት በላይ ለሆነ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብን ለሰቆቃ ኑሮ የዳረገ ሥርዓት በሕገ-ሕዝብ ላይ መሰረት ባደረገ ፍትሃዊ ሥርዓት እንዲተካ የሚደረግ ጥረትን የሚያኮላሽ አይደለምን? ምክንያቱም ይህ ከኢትዮጵያና ከሕዝቧ ጋር ጠብ የለንም የሚል ነገር ግን ከኢትዮጵያዊነቱ ይልቅ አማራነቱን የሚያስቀድም የአማራ ብሔረተኛ አልፎ ተርፎ ከትሕነግና ከኦነግ ጋር ማለትም የኢትዮጵያ ስም ሲጠራ ከሚያማቸውና ከኢትዮጵያ ነፃ የመውጣትን አቋም አጥብቀው ከያዙ ጋር አብሮና ካንተ በፊት እኔ በማለት እየሄደበት ያለው መንገድ በምንም አመንክዮ ስለብርቱና ጠንካራ ኢትዮጵያ እንዲጨነቅ ሊያደርገው አይችልም። 

በመሆኑም በአማራ ብሔረተኛ ነኝ ባዩ በተያዘ የጎሳ ፖለቲካ እሳቤ ብሎም የትሕነግንና የኦነግን አቋም ምንነት ከግምት ውስጥ በመክተት በአማራ ብሔረተኝነት አካሄድም ሆነ ይህንን ተከትሎ ከተፈጠረው ትብብር ለኢትዮጵያውያን መፍትሔ መጠበቅ ማለት ከዕባብ ዕንቁላል እርግብ መጠበቅ ነው የሚሆነው። በተጨማሪም ኢትዮጵያዊነትን “ዞር በል” በማለት ከፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር መጎዳኘት ለአመታት ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ጠፍንጎ ከያዘ የጎሳ ፖለቲካ ሥርዓት የሚገላግልና ፍትሃዊና ሕዝባዊ ሥርዓት ለማስፈን የሚረዳ ሳይሆን ያለውን የጥፋት አዙሪት የሚያስቀጥል ሲከፋም የአገርን ሉዓላዊነት የሚንድ ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ እንደሚሆን ለመረዳት የግድ ጠቢብ መሆን አይፈልግም። ስለዚህ ይህ የአማራ ብሔረተኛ ነኝ ባይ እየሄደበት ያለው መንገድ ፍትሃዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ደንቃራ ከመሆን አልፎ ለአገርና ሕዝብ የሚያስከትለው ጦስ ቀላል ስለማይሆን ኢትዮጵያንና ወገኔን የሚል ሁሉ ወገቡን ጠበቅ ማድረግ ይጠበቅበታል።  

ዋቢ ማጣቀሻ 

1 Anchor Media የፋኖ ትግልና ”ኢትዮጵያኒስት” – ጋዜጠኛ አንሙት አብረሃም – ክፍል 2 የተለቀቀው ሰኔ 9 2017  https://www.youtube.com/watch?v=6a3DBDxrMB4&t=80s 
2 Pausewang, S. (2005). THE TWO-FACED AMHARA IDENTITY. Scrinium, 1(1), 273-286. 3 ዝኒ ክማሁ 
4 ዝኒ ከማሁ 
5 ዝኒ ከማሁ 
6 ዝኒ ከማሁ 
7 ዝኒ ከማሁ

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News