Homeነፃ አስተያየትተጠየቅ ክርስቶስ! ለይሁዳ ሞትን ለቄሳር ምሕረትን ለምን?

ተጠየቅ ክርስቶስ! ለይሁዳ ሞትን ለቄሳር ምሕረትን ለምን?

Advertise Here
Advertise here
ክህደት

ኢያሱ ኤፍሬም ገ/ሃና
ለንደን ዮናይትድ ኪንግደም
መስከረም ፳፰, ፳፻፲፱ ቅፅ  005

የኃይማኖት ልሂቅም፣ አስተማሪም አይደለሁም፤ ነገር ግን መፅሐፍ ቅዱስን ለብዙ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ ልቦናዊ ጥያቄዎች መልስ እና የእምነት ምንጭ ከመሆኑም በላይ የኑሮ ኮምፓስ ነው ብል ብዙዎቻችሁ ትስማማላችሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡ መፅሐፍ ቅዱስ የእውቀት፣ የጥበብ ምንጭ እና መሠረት ነው። ጠቢቡ ሰለሞን እንዳለው ከፀሃይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡ ሁሉም ነገር በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተካቷል። ቁም ነገሩ ያለውን፣ የነበረውን፣ አልፎም ወደፊት የሚሆነውን፣ መርምሮና አጥንቶ ማወቁ ላይ ነው። ይህን ካልኩኝ በኋላ ዛሬ ወደ ተነሳሁበት ፅሁፍ ላቅና፤ ተከተሉኝማ፡፡ 

የዛሬው መልዕክቴ መሠረት ያደረገው በሁለት የመፅሐፍ ቅዱስ ክሰትቶች ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው የማቴዎስ ወንጌል፦ 26፡24 “የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፥ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” የሚለው እና በሁለተኛው በሉቃስ ወንጌል 23:34 የተፃፈው ነው። እንዲህም ይላል፦ “34 ኢየሱስም። አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ።” በሁለቱ የመፅሐፍ ቅዱስ ክስተቶች መካከል ጥልቅ ትምህርት እና ትርጉም ያለው ነገር እናገኛለን። ወደ ዝርዝሩ ከመግባቴ በፊት በጥቅሉ ይህን ልበል፡፡ ክርስቶስ ለሰቀሉት ምህረትን፣ ለካደው ሞትን ነው ያዘዘው፡፡ በነገራችን ላይ በመፅሐፍ ቅዱስ ብዙ የክህደት ታሪኮች ተመዝግበዋል፡ ለምሳሌ ቃየል ወንድሙን አቤልን ክዶታል።  

ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ሆኖ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያቁም እና ይቅር በላቸው” ሲል ይቅርታ የለመነው በእርሱ ላይ የሞትን ፍርድ ፈርደው፣ ገርፈው፣ በመስቀል ላይ የሰቀሉትን የዘመኑን የሮማን ባላስልጣናት ነበር፡፡ ከዛ በፊት በመጨረሻው የእራት ቀን ላይ  እሱን ሰለሚከዳው ሰው የተናገርው ነገር አለ እሱም በማቴዎስ ወንጌል የተገለፀው ነው፡፡ ኃይለ ቃሉ እንዲህ ይላል፦ “ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” ያም ማለት ቢሞት ይሻለዋል ማለት ነው፡፡  

እዚህ ላይ ክህደት ከመግደል ወይም ከመስቀል በላይ የከፋ ድርጊት መሆኑን ጌታ በዚህ መልኩ አስተምሯል፡፡ በጥቅሉ ስንመለከተው ግድያ የሚመነጨው ከጠላት፣ ከአንተ አላማ እና ፍላጎት ጋር ከሚቃረን ሰው ወይም አካል ነው። በተወሰነም ደረጃ በሟች እና በገዳይ መካከል የተመሰረተ ሕብረትም፣ አንድነትም፣ ቃል ኪዳንም የለም።  ጌታ በእሱ እና በሮማ ገዥዎች መካክለ ያለውን ልዩነት ሲናገር፣ ማርቆስ 12:17፦ “ኢየሱስም፣ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” ብሏል። እና እነሱ ቢሰቅሉት ቢያሰቅሉት ድርጊታቸው አንድም ከልዩነት፣ ሁለትም ካለማወቅ የመንጨ በመሆኑ ነው ጌታ በመስቀል ላይ ሆኖ አብን ይቅር እንዲላቸው የለመነው። 

በሌላ በኩል ክህደት የሚመነጨው ካመንከው፣ የእኔ ካልከው፣ ከአንተ ጋር ከተማማለ፣ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን ካለው፣ አንተም ለሱ፣ እሱም ለአንተ እስከ ህይወት ፍፃሜ ሊቆም ከሚችል/ከምትችል ሰው፣ ከባልደረባህ ወይም ከባልጀራህ ነው። ጠላት ሊክድህ አይችልም። በስነ-ቃሉም ጠላቴ ከዳኝ አይባልም፡፡ በሌላ በኩል ባልንጀራዬ፣ አጋሬ፣ ወዳጄ፣ ከዳኝ ነው የሚባለው። የሚከዳህ አጋር፣ ባልደረባና ጓዳኛህ ነው። ይህን በተመለከተ ከሙሴ ጀምሮ ከተፃፈው በአሰርቱ ትዕዛዛት ውስጥ ስለ ታማኝነት እንዲህ ይላል፦ “ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ።” የዚህን ቃል ትርጓሜ ስንመረምረው፣ ሰው ራሱን እንደማይከዳ ሁሉ ባልጀራውንም አይከዳም። ራስህን ካልከዳህ ባልጀራህንም አትክደውም፡፡ በጌታ ዘንድ ክህደት ከመግደል  (ከመስቀል) በላይ ኃጢያት እና አፀያፊ ተግባር ነው፡፡ ለዚህም ነው ጌታ ለይሁዳ፦ “የሚከዳኝ እሱ ባልተወለደ ይሻለው ነበር” ያለው፡፡ ያ ማለት የከዳውን ይሁዳ ከሰቀሉት ከሮማኖች በላይ አዝኖበታል፣ አውግዞታል፡፡ ከዛም አልፎ ሽል ሆኖ በጠፋ፣ ባይወለድ ይሻለው ነበር ይላል፡፡ ጌታ የክህደትን አስከፊነት የገለፀበት መንገድ፣ ባይረገዝ፣ ፅንስ ሆኖ ባያደግ፣ ባይወለድ ይሻለው ነበር በሚሉ መሪር ቃላት ነው። ምክንያቱም ይሁዳ ከደቀ መዛሙርቱ መሃል አንዱ ነው። አምኖ እንዲከተለው ከመረጣቸው ሰዎች መካከል አንዱ ብቻ ሳይሆን የጉባኤው ገንዝብ ያዥም ነበር። ይህ ምን ያሳየናል? ጌታ ይሁዳን ምን ያህል አምኖት እንደነበር ነው። ነገር ግን ይሁዳ ከክህደቱም በፊት እምነት አጉዳይ እንደነበር የዮሐንስ ወንጌል 12፡ 4-6 ይነግረናል፦ “4 ነገር ግን ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አሳልፎ ሊሰጠው ያለው የስምዖን ልጅ የአስቆሮቱ ይሁዳ። 5 ይህ ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ለድሆች ያልተሰጠ ስለ ምን ነው? አለ። 6 ይህንም የተናገረ ሌባ ስለ ነበረ ነው እንጂ ለድሆች ተገድዶላቸው አይደለም፤ ከረጢትም ይዞ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ስለነበረ ነው።”  ምንም እንኳ ይሁዳ ባደረገው ተፀፅቶ ጌታን የሸጠበትን ዲናር ቢመልስም ምህረትን አላገኘም። እንዲያውም በመለሰው ዲናር የተገዛው መሬት የደም መሬት ወይም አኬል ዳማ ተብሎ ለዘመናት ይታወሳል። ከመፅሐፍ ቅዱሱ ወጣ ብዬ ክሕደት በማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ሕይወት ምን እንደሚመስል እና ሊያስከትለው ስለሚችለው ጉዳት ትንሽ ልበል፡፡ 

የክሕደት ምክንያቱ እና ምንጩ ምንም ይሁን ምን ክሕደት ከፍተኛ የስነ ልቦና ቀውስ መገለጫው ስለመሆኑ የሚከተለው ፅሁፍ ይገልፅልናል፦ Betrayal is the sense of being harmed by the intentional actions or omissions of a trusted person. The most common forms of betrayal are harmful disclosures of confidential information, disloyalty, infidelity, dishonesty. They can be traumatic and cause considerable distress. The effects of betrayal include shock, loss and grief, morbid pre-occupation, damaged self-esteem, self-doubting, anger. Not infrequently they produce life-altering changes. Rachman S. Betrayal: a psychological analysis. Behav Res Ther. 2010 Apr;48(4):304-11፡፡ ከላይ ያለው ጽሑፍ ትርጓሜው እንደሚከተለው ይነበባል።  ክህደት ማለት አንድ ሰው በሚያምነው ግለሰብ፣ ሆን ተብሎ በተፈጸመ ድርጊት፣ ወይም ሆን ተብሎ በተተወ ተግባር ምክንያት ጉዳት ሲደርስበት የሚሰማው ስሜት ነው። በጣም የተለመዱት የክህደት ዓይነቶች ምስጢራዊ መረጃን ለጉዳት በሚዳርግ መልኩ ማጋለጥ፣ ታማኝነትን ማጉደል፣ የትዳር ወይም የፍቅር አጋርን አለመጠበቅ (ክህደት) እና ሐቀኝነትን ማጣት ናቸው። እነዚህ ድርጊቶች ከፍተኛ የስነ-ልቦና ጉዳት እና ጭንቀት ሊያስከትሉ ይችላሉ። ከክህደት ውጤቶች መካከል ድንጋጤ፣ የኪሳራ እና የሐዘን ስሜት፣ ጉዳዩን ያለማቋረጥ እያሰቡ መቸገር፣ በራስ የመተማመን መሸርሸር፣ በራስ ላይ ጥርጣሬ ማሳደር እና ቁጣ ይገኙበታል። ብዙውን ጊዜም እነዚህ ሁኔታዎች የአንድን ሰው ሕይወት የሚቀይሩ ለውጦችን ያስከትላሉ።

ክሕደት የማሕበራዊ ክስተት ነው፡፡ በሕይወት ዘመኑ ያልተካዳ ወይ ያልከዳ (በማወቅም ሆነ ባለማወቅ) ሰው አይኖርም ብሎ ማስብ ከባድ ነው። መካድ ካለ ከጂ አለ ማለት ነው፡፡ እኔ ክጄ ወይም ተክጄ አላውቅም የሚል ካለ እጁን ያውጣ፡፡ የፅሁፌ አላማ ስለ ማህበራዊ መካካድ ለመተንተን እና ለማስተማር ስላልሆነ በማሕበራዊ ክህደት ላይ የማደረገውን ትንታኔ እዚህ ላይ ልግታ፡፡   ይልቅስ አገራችንን ለዘመናት ያመሳት እና ለእዚህም መከራ የዳረጋት የፖለቲካ ክህደት ላይ ላተኩር። ያ ማለት ግን ለዘመናት የተከሰተውን የፖለቲካ ክህደት ዘርዝሬ አወጋለሁ ማለት አይደለም፡፡ የፅሁፌ አላማ ዛሬ በአማራ የሕልውና ትግል ውስጥ የተከሰተው ፖለቲካዊ ክህደት በትንሹ ስለሚያመጣው መዝዝ ለመጠቆም ነው። ከዚያ በፊት አንዳንድ በአገራችን ስለተከሰቱ ፖለቲካዊ ክህደቶች ትንሽ ልበል፡፡ ሩቅ ሳንሄድ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ የኢትዮጵያ መኳንት አገራቸውን ክደው ለጣሊያን አድረዋል። ከነሱም ውስጥ ደጃዝማች ኃ/ሥላሴ ጉግሳ፣ የንጉሱ አማች፣ የጎጃሙ ራስ ኃይሉ ተ/ሐይማኖት፣ የጅማው አባ ጅፋር ልጅ አባ ጆቢር፣ ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ብዙ ከመጓዜ በፊት ፖለቲካዊ ክህደት ምን ማለት ነው? እንዴት ይተረጎማል? Political betrayal is the deliberate or perceived deliberate violation by a political actor, party, government, institution or political movement of important and mutually understood expectations, commitments or obligations arising from a relationship of political trust, particularly where the violation is perceived to disregard the interests, rights, security, values or legitimate expectations of those who entrusted it with political authority, representation or support, and thereby causes or has the potential to cause significant harm or loss of trust. ( Source ChatGPT); Schuck, J., Greifeneder, R., & Lalot, F. (2026). Generalized loss of trust following political betrayal: Cross-country evidence in the context of elections. Political Psychology and Ohoku Wisdom: POLITICAL BETRAYAL AND IT’S CONSEQUENCE: አቻ ትርጉሙም፦ የፖለቲካ ክህደት ማለት፣ በፖለቲካዊ ተዋናይ፣ በፓርቲ፣ በመንግሥት፣ በተቋም ወይም በፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሆን ተብሎ ወይም ሆን ተብሎ እንደተፈጸመ የሚታሰብ፣ ከፖለቲካዊ እምነትና መተማመን ግንኙነት የሚመነጩ አስፈላጊና በጋራ የተገነዘቡ ተስፋዎችን፣ ቃል ኪዳኖችን ወይም ግዴታዎችን መጣስ ነው። በተለይም ይህ ጥሰት የፖለቲካ ሥልጣንን፣ ውክልናን ወይም ድጋፍን በአደራ ለሰጡት ሰዎች ጥቅም፣ መብት፣ ደኅንነት፣ እሴቶች ወይም ሕጋዊ ተስፋዎች ችላ እንደሚል በሚታሰብበት ጊዜ፣ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ወይም ኪሳራ ያስከትላል ወይም የመተማመን እጥረት እንዲፈጠር ከፍተኛ አቅም ይኖረዋል። 

በአገራችን የፖለቲካና የአገር ክህደት እንደ ጀግነትም እየተቆጠረ ከሃዲዎች ሲሾሙና ሲሸለሙ አስተውለናል። ባሕልም ያደረግነው  ይመስላል፡፡ ንጉሱ ከስደት ከተመለሱ በኋላ እና መንግስታቸውን ሲመሰርቱ በይቅርታ ስም እና በተለያዩ ምክንያቶች ባናዳዎችን አቅርበው ነበር፡፡ ለዚህም ድርጊት አንጀቱ ያረረው አርበኛ “እምዬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፣ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ!” ብሎ ተቀኝቷል (ገዳይና ከሃዲው ለጣሊያን እንቁላል ቀቃዩ ነበር፤ ሟች ደግሞ አርበኛውና የተከዳው ወገን ነው) ተግባባን? ዛሬ በዘመነ አብይ ተመሳሳይ ሁኔታ ሲደገም አይተናል፤ ትናንት  ከሱማሌው ዚያድ ባሬ የጀነራልነትን ማዕረግ ተቀብሎ ወገኖቹንና አገሩን የወጋው (የካደው) ዋቆ ክብር ተሰጥቶት፣ ሃውልት ቆሞለት፣ ትምህርት ቤት ተሰይሞለት ይገኛል። ክህደትን ባሕል ማድረግ እንዲህ ነው።  ለከሃዲዎች ክብር መስጠት ማለት ይህ ነው፡፡ በአንፃሩ የጣሊያንን ጦር ካንበረከኩት እና በዘመናዊ ትጥቅና አደረጃጀት የተሻለ ጦር ያዘመቱት የሐረሩ ራስ መኮንን ሃውልታቸው ፈርሶ፣ ስማቸው ተሽሮ እናገኛለን።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ዛሬም የታሪክ አዙሪት ውስጥ ያለን ይመስል ትናንትና ማህተብ በአንገታቸው፣ መስቀል በደረታቸው፣ ድጓ በጎናቸው፣ ክላሽ በክንዳቸው አንግተው፣ በአማራ ሕዝብ ስም ምለው እና ተገዝተው የአማራን ሕዝብ ከግፍና ከበደል ነፃ እናወጣለን ብለው ወደ ዱር ከገቡት ወገኖች መካካል በፖላቲካ ስልት እና ስሌት አሳበው ትናንት እና ዛሬ የአማራን ሕዝብ ሲገድሉ እና ሲያስገድሉ ከነበሩ አካላት ጋራ ሕብረት መፍጠራቸውን ከጠላት እልፍኝ ውስጥ ሆነው አውጀውልናል፡፡ 

ወደ መቀሌ ተጉዘው ከወያኔ ጋር አንሶላ የተጋፉት ወንድሞች የነገሩን ድርጊታቸው ፖለቲካዊ ስሌትና ስልት እሳቤ ያደረገ መሆኑን ነው።  እነሱም ብቻ ሳይሆኑ ድርጊቱን በአደባባይ የሚደግፉ አካላት ድርጊቱ የዘመናችን ድንቅ የፖለቲካ ጥበብ እና እርምጃ ነው ብለው ይሰብካሉ፡፡ ነገር ግን እሳካሁን ባቀረብኩት የክሕደት ባሕሪያት ትንታኔ ስመዝነው ከፖለቲካ ስሌትና ስልት ይልቅ ፖለቲካዊ ክሕደትነቱ አመዝኖ አገኘዋለሁ። በእርግጥ አንዳንድ የአፋብን አመራሮች የወሰዱትን እርምጃ መንግሥተ ሰማያት እንደመግባት የቆጠሩ ወገኖች ጥቂት አይደሉም፡፡ ለዚያም ብዙ ምክንያቶች አሏቸው፤ ለአሁኑ አላሳመኑኝም፡፡ ነገር ግን የጥቂት አፋብን አመራሮች የወሰዱትን እርምጃ እንደ ክሕደት የሚያዩትን ሰዎች በድንጋይ ለመውገር ሁሉም ወንዝ ወርዶ አለት በመሰብሰብ ላይ የገኛል፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ከመፅሐፈ ምሳሌ እንድ ቁም ነገር ልጥቀስ፡ Psalm 1:1-6፡ Blessed is the man who walks not in the counsel of the wicked, nor stands in the way of sinners, nor sits in the seat of scoffers. ፖለቲካዊም ሆነ ማሕበራዊ ክህደት አዲስ እንዳልሆነ ከይሁዳ ከህደት እስከ ዐቢይ ክሕደት የሰነድና የታሪክ ፍተሻ በማድረግ ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡ ይሁዳ አምላክን ከከዳ በኋላ ወደ ቀድሞ ማንነቱ ሊመለስ አልቻለም፡፡ ያ ማለት አንዴ ከዳተኛ የሆነን መመለስ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ካፈርኩ አይመልሰኝ ነው የሚባለው፡፡ ከዳተኛን ለመመልስ የሞራልም ሆነ የመንፈስ ጥንካሬ አይኖረውም፡፡ ቢመለስም የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው። ከይሁዳ ታሪክ እንዳየነው ተፀፅቶ በመለሰው ዲናር እንኳ የተገዛው የደም መሬት ነው፡፡ ዛሬ ጥቂት የአፋብን አመራሮች የአማራን ሕዝብ ሕልውና በዲናር ሸጠው ለአማራ ሕዝብ  ሊያመጡለት የሚችሉት ነገር ቢኖር የደም መሬት ወይም አኬል ዳማ መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል። ለዚህም ነው ክርስቶስ የሰቀሉትን ይቅር ብሏቸው ከዳተኞችን ይቅር ያላላቸው፤ ክህደት ከመግደል የበለጠ ሃጢያት እና በዲናር የማይከፈል እዳ ነውና።  

በፒዲኤፍ ለማንበብ አዚህ ይጫኑ

__

- Advertisement -

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena 

2 COMMENTS

  1. ወዳጄ ሆይ!
    ሃይማኖትና ፖለቲካ ወዲያና ወዲህ ናቸው። ሃይማኖት ጭፍን እምነትን ሲጠይቅ፤ ፖለቲካ ደግሞ የሚፈልጉትን ማወቅን እና ያንን ለማግኘት ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ቆራጥነትን ነው የሚጠይቀው። “ዛሬ ጥቂት የአፋብን አመራሮች የአማራን ሕዝብ ሕልውና በዲናር ሸጠው ለአማራ ሕዝብ ሊያመጡለት የሚችሉት ነገር ቢኖር የደም መሬት ወይም አኬል ዳማ መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል።” በማለትህ በጣም አዝኛለሁ። ተሳስተዋል! ማለት አንድ ነገር ነው። ከዚያ አልፎ ግን። ስድቡ፤ ሰዳቢውን እንጂ ተሰዳቢውን አያመለክትም። እኔ፤ ወደ አቀረብከው ትንተና ልግባ። በፖለቲካ ትግል ሀ ሁ ው፤ ራስህን በትክክል ማወቅ፣ ጠላትህን በትክክል ማወቅ እና ራስህን ለማብዛት፤ ጠላትህን ደግሞ ለማሳነስ መጣር ነው። በፖለቲካ ትግል፤ ጠላትን ለማደናበር ይዋሻል። በሃይማኖት ምንም ይሁን ምንም አይዋሽም። ካንተ የተሻለ ስለ ክርስትና ሃይማኖት አውቃለሁ እያልኩ አይደለም፤ አላውቅምና።
    የዐፋብን አመራር እንዴት እንደሚያስቡና ለምን የሚያደርጉትን እንደሚያደርጉ አላውቅም። አባል ስላልሆንኩም ጠይቄ ለመረዳት አልሞከርኩም። በትግል ዓለም ያለፍኩ ስለሆነ፤ ጥቂትም ቢሆን ስለፖለቲካ ትግል ግንዛቤ አለኝ። ብዙ ጠላቶች ያሉት አካል፤ ዋና ጠላቴ፣ በሁለተኛ ደረጃ የማስቀምጠው . . . እያለ፤ ቅደም ተከተል ያበጃል። ከዚያም ዋናውን ጠላት ለማጥቃት፤ ሙሉ ኃይሉን ያሰባስባል። ሌሎቹ ወዳጆቹንም ሆነ ጠላቶቹ፤ በዚህ በዋናው ጠላቱ ላይ እንዲረባረቡለት ይዘይዳል። ይህ ብልህነት ነው። እውነትህን ነው፤ ራሱን “የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር!” ብሎ የሚጠራው ቡድን ሆነ “የኦሮሞ ነፃነት ግንባር” የዐማራ ሕዝብ ጠላቶች ናቸው። እሳትን በሳት ይላል አዋቂ! ታዲያ አብይ መራሹን የአክራሪ ኦሮሞ ገዢ ቡድን የሚቃወም ኃይል ሲገኝ፤ በል ግፋ! ብሎ እንዲያዳክሙለት መተባበሩ፤ ምኑ ላይ ነው ወንጀሉ! በየተራውና በየደረጃው ደግሞ ሌላው እንዳመጣጡ ይስተናገዳል። አይመስልህም!
    አሁን ዐፋብን ባለው አቅም፤ ሁሉን ጠላቶቹን ሊወጋ አይችልም። ይሄ ሀቅ ነው። ታዲያ አቅሙን ወደ ዋናው ጠላት ሲያዞር፤ ሌሎቹ እንዲወጉት ራሱን ማጋለጥ የለበትም። እናም ጊዜያዊ ትብብር አድርጓል። በትብብር ለህልውና ሁለት ነጥቦችን ተመልክቻለሁ። የመጀመሪያው፤ አብይ መራሹ የአክራሪ ኦሮሞ ገዢ ቡድን፤ የኢትዮጵያዊያን ጠላት መሆኑን እና አገራ አፍራሽ መሆኑን ተገንዝበው፤ ይሄን ጠላት ተባብረው ለመጣል መስማማታቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ፤ ይሄ ጠላት ሲወድቅ፤ በኢትዮጵያ አንድ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት እና ሕዝቡ በሚወስነው መንገድ ለመሄድ መስማማታቸው ነው። ፍላጎቴ ከዚህ በላይም ሌሎች እንዲጨመሩ ነው። ነገር ግን ለአሁኑ እኒህን ተቀብለው ተባብረው ወደፊት እንዲሄዱ ወስነዋል። ለኔ ይሄ ትብብር ለህልውናን እንድደግፍ አሳምኖኛል። ባንተ ትንተና ውስጥ፤ “እነሱም ብቻ ሳይሆኑ ድርጊቱን በአደባባይ የሚደግፉ አካላት ድርጊቱ የዘመናችን ድንቅ የፖለቲካ ጥበብ እና እርምጃ ነው ብለው ይሰብካሉ፡፡ ነገር ግን እሳካሁን ባቀረብኩት የክሕደት ባሕሪያት ትንታኔ ስመዝነው ከፖለቲካ ስሌትና ስልት ይልቅ ፖለቲካዊ ክሕደትነቱ አመዝኖ አገኘዋለሁ።” በማለት የፖለቲካ ከሃዲ ብለኸኛል።
    አለማወቅ አንድ ነገር ነው፤ ሌሎችን አያውቁም ብሎ መሳደብ ደግሞ ሌላ ነገር ነው። እኔ ደግሞ የዐማራ ባህሪዬ፤ ከመሬት ተነስቼ ሌሎችን መሳደብ ቀርቶ፤ የሰደበኝን እንኳ በስድብ መመለስ ስለሚከብደኝ፤ የኔ ወንድም፤ ተሳስተሃል! ብዬ አልፈዋለሁ። የሃሳብ ልዩነት በመካከላችን መኖሩ ሊያኮራን ይገባል። ተገቢ የማይሆነው፤ ከኔ የተለዬ ሃሳብ የያዙትን በሙልሉ ከሃዲ! ወንጀለኛ! እያሉ ባደባባ ይመሳደብ ነው። የኔ አመለካከት ይሄ ነው! በማለት የራሴን አቀርባለሁ እንጂ!
    ለሁሉም፤ የዐፋብን አመራር አይሳሳቱም የሚል የለም። ተሳሳቱ ካልን ደግሞ፤ እነሱን መሳደብ ሳይሆን፤ እዚህ ላይ ተሳስታችኋል፣ የተሻለ ምርጫ አላችሁ፣ በማለት ልናስገነዝባቸው ይገባል። ይሄን የምለው፤ እነሱ የኛ ናቸው ከሚል ተነስቼ ነው። የራስህ የሆነውን አታጣጥልም። ታስተካክለዋለህ! ማረሚያ ታቀርባለህ። ተሳሳቱ ብለህ መሳደብና ማውገዝ፤ እነሱ እንዳይኖሩ ማድረግ ወይንም የነሱ ጠላት መሆን ነው። ጣት ገማ ተብሎ ተቆርጦ አይጣልም። በሚችሉት ሁሉ መዳኛ መንገድ በመፈለግ ያክሙታል እንጂ!
    እናም ወዳጄ፤ አብረን ለዐማራው ካለበት ፍዳ መውጣት እንታገል። እንዱ መንገድ፤ የትግሉን መሪ ድርጅት፤ ስህተቱን የሚያርምበት መንገድ እየፈለግን፤ ሃሳብ ማጋራት፣ በተቻለን ደግሞ መርዳት፣ የመሳሰሉትን እናድርግ። ፋኖዎቻችንን ካስወገድን፤ ምንድን ንው ምርጫችን? ማንን ይዘን ነው ወደፊት የምንሄደው። እኛ አዛዥ ናዛዥ ሆነን፤ የትክክልም ሆነ ትክክል ያልሆነ መመዘኛ ካዘጋጀን፤ በቦታው ተቀምጠው ህይወታቸውን እየከፈሉ ያሉትን መሪዎች፤ ጠምዛዦቹ እኛ መሆናችን ነው! መጀመሪያ እስኪ ለአንድ ፋኖ ጫማ ወይንም የዕለት ጉርሻ የሚሆን እንሰንዝር! ይህ የግል አስተያየቴ ነው።
    አመሰግናለሁ
    አንዱ ዓለም ተፈራ

  2. እያሱ ጥሩ ብለሃል ከሃይማኖትም ካለው ነባራዊ ምሳሌም እየጠከስክ አስተምረኸናል። ለባንዳ የሳሳ ልብ የተጀመረው በነጠላ ግንዛቤዬና ምክንያቴ በታላቁ መሪያችን በአጼ ምንሊክ ጊዜ መሰለኝ። እንደውም የምርኮኛ ምህረትንና ልውውጥን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስጀመሩት እሳቸው ሳይሆኑ አልቀሩም። ሱዳን እንግሊዛዊውን የጦር ጀነራል በሰይፍ ቀልቶ በጋቢ ላይ አስቀምጦ ለአለም ሲያሳይ አጼ ዮያንስን አንገታቸውን ቆርጦ በእንጨት አድርጎ ካርቱምን ሲዞር ሊወጉን የመጡ ጥልያኖች ግን ምንም እንዳላደረጉ ሁሉ በክብር ተሸኝተዋል የምንሊክ በሰብአዊነት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከዚህ በኋላ የባንዳ ፍቅር ክፉኛ ተቆራኝቶን ባህል ሁኖ ቀርቷል። ይኸው ይሄ ሁሉ ሪሶርስ ባክኖ የኢትዮጵያ መከላከያ ሙቶና ተጎሳቁሎ ትግሬን እንዲቆጣጠር የተሰጠው ለትግሬ ባንዳ ነው። ከተማዋ በትግሬ ቻይና ባንዲራ ስታቆጠቁጥ አንድም የኢትዮጵያ ባንዲራ አልታየም የኢትዮጵያ ወታደርም ፖሊሱም ፌደራሉም የኢትዮጵያን ባንዲራ ሲያይ ዛሩ ይነሳል የአባ ገዳን ባንዲራ ተከናንቦ ቢሄድ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ደብረ ጽዮንን አባርሮ ሳልሳዊ ወያኔን እንደገና ፍዳችንን አብላው ብሎ ያለው መንግስት መለመኑ ከጀርባው ያለውን ፍላጎት ማወቅ ይከብዳል። እንደውም ረስቼው ነበር አቶ ጌታቸው ረዳ አብይን ብርሃኑ ጁላን ባጫ ደበሌን የውሻ ቆዳ ሲያለብስ ከርሞ ይኸው ዛሬ አብይን ጣቱን ይዞ የሚያሽከረክረው እሱ ሁኗል እንደው የባንዳ አዜም ካልተዞረብን ጌታቸው ረዳ፤ብርሃኑ ነጋ፤አረጋዊ በርሄ፤ኬሪያ ኢብራሂም፤ሌንጮ ባቲ፤ቀጀላ መርዳሳ፤ሱሌማን ደደፎ የመሳሰሉት ሰው እንኳን ቢጠፋ እንኳን ለስልጣን በቤተ መንግስት በኩል እንዲያልፉ መፈቀድ ነበረበት? ብርሃኑን እንኳን አርጅቷል ረግሞኝ እንዳይሞት ብዬ ነው ብሏል አብይ።

    እንግዲህ የትግሬ ጉዳይ እንዲህ የሚረግብ አይመስልም ሳልሳዊ ወያኔ እኔም ልሞክረው በሚል አተያይ አለሁ አለሁ እያለ ነው። መከላከያው እዛው እያለ እነዚህን ነቀርሳዎች ቢገላግሉት ህዝቡ ኢትዮጵያዊነትን ሊመርጥ ይችል ይሆናል የሚል እሳቤ አለ። ለማንኛውም ዛሬ ባንዳነት ከመለስ አባት፤ከሃይለስላሴ ጉግሳ በላይ አዲሶቹ ትግሬዎች በጣም የሚኮሩበት ሁኗል አጼ ዮሃንስ ያቆዩላቸውን አገር አውድመው አንዴ ወደ አረበ አንዴ ወደ ጥልያን እየተንከራተቱ መከራቸውን የሚያዩ?

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News