Homeነፃ አስተያየትእውን ኢትዮጵያ አልፈረሰችም?(ጥሩነህ ግርማ)

እውን ኢትዮጵያ አልፈረሰችም?(ጥሩነህ ግርማ)

Advertise Here
Advertise here
ኢትዮጵያ አልፈረሰችም

ጥሩነህ ግርማ

ብዙዎች የሃገር መፍረስን ወሬ መስማት አይፈልጉም፣ አይወዱም። ሃገራቸውን ለሚወዱ ሁል ይህ አስደንጋጭ ነው፣ አስፈሪ ነው። ነገር ግን የምናውቃት ኢትዮጵያ ዛሬ በምናብ ካልሆነ የለችም። ሃገር ፈረሰ ማለት መሬቱ ተቆራረሰ አይደለም፣ ፈረሰ ስንል ሃገራዊው አንድነት፣ ነጻነት፣ ንብረት የማፍራትና ባለሃብት መሆን ወዘተ እንዳልነበሩ ሲሆኑ ነው። የአንድ ሀገር መፍረስ ወይም ውድቀት የሚለካው በካርታ ላይ በሚታየው የድንበር መቆራረስ ወይም የመሬት መበጣጠስ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያ በላይ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ተገንብቶ የነበረው ማህበራዊ(Social fabric) የህዝቦች መከባበር፣ የወል እሴቶችና  የእርስ በርስ እምነት ሲደርቅና ሲጠፋ ነው። መሬት ድንበር ሊኖረው ይችላል፤ ነገር ግን ሀገርን “ሀገር” የሚያደርጋትና አብሮና አጣብቆ የሚይዛት በህዝቦች መካከል ያለው የማይታይ ማህበራዊ ገመድ ነው። ዩጎዝላቪያ ከመፍረሷ በፊት ለብዙ  ዓመታት የተለያየ ብሔርና ሃይማኖት ያላቸው ህዝቦች በሰላም፣ በጋብቻና በንግድ ተሳስረው የሚኖሩባት ሀገር ነበረች። ነገር ግን ፖለቲከኞች የህዝቡን የቆየ ማህበራዊ መስተጋብር በመሸርሸር፣ “እኛ” እና “እነሱ” የሚል የጥላቻና የጥርጣሬ ትረካ ሲነዙ፣ በጎረቤታሞች መካከል ያለው እምነት ጠፋ።

በኢትዮጵያም ታሪክ ውስጥ አባቶችና እናቶች በዕድር፣ በዕቁብ፣ በማህበር፣ በጋብቻና በጉረቤትነት የገነቡት የማይበጠስ ማህበራዊ መሰረት ነበራቸው። ነገር ግን ለፖለቲካ ፍጆታ የውሸት ትርክቶች ምክንያት አብሮ የመኖር እሴትና የህዝቦች እርስ በርስ እምነት ስለተሸረሸረ የዩጎዝላቪያ ዓይነት የማህበራዊ መስተጋብር መፍረስ አጋጥሞናል። 

ሶማሊያ በአንድ ቋንቋ፣ በአንድ ሃይማኖትና በባህል የተሳሰረች ሀገር ብትሆንም፣ በጎሳ (Clan) ፖለቲካና በስልጣን ሽኩቻ ምክንያት ማህበራዊ አስተሳስሯ ጠፋ። የጎሳ ማንነት ከሀገርራዊ ማንነት በላይ ሲገዝፍና ህግና ስርዓት የሚጠበቅበት ማህበራዊ ውል (Social Contract) ሲፈርስ ሀገሪቱ ለዓመታት ወደማያልቅ ቀውስ ውስጥ ገባች። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ህብረ-ብሔራዊ ሀገር እንደመሆኗ ልዩነቶችን በውይይትና በፍትህ ማስተናገድ ባለመቻሉና ማንነትን ብቻ የፖለቲካ መሳሪያ በማድረግ የጋራ እሴቶች እየፈረሱ  ሶማሊያ ላይ የታየው ዓይነት የማህበራዊ ስርዓት መናጋት ሀገርን የመጠበቅ አቅምን አዳክሞት ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። 

በሶሪያና ሊቢያ  የተከሰተው ግጭት መሬታቸውን ብቻ ሳይሆን የህዝቡን ስነ-ልቦናዊና ማህበራዊ አንድነት አፍርሶታል። ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፣ የነበሩ የማህበረሰብ መዋቅሮች ፈርሰዋል፣ በህዝቦች መካከል ያለው ቁስል ደግሞ በቀላሉ የሚጠገን አልሆነም።  የኢትዮጵያ ታላቅነት መሰረቱ የህዝቦቿ መተሳሰብ፣ ችግርን በጋራ ማለፍና  ወገንን መደገፍ ነው። ግጭቶችና መፈናቀሎች ሲበዛ ግን ይህ አብሮ የመኖር ባህል ይኸው ደብዝዞ እየጠፋ ነው።  ከላይ ከተጠቀሱት ሃገሮች በምን እንለያለን?

በፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት፣ የፈረሰ/የወደቀ መንግሥት (Failed State) የሚለው ጽንሰ-ሐሳብ የሚያመላክተው ማዕከላዊው መንግሥት ሕጋዊ ሥልጣኑንና ቁጥጥሩን ማስከበር፣ የሕዝብን ደህንነት መጠበቅ፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥና መሠረታዊ የሕዝብ አገልግሎቶችን ማቅረብ ሙሉ በሙሉ ሲሳነው ነው። የሀገረ መንግሥት መፍረስ በአንድ ጀምበር የሚከሰት ድንገተኛ ክስተት ሳይሆን፣ የሥርዓቱ መዋቅራዊ ብቃት፣ የሕዝብ እምነትና የፖለቲካ ሕጋዊነት ደረጃ በደረጃ እየተሸረሸረ የሚሄድበት አደገኛ ሂደት ነው። በተጠቀሱት ሃገሮችም በአንድ ሌሊት አልተፈጸመም። 

አንድ መንግሥት ፈረሷል ለማለት ከሚያስችሉ ዋና ዋና መስፈርቶች መካከል የመንግሥት የኃይል አጠቃቀም የበላይነት  መላላት ወይም መጥፋት ወይም አላግባብ መጠቀም የመጀመሪያው ነው። ማዕከላዊው አካል የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ሲሳነው ወይም ፈቃደኛ ሳይሆን፣ በሀገሪቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች ሕገ-ወጥ የጦር ቡድኖች፣ አማፂያንና የወንጀል መዋቅሮች በይፋና በምስጢር  መነሳት ይጀምራሉ። የዚህም ውጤት የዜጎች ነፃ የመንቀሳቀስ መብት መገደብ፣ የማኅበራዊ መዋቅር መበታተንና የሕግ የበላይነት ሙሉ በሙሉ መክሰም ነው።

ዛሬ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበትን አጠቃላይ የፖለቲካ፣ የደህንነትና የማኅበራዊ ውጥረት በዚሁ የፖለቲካ ሳይንስ መነጽር ስንመረምረው፣ ሀገሪቱ ከተራ አለመረጋጋት አልፋ ወደ አደገኛ የመንግሥት መዋቅራዊ መፍረስ አቅጣጫ እያመራች መሆኗን የሚያሳዩ በርካታ ሁነቶችን እናስተውላለን። በእርግጥስ መዋቅራዊ መፍረስ የለም ወይንስ ስለፈራነው ስሙን መጥራት ተቆጠብን? 

ለዚህ አጠቃላይ ሀገራዊ ውድቀትና ቀውስ ዋናውና መሠረታዊው ምንጭ በብሔርና በማንነት ፖለቲካ ላይ የተዋቀረው የመንግሥት መዋቅር እራሱ ነው። አብዛኞቹ ሀገሪቱን እያመሱ ያሉ መዋቅራዊ ችግሮችና ግጭቶች ተፈጥሮአዊ ወይም ድንገተኛ ሳይሆኑ፣ እራሱ በመንግሥት የሚጠነሰሱና የሚመሩ ናቸው። የሥልጣን እድሜውን ለማራዘምና የብሔር የበላይነትን ለማንገሥ የሚሠራው ይህ ሥርዓት፣ በተለይም የአማራና የትግራይ  ሕዝቦችን የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የደህንነት መሠረቶች በመምታት፣ ለማዳከምና ለማሳነስ የታሰቡ ዘመቻዎችንና የተለያዩ  ስልቶችን በመጠቀም በይፋም ሆነ በስውር ሲሰራ እየታየ ነው። ይኸው በመንግሥት ደረጃ የሚካሄደው ስልታዊ ማገለልና ጥቃት የሀገሪቱን የማኅበራዊ ውልና ሀገራዊ አንድነት ሙሉ በሙሉ አፍርሶታል። ቆሜለታለሁ የሚለውና በስሙ ግፍ የሚፈጸምበት የኦሮሞ ህብረተሰብም ከዚህ እልቂት ነጻ አይደለም።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena
  • በመጀመሪያ ደረጃ፣ የዜጎች ነፃ የመንቀሳቀስ መብት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ታስሯል። ዜጎች ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ወጥተው ወደ ተለያዩ ክፍለ ሀገራት፣ ወይም ከአንድ ክልል ወደ ሌላው ክልል በነፃነትና በሰላም ተንቀሳቅሰው መኖርና መስራት ካቆሙ ብዙ አመታት አልፈዋል። በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ዋና ዋና የትራንስፖርት መስመሮች በአማፂያን፣ በታጣቂዎችና በመንግሥት ወገንተኝነት በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች በመዘጋታቸው ወይም አደገኛ በመሆናቸው ምክንያት የሀገሪቱ ግዛት በየአካባቢው የተቆራረሰ ሆኗል። ዛሬ ማነው ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ሃረር፣አሩሲ፣ ወልጋ፣ባሌ ወይም ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው? አንድ ሰው በሃገሩ ተዘዋውሮ መስራትና ሃብት ማፍራት ቀርቶ የሞተ ዘመዱን ለመቅበር የማይንቀሳቀስበት ወቅት ላይ ነን።  ማነው የሱልሉታን ሜዳ አቋርጦ ከጎጃምና ጎንደር አዲስ አበባ የሚገባ አማራ? አውቶቢሶች ሲታገቱ በሩቅ እርቀት ላይ ያለ የአብይ ሰርዊት፣ የኦሮሞ ሚሊሽያ እያየ የሚያልፋቸውና የሚተባበራቸው የቀን ዘራፊዎች የተፈለፈሉባት ሃገር ሆናለች። አሁንማ ከአዲስ አበባ ወደ ጓሮ ወደ ቃሊቲ የሚሄዱ ታክሲዎች የይለፍ እየተጠየቁ ነው እየተባለ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በመስተጓጎላቸው የንግድ ሰንሰለቱ በመበጣጠሱ በየክልሉ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት የስንዴና የምግብ እጥረት አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል።
  • ሁለተኛውና በጣም አስደንጋጩ ማሳያ፣ እገታና የካሳ ገንዘብ (Ransom) መቀበል የተለመደ የዕለት ተዕለት ንግድና መደበኛ ክስተት መሆኑ ነው። ሰላማዊ ዜጎች፣ መንገደኞች፣ የሕዝብ ትራንስፖርት ተሳፋሪዎችና የልማት ሠራተኞች ሳይቀሩ እየታገቱ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን እንዲከፍሉ ይገደዳሉ። ከዚህም በላይ፣ የካሳ ገንዘቡ የሚተላለፈው መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር አለኝ በሚላቸው የባንክ መዋቅሮች በኩል ሆኖ ሳለ፣ ወንጀለኞችን ከመከታተል፣ ሂሳባቸውን ከመያዝ ወይም ድርጊቱን ከመግታት አንጻር የመንግሥት አካላት ያሳዩት ድክመት ወይም ዝምታ፣ የሕግ ማስከበር ሥርዓቱ ምን ያህል እንደተደረመሰና የወንጀል መዋቅሩ ከመንግሥት አካላት ጋር ተሳስሮ እንደሚሰራ የሚያሳይ ግልጽ ማረጋገጫ ነው። ይህ የታጣቂዎችና የህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ጥምረት መንግስታዊ ያልሆኑ ገቢዎችን በማመንጨት የሀገሪቱን የፊስካል ደህንነት ሙሉ በሙሉ አደጋ ላይ ጥሎታል።
  • ሦስተኛው አሳሳቢ ነጥብ፣ በሰላማዊ ዜጎች እና በሕዝብ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚካሄደው ድሮንና የአየር ድብደባ ነው። የመንግሥት ዋነኛ ኃላፊነት የዜጎችን ሕይወት ማዳን ሆኖ ሳለ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሆስፒታሎች፣ በገበያ ቦታዎችና በሰላማዊ መንደሮች ላይ የሚፈጸሙ አሰቃቂ የአየር ጥቃቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት ቀጥፈዋል፣ ንብረታቸውንም አውድመዋል። ይህም መንግሥት የመሬት ላይ ቁጥጥሩን በማጣቱ ምክንያት ሕዝብን የመጠበቅ ኃላፊነቱን ወደ ጎን በመተው በገዛ ዜጎቹ ላይ ሆን ተብሎ የሚፈጸም የጦርነት ስልት መሆኑን  የሚያሳይ የጠራራ ጸሃይ እውነታ ነው። የአብይ አስተዳደር ተቃውሞው በበዛበት ቁጥር ቂሙን የሚወጣው በሰላማዊው ህዝብ ላይ መሆኑ ምን ያህል ጸረ ህዝብ እንደሆነ ያሳያል። ባጭሩ መንግስት ዋነኛና  የመጀመሪያው ህገ መንግሥታዊና ሞራላዊ ኃላፊነት የዜጎችን ሕይወት፣ ደህንነትና ንብረት ማዳን ነው። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው እውነታ ከዚህ ተቃራኒ ነው። በተጨማሪም የጤና ተቋማትና የትምህርት ቤቶች መውደም ቀጣዩን ትውልድ ከመማርና ከህክምና አገልግሎት በማፈናቀል የረጅም ጊዜ ማህበራዊ ቀውስ እየፈጠረ ይገኛል
  • አራተኛውና ከባድ አደጋ የደቀነው ጉዳይ፣ በማንነት ላይ የተመሠረተ ጥቃትና  የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው። በተለይም በአማራና  በትግራይ ሕዝቦች ላይ የሚፈጸሙ በማንነት ላይ የተመሠረቱ ግድያዎች  መፈናቀሎች፣ የታቀዱ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችና የሀብት ውድመቶች በሰፊው የሚፈጸሙ ሲሆን፣ እነዚህን ጥቃቶች መንግሥት ማስቆም አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ በጥቃቱ ላይ የሚሳተፉና  በመንግሥት የተዋቀሩ በስሩ የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች መኖራቸው የዜጎችን የመኖር ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል፤ የመንግሥትንም ሕጋዊነት ሙሉ በሙሉ አክስሞታል። አብይ በኦሮሞ ድንኳን ውስጥ ተወሽቆ በዘር ላይ የተመሰረተ እልቂት በማድረግ ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት ካለው ፍላጎቱ ጋር የተሳሰረ እርምጃ እየወሰደ ነው። በዘር ላይ የተመሰረተው መዋቅራዊ ጥቃት የእለት ከእለት ተግባሩ አድርጎታል። ይህም ማህበረሰባዊ እምነትን ሙሉ በሙሉ በመበጣጠስ ለቀጣይ መቶ ዓመታት የማይጠገን የጥላቻና የቁስል አዙሪት ውስጥ እየከተተን ይገኛል።
  • በመጨረሻም፣ ይፋዊ ተቃውሞዎችን እና ሀሳብን የመግለጽ ነፃነትን ለመጨቆን ሲባል የሚካሄደው የእስራት ማዕበል ሌላው ማሳያ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችና የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ያለ ምንም ሕጋዊ ፍርድና ጥፋት በእስር ቤቶች እንዲማቅቁ መደረጉ፣ የፍርድ ቤቶችን ነፃነት ያከሰመና የመንግሥትን ሕጋዊነት ያጣጣለ እርምጃ ነው። እንዲሁም ሃሳብን በነፃነት የመግለጽና የመሰብሰብ መብት ሙሉ በሙሉ በመታፈኑ ዜጎች በግፍ ላይ እንኳን ድምጻቸውን እንዳያሰሙ የማስፈራራት ስልት ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ባጠቃላይ፣ ሰላም በራቀበት፣ የዜጎች የደህንነትና የመንቀሳቀስ መብት በተገፈፈበት፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች በተቋረጡበት፣ የታጠቁ ኃይሎችና እገታ በነገሱበት፣ እንዲሁም መንግሥት በገዛ ዜጎቹ ላይ የኃይል እርምጃ በሚወስድበት ሁኔታ ውስጥ ሀገርን አጽንቶ ማስቀጠል አይቻልም። ኢትዮጵያን ከዚህ ሙሉ ለሙሉ ከፈረሰ መንግሥትነት (Total State Collapse) አደጋ ውስጥ አይደለችም ለማለት የሚያስደፍር ምን አለ? 

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 

- Advertisement -

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena 

2 COMMENTS

  1. ወንድም ጥሩነህ፦

    ኢትዮጵያ ከደርግ “አድሀሪ-ተራማጅ” ክፍፍልና እልቂት አልፋ፣ የጣሊያን ኢምፔሪያሊስቶች ክሪስፒና ሙሶሊኒ የከፋፍሎ አገዛዝና ብዝበዛ ያስተማሯቸው የወያኔ ግልብ የቡድን መሪዎች አገር ለዘጠኝ ጎሣ አካፍለው 74ቱ ጎሣ የዘጠኙ ተገዥ ያደረጉበትን ውድቀት አልፈን፣ የጎሣ አገዛዛ፣ በትግሬና በኦሮሞ ጎሣ መሪዎች የውድቀት አገዛዝ ተራክሶ በኢትዮጵያውያን ሁሉ ውድቅ ተደርጎ፣ መገንጠል ከድጡ ወደ ማጡ መሆኑን በኤርትራ አይተን፣ ዛሬ የአንድነቱ ኃይል ጠንክሮ “ትብብር ለሕልውና” ከትግሬ፣ ከአማራ፣ ከቤኒሻንጉል፣ ከጋምቤላ፣ ከደቡብ፣ ከኦጋዴን፣ ከኦሮሞና ከአፋር – ከሙሉ ኢትዮጵያ – የኢትዮጵያ ምርጥ ወጣቶች ተጠራርተው፣ የጎሣውንና የኮሙኒዝሙን ተደራራቢ አጥር አፍርሰው፣ በሕብረት ታግለው ለኢትዮጵያውያን የምትበጅ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን መክሮ ዘክሮ የሚመሠርቷት ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሊያደራጁ ተስማተው ነግረውናል። እንደ አውሬ መበላላቱ ሊያከትም ተስማምተዋል።

    በተለያየ ሰበበ ጩልሌዎች፣ በዝባዦችና አውሬ-አከል መሪዎች የዋሁን ወገናችንን ከፋፍለው የሚጫወቱባት ኢትዮጵያ እንድታበቃና ወደ ተደላደለ ጎሣ፣ ሃይማኖት፣ መንደር፣ ጾታና ዕድሜ ወደማይለይ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በትብብር እንድንሽጋገር እየተሠራ ነው። ከአውሬ የቡድን አገዛዝ ተላቅቀን፣ ሰው መሆናችን ተከብሮ ያለችንን ሀብታም አገራችንን በጋራ በሰላም ማልማት እንድንጀምር ጉዞ ተጀምሯል።

    ተማርሁ የሚል ሁሉ፣ በቡድን አሳብቦ ሥልጣንና ዝርፊያ የማይሻ ሁሉ፣ ለወገን እውነተኛ ተቆርቋሪ የሆነ ሁሉ፣ አገሩንና ሕዝቡን የሚወድና በኢትዮጵያዌቱ የሚኮራ ዜጋ ሁሉ ያልተቆጠበ ድጋፍ አድርጎ ራሱን፣ ወገኑን፣ ኢትዮጵያንም ከዓለም መሳቂያ መሳለቂያነት አውጥቶ ለጋራ ሕልውናና የተፋጠነ ዕድገት ርብርብ የሚያደርግበት ወቅት ላይ ነን። ከ12ኛ ክፍል ተፈታኞች 3.5 በመቶ ለዩኒቬርሲቲ ትምሕርት አልፈዋል መባሉ ትውልድና አገር ማቆርቆዙ፣ 2000 ዓመት ዕድሜ ባለው የእርሻ ባህል ራሳችንን ጠርንፈን ስንዴ ለማኝ መሆናችን፣ ሰፊ አገር፣ የተትረፈረፈ የውህ ሃብት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ሠራተኛ ወጣትና የተትረፈረፈ የማዕድን ሀብት እያለን፣ እኛው እርስ በእርስ እየተናከስን የፈጠርነው ችግር ነው። አሜሪካ ከ1000 በላይ ጎሣና የዓለም ሃይማኖቶች አማኞች እያሉባት ጦርነት የለም። የእኛ 83 ጎሣዎች የአገር ጊጥ እንጂ የጦርነትና የክፍፍል መንስዔ የተደረጉት በበሰበሰ የቡድን ጥቅም አግበስባሽ ፖለኢካ እንጂ ሌላ ምክንያት የለም። “ትብብር ለሕልውና” ይህን የአውሬ አገዛዝ ሥርዓት እንዲያጠፋ ይጠበቃል።

    ወንድም ጥሩነህ፣ ኢትዮጵያውያን፣ ከእምየ ምኒልክ የአድዋ የጋራ ታምር ወዲህ፣ ኢትዮጵያን በጋራ ለመታደግ የዛሬውን ዓይነት ትብብር ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ፈቃድ ሲመሠርቱ የዛሬው የመጀመሪያ ነው። ታሪካዊ ነው። ሕልውናችንን ማስከበር ብቻ ሳይሆን፣ ሰው መሆናችንንም እንደ ገና በራሳችን ትግል እንድንጎናጸፍና ከአውሬ አገዛዝ ሥርዓት እንድንወጣ ጅምሩ ይታያል። ለጥቁር ዘር ምሣሌና ተስፋ እንደነበርን፣ ዛሬም ያንኑ ለማስቀጠል ታሪካዊው አንድነታችን ያስችለናል።

  2. ወንድም ጥሩነህ፦
    ከመፍረስ ድናለች ። አትስጋ! ዛሬማ ከኢትዮጵያ ዙሪያ ያሉ ልጆቿ ከጋምቤላ፣ ክቤኒሻንጉል፣ ከኦሮሚያ፣ ከኦጋዴን፣ ከአፋር፣ ከአማራና ክርትግሬ ተጠራርተው “ትብብርን ለሕልውና” የመሠረቱት ዲሞክራሲዊት ኢትዮጵያን ለማዋለድ ነው። የተሰባሰቡት እኮ አንድም ኃይል ሳያስገድዳቸው ወደው ፈቅደው የኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓተ መንግሥት፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እንደተጠበቁ ሆነው፣ በጋራና ከሙሉ ሕዝባችን ጋር ለመወሰን ነው። አካሄዳቸው የ1982ዎቹን ዲሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪቃን እንዳዋለዱት የማንዴላ ደቡብ አፍሪቃ ይመስላል። ዳግም አንድ የጎሣ ቡድን ወይም ጠመንጃ ነካሽ አምባገነን እንዳይቀልድባት ለማድረግ ቆርጠው ተነስተዋል። የእኛ ድርሻ፣ ወሬውን፣ አጉል መፈላሰፉንና መነታረኩን አቁመን መደገፍ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News