

በሙሉዓለም ገ/መድኀን
“ጦራችን፣ ምግባችን፣ ንግዳችን በባሕሩ ላይ የተመሠረተ ነው።” ዴቪድ ቤንጉሪያን፣ (On the Red Sea)፣ 1950 እ.ኤ.አ.
የእስራኤል ሀገራዊ ኀልውና የተመሰረተው በባሕሩ ደህንነት ላይ ነው የሚል ግምገማ የነበረው፣ ዴቪድ ቤንጉሪያን የባህር ዳርቻውን አገራት መቆጣጠር “የዳር ስትራቴጂ” የሚል የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀርፆል።
ይህ ስትራቴጂ (ወደ ባህሩ መመለስ) በእስራኤል አገራዊ ኀልውና ውስጥ ቁልፍ ጉዳይ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ነው።
እስራኤል እንደ አገር ዳግም ስትቋቋም፣ አይሁዳዊያን እና ባሕሩ ኀልውናቸው ከሙሴ የመሻገር ታሪክ ጋር ተመልሶ ተቆራኝቷል።
እናም የዚህ ባሕር ዳርቻ ተዋሳኝ አገራት በሙሉ በትንሹ መመዘኛ ‘ፕሮ ዌስተርን’ መሆን አለባቸው። እንደ አይሁድ ልሂቃን ግምገማ፣ ፕሮ ዌስተርን አገራት ፀረ-ጺዮናዊ የመሆን ዕድል የላቸውም። ለእስራኤል አገራዊ ዕውቅና ሰጡም አልሰጡም፣ አደጋ የመሆን ዕድላቸው አነስተኛ መሆን አለበት (ልክ እንደ ሳዑዲ አረቢያ)።
እንደ የመኑ ነውጠኛ ሁቲ የባህሩን ውስን ዳርቻ መቆጣጠር መቻል፣ በእስራኤል አገራዊ ኀልውና ላይ እያስከተለ ያለውን አደጋ ይበልጥ የተረዳው የናታኒያሁ አስተዳደር፣ የዴቪድ ቤንጉሪያን የባህር ዳርቻውን አገራት መቆጣጠር “የዳር ስትራቴጂ” የሚለውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ደረጃውን አሳድጎ “Hexahon of Alliance” ብሎ ይዞት መጥቷል።
የእስራኤል አዲሱ “የሄክሳጎን” ጥምረት ዓለማቀፉን ማኀበረሰብ እያነጋገረ ነው፡፡ የጂኦ ፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው ጨዋታ ቀያሪ ብለውታል፡፡ ሌሎች ተቺዎች ደግሞ ዕውን ሊሆን የማይችል የኔታኒያሁ ቅዥት ሲሉ ጠርተውታል፡፡
እስራኤል በሜዲትራኒያን እና በቀይ ባህር ላይ ኀልውናዋን የመሰረተች ሲሆን፤ ይህን ባህር የመቆጣጠር ጉዳይ አስፍታ ሕንድን፣ ግሪክን እና ቆጵሮስን እንዲሁም ሌሎች “ያልተጠቀሱ” የአረብ፣ የአፍሪካ እና የእስያ አገራትን ያካተተ አዲስ ቀጣናዊ ጥምረት በናታኒያሁ እንደተመሰረተ ይነገራል።
በዚህ “ሥማቸው ያልተጠቀሰ” በተባሉ አገራት ውስጥ የአብርሃም ቃል ኪዳን ፈራሚዋ ኢምሬቶች (UAE) አለችበት።
ኔታንያሁ መካከለኛው ምስራቅ በሁለት “ጽንፈኛ” ጎራዎች የተከፈለ ነው ብለው ሲሉ የሰውየውን ዕይታ ያስረዳሉ፡፡
የናታኒያሁ ስትራቴጂ፣ ሁለት የምከታ ስልቶችን የያዘ ነው። አንደኛው የሺዓ ጽንፈኛ ጎራ ሲሆን፣ በኢራን የሚመራውን እና እንደ ሂዝቦላህ፣ ሁቲ፣ እና የኢራቅ ሚሊሺያዎችን ያካተተ ስብስብ ነው። ሌላኛው ደግሞ አዲስ እየመጣ ያለ “የሱኒ ጽንፈኛ ጎራ” ነው። የቱርክ፣ ፓኪስታን እና ሳውዲ አዲሱ ጥምረት ለእስራኤል ምቾት የሚሰጥ አይደለም። የኔታያሁን የምከታ ስትራቴጂ በሁለቱ ጽንፎች ላይ ያተኮረ ነው።
እናም፣ እስራኤሎቹ በሶማሊላንድ የዘረጉትን የግማሽ ክፍለ ዘመን ፕሮጀክት ወደ አገራዊ ዕውቅና ሲያሳድጉ፣ የዚሁ የባህር ዳርቻውን አገራት የመቆጣጠር ግባቸውን ለማሳካት ነው።
በእስራኤል ያልተፃፈ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የባህሩ ዳርቻ አገራት በሙሉ ቢቻል የአብርሃም ቃል ኪዳን ስምምነትን የፈረሙ፤ ካልተቻለም ደሞ ፕሮ ዌስተርን (ጸረ-ኢራን- ጸረ-ሁቲ- ጸረ ሐማስ-…ወዘተ) መሆን አለባቸው የሚል አቋም አለ።
የኔታንያሁ ዓላማ ከላይ የተጠቀሱትን የሺዓ እና ሱኒ ሁለት (ፅንፈኛ) ጎራዎች ለመመከት እስራኤልን ማዕከል ያደረገ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንብ መገንባት እንደሆነ ተንታኞች ስለ አዲሱ ጥምረት (Hexgaon of Alliances) ያስረዳሉ።
በርግጥ ኔታንያሁ ዕቅዱን ያቀረቡት እስራኤል በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መገለል ውስጥ ባለችበት ወቅት ቢሆንም፣ የጥምረቱን ተግዳሮቶች ለማለፍ ጉልበተኝነቷ እና የሴራ ብልት አዋቂነቷ በቂ ይመስላል።
እስራኤል ከህግ በላይ በሆኑ ድርጊቶቿ ህልውናዋን ለማስከበር የማትገባበት እንደሌለ ያለፈው 80 ዓመት የአገር ምስረታ እና ግንባታ ታሪካቸው ይነግረናል።
ኔታንያሁ “የሱኒ ጽንፈኛ ጎራ” የሚሏቸው እንደቱርክ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ግብጽ ያሉ አገራት በእስራኤል (የጋዛ፣ ኢራን ጦርነት) ምክንያት ይበልጥ እየተቀራረቡ መጥተዋል። ለዚህ መመከቻ የኢትዮጵያውን ገዥ ብልጽግናንም ይጨመራል የተባለው “ጥምረት” በአፍሪካ ቀንድ እየታየ መጥቷል።
የኔታንያሁ የጥምረት ሀሳብ በአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን በቀይ ባሕር ቀጠና ወታደራዊ፣ ጂኦ-ፖለቲካዊና የደህንነት ሁኔታዎችን የሚወስን እንደሆነ ተንታኞች ይሞግታሉ፡፡
እስራኤል በኢራን እና አጋሮቿ ላይ የወሰደችው ተከታታይ ወታደራዊ እርምጃ በቀጠናው የነበረውን የኃይል ሚዛን በእጅጉ ቀይሮታል። ይህ እርምጃ ሂዝቦላን፣ ሁቲንና ሃማስን በማዳከም ብቻ ሳይወሰን፣ እስራኤል በቴክኖሎጂና በመረጃ የበለፀገ “በግንባር የተፈተነ” ወታደራዊ አቅም ባለቤት መሆኗን አረጋግጧል።
ይህን የበላይነት ለማጠናከር እስራኤል ከሕንድና ከኢትዮጵያው ገዥ ጋር የፈጠረችው አጋርነት በቀላሉ የማይታይ ነው፡፡ በተለይም በሱማሊላንድ በኩል የምታገኘው ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ይዞታ በቀይ ባሕር መውጫ ባብ አል መንደብ “ጉሮሮ” ላይ ተሰሚነት እንዲኖራት ያደርጋታል።
እንዲያም ሆኖ፣ በኢትዮጵያ ያለው የአገር ውስጥ ጦርነት እና ከኤርትራ ጋር ያለው ወታደራዊ ፍጥጫ፣ በእስራኤል ፍላጎት ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት የሚታየው ኔታንያሁ “የሱኒ ጽንፈኛ ጎራ” የሚሏቸው እንደቱርክ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ግብጽ ያሉ አገራት በአፍሪካ ቀንድ ላይ ከፈጠሩት አሰላለፍ እና ካላቸው ነባር ተጽዕኖ አኳያ እንደሆነ የቀጠናው ጂኦ-ፖለቲካ ተንታኞች ይስማማሉ፡፡
እስካኹን ባለው ሁኔታ፣ እስራኤል፣ UAE እና ዐቢይ አሕመድ በአፍሪካ ቀንድ የውክልና ጦርነት (ሱዳን)፣ የግዛት አንድነትን በመፈታተን (ሶማሊያ-ሶማሊላንድ)፣ በአንዳንድ የአካባቢው አገራት ላይ ደሞ የሥርዓት ለውጥ (አስመራ) ለማምጣት እያሴሩ እንደሆነ ክስና መረጃዎች ይሰማሉ።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ወታደራዊ ውጥረት፣ የሰው ልጅ እርግማኖች ሁሉ በዐቢይ አሕመድ ላይ ይሁንና፣ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ ባለበት በዚህ ወቅት ዐቢይ፣ ከናታንያሁ ጋር በስልክ ተወያይቷል።
ዐቢይ ውይይቱን “ፍሬያማ እና ገንቢ” ሲል የገለጸው ሲሆን፣ ሁለቱ መሪዎች በጋራ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር መስማማታቸውን ተናግሯል።
ምንም እንኳን ይፋዊ መግለጫዎቹ የኢትዮጵያና ኤርትራን ግጭት ቀጥታ ማለታቸውን ባይጠቅሱም፣ ይህ እንቅስቃሴ ከአስመራ ቅድመ-ተስፋዎችና ማስጠንቀቂያዎች ጋር የሚገጥም ነው።
ይህ የስልክ ውይይት ከመደረጉ ቀደም ብሎ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ከእስራኤሉ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዴኦን ሳዕር ጋር ተመሳሳይ ውይይት አድርጎ ነበር።
እስራኤል ለዐቢይ ቀጠናዊ ጉዳዮች የምታሳየው ድጋፍና የአምባሳደሯ ንግግሮች፣ ከሶማሌላንድ እስከ ሱዳን፣ እንዲሁም በቀይ ባህር ሁኔታዎች ላይ እሱና አገዛዙ የውጭ ኃይሎች መጠቀሚያ መሆናቸውን ይበልጥ ያስረግጣሉ።
ዐቢይ ኤርትራን ‹‹ወደ ትግራይ ጦር አስገብታለች›› በማለት የሚያቀርበው የጥቃት ውንጀላ፣ ራሱ ለወረራና ለጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት ለመሸፈን ስለመሆኑ ብዙም የሚያከራክር አይመስልም።
የአዲስ አበባ እና የአስመራ ገዥዎች ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ያደረሱት ቢሆንም፣ የዐቢይና የኔታንያሁ ውይይት ግን ሁኔታው የውጭ ኃይሎች መጫወቻ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
በርግጥም ደጋግመን እንዳልነው፣ ዐቢይ የራሱ የሆነ ነፃ የፖለቲካ አጀንዳ የሌለው የውጭ ኃይሎች ተላላኪ ርባና ቢስ ኦሕዴድ ነው።
የ3ኛ ወገን ፍላጎቶች በኢትዮጵያ እና በቀጠናው ላይ የሚያስፈጽም፣ ከእነዚህ ፍላጎቶች የተረፈውን ደግሞ ለኦሕዴድ የፖለቲካ ኢምፓየር ግንባታ አልሞ የሚሰራ መሆኑን በግልጽ እየታየ ነው፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የአረብ ኤምሬትሱ መሐመድ ቢን ዛይድ የዐቢይን አገዛዝ በቀጥታ የሚመሩት ሲሆን፣ ከጀርባው ደግሞ የእስራኤሉ ሞሳድ ሰፊውን ቀጣናዊ ስትራቴጂያዊ ሴራ ይዞታል።
የዐቢይ ቀጠናዊ እንቅስቃሴዎች፣ የእስራኤልና የኤምሬትስ የረጅም ጊዜ አጀንዳዎች አካል እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎቶችን የሚያንጸባርቁ አይደሉም። ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ በጎረቤት አገራት ጊዜ ላይ ወረራ ፈጽማ አታውቅም፡፡
ጣልቃ ገብታ አሸማግላ እንጂ ለአንድ ወገን አድልታ ጦር አሰልፋ፣ መረጃና ሎጀስቲክ እያቀበለት የተዋጋችበት ጊዜ አልታየም፡፡ ከደርግ ጊዜ ወዲህ የመጡ ቀጠናዊ ቀውሶች፣ በዐቢይ አሕመድ የአገዛዝ ዘመን እጅግ ወደከፋው ምዕራፍ ተሻግሯል፡፡
የአስመራው መንግሥት ባለሥልጣናት ከወራት በፊት በሰጡት ማብራሪያ፣ በእስራኤልና በኤምሬትስ የሚመራው ቀጠናዊ ሴራ የተጠነሰሰው ዐቢይን መጠቀሚያ በማድረግ እንደሆነ በግልጽ ማጋለጣቸው ይታወሳል።
እስራኤል በሰባት ግንባሮች እና በውስጥ ችግሮቿ ተወጥራለች ቢባልም፣ የአምባሳደሯ ግልጽ ድጋፍና ከጀርባ የሚደረጉት ምስጢራዊ ውይይቶች ግን የዚሁ ሴራ አካል ናቸው።
ይፋዊ መግለጫዎች ወታደራዊ ስምምነቶችን አለመጥቀሳቸው ምንም ዓይነት የደህንነት ትብብር የለም ለማለት ማረጋገጫ አይሆንም።
ለአስመራና አጠቃላይ ለቀጣናው ሕዝቦች፣ አሜሪካን የተካችው እስራኤል በዐቢይና በሶማሊላንድ በኩል የኤርትራን ሉዓላዊነት እና የቀጠናውን ሰላም ለማወክ የተነሳች አዲስ ስጋት ሆናለች።
ይህ በውስጥ ጦርነቶች እየተናጠ ለሚገኘው የአፍሪካ ቀንድ መልካም ዜና አይደለም፡፡
ሁኔታዎችን በገለልተኛ ቀጠናዊ ትንታኔ ካየናቸው፣ ኤርትራ ከዐቢይ ጋር የሚኖራትን ማንኛውንም ግጭት የምትመለከተው፣ ከውጭ ወራሪዎችና የሴራ ኃይሎች ጋር እንደሚደረግ የሉዓላዊነትና የነጽነት ተጋድሎ አድርጋ መሆኑ የአደባባይ እውነት ነው።
እዚህ ላይ አንድ ወሳኝ የቅርብ ጊዜ መረጃ ማንሳት ይኖርብናል፡፡ በእስራኤል፣ የጸረ-ኤርትራ መንግሥት እንቅስቃሴ እናደርጋለን ያሉ ኃይሎች ስብሰባ እንዲያደርጉ ሁኔታዎች የተመቻቹትም በዚሁ ቀጠናዊ የሴራ ስሌት ነው፡፡
ጉዳዩ ከኢትዮጵያ እስከ አውሮፓ እና አሜሪካ ድረስ ያሉ የኤርትራ ተቃዋሚዎችን ያጣመረ መሆኑ መረጃው ትኩረት ይስባል፡፡
በጉዳዩ ላይ የእስራኤሉ ሃሬትዝ የተሰኘ ዜና መጽሔት የምርመራ ዘገባ አውጥቷል፡፡
እንደመረጃው ከሆነ የጸረ-ኤርትራ መንግሥት እንቅስቃሴ እናደርጋለን ያሉ ተቃወሚ ኃይሎች ወታደራዊ የጋራ ጥምረት ለመመስረት እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡
ከአሜሪካ እስከ ስዊድን፣ ከጀርመን እስከ ኢትዮጵያ እና በእስራኤል ቴል አቪቭ የሚኖሩ ኤርትራዊያን አሉበት የተባለው ይህ ስብስብ በዐቢይ አሕመድ፣ በጦር አጋሩ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና በእስራኤል ድጋፍ የሚደረግለት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
እስራኤል በዚህ የኢትዮጵያና ኤርትራ ውጥረት ውስጥ እጇ እንደሌለበት በይፋ ብታስታውቅ እንኳ፣ ዐቢይ የውጭ ኃይሎች መጠቀሚያ ሆኖ የቀጠናውን ሰላም ለማደፍረስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እና የእስራኤልን ድብቅ ፍላጎት የሚሸፍነው አይሆንም። ስለምን ቢሉ? ዛሬ እንኳን የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የእስራኤሉ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ሞሳድ ወኪሎች ከቀይ ባሕር አካባቢ እንቅስቃሴዎች እና ሁኔታዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለመሰለል እና ለመከታተል በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ የሚጠቁሙ ዘገባዎች እየወጡ ነውና።
በሌላ በኩልም፣ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አንድ የጋራ አቋም ላይ መድረስ ያልተቻለው የብልጽግና አገዛዝ ባቀረበው ክስ ምክንያት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ቻይና እና ሩሲያ ያሉ የ ‹ቪቶ ፓወር› ባለቤት አገራት፣ “በአገራት የውስጥ ጉዳይ አለመግባት” የሚለውን መርህ በመከተል፤ በቀጠናው ባላቸው የየራሳቸው የጂኦፖለቲካ ፍላጎት ምክንያት በምክር ቤቱ የኃይል ሚዛን በመፈጠሩ መሆኑን የብልጽግና ወንጌል አማኝ ካድሬዎች የሰሙ አይመስልም።
የሆነው ሆኖ፣ ራሱ ዐቢይ አሕመድ በዚህ ቀጠና የሚካሄድ ጦርነት ሦሥተኛው የዓለም ጦርነትን ሊያስነሳ እንደሚችል የዛሬ 8 ዓመት ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ላይ በተጋባዥነት ጽፎ ነበር።
ያኔ አረቦቹ ሊያጫርሱን ነው ያለው ሰውየ፣ ዛሬ ሌላ መልክ ይዟል፡፡ ከእምነትም፣ ከእውቀትም፣ ከእንጥፍጣፊ ሕሊናዊ ሰውነት ጋር የተጣላው የ50 ዓመቱ ጎልማሳ፣ ዛሬ በአረብ ስፓርታዋ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እየተመራ በአፍሪካ ቀንድ አስከፊውን አርማጌዲዮን እየጠራ ይገኛል፡፡
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






ውድ ወንድሜ አቶ ሙሉ ዓለም ገብረ-መድህን ለበጣም ጥሩ ትንተናህ በጣም አመሰግንሃለሁ። እንዳልከው አቢይ አህመድ የተባበሩት የአረብ ኢሚራት ቅምጥ መንግስት ነው። ከባበሩት የአረብ ኢሚራት በስቸጀርባ እስራኤልና እንግሊዝ አሉበት። የእነሱም ፍላጎት እንደ አቢይ አህመድ የመሳሰሉትን ሰይጣናዊ ኃይሎች ወደ ውስጥ ጦርነት እንዲያካሂድ በመገፋፋት ወደ ውስጥ ያተኮረ የአገር ግንባታ ስራ እንዳይሰራ በማድረግ አካባቢውን መቆጣጠር ነው። ችግሩ አብዛኛው ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ኢትዮጵያዊ አቢይ አህመድ የውጭ ኃይሎች አሻንጉሊት አገዛዝ መሆኑ በፍጹም አልገባውም። በተረፈ በርታ እልሃለሁ!
That is exactly right!!!
አብይና የብልጽግናን መንግስት ተግባር መጥላት በመሬት ላይ ያለውን እውነታ እየካድ መሆን የለበትም። የኤርትራ ሰራዊት ትግራይ ክልል እንደገባ በመረጃ የቀረበን ነገር የፈጠራ ወሬ አድርጎ ማቅረብ ለሃገርና ለህዝብ ማሰብ አይደለም። ጥላቻችን በአንድ ሰው ላይ ብቻ እየሆነ ዛሬም በፊትም እንሆ ሚዛናዊ እይታ እንዳይኖረን አድርጓል። በአንጻሩ አብይ ምጡቅ ነው ከሰማይ የወረደ ነው ሃገር አሻጋሪ ነው የሚሉን ሁሉ ረጋ ብለው በየስርቻው እነማን ታግተው እንዳሉ ቢያዪ መልካም ነው። ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የብልጽግናን መንግስት ስንመለከት 27 ዓመት ሙሉ ወያኔ ባርነት ትግራይ ያላሳካውን በጎ ተግባራት ብልጽግና ፈጽሟል። ስለሆነም አንድ መንግስት ሊመሰገን ሊደገፍ የሚገባው ተግባር ላይ አበጀህ ማለትና ከመንገድ ሲወጣ ደግሞ ለምን ማለቱ የአንድን ሰው እይታ ሚዛን ያስጠብቀዋል ባይ ነኝ። ግራም ነፈሰ ቀኝ የምድሪቱን ችግር መንግስት ላይ (ብልጽግና) ላይ ብቻ መቆለሉ የፓለቲካ አሻሮ መሆን ነው። የኢትዪጵያ ህዝብ ራሱ ለማስተዳደር አስቸጋሪ ነው። በህግ የተፈረደለት የፈረደውን ዳኛ አድኖ በሚገልበት ምድር ላይ መንግስት መንግስት ቢባል መንግስት ብቻውን ህግና ደንብን ማስከበር አይችልም። የአንድ መንግስት ከለላው ህዝብ ነው። ህዝብ ከመንግስት ጎን ካልቆመ ሁሌም ዘረፋና ግድያ የቀን ተቀን ተግባር ነው። ይህ ሲባል የመንግስት አካላት ችግር ፈጣሪ አይደሉም ለማለት አይደለም። ሃገሪቱን የምናምሰው በጋራ ሆነን ነውና!
የዛሬ 80 ዓመት ገደማ ዴቪድ ቤንጉሪያን የተናገረው ለዛሬው የድሮንና የኤ አይ አለም እምብዛም አይመጥንም። ግን እንበል እስራኤል ወደ አፍሪቃ ቀንድ ተጠጋች ቢባል ጭንቀቱ የቱ ላይ ነው? ወስይ አንተ የግብጽ ጦር ይሻላል እያልከን ነው? ጅቡቲን እንደ ጉንዳን የወረሯት ሃያላን መንግስታት ምን ሊያተርፉ ነው በዚያ በረሃ ውስጥ ተስጠው የሚገኙት? መገኘታቸውስ ከሁቲና ከኢራን የገጠመውን የባህር ላይ የነጻነት እንቅስቃሴ መግታት የት አለ መፍትሄ ያስገኙት? ጊዜው እንደ በፊቱ ሃያላን መንግስታት በጦር ሃይል አንድ ሃገርን ወረው እኔን እወቁኝ የሚሉበት ጊዜ ያከተመበት ይመስላል። የፈሪ ድላ ረጅም ነው እንዲሉ ከሩቅ ሆኖ መወራወሩም ይኸው እንሆ ምን ያህል ጥፋት በዪክሬን በራሽያ በኢራኑ ግጭት በአሜሪካ የጦር ሰፈሮችና በእስራኤል ላይ የደረሰው ዜናው ከዘገበው በላይ ነው። አያሌ ጥፋቶች ደርሰዋል። እዚህም እዚያም እሳት የሚነድባት ይህች የዛሬዋ አለማችን ሁሉ የጦር መሳሪያ አምራችና አከፋፋይ የሆነባት ናት። እንግዲህ ዝንተ ዓለም የመከራ በረዶ የሚወርድባት የሃበሻ ምድር ደግሞ አብዛኛው ችግሯ ከራሷ ልጆች የሚመነጭ ነው። ቀሪው ግብጽ/ሱዳን/ኤርትራና የዓረቡ ዓለም በስውርና በይፋ የሚያነድት እሳት ነው። ኢትዮጵያ ሰላም አግኝታ፤ እድገቷ ተፋጥኖ ከሃገሮች እኩል ወይም ቀድማ ተሰላፊ እንድትሆን ነጩም አረቡም ሌላውም አይፈልግም። ለዚህ ነው እርስ በእርስ እንድንጫረስ እሳት እያቀበሉን ያሉት። የብሄር ፓለቲካ ሸረኛ ነው። በዚህም ምክንያት የዛሬዋ ኢትዮጵያ በአፓርታይድ ክልል እንድትከፋፈል ወያኔ ያደረገው ራሱን በስልጣን ለማቆየት ከጎነጎነው አንድ የፓለቲካ ሴራው ነው። ይህኑ የብሄር ፓለቲካ ተከትለው ፋኖ/ኦላና ሌሎችም ህዝባቸውን ማሸበራቸው ያው ከወያኔና ከሻቢያ የተማሩት ነው። የትጥቅ ትግል ቀኑ የመሸበት፤ መደበቂያ ጫካና ዋሻ የሌለበት ለመሆኑ ዘመናዊ የውጊያ ዘዴዎችን አይቶ መፍረድ ይቻላል። ስለሆነም በሩቅም በቅርብም በዘርና በጎሳ ተሰልፎ ነገርን እያካረሩ ህዝባችን ከማያባራ ጦርነት ውስጥ ከመማገድ ይልቅ ለሰላም እድል ሰጥቶ ሁሉ በትግስትና በማስተዋል ማየት አስፈላጊ ይመስለኛል። ለገባውና የጊዜውን የፓለቲካ አሰላለፍ ለተረዳ እስራኤሎች በቀይ ባህር ዳርቻ ላይ በሱማሊላንድ እንዳሉ ሊገነዘብ ይገባል። በቀይ ባህር ዙሪያ ግብጾች፤ ቱርኮች፤ እንግሊዞች፤ አሜሪካኖች ሌሎችም ከዘመናት በፊት ብቅ ጥልቅ ብለዋል። ዛሬም ቢሆን በዚያው ዙሪያ በመርመስመስ ላይ ይገኛሉ። ግን ይህ ሁሉ ጥረት ለራሳቸው ጥቅም እንጂ ለጥቁር ህዝቦችን አንድነትና እድገት አስበው አይደለም። የእስራኤልም በአፍሪቃ ቀንድ ላይ ማተኮር በራሷ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው። ግን መቼ ነው እኛ የምንነቃውና ከእርስ በእርስ ጦርነት ጋር የምንፋታው? ያ ጊዜ ይመጣ ይሆን? ሰንብተን እንይ!
You can’t deny Abiye is being used by left and right because he is incompetent power monger.